[the_ad_group id=”107″]

“ቤቴ” ወይስ “ቤታችሁ”?

የጌታ ኢየሱስን ምድራዊ ሕይወት ለማሳየት የተሠሩ በርካታ ፊልሞች እና የተለያዩ ምስሎች አሉ። ከሞላ ጎደል በሁሉም ውስጥ ተሥሎ የሚቀርብልን ገጽታው ግን በሆነ መልኩ ተመሳሳይ ነው፤ ርጋታ እና ልስላሴ ጎልቶ የሚነበብበት ገጽታ። በርግጥም ይህ በአብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባቦች በቀረቡ ታሪኮች ላይ ሳይመሠረት አልቀረም። ሆኖም አንድ ቦታ ላይ ይህ ይቀየራል፤ ጌታ ኢየሱስ የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛ እየገለባበጠ እና ለሽያጭ የቀረቡ እርግቦችን እያባረረበ በቤተ መቅደሱ ግቢ ሲዘዋወር።ሆኖም በዚያ ቦታ መቅደሱን ለማጥራት ጌታ የወሰደው ቊጣን እና ሐዘንን ያዘለ ርምጃ መነሻው ለቤቱ ያለው ፍቅር ነው። “ʻቤቴ የጸሎት ቤት ይባላልʼ ተብሎ ተጽፏል፤ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት” በማለት መቅደሱን ሊያጠራ መጣሩ ለዚህ ነው (ማቴ. 21፥12-13)። ይህም በሌሎች ምንባቦች ውስጥ የማናየውን የተቈጣ ኢየሱስ እዚህ እንድናገኘው ምክንያት ሆኗል። ያ ቤተ መቅደስ የእግዚአብሔር ቤት ነበርና “ቤቴ” ቢለው ተገቢ ነው። ጌታችን የዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ሳለም ያንን ቤት “የአባቴ ቤት” ሲል ገልጾት ነበር (ሉቃ. 2፥49)።

ይህ ግን ለሁልጊዜም አልቀጠለም። ስፍራው ንግድ የሚጧጧፍበት፣ የትንሣኤ ሙታንን እና የመላእክትን ሕልውና የማይቀበሉ ካህናት የሚያገለግሉበት፣ ራሳቸውን በንጹሕ ልቡና ማቅረብ ሳያስፈልጋቸው እንስሳትን እየጎተቱ በዚያ ቦታ በማረዳቸው ብቻ እግዚአብሔርን የተሻረኩ የሚመስላቸው ምዕመናን መሰባሰቢያ ሆነ። ከዚህ ዐይነቱ የተንሻፈፈ ምልከታ ይቃኑ ዘንድ ጌታ አብዝቶ ሊገሥጻቸው እና ሊያስተምራቸው ቢበረታም፣ ሰዎቹ ቢነግሯቸው የማይሰሙ፣ ቢመክሯቸው የማይለሙ ሆኑ። ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ እንደምትሰበስብ ሊሰበስባቸው ቢሻም አልፈቀዱለትም። ስለዚህም “ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል” ሲል በሐዘን ተናገረ (ማቴ. 23፥38)። ይህ ንግግሩ መቅደሱን ለማጥራት የነጋዴዎችን የሽያጭ መደብ ሲገለባብጥ ከተናገረው ቃል ጋር አይመሳሰልም። ያኔ የእግዚአብሔር ቤት ቅጥ ማጣት ያስቈጣው ጌታ “ቤቴ …” የሚል ቃል ተናግሮ ነበር። አሁን ደግሞ “ቤታችሁ …” ሲል ነው የተናገረው። “የእኔ” ማለቱን ትቶ “የእናንተ” አለ፤ የባለቤትነት ለውጥ እንደ ተካሄደ ሁሉ፣ “ቤቴ” ወደ “ቤታችሁ” ተቀየረ።

በአውሮጳ ውስጥ ትናንት የእግዚአብሔር ቤትነታቸው የተመሰከረላቸው ተቋማት (የሰዎች ስብስብ)፣ ዛሬ የሰዎች ንብረት ብቻ ሆነው ቀርተዋል። ይህ ግን የሆነው በአንድ ጊዜ አይደለም፤ ቀስ በቀስ እንጂ። ዛሬም ደግሞ በእኛው መካከል ይህ ላለመሆኑ ዋስትና የለንም። እንዲያውም ቤቱን የራስ ለማድረግ የሚካሄደውን ጥረት እና ትግል በየአጋጣሚው እያየን ነው። ስለዚህም የቤቱ ባለቤት፣ “ቤቴ” ማለቱን ትቶ “ቤታችሁ” እንዳይለን ሥጋት አለን።

