[the_ad_group id=”107″]

ለግብ መብቃት

አዘውትረው ከሚደረጉ ስፖርቶች መካከል፣ በዓለም ሕዝብ ዘንድ የእግር ኳስ ጨዋታን የሚያህል የሚወደድ እንደ ሌለ ይታመናል። የአራት ዓመት ዙሩን እየጠበቀ የሚመጣውን የዓለም ዋንጫም ሆነ ወይም በየሁለት ዓመቱ የሚዘጋጀውን የአውሮፓ ዋንጫ ትልቁም ትንሹም በጕጕት የሚጠብቀው ስፖርታዊ ፉክክር ነው። በተለይ በተለይ ደግሞ በሲዝኖች ተከፋፍሎ የሚከወነው የእንግሊዙ ፕሪምየር ሊግ የሰውን ስሜት ከመግዛቱ ባሻገር ሉል ዐቀፍ የመግባቢያ ቋንቋ እስኪመስል ድረስ አንዱን ከአንዱ የሚያቀራርብ (በመጠኑም ቢሆን ማራራቁ እንደ ተጠበቀ ሆኖ) ተወዳጅ ወድድር ነው።

የዘንድሮውን ፕሪምየር ሊግ ሲዝን ለረጅም ጊዜ በመምራት ላይ የነበረው የመድፈኞቹ ቡድን ግስጋሴውን አስጠብቆ ዋንጫ ቢያነሣ ኖሮ ከ2004 (እ.አ.አ) ወዲህ የመጀመሪያው ይሆን ነበር። ነገር ግን፣ አያያዙን ዐይቶ ወደ ፊት ከመሄድ ይልቅ ወደ ኋላ ማፈግፈግን የመረጠ መምሰሉን መናገር ይቻላል። በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ዳኛው የሚያሰሙት የተፈጸመ ፊሽካ እስኪነፋ ድረስ በሜዳው ላይ ያልተጠበቀ ነገር ሊፈጠርና ውጤትም እንዳልተጠበቀው ሊሆን እንደሚችል ብናውቅም፣ ከዚህ በኋላ ግን የአርሰናል ብቸኛ ተስፋ የተንጠለጠለው የሌላ ቡድን ሽንፈት ላይ ብቻ ነው። ይህን ደግሞ የተቀናቃኙን ቡድን ወቅታዊ ብቃት፣ ያላቸውን የነጥብ የበላይነትና የቀራቸውን ጥቂት ጨዋታ ግምት ውስጥ በማስገባት የተሟጠጠ ተስፋ ያላቸው ብቻ መሆኑን መገመት አይከብድም።

የሚገርመው ግን አንድ ቡድን ሲዝኑን ሙሉ ለማለት በሚያስችል መልኩ ከፊት ሲሮጥ ቆይቶ፣ ሦስትና አራት ጨዋታ ሲቀረው ሸርተት ብሎ ሲጋደልለት የነበረውን ዋንጫ በሩቅ ለመሳለም ብቻ መብቃቱ ነው። ይህን ያነሣሁት ለጕዳይ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ከነገር ጅማሬ ይልቅ ለነገር ፍጻሜ ከፍተኛ አጽንኦት ይሰጣል። ለፍጻሜ ትኵረት የመስጠቱም ምክንያት ብዙዎች ከጠራቸው ከእግዚአብሔር ጋር ጕዞ እንደሚጀምሩ፣ ነገር ግን በጀመሩበት ፍጥነትም ሆነ ቅናት እንደማይቀጥሉ፣ ከዚያም ዐልፎ ከመሥመር እንደሚወጡ ለማሳየት ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ የነበሩትን አማኞች ግልጽ በሆነ መልኩ እንዲህ በማለት ሐዋርያዊ ምክሩን ይለግሳችዋል፦ “በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፥ ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ።” (1ኛ ቆሮንቶስ 9፥2)

መጽሐፍ ቅዱስ ከነገር ጅማሬ ይልቅ ለነገር ፍጻሜ ከፍተኛ አጽንኦት ይሰጣል። ለፍጻሜ ትኵረት የመስጠቱም ምክንያት ብዙዎች ከጠራቸው ከእግዚአብሔር ጋር ጕዞ እንደሚጀምሩ፣ ነገር ግን በጀመሩበት ፍጥነትም ሆነ ቅናት እንደማይቀጥሉ፣ ከዚያም ዐልፎ ከመሥመር እንደሚወጡ ለማሳየት ነው።

