[the_ad_group id=”107″]

“ስለ ዘፈን” የሚለው የዘሪቱ ጽሑፍ

መግቢያ

ወዳጆቼ ፍቃደ ጥላሁንና ሳባ በየነ፣ በሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር ድረ ገጽ ላይ፣ ዛሬ ለንባብ የቀረበውን ጽሑፍ ማስፈንጠሪያ ሰደዱልኝ[1]። ጽሑፉ የእኅታችን የዘሪቱ ከበደ ነው። ይህ የእኅታችን ጽሑፍ በዋነኝነት፣ ዘፈንን የሚመለከት ቢሆንም፣ ብዙ ነጥቦችን ለመዳሰስ ሞክሮአል። እኔ ትኲረት የማደርገው ግን:— አንደኛ፤ ስለዘፈን በሚናገሩ የተወሰኑ ነጥቦች ላይ ብቻ ይሆናል። ሁለተኛ፤ “በተወሰኑ ነጥቦች ላይ ብቻ” አስተያየት መስጠት ያስፈለገው፣ ዘፈንን በተመለከተ የእኅታችን ተዐሳቢያን መሠረቶች እንዲሁም እንደ ሙግት ያቀረበቻቸው ነጥቦች፣ ወንድም ዮናስ ጐርፌ ሲሟገትባቸው የቈዩ እንዲሁም እኔ፣ “‘ቤት ያጣው ቤተኛ’ የወር ተረኛው ርእሰ ጒዳይ” እንዲሁም፣ “የአትዝፈኑ ሥነ አመክንዮ፤ መዝፈን የሌለብን ለምንድን ነው?” በሚሉት ሁለት ርእሶች መልስ ለመስጠት የሞከርሁባቸው ነጥቦች ስለሆኑ ነው። ስለዚህ በዘፈን ርእሰ ጒዳይ ላይ ትኲረት ማድረጌ ብቻ ሳይሆን፣ ነገር በመደጋገም አንባቢን ማሰልቸት አግባብ ስለማይሆን፣ ዐዳዲስ ለሆኑ እንዲሁም ትኲረት ሊደረግባቸው ይገባል፣ በምላቸው ነጥቦች ላይ ብቻ አነጠጣጥራለሁ።

የእርሷን ጽሑፍ ቃል በቃል ካሰፈርሁ በኋላ፣ አስተያየቴንና ሙግቴን አስከትላለሁ። “ዘሪቱ” የሚለው የእርሷ ሙግት፣ “እኔ” የሚለው ደግሞ፣ የእኔ አጸፋ ነው። ንግባእኬ ኀበ ዐበይት ሙግት (ወደ ዋናው ሙግታችን እንመለስ):—

ዘሪቱ

1. “ጌታን በሙዚቃ ሕይወት ውስጥ ማግኘት”

“እኔም እንደ አንድ ልትድን እንደ ታደለች ነፍስ፣ የእርሱ ምስክር ሆነው የወንጌልን እውነት ሊያካፍሉኝ የወደዱት ወንድሞች፣ በሰፊው አማኝ ማኅበረ ሰብ መረዳት ‘ቤተ ክርስቲያን’ የሚሄዱና በዚያም በተለመደው መልኩ የሚያገለግሉ አልነበሩም፤ እንደውም “ዓለማዊ” ተብሎ የተፈረጀን ሙዚቃ በመጫወታቸው ምክንያት ከተቋማዊው ኅብረት የተገለሉ ነበሩ። እነኚህ ወንድሞች በርግጥ ዓለማዊ ሙዚቃን ተጫውተዋል፤ ከቤተ ክርስቲያን ርቀው በነበሩባቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታትም ፍጹም ዓለማዊ በሆነና ጠፉ በሚያስብል ዐይነት ሕይወት ዐልፈዋል። ሆኖም ግን፣ ለጥቂት ጊዜያት ተይዘውበት ከነበረው ክፉ አካሄድ ተላቅቀው፣ ራሳቸውን በቃሉ ጥናት እያተጕና እንደ ቃሉ ለመኖር፣ ብሎም ሌሎችንም ለመድረስ መለማመድን በጀመሩ ጊዜ፣ እንደ እኔ ላሉት መድረስ ችለው ነበር። ጌታን በእነርሱ በኩል ከማግኘቴ የተነሣ በቀጥታ የወረስሁት ወይም የተለማመድሁት የቤተ እምነት ሥርዐት ወይም ልማድ አልነበረም፤ ክርስትናንም የተረዳሁት ከአንድ የሃይማኖት ጎራ ከመመደብ በተለየ ነበር። በሕይወቴ የነበረው ለውጥ ከነበርሁበት የራስ ገዝ ሕይወትና አመለካከት፣ እግዚአብሔርን በቃሉ መሠረት ወደ መታዘዝ፣ እርሱን ወደ መምሰል ማደግና ወደ መሰጠት ሕይወት የመሻገር ነበር”።

እኔ

ሁላችንም ወደ ጌታ የመጣነው፣ በተለያየ መንገድ ነው። የጌታ አጠራር ልዩ ልዩ ነው። እግዚአብሔር በዚህ መንገድ ስላገኘሽ፣ ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን። ወደ ጌታ ለመምጣትሽ ምክንያት የሆኑ እነዚህ ሰዎች፣ “ከመጥፎ መንገዳቸው ተመልሰው”፣ በዘፈን ሙያ ውስጥ ያሉትን ወደ ክርስቶስ ለማምጣ ትልቅ ጥረት ማድረጋቸው፣ እጅግ የሚበረታታ ሠናይ ምግባር ነው። እግዚአብሔር ይባርካቸው!  

ይህ እንደዳለ ሆኖ ግን፣ ሌሎች በተመሳሳይ መንገድ ወደ ክርስቶስ ለማምጣት፣ እነዚህ ሰዎች በሙያው ውስጥ መቈየት አለባቸው፤ ወይም ውጤታቸው ጥሩ መሆኑ፣ ዘፈን ክርስቲያናዊ ድጋፍ እንዲያገኝ ያደርገዋል ለማለት ተፈልጎ ከሆነ[2]፣ ስሕተት ነው።  

ከረጅም ዓመት በፊት፣ መሠረታዊ የክርስትና ትምህርት አስተምረው የነበረ አንድ ወንድም፣ ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኙ ከተቀበለም በኋላ መጠጥ ቤት አዘወትሮ ይሄድ ነበር። ወደ መጠጥ ቤቱ የሚሄደው ጨለማን ተገን አድርጎ፣ ራሱን ደብቈ ቢሆንም፣ አንድ ሁለት፣ “ፉት!” ካለ በኋላ ግን፣ የዐንገቱን ጥምጣም፣ ጥቊር መነጽሩንና ኮፊያውን አውልቈ:— “ወገን አንድ ጊዜ እንደማመጥ! ለጥቂት ደቂቃ ጆሮአችሁን እንድትሰጡኝ እፈልጋለሁ፤ ዛሬ ለሁላችሁም የሚሆን ታላቅ የምሥራች አለኝ!”። በማለት ስለ ድነት መሠረታዊውን የክርስትና አስተምህሮ ይተነትናል። በየመጠጥ ቤቱ፣ በዚህ ሰው ምስክርነት ብዙዎች፣ ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኛቸው ተቀብለዋል። አንድ ታዋቂ የቤተ ክርስቲያናችን ዲያቆን ወደ ጌታ የመጣው፣ ይህ ወንድም፣ “እየቀመቀመ” ባስተላለፈው የድነት ወንጌል ነው። 

