[the_ad_group id=”107″]

“ዘመነ ነቢያት” በእግዚአብሔር ቃል ሲፈተሽ

ባለፈው ዕትም የ“ነቢይ” ቡሽሪን የኢትዮጵያ አገልግሎት አስመልክቶ አንድ መጣጥፍ አቅርቤ ነበር፡፡ የእኚህ ሰው “አገልግሎት” በሐሰት የተሞላና ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር የሚጣረስ መሆኑን አሳይቻለሁ፡፡ እንዲህ ዐይነቱ የስህተት አስተምህሮ እንደ ቡሽሪ ባሉ ከውጭ ሀገር በሚመጡ አገልጋዮች ላይ ብቻ የሚታይ ሳይሆን በእኛ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት እየተስተዋለ የመጣ ችግር ነው፡፡ የዛሬው መጣጥፍ የትኩረት አቅጣጫም ይህ ይሆናል፡፡ በቅርብ ጊዜ አንድ የመዲናችን የአዲስ አበባ ታዋቂ “መጋቢ” አንድን “ነቢይ” የበዓለ ሲመት አዘጋጅቶ የኢትዮጵያ “ሜጀር ነቢይ” አድርጎ ሾሞታል፡፡ የሜጀር ነቢይነትን ማዕረግ ከዬትኛው መጽሐፍ ቅዱሳቸው እንዳገኙት ግን እግዜር ይወቅ፡፡ እንግዲህ ይህ ሰው “የሜጀር ነቢይ” ቡሽሪ አምሳያ መሆኑ ነው፡፡ እስከ መቼ ነው ግን አገልግሎት በኩረጃ የሚሆነው? አገልጋዮችም ሆኑ ምዕመናን ለምን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን አያነቡም? እንዲሁም የቡሽሪንም ሆነ የሌላውን ሰው ሹመት ለምን በመጽሐፍ ቅዱስ መመዘኛ አይፈትሹም? እስከ መቼ በመጣው ንፋስ ሁሉ ወዲህና ወዲያ የሚላተሙ እንጂ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል እየተጓዙ፣ በነቢይነት ስም ኮንፍራንስ እያዘጋጁ፤ “ከድህነት ቀንበር ለመላቀቅ፣ የተትረፈረፈ ሀብት ለማካበትና ከበሽታ ለመፈወስ ይህንን የተጸለየበት ዘይትና ቁራጭ ጨርቅ ግዙ” የሚሉ “አገልጋይ ነጋዴዎች” በሀገራችንም ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ በቅርቡ አንድ ጓደኛዬ በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ለአገልግሎት ሄዶ ያጋጠመውን እንዲህ አጫወተኝ፡- ሁለት “አገልጋዮች” ከመዲናችን አዲስ አበባ ወደ ደቡቡ የሀገራችን ክፍል ለአገልግሎት ይሄዳሉ፡፡ በስታዲየም ውስጥ ትልቅ ኮንፍራንስ ተዘጋጅቶላቸው ስብከታቸውን ከጨረሱ በኋላ እንደለመዱት መርካቶ በትንንሽ መጠን ያስቆረጡትን ጨርቅ እንዲህ በማለት ማስተዋወቅ ይጀምራሉ፡፡ “መርገማችሁን የሚሰብር፣ ከድኅነት ቀንበር የሚያላቅቃችሁና ከማንኛውም በሽታ የሚፈውሳችሁ የተጸለየበትና ዘይት የተቀባ ጨርቅ ይዘን መጥተናል፡፡ ስለዚህ አንድ ሺህ ብርና ከዚያ በላይ የያዛችሁ በዚህ በኩል ተሰለፉ፣ አምስት መቶ ብር የያዛችሁ በዚህ በኩል ተሰለፉ፣ መቶ ብር የያዛችሁ በዚህ ተሰለፉ፤ ዝርዝር ብር ግን አንፈልግም” በማለት ሕዝቡን አሰልፈው ሲሸጡ የተመለከቱ ጸጥታ ለማስከበር የተመደቡ ፖሊሶች፣ “ጨርቅ ለመሸጥ ፈቃድ ስለሌላችሁ፣ እንዲሁም ጨርቁ የመንግሥት ግብር ስላልተከፈለበት መሸጥ አትችሉም” በማለት አስቆሟቸው አሉ፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፤ እዚህም ደረጃ ላይ ደርሰናል!

