[the_ad_group id=”107″]

ጋሽ በቀለ ይናገራል

መጋቢ በቀለ ወልደ ኪዳን ለአብዛኞቹ አንባቢዎቻችን የምናስተዋውቃቸው ዐይነት ሰው አይደሉም። በአጭሩ ለዐርባ ዓመታት ያህል በዘለቀው አገልግሎታቸው፣ መጋቢ ከሆኑባት የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ባሻገር ብዙዎቹን አብያተ ቤተ ክርስቲያናት፣ ከተማ ገጠር፣ አገር ቤት ውጪ አገር ብለው ያገለገሉ መሆናቸው፣ በወጣቱም ሆነ በቀደሙት ዘንድ ታዋቂ አድርጓቸዋል። ለዚህ ነው የምናስተዋውቃቸው ዐይነት ሰው አይደሉም ማለታችን። መጋቢ በቀለ በብዙዎች ዘንድ “ጋ በቄ” በሚል ስም ነው የሚጠሩት። እርሳቸው ግን “ጋሼ” የሚለውን የማዕረግ ስም ለታናናሾቻቸው እንኳ ሳይቀር ያለ ስስት ይጠቀሙበታል። ጋሽ በቀለን ቃለ መጠይቅ ልናደርጋቸው እንዳሰብን ስንነግራቸው በመጀመሪያ የሰጡን ምላሽ፣ “እኔ አወዛጋቢ (controversial) ሰው ሆኛለሁ፤ እናንት አወዛጋቢ ሰው ምን ያደርግላችኋል” የሚል ነበር። “ታዲያ ምናለ፣ አወዛጋቢ በሆኑባቸውም ጕዳዮች ላይ እናወራለና” አልናቸው። ትንሽ ካሰቡ በኋላ፣ “እንግዲያውስ ካላችሁ ይሁና! ምናለ፤ ሞግቱኝ” አሉን። ጋሽ በቀለ እጅግ ግልጽ በሆነ ቋንቋ ሐሳባቸውን መግለጽ የሚችሉ ብቻ ሳይሆን፣ ለማንም ደጃቸው የተከፈተ ትሑት ሰው መሆናቸውን መመስከር እንችላለን። “ጣልቃ እየገባ” የተሰኘውና ግለ ታሪካቸውን የያዘው ተወዳጁ መጽሐፋቸው ስለ መጋቢው ብዙ፣ እጅግ ብዙ ይናገራል! ሚክያስ በላይ ከግለ ታሪካቸው የተራረፉ ጥያቄዎችን ይዞ፣ “አወዛጋቢ ሰው ሆኛለሁ” ያሉባቸውን ጨምሮ ከመጋቢ በቀለ ወልደ ኪዳን ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል። ጋሽ በቀለ፣ አዘጋጁ “አንቱ” ሳይሆን “አንተ” ብሎ እንዲጠራቸው ግድ ብለውታልና ክብር ያጎደለ የመሰላችሁ አንባቢያን ካላችሁ አስቀድመን ይቅርታ እንጠይቃለን።


  • ሕንጸት፡- ከግለ ታሪክህ እንደተረዳሁት ብዙ መጻሕፍት እንደምታነብብ ነው። በአማካይ በሳምንት ስንት መጻሕፍት ታነባለህ?

መጋቢ በቀለ፡- እንደ መጻሕፍቱ ውፍረትና ይዘት፣ የራሴም የተውሶም የሆኑ፣ በሳምንት አንድም፣ ሁለትም፣ ሦስትም ያነበብኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። አሁን አሁን ደግሞ ከምርጫዬ ጠባብነት፣ ከመጻሕፍቱም እጥረት፣ ከጊዜም እጦት የተነሣ በወር አንድ አዲስ መጽሐፍ እንኳን የማላነብበት ጊዜ አለ።

  • ሕንጸት፡- ብዙ መጻሕፍት እንዳሉህ ሰምቻለሁ፤ ወደፊት ምን ልታደርጋቸው ዐስበሃል? አንድ ሰው እንድትናዘዝለት እንደሚፈልግ ነግሮኛል።

መጋቢ በቀለ፡- መጻሕፍት መኖሩን አሉኝ፤ “ብዙ” የሚባሉ ያህል ግን አይደሉም። ዓለማዊ (secular) ከሆኑት መጽሐፎቼ ውስጥ አብዛኞቹ እየተመዘበሩ፣ አንዳንዶቹም በውሰት ከሄዱበት ሳይመለሱ እየቀሩ፣ አሁን ያሉኝ በጣም ጥቂት ናቸው። ተናዝዤለት እንድሞት እንደሚፈልግ ላንተ የነገረህ ሰው ለእኔ አልነገረኝም። ከአንድ አምስት ዓመታት በፊት ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀረበችልኝ የቤተ ክርስቲያናችን ወንጌላዊት አለች። በእኔ በኩል ግን በቃልም ሆነ በጽሑፍ ተስፋ የሰጠሁት ሰው የለም። እስካሁን ያለኝ ዐሳብ ከመንፈሳዊ መጻሕፍቴ፣ ቢያንስ አንዳንዶቹን ለቤተ ክርስቲያናችን የመካከለኛው ቀጣና መጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ ቤተ መጻሕፍት ለመስጠት ነው። ላጋራቸው የሚገቡ ሌሎች ሰዎች ይኖሩ እንደ ሆነ ገና ወደ ውሳኔ አልደረስኩም።

  • ሕንጸት፡- መጽሐፍ ለማያነቡ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን ምክር አለህ?

መጋቢ በቀለ፡- መጽሐፍ ቅዱሳቸው በውስጡ 66 ትልልቅ መጻሕፍትን ይዟል፤ በውፍረታቸው ሳይሆን በቁም ነገራዊ ይዘታቸው። የግሪኩ ቢብልያ (Bible) ትርጓሜው ቤተ መጻሕፍት ማለት ነው ይባላል። ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እሱን በደንብ የሚያነብቡት ከሆነ ብዙ የሚጎዱ አይመስለኝም።

  • ሕንጸት፡- ስላሉበት ኅብረተ ሰብም ሆነ ስለ ሰፊ ዓለም ምን መረጃ አግኝተው ነው ታዲያ አማኞችን የሚሰብኩት? እንዴት “ብዙ የሚጎዱ አይመስለኝም” አልክ?

መጋቢ በቀለ፡- በጸሎትና በጥንቃቄ ከተነበበ፣ መጽሐፍ ቅዱሱ ስለ ኅብረተ ሰብም ሆነ ስለ ሰፊው ዓለም ዘመን ዘለቅ (transcendent) የሆኑ መረጃዎችን ይሰጠናል። ከዚያ ውጭ ጋዜጦችና መጽሔቶችም አሉ። ሬድዮና ቴሌቪዥንም ሳይሰሙ አይቀሩም። ሌሎች የወሬ ምንጮችም ሞልተዋል።

  • ሕንጸት፡- በብዙ መጋቢያን ዘንድ ባልተለመደ ሁኔታ የኪነ ጥበብ ፍቅር አለህ። ይህ ከየት የመነጨ ነው? ከድሮዎቹ ሰዓሊዎችና ገጣሚያን እነማንን ታውቃለህ?

መጋቢ በቀለ፡- መጋቢያን ሰዎች ናቸው። መጋቢ ከመሆናቸው በፊት ጸሐፊ፣ ሰዓሊ፣ ገጣሚ፣ ስፖርተኛ፣ ዘፋኝ፣ ወዘተርፈ የነበሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ከድሮዎቹ ሰዓሊዎችና ገጣሚዎች የአብዛኞቹን ዝናቸውን፣ የጥቂቶቹን ደግሞ ሥራቸውን ነው የማውቀው። በግል የማውቀው ሰዓሊና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታን ብቻ ነው።

  • ሕንጸት፡- ግጥሞችህን በማቃጠለህ አልተጸጸትክም?

መጋቢ በቀለ፡- ኦ! በፍጹም አልተጸጸትኩም። እግዚአብሔር በሚበልጥ ነገር እንደ ተካቸው ነው የማምነው።

  • ሕንጸት፡- የጻፍካቸው አምስቱም መጻሕፍት ለቤተ ክርስቲያን የተሰጡ ናቸው። እስካሁን ምን ያህል ገንዘብ ከሽያጩ ተገኘ?

መጋቢ በቀለ፡- የመጀመሪያውና የመጨረሻዎቹ ሦስቱ ለቤተ ክርስቲያኔ ነው የተሰጡት። ሁለተኛውን ለ“Ethiopian New Millennium 2000 Prayer Chain” ነው የሰጠሁት። ያሳተሙትም እነርሱ ናቸው። ከመጻሕፍቱ ሽያጭ ምን ያህል ገንዘብ እንደተገኘ አላውቅም። ብዙ የሚሆን ግን አይመስለኝም።

  • ሕንጸት፡- መረጃውን አይነግሩህም ማለት ነው?

መጋቢ በቀለ፡- መጻሕፍቱ ለእነርሱ የተሰጡ በመሆናቸው፣ ለእኔ ሪፖርት ማድረግ አይጠበቅባቸውም።

  • ሕንጸት፡- በየቀኑ ወደ 5 ሺህ ሜትር ገደማ እንደምትሮጥ ሰማሁ። እውነት ነው? ከሆነስ መሮጥ ከጀመርክ ምን ያህል ጊዜ ሆነህ?