“የዚህን ሰው ምስክርነት ጌታ ተጠቅሞበታል ወይ?” ከተባለ መልሳችን፣ “እንዴታ!” ነው። ሰዎች ወደ ድነት ሲመጡ፣ በመላእክትም በሰውም ዘንድ ትልቅ ደስታና ፍሥሓ እንደሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ሉቃ. 15÷7:10፤ 7÷47፤ 2ቆሮ. 7 ÷10፤ ሕዝ. 18÷32)። የክርስቶስ ቤዞታዊ ሥራ የአምላክ ቀዳማይ አጀንዳ ከሆነ፣ ይህን የምሥራች ለሰዎች መናገር፣ እንዴት ታላቅ ነገር አይሆንም? እግዚአብሔር በዚህ ሰው ምስክርነት ብዙዎችን ወደ መንግሥቱ አፍልሶአል። ይህ አስደናቂ ድል ግን፣ ግለ ሰቡ ወደዚያ ቦታ እየሄደ፣ “መቀምቀሙን” ትክክል ያደርገዋል ማለት በጭራሽ አይደለም። ክርስቲያን መጠጥ መጠጣት አለበት ወይስ የለበትም የሚለው ጥያቄ፣ በራሱ አግባብ የሚዳኝ እንጂ፣ መጠጥ ቤት የተገኘው ውጤት ጥሩ መሆን፣ ግለ ሰቡ መጠጥ መጠጣቱን ሠናይ ግብር አያደርገውም። ሠናይ የሆነው ግለ ሰቡ የድነት ወንጌልን ለቀምቃሚዎቹ መናገሩ እንጂ፣ እርሱ በቅምቀማው ተግባር መሳተፉ አይደለም። ይህ ወሳኝ ነጥብ ስለ ሆነ፣ የተወሰኑ አስረጆችን በመጨመር፣ የፅንሰ ዐሳቡን ርቱዕነት (ትክክለኝነት) ላጐላምስ።   

የአንድ ምግባር ውጤት ትክክል ነው ማለት፣ ውጤቱ እንዲመጣ ምክንያት የሆነው ግብዐት ትክክል ነበር ማለት ላይሆን ይችላል። የውጤት ማማር ወደ ውጤት የተሄደበት መንገድ ትክክል መሆኑን አያመለክትምና[3]። ነገሩን እንዲያፍታታ ተጨማሪ አስረጆች እነሆ:— የውርጃ ደገፊዎች እናቲቱ ተገድዳ ስለ ተደፈረች፣ ሽሉ መጨንገፍ (ልጁ መገደል) አለበት ይላሉ። መደፈር ትክክል ስላልሆነ፣ በዚህ መንገድ የተገኘም ልጅ ትክክል አይደለም የሚል ዐስተሳሰብ የተከተለ ሙግት ነው። ይህ የትክክለኛ ሙግት አካሄድ አይደለም። አስገድዶ የደፈረ ግለ ሰብ፣ ሕግ የሚፈቅደውን ሁሉ ቅጣት መቀበል (መቀጣት) እንዳለበት እሙን ነው። ወንጀሉ ትልቅ ወንጀል ነውና። ነገር ግን፣ አባት ለሠራው ወንጀል ልጅ በሞት ይቀጣ ማለት፣ ፍርደ ገምድልነት ነው። አባት አስገድዶ ስለ ደፈረ፣ እንከን አልባ የሆነውን ልጅ ይገደል ማለት ስሕተት ነው። ልጁ የአባቱ የሥጋ ክፋይ ብቻ ሳይሆን፣ የእናቲቱም የዐጥንት ፍላጭ እንደ ሆነ ልብ ይሏል። ተገድዳ ለተደፈረችው እናት፣ መንግሥትም ሆነ ማኅበረ ሰቡ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ የሚባለውን ፍቅር፣ ርኅራኄና ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ይህም በእናቲቱ ላይ የደረሰውን በደልና የሥነ ልቡና ጫና፣ ቢያንስ በተወሰነ መጠን ያለዝበዋል። ስለዚህ አስገድዶ መድፈር እኲይ ተግባር መሆኑ፣ ሕፃኑ በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ፈጽሞአልና ይገደል፤ ወደሚለው ድምዳሜ በጭራሽ አያደርስም። የሙግት ነጥቦቹ ስለ ድምዳሜው አንዳችም ድጋፍ የላቸውምና።   

ሌላ ምሳሌ ላክል። ሂትለር አይሁዳውያንን ወደ ማጐርጊያ ስፍራ (concentration camp) ሲያስገባ፣ ሌሎች አይሁዳውያን ያሉበትን ስፍራ የጠቈመ ሰው፣ ሥቃዩ እንደሚቀልለት ተስፋ ይሰጠው እንደ ነበር ይነገራል። አንድ ሰው የራሱን ሥቃይ ለማቅለል፣ ሌላው ሰው ለሥቃይ እንዲሁም ለሞት ተላልፎ እንዲሰጥ መጠቈሙ ስሕተተ ነው። ምክንያቱም የውጤት ማማር (ጥቈማውን ላካሄደው ሰው)፣ ወደ ውጤት የተሄደበትን መንገድ ትክክል ያደርገዋል ማለት አይደለም።   

ይህ የውርጃ ወይም የናዚዎች ጒዳይ ብዙ ሊያወዛግበን ይችል ይሆናል። በእነዚህ ምሳሌዎች አማካይነት ሊተላለፍ የተፈለገው መልእክት ግን፣ የሚነቀስ የሚገሠሥ ምግባራዊ መርሖ መሆኑ ይታወቅ! ይኸውም:— “አንድ ግብር ውጤቱ ትክክል ነበር ማለት፣ ወደ ውጤቱ የተሄደበት መንገድ ትክክል ነበር ማለት አይደለም”።

            ስለዚህ አንቺ ዘፈን በሚዘፈንበት ቦታና ሁኔታ ዘላለማዊ ድነት ማግኘትሽ፣ “ዘፈን ትክክል ነው” ወደሚል ድምዳሜ ሊያደርስ አይችልም። ዘፈን ትክክል ከሆነ ወይም ስሕተተ ከሆነ፣ በራሱ ተመዝኖ ማለፍ ወይም በራሱ ተመርምሮ መውደቅ ይኖርበታል[4]። ስለዚህ በዚህ መንገድ ወደ ድነት መምጣትሽ፣ ከዘፈን ርእሰ ጒዳይ ጋር በአገርም በዘመድም ግጣም የለውም። 

ዘሪቱ

2. ሙዚቃ የሥጋ ሥራ ወይስ ብርሃንና ጨው የመሆን ዕድል?