ሌላ አንድ ምሳሌ ልጨምር፡- በሀገራችን አንድ አንጋፋ የሃይማኖት ተቋም ውስጥ የሚሠሩ ሰው አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ከክፍለ ሀገር ቢሮአቸው በመደወል ይህንን የመሰለ አቤቱታ ማቅረባቸውን እንዲህ ሲሉ አጫወቱኝ፡፡ አንድ አገልጋይ ከአዲስ አበባ ወደ አንዱ የሀገራችን ትንሽ ከተማ በመሄድ የጀማ ስብከት ፕሮግራም በማዘጋጀት እግዚአብሔር የሕዝቡን ጉስቁልና ዓይቶ መፍትሄ እንደላከላቸው ሰበከ፡፡ ከዚያም ፕሮግራሙን ለመታደም የመጡ ሰዎችን በአገልግሎቱ መሃል ላይ በአንድ እጃቸው ከምድር ላይ አሸዋ ዘግነው ወደ ላይ እንዲያነሱ፣ በሌላኛው እጃቸው ደግሞ በኪሳቸው ውስጥ የሚገኘውን ገንዘብ ወደ ላይ እንዲያነሱ በማድረግ፤ ገንዘቡን መባ መሰብሰቢያ ዕቃ ውስጥ አሸዋውን ደግሞ በኪሳቸው እንዲከቱ ሕዝቡን አዘዘ፡፡ በመባ መሰብሰቢያ ዕቃ ውስጥ ያስገቡት ብር በኪሳቸው ውስጥ እንዳለው አሸዋ ልክ እንደሚበዛ ነገራቸው፡፡ “አገልጋዩ” ከሕዝቡ የሰበሰበውን ብር ይዞ ወደ አዲስ አበባ፣ ሕዝቡም “አሜን!” ብሎ አሸዋውን ተሸክሞ ወደ ቤቱ ገባ!

ሌላኛው የዘመኑ አገልጋዮች የብር መሰብሰቢያ መንገድ “ዘርን ዝሩ” የሚለው ብሂላቸው ነው፡፡ በረከታችሁ እንዳይለቀቅ አንቃችሁ የያዛችሁት እናንተ ናችሁ፤ በረከታችሁ እንዲለቀቅ ዘር ዝሩ ይሉናል፡፡ ይህን የንግድ ልውውጥ የመሰለው አካሄድ ምንም ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለውም፡፡ ዐሥር የሰጠ መቶ፣ መቶ የሰጠ ዐሥር ሺህ፣ ዐሥር ሺህ የሰጠ መቶ ሺህ ያገኛል የሚለው ብሂል መጽሐፍ ቅደሳዊ መሠረት የለውም፡፡ በእርግጥ አንዳንዶች ለዚህ አስተምህሮ የማርቆስ ወንጌልን 10:29-30 በእማኝነት ያነሳሉ፡፡ “ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም . . . እርሻን የተወ፥ አሁን በዚህ ዘመን . . . እርሻንም መቶ እጥፍ፥ . . . የማይቀበል ማንም የለም።” ነገር ግን ይህ ክፍል ከአውዱ ተነጥሎ ካልተነበበ በስተቀር ምድራዊ ሀብትን ሰለማካበት ስለማያወራ ለአስተምህሮዋቸው ዋቢ መሆን የሚችል አይመስለኝም፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች “ሁለት ሺህ፣ አምስት ሺህ ብር አትስጡ፣ እርሱን የልጆቻችሁን ትምህርት ቤት ክፈሉበት፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ብዙ ብር እየሰጣችሁ አስደንግጡት” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ እንዲህ ዐይነቱ ንግግር የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ በቅጡ ያላጤነ አልያም ለሕዝቡ ምንም ደንታ የሌለው ሰው ንግግር ነው፡፡

