[the_ad_group id=”107″]

አንብቡና አስተላልፋት

የምወድህ (የጽሑፍ ልማድ ኾኖ እንጂ አንቺም አለሽበት) አንባቢዬ ሆይ፣ “ምን ላንብብ? ለማንስ ላስተላልፋት?” እንደምትለኝ እገምታለሁ። ይህችን መጣጥፍ ለመጫር ምክንያት የኾነኝን ነገር መጨረሻ ላይ ነው የምነግርህ። በቅድሚያ ስለ ንባብ/ ማንበብ ጥቂት እንድጫጭር እያነበብህ ፍቀድልኝ። ልጆች ሳለን አባባ ተስፋዬ ሳህሉ በቀበሌ ቴሌቪዥን (ሥርጭቱ የኢቴቪ ቢኾንም እኛ የምናየው የቀበሌ ኅብረት ሱቅ በረንዳ ሥር ተሰጥተን ነበርና፣ “የቀበሌ ቴሌቪዥን” ነበር የሚመስለን) መስኮት ሲመጡ በጕጕት እንጠብቃቸው ነበር። ከጣፋጭና ተናፋቂ ዝግጅቶቻቸው ማሳረጊያ ላይ ታዲያ “ደኅና ሁኑ ልጆች፣ የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች” በምትሰኘዋ የስንብት ቃላቸው እየባባን ወደየመጣንበት እንበታተናለን፤ በአባባላቸው እንደሰታለን፤ የዛሬ “አበባዎች” ነገ “ፍሬዎች” እንኾናለን ብለን። አንተም ታስታውሳቸው ይኾናል።

ይህን ነገር ወደ አንባቢነት ብንለውጠውስ? የዛሬ አንባቢዎች የነገ መሪዎች የመኾናቸው ነገር የገባቸው “አንባቢዎች መሪዎች ናቸው” ብለዋል። እኛ መዳፍ ስናነብ፣ የቡና ሲኒ ገልብጠን ስንደናበርና ሞራ ስናጠና ኖረን አገሩን ከቡና ጠጪነት፣ ከበሬ ኢኮኖሚና ከሐሜት ሰባክያን ብኩንነት ሳናወጣው ቀርተናል። “ያነበቡስ የት ደረሱ?” የሚሉ ወገኖች እንዳሉም ሰምተናል። መልሱ “የት አልደረሱም?” የሚል ነው። በርግጥ አስተዋይነትን የግድ ከአንባቢነት ጋር ብቻ አናቈራኘውም። ፊደል ያልቈጠሩ ሕያው ቤተ መጻሕፍት በአፍሪካ ጓዳ ጐድጓዳውን ሞልተውታልና። ለዚህም እኮ ነው በአፍሪካ ሰማይ ሥር፣ አንድ አረጋዊ ሲሞት፣ “ላይብረሪውተቃጠለ” የሚባለው። ኾኖም የማንበብ ሸጋ ዋጋ ሲጣጣል ግን ዝም አይባልም። ከንባብ ርቀን ለመቅረታችን ማሳያ አምጡ ቢባል ከባድ አይኾንም። “ዕንቍህን ከአፍሪካዊ ለመደበቅ ከፈለግህ፣ በመጽሐፍ ውስጥ አስቀምጠው” በማለት የተሣለቁብን የሽሙጥ ቃል ብቻውን ብዙ ይናገራል።

