[the_ad_group id=”107″]

የቃላት ጡጫ እና ጉዳቱ

የብእር ሐሳብ ከማይነጥፍባቸው ነገሮች አንዱ የፍቅር ጉዳይ ነውና ዛሬም ስለ ፍቅር እናውጋ። የፍቅር ታሪኮችን ስናደምጥ ደግሞ ተያያዥ ስሜት መውረሩ አይቀርም። አንዳንዱ ታሪክ ልባችንን ጮቤ የሚያስረግጥ ነው፤ የተከፈለው መሥዋዕትነት ‘ብዙ ውኾች’ ፍቅርን ለማጥፋት የፈረጠመ ጡጫ እንደሌላቸው ምስክር ነው (መኀ. 8፥7)። ሌላው ደግሞ ውስጣችን በቁጭት እንዲብሰከሰክ ምክንያት የሚሆን ነው (2 ሳሙ. 13፥1-20)። በስመ ፍቅር አንዳንዶች የተጎነጩትን ጭቆና እና ግፍን ተመልክቶ አለመቆጣት በርግጥም የተባባሪ ያህል ያስቆጥራል። ከሁሉም የሚከፋው ደግሞ ተጠቂነታቸው ሳያንስ አጥቂያቸውን “የተዋጣለት አፍቃሪ” በሚል ሲያመሰግኑት መስማት ልብን የሚሰብር ነው። የእነዚህ ወገኖች አእምሮ የጭቆና ሂደቱን ከመላመዱ የተነሣ ራሳቸውን በአጥፊነት እንዲፈርጁ ማስገደዱ ሲታሰብ ደግሞ የበለጠ ያስከፋል። የያዛቸውን ምጥ ቢናገሩት እንኳ ነገሩን አቅልሎ የሚያይ ማኅበረ ሰባዊ ዕይታ መኖሩ ኀዘኑን በብቸኝነት እንዲገፉት ያደርጋቸዋል። ይህ ደግሞ የበለጠ ስሜት የሚጎዳ ይሆናል።

ይህ ጉዳይ ለውይይት ቢቀርብ ምናልባት አንዳንዶችን አድን ይሆናል በሚል፣ በፍቅር ስም በሚደረግ ጭቆናና ማጎሳቆል ላይ ብእሬ እንድትነሣ ግድ ብያታለሁ። በዚህም ስሜታዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጉዳትን ብቻ ለመዳሰስ ጥረት ተደርጓል። በስሜትና በሥነ ልቦና ላይ የሚደርስ ጥቃት በተደጋጋሚ በቃል የሚደረግ የማይነጥፍ ነቀፌታ፣ ንቀታዊ ምልከታ፣ ሌላውን ከመጠን ባለፈ መቆጣጠር መሻት፣ ያለ መፈናፈኛ መግዛት፣ ማንኳሰስ፣ በሰበብ አስባቡ መቅጣት፣ በንቀትና በማሳፈር ከሌሎች ለመለየት የሚደረጉ ሙከራዎችን ያካትታል።

1. “በፍቅር መጠቃት”

በርካቶች መጠቃት ከፍቅር ትሥሥር ጋር ተያይዞ ሲነገር የሚመጣላቸው አካላዊ ድብደባ እና ጉዳቶቹ ናቸው። እንዲህ ዐይነቱ የተንሰራፋ ማኅበራዊ ምልከታ የሚያስከትለውን ክፉ ፍሬ ደግሞ እያጨድን ነው። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ ተጠቂዎቹ አካላዊ ድብደባ እስካልደረሰባቸው ድረስ ምንም እንዳልተፈጸመ እንዲቆጠር ማድረጉ አይቀርም። መደብደባቸውን የሚያሳይ ሰንበር፣ የበለዘ ዐይን ወይም የተሰበረ አካል እስካልታየ ድረስ ሁሉ ደኅና እንደ ሆነ ይታሰባል። እንዲህ ያለውን ግንኙነት በድፍረት ሸሽተው ሲሄዱም ራሳቸውን እንደ ጥፋተኛ በመቁጠር የኅሊና ወቀሳ እንዲያስተናግዱ ምክንያትም ይሆናል። በአንጻሩ አጎሳቃዩ ሰው እንደ ተበደለ እያስወራ በኩራት የሚንጎማለልበትን ልብ ይሰጠዋል።

