[the_ad_group id=”107″]

ፖሊካርፕ ያኔ፣ ፖሊካርፕ ዛሬ

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ የምሥራቅም የኦሪየንታል ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት፣ እንዲሁም የአንግሊካን እና የሉተራን አብያተ ክርስቲያናት በአንድ ድምጽ ”ቅዱስ” ሲሉ የሰየሙት ሰው ነው− ቅዱስ ፖሊካርፕ።

ፖሊካርፕ በ69 ዓ.ም ገደማ የተወለደ ሲሆን፣ ውልደቱ የት እንደሆነ አይታወቅም። ገና ሕፃን ሳለ ካሊስቶ ለምትባል ባለጠጋ ሴት በባርነት ተሽጦ የነበረ ቢሆንም፣ ካሊስቶ ግን ፖሊካርፕን እንደ የራሷ ልጅ በእንክብካቤ አሳድጋዋለች። ፖሊካርፕ ክርስቲያን የሆነው ገና በልጅነቱ እንደሆነ የታሪክ ጸሐፍት ይገምታሉ። በዕድሜው ማብቂያ፣ ጌታን “ለ86 ዓመታት” ሲያገለግለው እንደነበር መናገሩም የዚሁ ጠቋሚ ተደርጎ ይወሰዳል።

ፖሊካርፕ “በዮሐንስ” እግር ሥር ሆኖ የተማረ ሲሆን፣ ይህ ዮሐንስ የትኛው ዮሐንስ እንደሆነ መቶ  በመቶ እርግጡ ባይታወቅም፣ የዘብዴዎስ ልጅ ሐዋርያው ዮሐንስ ነው ተብሎ ይገመታል። የ”ቀደምት ክርስቲያናዊ ጽሑፎች” (Early Christian Writings) ጸሐፊ የሆነው ማክስዌል ስታኒፎርዝ እንደውም ይህንን የማያሻማ አድርጎ ይገልጸዋል። ፖሊካርፕ፣ ሐዋርያው ዮሐንስ በኤፌሶን በኖረበት ጊዜ ፖሊካርፕ የእርሱ ደቀ መዝሙር እንደነበረም ያስረዳል። ከዚህ ከዚህ በመነሣት፣ ፖሊካርፕ በመጽሐፍ ቅዱስ በሚታወቁት ሐዋርያትና በቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶች መኻል እንደሚገኝ መሸጋገሪያ ድልድይም ይቆጠራል።

ፖሊካርፕ ኋላ ላይ የሰምርኔስ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ሆኗል። ሰምርኔስ የምትገኘው በአሁኗ ቱርክ፣ ኢዝሚር ግዛት ውስጥ ነው። የሰምርኔሷ ቤተ ክርስቲያን፣ በዮሐንስ ራእይ 3፥9−10፣ “መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ… እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ” የተባለላት ቤተ ክርስቲያን መሆኗን ያስታውሷል።

ስለ ፖሊካርፕ የግል ሕይወት ብዙ የሚታወቅ ዝርዝር የለም። ይሁን እንጂ፣ ብቸኛው ቀሪ የጽሑፍ ሥራው የሆነው ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች የጻፈው ደብዳቤ፣ ስለ ሰብእናው፣ እምነቱና አስተምህሮቱ ያስረዳል። ከዚህም በመነሣት፣ ፖሊካርፕ ከቀዳሚዎቹ የአዲስ ኪዳን ጽሑፎች ጋር ወይም ከጸሐፊዎቹ ከራሳቸው ጋር (ከወንጌላቱም፣ ከመልእክቶቹም ጋር) ያለውን  ከፍተኛ  ትሥሥር  ማስተዋል  ይቻላል።

ፖሊካርፕ የሰምርኔስ ጳጳስ የነበረው ለስድሳ ዓመታት ያህል ሲሆን፣ እንደሚታወቀው ያ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ከሮማ አገዛዝ በሚመጣ ብርቱ ስደት ላይ የነበረችበት ጊዜ ነበር። የፖሊካርፕ ምድራዊ ሕይወት ማብቂያ ሲቃረብ የነበረው የሮማ ቄሳር ማርከስ ኦውሬሊየስ ደግሞ ይበልጡን ክርስቲያኖችን ማሳደዱን አበርትቶ የቀጠለበት ጊዜ ነበር። ታዲያ በዚህ ሁሉ ውስጥ፣ ለብዙ ዓመታት ፖሊካርፕ በሮማ ወታደሮች ሳይያዝና እንግልትም ሆነ ግድያ ሳይኖርበት መኖሩ በራሱ እንደ ትንግርት የሚታይ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ የሰላም ኑሮው ጊዜ ማክተሚያው ደርሶ ነበር። በ150ዎቹ የሮማ ወታደሮች ፖሊካርፕን መፈለግ ጀምረው ነበር።

