[the_ad_group id=”107″]

ትርጕሙን የምንስተው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል

ኤን.. ራይት

እምነተአብ አየለ እንደተረጐመው

በጵጵስና ኀላፊነት እያለኹና ካህናትን ለደብራት አገልግሎት ቃለ መጠይቅ አደርግ በነበረበት ወቅት፣ ዐልፎ ዐልፎ ከማቀርባቸው ጥያቄዎች መካከል፣ “ማንም ወደሌለበት በረሓ ብትኼድና ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ምዕራፍ ይዘህ መኼድ ትችላለኽ ብትባል፣ የትኛውን ክፍል ትወስዳለህ?” የሚል ነበረ። ጥያቄው የበለጠ አጓጊ እንዲኾን፣ “በእጅህ ያለው ሮሜ ምዕራፍ 8 ነው እንበል” የሚል እጨምርበታለሁ (ወይም አብዛኛዎቹ ተጠያቂዎች ራሳቸው ይህንኑ ክፍል ሊመርጡ ይችላሉ)። ይህ ክፍል አጠቃላዩን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በዐጭሩ ከሚያቀርቡ ምንባባት መካከል አንዱ የሆነ፣ በሚፈትኑ ነገሮች የተሞላ፣ እጅግም ደግሞ የሚያጽናና ምንባብ ነው።

በሮሜ ምዕራፍ 8 ካሉ ቍጥሮች መካከል አንደኛው በተለይ እጅግ በጣም ታዋቂ ነው፤ ብዙ ጊዜ ግን በተሳሳተ አተረጓጐም ይቀርባል። ብዙ ክርስቲያኖች በልጅነታቸው ከሚያጠኗቸው ዐይነተኛ ከኾኑ ጥቅሶች መካከል የኾነ፣ “እግዚአብሔር ዓለሙን እንዲሁ ወድዶአልና…” ከሚለው የዮሐንስ ወንጌል 3፥16 ጥቅስ ባልተናነሰ የሚቀርብ ነው፤ ይኽም ጥቅስ፣ “እግዚአብሔርን ለሚወድዱና እንደ ሐሳቡ ለተጠሩ ነገር ኹሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን።” (ሮሜ 8፥28) የተሰኘው ነው።

ብዙ ሰዎች አስቸጋሪ ነገሮች በሚከሰቱበት ወቅት ይህን ክፍል ያስቡታል። [ይኼ ክፍል] “እያንዳንዱ ጭጋግ የራሱ ወገግታ አለው” ወይም “ከባድና አስቸጋሪ ጊዜአት ባሕርያችንን ይሠሩታል” ለሚሉ ዐይነት ብኂሎች መንፈሳዊ አቻ ጥቅስ ተደርጎ ይታሰባል። በዚህ ዘመን ብዙ ክርስቲያኖች ይህን ክፍል፣ ነገሮች ኹሉ ለበጎ ተደርገው እንደሚሠሩ ተስፋ በመስጠት የሚያጽናና፣ የሚደግፍ እና ርግጠኝነትን የሚሰጥ አድርገው በመውሰድ ርስ በርስ ይለዋወጡታል (ምንም እንኳን ጳውሎስ የጻፈው በዚህ መልኩ ባይኾንም)።

ኹላችንም እንደምናውቀው፣ ቀደም ብዬ በጠቀስኹት የ“ኪንግ ጄምስ” ዕትም በኾነው መጽሐፍ ቅዱስ መሠረት፣ “ነገር ኹሉ” (በዓለማችን ላይ ያለፉ ክስተቶች በአጠቃላይ) በበጎ እንደሚጠናቀቁ ዋስትና የሚሰጥ ድምፀት አለው። ነገር ግን፣ ጳውሎስ ምን እያለ እንደ ኾነ ላስተዋለ ሰው፣ “ነገር ኹሉ” እንዲህ ባለ መልኩ ወደ በጎ ይለወጣል ብሎ መናገር አንዳች የሚጎረብጥ ነገር አለው። ይህኛው ዐይነት ዕሳቤ የጥንት እስጦይኮችን ፍልስፍና እንጂ የጳውሎስን አይሁዳዊ የአስተሳሰብ መንገድ አይወክልም።

ጳውሎስ የተጠቀመው ግሥ፣ የኪንግ ጄምስ ዕትም “ይደረግላቸዋል!”ብሎ እንደሚተረጕመው አይደለም፤ ይልቁን “በአንድነት ይሠራሉ” የሚልን ትርጕም ይይዛል (በ1952 ዓ.ም. የተከለሰው መደበኛ ዕትም ይህን ትርጕም አግኝቶት ነበረ፤ ነገር ግን ሌሎች የክፍሉ አያያዥ መሥመሮች ስለተለወጡ፣ የክፍሉ ልከኛ ትርጓሜ ተሟልቶ አልቀረበም።) ጳውሎስ የኪንግ ጄምስ ዕትም በስሕተት ያቀረባቸውን ኹለት ነገሮች እየተናገረ ነበረ።

