[the_ad_group id=”107″]

መከራው እስካለ

ከወንጌል አማኞች (ፕሮቴስታንቶቹ) ወገን ሆኜ ሳለሁ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማሰብ ከጀምርሁ ሰነባብቷል። ስለ መጪው ዘመን ክርስትና እንደሚገድደው ሰው ያን ማድረጌ ምን ያስደንቃል? በምሥራቅ አፍሪካ፣ በመላዋ አፍሪካ እንዲሁም ከእስያ ደግሞ ቢያንስ በምዕራብ እስያ ለክርስትና መሰንበት ሚና ያላት በመሆኗ፤ ያላትን ምእመን ይዛ በመከላከል ብቻ በመኖር ፈንታ፣ ወንጌልን በንቃትና በአጥቂነት የምታሰራጭበትን ቀመሩን ልታገኝ ስለምትችል፤ የሚተዉአት ምእመኖቿ ለምን እንደሚለዩአት ምክንያቱን ለይታ አውቃ እንዳይተዉአት፣ የተዉአትም እንዲመለሱ ብልሃት ልታበጅ ብትችልስ ከሚል፤ እንደ ሁለት የአይሮፕላን ክንፍ ሆነን እኛ ወንጌላውያን ከእርሷ ጋር ወንጌልን ልናፈጥን የምንችልበት ዕድሉ ሙሉ ለሙሉ አልተዘጋ እንደ ሆነስ ከሚል ሕልም ተነሥቼ ነው በዐሳብ መንጎዴ።

ቤተ ክርስቲያኒቷ እንደምትሆነው፣ ‘የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትም እንደዚያው እንሆናለን፤ ማለትም ከተከፋፈለች እንከፋፈላለን፤ ከጠፋችም ኋላና ፊት የመሆን ጕዳይ ካልሆነ በስተ ቀር እንጠፋለን’ ብዬም እፈራለሁ። በእነዚህ ዐሳቦች ስለተነደፍሁ ነው ስለ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የማወጣውና የማወርደው። ይህን ስጽፍ ቤተ ክርስቲይኒቷ የእኔን ጥብቅና እንደማትፈልግ፣ እንዳልጠየቀችኝም ይታወቃል፤ ስለ ራሷ መሟገት ይሳናታል ብዬም አላስብም። እኔም አሻቅቤ ለመምከር የምቃጣ ያልተቈነጠጥሁም አይደለሁም። የምጽፈው ለብቻዬ ሆኜ ያሰብኩትን ለመተንፈስ ያህል ብቻ ነው።

ጌታ ኢየሱስ ዐይኑን እንደከፈተለት ዕውሩ ሰውዬ አጥርቶ ከማየቱ በፊት፣ “ሰዎች እንደ ዛፍ ሲመላለሱ አየሁ” (ማርቆስ 8፥24) እንዳለው እንዳይሆንብኝ እንጂ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስደት ላይ እንደ ሆነች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታየኝ ነው። መከራው ግን ስውር ነው። እንደምገመተው የሰወረውም፦

  • አቅም/ኀይል በነበራት ባለፉት ዘመናት አድርጋው ነበረ ወይም ከቀድሞዎቹ የአገር መሪዎች ጋር እጅና ጓንት ሆና ነበረ የሚለው ቅያሜ፤
  • ዳግመኛ አቅም ካገኘች መከራ ታመጣለች የሚል ሥጋት/ፍርሀት፤
  • ከብዙኃን እንጂ ከአናሳ ወገን ባለመሆኗ ተሰደደች ለሚል ወሬ አለመመቸቷ፤
  • እየደረሰባት ያለው መከራ በቀጥታ መጽሐፍ ቅዱስን ስታስተምር/ወንጌልን ስትናገር ሳይሆን፣ የዕለት ተዕለት ኑሮዋን እየኖረች ሳለ መሆኑ፤
  • የስደቱ መንፈስም በግልጽ ‘በዶግማሽ ወይም በቀኖናሽ ላይ መጥቻለሁ፤ ወዮልሽ!’ በማለት “የሚያስፈራራ” ወይም “የሚያገሣ” አለመሆኑ ሊሆኑ ይችላሉ።

እኔን በግሌ በተመለከተ ተሰውሮብኝ የነበረው ጕዳይ፦ ስደትን የወንጌላውያን ብቻ አድርጌ ሳስብ መኖሬና ቀድሞ ዘመን “ባደረገችው ነገር እግዚአብሔር እያስተማራት ይሆን እንዴ?” የሚለው መልስ የማይፈልግ ጥያቄዬ ነበር። ይሁን እንጂ፣ እየሆነባት ያለው ከስደት ጋር አንድ መሆኑን በጭላንጭልም ቢሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተረዳሁት ነው።