በሰሜን አሜሪካም ክርስትና “በመሠረቱ የሸማቾች ፍላጎት ማስጠበቂያ ሆኗል። አሜሪካውያኑ፣ እግዚአብሔርን ጥሩ ወይም የተሻለ ኑሮ እንዲኖራቸው የሚያበቃ ምርት አድርገው ነው የሚያዩት። ክርስትና እንደ አሁኑ የሕዝብ ግንኙነት፣ የገጽታ ግንባታ፣ የገበያ መር ዘዴዎች እና የውድድር መንፈስ ሰለባ የሆነበት ጊዜ አልነበረም።”1 አማኞቹ የትኞቹም ሸማቾች የሚያደርጉትን ያደርጋሉ። የተሻለ ምቾት የሚሰጣቸውን ቦታ ይመርጣሉ፤ ዘላቂ መሰጠት አይታይባቸውም። ሕንጻው ያማረበት ይነጉዳሉ፤ የጎላ ሙዚቃ ወዳለበት ይተምማሉ፤ ግርግሩን ተከትለው ይተራመሳሉ፤ በነፈሰበት ይነፍሳሉ። እኛም ጋ ከዚህ የተለየ ነገር እየተለመደ አይመስልም። አሁን ነገሩ ሁሉ ገበያ መር ሆኗል፤ ማስታወቂያውም ወደዚያው ነው። “እኛ ወዳዘጋጀነው ኮንፈረንስ ቢመጡ ለበሽተኞች ይጸለያል (ሕሙማን የሚለውን ቃል መቼ ይሆን የሚያውቁት?)፤ በብልጽግናዊ የጥርመሳ ቅባት ይለወሳሉ፤ ትንቢታዊ መልእክት ይለቀቃል፤ ነቢይ እገሌ በእጁ ይነካዎታል፤ እንትና በተባለው ዝነኛ ዘማሪ ዝማሬዎች ሰማይ ደርሰው ምርኮ ይበዘብዛሉ”። የሌላውም ማስታወቂያ ያው ነው፤ ሰዎች ገበያ ሄደው ለዐይናቸው ደስ ያላቸውን ዕቃ መርጠው እንደሚሸምቱት ምዕመናንም ያንኑ ፈለግ እንዲከተሉ ያበረታታል። የፈለጉትን እንጂ የሚያስፈልጋቸውን የሚሰጣቸው የለም፤ ለነገሩስ፣ የሚያስፈልጋቸውን የሚያውቅ ይኖራልን? አሊያ ሰው እግዚአብሔርን ፈልጎ አይመጣም። ለመማር እና ደቀ መዝሙር ለመሆን የመቀመጥ ትዕግሥት ያለው ምዕመን መኖሩንም እንጃ! ሸማችነት በተጠናወተው ዓለም እግዚአብሔር እንደ ፋብሪካ ምርት በመጠቀሚያነት ከቀረበ እና የምቾት ቁስ ከሆነ ያለንበት ስፍራ “ቤቴ” መሆኑ ቀርቶ “ቤታችሁ” ሆኗል ማለት ነው።

ዛሬ ዛሬ ከፍተኛ ተከታይ ያላቸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የጠላት ተባባሪዎች እየሆኑ ነው። ዓለም የምትፈልገው ሃይማኖት መዝናኛ ብቻ የሆነውን እንደ ሆነ በማወቃቸው ነው መሰል፣ እነርሱም ለተከታዮቻቸው የሚያቀርቡት ሃይማኖት መዝናኛ እና ጥሩ ጊዜ ማሳለፊያ ብቻ ነው። በመዝናኛ ዝግጅቶች መካከል “ከአፍታ ቆይታ በኋላ እንመለሳለን” ተብሎ ማስታወቂያ እንደሚተላለፍ ሁሉ፣ እነዚህም መሪዎች ስለ ሥነ ምግባር ጥቂት ካወሩ እንኳ በማስታወቂያ ቈይታው ወቅት ነው። ቁም ነገሩ መዝናናት ነው፤ወንጌሉም አዝናኝ ሆኗል። በዚህ ሁኔታ ከቀጠሉ “ቤቴ” ወደ “ቤታችሁ” መቀየሩ አይቀርም። ዋነኛው አጀንዳ ሕይወትን የሚለውጠውና ነፍስን የሚያሳርፈው ምክረ እግዚአብሔር ቢሆን እና የአፍታ ቈይታው ደግሞ ለአዝናኝ ነገሮች ቢመደብ ግን ቤቱ “ቤቴ” እንደ ተባለ ይቀጥላል።