መጋቢ በቀለ፡- ስለ እኔ የሚደርሱህ ወሬዎች ሁሉ የተጋነኑ ናቸው ልበል? በመሠረቱ እኔ ተወልጄ ያደግሁት ከኢትዮጵያ የገጠር ከተሞች በአንዲቱ ውስጥ ስለ ሆነ፣ በእግሬ እየተጓዝኩ ነው ያደግሁት። ወደ ትምህርት ቤትና ወደምላክባቸው የተለያዩ ቦታዎች ለመመላለስ ብቻ በየቀኑ በግምት እስከ 12 ኪሎ ሜትር ድረስ የተጓዝኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። አልፎ አልፎ ደግሞ፣ አሁንም በግምት እስከ 25 ኪሎ ሜትር ያህል መንገድ ውሎ ገባ የተጓዝኩባቸው ጊዜያትም አሉ። ደርሶ መልሱ 50 ኪሎ ሜትር ያህል ይሆናል ማለት ነው። እርግጥ እንደዚህ የሆነው ከብዙ ዓመታት በፊት ነው።

ወደ ሥራው ዓለም ከገባሁም በኋላ ቢሆን ከእግር ጉዞ ጋር ብዙ አልተራራቅንም። ላለፉት 25 ዓመታት ያህል ደግሞ፣ ሁኔታው እንደ አመቸኝ ዎክም፣ ጆግም አደርጋለሁ። ተጋንኖ ላንተ የተወራልህን ያህል ግን በፍጹም አይደለም። በየሳምንቱ ለሦስት ቀናት ያህል ከ5 እስከ 7፣ አንዳንዴም 10 ኪሎ ሜትር የሸፈንኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። በየመኻሉ ደግሞ ለብዙ ወራት፣ ምናልባትም ዓመታት፣ ምንም ዐይነት የአካል እንቅስቃሴ ያላደረግሁባቸው ጊዜያትም አሉ።

  • ሕንጸት፡- ታላቁ ሩጫ ላይ ሮጠህ ታውቃለህ?

መጋቢ በቀለ፡- አላውቅም።

  • ሕንጸት፡- ምነው እስካሁን ሳትወዳደር?

መጋቢ በቀለ፡- ለመወዳደር ሳይሆን ለመሳተፍ ፍላጎት ነበረኝ። እሑድ ለእኔ የሥራ ቀን ከመሆኑ የተነሣ ሳይሳካልኝ ቀርቷል።

  • ሕንጸት፡- ከመጽሐፍ ቅዱስ ከተሞች የትኞቹን ጎብኝተሃል?

መጋቢ በቀለ፡- ብዙ አልጎበኘሁም። አቴናን፣ ቆሮንቶስን፣ ፍጥሞ ደሴትን ብቻ ነው የጎበኘሁት። እነዚህንም የጎበኘኋቸው ለጉብኝት ብዬ ሄጄ ሳይሆን፣ ለአገልግሎት በሄድኩበት እግረ መንገዴን ነው።

  • ሕንጸት፡- ሰዎች ነገረ መለኮት ለመማር ፈልገው የድጋፍ ደብዳቤ ከአንተ ለማግኘት ሲመጡ ከልክለህ ታውቃለህ? ከሆነስ ለምን?

መጋቢ በቀለ፡- የድጋፍ ደብዳቤ እንድጽፍላቸው ከሚጠይቁኝ፣ ምናልባት ለአብዛኞቹ፣ ቶሎ አልጻፍኩላቸውም። ሥነ መለኮት ኮሌጅ ለመግባት የፈለጉበትን ምክንያት እጠይቃቸዋለሁ። ወደ ሥነ መለኮት ኮሌጅ ከመግባታቸው በፊት በሥጋ ዕድሜአቸው ትንሽ እንዲያድጉ የመከርኳቸው አሉ። በቀለም ወይም በሞያ ትምህርት ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዲሠሩ የመከርኳቸውም አሉ። በጌታ ትንሽ ሥር እስክትሰድዱ ድረስ ቆዩ ያልኳቸውም አሉ። ራሳቸውንና የመጀመሪያ ዲግሪ ያገኙበትን ትምህርት በሥራ/በአገልግሎት ላይ ሳይፈትሹት ሁለተኛ ዲግሪአቸውን በሥነ መለኮት እንዳይሠሩ የመከርኳቸውም አሉ። አንዳንዶች ምክሬን ሰምተዋል። ሥነ መለኮት ለመማር የነበራቸው ፍላጎት የተዋቸውም አሉባቸው። እኔ ጨርሶ የከለከልኩት ሰው መኖሩን ግን አላስታውስም።

  • ሕንጸት፡- በቀድሞው የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ታምራት ላይኔ የክርስትና ሕይወት ውስጥ የአንተ ድርሻ ምን ነበር?

መጋቢ በቀለ፡- “ድርሻ” ለመባል የሚበቃ መሆኑን እርግጠኛ አይደለሁም። ከርቼሌ በነበረ ጊዜ መጻሕፍት አውሼዋለሁ። አቶ ታምራት መጻሕፍትን በማንበብ በጣም ብርቱ ሰው ነው። ከርቼሌ ሆኖ የተረጎማቸው፣ በሕያው ተስፋ ሬድዮም ለንባብ ያበቃቸው መጻሕፍት ነበሩ። አልፎ አልፎ በምጎበኘው ወቅት በመጽሐፍ ቅዱሱ ወይም ባዋስኩት መጻሕፍት ዙሪያ እንነጋገራለን። ከተፈታ በኋላ ደግሞ የውሃ ጥምቀት ሥርዐት ለመፈጸም ፍላጎት ስለ ነበረው መሠረታዊ በሆኑት የክርስትና አስተምህሮች ዙሪያ ጥቂት ቁም ነገሮችን ላስጨብጠው ሞክሬአለሁ። ወደ አሜሪካ ሲሄድ ባለቤቱና ልጆቹ ላሉባት ቤተ ክርስቲያን መጋቢ ማስታወሻ ጽፌለታለሁ። ይኸው ነው።

  • ሕንጸት፡- አንዳንድ ሰዎች አቶ ታምራት በሥልጣን ዘመናቸው ሠርተውታል ለሚባሉ “በደሎች” ተገቢውን ይፋዊ ይቅርታ አልጠየቁም ይላሉ። ይቅርታ እንዲጠይቁ አላስተማራችኋቸውም ነበር እንዴ?

መጋቢ በቀለ፡- አቶ ታምራት በእስር ላይ እያለም ሆነ ከተፈታ በኋላ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮች በዙሪያው ነበሩ። ከእነርሱ አንዳንዶቹ አንሥተውበት እንደ ሆነ አላውቅም። እኔ ግን አላነሣሁበትም።

  • ሕንጸት፡- ለምን አላነሣህባቸውም? የንሥሓቸውን ፍሬ ሊያሳዩበት የሚችሉበትን ትልቅ ዕድል ያጡ አይመስልህም?

መጋቢ በቀለ፡- የምትለው ይገባኛል። ትክክልም ነው። እውነቱን ለመናገር፣ አቶ ታምራት እዚህ በነበረ ጊዜ ይህንን ለማድረግ የተመቻቸ ሁኔታ አልነበረውም። ከሄደ በኋላ አድርጎት ይሁን ወይም አይሁን የማውቀው ነገር የለም። እኔ ያላነሣሁበት ምክንያት ግን አለኝ። ሰውን ስለ ኀጢአቱ የሚወቅሰው (convict የሚያደርገው) መንፈስ ቅዱስ ነው። በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ንስሓ ጥልቅ የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ውጤት ነው። አንድ ጊዜ ተደርጎ የሚያበቃለት እንኳን አይደለም። ታላቁ ነቢይ ኢሳይያስ ትዝ ይልሃል? ሕዝቡን ሲወቅሳቸው፣ ሲከስሳቸውና “ወዮላችሁ” ሲል ኖሮ፣ አንድ ቀን ግን እርሱ ራሱ “ጠፍቻለሁ … ወዮልኝ” አለ (ኢሳ. 6)። መንፈስ ቅዱስ ይህንን ሥራ በሰው ሕይወት ውስጥ እንዲሠራ፣ እርሱም ሰውዬውም ጊዜ እና ዕድል ያስፈልጋቸዋል። በዚህ ውስጥ የእኔና የብጤዎቼ ድርሻ ስለ ሰው ኀጢአት ተሰቅሎ መሞት ግድ የሆነበትን ክርስቶስን ከቅዱስ ቃሉ ማሳየት፣ የእግዚአብሔርን ቃል በስፋቱና በጥልቀቱ ማስተማር፣ እግዚአብሔር ራሱ በሰው ሕይወት ውስጥ መሥራት የሚፈልገውን ሥራ ጥንቅቅ አድርጎ እንዲሠራ መጸለይና ለእርሱ መተው ይመስሉኛል።

  • ሕንጸት፡- ከቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ኀላፊነትህ ለምን ለቀቀህ?

መጋቢ በቀለ፡- ልጽፋቸው የማስባቸው መጻሕፍት በውስጤ ነበሩ። ዕድሜዬም እየገፋ እየመጣ ነበር። የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጊዜም ጉልበትም ይጠይቃል። እኔ ደግሞ ሁለቱም አልነበሩኝም።

  • ሕንጸት፡- አሁን በምን መልኩ ነው የምታገለግለው?

መጋቢ በቀለ፡- በቤተ ክርስቲያናችን ደንብ መሠረት፣ መጋቢያኑ ከሽማግሌዎቹ ጋር አብረው የመሪዎች ጉባዔ አባላት ናቸው። የመጋቢነቱንና የአስተዳደሩን ሥራ ይሠራሉ። እኔ አሁን የመሪዎች ጉባዔ አባል አይደለሁም፤ መጋቢ ብቻ ነኝ።

ንጸት፡- በቅርቡ ታሪኩ ቴዎድሮስ (መጋቢ) በቤተ ክርስቲያናችሁ ጉባኤ ላይ የነገረ መለኮት ትምህርትን እያጣጣለና እያራከሰ ሲሰብክ በቦታው ነበርክ። ግለ ሰቡ ነቀፋውን ሲጨርስ እንድትጸልይ ለአንተ ይመስለኛል ዕድሉን የሰጠው። ሆኖም ጉባኤውን በአጭር ጸሎት ከመዝጋት ባለፈ የሰጠኸው ምንም ዐይነት ማስተካከያ አልነበረም ተብሎ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ስምህ ሲነሣ ነበር። እውነት እንደዚያ ነው ያደረግኸው? ከሆነስ ለምን?