ይህ ሐዋርያው ጳውሎስ የቆሮንቶስ አማኞች እንዲሮጡት የሚያበረታታቸው ሩጫ ዐላማው “መሮጥ” ሳይሆን፣ “ለማግኘት መሮጥ” ነው። መሮጥ፣ ለማግኘት የሚፈለገውን ነገር ለማግኘት፣ ወይም ከግብ ለመድረስ የሚወሰድ ርምጃ እንጂ፣ በራሱ ግብ አይደለም። ለመሮጥ ሳይሆን የሚሮጠው የሚሮጥለትን ነገር ለማግኘት ነው። የአርሰናል ቡድን ገና ሲዝኑ ሲጀመር ዐላማው ሁለተኛ ለመሆን ሳይሆን በብቃት ተጫውቶ አሸናፊ ብቻ የሚያነሣውን ዋንጫ ለማግኘት ነው። ወይም መኻል መንገድ ላይ አቅም ሲጠፋ፣ ‘ግድ የለም ቢያንስ ለአውሮፓ ሻምፒዮን ሊግ ዐልፈናል’ ለማለት አይደለም። ለዚህ ነው ጳውሎስ በወንጌሉ ለወለዳቸው ለቆሮንቶስ ቅዱሳን በዐጭር ቃል፣ “ታገኙ ዘንድ ሩጡ” ብሎ የሚመክራቸው። በማግኘት ያልታጀበ ሩጫ ካለመሮጥ አይበልጥም። በብድራት ወይም በማሸነፍ ያልተጠናቀቀ ሩጫ ራሱ ሐዋርያው እንደሚለው፣ “ንፋስን እንደ መጐሰም ነው”። የቆሮንቶስ ሰዎች መሮጥ ያለባቸው ብዙዎቻችን “ታላቁ ሩጫ ላይ ሮጬ ነበር” እንደምንለው “ሮጠን ነበር” እንዲሉ ሳይሆን፣ ብድራቱን እንዲያገኙ ነው። ዐላማ የሰነቀና በዐላማ የሚተገበር ሩጫ ነው።

በማግኘት ያልታጀበ ሩጫ ካለመሮጥ አይበልጥም።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ መልኩ ጳውሎስ የሮጠ ሁሉ ብድራቱን እንደማያገኝ፣ “አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን?” በማለት በጥያቄ ያሳስባቸዋል። መሮጡ ሳይሆን ቍም ነገሩ፣ ዋጋ ወይም ብድራት ማግኘቱ ነው እያላቸው ነው። በእኛ ዐውድ የሩጫውን መጀመር የሚያበስረው፣ “ጥይት” ሲተኰስ ሁሉም የአገሩን ባንዲራ ወክሎ ተስፈነጥሮ ሲፈተለክ፣ ሁሉም አንደኛ የሚወጣና ብድራት የሚያገኝ ይመስላል። ነገር ግን፣ ሩጫውን የጀመረ ሁሉ ከግብ አይደርስምና አንደኛ ወጥተው የክብሩን ሽልማት አንገታቸው ላይ እንደሚያጠልቁ ዐስበው የተፈተለኩ ብዙዎች ከኋላ ይቀሩና አንዱ ብቻ የፍጻሜዋን ሪበን በጥሶ ይገባል። ምን ዐይነት ትጋትና ጽናት ይሆን የሚጠይቀው!? እንዲሁ ታገኙ ዘንድ ሩጡ!

ሐዋርያው ዮሐንስ ደግሞ በሁለተኛይቱ መልእክቱ ላይ ተደራስያኑን እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃቸዋል፦ “ሙሉ ደመወዝን እንድትቀበሉ እንጂ የሠራችሁትን እንዳታጠፉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” (2ኛ ዮሐንስ 8)

