[the_ad_group id=”107″]

የምዕራባውያንን የአስተምህሮ ዓሣ መብላት በብልሃት

ተሓድሶ በተሓድሶ ሆነናል። መንግሥት ከጥቂት ዓመታት በፊት የኢኮኖሚ ተራራ ጫፍ ላይ ሊያወጣን ያስጀመረንን ጒዞ “ህዳሴ” ብሎ ጠርቶት ነበር፤ የኀይል ማመንጫውን “ህዳሴ ግድብ” ሲል የሰየመውም ለዚሁ ነበር። “ጥልቅ ተሓድሶ” ራሱን በራሱ የሚያጸዳበት ብልሃቱ እንደ ሆነም ይነግረን ነበር።

ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በአንጻሩ፣ “ተሓድሶ ተሓድሶ” በሚሉና በሚቃወሙ መሓል ተወጥራለች፤ “ሃራጥቃ ተሓድሶ” ላስቀየሟት የወጣላቸው ስም ነው። እነዚህን ሁሉ ጒዳዮች ዛሬ አናነሣቸውም።

ልምምድ አስፈላጊ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም አስተማሪ ነው። ያለ ሕይወት ልምድ ዶክትሪን ብቻውን ምውት ነው። በአንጻሩ፣ ልምድ ብቻውን ያለ ዶክትሪን፣ ቦይ እንደ ሌለው ጎርፍ ብዙ ጥፋት ያስከትላል። እየሆነ ያለውም ይኸው ነው።

ዛሬ የምናነሣው ስለ ፕሮቴስታንታዊ ተሓድሶ ነው። ወንጌል አማኞች የሆንን (እንደ ጥሩ ኢትዮጵያዊ) አንድን አስተምህሮ ስንቀበል ግልብጥ ብለን ወጥተን ነው፤ ሌላ አዲስ አስተምህሮ ብቅ ብሎ የያዝነውን እስኪያስጥለን ድረስ። ይህ “የሐበሻ ሕመማችን” ነው። “የመሪ ያለህ” ከታተመ፣ “የአገር ያለህ”፣ “የፍትሕ ያለህ”፣ “የወንድ ልጅ ያለህ፣ ወዘተ. ይከተላል። ይህ በጥልቅ ያለ ማሰብ፣ ያለ መመካከርና የዐሳብ ድኽነት ምልክት ነው።

በ1960ዎቹ፣ ቲ ኤል ኦስበርን፣ ካትሪን ኲልማን፣ ኦራል ሮበርትስ ነበሩ። ካትሪን ኲልማንን በሴትነትዋ ምንም ያላሉ መሪዎቻችን፣ የእኅቶቻችን ጸጋቸው እየመሰከረ እንኳ፣ “ወንጌላዊ” ቀርቶ “ዲቊና” ቢያምራቸው ጒድ ይፈላ ነበር። የእኅቶች አገልግሎት ከስልክ ተቀባይነት፣ ከኳየር፣ ከ“ሕጻናት አገልግሎት”፣ ከሻይ ቀጂነት አያልፍም ነበር! ዛሬም እንኳ በየዩቱብ ቲቪ ጣቢያ ረከቦት ዘርግተው መድረክ ያሟሙቃሉ! ነቢዪት ዘማሪት መጋቢ(ት) ተብለው አደባባይ ከወጡት ውጭ፣ በዋነኛ ኮሚቴዎች ላይ የተሰየሙ እኅቶችን በፖሊስ አስፈልጎ ማግኘት አይቻልም!

