[the_ad_group id=”107″]

ዛሬ ያልተመቸን ሕዝቦች

ብሔራዊ ስፓርት

ኢትዮጵያዊ ባህሎች ትዝታ እና ናፍቆት ይጎላባቸዋል። የትዝታ ቅኝት ከሌሎች የሙዚቃ ስልቶቻችን ይልቅ በእኛ በኢትዮጵያውያኑ መካከል ገንኖ የመውጣቱ ምስጢርም፣ የማኅበራዊ ሥነ ልቦናችን ውቅር ከትዝታ እና ከናፍቆት ጋር በብርቱ ከመሰናሰሉ ጋር ይያያዛል። ይህንኑ እውነታ የታዘቡት፣ ሜትር አርቲስት የዓለም ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ “የኢትዮጵያውያን የሙዚቃ ነፍስ ትዝታ ነው” ብለዋል ይባላል።1  ኢትዮጵያን አስመልከቶ በርካታ የፎቶግራፍ ኤግዚቢሽን በዓለም አቀፍ መድረኮች እየተዘዋወረች የምታቀርበው አርቲስት አይዳ መርሻም፣ “ትዝታ እና ናፍቆት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ስፓርታችን ነው” ትላለች።2 ነገሩ እኛ ኢትዮጵያውያን በትዝታ እና በናፍቆት ተክነንበታል፤ የሚደርስብንም የለም ለማለት ነው!

አገርን የሚመለከቱ ዜማዎቻችንም ሆኑ ስእሎቻችን ከነገ ይልቅ ትላንት ላይ ያተኮሩ መሆናቸው ስለ ማኅበራዊ ሥነ ልቦናችንም ሹክ የሚሉን ነገር አለ። በመካከላችን ያሉ የናፍቆት ልዩነቶች፣ ‘የትኛውን ትላንት እናንቆለጳጵስ?’ በሚለው እንጂ፣ ትላንት ሊወደስ እንደሚገባ ብዙ ክርክር የለም። ሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ ለውጥን መረዳት በሚል ማኅበራዊ ውቅራችንን የሚተነትን መጽሐፍ ያበረከተልን ዶ/ር መሐመድ ግርማ፣ ባህላችንን “የትዝታ እና የናፍቆት ባህል” (nostalgic culture) ሲል ይጠራዋል።3

የዚህ መጣጥፍ ዐላማ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ከዛሬ ይልቅ በትላንት ናፍቆትና ትዝታ መወሰዳችን ዛሬ ያልተመቸን ሕዝብ እንድንሆን ማድረጉን በማመልከት፣ ናፍቆት እና ትዝታ ለዛሬ ሥጋት ከመሆን ይልቅ፣ ‘አጣነው’ የምንለውን ነገር ለማግኘት የምንጠቀምበት ውስጣዊ ኀይል ሊሆን እንደሚችል ማሳየት ነው።

ምን ሊረባን?

ያደጉትን አገራት በመዘመን ለመድረስ ለምትጣጣር አገር፣ ‘ትላንትን ተመልካች የሆነ ትዝታና ናፍቆት ምን ይረባታል?’ ብለን እንጠይቅ። ለምን ግን ይህን ጥያቄ ማንሣት አስፈለገን? ምክንያቱ ግልጽ ነው። ትዝታ እና ናፍቆት በጥንቃቄ ካልተያዘ፣ በአምላክ ቸርነት የምንቀበለውን አዲሱን ቀን (ዛሬን) ሳንሠራበት ሊያስረጅብን ስለሚችል ነው። የዛሬ ሰዎች እንደመሆናችንም መጠን፣ ልንሠራበት በምንችለው ቀን (በዛሬ) ላይ ሊደርስ የሚችለው ማንኛውም ዐይነት አሉታዊ ተጽእኖ ከምንም በበለጠ ያሳስበናል።4 ዛሬ በትላንት ልምድ (experience) እና ምልከታ (insight) የሚጎለብትበት ዕድል ቢኖርም፣ በነገ አዎንታዊ ጥበቃ (expectation) የዛሬን ተግዳሮቶች ለማለፍ የሚያስችል ውስጣዊ ኀይል ሊያስገኝ ቢችልም፣ እንድንሠራበት የተሰጠን ቀን ዛሬ ብቻ መሆኑ የሁል ጊዜ ሀቅ ነው። ስለዚህም በመርሕ ደረጃ የዛሬን አስፈላጊነት የሚቀንስ ምንም ዐይነት ነገር ልንቀበል አይገባም። ይህ ደግሞ ትውስታ እና ትዝታን በዛሬ ውጤታማነት ላይ በሚያመጣው ተጽእኖ እንድንፈትሸው ያስገድደናል።

