[the_ad_group id=”107″]

የጌታ የሆኑትን ማሳደድ ራሱን ጌታን ማሳደድ ነው

ሰሞኑን በአርባ ምንጭ ለሃይማኖታቸው በመቅናት በወንጌል እውነት ያመኑትንና ጌታን ለማምለክ የተሰበሰቡትን ወንድሞችና እኅቶች የደበደቡትና የዘረፉት አዝማቹ ጳጳስና ዘማቾቹ ወጣቶች፣ በድርጊታቸው ሲኰሩና ትልቅ ገድል እንደ ፈጸሙ ሲናገሩ ሳይ፥ በሌላ በኩል የተደበደቡትና ሀብት ንብረታቸውን የተዘረፉት ደግሞ ስለ ጌታ በደረሰባቸው መከራ እጅግ ሲደሰቱና ሐሤት ሲያደርጉ ስመለከት ይህን ማለት ወደድሁ።

በእግዚአብሔር ዘንድ ክብር የሚያስገኘው ለሃይማኖት ሲሉ መግደል ሳይሆን ለወንጌል እውነት ሲሉ መሞት፥ ለሃይማኖት ሲሉ መደብደብ ሳይሆን፥ ስለ ወንጌል እውነት መደብደብ፥ ለሃይማኖት ሲሉ ማሳደድ ሳይሆን ስለ ወንጌል እውነት መሰደድ ነው። ጌታ ስለ እኔ ደብድቡ፤ ግደሉ፤ ዝረፉ አላለም፤ ስለ እኔ መከራ ትቀበላላችሁ፣ ትስደዳላችሁ፣ ክፉውን ሁሉ በውሸት ይናገሩባችኋል፣ ወዘተ. ነው ያለው። የምንሞትለት ጌታ እንጂ የምንገድልለት ጌታ የለንም።

ስለ ሃይማኖት የሚገድሉ፥ የሚደበድቡና የሚያሳድዱ ስለ ፈጸሙት ድርጊት የሚያበረታታ ክብርና ምስጋና የሚያሰጥ ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ መጥቀስ አይችሉም፤ የለማ!!! ባይሆን ይህን ድርጊታቸውን በመንቀፍ ወዮላችሁ የሚል ማስጠንቀቂያ ዐዘል ቃልና የሚጠብቃቸውን አስፈሪ ፍርድ የሚያመለክት ብዙ ቃል አለ። ለምሳሌ፦ “ስለ እርሱ ደግሞ መከራ ለምትቀበሉለት ለእግዚአብሔር መንግሥት የምትበቁ ሆናችሁ ትቈጠሩ ዘንድ፥ ይህ የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ ምልክት ነው። ጌታ ኢየሱስ ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፥ መከራን ለሚያሳዩአችሁ መከራን፥ መከራንም ለምትቀበሉ ከእኛ ጋር ዕረፍትን ብድራት አድርጎ እንዲመልስ በእግዚአብሔር ፊት በእርግጥ ጽድቅ ነውና። እግዚአብሔርን የማያውቁትን፥ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል።” ይላል (2ተሰ. 5፥8)።

ስለ ወንጌል የተገደሉ፥ የተደበደቡና የተሰደዱ ግን እጅግ በርካታ የሚያጽናና፥ የሚያበረታ፥ በመከራቸው ደስ እንዲሰኙ የሚያደርግ፥ በመከራቸው የክርስቶስ መከራ ተካፋይ በመሆናቸው ራሳቸውን እንደ ትልቅ ዕድለኛ እንዲቈጥሩ የሚያደርግ ሺሕ ቃል አላቸው። እጠቅሳለሁ፦ “ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤ ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፥ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ። ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ። ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጒዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል፤ ክርስቲያን እንደሚሆን ግን መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር።” (1ጴጥ. 4፥12-16)።
ለሃይማኖት ሲሉ የሚገድሉ፥ የሚደበድቡና የሚያሳድዱ ለዚህ ድርጊታቸው ከእግዚአብሔር ወገን ምሳሌ የሚሆናቸውን ቅዱስ ሰው አያገኙም። ስለዚህ ምሳሌዎቻቸው ነቢያትን፣ ራሱን ክርስቶስንና ሐዋርያትን ያሳደዱ አይሁድ፣ የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍት፣ ፈሪሳውያን፣ አላውያን ነገሥታት፣ ወዘተ. ናቸው። ስለ ወንጌል የሞቱ፣ የተደበደቡና የተሰደዱ ግን ምሳሌዎቻቸው ነቢያት፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሐዋርያት ሰማዕታት ናቸው።