‘በፍቅር ምክንያት የሚደርስን ስሜታዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃትን ለምን እንዲህ አቃለን ተመለከትነው?’ መልሱ ብዙ ነው። በዋናነት ማጎሳቆሉ በምሥጢር የሚካሄድ መሆኑ፣ ቀስ በቀስ እየጨመረ ከመሄዱ የተነሣ ተጎሳቆዮቹ ስለሚለምዱት መጎሳቆላቸውን ልብ ማለት ስለሚቸግራቸው፣ የበደሉ መልክ ብዙና ተበዳዮቹም በቂ ግንዛቤ ስለሌላቸው “ጉስቁልና”፣“መበደል”የምንለውንሚዛንበየጊዜውእየሸረሸረውናእያላመደንስለሚሄድ ጭምር ነው።

ከብዙዎቻችን ግምት በተለየ ግን በሚሸነቁሩ ቃላት እንዲሁም በሌሎች መልኩ የሚደረግ ሽንቆጣ ከምንገምተው በላይ በስሜታችን ላይ የሚደርስ ሥነ ልቦናዊ ቅጥቀጣ ከአካላዊ ስብራት ባላነሰ ይጎዳናል። ስሜቱና ሥነ ልቦናው የተጠቃ ሰው ለራሱ የሚሰጠው ዋጋ፣ ተቀባይነት እና አድናቆት እንዲሁም ስለማንነቱ ያለው ግንዛቤ ክፉኛ የተጎዳ ይሆናል። ከዚህ ጉዳት ማገግም ቢቻልም የሚሰጡ ድጋፎች አናሳ ከመሆናቸው የተነሣ የረጅም ጊዜ ጠባሳን በሕይወታችን ውስጥ ጥሎ ያልፋል። ለዚህም ይመስለኛል ጠቢቡ ሲናገር፣ “የሰው ነፍስ ሕመሙን ይታገሣል፤ የተቀጠቀጠን መንፈስ ግን ማን ያጠንክረዋል?” የሚለን (ምሳ. 18፥22)፤ እንዲሁም በሌላ ሥፍራ፣ “ደስ ያላት ልብ መልካም መድኃኒት ናት፤ ያዘነች ነፍስ ግን አጥንትን ታደርቃለች።” (ምሳ. 17፥22) በሚል ውስጣዊ ጉዳቱ እንዲሁ በቀላሉ የሚተው አለመሆኑን የሚጠቁመን። የልብ ስብራት በርግጥም አደገኛና በቀላሉ የማይጠገን ነው። በርካቶች በፍቅር ስም እየደረሰባቸው ያለውን ጉስቅልና እና ጭቆና መነሾ ነቅሶ በማውጣት እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ራሳቸው ለተጠቂነታቸው ጥፋተኛ አድርገው በመቁጠር የራሳቸውን ሕመም ይበልጡኑ እንዲያባብሱት ይሆናል።

የዚህ ዐይነት ስሜት ክፋቱ ደግሞ ተጠቂና አጎሳቋይ በሚያደርግ ትሥሥር ውስጥ እንዲቆዩ አሊያም ነገሩን እጅጉን አቅልለው በመመልከት እርምጃን እንዳይወስዱ ወጥመድ መሆኑ ነው። መጥፎነቱ ደግሞ በስሜትና በሥነ ልቦና ላይ የሚደርስ ጥፋትን አንዴ ውስጣችን ከለመደ በኋላ አካላዊ ጉዳት በሂደት የመምጣት ዕድሉ የሰፋ መሆኑ ነው። ጥቃት ፈጻሚው በበኩሉ የልብ ልብ እየተሰማውና የሚያደርሰው የስሜትና የሥነ ልቦና ጉዳት አልበቃው እያለው ይሄዳል። እኛም መጠቃትን ውስጣችን ስለለመደው አካላዊው ጥቃት ሲመጣም የምናስተናግድበትን አእምሮና ልብ እናዳብራለን። ዑደቱ በዚህ መንገድ በመቀጠልም ጉዳታችንን እያባሰው የእውነታ ምልከታችንንም ጭምር ያዛባል። ከዚህም የተነሣ በሕይወት ውስጥ ያሉት በትክክለኛ መልኩ እንዲመለከቱ ተጠቂዎቹ ዕርዳታን ከማኅበረ ሰቡ በተለይ ደግሞ ከሚቀርቧቸው ሰዎች ይፈልጋሉ። መርዳት እንድንችል ደግሞ በፍቅር ስም የሚደረጉ ማጎሳቆሎችን አስመልክቶ በቂ ግንዛቤ ሊኖረን ያስፈልጋል።