በ1970ዎቹ ሃል ሊን(ድ)ሲ፣ ዋችመን ኒ፣ ፍራንኪልን ሆል፣ ዴሬክ ፕሪንስ ነበሩ። በ1980ዎቹ ዮንጊ ቾ፣ ቲም ላሄይ፣ ጂሚ ስዋገርት፣ ኬኔት ሄግን፣ ቤኒ ሂን ነበሩ። ከዚያ ቦንኬ፣ ቲዲ ጄክስ፣ ቲቢ ኤን፣ ቲቢ ጃሽዋ፣ ወዘተ.። ሁሉም “ፈረንጆች”።በዋነኛነት ዛሬ ድረስ የሚጠቀሱ ጥቅሶች ደግሞ ነበሩ፦ “ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ።” (ኢሳ 54፥13)፤ “ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች።” (መዝሙር 68፥31)፤ “እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም።” (1ኛ ዮሐንስ 2፥20፡ 27)። ጥቅሶቹ ትክክልና ተገቢ ጥቅሶች ናቸው፤ ችግሩ በቊንጽል እንጂ በቃሉ ሙላትና በታሪክ ላይ አለመመሥረታቸው ነው። (የሐሥ 20፥27) ችግሩ ለስንፍና፣ ለቤተ ክርስቲያን ላለመገዛት እና ‘የተመረጥን ሕዝብ ነን’ ለማለት መዋላቸው ነው። ልምምድ አስፈላጊ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም አስተማሪ ነው። ያለ ሕይወት ልምድ ዶክትሪን ብቻውን ምውት ነው። በአንጻሩ፣ ልምድ ብቻውን ያለ ዶክትሪን፣ ቦይ እንደ ሌለው ጎርፍ ብዙ ጥፋት ያስከትላል። እየሆነ ያለውም ይኸው ነው።

እነ ቄስ ማርቲን ሉተር (መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን፣ ቃለ ሕይወት) “ቃል፣ ቃል”፤ “ዶክትሪን፣ ዶክትሪን” ስለሚሉ፣ እንደ ሙሉ ወንጌል (መንፈስ መንፈስ፣ ልምምድ ልምምድ) ማለት ስለማያበዙ በጥርጣሬ ይታዩ ነበር። ዛሬ ዘመኑ ተለውጣል! አንዳንዶች፣ “መንፈስ ነን” ሲሉ፣ የክርስቶስን ማኅበር ሲያነዋውጡ፣ ጭፈራ ሲያበዙ፣ ሕዝብ ተራቊቶ መሪዎች ሲበለጽጉ፣ የ‘ዶክትሪን ያለህ’ አስብሏል!

ጥያቄው ይህ ነው፦ ከ “መንፈስ፣ መንፈስ” ወደ “ዶክትሪን፣ ዶክትሪን” መፈናጠር እንዳናበዛ፣ ልምምድና ዶክትሪንን እንዴት በሚዛን እንያዝ?

ዛሬ “ሪፎርሜሽን” ወይም የ“ተሓድሶ ቲዎሎጂ” እየጎላ መጥቷል። ለጌታ ክብር ይግባውና ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ት/ቤቶች በዘመናችን ተከፍተዋል። ቀድሞ የጌታን ቃል በጥልቀትና ከምንጩ ማጥናት ከመንፈሳዊነት መጒደል፣ አእምሯዊነት/ሥጋዊነት ሲባል እንዳልነበር! የእግዚአብሔርን ምሥጢራት ለማወቅ መጓጓት ሰይጣናዊ ተብሎ እንዳልነበር! (መዝሙር 25፥14፤ ኤፌሶን 3፥9) ዛሬ ደግሞ በተቃራኒው “ድግሪ” አለማወጅና አለመሞጋገስ ነውር መስሏል።

ጥያቄው ይህ ነው፦ ከ “መንፈስ፣ መንፈስ” ወደ “ዶክትሪን፣ ዶክትሪን” መፈናጠር እንዳናበዛ፣ ልምምድና ዶክትሪንን እንዴት በሚዛን እንያዝ?