በዚህ ወቀሳ የማይስማሙ ወገኖች ይኖራሉ። እንዲያውም አንድ ግብዝ በዚሁ ርእሰ ጕዳይ በተዘጋጀ ዐውደ ጥናት ላይ “የኛ አባቶች እንኳን መጽሐፍ ሞራ ያነብባሉ” በማለት ሲገደር ተሰምቷል። ድካማችንን ተረድተን ማስተካከሉ የተሻለ ነበር። ማንበብ ማነብነብ አይደለም፤ “የቀለም ቀንድ”ነትም አይኾንም፤ ብልቃጥም ቀለም ያስቀምጣልና። ያነበብነውን መተንተን፣ ማሔስ መተርጐምና በሕይወት ማዛመድን ይጠይቃል። ከሚነበበውም “ምርትና ግርዱን” መለየት ይሻል። የሚያነብብ ማኅበረ ሰብ ተስፋ ያለው ነው። “መጻሕፍት የገነቡትን ሕንጻ የዘመናት ብዛት አያፈርሰውም” የሚባለው ዝነኛ ጥቅስ የዋዛ መልእክት አልተሸከመም። የአንድ ተማሪ ውጤታማነት የሚለካው በማንበብ ልምዱና ትጋቱ ነው። በየትኛውም የሥራ መስክ የተሰማራ ሰው በሙያው ልኅቀት ለማሳየትም ኾነ ችግር ፈቺነቱን ለማጐልበት ንባብ ያስፈልገዋል።

ማንበብ ስለቻልን እግዚአብሔርን ማመስገን አለብን። ዛሬ፣ በ21ኛው ምእት ዓመት፣ ከስድስት ሰዎች አንዱ ማንበብ አይችልም ሲባል ስንሰማ ያስገርመናል፤ ያሳዝነናልም። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የትምህርት ዕድል ዕጦት ነው። ትምህርት አግኝተው ሳሉ የማያነቡም አሉ። ትምህርት ዐይን ይገልጣል፤ ያለ ትምህርት ሊቆም የሚፈልግ ማኅበረ ሰብ በድቡሽት ላይ የተመሠረተ ቤት ይመስላል ያሉት ማን ነበሩ? ጃንሆይ ይመስሉኛል። ለመማር መጨረሻ የለውም። መማር ያቆመ ልቡና እየዛገና እየሻገተ ነው የሚሄደው። መጻሕፍት ግን የትምህርት ገበያ ናቸው። በርግጥ ማንበብ ከሚችሉ መካከል፣ ብዙዎቹ፣ አዘውትሮ የማንበብ ልማድ የላቸውም ይባላል። ይሁንና ማንበባችን ዕውቀት ለመገብየት፣ ከሌሎች ሰዎች የሕይወት ልምድና ተሞክሮ ለመማር እንዲሁም በሕይወት የሚገጥሙንን አሳሳቢ ነገሮች ለመወጣት የሚያግዙ ሐሳቦች ለማግኘት እንደሚያስችለን የታወቀ ነው።

ዘነብ ኢትዮጵያዊ በመጽሐፈ ጨዋታ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ፣ እንዲህ ሲል ይጮኻል፤ “እናንተ ሰነፎች ድንቍርናን ከማይመለስበት ሽጡት፤ የሰነበተ እንደኾነ ይገድላችኋል”። ድንቍርና ከማይመለስበት ርቆ የሚሸጠው በቃለ እግዚአብሔር ዕውቀት፣ በማንበብ ገበያ፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በአሰላስሎ አይደለምን? “ሩቅ አስቦ ሩቅ ለማደር” መጽሐፍ ምርኵዝ ነው፤ መጽሐፍ መነጽር ነው። ዘነብ እንደሚለው “መጽሐፍ ምንድነው? ለሚመለከተው ሰው ሩቅ ያሳያል”። አርቆ በማያይ ካህን ስንት ሕይወት መከነ? የቅርቡን ብቻ በሚያይ መምህር ስንት እንቦቃቅላ ተቀጨ? አርቆ በማያይ ሐኪም ስንት ሕሙም ደከመ? አርቆ በማያይ ፖለቲከኛ ስንት ዜጋ ተፈጀ? አርቆ በማያይ ሰባኪና ነቢይ ምን ያህል ጎጆ አዘነበለ?