“ብዙ ሰዎች የሚያውቁት ‘ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት … የሚያውቅ የለም’ የሚለውን ጥቅስ ብቻ ይመስለኛል።”

መጋቢ በቀለ፡- አዎን! እንደዚያ ነው ያደረግሁት። ነገሩ እንዲህ ነው። ቤተ ክርስቲያናችን በቤተ እምነት ደረጃ አገልጋዮችን እስከ ማስተርስ ዲግሪ ድረስ የምታሠለጥንበት ሴሚናርዮም አላት። በቀጣናም ደረጃ አገልጋዮች በዲፕሎምና በመጀመሪያ ዲግሪ የሚሠለጥኑባቸው ብዙ ኮሌጆች አሉን። በአጥቢያም ደረጃ አገልጋዮችን በሰርቲፊኬትና በዲፕሎማ መርሓ ግብር የሚያስመርቁ አሉ። በቀጣና ሁለት አጥቢያ ምእመናን ሁሉ፣ በቤት ኅብረቶችና በወጣት ቡድኖች የሚያጠኗቸው የተለያዩ ትምህርቶች በማእከል እየተዘጋጁ ይሠራጫሉ። ረቡእ ረቡእ ለምእመናን ሁሉ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መርሓ ግብርም አለን። በየክረምቱም ለሁለት ወራት ያህል የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮርሶችን እንሰጣለን። በዚያን እሑድ በቤተ ክርስቲያናችን ያገለገለው መጋቢ ታሪኩ፣ ቀድሞ የእኛ አገልጋይ ስለ ነበረ ይህንን አሠራራችንን አሳምሮ ያውቃል።

እርግጥ ነው፣ በጊዜው እርሱንም ያስቆጣው ነገር ነበረ። ቢሆንም እንኳን ቁጣውን ዋጥ ማድረግ ነበረበት። እርሱ ግን በተቃራኒው “ቴዎሎጂን ጠቅልላችሁ ብሉት” እስከ ማለት ደረሰ። አክብራ በጋበዘችው ቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ ቆሞ የጋበዘችውን ቤተ ክርስቲያን መሳደብ ጨዋነት የጎደለው ድርጊት ነው። ለዕለቱ መርሓ ግብር ተዘጋጅቶ የመጣም አልመሰለኝም። እርሱ ሲጮኸ፣ ጉባዔውንም ሲያስጮኽ የተመደበለት ሰዓት ጥሎት ነጎደ። “ቅዳሴው ቢያልቅበት ቀረርቶ ሞላበት” እንደሚባለው ደብተራ ሆነብኝ። በጣም አዘንኩ፤ ተናደድኩም። ይባስ ብሎ፣ አገልግሎቱን ሲጨርስ መርሓ ግብሩን በጸሎት እንድዘጋ ጋበዘኝ። ማኖ ሊያስነካኝ የፈለገ ሁሉ መሰለኝ።

በመጀመሪያ የተሰማኝ ስሜት “እምቢ” ልለው ነበር። ነገር ግን፣ ይህ የቤተ ክርስቲያን ጉባዔ ነው። በውስጡ ያሉት  በጣም ብዙ ዐይነት ሰዎች ናቸው። “እምቢ” ብለው ወይም ለተናገራቸው ስሕተቶች ወዲያውኑ ማስተካከያ ብሰጥ ደስ የሚላቸው ይኖሩ ይሆናል። ግራ የሚጋቡትና የሚሰነካከሉት ሰዎች ቁጥር ግን እጅግ ያመዝናል። ከሁሉ በላይ፣ የሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን የምትከተለው የቡድን አመራር (corporate leadership) ነው። አገልጋዩን የጋበዘው አመራሩ ነው። የጋበዘውን አገልጋይ የመገሠጽም ሆነ የሠራቸውን ስሕተቶች የማስተካከል ኀላፊነት ያለውም በአመራሩ እጅ ነው። የአመራሩ አባላትም እዚያው አሉ። ቢፈልጉ አጭር ምክክር አድርገው ወዲያውኑ፣ ቢፈልጉ ደግሞ በቆይታ ተነጋግረው በሌላ ጊዜ መደረግ ያለበትን ያደርጋሉ። ስለዚህ እኔ የመዝጊያ ጸሎት ጸልዬ ብቻ ከመድረኩ ወረድኩ።

ያን ከሰዓት በኋላ ብዙ የስልክ ጥሪዎች ደረሱኝ። ደዋዮቹ እኔ ወይም ሌሎቹ መሪዎች የእርምት እርምጃ ሳንወስድ የመርሓ ግብሩ ፍጻሜ በመሆኑ ያዘኑ ሰዎች ነበሩ። ይህ ሳይደረግ መርሓ ግብሩን በጸሎት በመዝጋቴ የተቆጡም ነበሩ። ከአለቆቼ አካባቢ ሳይቀር ተደውሎልኝ እንደዚያ ተብያለሁ። “የቤተ ክርስቲያኗ አባል ብሆን ኖሮ፣ ያንን አገልጋይ ጎሮሮውን አንቄ ከመድረክ ላይ አወርደው ነበር” ያለኝም ሰው አለ። እኔ የማኅበራዊ ሚድያዎች ብዙ ተጠቃሚ ባልሆንም፣ እዚያም ላይ የሆነ የሆነ ነገር እንደ ተባለ ሰምቻለሁ። በዚህ የተነሣ ሳምንቱን ሁሉ ስሜቴ እንደ ደፈረሰ ነበር የሰነበትኩት። የሚገርመው ነገር፣ ይኸው መጋቢ በሌላ ጊዜ የሆነ ቦታ አግኝቶኝ “ስብከቴን እንዳልወደድከው ከፊትህ ላይ አውቄው ነበር፤ በኋላ ደግሞ ʻማስተዋልን ስጠውʼ ብለህ ጸለይክልኝ አይደል?” ሲል ወቅሶኛል።

  • ሕንጸት፡- በተያያዘም “ፉርሽካ” የሚል ቃል በጉባኤ ተጠቅመህ፣ ይቅርታ ጠይቀሃል ሲባል ሰምቻለሁ። እሱስ ምንድን ነው የሆነው?

መጋቢ በቀለ፡- ይሄኛው የሆነው ያኛው በሆነ በሳምንቱ ነው። በዚህኛው መርሓ ግብር ላይ አገልጋይ የነበረው ሰው ደግሞ በደንብ የተዘጋጀበትን፣ እኔን በተለይ አንጀቴን ያራሰኝን ትምህርት አስተማረ። እጅግ በጣም ደስ አለኝ። አገልግሎቱን ሲጨርስ ይሄኛውም አገልጋይ መርሓ ግብሩን በጸሎት እንድዘጋ ጋበዘኝ። በጣም ደስ ብሎኝ ስለ ነበረ፣ “እንዲህ ነው እንጂ!” በሚል ዐይነት አነጋገር ሰባኪያኑን የእግዚአብሔርን ሕዝብ “ፉሩሽካ” እንዳይመግቡት ጠየቅሁ። በዚያ ቃል በመጠቀሜ መንፈሴ በኀዘን የተመታው ገና ከመድረኩ ስወርድ ነበር። እና በጣም አዘንኩ። ወዲያውኑም እግዚአብሔርን ምሕረት ለመንኩት። አንዳንድ አገልጋዮችም ንግግሬ እንደ ጎዳቸው ገለጹልኝ። መሪዎችም ጠርተው የዚያ ዐይነት ንግግር ከእኔ እንደማይጠበቅ ነገሩኝ። እኔም የሆነውን ሁሉ አስረድቼ ይቅርታ ጠየቅኋቸው። እነርሱም ጉባዔውንም ጭምር ይቅርታ እንድጠይቅ አሳሰቡኝ። እኔም በደስታ ጉባዔውን ይቅርታ ጠየቅሁ። ይሄ ነው የሆነው።

  • ሕንጸት፡- ቤተ ክርስቲያኒቱ በመጋቢ ታሪኩም ሆነ በተናገረው ነገር ላይ የወሰደችው ምን ዐይነት የእርምት እርምጃ አለ?