  • እንደተቀበለችው ትምህርትና አኗኗር እንዳትመላለስ (ለዶግማዋና ለቀኖናዋ ታማኝ እንዳትሆን)፤[1]  
  • ምእመኖቿን የምትጠብቅበትና የምትመግብበት ሥርዐት እንዲሰነካከል (ፓትረያርክ፣ ኤጲስ ቆጶሳት፣ ሲኖዶስ እንዲከፋፈሉ ወይም ልሳናቸውን እንዲይዛቸው)፤
  • ምእመኗ አንድ ላይ እንዳይቈም በማሳወርና ዐልፎ ተርፎ እርስ በእርስ እንዲወነጃጀልና እንዲባላ፤
  • በማፈናቀል የኢኮኖሚ ድቀትና ማኅበራዊ ምስቅልቅል ላይ እንድትወድቅ በመደረግ ላይ በመሆኑ መከራዋን እያየች ነው።
  • በአንዳንድ ስፍራ ምእመኖቿ እምነታቸውን በሚያስታውቁባቸውና ለእምነታቸው ታማኝነታቸውን በሚመሰክሩባቸው ምልክቶች እየተሳለቀባቸውና እነዚህን በአደባባይ በሚያሳዩ ላይ ጉዳት እየደረሰባቸውም ነው።[2]

ይህ የሚደረገውም፣ የቤተ ክርስቲያኒቷን ፍላጎት ከተለያዩ ወገኖች ፍላጎት በታች አድርጋ እንድትይዝና ለእነዚያ ፍላጎቶች የምትመች ገራምና ለማዳ አድርጎ ለመግራት፣ እምቢ ካለችም ለማጥፋት ይመስላል። ታዲያ ስደት ምን ቦቃ አለው? ይኸው አይደል? ስደት ተብሎ የሚቈጠረው ወንጌልን አታስተምር ወይም አትስበክ ሲባል ብቻ አይደለም።[3] ለዚህ ቶማስ ሺርማሸርን እማኝነት እጠራለሁ። እርሱ ያለውን በግርድፉ ተርጕሜ እጠቅሰዋለሁ፦

ክርስቲያኖች የሚሳደዱበት ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ ባለ ብዙ ገጾች ነው። ሃይማኖታዊ ብቻ የሚሆንበት ጊዜ እምብዛም ነው። ፖለቲካዊ፣ ባሕላዊ፣ ብሔራዊ፣ ምጣኔ ሀብትዊ [ጕዳዮች]፣ የግል ምኞትም ሳይቀር አነሳሽ ሆነው ሊደረቡ ይችላሉ። ብሉይ ኪዳን ይህን አሳምሮ ያሳየናል። 1ኛ ነገሥት 16-19 ያለውን ክፍል ስናነብብ፣ ንግሥት ኤልዛቤል ለእግዚአብሔርና ለነቢያቶቹ የነበራት ጥላቻ ለሥልጣን ከነበራት ጉጉት እንዲሁም የግል ረብ ከማግኘት ፍላጎቷ ጋር የተደባለቀ እንደ ነበር እንመለከታለን። በቅዱስ ዮሐንስ ራእይ እንደተመለከተው፣ ለቤተ ክርስቲያን የሚኖር ጥላቻ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጕዳይ ሲያጅበው ይጦዛል። የጳውሎስ መልእክት ለገቢያቸው መቋረጥ ምክንያት ሆነ በማለት የኤፌሶን ብር ሠሪዎች ቁጣን ያነሳሡት (የሐሥ 19፥23፡ 29) የስደትን ባለ ብዙ ገጽነት ለማሳየት ሌላ ምሳሌ ነው። ጳውሎስ ከምዋርተኛዋ መንፈስን ያስወጣ ጊዜ ጌቶችዋ የትርፋቸው ተስፋ እንደ ወጣ በማየታቸው፣ ጳውሎስንና ሲላስን አሳሰሯቸው (የሐሥ 16፥16-24)። ከስደት ማዕበል ጀርባ ያሉትን የተለያዩ መነሻዎችና አጃቢዎቻቸውን ሁሉ ከታሪካዊና ጂኦግራፊያዊ ሁኔታቸው ጋር እያጣቀሱ በጥልቀት ለማውሳት ሥፍራ አይበቃንም። ይሁን እንጂ፣ ሃይማኖትን በተመለከተ የጠራ ሃይማኖታዊ ስደት የሚባል እምብዛም አለመኖሩንና ከሃይማኖታዊ ሥጋቱ (ስደቱ) ጋር የሚያደናግር ባሕላዊና ማኅበራዊ ችግር ምን ጊዜም ተቀላቅሎ እንደሚገኝ ልብ ማለት ይኖርብናል።[4]