የዚህ ሁሉ ችግር መሠረት ሁለትዮሽ ነው፡፡ በአንድ በኩል አገልጋይ ነን ባዮቹ ሰዎች አገልግሎትን የግል ጥቅም ማስገኛ መንገድ አድርገው መመልከታቸው፡፡ በሌላ በኩል የችግሩ ምንጭ ሕዝበ ክርስትያኑ አቋራጭ ከችግር የመላቀቂያና የመበልጸግያ መንገድ አጥብቆ መፈለጉ ነው፡፡ የክርስትና አንኳር መልዕክቱ ምድራዊ ብልጽግና እስኪመስል ድረስ የሕዝባችን አእምሮ በዚህ ነገር ተይዟል፡፡ መያዝ ብቻ አይደለም ይህንን መልዕክት ወደሚነግሩት አገልጋይ ነን ባዮች ዘንድ ዕለት ዕለት ይመላለሳል፡፡ በእርግጥ የሀገራችን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ኑሮን በሥራና በትግል ማሸነፍ የማይቻል አስመስሎታል፡፡ ስለዚህም ሕዝቡ ሁሉ በኑሮው ውስጥ የልዕለ-ተፈጥሮ ኃይል ጣልቃ ገብነት እንዲኖር ይሻል፡፡ መሻቱ ባልከፋ፣ ነገር ግን በአገልግሎት ስም ይብስ በሚበዘብዙ ሰዎች እጅ ጣለው አንጂ፡፡ አገልጋይ ነን ባዮቹም የሕዝቡን የውስጥ ፍላጎት ጠንቅቀው በማወቃቸው “የበረከት ዘመን መጥቶልሃል”፣ “እግዚአብሔር ያበለጽግሃል”፣ ወዘተ የሚሉ ቀቢጸ ተስፋዎችን በመስጠት እነዚህ በረከቶች እንዲለቀቁልህ “ዘርን ዝራ” በሚል ስሌት ለግል ፍላጎታቸው ማሟያ ይጠቀሙበታል፡፡ ሕዝቡ በምኞት ሲንገላወድ እነርሱ ግን ከሕዝቡ በ“ዘር” ስም በሰበሰቡት ብር ይከብሩበታል፡፡

ይህንን የሚያደርጉ ሰዎች ራሳቸውን “ነቢያት” ነን ብለው ይጠራሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “በነቢይነት” ማዕረግ የሚጠሩ “አገልጋዮች” በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቁጥር እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ አንዳንድ ቤተ እምነቶችም ይህንን ሹመት መስጠት ጀምረዋል፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች ዘመኑ “የነቢያት” ነው እያሉ ይገኛል፡፡ ስለዚህ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ መነጽር ነቢይ ማለት ምን ማለት እንደሆነ መመርመሩና በሀገራችን በአሁን ወቅት እየተንሰራፋ ያለውን አስተምህሮ መገምገሙ አስፈላጊ ይሆናል፡፡