ሙዚቃ በገላትያ መልእክት፣ “የመንፈስ ፍሬዎች” የተባሉትን እስካስገኘ ድረስ፣ “ሙዚቃዊ አገልግሎታችን የሥጋ ሥራ ሳይሆን፣ በዓለም ላይ ብርሃንና ጨው በመሆን የምንኖርበትን ኅብረተ ሰብ ከፍ ባለው ዕውቀትና ጥበብ የማነጽና የመገንባት ዕድልን የሚሰጠን መንፈሳዊ አገልግሎት እንደ ሆነ አምነን…”።

እኔ  

በዚህ ዐሳብ ላይ ሁለት መሠረታውያን ነጥቦችን ማንሣት እፈልጋለሁ: አንደኛ፤ በገላትያ መልእክት የተዘረዘሩት ዘጠኝ ፍሬዎች፣ እንደ መንፈስ ቅዱስ ዐሳብ በመመላለስ ገንዘብ የምናደርጋቸው ባሕርያት (moral virtues) ናቸው እንጂ፣ አንድ ተግባር ሥነ ምግባራዊ ደረጃውን ጠብቀን እንዴት ተግባራዊ እናድርገው የሚለውን መስፈርት የሚነግሩን ቀመሮች አይደሉም። ይህ ልብ ልንለው የሚገባ ትልቅ ቊም ነገር ነው። ለምሳሌ:— “ደስታ” ምግባራዊ ሕግ ነው ካልን፣ ያስደሰተን ነገር ሁሉ ትክክል ሊሆን ነው። “የሚያስደስቱ ነገሮች ሁሉ ትክክል ናቸው” ማለት፣ ስሕተት መሆኑ ቅቡል ነው። አንድ ሰው መጥፎ ነገር፣ “ማፍቀሩ”፣ (ለምሳሌ የተለያዩ ሱሶች)  በፍቅር የተካሄደ ስለ ሆነ፣ ትክክለኛ ምግባር ነው ወደሚል ድምዳሜ አያመጣም። ስለዚህ እነዚህን ፍሬዎች (moral virtues) ምግባራውያን ሕግጋት አድርገሽ በማቅረብ፣ ድርጊትሽን፣ “በመንፈስ ፍሬዎች” (ገላ. 5÷22-23) ለመመዘን መሞከርሽ፣ ከመነሻው ትክክል አይደለም። ከዚህ የተነሣ፣ “ሙዚቃ በገላትያ መልእክት፣ ‘የመንፈስ ፍሬዎች’ የተባሉትን እስካስገኘ ድረስ…መንፈሳዊ አገልግሎት” ነው የሚለው ድምዳሜሽ ስሕተተ ነው። ስለዚህ አንቺና ባልንጀሮችሽ እነዚህን “የመንፈስ ፍሬዎች”፣ ትክክልና ስሕተትን መለያ ቀመሮች አድርጋችሁ መጠቀማችሁ፣ ከመነሻው ስሕተት ነው። ለዘፈን ብቻ ሳይሆን፣ ለማንኛውም ምግባራዊ ግብር እነዚህን “የመንፈስ ፍሬዎች” መስፈርት አድርገሽ መጠቀም አትቺዪም። ቢያንስ ክርስቲያናዊው ሥነ ምግባር ይህን አይፈቅድም።   

ሁለተኛ፤ አንቺ እንዳልሽው ይዘታቸው ጥሩ የሆኑ ዘፈኖች እንዳሉ በእነዚህም ዘፈኖች ማኅበረ ሰብን ማነጽ እንደሚቻል፣ እኔ በግሌ አምናለሁ (“ጉባኤ ሙግት” መጽሐፍ ላይ ይህን ጒዳይ በግልጽ ተናግሬአለሁ)። ዐቢይ ጥያቄ ሆኖ የሚቀርበው፣ “‘ማኅበረ ሰቡን በምን መንገድ እናንጽ?’፣ የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ የሚወስነው ማን ነው?” የሚለው ነው። እያንዳንዱ ማኅበረ ሰብ ነገሮችን ተግብሮ የሚቀይርበት የራሱ ሆነ የአካሄድ ሥርዐት (ወግ፣ ባህል) አለው[5]። ስለዚህ ማኅበረ ሰቡን እንዴት ላንጽ የሚለውን ጒዳይ የሚወስነው ማኅበረ ሰቡ ራሱ እንጂ፣ እኛ (ማለትም “እናንጽ” ወይም “እናገልግል” የምንል ሰዎች አይደለንም)። ይህ ወሳኝ ነጥብ ነው። በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፣ ትክክለኛ በሆነም ይሁን ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ፣ ማኅበረ ሰባችን ዘፈንን እንደ ዓለማዊ ተግባር እንደሚመለከተው፣ እንቺው ራስሽ በጥሩ መንገድ ገልጸሽዋል:—

“ኢትዮጵያ ውስጥ ባለን አማኞች መካከል አንድ ሰው ወደ መንፈሳዊት ማዘንበሉን ወይም ከዓለማዊነት መላቀቁን ከሚገልጥባቸው ዋና ነገሮች መካከል፣ ዘፈን አለማድመጥ ወይም ሙዚቃ በሚቀርብባቸው ዝግጅቶች ላይ አለመታደም አንዱ ነው። ወደ እምነት የመጣው ሰው አስቀድሞ በሙዚቃ ሙያ ውስጥ የነበረ ከሆነ ደግሞ፣ ሙያውን ማውገዝና ከልምምዱ መውጣት የተለመደ ተግባር ነው።” 

እንግዲያው እውነታው ይህ ከሆነ፣ ሰውን የምናገለግለው፣ የምናገለግለውን ሰው ንቃተ ኅሊና በጠበቀ፣ ባህሉንና ወጉን በተከተለ መንገድ እንጂ፣ እኛ ትክክል ነው ብለን ባሰብነው መንገድ አይደለም። ክርስቲያኖች የአንድን ማኅበረ ሰብ ወግና ልማድ አልከተልም ማለት የሚችሉት፣ ጒዳዩ ከምግባራውያን ሕግጋት ጋር ሲቃረን ብቻ  ነው። ለምሳሌ:— አንድ ማኅበረ ሰብ የባሪያን ፍንገላ ትክክል የሚያደርግ ባህልና ወግ ቢኖረው፣ ይህ ባህል ልንቀበል አይገባም። እንዲያውም ከዚህ ተቃራኒውን አካሄድ በመሄድ፣ ምግባራዊ ኀላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል (በየአገሩ የታዩት ባህላዊ ተሐድሶች የዚህ ውጤት ናቸው)። ክርስቲያን የማኅበረ ሰቡን ንቃተ ኅሊና፣ ባህልና ወግ አልከተልም ማለት የሚኖርበት፣ ድርጊቱ ምግባራዊ ሕጸጽ ወይም ነገረ መለኮታዊ ስሕተት ሲኖርበት ብቻ ነው።

