ሁለት ልጆች አሉኝ። ትልቁ ልጄ ዕድሜው 20 ሲሆን የ3ኛ ዓመት የሕግ ተማሪ ነው። ሁለተኛዋ ልጄ ዕድሜዋ 9፣ በትምህርቷም የ4ኛ ክፍል ተማሪ ናት። ሁለቱን ልጆቼን ሳሳድግ “አባትነት” ማለት ምን ማለት እንደ ሆነ በተግባር ያየሁበት ግሩም ትምህርት ቤቴ ስለ ሆነ ይህንን ጽሑፍ ሳዘጋጅ ለመንደርደሪያነት ልጠቀምበት ወሰንኩ። ይህን በማደርግበት ጊዜ ደግሞ በተወሰነ ደረጃ ታሪኩን የማካፍላችሁን የትልቁ ልጄን ፈቃድና ስምምነት በማግኘቴም እንደ ሆነ መጥቀስ እወዳለሁ።
ልጄ ወደ ወጣትነት ዕድሜ ውስጥ ሲገባ ብዙም ሳልዘጋጅ ነበር። እናም ልጄ ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ ወራት ፈጅቶብኛል። በወጣትነቱ ወራት ብዙ ወጣቶች በሚያልፉባቸው አስቸጋሪና ጥልፍልፍ ጎዳናዎች ውስጥ አልፏል። በየጊዜው የማወጣቸውን የቤቴን ሥርዐት ተላልፏል። በእነዚያ ወራትና ከዚያም በፊት ልጄን መሥመር ለማስያዝ ያላደረኩት ነገር አልነበረም። ልጄ ነዋ! ከእግዚአብሔር በዐደራ የተቀበልኩት ልጄ ስለ ሆነ በገባኝና “ትክክል ነው” ብዬ ባመንኩት መንገድ እንዲጓዝ እጅግ ብዙ ጥሬያለሁ። በጤናማ ጎዳና ላይ የማይሄደውን ልጁን ለማረምና ወደሚፈለገው የሕይወት መንገድ ለመመለስ አንድ አባት “ያደርጋል” ተብሎ የሚታሰበውን ሁሉ አድርጌያለሁ። አውጥቼያቸው የነበሩትን የቤቴን ሥርዐት ቢተላለፍም ልጄ ነውና አንድ ቀን እንኳን የቤቴን በር አልዘጋሁበትም። ቢያጠፋም፣ ቢያበላሽም፣ ስሕተቶችን ቢሠራም፣ ሥርዐቶቼን ቢተላለፍም ቤቴ ቤቱ ነውና ይመጣል። ባዝንም፣ ብከፋም፣ አንዳንዴ ልቤ ቢሰበርም ልጄ ነውና አዎን፤ ልጄ ነውና እቀበለዋለሁ። እናም በብዙ ትዕግስት ከባለቤቴ ጋራ ሆነን እነዚያን የጭንቅ ወራት አሳለፍን።
ቸርነቱ የማያልቀውና ባለብዙ ጸጋው አምላካችን እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን። ራራልን፤ ደረሰልን፤ ጩኸታችንን ሰማ፤ እናም ዘንበል አለልን። ስሙ የተባረከ ይሁን! ለእግዚአብሔር ምን ይሳነዋል? የእነዚያን ወራት ታሪክ ተረት አደረገልን። አሁንም የእግዚአብሔር ስም ለዘላለም የተባረከ ይሁን!
