[the_ad_group id=”107″]

ይህ ደብዳቤ ለኦሮቶዶክሳውያን አባቶቼ ይድረስልኝ

አስቀድሞ የከበረ ሰላምታዬን አቀርባለሁ።

ዛሬ ሌላ ቤት ብገኝም ከየት እንደ ተገኘሁ የረሳሁ አይደለሁም። በክርስትና ስሜ ተጠርቼም የድቁና አገልግሎትም ሰጥቼ አላውቅም። ሆኖም፣ በልጅነቴ አቡነ መርቆሪዎስ (የጵጵስና ስማቸውን ዘንግቼ ሊሆን ይችላል?) ሲያደቁኑኝ ራሴ ላይ ‘እፍ’ ያሉብኝ እስከ ዛሬ ይሰማኛል። በመሆኑም ሊሆን ይችላል፣ በሌላ ቤት ብገኝም ፈጽሞ እንደ ተቆራረጠ ሰው ራሴን የማላየው።

አሁን ባለሁበት ቤት፣ ወንድምና እኅት እንጂ ‘አባት’ ባናውቅም፣ የጥንቱን እያስታወስሁ የእኔም አባቶች እንደ ሆናችሁ ባስብ ስሕተት ተደርጎ እንዳማይቈጠርብኝ አምናለሁ። ስለዚህ፣ “አባቶቼ” ለማለት አይከብደኝም። ለዚህ ነው ይህን ስጽፍ “ለአባቶቼ” በማለት የጀመርሁት። የግሌ ደብዳቤዬ ነው። ማንም አልወከለኝም።

ከሰሞኑ በሆነው ነገር ኦርቶዶክሳውያን የገጠማችሁን ሥጋትና እየተሰማችሁ ያለውን ስሜት የምረዳ ይመስለኛል፤ እንደ ራሴ (እንደ ራሳችን) ዐየዋለሁና።

ትዝ ይለኛል እኔ አባል ከሆንሁባት ቤተ ክርስቲያን፣ ሰዎች ከይሖዋ ምስክሮች (አርዮሳውያን) ወይም ኢየሱስ ብቻዎች (ሰባልዮሳውያን) ሲደባለቁ ወይም ነገር ዓለሙን ሲተውት፣ ወንድሞቼን እንደ ተነጠቅሁ/እንዳጣሁ ይሰማኝና ይቆጨኝ ነበር። እንዲመለሱም ለመርዳት በጊዜው ዐውቅ የነበረውን የክርክር መንገድ ሁሉ እጠቀም ነበር። ‘አሳቾች’ ያልኳቸው እነዚያን ወገኖች፣ የእኔን ወንድሞች ዒላማ ማድረጋቸውን አልወድደውም፤ ያስቆጡኝም ነበር።

ጴንጤቆስጤ አማኞች መኻልም፣ አንዱ ሌላውን ማግለሉንና ለዱላ እስከ መጋበዝ ይደረስ እንደ ነበር መመልከቴ የሩቅ ትዝታ ሆኖ አይታየኝም። ስለዚህ እናንተ በተለይ በኤጲስ ቆጶሳዊ ሥርዐት ውስጥ እንደ መኖራችሁ መጠን፣ “ምዕመኖቻችሁን እያሳቱ ወይም ሃይማኖታችንን እያንቋሸሹ ነው” በምትሏቸው ላይ ቁጣችሁ ቢበረታ እረዳችኋለሁ።

ተንኳሽ ድምፅ ከመንግሥት ጋር በተጠጋጉ ሰዎቾቻችን ሲነገር ስሜታችሁን እጅጉን እንደሚነካው ከሰሞኑ ተምሬአለሁ። ይህን ለመረዳትም የምቸገር አይመስለኝም፤ ምክንያቱም እናንተ ከመንግሥት ጋር ተቀራርባችኋል ባልንበት ጊዜ አበጅታችኋል የሚል ስሜት አልተሰማንም ነበርና።

“ ‘ለእምነታችን መከራ እንቀበላለን!’ብላችሁ ከፍ ባለ ድምፅ የምትናገሩት በአመዛኙ ከእኛ ጋር እስጥ አገባ ውስጥ ስትገቡ ነው። ከሌሎች ጋር ሲሆን ይህን ዐይነት ባሕርይ አታሳዩም። ይህ ደግሞ ተለይተን እንደ ተጠቃንና እንደ ተደፈርን እንዲሰማን ያደርጋል” ማለትን ከአንዳንዶች ሰምቼአለሁ። ነገሩ እውነት ነው ወይም ሐሰት ነው የሚለውን አሁን እንተወው። ሆኖም ግን፣ ወሳኙ ዕይታው ነውና ከዚህ ዕይታችሁ የተነሣ ብትበሳጩ እውነት አላችሁ። ስለሆነም የማልገነዘባችሁ አይደለሁም።