ትዝታ እና ናፍቆት በዛሬ ማኅበራዊ ግንኙነታችን ውስጥ የጤና እንዲሆን ከተፈለገ፣ የትላንትን በጎ ነገር በማንቆለጳጰስ ብቻ መወሰን የለበትም። በተለይ ደግሞ የምናቆለጳጵሰው ዘመን ከጦርነት እና ከዘመቻ ጋር ሲያያዝ እጅጉን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ትዝታ እና ናፍቆታችን፣ ትላንትን በሙሉ ቁመናው (ከራስ ፀጉር እስከ እግሩ ጥፍር) የሚመለከት እንጂ የሚመቸው ቦታ ላይ ብቻ አፍጥጦ፣ ሌላውን የአካል ክፍል መዘንጋት አይገባውም።

በዕለት ተዕለት ኑሯችን የጣእም ምርጫዎቻችን እንደመለያየታቻው መጠን፣ ‘ጀግና’ የምንላቸው ሰብእናዎች ቢለያዩ አያስገርምም፤ በራሱም ችግር አይደለም። የተለያዩ ጀግኖች ቢኖሩን ደግሞ ምንም አይደለ። ጀግኖቻችን ሰው እንደ መሆናቸው መጠን፣ በሠሩት ጥፋት ሌሎች ትምህርት እንዲወስዱ ለማድረግ በሰውነታቸው ብቻ እንዲታሰቡ ማድረግ፣ ክብራቸው እንደተነካ ተደርጎ መወሰድ አይኖርበትም። እኛ የመረጥነውን ትላንት ሌሎች ካልመረጡት፣ የእኛን ጀግኖች ሌላው ጀግና ካላደረጋቸው ‘ሰማይ ይደፋል’ ማለት አይበጅም።

ለማኅበራዊ ሕይወታችን የሚሻለው እና የሚያዋጣው መንገድ፣ የእኛን የትላንት ድል በተመለከትንበት መነፅር፣ በድሎቻችን ውስጥ የነበሩትን የእኛኑ ጥፋቶች ለማሰብ መፍቀድ የሚዛናዊነት መጀመሪያ ነው። ትላንት እንደ ባላንጣ ተያይተን በሌላችን ላይ ጨክነን ያጣጣምነውን ድል ዛሬ ላይ ከማግዘፋችን በፊት፣ ዛሬ ላይ ከእነዚህ ወገኖች ጋር ባላንጣናት ተሸሮ፣ ተዋድደን፣ ከበድን፣ ወልደን በአብሮነት እየኖርን መሆናችንን አንዘንጋ። ስለዚህም፣ የዛሬው አብሮነታችን ትላንት ውስጥ የነበረ ድልን ለማጣጣም ሲሻ፣ ትላንት ባላንጣ በሚል በሌሎች ላይ ያደረስነው በደል እና ግፍ የደረሰው በዛሬ ወዳጆቻችን ላይ መሆኑ አይጥፋን፤ በደሉ በግልጽነት እንዲነገርም እንፍቀድ። ስለ ጀግኖች እየተወራ በደላቸው መነሣቱ፣ ጀግኖቻችንን ለማሰይጠን ሳይሆን፣ በእውነት ላይ የተመሠረተ ዘላቂ እርቅ ለመፍጠር ስለሚረዳ ነው። በመወቃቀሱም አጥፊም፣ ተበዳይም አብረን ተላቅሰን የዛሬውን ግንኙነታቸንን ንፋስ እንደማያስገባው የአዞ ጥርስ እንድናደርገው ነው። አሊያማ ድል ድል እየሸሸተን የምናወጋው ትዝታ እና ትውስታ፣ ለጎረቤታችን ጆሮ የሚያስታውሰው የተወጋውን ጠባሳ ስለሚሆን፣ እርሱም በተረኛነት ስሜት እንዲያደባ ማዘጋጀቱ አይቀርም። ይህ ደግሞ ለማናችንም አይበጅም።

የትላንት ትዝታ እና ናፍቆት ዛሬ ከትላንት ጋር ምንም እንደማይገናኝ ካስመሰለ ልክ አይሆንም። ትላንትና ሲሰጠን፣ ዛሬ ደግሞ በማደግ ላይ የነበረ ጽንስ ነበር። በሌላ አነጋገር፣ ትላንት ዛሬ እንዲወለድ አድርጓል። ትላንት ከዛሬ ጋር ላለው ዝምድና እውቅና መስጠት እንዲሁም በትብብር ኀላፊነት መውሰድ መጀመራችንን ያሳያል። ‘የትላንት ትውልድ ለዛሬው ኀላፊነት አለው’ ስንል፣ ዛሬ ላይ ለሚታዩ ጉድለቶች ሁሉ ተጠያቂው እርሱ ነው በሚል ጣት ልንቀስርበት አይደለም። የዛሬው ትውልድ፣ በሚሠራበት ዛሬ ላይ የራሱ ምርጫ ስለ ነበረው፣ የዛሬው መልክ ሲሠራ አብሮ ሠራተኛ ነውና፣ ለዛሬው መልክ አብሮ ተጠያቂ ነው። እንዲህ ሲሆን፣ አንድ ትውልድ ከሌላው ትውልድ ጋር ያለውን ትሥሥር እና አብሮነት ማመን ይጀመራል። አሊያማ፣ ካለፈ ትውልድ ጋር ጣት እየተቃሰርን፣ ከትውልድ ትውልድ ሊተላለፍ የሚችለውን የከበረ ልምድ እየገፋን፣ ቀጥለንበት ልናሳድገው የምንችለውን የነገር ጅማሬ ሁሉ እያፈረስን፣ የሁል ጊዜ ጀማሪዎች በመሆን በሚቀጥለው ትውልድ እኛም ተረኛ ተወቃሽ እንሆናለን። ይህ አዙሪት እንዲያበቃ፣ ዛሬ የትላንት ቀጣይ መሆኑን ትዝታ እና ትውስታችን መገንዘብ አለበት።