በብሉይ ኪዳን ውስጥ ነቢያት በሰዎች ዘንድ የእግዚአብሔር ተወካዮች ናቸው፡፡ በመሆኑም የነቢያቱም ንግግር እንደ እግዚአብሔር ቃል ይቆጠር ነበር፡፡ ስለዚህም የብሉይ ኪዳን ነቢያት ከእግዚአብሔር ዘንድ ይዘውት የመጡትን መልዕክት ሲናገሩ በአብዛኛው “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣” በማለት ይናገሩ ነበር፡፡ ሕዝበ እስራኤልም ይህንን የነቢያትን መልዕክት ከሰማ በኋላ መታዘዝ ይጠበቅበታል፡፡ አለመታዘዝ ፍርድን ያስከትላል፡፡ የነቢያቱም ቃል ሙሉ ለሙሉ በተናገሩት መንገድ ፍጻሜን ያገኛል (1 ነገ 14:18፤ 16:12፤ 34፤ 17:16፤ 22:38፤ 2 ነገ 1:17፤ 7:16፤ 14:25፤ 24:2)፡፡ ስለዚህ በብሉይ ኪዳን በአጠቃላይ የነቢያቱ ቃል እና እግዚአብሔር ቃል እኩሉ ናቸው፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ማመንና የነቢያቱን ቃል ማመን የአንድ ሳንትም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ (2 ዜና 20:20፤ 29:25፤ ሐጌ 1:12) ምክንያቱም ነቢያቱ የሚናገሩት እግዚአብሔር መልዕክተኞች ነው (2 ዜና 36:15–16)፡፡ ስለዚህም እውነተኞቹን ነቢያን አለመቀበል ወይም የእነርሱን ቃል አለመታዘዝ እግዚአብሔር አለመታዘዝ ነው፤ ይህም ሰሚዎቹን ተጠያቂ ያደርጋል (1 ሳሙ 8:7፤ 1 ነገ 20:36; 2 ዜና 25:16፤ ኢሳ 30:12–14)፡፡ ይህም በብሉይ ኪዳን ውስጥ የነቢያቱ ቃል ከእግዚአብሔር ቃል ጋር እኩል ሥልጣን ስላለው ከሕዝቡ በቀጥታ የተባለውን መፈጸምን ይጠይቃል፡፡ በብሉይ ኪዳን ውስጠ ቢሆን እውነተኞቹን ነቢያት ከሐሰተኞቹ ነቢያት መለያ መስፈርት ተቀምጧል (ዘዳ 13፡ 1-5፤ 18፡20 ጋር ያነጻጽሩ)፡፡

ነገር ግን የአዲስ ኪዳን ትንቢታዊ መልዕክቶች ፈጽመው ከዚህ ይለያሉ፡፡ ምንም እንኳ መልዕክቶቹ ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጡ ቢሆኑም እንደ እግዚአብሔር ቀጥተኛ ቃል ግን አይወሰዱም ነበር፡፡ ምክንያቱም ሊፈተኑ፣ ሊፈተሹና ሊመዘኑ ይገባልና፡፡ ይህን ሀሳብ ለመረዳት ጥቂት የአዲስ ኪዳን ትንቢታዊ መልዕክቶችን እንመልከት፡-

