[the_ad_group id=”107″]

ተኣምረ ማርያም፣ ገድላትና ድርሳናት ምን ይኹኑ?

ሰሞኑን በተለይ በተኣምረ ማርያምና በገድለ ተክለ ሃይማኖት ውስጥ የተጻፉና መጽሐፍ ቅዱስን የሚቃረኑ ትምህርቶች ያስነሡት አቧራ ቀላል አይደለም። አቧራውን ያጫጨሰው ደግሞ በመጻሕፍቱ ላይ ለቀረበው ትችት ከዚህም ከዚያም ወገን እየተሰነዘሩ ያሉ ተገቢነት ያላቸውም የሌላቸውም አስተያየቶች ናቸው። አንዳንድ ጳጳሳትና የቤተ ክርስቲያኒቱ መምህራን የሚሰጧቸው እጅግ የወረዱና ከአባቶች የማይጠበቁ ተራና ቃላተ ጽርፈትን የተሞሉ አስተያየቶች ስሜት የወለዳቸውና አስገራሚም ናቸው፤ ምክንያቱም አንዳንዶቹ ተናጋሪዎች በገድላትና ድርሳናት ላይ ያላቸው አመለካከትና አቋም ይታወቃልና። ኾኖም ስንናገር በዚህ መንገድ መኾን የለበትም ሲሉ የተደመጡ አባቶችም አሉ። በዋናነትም ፓትርያርኩ ይጠቀሳሉ።

ከተነሣው ከዚህ ጕዳይ የተወለዱ ጠቃሚ ሐሳቦችም ያሉ ይመስላል። አንዱና ዋናው ቤተ ክርቲያኒቱ በስሟ በየመንደሩ በተከፈቱ ማተሚያ ቤቶች እየታተሙ የሚወጡትንና ቤተ ክርስቲያኒቱን የማይወክሉ ባለቻቸው መጻሕፍት ላይ፥ በሊቃውንት ጉባኤ በኩል የማጣራትና ገድላትና ድርሳናትን የማረምና የማስተካከል ሥራ እንደሚሠራ መነገሩ ነው። ነገር ግን ዮናታን ያነበባቸው መጻሕፍት በተለይ ተኣምረ ማርያምና ገድለ ተክለ ሃይማኖት በየመንደሩ የታተሙ ሳይኾኑ፥ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቅና የተሰጣቸውና በትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የታተሙ ናቸውና፥ ስሕተቱን ሌሎች እንደ ፈጸሟቸው አስመስሎ ማቅረብ የራስን ስሕተት ለመሸፈን ካልኾነ በቀር እውነትነት የለውም። 

አንዳንድ አባቶች ደግሞ ርእሰ ጕዳዩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዘንድ ከቀሰቀሰው ቍጣ ባሻገር፥ ጕዳዩ መነሣቱ እንድንነቃና ራሳችንን እንድንመለከት አድርጎናል የሚል መልክ ያለው አስተያየት ሲሰጡ ተደምጠዋል። ሌሎች ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ ቆመው ገድላትና ድርሳናት ምንም ስሕተት እንደሌለባቸውና ስም አጥፊዎች አለአግባብ እንደ ተሣለቁባቸው፥ ስለዚህ መሻሻል እና/ወይም መታረም ሳያስፈልጋቸው መቀጠል እንደሚችሉ የሚያሳይ አቋም ያዘለ ማብራሪያ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቴሌቪዥን ጭምር ቀርበው እየተናገሩ ነው። እንዲህ ሲያደርጉም መጽሐፍ ቅዱስን ባልተነገረበትና ባልተጻፈበት ዐውድ ጭምር እንዳሻቸው እየጠቀሱ ገድልን ከሐዋርያት ሥራ ጋር እስከ ማነጻጸር ደርሰው፥ ጥቅሶችን ባልተነገሩበት ዐውድም በመተርጐም ሲያደናግሩና ሲያምታቱ አስተውለናል።  

አንድ ሐቅ አለ። መጽሐፍ ቅዱስ ታትሞ በብዙዎች እጅ ከመግባቱና ብዙዎች አንብበው ሕይወታቸው መለወጥ ከመጀመሩ በፊት፥ በየሰዉ እጅ ይገኙ የነበሩት፣ ሰዉም የተማረውና የተሰበከው ከገድላትና ከድርሳናት ነው። በአብዛኛው ኦርቶዶክሳዊ ሕይወት ውስጥ የተሰበኩና ከአብዛኛው ሕዝብ ሕይወት ጋር የተዋሐዱትም እነርሱው ናቸው። በተለይም ፊደል ያልቈጠረውና የቈጠረውም ጭምር፥ በገጠርም በከተማም የሚኖረው ሕዝብ ለመጽሐፍ ቅዱስ እንግዳ ለገድላትና ለድርሳናት ወይም ለትምህርቶቻቸው ደግሞ ቅርብ ነው። የሚኖረውም ከእነርሱ እንደ ተሰበከውና እንደ ተማረው፥ በዋናነትም በቅዱሳን ስም ልዩ ልዩ ተግባራትን በመፈጸምና በቅዱሳኑ ስም በመማጸን መዳን አገኛለኹ ብሎ ነው። ከኹሉም በላይ ደግሞ እነዚህ መጻሕፍት በየቀኑ በቤተ ክርስቲያንና በግለ ሰቦችም ሥርዐተ አምልኮ የሚፈጸምባቸው የሥርዐተ አምልኮ ክፍል ናቸውና ከዚህ አንጻር ገድላትንና ድርሳናትን ማረም ቀላል ሥራ አይደለም። ይህን ኹሉ የሚንድ ስለ ኾነ፥ በወሬ ካልቀረ በቀር ሊደረግ የሚችለው ጥገናዊ ማሻሻያና ነቀፌታን ሊያስወግድ በሚችል መልኩ የማስተካከል ሥራ እንደሚኾን ይጠበቃል።

ገድላትን የማረም ሥራ የሚሠራ ከኾነ እነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት አለባቸው፦

የቀደሙ ድርሰቶችን (የአንዱን ድርሰት ሌላው) ማረም ምን ያኽል መብት ነው? ምን ያኽልስ ተገቢ ነው? 