በሌላ በኩል በማንበብ መበርታት ይገባናል ሲባል የግድ በአውሮጳዊው ዕውቀት ብቻ መምጠቅ አለብን ማለት አለመኾኑ ከግንዛቤ መግባት አለበት። ዐውዳዊ ለመኾን እንችል ዘንድ የራሳችንንም ጓዳ ማሠሥ ይኖርብናል። ብርሃኑ ድንቄ በአልቦ ዘመድ ላይ “መቼም የዛሬው የኢትዮጵያ ትውልድ መማር አይፈልግም። እንዲያው በባዶ ቤት ዐዋቂ ነኝ ብሏል። ለማንበብ የሚፈልገው ርካሽ የኾነ እንግሊዝኛ succsus story ብቻ ነው። ቍም ነገር ያለው ባሕላዊ፣ ታሪካዊ የአማርኛ መጽሐፍ አንብብ ያልከው እንደ ኾነ መላሱ ይተሳሰራል። ወይም ይሥቅብሃል” ይላሉ። ተሓዝቦታቸው ከእውነታው የራቀ ነው ለማለት ይከብደኛል።

ዛሬ፣ ዛሬ ከመጽሐፍ ይልቅ የሆሊዉድ፣ የቦሊውድና ሌሎችም ፊልሞች በብዙዎቻችን እጅ በብዛት መገኘታቸው ምን ያመለክተናል? ከመጽሐፍ ቤት ይልቅ የጫት ኪዎክስና የሺሻ ጕረኖ እንደ እንጕዳይ የሚፈላበት ሀገር ውስጥ መኖር “ባይቈጭም፣ ያንገበግባል”። ከመጽሐፍ መደብር ይልቅ ቡቲክ፣ ካፌና የ“ኑ ቡና ጠጡ” ታዛዎች የምናስፋፋ ወገኖች ኾነናል። በብዛት ሲነበቡ ከተገኙም ጋዜጦች በተለይም ቀለማም የስፖርት ጋዜጦች ናቸውና ይገርመናል።

አስቂኝ ድራማዎችና የኤሌክትሮኒክ ብዙኀን መገናኛ መርሐ ግብሮች ከሌሎች ነገሮች ጋር ተዳምረው ንባብ በብዙ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ቦታ እንዲነፈገው ምክንያት አልኾኑም ማለት ይቻላል? አንድ ሰው አዘውትሮ ቴሌቪዥን ብቻ የሚመለከትና እምብዛም የማያነብብ ከኾነ የማንበብ ችሎታው ብቻ ሳይኾን በትክክል የማሰብና የማመዛዘን እንዲሁም ሐሳቡን አቀነባብሮ የመግለጽ ክኅሎቱ እንደሚዳከም ባለሙያዎች ይናገራሉ። የብዙኀን መገናኛው በስፋት ሽፋን የሚሰጠው ለዘፈን፣ ለኳስና ለቀልድ መኾኑ በንባብ ባህል ዕድገታችን ላይ የራሱን ችግር ሳያደርስ አልቀረም። ማኅበራዊ ድረ ገጾችም ያመጡት ጣጣም ቀላል አይመስልም።

ርእሰ ጕዳዩን ለማጕላት “ማንበብ አማራጭ አይደለም” የሚሉ አሉ። “ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል” ሲባልም ሰምተናል። ታዲያ “ማንበብ ተማሪ ያደርጋል” ቢባልም ጥሩ ነው፤ ትሕትና ይጨምራልና። በርግጥ ተምህሯዊ ዕብሪተኛነት እንደሚታገለን አልጠፋኝም። በጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት ተሞልተን “በሰማበት ጣዱን” ብንል ግን የሚተርፈን ትዝብት መኾኑን ለማጠየቅ ነው እንጅ። በየኔታ የአብነት ትምህርት ቤት ደጃፍ አንጻር ያልፍ የነበረ አንድ ሰው ተማሪዎቹ “ሀ” ሲሉ ስለሰማ፣ “አዬ፣ ገና ምኑ ተይዞ” ሲል ተደመመ። በአንዲት የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪያችንን እንዳጠናቀቅን ሁሉን ያወቅን ለመምሰል ሲዳዳን ቢመለከተን ምን ሊለን ኖሯል? “አምስት ስንኝ በወጉ አገጣጥመን ማወናገር ሳይሳካልን ‘ገጣሚ፣ ባለቅኔና ሎሬት’ መሰኘት ያስጐመዠናል” ያለው ማን ነበር? ደራሲ፣ አርቲስት፣ ኮሜዲያን፣ ኢንጂኒየር … ለመባልማ ማን ከልካይ አለብን? ያላነበቡትን መጽሐፍ ድንቅነትና ለትውልድ ሁሉ ያለውን ጠቀሜታ አጀብ በሚያሰኝ አስተያየት የሚመሰክሩባት ሀገር ከእኛዋ ሌላ ትኖር አይመስለኝም፤ ብቻ ታዋቂነት፣ ገንዘብ፣ ዝና እና አፍ ይኑር። አንድ ነገር ግን መታወቅ ያለበት ይመስለኛል፤ የማናነብብ ከኾነ የሚያነብበን የለም።