ተንኳሽ ድምፅ ከመንግሥት ጋር በተጠጋጉ ሰዎቾቻችን ሲነገር ስሜታችሁን እጅጉን እንደሚነካው ከሰሞኑ ተምሬአለሁ። ይህን ለመረዳትም የምቸገር አይመስለኝም፤ ምክንያቱም እናንተ ከመንግሥት ጋር ተቀራርባችኋል ባልንበት ጊዜ አበጅታችኋል የሚል ስሜት አልተሰማንም ነበርና።

“ለእኛ ነፍስ የተለየ ኀላፊነት ያለባችሁ ይመስል በአብዛኛው ወንጌላችሁን የምትናገሩት ለእኛ ሰዎች ነው። ይህን የምታደርጉት ከሃይማኖታችን በዘለለ፣ አገሪቷን እንደ ሲሚንቶ አጣብቀን መያዛችንን ለመሸርሸርና ኀይላችንን ለማድከም/ስስ ለማድረግ) እንደ ሆነ እንጠረጥራለን” የሚሉም አጋጥመውኛል። እነዚህ በተለይ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በአገሪቷ ያደረገችው አስተዋጽዖ ከንቱ እንዳይቀር የሚቀኑ ወገኖች ይመስሉኛል።

እኛ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን (ፕሮቴስታንቶች) እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ በኢትዮጵያ የምንኮራና ለኢትዮጵያ የሚገድደን መሆኑን ለመመስከር እችላለሁ። አገራችንንና ወገናችንን መውደዳችንን የምንገልጥበት መንገድ የተለያየ ሊሆን ቢችልም፣ መውደዳችንን ግን ከወንጌላውያን ጋር በቈየሁበት ዘመን ሁሉ ያስተዋልሁት ነው። 

ሚሲዮናውያን አፍሪካን ቅኝ በማስገዛት ተከሳሽ እንደ ሆኑ የሚታወቅ ነው። ከሚሲዮናውያን ጋር በመዋላችን፣ አያይዛችሁን ሊሆን እንደሚችል ስለምረዳ በዚህ እጅግም አልተደነቅሁም። የዛሬዎቹና በኢትዮጵያ ያሉት ሚሲዮናውያን ያንን ያደርጉ እንደሆን የማውቅበት መንገድ ስለ ሌለ፣ የራሴን ምስከርነት መስጠት አልችልም። ሆኖም እኛ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን (ፕሮቴስታንቶች) እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ በኢትዮጵያ የምንኮራና ለኢትዮጵያ የሚገድደን መሆኑን ለመመስከር እችላለሁ። አገራችንንና ወገናችንን መውደዳችንን የምንገልጥበት መንገድ የተለያየ ሊሆን ቢችልም፣ መውደዳችንን ግን ከወንጌላውያን ጋር በቈየሁበት ዘመን ሁሉ ያስተዋልሁት ነው።

ከዚህ የተለየ የሚያደርግ ቢኖር በማንኛውም ኢትዮጵያዊ ማኅበረ ሰብ መካከል እንደሚገኘው እንጂ፣ የተለየ ነገር በእኛ ዘንድ ኖሮ አይመስለኝም። ደግሞ አብዛኞቻችን ከእናንተ መኻል የወጣን መሆናችንን አትዘንጉ፤ እኛም አንዘነጋውም። ከእናንተ ለአገርና ለወገን የመቆርቆርን ነገር አልወረስንም ለማለትም አያስደፍርም።

እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ ጕዳዮች እያወጣችሁና እያወረዳችሁ ዕረፍት ሊነሧችሁ እንደሚችሉ እገምታለሁ። ነገር ግን፣ የስሜታችሁ መጎዳት አካሄዳችሁን ወደ ኀይል ሥራ እንዳያደርሳችሁ ልጠይቃችሁ ደፈርሁ። በዚህ ጥቂት ድፍረቴ አትዘኑብኝ። ይህን የምጠይቀው በምሥራቅ አፍሪካና በአጠቃላይ በአፍሪካና በእስያ ክርስትና እንዳይኖር ለሚፈልጉ ወገኖች ወጥመድ ውስጥ እንዳንገባ ነው። “ማን ያሸንፋል?” አላልኩም።

ዛሬ ግን ቍጥራችን ከመብዛቱ የተነሣ፣ በመምረጥ ድምፃችን በመመካት የኀይል ሥራ ውስጥ እንዳንገባ አሳስባለሁ። የቍጥራችንን ብዛት ከጀርባችን የማን “ቡዳ ዐይን” እንደሚያይ አይታወቅምና፣ ይህን ልብ እንድንል አመለክታችኋለሁ።

