[the_ad_group id=”107″]

ስለ ብሽሽቅና ፉክክር ተኮር ስብከቶች

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብቅ እያሉ ያሉ አንዳንድ የአዳዲስ ቤተ ክርስቲያናት አገልጋዮች፣ የሚያምኑትን እውነት ለሌሎች ለማስተላለፍ እየሄዱበት ያለው አካሄድ፣ ወንጌል ከማዳረስ ዐላማ ይልቅ ብሽሽቅና ፉክክር የነገሠበት እንዲሆን አድርጓል። በብሽሽቅና ፉክክር ደግሞ የሚሠራ የእግዚአብሔር መንግሥት ሥራ ይኖራል ብዬ አላምንም።

የወንጌል መልእክት ዐውዳዊ ይዘቱን የጠበቀ መሆን እንዳለበት ከሐዋርያው ጳውሎስ የበለጠ ያስተማረን የለም። ይህን ዐውዳዊ የወንጌል ስብከት ጥበብን ግልጽ ለማድረግ፣ በቀዳሚነት የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 17ን መመልከት ጥሩ ግንዛቤ እንድንጨብጥ ያስችለናል ብዬ ዐስባለሁ።

በክፍሉ ሐዋርያው ጳውሎስ የግሪክ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ወደ አቴንስ በገባ ጊዜ፣ መንፈሱ እንደተበሳጨበት በክፍሉ ተገልጿል። የእግዚአብሔር መንፈስ ያደረበት ማንም ሰው፣ የጣዖት አምልኮን ሲመለከት መንፈሱ ይበሳጭበታል። እንዲያውም ግራ ሊገባን የሚገባውና ራሳችንን መፈተሽ ያለብን መንፈሳችን ባይበሳጭ ነው።

ታዲያ ይህን የውስጥ ብስጭት አምቆ ይዞ፣ የእውነትን ወንጌል በፍቅር ለሌሎች ለማድረስ ራስን የመግዛት መንፈስና ጥበብ ሊኖረን ይገባል። ለምሳሌ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በተበሳጨበት ልክ፣ ‘የአቴና ሰዎች ሆይ፤ እናንተ የምታመልኩት ጣዖት ነው፤ ዕንጨት ነው፤ ጣውላ ነው፤ ቍም ሳጥን ነው፣ ወዘተ.’ እያለ ስብከቱን አልጀመረም። ሆኖም ሐዋርያው፣ የአቴና ሰዎች ከያዙት እምነት ውስጥ የጋራ ዕሴቶችን ፈለገ፤ ወደ አንድ መሠረታዊ እውነትም ደረሰ። የአቴና ሰዎች ቢያንስ በፈጣሪ መኖር ያምናሉ።

የእግዚአብሔር መንፈስ ያደረበት ማንም ሰው፣ የጣዖት አምልኮን ሲመለከት መንፈሱ ይበሳጭበታል። እንዲያውም ግራ ሊገባን የሚገባውና ራሳችንን መፈተሽ ያለብን መንፈሳችን ባይበሳጭ ነው። 

ስለሆነም፣ ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በመክተት ስብከቱን እንዲህ ሲል ቀጠለ፦ “ጳውሎስም በአርዮስፋጎስ መካከል ቆሞ እንዲህ አለ፥ የአቴና ሰዎች ሆይ፥ እናንተ በሁሉ ነገር አማልክትን እጅግ እንደምትፈሩ እመለከታለሁ።” (ቍጥር 22)።

አክሎም፣ “የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው። ቢሆንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም። ከእናንተ ከባለ ቅኔዎች አንዳንዶች ደግሞ ‘እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነንና’ ብለው እንደ ተናገሩ፥ በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን።” (ቍጥር 28) ሲል ሁለተኛ የጋራ መንፈሳዊ ዕሴት በእምነታቸው ውስጥ እንዳገኘ ነገራቸው። ባለቅኔዎቻቸውም የእግዚአብሔር ዘመዶች ነን ብለው “እንደ ተናገሩ” እያጣቀሰ፣ እግዚአብሔር ከሰው ሩቅ አለመሆኑን ሲያስገነዝብ እመለከታለን።