የ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተሓድሶ ንቅናቄ መሪዎች ማርቲን ሉተር፣ ካልቪን እና ዝቪንግሊ የሐዋርያ ጳውሎስን መልእክቶች የተረጐሙት በአውሮጳዊ አእምሮ፣ በግሪክ ፍልስፍናዎችና ባሕላዊ ተጽእኖ፣ በሮማ ካቶሊካዊት ግዛታዊ ዕይታ ውስጥ ታቅፈው ነው። ንቅናቄው ከጀርመን፣ ከፈረንሳይ፣ ከሆላንድ፣ ከስዊትዘርላንድ፣ ከሮማ እና ከእንግሊዝ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውጭ፣ ሰፊውን የኦርቶዶክሱን ዓለም አይወክልም ነበር። የአውሮጳው ተሓድሶ የመጀመሪያውን መቶ ክፍለ ዘመን ታሪካዊ ዐውድ እንደሚገባ ስላላጤነ፣ የጳውሎስን አይሁዳዊነት ዘንግቶ፣ ጳውሎስን አይሁድ ጠል አመስሎታል። የጌታ ባርያ ቄስ ማርቲን ሉተር አይሁድ ጠል መሆኑ ስውር አልነበረም።

በአሁኑ ወቅት በአገራችን ጎልተው የሚጠቀሱ የተሓድሶ መምህራን፣ ከቀደሙት ጆን ዊንትሮፕ (1588—1649 እ.አ.አ.)፣ ጆናታን ኤድወርድስ (1703—1758 እ.አ.አ.)፣ ከቅርቦቹ ጆን ማካርተር፣ አር. ሲ. ስፕሮል (ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ ጌታ የሄዱ)፣ ጆን ፓይፐር፣ አል ሞለር፣ ወዘተ. ናቸው።

የተሓድሶ አስተምህሮ መሠረቱ እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባው ቃል ኪዳን ነው (ዘፍጥረት 12፣ 15፣ 17፤ ገላትያ 3፥16)። ይህ በራሱ አጠያያቂ አይደለም፤ እግዚአብሔር ከአሕዛብ አንድ አብርሃምን ጠራው፤ የተለየ ሕዝብ ያደርገው ዘንድ። ዐላማው በእርሱ በኲል ሰዎችን ሁሉ ወደ ራሱ መጥራት ነው። ሁሉ ከጠሪው ነው። ጠሪው ማንንም አይለይም፤ ኪዳኑንም አይለዋውጥም። የኪዳኑን ስጦታ መቀበል ብቻውን የእግዚአብሔር ሕዝብ ያደርጋል። ሆኖም፣ ሁለት ጒዳዮች መጤን ይኖርባቸዋል። አንደኛ፣ የተሓድሶ ታሪክና የተገኘበት ባሕል ተጽእኖ ውጤት። ሁለተኛ፣ ዛሬ የሚታየው ሥነ መለኮታዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዳራዎቹ።

የተሓድሶ ትምህርት በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ መነጽር ሲታይ ምን ይመስላል? ከአውሮጳውያኑና ከሰሜን አሜሪካኑ ክርስትና ይልቅ፣ ባሕላችን ለጥንት ምሥራቃዊት ቤተ ክርስቲያን ቋንቋና ልማድ የቀረበ መሆኑ፣ የተሓድሶን ይዘት እንዴት ሊጠይቅና ሊያጠናክር ይችላል? ያለ በቂ ጥንቃቄ የተቀበልነው ምዕራባዊ ክርስትና ምን ዐይነት እርምት ይሰጠው? የተሓድሶ ትምህርት በተገኘባቸው አህጉራት ማኅበራዊውን እውነታ እንዴት አበጀው ወይም ቀረጸው?