ይህ ወንጌላውያንን ታሳቢ አድርጎ የተጻፈ ቢሆንም፣ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ ስደት ለሚደርስበት ማንኛውም ቤተ እምነት አያገለግልም ማለት አይቻልም።

መከራው ወይም ስደት መኖሩን ማወቅ አንድ ነገር ነው። ነገር ግን፣ በመከራው ወይም በስደቱ ውስጥ ያለ ክርስቲያን እንዴት ይኑር የሚለውንም ተረድቶ በዚያ መሠረት መኖር ሌላውና ዋናው ጕዳይ ነው። ስለ አኗኗሩም ያንኑ ቶማስ ሺርማሸርን አሁንም እጠቅሳለሁ።

የዕብራውያን መልእክት፣ 1ኛ ጴጥሮስ እና የቅዱስ ዮሐንስ ራእይ በትክክል ‘የሰማዕትነት መጻሕፍት’ ሊባሉ የሚችሉ ናቸው። የእነዚህ መጻሕፍት ዐላማ ጕባዔዎችን ለሰማዕትነት ማዘጋጀት ወይም በመከራ ያሉትን ማጽናናት ነው። ክርስቲያኖች ከማንኛውም ነገድና ቋንቋ (ባሕል) ወንድምና እኅት አላቸው [አንድ ቤተ ሰብ ናቸው]። ቤተ ሰብ መሆን ደግሞ የሚያስከትለው ኀላፊነት አለ። ቤተ ክርስቲያን በመከራ ጊዜ እንደ አንድ አካል ሥራዋን ልታከናውን፣ አንዱ ብልት ለሌላው ሊገድደው፣ አንዱ ሌላውን ሊንከባከብ፣ ሁሉም በመተባበር በአንድነት ሊቈም እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ ግልጽ አድርጓል። ይህ እግዚአብሔር ለልጆቹ ካኖራቸው ቁልፍ ዕቅዶች አንዱ ነው።[5]

የኢትዮጵያና የኤርትራ ቅዱሳን ፓትረያርኮችና ብጹዓን ጳጳሳት (ኤጲስ ቆጶሳት) ምእመናኖቻቸው ስደት ላይ መሆናቸውን አያውቁም ወይም መከራን ለመቋቋም የሚሆን የአኗኗር ዘይቤ ምን እንደ ሆነ ይስቱታል ብዬ አላስብም። ጠንቅቀው ያውቁታል ብዬ በድፍረት መናገርም እችላለሁ። ሁሉም ኦርቶዶክሳውያን እግዚአብሔር ስለ መከራ ባኖረው ዕቅድ መሠረት የሠመረ ሕይወት እንዲኖሩ ይሳካላቸው በማለት ወደ ቀጣዩ ልሻገር።

ከዚሁ ከመከራ ጋር የተያያዙ ሌሎች ነገሮችንም ዐስባለሁ፤ እጠይቃለሁ። 

  1. በቤተ ክርስቲያን ምንኵስና የተጀመረው ንጉሥ ቁስጠንጢኖስ የክርስቲያኖችን ስደት ካስቀረ በኋላ ነው ይባላል፤ በመከራው ጊዜ የነበረውን የሰማዕትነት (ማለትም ለእምነት፣ ለጌታ ኢየሱስ፣ ለቤተ ክርስቲያን ፈጽሞ የመሰጠት) ሕይወት አምሳያ ኑሮ ለመኖር ነው በሚል።[6] አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች በሚኖሩ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን አማኞች ቤት ላይ፣ ስደት/መከራ እየገባ ስለ ሆነ (ስለ ኤርትራ በቅርብ ጊዜ ሲወራ አልሰማሁም)፣ ሁሉም በያለበት የምንኵስና ኑሮ ሊኖር ነው ማለት አይቻልም? መከራው እስካለስ ምንኵስና ቤቴ ድረስ መጣልኝ አያሰኝም? ከእነዚህ መኻል የሚገደሉቱስ የሰማዕትነት ማዕረግ ሊቀዳጁና መታሰቢያ ሊበጅላቸው አይገባም?