ሆኖም ከላይ የጠቀስኩትን ሁለቱን የጋራ ዕሴቶች ካመለከተ በኋላ፣ ሐዋርያው እውነትን በፍቅር እንዴት እንደ ገለጸ እንመልከት፦ “የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ ‘ለማይታወቅ አምላክ’ የሚል ጽሕፈት ያለበትን መሠዊያ ደግሞ አግኝቼአለሁና። እንግዲህ ይህን ሳታውቁ የምታመልኩትን እኔ እነግራችኋለሁ። ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም።” (ቍጥር 23)።

በዚህ በሐዋርያው ጳውሎስ ማብራሪያ ውስጥ፣ “ሳታውቁ የምታመልኩትን” የሚለውን ልብ በሉልኝ። ምን ማለት ነው? ‘አምልኮ ዕውቀትን ይቀድማል? ወይስ ዕውቀት አምልኮን ይቀድማል?’ በእኔ አረዳድ የሰው ነፍስ የፈጣሪዋ እስትንፋስ ስላለባት፣ ዕውቀት በሌለበት ፈጣሪዋን ፍለጋ ትኳትናለች። ስለዚህም ጳውሎስ፣ “ለማይታወቅ አምላክ” ያሉትን በጥበብ ወደ እውነተኛው አምላክ ለመጠቆም ተጠቀመበት።

ኢየሱስ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ግብዝ የሃይማኖት መሪዎችን ፊት ለፊት ይጋፈጣቸው ነበር። ስብከቶቹና ትምህርቶቹ ግን ልክ እንደ ዘመናችን ሰባኪዎች ጅምላ ጨራሽ አልነበሩም።

ቀጣዩ የጳውሎስ ማስተካከያ ደግሞ በቍጥር 29 ላይ ተጠቅሶ እናነብባለን። “እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን፥ አምላክ በሰው ብልሃትና አሳብ የተቀረጸውን ወርቅ ወይም ብር ወይም ድንጋይ እንዲመስል እናስብ ዘንድ አይገባንም።”

እዚህ ላይ የጳውሎስ የሙግት አመክንዮ ግልጽ ሆኖ ይታያል፤ የአመክንዮውም መነሻ የራሳቸው እምነት ነው፤ ‘እንግዲህ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆንን’ የሚለው አባባል። የጳውሎስ ጥያቄ፣ ‘እንግዲህ በእናንተና በእግዚአብሔር መካከል ዝምድና ካለ፣ እናንተም በእግዜር አምሳል ከተፈጠራችሁ፣ ከተቀረፀ ድንጋይ ወይም ወርቅ ጋር እንዴት ልትቆራኙ ወይም ልትዛመዱ ቻላችሁ?’ የሚል ነው።

እንግዲህ ከላይ ያለውን የዐውዳዊ ስብከት ዘዴን ጠቅሰን ስንሞግት፣ አንዳንዶቻችን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢየሱስም በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 13 ላይ፣ “ደንቆሮዎች”፣ “ዕውሮች”፣ “እባቦች”፣ “የእፉኝት ልጆች”፣ “በውጭ በኖራ የተለሰነ መቃብር”፣ ወዘተ. የሚሉ ኀይለ ቃላትን ተጠቅሞ የለም ወይ? የሚል ጥያቄ ልናነሣ እንችላለን። ሆኖም ግን፣ ይህ የማቴዎስ 23 መልእክት ማንን ተደራሽ እንዳደረገ መገንዘብ ይኖርብናል። የማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 23 ቍጥር 13 እንደሚያመለክተው፣ መልእክቱ የተላለፈው ለግብዝ ፈሪሳውያንና ጻፎች እንጂ፣ ለተርታው ምእመን አይደለም። ኢየሱስ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ግብዝ የሃይማኖት መሪዎችን ፊት ለፊት ይጋፈጣቸው ነበር። ስብከቶቹና ትምህርቶቹ ግን ልክ እንደ ዘመናችን ሰባኪዎች ጅምላ ጨራሽ አልነበሩም።

ኢየሱስም ሆነ ቀደምት ሐዋርያትና ነቢያት (መጥምቁ ዮሐንስን ጨምሮ) ግብዞችን በገሠጹበት ልክ መገሠጽ የምንችልበት ከሞራል ልዕልና የሚመነጭ “ሥልጣን” ይኖረን እንደ ሆነ ራሳችንን መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል። 