“‘ቤት ያጣው ቤተኛ’ የወር ተረኛው ርእሰ ጒዳይ” በሚለው ጽሑፍ ላይ ያነሣሁትን፣ “የፖፖ ምሳሌ” እዚህ ካመጣሁት፣ “ፖፖው ንጹሕ ነው” የሚለው ጒዳይ፣ “በፖፖ እህል እንብላ ወይስ አንብላ” የሚለውን ጥያቄ አይመልስም። ፖፖው ሺሕ ጊዜ ንጹሕ ሊሆን ይችላል፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ግን በፖፖ አንበላም። “ንጽሕና እንጂ ቅርጽ ለምግብ ማቅረቢያ በመስፈርትነት መዋል የለበትም” የሚል ተሟጋች ካለ በብዙ ተሳስቶአል። ሳሕንን ሳሕን የሚያደርገው፣ ፖፖንም ፖፖ የሚያደርገው ባህልና ልማድ ነውና። ስለዚህ በፖፖ የማንበላው ፖፖ ንጹሕ ስላልሆነ አይደለም፤ ባህላችን (አስተዳደጋችን) በፖፖ መመገብን ስለማይፈቅድ ብቻ ነው።

ማኅበረ ሰቡ ልማዱን ይተው ከተባለ፣ የትኛውም ማኅበረ ሰብ “በፍጥነት” ልማዱን ሊተው አይችልም (“አበው ልማድ ሲሠለጥን ቀኖና ይሆናል” የሚሉት በዚህ ምክንያት ይመስለኛል። የትኛውም ማኅበረ ሰብ፣ “ቀኖናውን” በፍጥነት ሊለቅ አይችልም)። እንግዲያው ማኅበረ ሰባችን ልማዱን “በፍጥነት” የማይተው ከሆነ፣ በአንጻሩ ደግሞ እኛ የምንወድደውን ነገር የማንለቅ ከሆነ፣ “በምን ሚዛን እንታረቅ?” የሚለው ጒዳይ ወሳኝ ይሆናል። በተለይ እንዲህ ባለው አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ፣ ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን እንዴት እንፈጽም የሚለው ጥያቄ የሙግታችን ማዕከል መሆን ይኖርበታል።  

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ እኛን ለማገልገል “ሥጋ ሆነ”፣ “ራሱን ያለ ልክ ዝቅ ዝቅ አደረገ” ይለናል (ዮሐ. 1÷14፤ ፊልጵ. 2÷7)። ይህ የጌታ አካሄድ፣ ለማገልገል ወደ ተገልጋዩ “ዝቅታ”፣ “ያለ ልክ” መውረድ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን የሚያስተምር ነው[6]። ማኅበረ ሰቡን እናገልግልህ ብለን፣ በአንጻሩ ወደ ማኅበረ ሰቡ መንደር (ባህል) አንወርድም ብለን እንዴት ይሆናል? አገልጋይ ወደ ተገልጋዩ ሕዝብ፣ “ይወርዳል” እንጂ፣ ተገልጋዩ ሕዝብ ወደ አገልጋዩ ምጥቀት ሊወጣ አይችልም።

እናቴ የተማረች ሴት አይደለችም። እኔ ከእናቴ ጋር ሳወራ በእርሷ ልክ “ዝቅ” ማለት ይጠበቅብኛል፤ እርሷ በእኔ ልክ “ልትመጥቅ” አትችልምና። እኔ የእርሷን እረዳለሁ፤ እርሷ ግን የእኔን ክልል ልትረዳው አትችልም። እኔ፣ “መውረድ” እችላለሁ፤ እርሷ ግን በእኔ ልክ “ልትወጣ” ዐቅሟ አይፈቅድም። የክርስቶስ አገልጋይ የራሱን ፈቃድ (ፍላጎት፣ ምቾት) ለክርስቶስ ወንጌል ሲል መተው ይኖርበታል። ምናልባት፣ “ማገልገል” በሚለው ቃል ውስጥ “ግልገል” የሚለው ቃል የተቀየጠው፣ አገልጋይ ራሱን ታናሽ አድርጎ ማቅረብ እንዳለበት ለማሳየት ሊሆን ይችላል።

ቲም ብራኒገን (Tim Brannigan) የተባለ አንድ መምህር፣ ሚስዮናዊ ሆኖ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት፣ ለተወሰኑ ዓመታት በምዕራብ አፍሪካዋ አገር ላይቤሪያ አገልግሎአል። ብዙ ጊዜ ቤታቸው እየሄደ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምራቸው አንድ ቤተ ሰብ፣ ቲም ቤታቸው መጥቶ ራት እንዲበላ ግብዣ አቀረበለት። ላይቤሪያውያን አንድን ሰው እቤታቸው ለራት የሚጋብዙት፣ ለግለ ሰቡ ትልቅ አክብሮት ሲኖራቸው ብቻ አይደለም፤ ተጋባዡ ግለ ሰብ የቤተ ሰቡ አባል እንዲሆን፣ “የቅልቅል ግብዣ ማቅረቢያ” ሥርዐት ጭምር ነው። በራት ግብዣው ላይ ያለመገኘት ወይም የቀረበን ምግብ አለመመገብ ደግሞ፣ የቅልቅሉን ግብዣ አልቀበልም ማለት ነው።

ቤተ ሰቡ ይህን ትልቅ ክብር ስላጐናጸፈው፣ ቲም ወደ ወዳጆቹ ቤት የሄደው በትልቅ አክብሮት ነበር። አባወራው ቅቅሉን በጐድጓዳ ሣሕን እየጨለፈ፣ “እንካ ይህ ወደዚህ ቤት በምትመጣበት ጊዜ ሁሉ፣ ከመኪና ይቀበልህ የነበረው የነጩ ውሻ ሥጋ ነው። ለአንተ ትልቅ አክብሮት ስላለን፣ የቤተ ሰቡን ተወዳጅ ውሻ ዐርደንልሃል” ይለዋል። ቲም በብዙ እንደ ደነገጠ ይናገራል። ነገር ግን የውሻውን ሥጋ አለመብላት፣ ሾርባውን አለመጠጣት፣ “ከዚህ ቤተ ሰብ ጋር እስከ ወዲያኛው እንደሚያቈራርጠኝ፣ ምናልባትም ከተቀበሉት ወንጌል ለማፈግፈግ ምክንያት እንደሚሆን ስላሰብሁ፣ እየዘገነነኝ ምግቡን በልቼ ሄድሁ” ይላል።

አንድን ማኅበረ ሰብ የምናገለግለው የማኅበረ ሰቡን ባህል ተከትለን፣ ወጉን አክብረንለት ነው። ባህልና ወገን ወግድ ማለት የምንችለው፣ ምግባሩ ከክርስቲያዊ አስተምህሮ ወይም ሥነ ምግባር ጋር ሲቃረን ብቻ ነው።  