ሰዎች ትኵረታቸውን ወደ ራሳቸው አድርገው የክርስቶስ ማዕከላዊነት ከተዘነጋ ለእርስ በርስ ትሥሥራችንም አደጋ ነው። ሁሌም ጠንካራና ብርቱ ሆኖ የሚኖር ደግሞ የለም። ክርስቲያኖች “ጠንካራ ወይም ደካማ አይደለንም፤ ሁሌም ጠንካራ እና ደካማ ነን። በዚህ ቅንጅት መኻልም ሰው መሆናችንን እናያለን።”3እያንዳንዳችን የሌላኛው አማኝ ሐዘን፣ ማጣት እና ሕመም ሊቆጠቁጠን ይገባል፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ቤት እስካለን ድረስ አንዳችን ለሌላኛችን ማስፈለጋችን ግድ ነው። ክርስቶስን ማዕከል ማድረጋችን የቤተ ሰባዊነታችን ምሰሶ፣ የግንኙነታችን ማጥበቂያም ነው። ትሥሥራችን የብስክሌት ጎማ ይመስላል። የብስክሌት ጎማ ላይ ከመኻል ወደ ዳር የተወጠሩት ማጠናከሪያ ሽቦዎች የጎማው ማዕከላዊ ስፍራ ላይ ይቀራረባሉ፤ ወደ ዳር ሲሄዱ ግን ይራራቃሉ። እንዲሁ እኛም ወደ ማዕከሉ፣ ወደ ክርስቶስ ስንጠጋ እንቀራረባለን፤ ከማዕከሉ ስንርቅ ደግሞ እርስ በርስም እንራራቃለን። እርስ በርስ እንደ ቤተ ሰብ ስንተሣሠር የቤቱ ራስ “ቤቱ ቤቴ ነው” እንዳለን እንቀጥላለን፤ መሠረታዊ ያልሆነ ልዩነታችንን የምናጎላ ከሆነ “ቤቱ ቤታችሁ እንጂ ቤቴ አይደለም” እንባላለን።

በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ ያላቸው ነገሮችንም ተገቢ ትርጕማቸውን ቀይረን ደስ በሚያሰኘን እየተካን መሆኑም ሌላ አደጋ ነው። ዘመኑ አእምሮ አልባ ነውና የነገሮች ፋይዳ ደስ ማሰኘታቸው ላይ ብቻ እየሆነ ይመስላል። “መሰለኝ፤ ደስ አሰኘኝ” የዘመኑ ግዙፍ ማሳመኛዎች ናቸው። ከልጅ እስከ ዐዋቂ ሁሉም ሰው “ደስ ካሰኘህ አድርገው፤ ካልመሰለህ ተወው” የሚል ስብከት ተከታይ ሆኗል። በአገልጋዮች ዘንድ እንኳ ጋብቻ እና ጾታዊ ቅድስና ዋጋ እያጡ የመሰለበት ጊዜ ላይ መድረሳችን ለዚህ ሳይሆን አይቀርም። አምልኮም በሁለንተናዊ ኑሮአችን የሚገለጥ ሆኖ ሳለ፣ ለአንዳንዶች ዝማሬ ብቻ ነው። ስለዚህ የትኛውም ሰው እየዘለለ ከዘመረ ወይም እየዘመረ ከዘለለ፣ “አምልኮዬን አድርሻለሁ” ብሎ እስከ ማሰብ ይደርሳል። በዚህ መልኩ ፈጽመን ለጌታ መገዛት ካቃተን፣ እየዘመርን ቅድስና ከሌለን ከንቱዎች ነን። የምንኖረውም በ“ቤታችን” እንጂ በቤቱ አይደለም።