እንዲህ ያለ ተመክሮስ አለ ወይ? ደራሲዎቻቸው በወደዱት መንገድ የጻፏቸው ስለ ኾነ የአንድን ሰው ድርሰት ወይም የፈጠራ ሥራ መሔስ እንጂ ማረም እንዴት ይቻላል? ማረም ካለበትም ደራሲው ነው እንጂ ሌላው ሰው መኾን አለበት ወይ? 

ከእምነት አንጻር ሊወሰድ የታሰበው ርምጃ ሥነ ጽሑፋዊና ታሪካዊ ሀብትነታቸውን አያጠፋም ወይ? 

ከዚህ ይልቅ ከክርስትና ትምህርትና ሥርዐት ውጪ ተደርገው ከቤተ ክርስቲያን ወደ ሙዚየም ቢዛወሩና ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ ሰዎች አገልግሎት ቢሰጡ አይሻልም ወይ? ደግሞስ ገድላትንና ድርሳናትን ማስተካከል እና/ወይም ማረም ያስፈለገው ለምንድን ነው?  

ገድላትንና ድርሳናትን እናስተካክላለን የተባለው፥ መጻሕፍቱ በዋናነት ከታሪክና ከሥነ ጽሑፍ ቅርስነት ይልቅ፥ የሃይማኖት አካል ኾነው እንዲቀጥሉ ከመፈለግ የመነጨ ነው። ይህ ከችግሩ አዙሪት የሚያወጣ አይደለም። ስለዚህ በእኔ እምነት ተኣምረ ማርያምን፣ ገድላትንና ድርሳናትን ከማስተካከል እና/ወይም ከማረም ይልቅ፥ ፕሮፌሰር ጌታቸው እንደ ሰጡት ምክረ ሐሳብ 1 እነርሱን ከእምነትነት ወደ ታሪክነት ማሻገሩ የተሻለ ነው። ይህም በአንድ ጊዜ ሳይኾን በቂ ጥናትና ዝግጅት አድርጎ ሊወሰድ የሚገባው ርምጃ መኾን አለበት። አሊያ ይደረጋል የተባለው ማስተካከያ እና/ወይም ዕርማት የድርሰቶቹን ሥነ ጽሑፋዊ ቅርስነትና ታሪካዊነት ያበላሻል። ጥገናዊ እንጂ ሥር ነቀል ለውጥም አያመጣም። ለጊዜው ነቀፌታን ሊያስወግድ ቢችል እንኳ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር በረቀቀ መንገድ መጋጨቱ አይቀርም።

[1] https://t.me/agiztefera/413

Share this article:

ሚሲዮናዊ ተልእኮ ባ’ገር ልጅ

በወንጌላውያን የሚሲዮን ታሪክ ፋና ወጊ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው በዐፄ ፋሲል ዘመነ መንግሥት (1625 – 1660 ዓ.ም.) እንደ መጣ የሚታመነው ጀርመናዊው ፒተር ሄይሊንግ ነው። ፒተር በኢትዮጵያ ቆይቶ በ1644 አካባቢ ወደ አገሩ ለመመለስ በመንገድ ሳለ፣ ቱርኮች አግኝተው እስልምናን እንዲቀበል ቢያስገድዱትም አሻፈረኝ በማለት አንገቱን ቀልተው ገደሉት። ይህ ሚሲዮናዊ በኢትዮጵያ ሳለ የአማርኛ ቋንቋን አቀላጥፎ መናገር ችሎ የነበረ ሲሆን፣ የዮሐንስ ወንጌልን ወደ አማርኛ በመመለስ ለሕዝቡ እንዳበረከተ ታሪክ ዘግቦታል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ወርኀ ጽጌ ወስደት

“ወርኀ ጽጌ ወስደት” የተሰኘው ይህ ጽሑፍ፣ በወንጌላውያኑ ዘንድ ብዙ ትኩረት ስለማይሰጠውና ጌታ ኢየሱስ በሕጻንነቱ ወራት ከእናቱ ማርያምና ከዮሴፍ ጋር ወደ ግብፅ የተሰደደበትን ታሪክ መነሻ በማድረግ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ ሁነቱ ያለውን ትርክት ያስቃኛል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ሰባዎቹ የጆናታን ኤድዋርድስ ቁርጠኛ ውሳኔዎች:- (The 70 Resolutions of Jonathan Edwards)

በዐሥራ ስምንተኛ ክፍለ ዘመን፣ በምድረ አሜሪካ ለተነሣው መንፈሳዊ መነቃቃት ግንባር ቀደም አስተዋጽዖ እንዳደረገ የሚነገርለት ጆናታን ኤድዋርድስ፣ በግል ሕይወቱ ለመተግበር የቆረጠባቸውን ውሳኔዎቹን አማረ ታቦር፣ “ሰባዎቹ የጆናታን ኤድዋርድስ ቁርጠኛ ውሳኔዎች” በሚል ወደ አማርኛ የመለሰው እንደሚከተለው ቀርቧል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.