ዘሪቱ 

3. የሆኑቱ የማይገባ ዘፋኝነት

“በዐጭሩ በሚያግባባን ቋንቋ ለመግለጽ፣ እኔ አሁን ዘፋኝ አይደለሁም። ስለ ዘፈን ለመጻፍ የተገደድሁት፣ እኔና እኔን መሰል ሙዚቀኞች ‘መብታችን ነው’ ባልነው መንገድ ስንሄድ የሚመለከቱን ወጣቶች፣ ‘የኢየሱስም የሙዚቃም መሆን ይቻላል’ የምንልበትን ዐሳብ ወይም ልብ ሳይረዱ በተሳሳተ ጎዳና እንዳይሄዱ ለማድረግ ነው። እኛን ተመልክተው እንደ ቃሉ ሳይሆን ለተጠላውና የኢየሱስ ለሆኑቱ ለማይገባው ዘፋኝነት የተጋለጡ ቢኖሩ፣ እነርሱን ለመመለስና አካሄዳቸውን የማስተካከል ዕድል ለመስጠት ነው”።

እኔ

በዚህ ክፍል፣ ያልገባኝም ግራ ያጋባኝም ጒዳይ አለ። “የኢየሱስ ለሆኑቱ የሚገባው ዘፋኝነት” ስትዪ ምን ማለት ፈልገሽ ነው? የኢየሱስ የሆኑት የሚገባቸውና፣ “የማይገባቸው” ዘፋኝነት የቱ ነው? ማኅበረ ሰቡ ዘፈንን በጅምላ ወግድልኝ እንዳለ፣ አንቺም በጽሑፍሽ በጥሩ ሁኔታ አፍታትተሽ ነግረሽናል። ማኅበረ ሰቡ ዘፈንን በጅምላ አወገዘ እንጂ፣ “የሚገባ” እና “የማይገባ” የሚል መረጣ አላካሄደም። ዘፈን ተብሎ፣ “ለኢየሱስ ለሆኑት የሚገባ” የሚባል የዘፈን ዐይነት መኖሩን ክርስቲያኑ ማኅበረ ሰብ አያውቅም።

ምናልባት መልእክታቸው (ይዘታቸው) መልካም የሆኑ ዘፈኖችን ለማመልከት እንዲሁም ክርስቲያኖች ይህ ዐይነቱን ዘፈን እንዲዘፍኑ እያበረታታሽ ከሆነ፣ ልብ ልትዪው የሚገባ ነጥብ አለ። ይኸውም:— ማኅበረ ሰቡ ዘፈን በሚለው ማዕቀፍ ውስጥ፣ “ጥሩ” እና “መጥፎ” የሚል መለያ መሥመር የለውም። ማኅበረ ሰቡ ዘፈንን፣ “ጥሩ” እና “መጥፎ” ብሎ ያልከፋፈለ ከሆነ፣ “ጥሩ” እና “መጥፎ” የሚለው መሥመር (አደላደል) የአንቺው የራስሽ ብቻ እንጂ የማኅበረ ሰቡ አይደለም። ማኅበረ ሰቡ ዘፈንን በዚያ መንገድ አይመለከተውምና። ይህ ከሆነ ደግሞ፣ በዚህ አንጻር አንቺና ማኅበረ ሰቡ እየተግባባችሁ (እየተደማመጣችሁ) አይደለም ማለት ነው። ክርስቲያናዊ አገልግሎት፣ ለተገልጋዩ ሕዝብ መብትን አሳልፎ መስጠት (መብትን መተው) የግድ እንደሚል ከላይ ገልጫለሁ።  

በዘፈን ሙያ ውስጥ ሆነው ወደ ክርስቶስ የሚመጡ ሰዎች፣ ቤተ ክርስቲያን መላ ልትፈልግላቸው (ሸክማቸውን ዐብራ ልትሸከም) ይገባል የሚል ጽኑ እምነት እንዳለኝ ይታወቅ። በአንጻሩ ከዚህ ሙያ ወደ ክርስትና የሚመጡ ሰዎች፣ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር በመሆን የሚከፈሉት ዋጋ እንዳለ (የሚሸከሙት መስቀል እንዳለ) በግልጽ ሊነገራቸው ይገባል[7]።   

ዘሪቱ

4. አስተዋጽዖ ለማበርከት

“የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በተገቢው መንገድ ከመግለጽ ይልቅ፣ ከእግዚአብሔር በላይ ሰውን በመፍራትና ከተጠያቂነት ለመሸሽ ሲሉ፣ የብዙዎችን ጥያቄ በቸልተኝነት ሳያስተናግዱ በቀሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን፣ አገልጋዮችና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምክንያት የተሰናከሉ ታናናሾች ቢኖሩ አቋሜንና መረዳቴን በማካፈል በጎ አስተዋጽዖ ለማበርከት ነው”።

እኔ

በጐ አስተዋጽዖ ለማበርከት መፈለግሽን ወድጄዋለሁ፤ ከጌታ ደቀ መዛሙርት የሚጠበቅ ተግባር ነውና። በአንጻሩ፣ “የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በተገቢው መንገድ መግለጽ” ያለሽው ዐሳብ እውን መሆን የሚችለው፣ የማኅበረ ሰቡን ወግና ባህል ተከትለን፣ ሕዝባችንን ስናገለግል እንደ ሆነ ሊጠፋሽ አይገባም።

የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራንና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች፣ “ታናናሾችን”፣ “ማሰናከላቸው” ያሳዝናል። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን፣ እየተነጋገርንበት ያለውን የዘፈንን ጒዳይ አስመልክቶ፣ “እግዚአብሔርን መፍራት” እና “ሰውን መፍራት” የሚሉት ጒዳዩች እንዴት እንደሚብራሩ አልገባኝም። ሰውን ከመፍራት የተነሣ፣ ሕገ እግዚአብሔርን አፍርሰን ከሆነ ተሳስተናል። ያፈረስነውን ምግባራዊና አስተምህሮአዊ ሕግም መልሰን ልናንጽ ይገባል። ሰውን የፈራነው፣ ሰዎች ሕገ እግዚአብሔርን በተሳሳተ መንገድ እንዳይረዱት ከመፍራት የመነጨ ከሆነ፣ እያንዳንዱ ክርስቲያን ይህ ዐይነቱን ፍርሓት ሊፈራ ይገባል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህ ዐይነቱን ፍርሓት እንድንፈራ አስተምሮናል፣ “መብል ወንድሜን የሚያሰናክለው ከሆነ፣ ወንድሜን እንዳላሰናክለው ለዘላለም ከቶ ሥጋ አልበላም” (1ቆሮ. 8÷13)። ስለዚህ ሰውን በመፍራት ሕገ እግዚአብሔርን ልናፈርስ አይገባም። ሕገ እግዚአብሔር ጸንቶ እንዲኖር፣ ለሰዎች ኅሊና የተመቸ አገልግሎት ለማቅረብ፣ ለባህልና ለወግ መገዛት ተገቢ ነው፤ ክርስቲያናዊ ግዴታም ነው።

ዘሪቱ

5. “ዘፈን” ማለት ምን ማለት ነው?