በዚህ ሰሞን በየዩትዩቡና መገናኛ ሚዲያው ከካህናቱ፣ ከዲያቆናቱና ከመምህራኑ በኵል የስድብ ቃል ብዙ ይሰማል። ምዕመኖቻቸውን (በጎቻቸውን) ለመመገብና ለመጠበቅ ያለባቸውን ኀላፊነት እንዳይወጡ፣ ድምበር ታልፎ እንቅፋት እንደኖረባቸው ማየታቸው፣ ለስድቡ እንደዳረጋቸው ብረዳም፣ የሚባርክ ስለማይመስለኝ ያንንም እንዲያቀዘቅዙ ማበረታታቱ በጎ ነው እላለሁ።

ለራሴ ወንድሞችና እኅቶችም (ወንጌላውያን) ይህን እላለሁ። እንደ ቀድሞው ከሆነ የኀይል ሥራ ውስጥ የመግባት ፍላጎት (አፒታይት) እንደማይኖረን ዐውቃለሁ። ዛሬ ግን ቍጥራችን ከመብዛቱ የተነሣ፣ በመምረጥ ድምፃችን በመመካት የኀይል ሥራ ውስጥ እንዳንገባ አሳስባለሁ። የቍጥራችንን ብዛት ከጀርባችን የማን “ቡዳ ዐይን” እንደሚያይ አይታወቅምና፣ ይህን ልብ እንድንል አመለክታችኋለሁ። ከኦርቶዶክሳውያን የምንለይበትን በማስረዳቱ ላይ ብቻ ብናተኵርም ክፋቱ አልታይህ ብሎኛል። ለጊዜው ሳይሆን ለዘላቂው ክርስትና ከኦርቶዶክሳውያኑ ጋር የጋራ ኀላፊነት አለብን ብዬ አምናለሁ።

ከምሥራቃዊ አክብሮት ጋር
ለአባቶቼም ታናሽ ልጃችሁ፣ ለወንድሞቼም ታናሽ ወንድማችሁ
ባንቱ ገብረማርያም (ወልደ ሐና) ነኝ
ቸር ሰንብቱልኝ

Share this article:

አዙሪቱ ይገታ፤ ተልእኮው ይፈጸም!

ወንጌል የአንድን ማኅበረ ሰብ ዐውድ በመጠቀም ለማኅበረ ሰቡ አባላት መድረስ አለበት። በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚገኙ ሕዝቦች የራሳቸው የሆነ ባህል አላቸው። ባህል ደግሞ በራሱ ክፉ አይደለም።” የሚለው ይህ የናዖል በፈቃዱ ጽሑፍ፣ የሚሲዮን ተልእኮ በኢትዮጵያ በሚፈለገው ደረጃ እንዳይሄድ ከሚያደርጉ እክሎች አንዱ ስለ ሆነው የዐውዳዊነት ዕጦት እንዲህ ያስነብባል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ድምፃዊ ተፈራ ነጋሽ:- “ታንክ ቢመጣ ወደኋላ አልመለስም”

5 አልበሞች ለአድማጭ አድርሷል፤ ከእነ አረጋኸኝ ወራሽና ሌሎች ድምፃውያን ጋር የሠራቸው ስብስብ ሥራዎችም አሉት። “ደህና ሁኝ ልበልሽ በእንባ እየታጠብኩኝ”፣ “ምነው ቀዘቀዘ ፍቅራችን”፣ ከሥራዎቹ መካከል ጎልተው የሚጠቀሱት ናቸው። ሰሞኑን በታክሲ ሾፌርነት መታየቱ ተሰምቶ አነጋግረነዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ባህላዊ እምነቶች ያጠሉበት የአፍሪካ ክርስትና

ቤተ ክርስቲያን ከ2000 ዓመታት በላይ ባስቈጠረው ዕድሜ ዘመኗ፣ በተለያዩ ባህሎች እና ወጎች ውስጥ አልፋም እንኳ ቢሆን ታላቁን የክርስቶስን የማዳን መልእክት ይዛ ስለ መቀጠሏ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ ይህ ሲባል ግን በዘመናቱ መካከል ከዚህ መሠረታዊ መልእክት የተለየ ያስተላለፈችባቸው ጊዜያት የሉም ማለት አይደለም፡፡ ዛሬም እንኳ ስሑት የሆነ መልእክት የምታስተላልፍበት አጋጣሚ እንዳለ እናስተውላለን፡፡ (“ስሑት” የምንልበት ሚዛናችን መጽሐፍ ቅዱሳዊው ክርስትና መሆኑን እዚህ ላይ ጠቊሞ ማለፉ ተገቢ ይሆናል፡፡) ይህ ታላቁ መልእክት በንጽሕናው እንዳይተላለፍ እንቅፋት እየገጠማቸው ካሉ ሕዝቦች መካከል ደግሞ አፍሪካውያኑ ይገኙበታል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.