መጋቢ በቀለ፡- በእሑድ ጉባዔ ላይ ሲነገር የሰማሁት ነገር የለም። እኔ የመሪዎች ጉባዔ አባል ስላልሆንሁ ከአገልጋዩ ጋር በግል የተደረገ ነገር ካለ አላወቅሁም።

  • ሕንጸት፡- ግለ ታሪክህ እንደሚናገረው በተለያዩ ፍልስፍናዎች ውስጥ አልፈሃል፤ ምናልባት ብዙዎች እንደሚወቅሱህ አንዳንድ ጊዜ ግልጽ አቋም ለመያዝ የምትቸገረው ለዚህ ይሆን? አንተም ራስህ “የአቋም መዋዠቅ” ውስጥ በመግባትህ ራስህን እንደ ወቀስህ ጽፈሃል።

መጋቢ በቀለ፡- ከቀድሞም ጀምሮ አቋም ልይዝበት በሚገባኝ ጉዳይ ላይ አቋም ለመያዝ፣ አቋሜን መለወጥ በሚያስፈልገኝ ጉዳይም ላይ አቋሜን ለመቀየር ብዙ ተቸግሬ አላውቅም። ከእኔ ዐሳብ ጋር ቢቃረንም፣ የሌላን ሰው ዐሳብ የማከብርም ይመስለኛል። ዐሳብን የመግለጽ ነጻነትን በተመለከተ ፈረንሳዊው ፈላስፋ ቮልቴር አለው የሚባለው ዝነኛ አነጋገር የተዋጠልኝ ከዛሬ 53 ዓመታት በፊት ነው፡- “I disapprove of what you say; but I will defend to the death your right to say it.” (በምትለው አልስማማም፤ ልትለው ያለህን መብት ለማስከበር ግን እስከ ሞት ድረስ እቆማለሁ) እንደ ማለት ነው። እና የዚህ ዐይነቱ የአቋም መዋዠቅ በእኔ አስተያየት አዎንታዊ ነው። አንተ ካልከው በተቃራኒው እነዚያ ፍልስፍናዎች ናቸው እንደዚህ flexible እንድሆን የረዱኝ።

“ከእኔ ዐሳብ ጋር ቢቃረንም፣ የሌላን ሰው ዐሳብ የማከብርም
ይመስለኛል።”

  • ሕንጸት፡- “ጋሽ በቀለ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከመሥመሩ እየለቀቀ ነው” የሚሉህ ሰዎች አሉ። ለዚህ ደግሞ እንደ ምክንያትነት ከሚያቀርቡት መካከል ከታምራት ታረቀኝ (“ነቢይ”) ጋር ያለህን ግንኙነት በማንሣት ነው። ይህን በማድረግህ ከመሥመር እየወጣህ እንዳለህ ይሰማኻል?

መጋቢ በቀለ፡- በፍጹም አይሰማኝም። ለምን መሰለህ? ይቅርታ አድርግልኝና ትንሽ ወደ ኋላ ልመልስህ። እኔ ወደ ጌታ የመጣሁባቸው ዓመታት በሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የብርቱ ጦርነት ዓመታት ነበሩ። ቤተ ክርስቲያኗ በዲሞኖሎጂ (demonology) እና በደሊቨራንስ (deliverance) ትምህርት የተነሣ ተከፋፍላ ነበር። በትምህርቱ ውስጥ ክርስቲያን በአጋንንት ሊያዝ ይችላል፤ አጋንንት ከሰው ውስጥ በሚወጡ ጊዜ በማስጮኽ ብቻ ሳይሆን በማስፋሸክና በማስታወክ፣ በማስገሳትና በማስፈሳት ጭምር ሊሆን ይችላል፤ ክርስቲያን መንፈሱ ነው የዳነው እንጂ ሥጋው በአጋንንት ሊያዝ ይችላል የሚሉ ነገሮች ነበሩ። አጋንንት አንተ ወደ መኝታህ ስትሄድ አልጋህ ውስጥ፣ ሚስትህ ወደ ማድቤት ስትገባ ምድጃ ሥር፣ የትም ቦታ አድፍጠው ሊጠብቋችሁ ይችላሉ የሚል ዐይነት ወሬ ሁሉ እንሰማ ነበር።

እንደʼኔ ላለ፣ በክህደት ፍልስፍናዎች ሲንገላታ ለኖረ፣ በጌታም ገና ላልጠነከረ ሰው ሁኔታው ምን ያህል ከባድ እንደ ነበረ ልነግርህ አልችልም። እግዚአብሔር በታላቅ ምሕረቱ ባይጠነቀቅልኝ ኖሮ በሕይወት አልኖርም ነበር። በሕይወትም ብኖር ባለ ጤናማ አእምሮ አልሆንም ነበር። በኋላ እንደ ተረዳሁት፣ ትምህርቱን የሚያራምዱት በአሜሪካን አገር የሚኖሩ በጣም የታወቁ ጴንጤቆስጤአውያን መምህራን ናቸው። በጊዜው ከሁሉም ይልቅ ትልቅ የሚባለው የAssembleys of God ቤተ እምነት ትምህርቱን አውግዞታል ሲባልም ሰምቻለሁ። ከትምህርቱ አራማጆችም ውስጥ አብዛኞቹ የእነርሱ አባላት የነበሩ ይመስለኛል።

“የዚህ ዐይነቱ የአቋም መዋዠቅ በእኔ አስተያየት አዎንታዊ ነው።”

በኢትዮጵያ ውስጥ ያንን ትምህርት ተቀብለዋል ከሚባሉት የሙሉ ወንጌል አገልጋዮች መካከል ስሙ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሰው ሰው ጋሽ አሰፋ ዓለሙ ነበር። ጋሽ አሰፋ ከመጀመሪያዎቹ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሽማግሌዎች መካከል አንዱ ነበረ። ከመጀመሪያዎቹ ሁለት ወንጌላውያንም መካከል አንዱ ነው። በጊዜው እኔ ጋሽ አሰፋን በዓይኔ አይቼው፣ ሲያስተምርም ሰምቼው አላውቅም። ሆኖም ስለርሱ ሲወራ ከሰማሁት በመነሣት በጣም ጠልቼዋለሁ። ስለ እርሱ የሰማኋቸውን መጥፎ መጥፎ ነገሮችም ለሌሎች ሰዎች አውርቻለሁ፤ ምናልባትም ጨማምሬ። በጊዜው ያንን ማድረግ ራሱ እንደ ትልቅ አገልግሎት ነበር የሚቆጠረው።

ወደ አዲስ አበባ ከተዛወርኩ በኋላ፣ በ1971 ዓ.ም. ይመስለኛል አንድ ዓርብ ቀን ምሽት ከቢሮ ወጥቼ ወደ ፓ/ር መርዕድ ለማ ቤት ሄድኩ። የእኔ ቢሮ እና የእርሱ መኖሪያ ቤት ቅርብ ለቅርብ ነበሩ። በዚያም ፓ/ር መርዕድንና ወንጌላዊ ጻድቁ አብዶን (አሁን መጋቢ) አብረው አገኘኋቸው። ስለ ምን እየተጫወቱ እንደ ነበረ አላውቅም፤ ብቻ በጨዋታቸው መካከል ጋሽ አሰፋ ዓለሙን አነሡት፤ በጣም በበጎ ጎኑ። በእርሱ አገልግሎት ይታይ ስለ ነበረው አስደናቂ የሆነ መናፍስትን የመለየት ስጦታ እየተቀባበሉ ሲናገሩ ሰማኋቸው። “ያንን ልምምድ ክርስቲያን በአጋንንት ሊያዝ ይችላል ከሚለው የደሊቨራንስ አስተምህሮ ጋር ባያያይዘው ኖሮ፣ ማንም ምንም ሳይለው በአገልግሎቱ ተወድዶና ተከብሮ ይቀጥል ነበር። ቤተ ክርስቲያንም እጅግ በብዙ ትጠቀምበት ነበር” እያሉ ክፉኛ ሲቆጩ ሰማኋቸው።

በእምነት አባቶቼ አድርጌ የምቆጥራቸው እነዚህ አገልጋዮች ስለ ጋሽ አሰፋ እንደዚያ ሲናገሩ ስሰማቸው፣ እኔ በእርሱ ላይ ስለ ተናገርኳቸው መጥፎ ነገሮች ራሴን ተጸየፍኩት። ጨዋታቸው አልቆ ወደ ቤቴ ለመሄድና በእግዚአብሔር ፊት ለመውደቅ ቸኮልኩ። ከቤቴ እንደ ደረስኩም እንደዚያ አደረግሁ። እግዚአብሔር ፈቅዶ እርሱን በማገኘው ጊዜ ይቅርታ ልጠይቀው ለእግዚአብሔር ቃል ገባሁ። የእኛ ቤተ ክርስቲያን ዝግ ስለ ነበረች ለአምልኮ እሄድ የነበረው ወደ መሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ነበር። በሚቀጥለው እሑድ እንደ ልማዴ ወደዚያው ሄድኩ። ቦታ ስለሌለ ውጭ ነበር የቆምኩት። የዕለቱን ሰባኪ ለጉባዔው ሲያስተዋውቁ ስሙን ሳልሰማ ቀርቻለሁ። መልእክቱ ግን ግሩምና ውስጤን በእጅጉ ያረሰረሰ እንደ ነበረ አስታውሳለሁ። ሰባኪው ስብከቱን ሲጨርስ ፓ/ር ዳንኤል የሰባኪውን ስም ጠርቶ ሲባርከው ሰማሁ። ለካ ጋሽ አሰፋ ኖሯል። ከትናንት በስቲያ ማታ ንስሓ ገብቼ ባይሆን ኖሮ፣ ያ መልእክት ሊያስመልሰኝ ሳይተናነቀኝ እንደማይቀር ከልምድ አውቀዋለሁ።

“ጋሽ አሰፋ ከመጀመሪያዎቹ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሽማግሌዎች መካከል አንዱ ነበረ . . . ፓ/ር መርዕድንና ወንጌላዊ ጻድቁ አብዶን (አሁን መጋቢ) አብረው አገኘኋቸው። ስለ ምን እየተጫወቱ እንደ ነበረ አላውቅም፤ ብቻ በጨዋታቸው መካከል ጋሽ አሰፋ ዓለሙን አነሡት፤ በጣም በበጎ ጎኑ። ‘ቤተ ክርስቲያንም እጅግ በብዙ ትጠቀምበት ነበር’ እያሉ ክፉኛ ሲቆጩ ሰማኋቸው።”

በዕለቱ ይቅርታ ልጠይቀው አልቻልኩም። ከዚያም ሳንገናኝ እርሱ ወደ ኬንያ ሄደ። ከብዙ ዓመታት በኋላ ለሥራ ወደ ኬንያ በሄድኩ ጊዜ ተገናኘን። ሆኖም ሁኔታው ስላልተመቻቸልኝ ይቅርታ ሳልጠይቀው ቀረሁ። በመጨረሻ በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር በ1990 አሜሪካን አገር ቺካጎ ኮንፈረንስ ላይ ተገናኘንና ነገሩን ሁሉ አስረድቼው ይቅርታ ጠየቅሁት።