የሮማ ወታደሮች ሊይዙት እንደሚፈልጉ ወሬው መናፈስ ሲጀምር፣ ደኅንነቱ ያሳሰባቸው ወዳጆቹ ቀድመው እዛው ሰምርኔስ የሚገኘው ቤቱ ደርሰው ዜናውን “አበሰሩት”።  በመጀመሪያ እዛው ሰምርኔስ ቆይቶ የሚመጣውን ለመጋፈጥ ወስኖ የነበረ ቢሆንም፣ ወዳጆቹ ጉትጎታና ሥጋት እረፍት የነሳው (ሥጋታቸው እነርሱንም እረፍት ነሥቷቸው ነበርና) አዛውንት፣ ከከተማ ወጣ ብሎ ወደሚገኝ አነስ ያለ ቤት ሄዶ ለመሸሸግ ተስማማ። እዚያ ሆኖ ለበርካታ ቀናት ሲጸልይ ከቆየ በኋላ ከሥጋታቸው ጋብ ያሉ ወዳጆቹን የሚያስበረግግ ሌላ “ብስራት” ነገራቸው። ይህም ከነሕይወቱ በእሳት ተቃጥሎ መሞት እንዳለበት መረዳቱን ነው። ለነገሩ ፖሊካርፕ ቀድሞውኑም ቤተ ክርስቲያን የተጋረጠባት ትልቁ አደጋ ስደት ሳይሆን ኑፋቄ እንደሆነ ያምንም፣ ያስተምርም ነበር።

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የሮማ ወታደሮች ፖሊካርፕ የት እንደተሸሸገ ደረሱበት። ጊዜ ሳያጠፉ የተሸሸገበት ቤት መዝጊያ ጋር ደርሰው “ፖሊካርፕ የታል?“ አሉ። ታዲያ ወዳጆቹ አሁንም ፖሊካርፕን፣ ”እነሆ፣ ደግመን ሌላ ቦታ ወስደን እንሸሽግህ“ ሲሉ ተማጸኑት።

ፖሊካርፕ ግን የሰማዕትነቱ ጊዜ መድረሱን ተረድቶ ነበር፤ እናም አሻፈረኝ አለ። ”የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን“ ብሎም፣ ሊይዙት የመጡትን ጭፍሮች በር ከፍቶ ወደ ቤቱ አስገባቸው። ፖሊካርፕን ለመያዝ የተላኩት ወታደሮች በርካታ የነበሩ ሲሆን፣ ሊቀበላቸው ከላይኛው የቤቱ ወለል የወረደው ዕድሜው የገፋ አዛውንት ሰው መሆን፣ ይህንን አረጋዊ ለመያዝ ይህን ያህል ሆነው እንዲመጡ መታዘዛቸውም ለወታደሮቹ ግራ አጋቢ ሆኖባቸው ነበር።

ፖሊካርፕ ወደ ቤት አስገብቶ ግሩም እራት ጋብዟቸው አብረው ማዕድ ተቋደሱ። እንደውም ተከትሏቸው ከመውጣቱ በፊት፣ ሲጸልይ ካዩት ወታደሮች ብዙዎቹ ክርስቶስን ተቀበሉ። እራት ተበላ፤ ከቤት ተወጣ፤ ፖሊካርፕ በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ሰምርኔስ ጉዞ ተጀመረ።

ሰምርኔስ ሲደርሱ፣ አዘኔታ አንጀታቸውን ያባባቸው ወታደሮች ፖሊካርፕ፣ ቄሳር አምላክ ነው ብሎ መሥዋዕት እንዲያቀርብ፣ እምነቱን በልቡ ይዞ ከሁኔታው እንዲያመልጥ ይወተውቱት ገቡ። ”እስቲ ምናለበት“ የሚል ጉትጎታ ሳይታክቱ አወረዱበት። በመጀመሪያ ፖሊካርፕ ለውትወታቸው መልስ ሳይሰጥ ሁሉንም በዝምታ ሲያሳልፍ ቆየ። ኋላ ላይ፣ ዝም ብሎ ማለፉ የማይበቃ ሲሆን ነው መሰል፣ በአጭሩ፣ “የምትሉትን ነገር ፈጽሞ አላደርግም“ ሲል መለሰላቸው። የወታደሮቹም ውትወታ በዚሁ ተቋጨ። ”ድርቅናው” ያበሸቃቸው ወታደሮች እንደውም ከሠረገላው ላይ ገፍትረው ጥለውት ጭኑ ላይ ቆስሎ ነበር።

የመጨረሻዋ ሰዓት

ፖሊካርፕ፣ የአካባቢው ገዥ ጋር ተወሰደ። እርሱ መያዙን የሰማ የአካባቢው ሕዝብ የገዥውን ግቢ ሞላው። ሕዝቡ በጥላቻና በቁጣ ፖሊካርፕ ላይ እየጮኸ ነበር። ፖሊካርፕ እርሱ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ገዢው ከእርሱ ጋር የነበረው ምልልስ ይህን የመሰለ ነበር፦

“በቄሳር ማል! ንስሓ ግባ! ‘አምላክ የለሾች ይውደሙ’ ብለህ አውጅ!”