ይህንን የቤተ ሰቤን፣ በተለይም የልጄን ታሪክ ያለ ምክንያት ለመንደርደሪያነት አላመጣሁትም። ፍጹም የሆንኩ አባት ነኝ ለማለት ባልደፍርም፣ “አባትነት” ምን ማለት እንደ ሆነ ትንሽ ስለተረዳሁ፣ የአባትነት የትዕግስት ፍሬም እንዴት እንደሚጣፍጥ ስለቀመስኩ፣ ይህንን ጽሑፍ ለሚያነቡ ሁሉ፣ በዋናነት ደግሞ የሰሞኑን የኅብረቱን ውሳኔ አስመልክቶ መልእክት ለማስተላለፍ ስለወደድኩ ብቻ ነው።
ይህንን ጽሑፍ የምታነብቡና አባት/እናት የሆናችሁ ወላጅነትን እንዴት ሆኖ አገኛችሁት? የልጅን ፍቅር እንዴት አገኛችሁት? ምናልባትም እናንተ ወላጅ ባትሆኑም እንኳን በወላጅ እጅ ያደጋችሁ ልጅነትን እንዴት አገኛችሁት? ወላጅ አባቴ ገና በ10 ዓመቴ በሞት ስለተለየኝ የአባትን ፍቅር እንደ እኔ የማታውቁ፣ ያሳዳጊን ፍቅር እንዴት አገኛችሁት? መቼም አንድ ሰው በአባት ወይም በእናት እጅ ባያድግ እንኳን ቢያንስ አንድ ቸር ሰው፣ አንድ መልካም ሰው በሕይወቱ ውለታ ውሎለታልና በዚህ ውለታ በዋለለት ሰው ዘንድ ባይታሰብ ኖሮ ምን ይውጠው ይሆን? ዛሬ ስለ እነዚህ እጅግ ብዙ መልካም ሰዎች በጎነትና ቸርነት ማንሣት ባልችልም፣ ስለ አባትነት ግን እንድጽፍ ፍቀዱልኝ። ስለ አባትነት በምጽፍበት በዚህ ጽሑፌ ከቤተ ክርስቲያን አመራር ጋር በማያያዝም እንደ ሆነ ለመጠቆም እወድዳለሁ።
መጽሐፍ ቅዱሳችን አመራርን አስመልክቶ እጅግ ግሩም የሆኑ ትምህርቶችን ያስተምረናል። እነዚህን ትምህርቶች በሙሉ ጠቅሶ ለመዘርዘር ጊዜውም፣ ቦታውም አይፈቅድልንም። ይሁንና ለተነሣሁበት ዐላማ የሚስማማውንና ከአዲስ ኪዳናዊው የአመራር ዘይቤ አንዱ የሆነውን የአባትነትን ዘይቤ በመምረጥ እንደሚከለተው አቀርባለሁ።
አባትነት – አዲስ ኪዳናዊው አመራር
የቤተ ክርስቲያንን አመራር በምን እንመስለዋለን? መጽሐፍ ቅዱሳችንስ ምን ዐይነት ምሳሌ ይሰጠናል?
በየወቅቱ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን (በተለይም ሽማግሌዎችን) ለመሾም ሲታሰብ የሚነበበው ክፍል ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የጻፈው የመጀመሪያው መልእክት፣ ሦስተኛው ምዕራፍ ነው። በዚህ ምዕራፍ ከቁጥር 1 እስከ 7 ድረስ የመሪዎች (የሽማግሌዎች) መመዘኛዎች አሉ። እንደ ማንኛውም ክርስቲያን እነዚህን መመዘኛዎች ለዓመታት አንብቤያለሁ። ከአራት ዓመት ወዲህ ግን በተለየ መንገድ እያነበብኩት እገኛለሁ። ይህ በተለየ መንገድ እያነበብኩት ያለው ክፍል እንዲህ የሚለውን ጥቅስ ይዟል፡- “ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር” (1ጢሞ 3፥4)። እንደምትመለከቱት ይህ ጥቅስ ቁጥር 5 ላይ የተጻፈ ማብራሪያ አለው። ማብራሪያው እንዲህ ይላል፡- “ሰው ግን የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር ባያውቅ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል?”።
በዚህ ምዕራፍ ውስጥ እስከቁጥር 3 ድረስ ያሉት መመዘኛዎች 12 ሲሆኑ፣ የትኛውም መመዘኛ ነጥብ ምንም ዐይነት ማብራሪያ አልተሠጠበትም። ይሁንና ቁጥር 4 ላይ ሲደርስ አባትነትን ዝም ብሎ አላለፈውም። እስከ ቁጥር 3 ድረስ የመጣበትን አኳኋን በመቀየር ማብራሪያ ይሰጠዋል። በርግጥ ቀጥለው የተጠቀሱትን ሁለት መመዘኛ ነጥቦች አዲስ በጀመረው መንገድ ሲያብራራ እናያለን።