“እነዚህ ሙዚቃዊ የጥበብ ሥራዎችና የታዳሚዎቹ የተሳትፎ ሁኔታ ከሚከናወንበት ቦታና ሁኔታ ባሻገር፣ የሚተላለፈው መልእክት ከእግዚአብሔር ቃል አንጻር በሰዎች አእምሮ ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ፣ እንዲሁም ስሜታቸው እንዲነሣሣ የሚያደርግበት አቅጣጫ ኀጢአት ነው ወይም አይደለም የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ እንደ ሆነ አምናለሁ”።

“ይሁን እንጂ፣ ከዚህ ሕዝብ መካከል እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሙዚቃ ተሰጥኦ ያላቸው ቢኖሩና ያንንም በጌታ ባመኑትም ሆነ፣ ባላመኑት ፊት ሊከውኑ እንደ ተሰጣቸው ተረድተው በታማኝነት ቢያገለግሉ፣ ሥራቸው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በዝማሬ የሚቀርብ አምልኮ ባለመሆኑ ዓለማዊ አይሆንም። የአገልግሎቱ ስያሜ ዘፈንም ይሁን መዝሙር፣ የሚቀርብበት መንፈስና የሚያነሣው ዐሳብ እግዚአብሔር የሚከብርበት ይሁን ወይም አይሁን የሚወስነው ይሆናል”።

“ስለ ጾታዊ ግንኙነት (ስለ ባልና ሚስት/እጮኛሞች ፍቅር) የተጻፈ ዘፈን ሁሉ ኀጢአት አይደለም። ጋብቻንና ጾታዊ ግንኙነትን በተመለከተ የሚቀርቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ መልእክቶችን፣ የጽሑፍ እንዲሁም የፊልምና የቴሌቪዥን ሥራዎችን እያጣጣመ ለመከታተል ምንም ዐይነት ክልከላ የማይታይበት ሕዝብ፣ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ሥራዎች በሙዚቃ ሲቀርቡለት ከኀጢአት አድርጎ የሚቈጥርበት መለኪያ ትልቅ ጥያቄን የሚፈጥር ሆኖ አገኘዋለሁ”።

“አንዲት ሴትና አንድ ወንድ በፍቅር ሕይወት ውስጥ ሲጓዙ፣ ግንኙነታቸውን የሚያጣፍጥ ገንቢነት ያላቸው የተለያዩ ነገሮችን ያደርጋሉ፤ ሙዚቃ በዚህ ውስጥ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፤ ይህንም በአማኙ ማኅበረ ሰብ ውሰጥ በቅርበት እንዳየሁት በስፋት ተጠቃሚ ያለው አገልግሎት ነው። ይህን ስመለከት ‘ሁሉም በየጓዳው የሚያደርገውን ነገር በአደባባይ እየወጣ የሚያወግዘው ማንን ፈርቶ ነው?’ እያልሁ እጠይቃለሁ። እግዚአብሔርን? በፍጹም። እግዚአብሔርን የምንፈራበት ጒዳይ የአደባባይ ብቻ ሳይሆን የጓዳ ሕይወታችንንም ያካትታል። አማኙ ከዚህ አንጻር ዘፈንን በየመድረኩና በየሰዉ ፊት የሚያስረግመው ግብዝነትና ዐድር ባይነት እንደ ሆነ ተገንዝቤአለሁ። ይህን ስል ፈጽሞ ዘፈን የማይሰሙና ከልባቸው ተገቢ እንዳልሆነ አምነው በወጥ ማንንነት የሚመላለሱ አማኞች የሉም ማለት እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፤ በርግጥም አሉና”።

እኔ

በመጀመሪያው ነጥብ ላይ፣ ዘፈንን ኀጢአት ነው ወይስ አይደለም የሚለውን መወሰኛ መስፈርቶች ዘርዝረሻል። ያሰፈርሻቸው መመዘኛዎች፣ ለእኔ ግልጽ አልሆኑልኝም። አንደኛ፤ “የጥበብ ሥራዎችና የታዳሚዎች የተሳትፎ ሁኔታ”፣ ሁለተኛ፤ “የሚከናወንበት ቦታና ሁኔታ”፣ ሦስተኛ፤ “የሚተላለፈው መልእክት ከእግዚአብሔር ቃል አንጻር በሰዎች አእምሮ ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ”፣ አራተኛ፤ “ስሜታቸው እንዲነሣሣ የሚያደርግበት አቅጣጫ ኀጢአት ነው ወይም አይደለም”። 

ይህን አስተያየት በአብዛኛው የሰጠሽው የምሽት ጭፈራ ቤቶችን ታሳቢ አድርገሽ እንደ ሆነ እገምታለሁ። ግምቴ ትክክል ከሆነ፣ “የጥበብ ሥራዎችን” እንዲሁም “የታዳሚዎችን ተሳትፎ” የሚወስነው ማነው? “መወሰን” የሚለው ቃል፣ የጭፈራውን እንዲሁም የዘፈኑን ዐይነት ከሆነ፣ ውሳኔን ለታዳሚው ምርጫ የሚያቀርቡ ጭፈራ ቤቶች አሉ እንዴ? ቦታ የዘፈንን “ይዘት” ለመወሰን እንዴት እንደሚያገለግል አልገባኝም። “በሰዎች አእምሮ ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ” የዘፈንን ይዘት ለመወሰን እንዴት ግልጋሎት ላይ እንደሚውልም አልገባኝም። በአእምሮ ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ እንዲሁም “ስሜታቸው እንዲነሣሣ የሚያደርግበት አቅጣጫ” ከሰው ሰው አይለያይምን? እነዚህ መስፈርቶች ለሰው ሁሉ የሚያገለግሉ ነባራውያን መስፈርቶች እንዴት ሊሆኑ እንደሚችሉ፣ ለእኔ ግልጽ አይደለም። ከእነዚህ መስፈርቶች ነባራዊ ሕግ ማዋቀር እንዴት ይቻላል? ነባራዊ ሕግ ማቈም የማይቻል ከሆነ ደግሞ፣ መስፈርቶቹ አንጻራዊ ስለ ሆኑ፣ ሁሉም ሰው ይቀበለው ልትዪ አትቺዪም። 

በሁለተኛው ነጥብ ላይ፣ “በታማኝነት ቢያገለግሉ…አምልኮ ባለመሆኑ ዓለማዊ አይሆንም” የሚለው መስፈርት ትክክል አልመሰለኝም። ምክንያቱም፣ “ታማኝነት” የሥነ መግባር መርሖ ሳይሆን፣ የሥነ ምግባር ፍሬ (moral virtu) ነው (ከላይ ያቀረብሁትን ማብራሪያ ያስተውሏል)። ስለዚህ የሥነ ምግባር መስፈርትን፣ ከሥነ ምግባር ፍሬ ጋር ቀላቅለሻል፤ ይህ ስሕተተ ነው።

ሦስተኛውን ነጥብ በተመለከተ፣ “ስለ ጾታዊ ግንኙነት (ስለ ባልና ሚስት/እጮኛሞች ፍቅር) የተጻፈ ዘፈን ሁሉ ኀጢአት አይደለም” በሚለው ገለጻ ውስጥ፣ “ሁሉ” የሚለው ቃል አንዳንዶች ኀጢአት እንደ ሆኑ ታሳቢ ያደረገ ይመስላል (“ሁሉ ኀጢአት ካልሆነ” ኀጢአት የሚሆን ዘፈን አለ የሚል እንድምታ አለው) እንግዲያው ኀጢአት የሆነውና ያልሆነው በምን መስፈርት ነው የሚለየው?