በዲሞኖሎጂ እና በደሊቨራንስ ትምህርት ዙሪያ በሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተነሣውን ያንን ውዝግብ፣ ሰይጣን በኢትዮጵያ የፈነዳውን ያንን ጴንጤቆስጤአዊ ሪቫይቫል ለማሽመድመድና በአጭሩ ለመቅጨት በእጅጉ እንደ ተጠቀመበት፣ በጊዜው በሁለቱም ጎራዎች ከነበሩት አገልጋዮች አለማስተዋል የተነሣም እንደ ተሳካለት ብዙዎች በጉባዔ ሳይቀር ሲናገሩ ሰምቼ አውቃለሁ። በዚያኛው ጎራ ውስጥ ያሉት ወገኖች ፆምና ጸሎት ያዘወትሩ ስለ ነበረ፣ በዚህኛው ጎራ ውስጥ ባሉት ወገኖች ዘንድ ፆምና ጸሎት ማዘውተር ተፈራ። እነዚያኞቹ መገሠጽ ያበዙ ስለ ነበረ፣ በእነዚህኞቹ ዘንድ አጋንንትን “በኢየሱስ ስም!” ብሎ መገሠጽ ቀረ። እነዚህ ልምምዶች ወደ ቤተ ክርስቲያናችን የተመለሱት ከረዥም ጊዜና ከብዙ ለቅሶ በኋላ ነው። አሁንም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ለመመለሳቸው በጣም እርግጠኛ አይደለሁም።

ዛሬ በነቢይ ታምራት አገልግሎት ዙሪያ የሚነፍሱት ወሬዎች ያንን ዘመን ነው የሚያስታውሱኝ። የሚባሉት ነገሮች ሆነው ከሆነም ዓመታት አልፏቸዋል። እውነት ቢሆኑ እንኳን፣ ሰውየው ዛሬም እዚያው ላይ መሆኑን ወይም አለመሆኑን ጠጋ ብሎ ለማጣራት ሙከራ የሚያደርግ ሰው የለም። አንድ አገልጋይ የተሰቀለውን ክርስቶስን በግልጽ ሲሰብክ ከመስማት፣ በአገልግሎቱ በጣም ብዙ ሰዎች ጌታ ኢየሱስን የግል አዳኛቸው አድርገው ሲቀበሉ ከማየት፣ አጋንንትን በጌታ በኢየሱስ ስም እያዘዘ በአደባባይ ሲያስወጣና ለሕሙማንም በጌታ በኢየሱስ ስም እየጸለየ በአደባባይ ሲፈወሱ ከመመልከት ሌላ ምን እንደምንፈልግ አይገባኝም። ሰይጣን የተሰቀለውን ክርስቶስን ይሰብካል ነው የምንለው? አጋንንትም አጋንንትን ያስወጣሉ ነው የምንለው? ጌታ እንደዚያ አላስተማረንም። መጽሐፉም እንደዚያ አይልም። የባሕርይ ጕዳይ የሆነ እንደ ሆነ፣ የመጠን ልዩነት ካልሆነ በስተቀር፣ እኔን ጨምሮ ማንኛችንም ከድካም ነጻ አይደለንም። ደግሞስ “ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት” (ገላ. 6፥1) የሚለውን ኀይለ ቃል እንዴት ነው በተግባር የምንተረጉመው?

  • ሕንጸት፡- “ይነፍሳሉ” ያልካቸው “ወሬዎች” ብቻ ስለ መሆናቸው ምን ማስረጃ አለህ? ወይስ አንተ በግልህ ያደረግኸው የማጣራት ሂደት አለ? ከአንድ ወገን ብቻ ሰምተህ እንዳይሆን?

መጋቢ በቀለ፡- ከሳሾቹ የሚሉትን ከተጻፉበት መጽሔቶች አንብቤአለሁ። በማኅበራዊ ሚድያዎች የተባለውንም ሰምቻለሁ። በግንባር ያነጋገሩኝ ግለ ሰቦችና የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም አሉ። ለሚሰነዘሩበት ክሶች ሁሉ ታምራት የሚሰጣቸውን መልሶች ደግሞ ከራሱ አፍ ሰምቻለሁ። እነዚህን ሁሉ እኔ ለግል ፍጆታዬ ተጠቅሜባቸዋለሁ። አንተ ደግሞ እንደ ጋዜጠኛ ከእኔም የተሻለ ማድረግ ትችላለህ ብዬም ዐስባለሁ።

  • ሕንጸት፡- ከአብያተ ክርስቲያናት ተቃውሞ የሚደርስበት እንደ ሆነ የሰማህ ይመስለኛል። ታዲያ ማነው ትክክል? አንተ ወይስ አብያተ ክርስቲያናቱ?

መጋቢ በቀለ፡- እኔ እስከማውቀው ድረስ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ነቢይ ታምራትን አላወገዘውም። አሁንም እኔ እስከማውቀው ድረስ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያሉት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የራሳቸው የሆነ ከተማ አቀፍ ኅብረት የላቸውም። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ያሏቸው በአገር አቀፉ ኅብረት ሥር የተደራጁ የዞኖች ኅብረቶች ናቸው። በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያሉት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በደብረ ዘይት ወይም በናዝሬት ወይም በአምቦ ከተሞች እንዳሉት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በቀጥታ ለእነርሱ ተጠሪ የሆነ ኅብረት የላቸውም ማለቴ ነው። ቲ. ቢ. ጆሽዋን ወደ አዲስ አበባ የመጋበዝ ጉዳይ የዚያን ያህል ውዝግብ ያስነሣው ለምን ይመስልሃል? ቲ. ቢ. ጆሽዋ ወደ ጅማ ወይም ወደ ድሬዳዋ ወይም ወደ ጅጅጋ ተጋብዞ ቢሆን ኖሮ የዚያን ያህል ውዝግብ የሚኖር ይመስልሃል?

እና “አብያተ ክርስቲያናት ተቃወሙት” የምትለውን ነቢይ ታምራትን የትኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው የተቃወሙት? የዛሬ ዓመት ይሁን ወይም ሁለት ዓመት ገደማ በሚሌንየም አዳራሽ አዘጋጅቶት የነበረውን ኮንፈረንስ በማኅበራዊ ሚድያዎችና አንዳንድ ባለ ሥልጣኖችን በመጠቀም ያስቆሙት ግለ ሰቦች ናቸው። በእኔ አስተያየት፣ የዚያ ዐይነቱ አካሄድ ከእኛ የሚጠበቅ አይደለም። ወንጌልን በሚሰብክ ሰው ላይ ይቅርና በሌላ በማናቸውም የሃይማኖት ሰባኪ ላይ እንደዚያ ሊደረግ አይገባም። አገሪቱ ከምትመራበት ሕገ መንግሥትም ጋር ይጣረሳል። በደብዳቤና በመጽሔት የተቃወሙት ጥቂት አብያተ ክርስቲያናት እንዳሉ አውቃለሁ። ያንን ተቃውሞ እኔ የአዲስ አበባ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ድምፅ ነው አልለውም። ለወዲያኛውም ቢሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያሉ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ድምፃቸውን የሚያሰሙበት የራሳቸው የሆነ ፎረም እንደሚያስፈልጋቸው ነው እኔ የማምነው።

  • ሕንጸት፡- ምናልባት አንተ ባልከው መልኩ አብያተ ክርስቲያናቱ አልተዋቀሩ ይሆናል። እንደ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል፣ የአንተ ቤተ እምነት አጥቢያን ጨምሮ በኮልፌ አካባቢ ያሉ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ተቃውሟቸውን በግልጽ አሰምተዋል። በሚሌንየም አዳራሽ ሊካሄድ የነበረው ኮንፈረንስም በኅብረቱ የቦርድ አመራር አካላት በኩል በተደረገ እንቅስቃሴ እንጂ አንተ ባልከው መንገድ አይመስለኝም።

መጋቢ በቀለ፡- ነቢይ ታምራትንና አገልግሎቱን በተመለከተ ማለት ያፈለግሁትን ያልኩ ይመስለኛል። ኀጢአትን እሹሩሩ እንበል ግን አላልኩም። ወንጌላውያኑ አብያተ ክርስቲያናት በአገር አቀፍ ደረጃ ኅብረት መሥርተን አብረን እያገለገልን ያለነው አንዳችን የሌላችንን አስተምህሮና ልምምድ መቶ በመቶ ስለምናጸድቅ (endorse ስለምናደርግ) አይደለም። በመካከላችን ያሉት የአስተምህሮና የልምምድ ልዩነቶች መሠረታዊ አይደሉም ብለን ስለምናምን ነው። እኔ የምለው ባጭሩ፣ ይህንን ዕድል ለታምራትስ ለምን እንነፍገዋለን? ነው።

  • ሕንጸት፡- አንድ በቤተ ክርስቲያን አመራር ደረጃ ላይ ያለ ሰው የምግባርም ሆነ የአስተምህሮ/የልምምድ ችግር አለበት ሲባል፣ ግለ ሰቡን ለማቅናት የሚደረገው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አካሄድ ምን ዐይነት መሆን አለበት ትላለህ? ይህን ጥያቄ የማነሣው፣ ታምራት ሠርቷቸዋል ለሚባሉ ስሕተቶች በተገቢው መንገድ ማስተባበያ ሳይሰጥ ወይም ደግሞ በአንጻሩ ይፋዊ ይቅርታ ሳይጠይቅ ነው አንተ በእርሱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ቀርበህ የታየኸው። ዕውቅና ለመስጠት የቸኮልክ አይመስልህም?