የክርስትና ትርጓሜም እየተቀየረ ይመስላል። የክርስትና ፋይዳ በገንዘብ እየተሰላ ነው። ቢሊ ግራሃም፣ “አንድ ሰው ገንዘብን የሚመለከት ዝንባሌው ከተቃና፣ ከሞላ በጎደል በሕይወቱ ያሉ ሌሎች ዘርፎች ሁሉ እንዲቃኑ እገዛ ይሆነዋል”4 እንዳሉት በዚህ ጒዳይ ላይ ያለን አቋም እጅግ ወሳኝ ነው። ለአንዳንዶች ወንጌል ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና ነው። ብልጽግናን ይዘን ቅድስና ካጣን ግን በእግዚአብሔር ቤት አይደለም። ለአንዳንዶች ደግሞ ወንጌል ድኽነት እና ጕስቁልና ነው። ይህም ግን ያለ ቅድስና ከንቱ ነው። ሰዎችን ስንጋብዝ ለድነት፣ እግዚአብሔርን ለመምሰል እና ለደቀ መዝሙርነት ካልሆነ የጋበዝናቸው ወደ ገዛ ቤታችን ነው፤ ወደ እርሱ ቤት አይደለም።

ቅድስና ደግሞ ለአንዳንዱ ውጫዊ ደንቦችን መከተል ነው፤ ለሌላው ደግሞ ከውጫዊ ደንቦች አርነት አግኝቶ እንዳሻው መሆን። የአውሮፕላን አብራሪዎች የአቅጣጫ ጠቋሚ “ኮምፓስ” ቢኖራቸውም፣ መሬት ላይ ባሉ ባለሞያዎች ቢታገዙም ለማረፍ ሲፈልጉ የማረፊያ መንገዱን መብራቶች ይከተላሉ። ልክ እንዲሁ በውስጣችን ያለው ቅዱስ መንፈስ ውስጣችንን ቢመራውም ምሪቱን በራስ ወዳድነት ከመተርጐም የሚጠብቁ ውጫዊ ሥርዐቶችና ደንቦችም ያስፈልጉናል፤ ለእርስ በርስ መግባቢያነትም ይጠቅሙናል። ስለዚህም ቅዱሱ መጽሐፍ እንደሚያቀርበው የውስጡ ሕይወት እና የውጭው ደንብ የተጣጣመበት ቤት ቤቱ ነው። ክርስትናን የሆኑ ሕግጋትን በመከተልና ባለመከተል ብቻ ከተተረጐመ እና ውስጣዊው ሕይወት ችላ ከተባለ ግን ስፍራው ቤታችን መሆኑ ርግጥ ነው።

አማኞች ክርስቶስን እንዲመስሉ የሚደክሙ መሪዎች ከሌሉ፣ ልፋቶቻችን በሙሉ የየሳምንቱ የቤተ ክርስቲያን መርሓ ግብሮች እንዲፈጸሙ ከሆነ ከስረናል። “ሰንበት ለሰው ልጅ ተፈጠረ እንጂ፣ የሰው ልጅ ለሰንበት አይደለም” እንደተባለው ሁሉ፣ የቤተ ክርስቲያን መርሓ ግብሮች ለሰው ልጅ ተፈጠሩ እንጂ የሰው ልጅ ለእነርሱ አልተፈጠረም። በቤተ ክርስቲያን የሚኖረን መርሓ ግብር ሁሉ የሰዎችን ሕይወት ለመሥራት፣ የእግዚአብሔር ቤት የሚታነጽባቸውን ሕያዋን ድንጋዮች ለመቅረጽ ማገዝ አለበት። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ሥራው ሁሉ ለራስ ክብር ለማምጣት እና ለእግዚእብሔር ክብር መዋጮ ማድረግን ለማሳየት መሆኑ አይቀርምና ቤቱን ወደ ቤታችን ይቀይረዋል። ስለዚህ ቤቱን ከባለቤቱ እየወሰድን ወይም ባለቤቱ ቤቱን ትቶልን እየሄደ እንዳይሆን ያስፈራል። ዛሬን ብቻ እያየን ነገን ከማየት ከታወርን፣ የዛሬ ድርጊታችን በአገሪቱ፣ በቤተ ክርስቲያን እና በመጪው ትውልድ ነገ ላይ ለሚፈጥረው ጫና ግድ ከሌለን፣ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ያለችውን እንስሳ መስለናልና ጌታ “ቤቴ” ያለው ስፍራ ያለ ጥርጥር “ቤታችን” ብቻ ሆኖ ቀርቷል።

ጆሮ ያለው ይስማ!