 ክርስቲያኑ ማኅበረ ሰብ ዘፈንን በዚህ መንገድ ይመለከተዋል ወይ? ካልሆነ ይህ መስፈርት አንቺ መሆን አለበት የምትዪውን እንጂ ሆኖ የተገኘውን (ማኅበረ ሰቡ ትክክል ነው ብሎ የሚያስበውን) የሚገልጽ አይደለም። ለዚህ ነው አንቺና ማኅበረ ሰቡ እየተደማመጣችሁ አይደለም የምለው። የማኅበረ ሰቡን ዐስተሳሰብ “ጥያቄ የሚፈጥር” እንደ ሆነ ገልጸሻል። ጥያቄ ሊፈጥር እንደሚችል እኔም እቀበላለሁ። ጥያቄ መፍጠሩ ግን፣ ‘ትክክል አይደለህም’ እንዲሁም ‘የእኔን ተቀበል’ ወይም ‘የአንተን አካሄድ አልከተልም’ እንድንል የሚያደርገን አይደለም። ለአእምሮ የሚመች ክርስቲያናዊ አገልግሎት ለመስጠት የምንፈልግ ሰዎች ከሆንን (ሮሜ 12÷1-2)።

የዘፈንን ምንነት ባብራራሽበት ቦታ ላይ የሚከተለውን ብለሻል:—

“‘ሁሉም በየጓዳው የሚያደርገውን ነገር በአደባባይ እየወጣ የሚያወግዘው ማንን ፈርቶ ነው?’ እያልሁ እጠይቃለሁ። እግዚአብሔርን? በፍጹም። እግዚአብሔርን የምንፈራበት ጒዳይ የአደባባይ ብቻ ሳይሆን የጓዳ ሕይወታችንንም ያካትታል። አማኙ ከዚህ አንጻር ዘፈንን በየመድረኩና በየሰዉ ፊት የሚያስረግመው ግብዝነትና ዐድር ባይነት እንደ ሆነ ተገንዝቤአለሁ”።

አንቺ እንዳልሽው፣ “ዐድር ባይነት” ሊሆን ይችል ይሆናል። ይህ ማለት ግን፣ መዝፈን አለብን የሚለውን ሙግትሽን ሊያጸና አይችልም። 

እኅት ዓለም እግዚአብሔር አትረፍርፎ እንዲባርክሽ ምኞቴም ጸሎቴም ነው!


[1] https://hintset.org/articles/about-zefen/ ዘሪቱ ከበደ፤ ስለ ዘፈን፤ ሐምሌ 18 ቀን፤ 2022 ዓ.ም (እንደ ጐርጐሮሳውያኑ አቈጣጠር)።

[2] “ከሆነ” በሚል የተዋቀረ፣ መላምታዊ ሙግት እንደ ሆነ ልብ ይሏል። እኅቴ ዘሪቱ ይህን ዐሳብ ያቀረበቸው ለምን እንደ ሆነ፣ በጽሑፏ ውስጥ በግልጽ አልነገረችንም። ምናልባት፣ “ውጤቱ ስላማረ መነሻው ትክክል ነው” የሚለውን ዐስተሳሰብ ለማጽናት ፈልጋ ከሆነ ግን፣ አካሄዷ ስሕተት መሆኑን የሚሞግት ነጥብ ነው። 

[3] ነባራዊ የሆነ ግብረገባዊ መስፈርት የለም የሚሉ አንጻራውያን፣ እንዲሁም የገቢራዊነትን ፍልስፍና (Pragmatism) የሚከተሉ ሰዎች፣ የአንድን ምግባር ሠናይነትንም ሆነ እኲይነትን የሚለኩት (በአብዛኛው) በውጤት ነው። ይህ ዐስተሳሰብ ስሕተት መሆኑን (“the end does not justify the means”) ለማሳየት፣ “ሥነ አመክንዮ” በሚለው መጽሐፌ ላይ ሰፊ ሙግት አቅርቤአለሁ (ገጽ 287-308 ያለውን ክፍል ይመለከቷል)።  

[4] መዝፈን ስሕተተ የሚሆነው በምን አግባብ እንደ ሆነ ከላይ በቀረቡት የተለያዩ ጽሑፈች ውስጥ፣ ሰፊ መጽሐፍ ቅዱሳዊና አመክንዮአዊ ሙግት ቀርቦበታል።

[5] ‘ባህል ተገላጭ (descriptive)፣ ሥነ ምግባር ገላጭ (prescriptive) የጥናት ዘርፍ ነው’ የሚባለው በዚህ ምክንያት ነው። ሥነ ምግባር ሰዎች ምን ማድረግ አለባቸው የሚለውን ጒዳይ የሚያጠና የትምህርት ዘርፍ ሲሆን፣ ባህል ደግሞ በአንድ አካባቢና ቦታ የሚኖሩ ሰዎች፣ ምግባራዊ ኀላፊነታቸውንና ተጠያቂነታቸውን እንዴት እውን ያደርጋሉ የሚለውን ጒዳይ ይተነትናል። ለዚህ ነው ባህል አንጻራዊ፣ ሥነ ምግባር ደግሞ ነባራዊ ነው የሚባለው።   

[6] በክርስቲያናዊ አገልግሎትና አስተምህሮ ውስጥ፣ ትሥጉታዊ አገልግሎት (incarnational ministry) የሚባለው ይህ ነው። 

[7] ለዚህ ድንቅ ዐሳብ፣ ወንድም ላዕከ ታፈሰን አመሰግናለሁ።

Share this article:

ለሚድን በሽታ የሚገድል መድኃኒት መውሰድ ይብቃ! (ደወል 3 ዘ ኢትዮጵያ)

“አንዱ በብሔሩ ዘረኛ ሲሆን፣ ሌላኛው በዜግነቱ ዘረኛ ይሆናል። አንዱ ብሔሩን ሲያስቀድም፣ ሌላኛው ዜግነቱን ያስቀድማል። አንዱ የብሔር ዘረኛ የራሱን ብሔር ለብቻው ሊያገንን ሲፈልግ፣ ለኢትዮጵያ ዐብሮነት መሠረት ውጋት ይሆናል። እንደዚሁም የዜግነት ዘረኛ ኢትዮጵያን ለብቻዋ እንድትገን ሲፈልግ፣ በጨለማ ላለ ጥቁር አፍሪካ ሕዝብ አንድነት ውጋት ይሆናል።