መጋቢ በቀለ፡- እኔስ እሺ “ቸኮልክ” ተባልኩ። በመቸኮልና በመዘግየት መካከል ያለው ሚዛን ጠፍቶብኝ ይሆናል። በመኻሉ በእግዚአብሔርም መንግሥት አገልግሎት ላይ እየደረሰ ላለው ጉዳት ግን ተጠያቂው ማነው? ጥያቄህን በጥያቄ የምመልሰው ለሞጋች ጥያቄዎችህ ሞጋች መልሶች ለመስጠት ፈልጌ አይደለም። ሌላ መልስ ሽቼ ወይም አተካራ ለማንሣት ብዬም አይደለም። እንደ ሥጋዊው ሁሉ፣ በመንፈሳዊውም ጦርነት ውስጥ ከሁለቱም ወገን ብዙ ሰዎች እንደሚቆስሉ፣ ብዙዎችም እንደሚወድቁ ከልምድ ስለማውቅ ብቻ ነው።

  • ሕንጸት፡- እውን ጋሽ በቄ፣ ልንጠነቀቃቸውና ልንከላከላቸው የምንችላቸው ስሑት ልምምዶችም ሆኑ አስተምህሮዎች የሉም እያልክ ነው?

መጋቢ በቀለ፡- አላልኩም። ምን ጊዜም ቢሆን፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ዓሣ እንደሚበላ ሰው ነው መሆን ያለበት። “ዓሣን መብላት በብልሃት” ይባል የለ? የእግዚአብሔርን ቃል ብቻ ነው እንዳለ የምንውጠው። ሌላውን ሁሉ በጠቅጣቃ ወንፊት ውስጥ እናሳልፈዋለን። ይህንን ማድረግ እንደሚጠበቅብን መጽሐፉ ራሱ ነው የሚመክረን። አገልጋዮችም ይህንን ከአምላክ የተሰጠንን መብት ሊጋፉ አይገባቸውም። እኛም አንፈቅድላቸውም። ለምሳሌ ወንጌላውያኑ ምእመናን ሰዎች ወደ መላእክት መጸለይ እንደሌለብን ስናስተምር ኖረናል። አሁን ግን “መላእክትን አዝዛቸዋለሁ” የሚሉ አገልጋዮች በመካከላችን ብቅ እያሉ ነው። በእውነት እንደዚህ ማድረግ ይቻላል? ዛሬ እናዝዛቸዋለን ያሏቸውን ነገ እንለምናቸዋለን ቢሉንስ? ወይስ አንድ አገልጋይ ሕሙማንን እንደሚፈውስ መናገር ይችላል? ፈዋሹ ጌታ እና ጌታ ብቻ አይደለም? ይህ አፍ ወለምታ ብቻ ነው? ለጸሎታችን እና ለስብከታችን ክፍያ መጠየቅስ እንችላለን? በከንቱ አይደለም የተቀበልነው? በከንቱ የተቀበልነውን በከንቱ እንድንሰጥስ አልታዘዝንም?

  • ሕንጸት፡- “ከሌሊቱ ስንት ሰዓት ነው?” በተሰኘው መጽሐፍህ ላይ የጌታን ዳግም ምፅዐት፣ ዘመን አስልተህ በዚህ ጊዜ የሚሆን ይመስለኛል ብለሃል። ጋሽ በቄ፤ በርግጥ ያንን ያህል እንቅጩን መናገር ነበረብህ? መጽሐፍ ቅዱሳዊስ ይመስልሃል?

መጋቢ በቀለ፡- እቅጩንማ አልተናገርኩም። ያልተናገርኩት ስለማላውቀው ነው። ሆኖም በሉቃስ ወንጌል 21፥32 ላይ ያለውን የጌታን ንግግር እንደዚያ የሚተረጉሙት ሊቃውንት እንዳሉ ተናግሬአለሁ። ካነሣኸውስ የዓለሙን ሁኔታ ስንመለከት፣ እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎችም ጭምር የዚያን ያህል መቆየታችንን መጠራጠር ጀምረናል።

  • ሕንጸት፡- 37 ዓመት እኮ ብለሃል?

መጋቢ በቀለ፡- ብዙ ሰዎች የሚያውቁት “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት … የሚያውቅ የለም” የሚለውን ጥቅስ (ማቴ. 24፥36) ብቻ ይመስለኛል። “… እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ ዕወቁ” የሚለውሳ?” (ማቴ. 24፥33)፤ “እናንተ ግን … ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም …” የሚለውሳ? (1ተሰ. 5፥4-5)

ንጸት፡- ልክ እንደ ዛው “በደጅ እንደ ቀረበ ዕወቁ” ማለት ብቻ ነዋ?

መጋቢ በቀለ፡- ሳቅ…

  • ሕንጸት፡- “ጣልቃ እየገባ በተሰኘው ግለ ታሪክህ ላይ “… አሳብ ደግሞ – ሥጋዊውም ሆነ መንፈሳዊው – ዛሬም ቢሆን ብዙ ጊዜ ነው የሚጠጥርብኝ።” (ገጽ 142) ብለህ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሠራኻቸው የሚባሉ ስሕተቶች ከዚህ የሚመነጭ ይሆን?

መጋቢ በቀለ፡- ሠራኋቸው የሚባሉት ስሕተቶች ይነገሩኝና በእነርሱ ዙሪያ እንነጋገር። በተረፈ ይሄኛው ጥያቄ ድፍን ቅል ነው።

  • ሕንጸት፡- ቅሉን እንስበረው፤ ለምሳሌ የጌታን ዳግም ምፅዓት ዓመት ጠቅሶ ማስቀመጥ፣ ከአስተምህሯዊ ጥንቃቄ ይልቅ ተገለጡ ለሚባሉ “ድንቆችንና ተኣምራት” ያለህ ሥሡነት።

መጋቢ በቀለ፡- ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከ1,960 ዓመታት በፊት ጌታ በእርሱ ዕድሜ እንደሚመጣ ለተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን ሲጽፍላት (1ተሰ. 4፥15-17) ምን እየሆነ ነው የነበረው? ጠንቃቃ ወይስ ሥሡ?

  • ሕንጸት፡- መቼም የጠቀስከው ሐዋርያም ሆነ ሌሎቹ ለአስተምህሮ ንፅሕና እጅግ ጠንቃቆች እንደ ነበሩ ነው የምረዳው። የጠቀስከው የተሰሎንቄ መልእክት የተጻፈውም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ይመስለኛል።
  • ሕንጸት፡- እሺ፤ ወደ ሌላኛው ጥያቄዬ ልለፍ። የነገረ መለኮት ትምህርት አለመማርህ በአገልግሎትህ ላይ ክፍተት እንዳመጣብህ ታስባለህ?

መጋቢ በቀለ፡- ዐላስብም። ምክንያቱም ነገረ መለኮት ለመማር ብዙ ጸሎትም፣ ብዙ ጥረትም አድርጌ አልተሳካልኝም። ያ ለእኔ የእግዚአብሔር ፈቃድ ስላልመሰለኝ፣ ከ1977 ዓ.ም. መጨረሻ ገደማ ጀምሮ እርግፍ አድርጌ ትቼዋለሁ።

  • ሕንጸት፡- ጋሽ በቀለ የሪቫይቫል አቀንቃኝ ከመሆኑ የተነሣ ሁሉንም እንቅስቃሴዎች ያለ ማጥለያ ያግበሰብሳል የሚሉህ ሰዎች እየተበራከቱ መጥተዋል። ለእነዚህ ሰዎች ምን ምላሽ አለህ?

መጋቢ በቀለ፡- እንደዚህ የሚሉኝ ሰዎች ሁለት ወይም ሦስት የሪቫይቫል እንቅስቃሴዎችን በማጥለያቸው ያጠለሉና የጣሉ ሰዎች ከሆኑ፣ ከእነርሱ ጋር ስለ ጣሉአቸው እንቅስቃሴዎችና ስለ ማጥለያቸው ለመነጋገር በጣም ፈቃደኛ ነኝ። ሕንጸት መድረኩን ሊያመቻችልን ይችላል። እኔ እንደሚመስለኝ፣ ከኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሪዎችና አገልጋዮች አብዛኞቹ ከምቾት ቀጣናቸው (comfort zone) ለመውጣት በጣም ይፈራሉ። ይህም በብዙ ሰው ዘንድ ያለ ድካም ነውና አልፈርድባቸውም።

  • ሕንጸት፡- ኢትዮጵያን ማእከል ያደርጋል የተባለው “የመጨረሻው ሪቫይቫል” አስተሳሰብ ምንጩ ብርቱ የኢትዮጵያዊነት ፍቅር ይሆን?

መጋቢ በቀለ፡- አይደለም። “ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረገ” ማለቴንም አላስታውስም። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቁልፍ ሚና ትጫወታለች ያልኩ ነው የሚመስለኝ። እንደዚያ ማለት፣ ሌሎች ማእከሎች አይኖሩም ማለትም አይደለም። ላልኳቸው ነገሮች ከቃለ እግዚአብሔር፣ ከትንቢቶችና ከታሪክ ማስረጃዎችን ጠቅሻለሁ። ከዚህ ያለፈ ምን እንዳደርግ እንደሚጠበቅብኝ ቢነገረኝ ደስ ይለኛል።

  • ሕንጸት፡- የአንተ የሪቫይቫል ትርክት (በኢትዮጵያ) ከጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ ጋር እጅጉኑ ሲያያዝ ይስተዋላል። ከዚያ ውጪ ሪቫይቫል የለም እንዴ?