መሠረተ ትምህርት አጠናቀው “ከማይምነት የነጹ” እናት በሚኖሩባት አንዲት መንደር ታላቅ አክብሮት ይሰጣቸው እንደ ነበር ይነገራል። በወቅቱ ከየዘመቻ ጣቢያውና ከየጦር ግንባሩ የሚላኩ ደብዳቤዎችን ለመንደርተኛው በማንበብ በሚሰጡት አገልግሎት ምክንያት ሴትዮዋ እንደ መንደሪቱ “ዐይን” ይቈጠሩ ነበር። በሰፈሩ ያለሳቸው ሌላ አንባቢ አለመኖሩን ስለተገነዘቡ ለንባብ ሥራቸው ወሮታ እስከ መጠየቅ ደረሱ። አስነባቢም ወደ ወይዘሮዋ መጥቶ ሲለማመጥ መዋሉ የዘወትር ልማድ ኾነ። ተራ እስኪደርስ በትግሥት መጠበቁም ግድ ነበር። የኾነ ኾኖ ሴቲቱ በድንገተኛ ሕመም ተይዘው ሕይወታቸው በማለፉ ምክንያት መንደሪቱ ተደናገጠች። በልቅሶው ሥነ ሥርዐት ላይ የመንደሪቱን ነዋሪዎች እንባ ያራጨው ነገር ታዲያ የአስለቃሿ ሙሾ ነበር፤ “ዋይ፣ ዋይ ተምሮ ላፈር” ተብሎላቸው ነበርና።

“አለማወቅ ደጉ ዐዋቂ ያስመስላል” ይላል አንድ ወዳጄ፤ እንዳመጣለት ያናግራላ። ታዋቂው አሜሪካዊ ሳታየር ማርክ ትዌይንም፣ “በዚህ ሕይወት የሚያስፈልግህ ድንቍርና እና ድፍረት ነው፤ ከዚያማ ስኬትህ እውን ይኾንልሃል” እያለ የሚሣለቀው በዋዛ አይመስለኝም። “ከመጠምጠም፣ መማር ይቅደም።”

ማንበብን ከክርስቲያኖች መካከል ልናጠፋው አንችልም። ለምን? የእግዚአብሔር መገለጥ እንኳ የተሰጠን በታላቁ መጽሐፍ በኩል ነውና። ሕዝበ እግዚአብሔር “የመጽሐፉ ሕዝብ” እንደ መባሉ ታሪኩና ሕይወቱ ከንባብ ጋር የተቈራኘ ነው። እግዚአብሔር ለእስራኤል ነገሥታት ከመጽሐፉ ሰፈር አትራቁ ብሎ አዝዞ ነበር። ንጉሡ አምላኩን እግዚአብሔርን መፍራት ይማር ዘንድ፥ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ ይህችንም ሥርዓት ጠብቆ ያደርግ ዘንድ፥ ልቡ በወንድሞቹ ላይ እንዳይኰራከትእዛዙም ቀኝና ግራ እንዳይል፥ እርሱም ልጆቹም በእስራኤል ልጆች መካከል ረጅም ዘመን ይነግሡ ዘንድ መጽሐፉ ከእርሱ ጋር ይኑር፥ ዕድሜውንም ሁሉያንብበው (ዘዳ. 17፥19-21)።

ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ፈቃድና ሐሳብ በመረዳት በሕይወታቸው እንዲበረቱ ማንበብ ይኖርባቸዋል። እንዲያነቡ ብቻ ሳይኾን ሲነበብ እንዲሰሙም ተመክረዋል፤ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ፣ እስክመጣ ድረስ ለማንበብና [Public Reading of Scripture] ለመምከር ለማስተማርም ተጠንቀቅ” (1ጢሞ. 4፥13) ብሎታል። ዛሬ መንገደኛው ሁሉ ለማስተማር፣ ለመምከርና ለመስበክ የሚጣደፈውን ያህል ለማንበብ ይተጋልን? ምነዋ፣ “ከመጠምጠም፣ ማንበብ ይቅደም” የሚለን ቢበዛልን።

ይህ ሲባል የሰው ሕይወት ጤናማነት በማንበብ ውስጥ ብቻ ተቀምጧል ለማለት አይደለም። አሰስ ገሰሱን ሁሉ በማግበስበስ ኖሮ በአልቦ የመባዛት ዕዳ ሊገጥም መቻሉም እውነት ነው። ሰባኪው እንዳለው፣ ብዙ መጻሕፍትን ማድረግ ፍጻሜ የለውም፥ እጅግም ምርምር ሰውነትን ያደክማል” (መክ. 12፥12)።

አንዳንድ ሰዎች ማንበብን የሚፈሩበት ምክንያት አላቸው። ማንበብ ምቾትን ብቻ አይሰጥም፤ ሕመም አለው። አንዳንድ ጊዜ የተደላደልንበትን ነገር ሊነቀንቅብን ይችላል። ከታዛችን ሌላ ዓለም እንደ ሌለ ለምንቈጥር ሰዎች ማንበብ የሚከፍተው ደጃፍ ያልተጠባበቅነውን መርገድገድ ይዞብን ይመጣል። ስለዚህ ይመስላል አንዳንዶች ኾነ ብለው ኅሊናቸውን በማስተኛት፣ “መቃጠል ስለማልፈልግ አላነብም፤ አለማወቅ ይሻለኛል፤ ምን አቃጠለኝ?” ሲሉ የሚደመጡት።

ወደ ተነሣሁበት ልመለስ። ብዙ ጊዜ ሲባል እንደምንሰማው ለማንበብ ብንሻም የሚነበብ የለም የሚል ሮሮ አለ። ለዚህ አንደኛው መድኀኒት የምናነብበውን ያገኘን ሰዎች ካነበብን በኋላ ለሌሎች ማስተለለፍ የመቻልን ጥበብ በመለማመድ ነው። ደግሞም ከንባብ በኋላ የምንወያይባቸውና በሐሳቦቹ ላይ የምንከራከርባቸው የንባብ ቡድኖች፣ የቡና ላይ ውይይት ክለቦች ማዘጋጀት ይቻላል። ታዲያ ለምን ዛሬ አንጀምረውም። ለምሳሌ ሕንጸትን ገዝተህ እያነበብህ አይደል? አንብና አስተላልፋት። በውስጧ በቀረቡ ሐሳቦች ላይ በአጠገብህ ከሚገኙ ወገኖች ጋር ብትወያዩስ? ብትከራከሩስ? ያልተስማማህበት ሐሳብ ካገኘህም መልሰህ ሕንጸትን ብትሞግታትስ?

አንዳንድ ጊዜ “ለመጽሐፍ በሚከፍለው ገንዘብ የማይቈጭ ትውልድ የሚኖረን እንዴት ነው?” ብዬ አስባለሁ። የዘንድሮ በገና በዓል ሰሞን በአንድ ክርስቲያን የመዝሙር ቤት ጐራ ብዬ ነበር። ወደ 300 ገጽ ያለውና በይዘቱም የማደንቀውን መጽሐፍ ለመግዛት ከባለሱቁ ጋር የሚደራደር ሰው ተመለከትሁ። የመጽሐፉ ዋጋ ብር 50.00 ነበርና ገዢው በንዴት ጦፈ፤ እንዴት 50 ብር ይተመናል በማለት። የተጠቀመበትም ቃል “ሊበላ!” የሚል ነበር። የሚያሳዝነው ግን ይኸው ሰው መዝሙር ቤቱን የለቀቀው ሁለት የስጦታ (ፖስት) ካርዶችን በብር 50.00 ሸምቶ መኾኑ ነበር።