ይህ አንድ የሚጠቁመን ነገር አለ። ሐዋርያው አባትነትን የቤተ ክርስቲያን አመራር ምሳሌ አድርጎ ማቅረቡና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የአባትነትን ባሕርይ የተላበሰ መሪ አስፈላጊነትን የሚያጎላ ይመስላል። አንድ ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን መሪነት ከመምጣቱ በፊት አመራርን ቤቱ መማር እንዳለበትም ያሳየናል። መሪው ባለ ትዳር ከሆነና ልጆች ካሉት በቤተ ሰቡ ላይ (በተለይም በልጆቹ ላይ) ያልተለማመደውን መሪነት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማሳየት ከባድ ይሆንበታል። ይህ ማለት በተለያየ መንገድ አባት መሆን ያልቻለ ሰው አይምራ ወደሚለው አንድምታ እንዳይሄድ ያስፈልጋል። ለእኔ የሚገባኝ በዚህ ምንባብ መሠረት አንድ ሰው ቤተ ሰብ ካለው፣ ቤቱን እንደሚገባ የሚያስተዳድር፣ ልጆቹን በጭምትነት የሚመራ ሊሆን የግድ ነው።
በዚህ ክፍል ውስጥ “በመልካም የሚያስተዳድር” እና “ልጆቹን በጭምትነት የሚገዛ” የሚሉት ሐሳቦች ከአመራር ጋር ይያዛሉ። እነዚህ ሐሳቦች የቤተ ሰብ አመራርን አስተዳደርንና መሳሳት (ላልቶ ይነበብ) የጎላበት ጥንቃቄን (care, concern) እንደሚያመለክት ምሁራን ይጠቁማሉ።1 ሃዋርድ ማርሻል የተባሉ እንግሊዛዊ ስመ ጥር የመጽሐፍ ቅዱስ አጥኚ ይህንን መመዘኛ ነጥብ ወስደው ሰፊ ትንተና ከሰጡበት በኋላ፣ “ልጆችን መቆጣጠር የአንድ አባወራ ዋና ሥራ ሆኗል”2 ብለው የአባትነትን ኀላፊነት ከባልነት በላይ ያስቀምጡታል። ከእርሳቸው ሐሳብ ጋር ሳሙኤል ኤንጌዋ የተባሉ አፍሪካዊ ምሁርም ይስማሙበታል።3 ሳሙኤል ኤንጌዋ ይህንን አባቶች በቤት በልጆቻቸው ላይ መለማመድ ያለባቸውንና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲያሳዩ የተጠየቁትን አመራር “loving leadership” (“የፍቅር አመራር” እንደ ማለት ነው) በማለት ሰይመውታል።4 ሐዋርያው ጳውሎስ አባቶች ልጆቻቸውን “በጭምትነት” እንዲያስተዳድሯቸው ሲያመለክት፣ ይህ ፍቅር የተሞላው አመራር እንዴት መተግበር እንዳለባቸው ማሳየቱ ነው። በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “ጭምትነት” የሚለው ቃል በተለያየ መንገድ ቀርቧል። ለምሳሌ ያህል ሦስት ትርጉሞችን ብንወስድ “with all gravity” (1Tim 3:4, KJV) ወይም “with all dignity” (NAS) ወይም “in a manner worthy of full respect” (NIV) በማለት ተርጉመውታል። ፊሊፕ ግራሃም ራይኪን የሚባል ምሁር ይህ ቃል፣ “(በእግዚአብሔር አምሳል እንደተፈጠሩ በመቁጠር) በአክብሮት… ያለማዳላት፣ በአዝልቆት፣ በርኅራኄና በምሕረት”5 መምራትን እንደሚያመለክት በማብራራት ጽፈዋል። ፍጹም ሥልጣን እንዳላቸው በሚቆጠርበት በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን አባቶች ልጆቻቸውን እንዲህ ባለ መሳሳት (ላልቶ ይነበብ)፣ ርኅራኄ፣ ምሕረትና ፍቅር እንዲመሩ መታዘዛቸው ትልቅ የአቅጣጫ ለውጥ (Paradigm Shift) እንደ ሆነ ሃዋርድ ማርሻል አመልክተዋል።6