  1. የሐዋርያት ሥራ 21፡4፡፡ በሐዋ 21፡4 ላይ በጢሮስ የነበሩት ደቀ መዛሙርት ለጳውሎስ እንዲህ የሚል መልዕክት አምጥተውለት እንደነበር እናነባለን፡፡ “እነርሱም ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ በመንፈስ አሉት።” ይህ እንግዲህ ለጳውሎስ የተነገረ ትንቢታዊ መልዕክት ነው፡፡ ነገር ግን ጳውሎስ ይህንን መልዕክት አልተቀበለውም፡፡ ይህ ትንቢታዊ መልዕክት እንደ እግዚአብሔር ቃል ቢሆንና ከእግዚአብሔር ቃል ጋር እኩል ሥልጣን ቢኖረው ኖሮ ጳውሎስ የመጣለትን መልዕክት መታዘዝ በተገባው ነበር፡፡ እርሱ ግን ምንም እንኳ በትንቢታዊ መልዕክቱ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም፣ ወደዚያ አቅንቷል፡፡
  2. የሐዋርያት ሥራ 21፡10-11፡፡ አጋቦስ የተባለ ነቢይ በኢየሩሳሌም ያሉ አይሁዶች ጳውሎስን አስረው ለአሕዛብ አሳልፈው እንደሚሰጡት ተንብየዋል፡፡ ይህ ትንቢታዊ መልዕክት አጋቦስ በተናገረው መልኩ ባይሆንም ፍጻሜን አግኝቷል፡፡ ጳውሎስን ያሰሩት አይሁዶች ሳይሆኑ ሮማዊያን መሆኑን ልብ ይሏል (ቁ. 33 እና 22፡29 ጋር ያነጻጽሩ)፡፡ እንዲያውም አይሁዳዊያኑ በፈቃደኝነት እርሱን አሳልፈው ከመስጠት ይልቅ ሊገሉት ፈልገው ነበር፤ ሮማዊያኑ ግን ከአይሁዳዊያኑ እጅ ታደጉት፣ (ቁ. 32)፡፡ በአጋቦስ ትንቢታዊ መልዕክት ውስጥ ቁ. 21 ላይ የሚገኘው “አሳልፎ መስጠት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል አዲስ ኪዳን በተጻፈበት ቋንቋ “በፈቃደኝነት አሳልፎ መስጠት” የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ ነገር ግን አይሁዶቹ በፈቃደኝነት ጳውሎስን ለሮማዊያን አሳልፈው አልሰጡትም፤ ሮማዊያኑ በግድ ከእጃቸው ነጥቀው ወሰዱት እንጂ፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳ የጳውሎስን መታሰር በተመለከተ የተነገረው ትንቢት በአጠቃላይ ሲታይ ትክክል ቢሆንም ፍጻሜውን ያገኘው ግን አጋቦስ በተናገረው መንገድ አልነበረም፡፡ ይህም የሚያሳየን ትንቢታዊ መልዕክቶች ከብሉይ ኪዳን ትንቢቶች በተለየ መልኩ ትክክለኛነታቸው ጥያቄ ውስጥ መግባት መቻሉን ነው፡፡
  3. በ1ተሰሎንቄ 5፡19-21 ላይ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች እንዲህ በማለት ጽፎላቸዋል፣ “መንፈስን አታጥፉ፤ ትንቢትን አትናቁ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ”፡፡ የተሰሎንቄ ሰዎች ትንቢታዊ መልዕክትን በተሳሳተ መልኩ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር እኩል አድርገው ባይመለከቱ ኖሮ ጳውሎስ ይህንን ሀሳብ ባልጻፈላቸው ነበር፡፡ ምክንያቱም 1 ተሰ 1፡6፣ 2፡13 እንዲሁም 4፡15 ላይ የተሰሎንቄ ሰዎች የእግዚአብሔር ቃል በመንፈስ ቅዱስ በመነዳት የእግዚአብሔር ሰዎች የጻፉት መጽሐፍ መሆኑን አምነው በደስታ መቀበላቸውን ገልጾአል፡፡ እንግዲህ በ5፡19-21 ላይ ጳውሎስ “ሁሉን ፈትኑ” በማለት ያስጠነቀቀው ትንቢታዊ መልዕክቶች በውስጣቸው መልካምና ክፉን ነገር ስለሚይዙ ነው፡፡ ስለዚህም ከትንቢታዊ መልዕክቶች ውስጥ “መልካሙን ያዙ” በማለት ይመክራቸዋል፡፡ የአዲስ ኪዳን ትንቢታዊ መልዕክቶችን ከብሉይ ኪዳን ትንቢታዊ መልዕክቶች መለያው የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች መታዘዝን በቀጥታ ከሕዝቡ ሲጠብቁ የአዲስ ኪዳን ትንቢታዊ መልዕክቶች ግን በመጀመሪያ የመልዕክቱን ትክክለኝነት መፈተሽን ይጠይቃል፡፡
  4. 1 ቆሮንቶስ 14፡29-38፡፡ ስለ አዲስ ኪዳን ትንቢታዊ መልዕክቶች በስፋት በ1 ቆሮ 14 ላይ እናገኛለን፡፡ በዚሁ ክፍል ውስጥ እንዲህ ይላል፣ “ነቢያትም ሁለት ወይም ሦስት ሆነው ይናገሩ ሌሎችም ይለዩአቸው፤” (14፡29)፡፡ “ይለዩአቸው” የሚለው ቃል የሚያመለክተው “የተነገረውን ነገር መመዘን፣ መመርመርን” ነው፡፡ እንደ ኢሳይያስ ያሉ የብሉይ ኪዳን ነቢያት “የምናገረውን ነገር በጥንቃቄ አድምጡና መርምሩት፣ ከንግግሬ መካከል መልካሙን ከክፉ ለዩ፣ የምትቀበሉትን ከማትቀበሉት ለዩ” አይሉም፡፡ ነገር ግን ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው መልዕክት ውስጥ የአዲስ ኪዳን ትንቢታዊ መልዕክቶችን በመመርመር መልካሙን መያዝ ክፉን መተው እንደሚያስፈልግ ይናገራል፡፡

እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሚያስተምሩን በአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የትንቢት መናገር ስጦታ ለቤተ ክርስቲያን እንደተሰጠ ነገር ግን የተነገረ ትንቢት ሁሉ ትክክል እንዳልሆነ ነው፡፡ ስለዚህም በአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚነገር ትንቢት በብሉይ ኪዳን እንደነበሩ ነቢያት “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣” ማለት አይገባቸውም፡፡ ምክንያቱም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሲናገር ቃሉን የሰሙ ሰዎች ሁሉ መታዘዝ ይገባቸዋልና፡፡ ነገር ግን የአዲስ ኪዳን የትንቢት ስጦታ የሚመረመር፣ የሚመዘን በመሆኑ ሰዎች የሰሙትን ነገር መልካሙን ከክፉው የሚለዩበት ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

የአዲስ ኪዳን ትንቢታዊ መልዕክቶች በብሉይ ኪዳን “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣” ከሚሉ መልዕክቶች የሚለዩ ከሆነ የአዲስ ኪዳን ትንቢታዊ መልዕክቶች ምንድን ናቸው? ከእግዚአብሔር የሆኑት በምን ዐይነት መልኩ ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ቆሮ 14፡30-31 ላይ እግዚአብሔር ለሰዎች የተለያዩ ነገሮችን ሊገልጥ እንደሚችል ይናገራል፡፡ “በዚያ ለሚቀመጥ ለሌላ ግን አንድ ነገር ቢገለጥለት ፊተኛው ዝም ይበል። ሁሉም እንዲማሩ ሁሉም እንዲመከሩ ሁላችሁ በእያንዳንዳችሁ ትንቢት ልትናገሩ ትችላላችሁ።” ይህ መገለጥ ማለትም በጽሑፍ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተካተተ ለአንድ ክርስቲያናዊ ጉባዔ የሚነገር መልዕክት መገለጥ ወይም ትንቢታዊ መልዕክት ይባላል፣ (ፊል 3:15፤ ሮሜ 1:18፤ ኤፌ 1:17፤ ማቴ 11:27)፡፡ በተጨማሪም “ሁሉ ትንቢት ቢናገሩ ግን የማያምን ወይም ያልተማረ ሰው ቢገባ በሁሉ ይወቀሳል፥ በሁሉም ይመረመራል፤ በልቡም የተሰወረ ይገለጣል እንዲሁም፡- እግዚአብሔር በእውነት በመካከላቸው ነው ብሎ እየተናገረ በፊቱ ወድቆ ለእግዚአብሔር ይሰግዳል።” እነዚህ ትንቢታዊ መልዕክቶች እግዚአብሔር በጉባኤዎች መካከል መሆኑን በማሳየት “ለሚያምኑ” ሰዎች ምልክት ይሆናሉ (1ቆሮ 14፡22 ጋር ያነጻጽሩ)፡፡ እንዲሁም ትንቢታዊ መልዕክቶች የማያምኑ ሰዎች እንዲያምኑ ምክንያት ስለሚሆን “ሁሉ ትንቢት ቢናገሩ ግን የማያምን ወይም ያልተማረ ሰው ቢገባ በሁሉ ይወቀሳል፥ በሁሉም ይመረመራል፤” (14፡24) በማለት ጳውሎስ አማኞች በጉባኤ መካከል ይህን የትንቢት ስጦታ እንዲጠቀሙ ያበረታታል፡፡