2. ጉዳቱ

በስሜት እና በሥነ ልቦና ላይ የሚደርስ ጥቀት በማንነት ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮች እንዲከሰቱ ያደርጋል። በዚህ ዐይነት ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ለዘላቂ ድብታ፣ ለነገሮች ያላቸው መነሣሣት መጥፋት፣ የነገሮች መደበላለቅ፣ ውሳኔ መወሰን መቸገር፣ ትኩረትን ለዓላማ ማሰባሰብ አለመቻል፣ ስለ ራስ ያላቸው አዎንታዊ ምልከታ መቀነስ፣ እርባና እንደሌላቸውና እንደማይጠቅሙ ማመን፣ ራስን መውቀስ እንዲሁም የሚጎዱ ነገሮችን በራስ ላይ በማድረግ ጭምር ሊጠመዱ ይችላሉ። ከላይ ከተጠቀሱት ችግሮች የተነሣም ተጠቂው ግለ ሰብ በራሱ ያለው መተማመን፣ ለራስ ያለው ግምት፣ በራሱ ዕይታ ላይ ያለው መደገፍና ራሱን የሚመለከትበት አቅም እየተሸረሸረ ይሄዳል። ይህ ሁሉ የሚካሄድበት መንገድ ነገሮቻችንን ሁሉ አቅልሎ በመመልከት፣ በዕይታችን የበታችነት እንዲሰማን ለማድረግ ወይም በመሪነትና በአስተማሪነት ስም ጭምር ሊደረግ መቻሉ ነው። በየትኛውም መንገድ ነገሩ ይደረግ ፍጻሜው ስለ ራስ ያለንን ግንዛቤና ትርጉም እንድናጣ ማድረግ ይሆናል።1

የዚሁ ድርጊት ሰለባዎችም የሚደርስባቸውን ተደጋጋሚ ወቀሳና ትችት ወይ እንዳለ ይቀበሉታል አሊያም ደግሞ ግራ ይጋቡበታል። ራሳቸውንም ደጋግመው ‘ይህን ያህል ችግር ያለብኝ ሰው ነኝ ወይስ ማንም ሰው የማያስደስተው ሰው ከመሆን የተነሣ ነው?’ ብለው ይጠይቃሉ። ትሥሥራቸውን አስመልክቶ እንዲሁ ‘መቀጠል አለብኝ ወይስ መቋረጥ ይኖርበታል?’ ይላሉ። በመጨረሻም ይህን ያህል የማልረባ ከሆንኩ ነገሮችን በራሴ መወሰን አይኖርብኝም የሚል ድምዳሜም ላይ ሊደርሱ ይችላሉ። አያይዘውም ምናልባትም ‘ከእርሱ ብለይ ሌላ የሚወደኝ ሰው ሁሉ ላይኖር ይችላል’ በማለትም ጭምር ሊያምኑ ይችላሉ። በሂደትም ራሳቸውን አስመልክቶ ለጥፋት ሁሉ ተጠያቂ፣ ለነገሮች ብቁ ያልሆነ፣ የማያጓጓ እና የማይወደድ አድርገው ሁሉ ይቆጥራሉ። ሰለባው እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሣም እጅጉኑ ሕመም እንዲሰማን ያደርጋል።