ማስታወሻ

1 Eugene H. Peterson, Under the Unpredictable Plant: An Exploration in Vocational Holiness (Grand Rapids: Eerdmans, 1992), 37-38.

ዝኒ ከማሁ።

Lewis B. Smedes, Forgive & Forget: Healing the Hurts We Don’t Deserve (New York: HarperOne, 1996), 141.

Jay Kesler, Being Holy, Being Human: Dealing with the Expectation of Ministry (Carol Stream: Word Books, 1988), 153.

Paulos Fekadu

ጳውሎስ ፈቃዱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኮምፒውተር ሳይንስ ማስተርስ፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ የሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ት/ቤት በስልታዊ ነገረ መለኮት (Systematic Theology) ማስተርስ አለው፡፡ "የእግዚአብሔር ልጅ"፣ “ያልተንኳኩ በሮች” እና "የብርሃን አንጓዎች" የተሰኙ መጻሕፍትን ሲጽፍ፣ ሌሎች ዐሥራ አንድ የትርጕም መጻሕፍትን ለንባብ አቅርቧል። ለበርካታ መጽሔቶችና ድረ ገጾች የተለያዩ ጽሑፎችን ሲያበረክት ቆይቷል። ለንደን በምትገኘው የኢትዮጵያውያን ቤተ ክርስቲያን (ECFCUK) በመጋቢነት የሚያገለግለው ጳውሎስ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነው።

Share this article:

የአብርሃም እንግዶች እነማናቸው?

እውነተኛ ገጠመኝ ነው። ከኹለት ዐሠርት ዓመታት በፊት ታቦተ ሥላሴ ደባል[1] በኾነበት በአንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሐምሌ ሥላሴ ክብረ በዓል የተገኙት ምእመናን በቍጥር ጥቂት ነበሩ። ይህን የታዘቡትና በሥልጣን በመናገር የሚታወቁት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በኹኔታው ዐዝነው እንዲህ ብለው ነበር፤ “ምእመናን ዛሬ የሥላሴ በዓል እኮ ነው? ምነው ታዲያ ምእመናኑ ጥቂት ኾኑ? ይህን ጊዜ የገብርኤል በዓል ቢኾን እንኳን ለዓመቱ ለወሩም ብዙ ሕዝብ ይገኝ ነበር፤ ምእመናን ከገብርኤል እኮ ሥላሴ ይበልጣሉ? ስለዚህ ማንን ማምለክ እንዳለብን ማስተዋል ይገባናል።”

ተጨማሪ ያንብቡ

የጸሎት ኀይል ለአእምሮ ተሓድሶና ለውጥ

እግዚአብሔርን ያስደነቀና ያስገረመ ነገር ካለ በርግጥም አስገራሚና አስደማሚ ጕዳይ ነው። የእግዚአብሔር ቃል በኢሳያስ 56፥19 ላይ እንዲህ ይላል፡- “ሰውም እንደሌለ አየ፥ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ ተደነቀም …”፡፡ እግዚአብሔር በምንም የማይገረምና የማይደነቅ አምላክ ነው። ታድያ በሰው ልጆች አለመጸለይና አለመማለድ ስለ ምን ይሆን የተደነቀው? የምር ልብ ብለን ብናየው እርሱን ያስደነቀ ነገር እውነትም ድንቅ ነው። በጸሎት ውስጥ ያለው ኀይል ወሰን የማይገኝለት ነው፤ አምሳያም የሌለው ነው። ፀሓይንና ጨረቃን በስፍራቸው ያቆመና ባህርን ከፍሎ እንደ ግድግዳ ያቆመ ኀይል ከጸሎት ውጪ ከየት ሊያገኝ ይችላል? ሙታንን ማስነሣትና አጋንንትን ማስወጣት የሚችል ጉልበት በየትኛውም የምርምር ጣቢያና ዩኒቨርስቲ ውስጥ እንዳለ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አልተሰማም። መናን ከሰማይ የሚያወርድና ውሃን ከዐለት ለማፍለቅ የሚችል ኀይል በታሪክ ውስጥ አልተመዘገበም። ጸሎት ለደካማ ሰዎች የተሰጠ ብርቱ መለኮታዊ ክንድ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.