ጳውሎስ ትንቢታዊ መልዕክቶች “ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ” (1ቆሮ 14፡12) እና በጉባዔ መካከል የተለያዩ መገለጦችን በመስጠት “ለማነጽና ለመምከር ለማጽናናትም” (14፡3) እንደሚጠቅም ይናራል፡፡ ምንም እንኳ ትንቢታዊ መልዕክት ሊፈተኑና ሊመዘኑ የተገባ ቢሆንም በጉባዔ መካከል የሚነገሩት ትንቢታዊ መልዕክቶች እግዚአብሔር በጉባዔው መካከል ሆኖ ቤተ ክርስቲያንን እየመራ፣ እያስጠነቀቀ፣ መጪውን ነገር እያመለከተ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በዚህ መንገድ ትንቢታዊ መልዕክቶች እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው የሚያሳዩ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ በዘመናችን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከትንቢታዊ መልዕክቶች ጋር በተያያዘ እየታየ ያለው ውዥንብር የእግዚአብሔርን ቃል ጠንቅቆ ካለማወቅ የመነጨ ነው፡፡ ከላይ ለመመልከት እንደሞከርነው ትንቢታዊ መልዕክቶች በእግዚአብሔር ጉባዔ መካከል የሚነገሩበት ምክንያት ጉባዔውን ለማነጽ፣ ለመምከር፣ ለመገሰጽ፣ እንዲሁም ለሚያምኑ ሰዎች ምልክት እንዲሆን ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በትንቢታዊ መልዕክቶች ስም የሚደረግ ማንኛውም ነገር መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለውም፡፡ ይህንን ትንቢታዊ መልዕክት የሚናገሩ ሰዎች እንደ ማንኛውም ምዕመን አንድ የጸጋ ስጦታ የተሰጣቸው ሰዎች እንጂ ከሌሎች የተለዩ “ሜጀር” የሚባል ሹመት መሾም የተገባ አይደለም፡፡ ሹመቱም ቢሆን በውትድርና ዓለም እንጂ በክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፈጽሞ የለም፡፡ ሿሚዎቹም ሆኑ ተሿሚዎቹ ራሳቸውን በእግዚአብሔር ቃል ሊመረምሩ ይገባል እላለሁ፡፡

በተጨማሪም ከዚህ በላይ ለመመልከት እንደሞከርነው የአዲስ ኪዳን ትንቢታዊ መልዕክቶች በእግዚአብሔር ቃል የሚፈተኑ፣ የሚፈተሹና የሚመዘኑ በመሆናቸው “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” በሚል ቅድመ ተቀጥላ ሊነገሩ ፈጽሞ አይገባም፡፡ እግዚአብሔር ስለ አንተ/አንቺ ይህንን መልዕክት ሰጥቶኛል፤ አስብበት/አስቢበት በሚል ሰዎች የሰሙትን መልዕክት መመርመር እና መፈተሽ በሚችሉበት መልኩ ሊነገር ይገባል እላለሁ፡፡

በአጠቃላይ እኔም ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር በመስማማት ሕዝበ ክርስትያኑን፣ “መንፈስን አታጥፉ፤ ትንቢትን አትናቁ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ፤” እንዲሁም በእግዚአብሔር ቃል ትክክለኛውን ትንቢታዊ መልዕክት ከሐሰተኛው ለዩ እላለሁ፡፡ እግዚአብሔር በቸር ያሰንብተን!

ፍቅር፣ ፍትሕ እና ሰላም የኢየሱስ መንገድ

በዚህ ልዩ ዕትም፣ ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆነው እስክንድር ነጋ የሕንጸት ዕንግዳ ሆኖ ቀርቧል። አገራችን ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶችና ዴሞክራሲ የሚከበሩባት አገር እንድትሆን መሥዋዕትነትን የጠየቀ ትግል አድርገዋል ከሚባሉት ግለ ሰቦች መካከል አንዱ እስክንድር ነው። በዚህም፥ ከዘጠኝ ጊዜያት በላይ ደጋግሞ ለእስር የተዳረገው እስክንድር፣ በአጠቃላይ ከዘጠኝ ዓመታት በላይ በእስር አሳልፏል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.