ይህ ትንተና የሚያሳየን አዲስ ኪዳናዊው የአመራር ዘይቤ በመልካም አባትነት የተመሰለ ሲሆን፣ ያንን በቤት ውስጥ አባቶች ለልጆቻቸው እየራሩ፣ እያዘኑ፣ እየወደዷቸውና እየሳሱላቸው የሚለማመዱትን አመራር ወደ ቤተ ክርስቲያን ይዘው እንዲመጡ መፈለጉን ነው። ሰዎች ደግሞ ለሌላው ምን ክፉዎች ቢሆኑ ለልጆቻቸው እጅግ መልካም ናቸው። ጌታ ኢየሱስ እንደተናገረው ሰዎች ለሌላው ሰው ክፉ ቢሆኑም እንኳን ልጆቻቸው እንጀራ ሲለምኗቸው በፍጹም ድንጋይ አይሰጧቸውም፤ ዓሣ ሲለምኗቸው እባብ አይሰጧቸውም፤ እንቁላልም ሲጠይቋቸው ጊንጥ አይሰጧቸውም (ሉቃ 11፥11-13)። የሚገርመው ግን እነዚህ አባቶች “ለልጆቻቸው አልጋ፣ ለሌላው ቀጋ” (ተረቱ እንደተገላበጠ ይታወቅልኝ) ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ ግን ለልጅ አልጋነት “በጭምትነት”፣ “በፍቅር”፣ “በመሳሳት” (ላልቶ ይነበብ) ይገለጥና ይህንኑ የአመራር ዘይቤ ይዘው ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመጡ አዘዘ። “የቤት ቀጋ፣ የደጅ አልጋ“ ሆነ “የቤት አልጋ፣ የውጪ ቀጋ” የሚባል ጉራማይሌነት በቤተ ክርስቲያን እንዲኖር አይታሰብም።
ይህ ነው እንግዲህ አዲስ ኪዳናዊው የአመራር ዘይቤ፤ አባትነት። ለልጅ፣ ምናልባትም ለአጥፊ ልጅ የሚገለጥ አባትነት። አባካኙን ልጅ የተቀበለ በፍቅር፣ በምሕረትና በደስታ የሚቀበል አባትነት። ከዚያም አልፎ እንደ ሰማዩ አባት ፍጹም አባትነትን መላበስ። የፍቅርንና የምሕረትን እጅ እየዘረጉ ሁሌ ወደ እውነት ለመምራት መናፈቅ፣ መትጋት። ይህ ነው አባትነት፤ ይህ ነው መሪነት፤ አዲስ ኪዳናዊው መሪነት። ያን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሚያዝንም ሆነ የሚከፋ አይኖርም፤ ያን ጊዜ የመሪዎችን ምክር የሚገፋ አይኖርም፤ ያን ጊዜ የወደቀ አባት በሆኑ መሪዎች ይነሣል፤ ያን ጊዜ የተጣመመውም ይቃናል።
የኅብረቱ ውሳኔ ከአዲስ ኪዳናዊው አመራር አንጻር
በርእሳችን ላይ እንደተመለከተው የኅብረቱ ውሳኔ (ማለትም “አጋር አባል” በሚል ስያሜ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን ለመቀበል ያደረገው ውሳኔ ) ከአዲስ ኪዳናዊው አመራር አንጻር ሲታይ ምን ይመስላል? ከላይ አዲስ ኪዳናዊውን የአመራር ዘይቤ እንደ ጽንሰ ሐሳባዊ መዋቅር (theoretical framework) ስንጠቀምበት መልሱ እናገኛለን።
ወላጅ የሆናችሁ ንገሩኝ። አንድ ልጃችሁ ሲያጠፋ ምን ታደርጋላችሁ? ባሰመራችሁለት መሥመር ባይገኝ ትገርፉት ይሆናል፤ አለንጋውን ባይሰማ ትመክሩት ይሆናል፤ ያንንም ባይሰማ ምን ታደርጉታላችሁ? ከቤት ታባርሩታላችሁ? ደጅ ታወጡታላችሁ? ለጎዳና ተዳዳሪነት ትዳርጉታላችሁ? እያለቀሳችሁም ቢሆን አትታገሱትም? እያለቀሳችሁም ቢሆን በመሥመር ላይ እንዲመላለስ አትለምኑትም? እኔ የተለየሁ አይደለሁም። ይሁን እንጂ ለልጄ “መፍትሔ ይሆናል” ያልኩት በሙሉ አልሠራ ባለ ጊዜ በፊቱ አለቅስ እንደ ነበር ልንገራችሁ? እንዲህ በማድረጌ ልጄን ገንዘብ አድርጌዋለሁ።
ማነው ታድያ ለልጁ ራርቶ በሌላው የሚጨክን? ማነው ታድያ ልጁን ገንዘብ በማድረግ የተካነው ሰው ሌላውን ለማዳን የሚቻለውን ያህል የማያደርገው? አንድ ሰው ልጁን ይቅርና በጉን እንኳን የሰንበትን ሕግ ጥሶ ከወደቀበት ጉድጓድ ያወጣው የለ? እና ሰውን ለማዳን ምን ያህል ርቀት እንሄዳለን? ሰው ከበግ አይበልጥምን (ማቴ 12፥11-12)?