ሠርታችሁ ሠርታችሁ፣ ወይም ሮጣችሁ ሮጣችሁ መጨረሻ ላይ እንዳታበላሹና እንዳትበላሹ ተጠንቀቁ ያላል። የዚህ መሠረታዊ ምክንያት ደግሞ ሩጫውን የጀመሩት “ሙሉ ደመወዝን” ለመቀበል እንጂ፣ “የጸባይ ዋንጫን” ለመሸለም አለመሆኑ ነው። ላባቸውንና ደማቸውን ጠብ አድርገው ሲሠሩና ሲለፉ ሰንብተው፣ ሙሉ ደመወዝን አለመቀበል እንዴት ያላ ታላቅ ኪሣራ ነው?! ሐዋርያው ዮሐንስ፣ “እንዳታጠፉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” ነው የሚላቸው። ያጠራቀሙትን ሁሉ በስተመጨረሻ መበተን ሊመጣ ይቻላልና፣ የለፋችሁበትን እንዳትበትኑ ወይም እንዳታጠፉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ ይላቸዋል። ለረጅም ዕድሜ ያጠራቀምነው በስተመጨረሻ በአንድ ቀን ስንፍና ወይም ቸልተኝነት ሲበተን ማሰብ እጅግ ይከብዳል። ስለዚህ መጠንቀቅ እየሰበሰብን ሳለ እንጂ ሊበተን ሲል ብቻ አይደለም።

ሠርታችሁ ሠርታችሁ፣ ወይም ሮጣችሁ ሮጣችሁ መጨረሻ ላይ እንዳታበላሹና እንዳትበላሹ ተጠንቀቁ

ለረጅም ጊዜ ሊጉን ሲመራ የቆየው የአርሰናል ቡድን ምን አግኝቶት ይሆን ዋንጫዋን ከዐሥራ ዘጠኝ ዓመት በኋላ በእጅ ከማንሣት ይልቅ ከሩቅ በዐይኑ ብቻ እንዲሳለም ያስገደደው? ምን ይሆን የናፈቀችውን ዋንጫ፣ ከአሁን አሁን ያዝኋት ብሎ እጁን በመዘርጋት ላይ ሳለ ከእጁ ላይ የመነተፈው? ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ብድራቱ እስኪገኝ ድረስ በአግባቡ ካልተሮጠ፣ እጅ ውስጥ የገባ የሚመስለው ዋንጫ እንኳን ከእጅም ከዐይንም ሊርቅ ይችላል።

እንደ አርሰናል ሮጠን ሮጠን መጨረሻ ላይ ያሯሯጡን ቀድመውን ዋንጫውን እንዳያነሡብንና የሠራነውን እንዳናጠፋ እንጠንቀቅ። በክርስትና ዐውድ ውስጥ ቍም ነገሩ መሮጥ ሳይሆን መጨረስ ነው። ስለዚህም ነው ጌታችን “እስከ መጨረሻ የሚጸና ይድናል” በማለት የጽናትን አስፈላጊነት አጽኖት የሚሰጠው። 

ሐዋርያው ጳውሎስ አማኞች የሚሮጡለት ሩጫ ምን ዐይነት ብድራት እንዳለው ሲናገር እንዲህ በማለት ነው፦ “እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው፥ እኛ ግን የማይጠፋውን” (1ኛ ቆሮንቶስ 9፥25)

በክርስትና ዐውድ ውስጥ ቍም ነገሩ መሮጥ ሳይሆን መጨረስ ነው። ስለዚህም ነው ጌታችን “እስከ መጨረሻ የሚጸና ይድናል” በማለት የጽናትን አስፈላጊነት አጽኖት የሚሰጠው። 

በሮም ኮሎዚየም ውስጥ ይሁን፣ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሚሮጡ ወይም የሚጫወቱ ሁሉ “የሚጠፋውን አክሊል” ለማግኘት ነው። ጳውሎስ እኛ ግን፣ “የማይጠፋውን” ለማግኘት ነው ይለናል። እንግዲህ እነዚያኞቹ የሚጠፋውን አክሊል ለማግኘት የሚያስከፍላቸውን ሁሉ የሚክፍሉ ከሆነ፣ እኛ የማይጠፋውን ለማግኘት ምን ያህል ለመክፈል ዝግጁ ነን? 

የብድራቱ ዐይነትና ልዕቀት የገባው ሰው ብድራቱን ለማግኘት በሚከፍለው ዋጋ ያስታውቃል። ተገቢውን ሩጫ በተገቢው ፍጥነትና በተገቢው መንገድ ሮጠን የምንፈልገው ሳይሆን የምንፈለግበት ስቴዲየም ለመጨረስ ያብቃን።

ጸጋ ለሁላችንም ይብዛልን።

Yilikal Daniel

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.