መጋቢ በቀለ፡- አለ። ትልቁ የ15ኛው ምዕት ዓመቱ የደቂቀ እስጢፋኖስ የተሐድሶ ንቅናቄ ነው። በ19ኛው ምዕት ዓመት በኤርትራ፣ በትግራይና በጎንደር ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የታየውን ንቅናቄም “ሪቫይቫል” ማለት ይቻላል። በ20ኛው ምዕት ዓመት መጀመሪያ ላይ በምዕራብና በደቡብ ኢትዮጵያ የተነሡት መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ግን ሪቫይቫል አይባሉም። የማይባሉበት ምክንያት የተነሡት በአማኞች መካከል ሳይሆን፣ በአረማውያን መካከል ስለ ሆነ ነው። ሪቫይቫል ወደ አላማኞች መፍሰሱ የማይቀር ቢሆንም፣ ያ የሚሆነው ግን በሁለተኛ ደረጃ ነው። ስለዚህ እነዚያን ብርቱ የሆኑ የወንጌል ሥርጭት ወይም የሚስዮናዊነት ንቅናቄዎች ነው የምንላቸው። በ1960ዎቹ በጎሬ ቤቴል ቤተ ክርስቲያን፣ በ1970ዎቹ ውስጥ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ፣ መጀመሪያ በመሠረተ ክርስቶስ፣ ቀጥሎም በመካኒሳና በእንጦጦ መካነ ኢየሱስ አብያተ ክርስቲያናት የተነሡት መለስተኛ ሪቫይቫሎች ሁሉም ጴንጤቆስጤአዊ ሪቫይቫሎች ነበሩ።

  • ሕንጸት፡- በመድረክ ላይ እያገለገልክ እያለህ በልሳን ስትናገር ተሰምተህ አታውቅም። ሐዋርያው ጳውሎስ “በልሳን የሚናገር ቢኖር፥ ሁለት ቢበዛ ሦስት በየተራ ይናገሩ፤ ሌላው ደግሞ ይተርጉም፤ የሚተረጉም ሰው ከሌለ ግን በጉባዔ መካከል ዝም ይበልና፤ ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር” (1ቆሮ. 14፥27-28) የሚለውን ቃል ለመታዘዝ ብለህ ነው? ወይስ ሌላ ምክንያት አለህ?

መጋቢ በቀለ፡- እኔ በልሳን መጸለይ በጣም እወዳለሁ። ጳውሎስ … በመንፈስ እጸልያለሁ፤ በአእምሮም ደግሞ እጸልያለሁ፤ በመንፈስ እዘምራለሁ፤ በአእምሮም ደግሞ እዘምራለሁ” ሲል (1ቆሮ. 14፥15)፤ “… በማንኛውም  ሁኔታ በመንፈስ ጸልዩ” ሲል (ኤፌ. 6፥18)፤ ይሁዳም “ራሳችሁን ለማነጽ ትጉ፤ በመንፈስ ቅዱስም ጸልዩ” ሲል (ይሁዳ 20) እየተናገሩ ያሉት በልሳን ስለ መጸለይ እና በልሳን ስለ መዘመር እንደ ሆነ ነው የማምነው። አንተ እንዳልከው፣ በመድረክ ላይ እየሰበክሁ ወይም እያስተማርኩ እያለሁ በልሳን የተናገርኩበት ጊዜ ትዝ አይለኝም። በመድረክ ላይ ወይም በጉባዔ ውስጥ ሆኜ በሚካሄድ የጸሎት መርሐ ግብር ወቅት ግን እንደ ልቤ በልሳን እጸልያለሁ። ያኔም ቢሆን ግን የምጸልየው ድምፄን ሌሎች ሁሉ በሚሰሙት መጠን ከፍ አድርጌ አይደለም። እኔ አብዘቼ በልሳን የምናገረው በግል የጸሎት ጊዜዬ ነው። በግል የጸሎት ጊዜዬ፥ በአእምሮ ከመጸለይ ይልቅ በልሳን መጸለይን ነው የምመርጠው።

እንደዚህ የማደርገው የሐዋርያውን ምክር ለመፈጸም ብዬ ግን አይመስለኝም። የባሕርይ ጉዳይ ይመስለኛል። ዛሬ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ “ካሪዝማዊ” ስለ ሆኑ፣ ከዓለማውያንም እንኳን ብዙ ሰዎች ስለ ልሳን ያውቃሉ። ለሌሎች ስሜት የመጠንቀቁ አስፈላጊነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ፣ የእኛ ዘመን እንደ ጳውሎስ ዘመን እንግዶች ወደ ጉባዔዎቻችን ቢገቡ “አብደዋል” ይሉናል ተብሎ የሚፈራበት ዐይነት ዘመን አይደለም። ስለዚህ እኔ በመድረክ ላይ በልሳን ባልናገርም እንኳን ሌሎች መናገራቸውን ግን በጣም አላጥላላም።

  • ሕንጸት፡- ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ለልምምዳቸው ሲሉ በግልጽ ሲተላለፉ እያየህ ለምን ዝም ትላለህ? “አብደዋል” ላለመባሉስ ምን ማስረጃ ይኖራል? ለምሳሌ እኔ እስከማውቀው ድረስ “አብደዋል” ነው የሚባሉት?

መጋቢ በቀለ፡- እውነቱን ለመናገር፣ ሌሎችን እስከሚያውክ ድረስ ጮሆ በልሳን መናገርም ሆነ ወይም ጨርሶ በልሳን የመናገር ጉጉት ማጣት ሁለቱም ለእኔ መልካም ነገሮች አይደሉም። ሚዛናዊ መሆን አስቸጋሪ እየሆነ በመጣበት በዚህ ዘመን፣ የበለጠ የሚጎዳን በመድረክ ላይ በልሳን ከመናገር ይልቅ፣ በልሳን የመናገር ጉጉት ጨርሶ ማጣቱ ስለሚመስለኝ ነው ዝም የምለው።

  • ሕንጸት፡- ስለ ትዳርህ መስተካከል የተለያዩ ትንቢቶችን ሰምተሃል፤ እስካሁን ግን አልተፈጸሙም። ይህን እንጂ ስለ ትንቢት ባለህ አመለካከት ላይ ተጽእኖ ያሳደረብህ አይመስልም። እንዴት?

መጋቢ በቀለ፡- አዎን፤ አላሳደረብኝም። ምክንያቱም እግዚአብሔር ዛሬም ይናገራል፤ በትንቢት፣ በሕልም፣ በራእይ፣ በልሳንና በትርጉም እንዲሁም በድምፅ። እግዚአብሔር የተናገረው ነገር ያልደረሰ እንደ ሆነ፣ ያልደረሰበት ምክንያት ሁልጊዜም ትንቢቱ ውሸት ስለ ነበረ ነው ብዬ አላምንም። ሰው አይሳሳትም ወይም አይዋሽም ለማለት ሳይሆን፣ ትንቢቱ ያልደረሰበት ምክንያት ግን ያ ብቻ ላይሆን ይችላል ማለቴ ነው። እነዚያ ሁሉ የእግዚአብሔር ሰዎች የተናገሩልኝ ትንቢቶች ለምን ሳይደርሱ ቀሩ? እኔም ያየኋቸው በጣም አስገራሚ የሆኑ ሕልሞች የት ደረሱ? በእውነቱ አላውቅም። ሁሉንም የተናገራቸው እግዚአብሔር ነበር ለማለት ባልደፍርም፣ እግዚአብሔር አልነበረም ለማለትም ዛሬም ቢሆን ዝግጁ አይደለሁም። ወንድሜ ሚክያስ! “አላውቅም” እኮ መልስ ነው። ለምንድነው እሱ ሁሉን ማወቅ እንዳለብን የሚመስልህ?

  • ሕንጸት፡- አሁንም የትዳርህን መመለስ ትጠብቃለህ?

መጋቢ በቀለ፡- አልጠብቅም። ባይገርምህ አሁን እየተሰማኝ ያለው ስለ ትዳሬ በማልቀስ ያሳለፍኳቸውን እነዚያን ዓመታት በከንቱ እንዳባከንኳቸው ነው። እግዚአብሔር እኔን ለመቅረጽ እንደ ተጠቀመባቸው አውቃለሁ። ቢሆንም፣ ምነው ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ሥራ ጸልዬባቸው በሆነ ኖሮ እያልኩ ደግኛ (ክፉኛ ሳይሆን) እየተጸጸትኩ ነው።

  • ሕንጸት፡- ብቸኛ እንደ ሆንክ ይሰማሃል?

መጋቢ በቀለ፡- በጣም። የጌታ ጸጋ ግን እጅግ በዝቶልኛል። ክብር ለስሙ ይሁን!

  • ሕንጸት፡- አሁን የጋሽ በቀለ የቅርብ ጓደኛ ነው የሚባለው ማን ነው? “ቡና ሻይ” ከማን ጋር ነው የምትለው?

መጋቢ በቀለ፡- ኦ! ብዙ ወዳጆች አሉኝʼኮ! የአንገትም የአንጀትም። ወንዶችም ሴቶችም። ወጣቶችም ጎልማሶችም። እነርሱም ሆኑ እኔ ሲያሰኘንና ጊዜም ሲፈቅድልን አብረን ቡና ሻይ እንላለን። እርግጥ ይህንን አዘውትሬ አደርግ የነበረው ከወንድም በዛብህ ወርቅነህ ጋር ነበር። እርሱ አሁን ባገር የለም። እርሱ በነበረ ጊዜ አደርግ የነበረውን ያህል ባይሆንም፣ ዛሬም ከሌሎቹ ወዳጆቼ ጋራ አደርገዋለሁ። ብቸኛነትና ባለ ብዙ ወዳጅነት አብረው የማይሄዱ አይምሰልህ።

  • ሕንጸት፡- አሁን ስንት ዓመት ሆነህ? ።

መጋቢ በቀለ፡- መጋቢት 19 ቀን ሲመጣ 74ኛ ዓመቴን እደፍናለሁ።

  • ሕንጸት፡- በ75 ዓመትህ ላይ ወደ ጌታ እንደምትሄድ እያመንክ ይመስለኛል። ሥራህን እንደጨረስህ ነው የምታስበው ማለት ነው? ባይሆንስ?