ምን ያህል አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ነው ለቤተ መጻሕፍት ክፍል ያዘጋጀ። የማንበቢያ ቦታ ያመቻቸ? በዓመት ባጀታችን ውስጥ የመጽሐፍ ግዢ ይካተታል? ለስንት መንፈሳዊ መጽሔቶች በቋሚ ደንበኛነት ተመዝግበናል? ተስፋ የሚጣልባቸው ጽሑፎች ከገበያ የሚወጡት በመልእክት መንጠፍ ብቻ ሳይኾን የኅትመት ወጪን መሸፈን ባለመቻልም ነው።

ጉዳዩን ወደ ቤት እንመልሰው። ወዳጆቻችን ለልጆቻቸው ልደት በዓል ሲጠሩን አንድ የላስቲክ ከረጢት ሙሉ ከረሜላ ወይም የፈረንጅ አንጫቄ ተሸክመን ከምንሄድ መጽሐፍ መስጠት ብናስለምዳቸውስ? የልጆች መጻሕፍት ዕጥረት እንዳለብን ዘንግቼው አይደለም። ያሉትን እንኳ ብንጠቀመስ? ደግሞ ከገዛ ቤታችን ብንጀምርስ? በዚያውም የልጆች መጽሐፍ ሊጽፉ የሚችሉ ሰዎች ይበረታታሉ። ልጆቻችን ስናነብ ያዩናል? መጽሐፍ ቅዱሳችን በአንድነት ይጠናል? ከቤተ ሰቦቻችን ጋር ባነበብነው ጕዳይ ላይ እንወያያለን? ልጆቻችን ልብስና ጫማ እንድንገዛላቸው የሚወተውቱንን ያህል መጽሐፍ እንዲሸመትላቸው ይጨቀጭቁናል? ይህን ማድረግ ብንለምድ፣ ቅጣት የሚያስከትል ጥፋት በፈጸመ ጊዜ በዱላ መኻል እርግብግቢቱ የሚነደል ሳይኾን ማንበብ እንዲያስታጕል በማስገደድ የምንቀጣው ልጅ ይኖረን ነበር። እባክህ ወዳጄ፣ ይህችንም ጽሑፍ አንብብና አስተላልፋት።

ዳገትና ተስፋ

ልጆች ሳለን በሚነገሩን ጣፋጭ ተረቶች በኩል አጮልቀን የምናያቸው የሕልም ዓለማት ነበሩን። (ርግጥ፣ በነ “አያ ጅቦ” ታሪክ ብቻ ላደገ ልጅ ይህ አባባል አይሠራም።)

ተጨማሪ ያንብቡ

ለፈጣሪ መኖር ድጋፍ ከሳይንሱ ዓለም?

በባለፈው የፈረንጆች ዓመት ማብቂያ ላይ፣ ማለትም እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 25 2014 ኤሪክ ሜታክስስ የተባለው ዕውቅ ጸሐፊ በዎልስትሪት ጆርናል “Science Increasingly Makes the Case for God” በሚል ርእስ ሳይንስ ፈጣሪ ስለ መኖሩ የሚቀርቡ ሙግቶችን ዕለት ዕለት ይበልጥ እየደገፈ ስለ መምጣቱ ጽፏል።1 ይህ አነጋጋሪ ጽሑፍ እ.ኤ.አ. በ1966 በታይም መጽሔት “ፈጣሪ ሞቷል?” የተሰኘውን ጽሑፍ መነሻ በማድረግ የዘመኑ ሳይንስ የፈጣሪን አለመሞት፣ ብሎም ስለ መኖሩ ይበልጥ ርግጠኛነትን የሚያስጨብጥ ግኝት ላይ እንደ ደረሰ ይናገራል። ይህ ግኝት ምን እንደሆነና ከሜታክስስ ጽሑፍ ጋር የተገናኙ አንዳንድ ሐሳቦችን በዛሬው ጽሑፋችን ለመዳሰስ እንሞክራለን።

ተጨማሪ ያንብቡ

1 comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.