አንደኛው፤ ጳውሎስ የሚናገረው “ነገሮች በራሳቸው ኀይል” ሳይኾን እግዚአብሔር ራሱ ኹሉን ለበጎ እንደሚያከናውን ነው። በኹለተኛው ደረጃ ጳውሎስ የሚያብራራው፣ እግዚአብሔር ይህን ሥራ እንዴት እያከናወነ እንዳለ ነው። በተለየ መልኩ፣ እግዚአብሔር ይህን የሚሠራው “ከኾኑ ሰዎች ጋራ” በአንድነት በመኾን ነው። ርሱ (እግዚአብሔር) የዐላማው ተካፋዮች እንዲኾኑ የሰው ልጆችን መርጧል።

ይህ ሐሳብ የአንዳንድ ነገረ መለኮታዊ አተያይን አከርካሪ የሚሰነጥቅ ነው። ኹልጊዜ፣ በእግዚአብሔር የማዳን ሥራ ውስጥ ሰዎች ዐብሮ ሠራተኞች እንደ ኾኑ ከሚያቀነቅን የትኛውም ዐይነት አመለካከት ራሳችንን መጠበቅ እንዳለብን ስንጠነቀቅ ኖረናል። ነገር ግን፣ የመዳን ጒዳይ የዚህኛው ክፍል ትኵረት አይደለም። በርግጥ መዳን የምዕራፉ ሰፊው አድማስ ቢኾንም፣ ይህ ምንባብ (ቍ. 28) የሚናገረው ግን ስለ ግብር ነው፤ እግዚአብሔር ላደረገልን ነገር መልሰን ስለምንሰጠው የምስጋና ክፍያ (ቍ. 12)። በኢየሱስ ወንጌል የተያዙ እና መንፈስ ቅዱስ በልባቸው ውስጥ የሚሠራባቸው፣ አሁን ቀጣይነት ባለው በእግዚአብሔር ዐላማ ውስጥ የተለየ ሚና አላቸው።

ይህ ከትልቁ የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት አንጻር እጅግ የላቀ ስሜት የሚሰጥ ነው። ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ ውስጥ በተደጋጋሚ ወደ ኋላ እየዞረ በሚጠቁመው የዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ እንደምናየው፣ እግዚአብሔር ሰዎችን የሠራው በፍጥረት ሥራው ውስጥ አጋሩ እንዲኾኑ አድርጎ ነው። እነርሱ በዋናነት የእግዚአብሔርን ምስል ገላጮች ናቸው፤ የተወደደውን ዐላማውን ለተቀረው ዓለም የሚያንፀባርቁና የፍጥረትን ምስጋናና ጸሎት ለእግዚአብሔር መልሶ የሚያቀርቡ የእግዚአብሔር ወኪሎች ናቸው።

በሮሜ ምዕራፍ 8 ጳውሎስ የሚያብራራው፣ ይኸው እውነት እንዴት ተግባራዊ እንደሚኾን ነው። በምጥ እንዳለች ሴት፣ ፍጥረት በአንድነት በመቃተት እንዳለ እግዚአብሔር ያውቃል። እነዚህ የምጥ ሕመሞች፣ የእግዚአብሔር አዲስ ፍጥረት ውልደት ማሳያ ናቸው። በወንጌሉ የተያዙና በመንፈስ የሚመሩቱ ሰዎችም፣ በሙሾ ጸሎታቸው በኩል ዐብረው የሚቃትቱ ናቸው። (ጳውሎስ ጠንቅቆ እንደሚያውቀው፣ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እንዲህ ዐይነቱ ጸሎት እንዴት እንደሚጸለይ በርካታ መመሪያዎችን ይሰጡናል።)

ጳውሎስ በቍ. 26 እና 27 እንደሚገልጠው፣ ያ በመንፈስ የሚመራው ሙሾ ሲካኼድ፣ የሰውን ልብ የሚመረምረው አምላክ ራሱ፣ በጣም አስጨናቂ ከኾነው የፍጥረት ሕመም ውስጥ የሚወጣውን መቃተት ያደምጣል። በዚያ መንገድ የሚጸልዩም፣ ስለ ምን እንደሚጸልዩና መቼ እንደሚኾን ሳያውቁ እንኳን፣ የኢየሱስ ምሳሌና የመስቀሉ አርኣያነት ወደተገለጠበት እና የመላ ዓለሙ ቤዝዎት ወደሚመጣበት የፍጥረትን ሕመም የመካፈል የሕይወት መሥመር ውስጥ ይገባሉ፤ ጳውሎስ ይህንኑ እውነት በቍ. 29 ላይ አስረግጦ ያስቀምጣል። በዚህም፣ እነርሱ የራሳቸውን መዳን ለመፈጸም ሳይኾን፣ እግዚአብሔር ስለተሰበረውና እየደማ ስላለው ዓለሙ ላለው ዐላማ ዐብሮ ሠራተኞች ይኾናሉ።