ፖሊካርፕ ግራ ቀኙን ቃኘ። አንገቱን ቀና አድርጎ በእርጋታ በእጁ ሰላምታ እየሰጠ፣ “አምላክ የለሾች ይውደሙ!” ብሎ አወጀ።

ገዥው ግን ፖሊካርፕ ያለው ነገር በሚገባ ገብቶት ነበር። እናም እንዲህ ሲል ቀጠለ፦

”እምነትህን ካድ! አንድ ጊዜ ብቻ ክርስቶስን ክጃለሁ በልና በነጻ ልልቀቅህ።“

“ለሰማንያ ስድስት ዓመታት ሳገለግለው፣ አንዴም ተከፍቼበት አላውቅም። ታዲያ ያዳነኝን ይህን ንጉሥና ጌታ መካድ እንዴት ይሆንልኛል?”

”በቄሳር ማል!”

“እኔን ለማግባባት በመጣር ራስህን አታድክም። በእውነት ከልቤ ሆኜ ልንገርህ፤ ክርስቲያን ነኝ።”

“እንዳሻኝ ላወጣ ላገባቸው፣  የምችል አንበሶች እዚህ እንዳሉኝ ታውቃለህ?“

”እንዳሻህ ትዕዛዝ አስተላልፍ። እኛ ክርስቲያኖች እኮ ስንለወጥ የምንለወጠው ከመልካምነት ወደ ክፋት አይደለም። በክፋት ውስጥ አልፎ የእግዚአብሔር ፍትሕ ጋር መድረስ እንዴት ግሩም መሰለህ!“

”አንበሶቹ ምንም አልመሰሉህ ማለት ነው። አሁኑኑ ሐሳብህን ቀይረህ ንስሓ ካልገባህ፣ በእሳት ተቃጥለህ እንድትሞት ነው የምፈርድብህ!”

“የምታስፈራራኝ እኮ ለአንዲት ሰዓት ነድዶ በሚጠፋ እሳት ነው። ግና ስለሚመጣው የዘላለም ፍትሕ እሳት ታውቅ ይሆን? አምላክን የማይፈሩትን ስለሚያጠፋቸው ቅጣት ታውቅ ይሆን? ፍጠን፤ አትዘግይ! የፈቀደህን አድርግብኝ።”

ገዥው የፈቀደውን አደረገ። ፖሊካርፕ በእሳት ተቃጥሎ እንዲገደል ፈረደ።

ወታደሮቹ ወደሚቃጠልበት ቦታ ወስደውት ከእንጨቱ ጋር በምስማር ሊቸነክሩት ሲሰናዱ፣ ፖሊካርፕ እንዲያ ማድረግ እንደማያስፈልጋቸው፣ ከቶውኑም ከእሳቱ ለማምለጥ እንደማይጥር አረጋገጠላቸው፤ ”እንዳለሁ ተዉኝ፤ እሳቱን ለመቋቋም ብርታት የሚሰጠኝ እርሱ፣ ማገዶው መኻል በምስማር ሳልቸነከር እንድቆም ብርታት ይሰጠኛል።“ ወታደሮቹ እንደው ለወጉ ያህል በገመድ ብቻ እንጨቱ ላይ አሰሩት። በፖሊካርፕ ላይ በተፈረደው ፍርድ የፈነጠዘው ሕዝብ “ሆ…” እያለ እሳቱ ላይ የሚማግደው እንጨት ለማምጣት ተራወጠ።

እሳቱ ከተለኮሰ በኋላ ግን፣ አንድ ያልተጠበቀ ነገር እንደሆነ ተመዝግቦ ይገኛል። እሳቱ ፖሊካርፕን በማቃጠል ፈንታ ዙሪያውን መክበብ ያዘ። ከአፍታ በኋላ፣ ፍርድ አስፈጻሚው በጦር ፖሊካርፕን ወጋው። በመወጋቱ የፈሰሰው ደም ብዛትም በዙሪያው የነበረውን እሳት እስኪያጠፋው ነበር። እሳቱ መልሶ ተለኩሶ የፖሊካርፕ አስከሬን ዐመድ ሆኖ እስኪቀር ድረስ እንዲቃጠል ተደረገ። በመጨረሻ፣ የፖሊካርፕ ወዳጆች ለመቅበር የሚበቃ ጥቂት እንኳን አጥንት ሊያገኙ የቻሉት ተቸግረው ነበር። ይህ የሆነው በ155 ዓ.ም. ግድም ነበር።