ለሃይማኖት ሲሉ የሚገድሉ፥ የሚደበድቡና የሚያሳድዱ እግዚአብሔርን ያገለገሉ የሚመስላቸው ነገር ግን እግዚአብሔርን ያላወቁና ደስ የማያሰኙ ናቸው (ዮሐ. 16፥2-3)። “እነዚያም ጌታን ኢየሱስን ደግሞ ገደሉ ነቢያትንም እኛንም አሳደዱ፥ እግዚአብሔርንም ደስ አያሰኙም፥ ሰዎችንም ሁሉ ይቃወማሉ፥ ሁልጊዜ ኀጢአታቸውን ይፈጽሙ ዘንድ አሕዛብ እንዲድኑ እንዳንናገራቸው ይከለክሉናልና። ነገር ግን ቍጣው ወደ እነርሱ ፈጽሞ ደርሶአል።” (1ተሰ. 2፥15-16)።

ስለ ወንጌል የሞቱ፣ የተደበደቡና የተሰደዱ ግን ወንጌል እንዲህ ዐይነት የመስቀል መንገድ መሆኑን ቀድመው ያወቁና ስለ ስሙ መከራ ለመቀበል የተዘጋጁ የእምነት ዐርበኞች ናቸው። ስለዚህ “እናንተ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በይሁዳ የሚኖሩትን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን የእግዚአብሔርን ማኅበሮች የምትመስሉ ሆናችኋልና፤ እነርሱ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፥ እናንተ ደግሞ ያንን መከራ ከአገራችሁ ሰዎች ተቀብላችኋልና።” (1ተሰ. 2፥14) ደስ ይበላችሁ።

በመጨረሻ ማሳደድን ማንገላታትን መደብደብን እንደ መንፈሳዊ አገልግሎት የያዛችሁ ወገኖቼ እባካችሁ እያደረጋችሁ ያላችሁትን ድርጊት ቆም ብላችሁ ዐስቡት። ይህ ከእግዚእበሔር አይደለምና እባካችሁ ይህን መንገድ ተዉ። ሳምራውያን ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም ሊሄድ መሆኑን ተረድተው ባልተቀበሉት ጊዜ ዮሐንስና ያዕቆብ “ጌታ ሆይ፥ ኤልያስ ደግሞ እንዳደረገ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው እንል ዘንድ ትወዳለህን?” ባሉት ጊዜ፥ “እርሱ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸውና፦ ምን ዐይነት መንፈስ እንደ ሆነላች

Agizachew Tefera (Deacon)

መምህር አግዛቸው ተፈራ በተሐድሶ አገልግሎት ውስጥ የሚያገለግሉ፣ በዚሁ አገልግሎት ውስጥ፦ የተቀበረ መክሊት (1993 ዓ.ም.)፤ ጥላና አካል (1995)፤ የለውጥ ያለህ!!! (2001 ዓ.ም.)፤ አልተሳሳትንምን? (2003 ዓ.ም.)፥ ትምህርተ ድኂን በአሚነ አበው (2005) የተሠኙ ተሐድሷውያን መጻሕፍትን ለአንባብያን ያበረከቱ ሲኾን፥ የሚያገለግቡበት “ማኅበረ በኵር” የሚያሳትመው የጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ዋና አዘጋጅም ናቸው።

Share this article:

ሚሲዮናዊ ተልእኮ ባ’ገር ልጅ

በወንጌላውያን የሚሲዮን ታሪክ ፋና ወጊ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው በዐፄ ፋሲል ዘመነ መንግሥት (1625 – 1660 ዓ.ም.) እንደ መጣ የሚታመነው ጀርመናዊው ፒተር ሄይሊንግ ነው። ፒተር በኢትዮጵያ ቆይቶ በ1644 አካባቢ ወደ አገሩ ለመመለስ በመንገድ ሳለ፣ ቱርኮች አግኝተው እስልምናን እንዲቀበል ቢያስገድዱትም አሻፈረኝ በማለት አንገቱን ቀልተው ገደሉት። ይህ ሚሲዮናዊ በኢትዮጵያ ሳለ የአማርኛ ቋንቋን አቀላጥፎ መናገር ችሎ የነበረ ሲሆን፣ የዮሐንስ ወንጌልን ወደ አማርኛ በመመለስ ለሕዝቡ እንዳበረከተ ታሪክ ዘግቦታል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ወንድሞችና እኅቶች ተስማምተው በአንድነት ሲኖሩ እንዴት መልካም ነው!

የአንድና የብዙ ጉዳይ የዓለም አፈጣጠር ምሥጢር ነው። የአንድና የብዙ ሁኔታ የብዙ ጠቢባን፣ የብዙ ፈላስፋዎች ጥያቄ ነው። አንዳንዶቹ በአሐዳዊው ላይ ሌሎቹ ደግሞ በብዙው ላይ ያተኩራሉ። ሆኖም ብዝኃነትን ያለ ኅብረት፣ አንድነትን ያለብዝኃነት ማሰብ ይቻል ይሆን? ብዝኃነት ውበት የሚሆነው መቼ ይሆን? አንድነትስ አስደሳች የሚሆነው መቼ ይሆን? 

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.