መጋቢ በቀለ፡- አዎን፤ እኔ እያመንኩ ነው። ሥራዬን ልጨርስ አልጨርስ የሚያውቀው ግን አሠሪዬ ነው። ያልጨረስኩም ከሆነ ምን አለ? በሌላ ሠራተኛ ያስጨርሰዋል።

  • ሕንጸት፡- በአገልግሎት ዘመኔ ትልቅ ስሕተት ሠርቻለሁ የምትለው ምን ነገር አለ? በዚሁ አጋጣሚ ይቅርታ መጠየቅ ትችላለህ።

መጋቢ በቀለ፡- ሰው ከስሕተት የጸዳ ሊሆን እንደማይችል የታወቀ ነው። ሁላችንም፣ በሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው ቋንቋ፣ “ዐፈር ያነሣ ሥጋ” ነን። እና እኔም በአገልግሎት ዘመኔ የተሳሳትኩባቸው፣ የማውቃቸውና የማላውቃቸው ከቁጥር በላይ ጉዳዮች እንዳሉ እርግጠኛ ነኝ። ይሁን እንጂ፣ ትልቅና ይቅርታ ያልጠየቅሁበት የምለው ስሕተት ትዝ አይለኝም።

  • ሕንጸት፡- ከግል ሕይወትህ ወይም ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎትህ ጋር ባልተያያዘ ሁኔታስ በጣም ያዘንክበት አጋጣሚ አለ?

መጋቢ በቀለ፡- ሞልቷል። በ1970 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ተዛውሬ ስመጣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ Organization and Methods የሚባል ክፍሉ (department) ውስጥ መደበኝ። በዚያን ዘመን የሠራተኛን ጉዳይ (labour case) የሚዳኝ፣ የወረዳ ፍርድ ቤት ሥልጣን ይመስለኛል ያለው “የክርክር ኮሚቴ” የሚባል አካል በመንግሥታዊ ድርጅቶች ውስጥ ነበረ። የንግድ ባንኩ የክርክር ኮሚቴ ጸሐፊው አድርጎ መረጠኝ። የመኢሶንና የኢሕአፓ አባላት የነበሩ የባንኩ ሠራተኞች የፖለቲካ ወገንተኛነታቸውን በየሆዳቸው ደብቀው ይዘው፣ ሥራ ነክ በሚመስሉ ምክንያቶች ከድርጅቱ ጋር ይካሰሱ ነበር። የክርክር ኮሜቴውን ቃለ ጉባዔ የምጽፈው በአብዛኛው ከሥራ ሰዓቶች ውጭ እቢሮዬ ውስጥ ሆኜ ነበር። ጉዳዩ በይግባኝ ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት ሊሄድ ስለሚችል ቃለ ጉባዔዎቹን በጥንቃቄ ነበር የምጽፋቸው።

አለቃዬ ወይዘሮ ድንቅነሽ ትባላለች። ከሁለቱ የፖለቲካ ጎራዎች የአንደኛው አባል ወይም sympathizer ናት። ቃለ ጉባዔውን ስጽፍ አንዳንድ ጊዜ ትመጣና አጠገቤ ትቆማለች። እርሷ እንደዚህ በምታደርግ ጊዜ ሁሉ እኔ ደግሞ ፋይሎቹን አጣጥፋቸውና መሳቢያዬ ውስጥ እከትታቸዋለሁ። በሌላ ጊዜ ደግሞ በጨዋታ ልታውጣጣኝ ብዙ ትሞክራለች። እንደዚህ በምታደርግ ጊዜ ደግሞ ጨዋታውን እቀይርባታለሁ። አንድ ቀን ስለ እምነትህ ንገረኝ አለችኝና በሥራ ሰዓት ከቢሮ ይዛኝ ወጣች። ስለ እምነቴ እየነገርኳት፣ ጥያቄዎች እየጠየቀችኝና እየመለስኩላት በቸርችል ጎዳና ወደ ቴዎድሮስ አደባባይ በሚወስደው መንገድ በእግራችን ብዙ ተጓዝን። ወደ ቢሮ ስንመለስ መንፈሳዊ መጻሕፍትና የመዝሙር ካሴቶች እንዳውሳት ጠየቀችኝ። ይህንን የምታደርገው ለነፍሷ ጩኸት ምላሽ ፍለጋ ይሁን የሆነ የፖለቲካ ትርፍ (advantage) ለማግኘት፣ የማውቅበት መንገድ አልነበረኝም። ብቻ ከልቧ ስለ መሰለኝ ደስ ብሎኛል። በግሌ ልጸልይላትም ጀምሬአለሁ። ሆኖም ብዙም ሳንቆይ፣ እርሷም ወደ ውሳኔ ሳትደርስ ሕይወቷን በገዛ እጇ አጠፋች።

በጣም፣ እጅግ በጣም አዘንኩ። እኔ ያኔ የምጸልየው ጸሎት ሁሉ መመለስ ያለበት ነበር የሚመስለኝ። ከእርሷ በፊት ሦስተኛው ታናሽ ወንድሜ እንደዚሁ ከመሰከርኩለትና በግሌ እየጸለይኩለትም እያለሁ በኢሕአፓ አባልነት ተገድሏል። በግል ሕይወቴ ካደረገው ነገር የተነሣ መድኀኒቱ ፍቱን እንደ ሆነ አውቃለሁ። መቼም ቢሆን ያንን መካድ አልችልም። ስለዚህም ለምቀርባቸው ሁሉ ስለ ጌታ መድኃኒትነት እናገራለሁ። እኔ ሳዝዘው (prescribe ሳደርገው) አይሠራም። እንዲያውም ያዘዝኩላቸው ሰዎች ይሞታሉ። ስለዚህ ከእንግዲህ በኋላ እኔ ይህንን መድኀኒት ለማንም ማዘዝ የለብኝም ብዬ ወሰንኩ። እና ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ከማንም ሰው ጋር መንፈሳዊ ነገር መነጋገር አቆምኩ። ለረዥም ጊዜ አፌን ዘግቼ ከቆየሁ በኋላ ነው በሌላ አስገራሚ አጋጣሚ ጌታ አፌን ያስከፈተኝ።

በ1971 ዓ.ም. ለሥራ ጉዳይ ወደ ባሕር ዳር ሄጄ ነበር። በዚያ ሳለሁ ስለ ደራሲ አቤ ጉበኛ ሸክም (burden) ወደቀብኝ። አድናቂው ብሆንም፣ አንተዋወቅም። ቀደም ሲል እርሱ በዚያ ከተማ ይኖር እንደ ነበረ ግን መረጃ ነበረኝ። እና መጸለይ ጀመርኩ። ለጥቂት ቀናት ከጸለይኩለት በኋላ በዚያ ከተማ መኖሩን ለማረጋገጥ አጠያየቅሁ። መኖሩን ሰማሁ። አሁን ሸክሙ እርሱን ለማግኘትና ስለ ጌታ ለመመስከር ሆነ። በግል ምስክርነት (personal evangelism) ከዛሬ ይልቅ ያኔ ሳልሻል አልቀርም። ዛሬ “የመድረክ ላይ አንበሳ” ብቻ ሆኟለሁ። እንደዚያም ሆኖ ግን አቤን ላገኘውና ፊት ለፊት ላነጋግረው ፈራሁ።

የማደርገው ሲጠፋኝ በደብዳቤ ልመሰክርለት አሰብኩ። አንድ ማታ መኝታ ክፍሌ ውስጥ ሆኜ ባለ ብዙ ገጽ ደብዳቤ ጻፍኩለት። ሲነጋ የጻፍኩትን ሳነብበው ስሜት አልሰጥህ አለኝ። ቀዳድጄ ጣልኩት። በማግስቱ ማታ ደግሞ ያንኑ የሚያህል ሌላ ደብዳቤ ጻፍኩለት። ማለዳ ላይ ሳነብበው እሱም አልጥምህ አለኝ። አሁንም ቀዳድጄ ጣልኩት። ምን አደከመህ? በየማታው ሦስቴ ይሁን ወይም አራቴ እየጻፍኩ በየማለዳው ደግሞ ሦስቴ ይሁን ወይም አራቴ ቀደድኩ። በመጨረሻም አቤን ሳላገኘው፣ ደብዳቤም ሳልልክለት፣ ሸክሙም ሳይቀልልኝ ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ዜና ዕረፍቱን በሚድያ ሰማሁ። እጅግ በጣም አዘንኩ። ጌታ በሌላ መንገድ ተገናኝቶት ካልሆነ በስተቀር፣ ደሙ በእጄ ላይ እንዳለ ለረዥም ጊዜ ሲሰማኝ ቆይቷል። ባይገርምህ አሁን ደግሞ፣ ልክ እንደዚያን ጊዜው የሁለት የማደንቃቸው ጸሐፊዎች “ሸክም” እያንገላታኝ ነው። ምን እንደማደርግ አላውቅም። አንተም ብትጸልይልኝ፣ የመጽሔትህን አንባቢዎችም እንዲጸልዩልኝ ብታሳስብልኝ ደስ ይለኛል።

  • ሕንጸት፡- የጸሎት ጥሪህን ለውድ አንባቢያን እዚሁ አስተላልፋለሁ፡፡ ስለ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ፤ እግዚአብሔር ያክብርልኝ ጋሽ በቄ!

መጋቢ በቀለ፡- በተወዳጁ መጽሔታችሁ ላይ የሆድ የሆዳችንን እንድንነጋገር ዕድሉን ስላገኘሁ እግዚአብሔርን እጅግ አድርጌ አመሰግነዋለሁ። እናንተንም እግዚአብሔር ይባርካችሁ እላለሁ።

Share this article:

1 comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.