  2. ወንጌላውያንስ ለሚሰደዱት ኦርቶዶክሳውያን ልናደርግ የምንችለው የለምን? ኦርቶዶክሳውያን የሥጋ ዘመዶቻችን አይደሉምን? ስለ ቤተ ሰዎቻችን ኀላፊነት የለብንም?[7] መጽሐፍ፣ “ነገር ግን ለእርሱ ስለ ሆኑት፣ ይልቁንም ስለ ቤተሰዎቹ የማያስብ ምንም ቢሆን ሃይማኖትን የካደ፣ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው።” (1ጢሞ 5፥8) ማለቱን ልብ ይሏል። ይህ፣ ‘ባፕቲስት’ የሆነ ‘ባፕቲስት’ ቤተ ሰዎቹን፤ ‘ሉተራን’ ደግሞ ‘ሉተራን’ ቤተ ሰዎቹን እንደ ማለት ነው ተብሎ ካልተተረጐመ በስተ ቀር፣ የኦርቶዶክስ ቤተ ሰዎቻችንንም ማሰብ ይጨምር ይመስለኛል።

  3. የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርቲያንና ፕሮቴስታንቶች ምክክር/ውይይት እያደረጉ ይገኛሉ።[8] በርግጠኝነት ሁሉም ይሳካል ባይባልም፣ የሚጠበቁት ውጤቶች ግን በየደረጃው የሚከተሉት ናቸው፦
     
  4. አንዱ በሌላው ላይ ያለውን ውግዘት ማንሣትና በሚሲዮን ሥራ መተባበር (አንዱ ሌላውን ክርስቲያን አድርጎ መቀበልና ተባብሮ መሥራት)፤
  5. አንዱ በሌላው ቤተ ክርስቲያን ሥርዐተ ምስጢር ላይ መካፈል፤
  6. ፈጽሞውኑ አንድ ቤተ እምነት ወደ መሆን መምጣት የተሰኙት ናቸው።

እነዚህ ባይሳኩ እንኳ፣ በመካከላቸው በታሪክ ያለው ቁርሾ ተወግዶ ግኝኑነታቸውን ከመሻከር ማውጣት ይቻላል ተብሎ ይታመናል። ለዚህም ፓፓው በፕሮቴስታንት ተሐድሶ እንቅስቃሴ 500ኛው ዓመት በዓል መነሻነት፣ ፕሮቴስታንቶችን ይቅርታ መጠየቃቸው መንገዱን ሳይጠርግ አልቀረም።[9] እንደውም በቅርቡ ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች በጀርመን አገር አንዳቸው በሌላቸው ቅዱስ ቁርባን እስከ መካፈል ደርሰዋል።[10] ታዲያ ይልቁንም በመካከላችን በታሪክ የከረረ ጠብ በሌለን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በኢትዮጵያ ወንጌላውያን መካከልስ ለተመሳሳይ ዐላማ ውይይት ማድረግ አይቻልምን? ብዙ የማይኳሃኑ ጕዳዮች በመኖራቸው ይህ ዐሳብ ከሁለታችንም ወገን የከረረ ተቃውሞ እንደሚገጥመው አያጠራጥርም። ይህን ማየት እስከሚሳነኝ ድረስ ገራ ገር አይደለሁም። አሁን ባለው ትውልድ ውጤት ይገኛል ብዬም አላስብም። ቢያንስ ግን ስለ ውይይቱ አስፈላጊነት መነጋገር አይቻልም ወይ? ለማለት ነው።

  • እስከዚያው ግን አብላጫ ምእመን ያለው ቤተ ክርስቲያን በአካባቢው አናሳ ምእመን ባለው ቤተ ክርስቲያን ላይ መከራን እንዳያመጣ (ስደትን እንዳይስነሣ) ብልሃት ማበጀቱ (መጠበቂያ ቃታ ማኖሩ) ውይይትን የሰመረ ለማድረግ ይረዳል የሚል ቅን እምነት አለኝ። ለምሳሌ በትግራይ፣ በአማራ ክልልና በኤርትራ ኦርቶዶክሳውያኑ ፕሮቴስታንቶቹን እንዳያሳድዱ፣ እንዲሁም በደቡብና በምዕራብ ኢትዮጵያ ወንጌላውያኑ ኦርቶዶክሳውያኑን እንዳያሳድዱ ብልሃት ቢበጅለት ለክርስትና ዘለቄታ ይበጃል እላለሁ።

ነገርን ነገር ያነሣዋል እንዲሉ፣ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትዕዛዝ እንደተደረገ ባላምንም፣ በቅርቡ በአቃቂ በሰቃ መካነ ኢየሱስ ማኀበረ ምእመናን ላይ የደረሰው ጥቃት አሳዛኝ ሆኖ ነው ያገኘሁት። እንዲህ ያለው ተግባር ምን በረከት ሊያስገኝ እንደሚችልም አልገባህ ብሎኛል። እኛ ወንጌላውያን በተወላጅነትና በባሕል ልጆቻቸው እንደ ሆንን ለኦርቶዶክሳውያኑ የተሰወረ አይመስለኝም። ይህን ዐይነት ጕዳት ለማድረስ ምን አስገዳጅ ሁኔታ ተፈጠረባቸው? በአደባባይ መግለጹ ባይመች እንኳ የአካባቢው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በውስጥ መሥመር የደረሰው ተገቢ አለመሆኑንና ማዘኑን ለአቃቂ በሰቃ ምእመና ይገልጻል ብዬም ዐስባለሁ።

በቸርነቱ ያኑራችሁ፣ በቸርነቱ ያኑረን!