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት በ32ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔው ባወጣው የአቋም መግለጫ ላይ ተ.ቁ 8 እንዲህ ይነበባል፡-
እኛ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች፣ ከላይ በተጠቀሱት የተሳሳቱ የአስተምህሮ፣ የልምምድና የሞራል መንገድ ውስጥ ያሉ ቤተ እምነቶች፣ መገናኛ ብዙኀን እንዲሁም ግለ ሰቦች፣ ካሉበት የተሳሳተ አካሄድ እንዲመለሱ በራችንን ክፍት አድርገን በክርስቲያናዊ ፍቅር ጥሪ እናደርጋለን፤ ነገር ግን ይህን ለማድረግ ፈቃደኞች በማይሆኑትና በስሕተት መንገዳቸው ለመቀጠል በፈቀዱት ላይ ተገቢው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርምጃ እንዲወሰድ፣ ይህንንም የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የሥራ አመራር ቦርድና የኅብረቱ ፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት በጋራ እንዲያስፈጽሙት ሙሉ ኀላፊነት እንሰጣለን::
በዚህ የአቋም መግለጫ መሠረት የኅብረቱ የሥራ አመራር ቦርድና የኅብረቱ ፕሬዝዳንት ሁለት ሥራዎችን እንዲያስፈጽሙ ከጠቅላላ ጉባዔው “ሙሉ ኀላፊነት” ተሰጥቷቸዋል። እነዚህም በስሕተት ጎዳና ላሉ ቤተ እምነቶችና ግለ ሰቦች “ካሉበት የተሳሳተ አካሄድ እንዲመለሱ (በራቸውን ክፍት አድርገው በክርስቲያናዊ ፍቅር ጥሪ እንደሚያደርጉላቸው)” እና “ይህን ለማድረግ ፈቃደኞች በማይሆኑትና በስሕተት መንገዳቸው ለመቀጠል በፈቀዱት ላይ ተገቢው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርምጃ እንዲወሰድ” የሚያዝዙ ናቸው። ይህንን አስመልክቶ ሕንጸት መጽሔት በቁጥር 9፣ 2009 ዓ.ም. ዕትሙ ላይ ባሰፈረው ሐቲት ላይ “በተለይም፣ በአቋም መግለጫው ተራ ቊጥር 8 ላይ፣ የኅብረቱ ጽ/ቤት እና የሥራ አስፈጻሚው ቦርድ በጋራ እንዲተገብሯቸው የተሰጡ ኀላፊነቶች፣ የአቋም መግለጫውን ከማውጣት ያለፈ ተግባር በኅብረቱ ላይ መውደቁን ያመለክታል”7 በማለት አመላክቷል።
በዚህ የአቋም መግለጫ መሠረት ሙሉ ውክልናው ከምን እስከ ምን ድረስ እንደ ሆነ ከመገመት ውጪ ርግጠኛውን ማወቅ አይቻልም። በኅብረቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት አባላትንም ሆነ ተባባሪ አባላትን የመቀበል የመጨረሻው ሥልጣን የጠቅላላ ጉባዔው ነው። ጠቅላላ ጉባዔው ይህንን በመረዳት ከዚህ ከሥልጣኑ ቆርሶ ለሥራ አመራር ቦርዱና ለፕሬዝዳንቱ “ሙሉ ኀላፊነት” ከሰጠ ሂደቱንም ሆነ ውሳኔውን “እሰየው” ያስብላል። እዚህ ላይ በኅብረቱ መተዳደሪያ ደንብ የሌለ “አጋር አባል” የሚባል መስፈሪያ መበጀቱ እንደ ሥነ አመራር ባለሙያ ይበል የሚያሰኝ ነው። የኅብረቱ የሥራ አመራር ቦርድና ፕሬዝዳንቱ “ሙሉ ኀላፊነት” ከተሰጣቸው፣ “ኀላፊነቱ” ደግሞ “ ጥሪ ከማድረግ እስከ መቀበል ድረስ ከሆነ፣ የሚቀላቀሉት ቤተ እምነቶችና ግለ ሰቦች ደግሞ እስካሁን ባለው የአባልነት “ቋት” ውስጥ ሊካተቱ የማይችሉ ከሆነ፣ ሊካተቱ የሚችሉበትን “መዋቅር (Framework)” ማዘጋጀት ብልህነት፣ በአመራር ሳይንስ ደግሞ የፈጠራ ችሎታ (Creativity) ነው።
