[the_ad_group id=”107″]

ፖለቲካችን ክርስቲያናዊ ዕሴቶችን ይሻል!

አገራችን ኢትዮጵያ በለውጥ ሂደት ላይ እንዳለች በብዙዎች ዘንድ መግባባት አለ። የተጀመረው ለውጥ የሚፈለገው ቦታ ላይ እንዲደርስ ሁሉንም የኅበረተ ሰብ ክፍል ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ አሁንም በብዙዎች ዘንድ እምነት አለ። የወንጌላውያን አማኞች የኅብረተ ሰቡ አካል እንደመሆናችን ለአገራችን ሰላም፣ ፍትሕ እንዲሁም ብልጽግና የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እስከ አሁን በነበረን አገራዊ ተሳትፎ ‘ብዙ ትኩረት አልሰጣችሁም’ ተብለን የምንወቀሰው እኛ ወንጌላውያን፣ ለዚህ ወቀሳ አዎንታዊ ምላሽ የምንሰጥበት ጊዜ ላይ እንዳለን ይሰማናል።

በአገር ግንባታ ውስጥ የሚኖረን ሚና ጠባብ ትርጉም ከሰጠነው “መንፈሳዊነት” ባሻገር፣ የሰውን ልጅ እኩልነት የሚያስጠበቅ፣ ፍትሕ ከተነፈጉ ጋር የሚያስወግን፣ ድምፅ ለሌላቸው ድምፅ መሆን የሚያስችል፣ ለአሸናፊዎች ከማጨብጨብ ባለፈ፣ ሲሳሳቱ ለመገሰጽ ድፍረት የምንይዝበት ሊሆን ይገባል። በዚህ መንገድም የምንሰብከውን ክርስትና ዋጋ ከፍ ወዳለ ደረጃ እናልቀዋለን።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድና እና በዙሪያቸው ያሉ አንዳንድ የመንግሥት ኀላፊዎች የወንጌላውያን ክርስትና እምነት ተከታዮች በመሆናቸው የእኛ ብቻ ለማድረግ የምንሯሯጠውን ትዝብት ውስጥ የሚከትት ሩጫ ጋብ አድርገን፣ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን የሰጣትን ሰውን በሙላቱና በማንነቱ የማገልገል ተልእኮ ከጣልንበት ማንሣት ይኖርብናል። በኅብረተ ሰቡ ውስጥ የበለጠ ፋይዳ ያለው ማኅበረ ሰብ ለመሆን ከእኛ ባለፈ ለሌሎች መኖር መጀመር አለብን። ክርስትና ስለ ራስ ብቻ የሚኖርበት ሃይማኖት አይደለም። እንደውም ክርስትና ለሌሎች መኖርን ነው የሚያዝዘው። ለድኾች፣ ለአቅመ ቢሶች፣ ፍትሕ ላጡና ለተገፉት መኖርን ይጠይቃል፣ ያበረታታል፣ ያዝዛል። ፍቅርን፣ ምሕረትንና ይቅርታን የሕይወታችን መርሕ እንድናደርግ ያስተምራል።

ምንም እንኳ የክርስትና ሃይማኖት በምድራችን ብዙ ሺህ ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም፣ ዕሴቶቹ በአማኒያኑም ሆነ ሕዝቡን በሚመሩት ዘንድ ምን ያህል ሠርጾ ገብቷል የሚለው ብዙ የሚያነጋግር ይሆናል። ‘የክርስትና ዕሴቶች ያየሉባት አገር መሥርተን ቢሆን ኖሮ፣ ይህ ሁሉ ግጭት፣ ቁርሾና መቆራቆስ የማንነታችን መገለጫ ለምን ሆነ?’ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለናል። በመሆኑም፣ ለፖለቲካችን ፈውስ ይሆን ዘንድ የክርስትና ዕሴቶች በሕዝባችን መካከል እንዲሠርጹ እኛ የክርስትና እምነት ተከታዮች ብዙ ሥራ ከፊታችን ይጠብቀናል። የክርስትናን ዕሴት ማሥረጽ ማለት ግን፣ የክርስትና ሃይማኖት በሌሎች ላይ መጫን ተደርጎ መወሰድ የለበትም! ሁለቱ የሚለያዩ ጉዳዮች ናቸው።

ሕንጸት ይህንን ዕትም፣ አገራችን ያለችበትን የለውጥ ሂደት ከግምት በመክተት ዝግጅታችንን በዚሁ ዐውድ ውስጥ እንዲሆን አድርጓል። በጸሐፊዎቻችን የቀረቡት ጽሑፎች አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ሐሳብ ለመፈንጠቅ የቀረቡ ናቸው። በዚህም ወንጌላውያን በአገራችን የለውጥ ሂደት ላይ ለሚደረገው ተዋስኦ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት አንድ መድረክ አድርገን እንወስደዋለን። ይህን መሰሉ መድረክና ተሳትፎም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት በዚሁ አጋጣሚ መጠቆም እንወድዳለን፤ ይህንን ለማድረግ የሚችሉ እጅግ ብዙ ሰዎች እንዳሉም እናምናለን።

ጋዜጠኛና አክቲቪስት እስክንድር ነጋ በመጨረሻ የእስር ቆይታው በልዩ መንገድ የተረዳውን የክርስትና ሕይወቱን እንዲያካፍለን አድርገናል። ምንም እንኳ እስክንድር የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ እንደ ሆነ ብናውቅም፣ የሕይወት ልምዱ በዋናነት ወንጌላዊውን ክርስትና ለሚከተለው የሕንጸት ተደራሲ የሚያስተላልፈው ትልቅ መልእክት እንዳለው እናምናለን። እስክንድር ነጋ በመጽሔታችን ላይ በመቅረብ ሐሳብና ልምዱን ለማካፈል ፈቃደኛ በመሆኑ አክብሮታችን የላቀ ነው። በአንባቢያን ስም ክብረት ይስጥልን ብለናል!

ኢየሱስ? ወይስ ሞት?

“በኢየሱስ የሆንን እኛ በሕይወት ነን፤ ማንም እርሱን በሕይወትነቱ ቢያውቀው በሕይወት ይኖራል። ሊያውቀው ባይወድድ ግን በሞት ይቀራል፤ መጨረሻውም ለዘላለም ከእግዚአብሔር የመለየት ቅጣት ይሆናል።” ዘሪቱ ከበደ

ተጨማሪ ያንብቡ

ፍትሕ ወይስ ምሕረት

ጸሐፊ፣ ተመራማሪ እና አስተማሪ የሆነው ምኒልክ አስፋው ከሚኖርበት አሜሪካ ሆኖ ስለ ፍትሕ እና ምሕርት/ይቅርታ ባዘጋጀው ጽሑፉ የዚህ ዕትም ዋና ርእሰ ጉዳይ ጸሐፊ ሆኖ ቀርቧል። ጽሑፉ በዋናነት ከፍትሕ እና ከምሕረት የትኛው የበለጠ ፋይዳ ያለው መሆኑን በመጠቆም የተሰናዳ ነው። ምኒልክ ለዚህ መነሻ የሚያደርገውም እውቁን የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩትን ሟቹ ኔልሰን ማንዴላን ነው። እንደ እርሱ እምነት ከሆነ የማንዴላ የዕርቅ መንገድ በቅራኔ ለተሞላ ኅብረተ ሰብ ዐይነተኛ ምሳሌ ነው። ትልቅነት የሚለካውም ይቅር በሚሉና ምሕረት በሚያደርጉ ሰዎች የሕይወት ፈለግ መሆኑንም ይሞግታል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.