ነገሩ ውስጥ ድረስ ዘልቆ እንደመግባቱም በቀላሉ ወደነበረበት የማይመለስ ጠባሳን ሁሉ ትቶ የሚያልፍባቸው አጋጣሚዎች ትንሽ አይደሉም። ውስጣችንንም በዝግታ በመገዝገዝና በራሳችን ላይ ያለንን መተማመን በመሸርሸር የትኛውንም ነገር በትክክል ተመልክተን መወሰን የምንችልበትን አቅማችንን ሁሉ ሊያሳጣንም ጭምር ይችላል። ነገሩ ሥር እየሰደደ ሲሄድ የሆነ ዐይነት ችግር እንዳለብን ወይም አእምሯችንን በተወሰነ መልኩም ጭምር እያጣነው እንደ ሆነ ሁሉ ሊሰማንም ይችላል። ስሜታችን መጎዳቱ በቀጠለ ቁጥር ግን በግንኙነታችን ላይ አሉታዊ ጥላውን ማሳደሩ አይቀርም። ከዚህም የተነሣ ቅራኔንና ጥላቻን በሂደት የሚወልድ ዘር የመተው ዕድል ከፍተኛ ነው።

ከዚህ በፊት ምንም ያህል ተዋደን ቢሆን እንኳ ስሜታችን እጅጉን በተጎዳ ጊዜና የሕይወታችን ቀጣይ አካል ሲሆን ፍቅራችን በፍርሃት፣ በንዴት፣ በጥፋተኝነት ስሜትና በእፍረት ሊሞላ ይችላል። በሂደትም ልክ በደም ሥራችን ውስጥ እንደገባ መርዝ ይበልጡኑ አደገኛ ይሆናል። ስለዚህም ፍቅር በሚፈለገው መልኩ እንዳያብባና እንዳይጎመራ መደናቅፍ ይሆናል። ከዚህ በፊት በሌላኛው ሰው ውስጥ እንመለከታቸው የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን እንኳ ማድነቅ እስክንቸገር ሁሉ ልንደርስ እንችላለን። አንዳችን ለሌላችን የሚኖረን ክብር ከዕለት ወደ ዕለት እጅጉን እየደበዘዘ ይሄዳል። በተለይ እየተጠቃ ያለው ሰው ጥላቻን በውስጡ እያዳበረ ይሄዳል። በሂደትም ለሚያጠፏቸው ጥፋቶች ይቅርታ ከመጠየቅና ከማስተካከል ይለቅ ሰበብ የሚፈልግና ትሥሥሩን ይበልጡኑ የሚጎዳ ይሆናል። በሂደትም በቃላትና በድርጊት ጅማሬን ያገኘው ጥሰት ደግሞ አካላዊ ድብደባን የሚያስከትል ይሆናል።

ቤቱም ጭቅጭቅ የሞላበት ማንም ማንንም የማይቀበልበት ድባብ ይፈጠርበታል። ዕለታዊ ተግባራትን በትክክል መፈጸም የሚያስችል ጉልበትን ጭምር እስኪያሳጣ የሚደርስባቸው አጋጣሚዎችም በርካቶች ናቸው። በተለይ ደግሞ ጥሰቱ የሚካሄደው በሁለቱም አቅጣጫ ሲሆንና በቤተ ሰቡ ውስጥ ተንሰራፍቶ ሲቀመጥ ሁለቱም ስለራሳቸው ያላቸው መተማመን እየቀነሰ ስለሚመጣ ቅርርባቸውና መጣበቃቸው በሚያስገርም ሁኔታ ይበልጡኑ እየጠነከረ ይሄዳል። ይህ ቅርርብ የሚከናወነው አንዳቸው ሌላቸውን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሱበት ባለበት ድባብ እንደ መሆኑ ፍቅርን ከማሳበብ ይልቅ ይበልጡኑ እንዲፈራርስ ማድረጉ አይቀርም። እያንዳንዱም አባል ሌላውን ሰው መጉዳት የሚችልበት አጋጣሚ እየጨመረም ይሄዳል።