ለምሳሌ በዮሐንስ ወንጌል ምእራፍ 4 ላይ፣ ኢየሱስ ውሃ ልትቀዳ የመጣችው ሴት አመንዝራ መሆኗን እያወቀ ተግባቦቱን የጀመረው፣ ‘አንቺ ሴተኛ አዳሪና 5 ባሎች የነበሩሽ ነሽ’ በማለት ሳይሆን፣ “ውሃ አጠጪኝ” በሚል ልመና ነበር። እንዲሁም ነቢዩ ናታን ንጉሥ ዳዊት እንዳመነዘረ ካወቀ በኋላ፣ ከእግዚአብሔር የተቀበለውን መልእክት ለንጉሡ ስለሚያቀርብበት መንገድ የጸለየ ይመስለኛል። መልእክት መቀበል አንድ ርምጃ ነው፤ የተቀበልነው መልእክት እንዴት ይተላለፍ የሚለው ግን ሌላ ጕዳይ ነው። ለንጉሥ የተግሣጽ መልእክት የሚተላለፍበት መንገድና ለተርታ እስራኤላዊ መልእክት የሚተላለፍበት መንገድ ለየቅል ነው። እናም ናታን ጥበብ በተሞላ መልኩ፣ ዳዊት ራሱን እንዲወቅስ አደረገው (2 ሳሙኤል 12)። ስሕተትን ከማረም አኳያ ከሁሉም በላይ ስኬታማ የተግባቦት መንገድ፣ ሰዎች የራሳቸውን ስሕተት እንዲመለከቱና ራሳቸውን እንዲወቅሱ የማድረግ ክኅሎት ነው።

በእኔ አተያይ ኢየሱስ በኀይለ ቃል ግብዞችን የገሠጸበትን ግሣጼ፣ ግብዝ ለሆኑ ሰዎች ሥራ ላይ ማዋል እንችል ይሆናል። ነገር ግን፣ ይህን ተግባራዊ ከማድረግ ባለፈ፣ ኢየሱስም ሆነ ቀደምት ሐዋርያትና ነቢያት (መጥምቁ ዮሐንስን ጨምሮ) ግብዞችን በገሠጹበት ልክ መገሠጽ የምንችልበት ከሞራል ልዕልና የሚመነጭ “ሥልጣን” ይኖረን እንደ ሆነ ራሳችንን መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል።

Share this article:

የተዘነጋው አሁን

ሁላችን በሐሳብ ባህር ላይ ቀዛፊዎች ነን። ቀዘፋው ደግሞ በትላንት እና በነገ የሐሳብ ማዕበል የሚናጥ ነው። ከትላንት ለመማርም ሆነ ነገን የተሳካ ለማድረግ አሁንን መኖር መጀመር እንዳለብን ይህ የተካልኝ ነጋ (ዶ/ር) መጣጥፍ መንገድ ይጠቁማል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ሊላሽቅ የሚገባው የኢትዮጵያውያን ልቅ ጀብዱ

የታሪክ አጥኚው አፈወርቅ ኀይሉ (ዶ/ር) በዚህ ጽሑፉ፣ ኢትዮጵያዊነት “ጨዋነት” ብቻ አለመሆኑን፤ ይልቁን ጸያፍ የሆነ “የጀብደኝነት” አመለካከት ከማንነታችን ጋር የተጋባ መሆኑን ከታሪካችንና ከአሁኑ ሁናቴ ጋር ያዛምደዋል። “ልቅ” የተባለው ይህ “ጀብደኝነት” በቶሎ ካልላሸቀ ያጠፋናል ይላል ዶ/ር አፈወርቅ።

ተጨማሪ ያንብቡ

ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ – መፍቀሬ አፍላጦን ካህን

በብርታቱ ኀያልነት ያስገበራቸውን አገራት በግሪክ ፍልስፍናና ባህል ማጥመቅን እንደ ዐቢይ ተግባሩ አድርጎ ይዞታል፡፡ እናም የመከከለኛው ምሥራቅ፣ የአውሮፓና የሰሜን አፍሪካ ግዛቶችን በእጁ ባስወደቀ ጊዜ በጽርዕ ባህልና ፍልስፍና ከመንከር ወደ ኋላ አላለም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.