[1] ዶግማዋና ቀኖናዋ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው ወይም አይደለም የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባይሆንም እንኳ፣ ‘ጎሽ፤ ትሰደድ’ አያስብልም ለማለት ያህል ነው።

[2] ከጊዜው ርዝማኔ የተነሣ ቃሎቹን በትክክል አላስታወስኩ ይሆናል። እኛም በደርግ አገዛዝ ጊዜ በገሐድ በስተ ውጭ በምንደርባቸው ልብሶችና በመሳሰሉት ላይ (እምነታችንን እንዲመሰክርና አንዳንዶችንም እንዲያጽናና) “Jesus Saves”፣ “ኢየሱስ ያድናል”፣ “God is Love”፣ “ማራናታ”፣ “Jesus is coming”፣ “በመከራ ጽና” የመሳሰሉትን የያዘ አርማ (ባጅ) እንለጥፍ ነበር። ማንበብ ባንችል ወይም መልእክቱ የሚደርሳቸው ወገኖች ማንበብ የማይችሉ ናቸው ብለን ብናስብ ኖሮ ምን እናደርግ እንደ ነበር ማን አውቆት?  

[3] በነገራችን ላይ ደርግም እኛን ወንጌላውያንን ሲያሳድድ ወንጌል በመስበካችሁ ሳይሆን፣ ‘ለኅብረተ ሰባዊ ርእዮተ ዓለም መስፋፋት እንቅፋት በመሆናችሁ ነው’ ይል ነበር።

[4] Thomas Schirrmacher. The Persecution of Christians Concerns Us All. The WEA Global Issues Series. 2018

[5] ዝኒ ከማሁ።

[6] Monasticism – OrthodoxWiki፡ “Origins of Christian monasticism” ይመልከቱ።

[7] ጽሑፉ ኦርቶዶክሳውያንን የተመለከተ ስለ ሆነ እንጂ፣ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችም ቤተ ሰዎቻችን መሆናቸው የታወቀ ነው።

[8] በርእሱ ዙሪያ በጉጉል አሰሳ በማድረግ በርካታ ጽሑፎችን ማግኘት ይቻላል። ውይይቱ መኖሩን ለማሳየት ያህል ነው ይህን ያቀረብሁት፦ PROTESTANT‐ROMAN CATHOLIC ENCOUNTER AN ECUMENICAL OBLIGATION – Kinder – 1955 – The Ecumenical Review – Wiley Online Library.

[9] https://www.reuters.com/Pope asks Protestants for forgiveness for persecution. January 25, 2016.

[10] https://www.ncregister.com/:Catholics and Protestants Share Communion at German Ecumenical Convention.


Share this article:

እኔነት የሚፈታተነው የክርስቶስ ማኅበር አንድነት

“ደሞዛችን አልደረሰም እንዴ?” ስትል ጠየቀችኝ። ጠያቂዋ ሚስቴ ስትሆን፣ ትዳር ከመሠረትን ሁለት ሳምንት ገደማ የሆነን ይመስለኛል። ለካንስ ላቤን አንጠፍጥፌ የማገኘው ደሞዝ፣ ከትዳር በኋላ ደሞዛችን ሆኗል! ላቤም የግሌ አይደለም ማለት ነው። ይሄን ማሰቡ ድንጋጤ ለቀቀብኝ። ባልና ሚስት አንድ አካል፣ አንድ አምሳል እንደሆኑ አልጠፋኝም፤ ክርስቲያናዊው ትዳር፣ “ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም፤ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ” በሚል…

ተጨማሪ ያንብቡ

1 comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

  • ኦርቶዶክስ ይሁን ካቶሊክ ይሁን ፕሮቴስታንት፣ ጥያቄው፦ የቤተ ክርስቲያን ራስ ማን ነው? ኢየሱስ ክርስቶስ ከሆነስ፣ መካከለኛውን ሥፍራ ይዟል? ቀጥሎ፣ ምእመን የክርስቶስን ወንጌል ሰምቷል? ነው።

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.