3. መነሾዎቹ

በጥቅሉ በፍቅር ስም የሚደረጉ ጉዳቶች ዋና መነሾዎቻቸው በሌላው ላይ የበላይ ከመሆንና ከመቆጣጠር ፍላጎት ጋር ይያያዛል። ሌላውን መቆጣጠር ሲባል ብዙዎቻችን የሚመጣልን ጉልበት ወይም ኀይልን መጠቀም ነው። ኀይል ስንል ግን ጉልበትን መጠቀም ከሚለው ጋር ሁልጊዜ ላይያዝ መቻሉንና አደራረጉም ለተጠቂው ግልጽ ባልሆነ መንገድ ሊተገበር እንደሚችልም ጭምር መገንዘብ ይኖርብናል። ቁጥጥሩ የሚደረገው በቃላትና በተግባራት ስለሆነም ልብ ካላሉት በአስተውሎታችን ላይ መዘገብም ይችላል። ለምሳሌም ያህል ከሌላ ሰው ጋር በታየች ቁጥር ሰበብ ፈልጎ ያንን ሰው ለመጣላት የሚፈልገውን ሰው በፍቅር ድብን እንዳለላትና እንደ ሚቀናባት በማሰብ “ልዩ ዐይነት ሴት” እንደሆነች ልታስብ ትችላለች። እንዲሁም ደግሞ ከጓደኞቿ ጋር ተነጥላ በዋለች ቁጥር እንዴት እንደናፈቀችው መልእክት ቤት የሚተውላትን ሰው “የሚገርም አፍቃሪ ነው” ብላ ልታስብ ትችላለች።

እነዚህ ድርጊቶች ግን እንዲያው ለብቻቸው ተንጥለው የምንመለከታቸው ሳይሆን የተደረጉበትን ዓላማም ለመገንዘብ የምንሞክርባቸው ሊሆኑ ያስፈልጋል። የእነዚህ ድርጊቶች ዋንኛ ዓላማ በተፈቃሪ ላይ ለመሠልጠንና ለመቆጣጠር ከመሻት የተነሣ ሊሆን ስለሚችል በጥንቃቄ ልንመረምር፣ ገደቡን በሚያልፉበትም ጊዜ ልናቆማቸው ያስፈልጋል። ከዚህ በፊት እንደጠቀስኩት ለእንዲህ ዐይነት ጥቃት መሠረት በመጣል ሂደት በማኅበረ ሰቡ ውስጥ ያሉ ዕይታዎች ከፍተኛ ድርሻን ይወስዳሉ። ስለዚህም ከዚህ በታች በፍቅር ስም የሚደረጉ ስሜታዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃቶችን አስመልክቶ እንደ ማኅበረ ሰብ መቃኘት የሚያስፈልጉንን አቅጣጫዎች አነሣለሁኝ።

4. ለመጠቃት አንተባበር

ሥነ ልቦናዊ ጥቃት አናሳ ስፍራ እንዲሰጠው ያደረጉና ማስተካከያ የሚፈልጉ ዕይታዎች በማኅበረ ሰቡ ውስጥም ሆነ በግለ ሰብ ደረጃ አሉ። ከእነዚህ መካከል በፍቅር ስም ለሚደረጉ ጥቃቶች ጥፋተኛ አንዱን ብቻ አድርጎ ማቅረብ ነው። በጥንዶች መካከል የሚከሰት ማንኛውም ችግር የጋራ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ለዚህም ሦስት ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ። አንደኛው፣ ችግሩ የመነጨው በጉድኝታቸው ውስጥ ከመሆኑና ትሥሥሩ በሌለበት ችግሩ ሊነሣ ካለመቻሉ ጋር ይያያዛል። ሁለተኛው፣ ጉዳቱ የሚያደርሰው ተጽእኖ በዋነኛነት ትሥሥሩ ላይ ከመሆኑ አንጻር ሲሆን፣ ሦስተኛው ደግሞ ነገረ ጉዳዩ መፍትሔ እንዲያገኝ ከተፈለገም ኀላፊነቱ የሁለቱም መሆኑን መዘንጋት ስለሌለበት ጭምር ነው።