ምንም እንኳን እውነታው ስለ ክርስቲያኖች ግብር የሚናገር ተገዳዳሪ ክፍል ቢኾንም፣ በሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ እንዴት ኹሉ ነገር ለበጎ ኾኖ እንደሚቀየር የተማርንበት መንገድ እጅግ የሚያጽናና ነበረ። ነገር ግን፣ ማንም ሊናገር በማይችል መቃተት ውስጥ በተያዝን ቅጽበት፣ ከእግዚአብሔር የፍቅርና የፈውስ ዐላማ ጋር እንድንያያዝ መንፈስ ቅዱስ በልባችን ውስጥ ኾኖ ይሠራል።

እግዚአብሔር ሰዎችን የሥራው ተካፋዮች እንዲኾኑ ፈጥሯቸዋል። በሚታመም ዓለም ውስጥ የሚጸልዩ ሰዎች እንድንኾን ተደርገናል። በአኹን ወቅት፣ ጸሎት ይህን ዐይነት ሙሾ ይመስላል። ይህን ጥሪያችንን ስናነሣ፣ በእግዚአብሔር ፍቅር የተያዝን እንኾናለን፤ እግዚአብሔርም ርሱን ከሚወድዱ ጋራ ኹሉን ለበጎ አድርጎ ይሠራዋል። “አዲስ ኪዳን ለኹሉ” በሚለው አዲሱ መጽሐፌ፣ ሮሜ 8፥28 ን “ እግዚአብሔር ርሱን ከሚወድዱና፣ እንደ ሐሳቡ ከተጠሩ ጋ ነገርን ኹሉ ለበጎ እንደሚያደርግ እናውቃለን።” ብዬ የተረጐምኹት በዚሁ ምክንያት ነው።  “Into The Heart of Romans” የሚል ሙሉ መጽሐፍ የመጻፌ ከፊል ምክንያት ይኸው የዚህ ክፍል ንባቤ ነው።

ስለዚህ እናንተ መምህራን፣ ሰባኪዎችና የሰንበት ትምህርት መሪዎች፣ ወጣቶች ሮሜ 8፥28ን የበለጠ እንዲያውቁ መርዳታችሁን ቀጥሉ። ነገር ግን፣ ልከኛ በኾነ መንገድ እንዲያውቁ ርዷቸው። በእግዚአብሔር ፍጥረት ውስጥ ዐብሮ ሠራተኛ ለመኾን የተዘጋጀ አዲስ ትውልድ ያስፈልገናል። እንዴት እንዲጸልዩና እንደሚጋደሉ የሚያውቁ፣ በተለይም ደግሞ እንቆቅልሻዊ የኾነውን የሙሾን ጸሎት እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው የሚያውቁ ያስፈልጉናል፤ በተለይም እንዲህ ባለው ዘመን።

Ementeab Ayele

እምነተአብ አየለ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአዳማ ዩኒቨርሲቲ በመካኒካል ምህንድስና ያጠናቀቀ ሲሆን፣ በዚሁ ሙያ “አስኩ ፒ ኤል ሲ” በሚባል ድርጅት ውስጥ ይሠራል። እምነተአብ የመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አባል ሲሆን፣ የሁለተኛ ዲግሪውን በኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት፣ በአዲስ ኪዳን የጥናት ዘርፍ በመከታተል ላይ ይገኛል።

Share this article:

ለሚድን በሽታ የሚገድል መድኃኒት መውሰድ ይብቃ! (ደወል 3 ዘ ኢትዮጵያ)

“አንዱ በብሔሩ ዘረኛ ሲሆን፣ ሌላኛው በዜግነቱ ዘረኛ ይሆናል። አንዱ ብሔሩን ሲያስቀድም፣ ሌላኛው ዜግነቱን ያስቀድማል። አንዱ የብሔር ዘረኛ የራሱን ብሔር ለብቻው ሊያገንን ሲፈልግ፣ ለኢትዮጵያ ዐብሮነት መሠረት ውጋት ይሆናል። እንደዚሁም የዜግነት ዘረኛ ኢትዮጵያን ለብቻዋ እንድትገን ሲፈልግ፣ በጨለማ ላለ ጥቁር አፍሪካ ሕዝብ አንድነት ውጋት ይሆናል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ድምፃዊ ተፈራ ነጋሽ:- “ታንክ ቢመጣ ወደኋላ አልመለስም”

5 አልበሞች ለአድማጭ አድርሷል፤ ከእነ አረጋኸኝ ወራሽና ሌሎች ድምፃውያን ጋር የሠራቸው ስብስብ ሥራዎችም አሉት። “ደህና ሁኝ ልበልሽ በእንባ እየታጠብኩኝ”፣ “ምነው ቀዘቀዘ ፍቅራችን”፣ ከሥራዎቹ መካከል ጎልተው የሚጠቀሱት ናቸው። ሰሞኑን በታክሲ ሾፌርነት መታየቱ ተሰምቶ አነጋግረነዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.