ፖሊካርፕ ያኔ፣ ፖሊካርፕ ዛሬ

የፖሊካርፕ ሞትና አሟሟት፣ በክርስቲያኖች ዘንድ ብቻ ሳይሆን በማያምኑትም ዘንድ ለዘመናት ከዓይነ ኅሊናቸው የማይጠፋ ትውስታ ሆኖ ከርሟል። በወቅቱ የነበሩ አማኞች፣ በየዓመቱ ፖሊካርፕ የተገደለበትን ቀን እየዘከሩ እርስ በርስ ሲበረታቱ፣ ወንጌልን የሚናገሩበት ድፍረትን ሲያድሱ ቆይተዋል። ለፊልጵስዩስ አማኞች በላከው ደብዳቤ “እምነታችሁን ሳትጥሉ ጸንታችሁ ቁሙ” ያለውን ምክርም በገቢር በማሳየቱ ለቤተ ክርስቲያን ደማቅ ምሳሌ ሆኗል።

በወቅቱ በርካታ ክርስቲያን አማኞች የተሰዉ ከመሆናቸው ጋር ተዳምሮ፣ በሚገባ ተመዝግቦ የሚገኘው የፖሊካርፕ የአሟሟት ሁናቴ፣ “ክርስትና ለተከታዮቹ የግል ጥቅም ሲባል የተፈበረከ እምነት ነው” የሚለውንና በወቅቱ ሲናፈስ የነበረውን የወሬ ንፋስ ለማስቆም ከፍተኛ ሚና ነበረው።

ዳሩ ግን፣ ፖሊካርፕ ለክርስቶስ ሊሞት የቻለው ለክርስቶስ ይኖር የነበረ በመሆኑ የተነሣ እንደሆነ ማስታወስ ያሻል። “ፖሊካርፕ ምድራዊ ኑሮውን ለጌታ መስጠት የተቻለው፣ ቀድሞውኑስ ኑሮው ለጌታ የተሰጠ ስለነበር አይደለም ወይ?” ብሎ ማጤን አግባብ ነው። ፖሊካርፕ እና ሌሎች ብዙዎች ሕይወታቸውን የሰጡለትን ጌታ የምናምንና የእነርሱን እምነት የምንጋራ ከሆነ፣ “እስከ ሞት ድረስ የታመንን” ለመሆን ምን ያህል የተዘጋጀን እንሆን? የዛኔውን መሰል የተጋረጠና የሚታየን ፈተና ባይኖርም (ወይም ቢኖርም)፣ ቀደምት አበው የሞቱትን ዐይነት ሞት የምንሞትበት ብዙ ዕድል (ወይ ፈተና) ያለ ባይመስለንም፣ እነርሱ የኖሩትን ዐይነት ሕይወት ለመኖር መጋደል ግን አንድ ነገር ነው። ያንን መሥዋዕትነት እንዲከፍሉ ያስቻለ፣ እንዲያ ላለ ሞት ያዘጋጃቸው፣ እንዲያ ያለ ሕይወት አለ። “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና፣ ዛሬ፣ እስከ ለዘላለምም ያው ነው።“

“ፖሊካርፕ ምድራዊ ኑሮውን ለጌታ መስጠት የተቻለው፣ ቀድሞውኑስ ኑሮው ለጌታ የተሰጠ ስለነበር አይደለም ወይ?” ብሎ ማጤን አግባብ ነው።

ለሚድን በሽታ የሚገድል መድኃኒት መውሰድ ይብቃ! (ደወል 3 ዘ ኢትዮጵያ)

“አንዱ በብሔሩ ዘረኛ ሲሆን፣ ሌላኛው በዜግነቱ ዘረኛ ይሆናል። አንዱ ብሔሩን ሲያስቀድም፣ ሌላኛው ዜግነቱን ያስቀድማል። አንዱ የብሔር ዘረኛ የራሱን ብሔር ለብቻው ሊያገንን ሲፈልግ፣ ለኢትዮጵያ ዐብሮነት መሠረት ውጋት ይሆናል። እንደዚሁም የዜግነት ዘረኛ ኢትዮጵያን ለብቻዋ እንድትገን ሲፈልግ፣ በጨለማ ላለ ጥቁር አፍሪካ ሕዝብ አንድነት ውጋት ይሆናል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.