ተጨማሪ ያንብቡ

የአዲሱ ጅምር “አብዮት” ዕጣ ፈንታ

ምኒልክ አስፋው በዚህ ዘለግ ባለ ጽሑፉ በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ የሚፈለግበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ክርስቲያናዊ የሆነ ዕይታውን ያካፍላል። በዚህም በተለይ ብዙዎች የሚመኙት “ዴሞክራሲ” እውን እንዲሆን መሠረታውያን ያላቸውን መስፈርቶች ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ ጋር እያመሳከረ ምክረ ሐሳቡን ያካፍላል።

ተጨማሪ ያንብቡ

እግዜር እንግዳ ሆኖ ሲመጣ

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን በምናስብበት በዚህ ሰሞን፣ “እግዜር እንግዳ ሆኖ ሲመጣ” ሊኖረን ስለሚችልና ስለሚገባ ምላሽ የሚከተለውን ጽሑፍ ሰሎሞን ጥላሁን ያስነብበናል።

ተጨማሪ ያንብቡ

7 comments

Your email address will not be published. Required fields are marked *

  • እውነትን ለማወቅ ስለምፈልግ ትውልድ አስተማሪ በሆነ አቀራረብ የቀረበ ለእህታችን በቂ ግንዛቤ ይፈጥራል ብዬ አስባለሁ እግዚአብሔር ዘመናችሁ ይባረክ እንዲሁም ዶከተር ተስፋዬ ጭምር የዶክተር ተስፉ መጻሕፍትን ማንበብ በጣም ነው።

    • እግዚአብሔርን ስለ እርሶ እጅግ አመሰግናለሁ ፅሁፍዎን ሳነብ ብዙ ተምሬያለሁ ጠይቄያለሁ ጥልቅ ስለሆነው ሐሳብዎ እግዚአብሔርን ከማመስገን ውጭ ምንም ማለት አልችልም እግዚአብሔር ሁሌም ቅሬታዎች አሉት ለትውልድ ለአገር ።

  • እውነት ለመናገር ዶክተር ተስፋዬ ግሩም ጸሃፊ ቢሆንም ቅሉ በዚህ ጉዳይ ላይ ሃሳብ ለመስጠት የሚያስችል authorityም ሆነ exposure ያለው ሆኖ አልተሰማኝም፡፡ በሙሉ ጽሁፉ የታዘብኩት ተደጋጋሚ መሞገቻው ባህል እና ወግ ብቻ እና ብቻ እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ ክርስትና የሰፋ ልብ ፤ ኢየሱስን የሚሸት ቅንነት ፤ ሁሉን የሚያቅፍ ከባቢ ያለው ወደፊትም እንዲኖረው መስዋዕትነት የሚከፈልበት እንጂ በጊዜ ሂደት evolve ለሚያደርግ ወግና ባህል ሽንጣችንን ገትረን የምንከራከርለት ልማድ አይደለም፡፡ ስነ ጽሁፏን በማረም በደከምክበት ልክ ልቧን ለመረዳት ብትሞክር ምንኛ ደስ ባለኝ፡፡ ይህን የምለው ዘፈንን ደግፌ አይደለም ፤ if you noticed the big elephant in the room, እሷም ዘመኗን የደከመችለትን የ’ዘፈን’ መንገድ እየተወች ነበር ይህን ያለችው፡፡ ፊደል ይገድላል ፤ መንፈስ ግን ህይወትን ይሰጣል፡፡

  • God bless u dear God servant , this is what I expect from Hintset.org for this issue (Zefen) inviting scholars instead of ‘infant person like zeritu’

  • ዶክተር የሐሳቡን አገላለጽ መንገድ ባብዛኛው ወድጄዋለሁ ።
    ደሞ በአንዳንድ ጉዳዮች እንደገለፁት እሷ ለማለት የፈለገችውን በደንብ ያለተረዱም ይመስላል እርሶም እንደገለፁት ስለዚህም በድምጽ ወይ በአካል ተገናኝተው ቢነጋገሩ መንፈስቅዱስም እውነተኛውን መግባባት እንደሚሰጥ እርግጠኛ ነኝ ።
    በዛ ላይ ጥያቄም ፈጥሮብኛል ከላይ ያለዉ ማብራሪያ እነሱም…
    1,በፖፖው ምሳሌ ላይ አገላለፁ ልክ ሆኖ ሳለ ንጹ በሆነ ፖፖ መብላት ሚፈል ካለ ጉዳት እስከሌለበት ውሳኔውን ለምን ለዛ ሰው አንተውለትም ለምን እንወስንለታለን?2, ክርስትና majority rule minorities right እና ባህል ጉዳይ ባብዛኛው የማይሰራበት ብቸኛው ቦታ ይመስለኛል እና የፈሪሳውያን ነገር ምሳሌ ሊሆን ይችላል እና ህዝብ ህዝብ ሚለው አመላለስ አልገባኝም ?
    3,እኔ እንደምረዳው ክርስትና ከ ጊዜ ወደ ጊዜ እድገት ነው። ዘሪቱም የዛ ውጤት ነች እና እራሷን ለመንፈስ ቅዱስ ሰታ ከ ጊዜ ወደ ጊዜ እያደገች ያለች አህታችን ነች።ህይወቷን ወደ ኋላ ማየት በቂ ነው። ለምንድነው ቆይ የተለየ ሀሳብ ሲመጣ ቤተክርስቲያን ወይም መሪዎችዋ ከሩቁ ሚገጽጹት? ቀድመው እኛ ካልናቹ ውች ልክ እይደለም የሚባለው? መንፈስ ቅዱስ እኮ ለፈለገ ለሁሉም ተሰቷል ደሞም በሂደት ያስተምራል ያሳድጋልም ስለዚህ እንደ ፈሪሳውያን እንዳንሆን እንጠንቀቅ እላለው።
    ዘሪቱን እኔ ስረዳት ከነሙዚቃ ሚባል የጥበብ ስራ ከ አለም ወደ ክርስቶስ የመጣች እህታችን ነች በዛ ላይ ከኛ በላይ ስለሙዚቃ የምታውቅ ሙያዋ የሆነ እና ስለ ሙዚቃ (ሙያዋ) ትክክል መሆን አለመሆን ክርስቶስን እና መንፈስ ቅዱስን በተረዳች እና ባስረዷት መጠን በሂደት ተረድታ የምትለይ ሆኖ ሳለ እኛ የምንገመግምበት ምክንያ አለገባኝም ይልቁንስ በምንግባባው ክርስቶስ እየተከተልን መልስ ብንጠብቅ አይሻልም? እሷ ራሱ እኮ ኩነኔው በርትቶባት መሰለኝ ከርክሩዋ ።

  • እግዚአብሔርን ስለ እርሶ እጅግ አመሰግናለሁ ፅሁፍዎን ሳነብ ብዙ ተምሬያለሁ ጠይቄያለሁ ጥልቅ ስለሆነው ሐሳብዎ እግዚአብሔርን ከማመስገን ውጭ ምንም ማለት አልችልም እግዚአብሔር ሁሌም ቅሬታዎች አሉት ለትውልድ ለአገር ።

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.