የትላንት ትውስታ፣ የምንሠራበትን ዛሬን ፈጽሞ ማስረሳት የለበትም። በእኛ እጅ በሌለው ትላንት ውስጥ ገና ያለን ይመስል፣ በቁም ቅዠት ትዝታ እና ናፍቆታችን እያነሆለለ ከዛሬ ጋር ካፋታን ልንሠጋ ይገባል። የትላንት ትዝታ እና ትውስታ ከዛሬ እውነታ ጋር ሊያጋጥመን የሚያዘጋጀን እንጂ፣ ትጥቃችንን አስፈትቶ ባዶ እጃችንን የሚሰድደን ሊሆን አይገባም። ናፍቆት እና ትዝታችን ለራሳችን ያለንን አክብሮት (Self-esteem) እና ዋጋ (Self-worth) እያስታወሰ የሚያበረታን ምርኩዝ እንጂ፣ የዛሬ ባዶነታችንን እየሰበከ ይበልጡኑ የሚሰባብረን ሊሆን አይገባም። የትላንት ናፍቆት እና ትዝታ፣ ‘መልካሙ ነገር ሁሉ ትላንት ቀረ’ በሚል፣ ዛሬ ያሉንን ዕድሎች እና መልካም አጋጣሚዎች ፈጽሞ እንዳንመለከት እንዲሁም እንዳንጠቀምበት ካደረገ በብርቱ ይጎዳናል። ትላንት በዛሬው ጨለማ ላይ ብርሃን ፈንጣቂ መሆን አለበት። የትላንት ናፍቆት እና ትዝታ፣ ታሪክን እንደ መዝናኛ ብቻ እንድናየው ካደረገና ለዛሬው ሕይወት ፋይዳ እንዳይኖረው ካደረገ ኪሳራ ብቻ ይሆናል።


1. Ayele Bekerie, Ethiopic, an African writing system: its history and principles (The Red Sea Press, 1997), 126.

2. M. Neelika Jayawardane and Aida Muluneh, “Between Nostalgia and Future Dreaming.” Transition: An International Review 120 (2016): 116-13, 128.

3. Mohammed Girma, Understanding religion and social change in Ethiopia: Toward a hermeneutic of covenant (Springer, 2012), 184.

4. Sprengler, Christine. Screening nostalgia: Populuxe props and technicolor aesthetics in contemporary American film (Berghahn Books, 2009), 31

Share this article:

ጽዋ ሲሞላ

በአንዳንድ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም ሚኒስትሪ መሪዎችና አገልጋዮች ዙሪያ ያሉትን ድክመቶች አስመልከቶ ለየት ባለ ግልጽነትና ʻአሁንስ በዛʼ ብለው የተነሡ ይሆኑ? በሚያሰኙ ብዕሮች የተጻፉ የሚመስሉ ጠንከር ያሉ መልእክቶች በመጽሔቶች አማካይነት ብቅ ብቅ እያሉ ነው። ደስ ይላል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ወንድሞችና እኅቶች ተስማምተው በአንድነት ሲኖሩ እንዴት መልካም ነው!

የአንድና የብዙ ጉዳይ የዓለም አፈጣጠር ምሥጢር ነው። የአንድና የብዙ ሁኔታ የብዙ ጠቢባን፣ የብዙ ፈላስፋዎች ጥያቄ ነው። አንዳንዶቹ በአሐዳዊው ላይ ሌሎቹ ደግሞ በብዙው ላይ ያተኩራሉ። ሆኖም ብዝኃነትን ያለ ኅብረት፣ አንድነትን ያለብዝኃነት ማሰብ ይቻል ይሆን? ብዝኃነት ውበት የሚሆነው መቼ ይሆን? አንድነትስ አስደሳች የሚሆነው መቼ ይሆን? 

ተጨማሪ ያንብቡ

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ መንግሥትና ሕዝብ ልብ ልንል የሚገባቸው ነጥቦች

ይህ ጽሑፍ ከቀናት በፊት ለንባብ የቀረበ ሲሆን፣ ዐቢይ ትኩረቱም ማኅበራዊ ንክኪን መቀነስ ላይ ያተኩራል። ጽሑፉ አነስተኛ አርትዖት ተደርጎበት ለሕንጸት አንባቢያውን እንደሚከተለው ቀርቧል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.