በማኅበረ ሰቡ ተንሰራፍቶ ያለው ምልከታ አንዱን ጥፋተኛ ሌላኛውን ተበዳይ አድርጎ መቁጠር ነው። ከዚህም የተነሣ ሁለቱን በትብብር የሚያሠራ የሚሆንባቸው ጊዜያት አናሳ ናቸው። እርግጥ ነው፤ ማንኛውም ጥፋት በመነሾነት ወደ አንዱ ሊጠቆም ይችላል። ይሁን እንጂ፣ ያው ጥፋት በዘላቂነት የቀጠለ እንደ ሆነ የሌላኛው ሰው ትብብር እንዳስፈለገው መዘንጋት የለበትም። የዚህ አንድምታ ደግሞ ግልጽ ነው፤ ቀጣይነት ያለው የሥነ ልቦና እና የስሜት ጥቃት ተበዳዩን በተወሰነ መልኩ የጥፋቱ ተባባሪ ማድረግ ሲቻል ነው። ተበዳዩ እንዲህ ዐይነት አሉታዊ ተጽእኖን እምቢ የሚልበት ቁርጥ ያለ አቋም ሲይዝ አጥቂው በቀላሉ ነገረ ጉዳዩን ለመፈጸም ይቸገራል። ለአጥቂው የሚያስተላልፈው መልእክትም ይህን የመሰለው ባሕርይ በምንም መልኩ ተቀባይነት እንደማይኖረው ግልጽ በሆነና በማያሻማ መልኩ ያሳያል፤ ግንኙነቱ ወደ ፊት መቀጠል ካለበት መለወጥ ግዴታው እንደ ሆነም አያይዞ ያስገነዝበዋል። በዚህ መልኩ ማኅበረ ሰቡ ሲስተካከል በቤተ ሰብ ውስጥ የሚደረጉ በርካታ አሰቃቂ ግፎችን የማይቀበልና እንቢ የሚሉ ሰዎች እየተፈጠሩ ይሄዳሉ።


ማጣቀሻ

  1.  Beverly Engel, The Emo onally Abusive Rela onship: How to Stop Being Abused and How to Stop Abusing (New York: John Wiley & Sons, 2002), 12-14.

Tekalign Nega (Ph.D.)

ተካልኝ ነጋ (ፒኤችዲ) ከባለቤቱ ከትኅትና መስፍን ጋር በአዲስ አበባ ይኖራል። በአሁኑ ጊዜ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት መዕረግ የሚያስተምር ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የድኅረ ምረቃ የሥነ መለኮት ትምህርት ቤት (ኤገስት) ተጋባዥ መምህር ነው። ዶ/ር ተካልኝ “የጸሎት-የንግድ ቤት?!” መጽሐፍ ደራሲ ከመሆኑ ባሻገር፣ የተለያዩ መጣጥፎችን በክርስቲያናዊ ሚዲያ በማቅረብ፣ በተለያዩ ርእሰ ጉዮች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎችን በማዘጋጀት፣ ለመሪዎች ሥልጠና በማቅረብ፣ በተለያዩ አገር አቀፋዊ ኮሚቴዎች ውስጥ በመሳተፍ እንዲሁም በስብከተ ወንጌል አገልግሎቱ በወንጌላውያን አማኞች መካከል ይታወቃል። የፒኤችዲ ትምህርቱንም ያጠናቀቀው ኔዘርላንድ አገር ከሚገኘው ቲልበርግ ዩኒቨርስቲ በካልቸራል ስተዲስ (Islamic studies) ነው። ከዚህ ቀደምም በአካውንቲንግ እና ፋይናንስ፣ እንዲሁም በሥነ ልቦና ጥናት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አጠናቅቋል። ከኤገስትም እንዲሁ የማስተርስ ዲግሪ በሥነ መለኮት እና የሪሰርች ማስተርስ በክርስቲያን ሙስሊም ግንኙነት ላይ ሠርቷል። የጋራ ትውስታ (Collective memory)፣ በኢስላማዊ ቅስቀሳዎች (Islamic activism)፣ በብልጽግና ወንጌል፣ በጋራ ጥቅሞች (Common good)፣ በሜንቶሪንግና በማማከር ላይ ምርምር የማድረግ ፍላጎት አለው።

Share this article:

Mindset of Africa

“The mindset of citizens that thought of tribal differences had the same potential to think of commonalities…” Writes Genaye Eshetu, as she briefly examines the root cause of the Continent–Africa.

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.