እነዚህ ቤተ እምነቶችና ግለ ሰቦች “ራሳችንን ለኅብረቱ እናስገዛለን” ብለው ከነበሩበት ጥግ ለመምጣት መወሰናቸው “በቂ ነው” ባይባልም ቀላል ርምጃ ግን አይደለም። የኅብረቱ የሥራ አመራር ቦርድም ሆነ ፕሬዝዳንቱ በአባትነት መንፈስ ቢያደርጉትም ባያደርጉትም ለእኔ የቤተ እምነቶቹንና የግለ ሰቦቹን ርምጃ መቀበላቸውና ወደ ስምምነት መድረሳቸው፣ “ከአባት የሚጠበቅ ነው” እንዲባል ያደርጋል። የልጁን ወደቀና ጎዳና መመለስ ለሚናፍቅ አባት እንዲህ ዐይነቱ ርምጃ አስደሳች ነው። እንዲህ የተጀመረ የመመለስ ጉዞ በበለጠ የአባትነት መንፈስ ሲታገዝ ወደሚፈለገው ደረጃ ማድረስ ይቻላል። እየተወተወተ ያለውና ተገቢም የሆነው የንስሐ ፍሬ ዘንድ ማድረስ የአባት ድርሻ ነው። አስቀድሜ እንዳልኩት የኅብረቱ የሥራ አመራር ቦርድም ሆነ ፕሬዝዳንቱ ይህንን ውሳኔ በአባትነት መንፈስ ቢያደርጉትም ባያደርጉትም፣ ከዚህ በኋላ ሆን ብለው በአባትነት መንፈስ ቢያደርጉት እነዚህን ሰዎችና አብያተ ክርስቲያናቱን ሁሉ ገንዘብ ማድረግ ይቻላል። ለአንድ አባት የጠፋ፣ የሳተ ልጁ መመለስ ካልሆነ በቀር ምን ደስ የሚያሰኘው ነገር ይኖራል? ልጁ እንዴትም ይመለስ ዋናው ነገር መመለሱ ነው። መረሳት የሌለበት ነገር ጌታ ኢየሱስ በሰጠው የአባካኙ ልጅ ምሳሌ ውስጥ’ኮ ልጁ ወደ አባቱ የተመለሰው ከስሮ፣ ያሰበው አልሆን ብሎት፣ የሄደበት መንገድ ስላላዋጣው እንጂ የሠራው ሥራ ስሕተት እንደ ሆነ ተገንዝቦ አይደለም። የመመለሱ ዋና ምክንያት እንጀራ ነበር። ቃሉ “ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ፦ እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ” (ሉቃ 15፥17) ይላልና።
እናም ለአባት ትልቁ ቁም ነገር የልጁ መመለስ ነው። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በእንደዚህ ዐይነት የአባትነት መንፈስ ከተቃኙ ልጆቻቸው ከነጎዱበት ስሑት ጎዳና ሲመለሱ ከነብዙ ጣጣቸው ቢመጡም የማጠቡ፣ የማጽዳቱ፣ ልብስ የመቀየሩ፣ ደስታን የማወጁ ሥራ የአባቶች ነው። “እሰይ! ደስ ይበለን” ይባላል።
ማጠቃለያ
ይህንን ጽሑፍ በተለያዩ ቅርጾች በሁለት መድረኮች ላይ አቅርቤዋለሁ። አንደኛው ሐምሌ 2009 ዓ.ም. አየር ጤና አካባቢ ለሚገኙ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ኮንፈረንስ ላይ ሲሆን፣ እንዲህ በተደራጀ መልኩ ባይሆንም በተወሰነ መልኩ “አሁን ላለው እንቅስቃሴ የመሪዎች ሚና ምን መሆን አለበት?” በሚል ሐሳብ ዙሪያ የትምህርት ርእስ ሆኖ ቀርቦ ነበር። ያ ወቅት መጋቢት 2009 ዓ.ም. ከተካሄደው 32ኛው መደበኛ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጠቅላላ ጉባዔ ማግስት ስለ ነበር፣ የአየር ጤናው ዞን መሪዎች ኮንፈረንስም ያንኑ አጀንዳ ተከትሎ የተካሄደ ስብሰባ ነበር። በቀረበው የትምህርት አገልግሎትም የተወሰኑ ፓስተሮችና አገልጋዮች ስልክ በመደወል የተሰማቸውን ደስታ ገልጠውልኛል። ሁለተኛው ይህ ጽሑፍ በጣም ተደራጅቶ፣ ተስፋፍቶና ከአባትነት ጋር ተያይዞ መረጃ በመሰብሰብ በጥናት ወረቀትነት መልክ ቀርቦም ነበር። በተለይም አዲስ ኪዳናዊው የአመራር ዘይቤ ከዘመናዊውና ከባህላዊው የአመራር ዘይቤ ጋር ተሰናስሎ በሚያዝያ 2010 ዓ.ም. (እ.አ.አ. ሜይ 2018) ናይሮቢ፣ ኬንያ በተካሄደ ስምንተኛው የሎዛን ዓለም አቀፍ የተመራማሪዎች ኮንፈረንስ ላይ ቀርቧል። የጥናት ወረቀቱ “Image of Fatherhood as a Model of Church Leadership “ በሚል ርእስ ላይ የቀረበ ሲሆን፣ በተሳታፊዎችም ውይይት ተካሂዶበት ነበር።8
ዐቢዩ ነጥብ ይህ ነው፦ እኔ ልጄን ገንዘብ ለማድረግ የሚከፈለውን ዋጋ ከከፈልኩ፣ በአባትነት የተመሰለው አዲስ ኪዳናዊው የቤተ ክርስቲያን አመራር ልጅን በፍቅር፣ በመሳሳት፣ በምሕረትና በርኅራኄ መምራት ከሆነ፣ የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የሥራ አመራር ቦርድና ፕሬዝዳንቱ በ32ኛው የኅብረቱ ጠቅላ ጉባዔ በተሰጣቸው “ሙሉ ኀላፊነት” መሠረት ሥራቸውን ካከናወኑ፣ ሆን ብለው ባያደርጉትም እንኳን የሠሩት ሥራ የአባት ሥራ ነውና “እሰየው” ያስብላል። ከአሁን በኋላም ይህን የአባትነት መንፈስ በበለጠ በመላበስና የአባትነትን አመራር በመለማመድ ለወደቀው የመነሣት፣ ለታመመው የመፈወስ፣ ለተሰበረው የመጠገን፣ ላለቀሰው የመጽናናት፣ ለተበተነው የመሰብሰብ፣ በአጠቃላይ በክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሊኖር ለሚገባው ሙሉ በረከት ምክንያት ያድርጋችሁ!
VIDEO
ተያያዥ ጽሑፎች
የግርጌ ማስታወሻ
I. H. Marshall, A Critical and Exegetical Commentary on the Pastoral Epistles, (London : T & T Clark, 1999),
479; Samuel Ngewa, 1 & 2 Timothy and Titus, (Grand Rapids: Zondervan/HippoBooks, 2009), 67; Philip Graham Ryken, 1 Timothy: Reformed Expository Commentary. (Phillipsburg: P&R Publications, 2007), 116 Marshall, A Critical and Exegetical Commentary on the Pastoral Epistles, 479; Ngewa, 1 & 2 Timothy and Titus, 67. ዝኒ ከማሁ። Ryken, 1 Timothy: Reformed Expository Commentary, 116-117. Marshall, A Critical and Exegetical Commentary, 479ሚክያስ በላይ፣ “ታሪካዊ” የተባለው የኅብረቱ ውሳኔ እና የተሰጠው ምላሽ ፣ ሕንጸት ቅጽ 9 Lidetu Alemu Kefenie, Image of Fatherhood as a Model of Church Leadership, (Unpublished paper presented at the Eighth Lausanne International Researchers’ Conference: Nairobi, Kenya, May 2018).
Add comment