ከመጨረሻው ጥያቄ ብንጀምር፣ ዊንትሮፕም ኤድወርድስም ሰው ሁሉ በአምላክ አምሳል መፈጠሩን፣ የኅሊና ነጻነት መጎናፀፉንና በአምላክ ፊት እኲል መሆኑን መስክረዋል። በአስተምሯቸው፣ የሚሆነው ሁሉ እግዚአብሔር እንደ ወሰነው ነው። እግዚአብሔር የሚድኑትን እና የሚጠፉትን አስቀድሞ አውቋቸዋል፤ እኛ ምርጦቹ ነን፤ እግዚአብሔር ያልመረጣቸው፣ ለጥፋት የመደባቸው አሉ። እኛን የመረጠ እግዚአብሔር አንዳንዶች “አናሳዎች”ን አልመረጣቸውም። ታዲያ ይህ አተረጓጐም (“አናሳዎችን”) ባርያ አድርጎ ለመግዛትና ለመሸጥ አስችሏቸው ነበር። እንግሊዞች ከአውሮጳ ፈልሰው አሜሪካ ሲሠፍሩ የእስራኤል ምርጦች ነን ብለው ነው (ውሸት ነው)። አፈናቅለው፣ ገድለውና አታልለው የወረሱትን ምድር በከነዓን ምድር መስለው ነው (ውሸት ነው)። አውሮጳውያኑ ባመጡት ፈንጣጣ የአገሬው ሕዝብ ሲያልቅ እግዚአብሔር እንድንስፋፋ ምልክት ሲሰጠን ነው አሉ (ውሸት ነው)።

የተሓድሶ ትምህርት በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ መነጽር ሲታይ ምን ይመስላል? ከአውሮጳውያኑና ከሰሜን አሜሪካኑ ክርስትና ይልቅ፣ ባሕላችን ለጥንት ምሥራቃዊት ቤተ ክርስቲያን ቋንቋና ልማድ የቀረበ መሆኑ፣ የተሓድሶን ይዘት እንዴት ሊጠይቅና ሊያጠናክር ይችላል?

ሰዘርን ባፕቲስቶች ወንጌልን በዓለም ዙሪያ ማዳረስ እና ጥቊሮችን ባርያ ማድረግ አይጣሉም ብለው ነበር። ዛሬም እንኳ ድርጅታዊ መዋቅራቸው ነጭና ጥቊር አማንያንን የለያየ ነው። እንደ አውሮጳ ዘመን አቈጣጠር በ1973፣ ፕሬስብቴሪያን ቸርች ኦፍ አሜሪካ ከሰሜኑ ተከፍሎ በደቡባዊ የአሜሪካ ግዛት ሲደራጅ ጥቊር አማኝ ነጩን እንዳያስተምር፣ ሴት አማንያን በጒባዔ እንዳይጸልዩ ከልክሎ ነበር፤ ዛሬም ብዙ አልተለወጠም። የቀድሞዎቹ ሚሲዮናውያን ይዘው የመጡት ወንጌል፣ ርዕዮተ ዓለማዊ ይዘቱ ምን እንደሚመስልና ምንጩ ግልጽ ይመስለናል! በሌላ አነጋገር፣ የተሓድሶን ትምህርት አተረጓጐም መመርመር፣ ከአገራችን እውነታዎች አንጻር፣ ይልቊን ከእግዚአብሔር ቃል አንጻር ብዙ ጸሎትና ምክክር ይጠይቃል። ከላይ በርእሱ እንዳመለከትነው፣ የምዕራባውያንን የአስተምህሮ ዓሣ መብላት በብልሃት ነው!

አንድ ምሳሌ ብቻ እናንሣ። ዶ/ር ዌይን ግሩደም በአሜሪካ ወንጌላውያን ዘንድ የታወቁ የሥነ መለኮት ሊቅ ናቸው። ደግሞ የዘረኛ፣ ሰው አዋራጅና ዋሾ የቀድሞ ፕሬዚደንት ትረምፕ ደጋፊ ናቸው (አክብሮት ለመንሳት ሳይሆን በአደባባይ የተነገረ እና እውነት ስለሆነ ነው)[1]። ዌይን ማንንም መደገፍ የዜግነት መብታቸው ስለሆነ አያስወነጅላቸውም። ችግሩ ትረምፕ ደቡባዊውን የአሜሪካ ድንበር ‘በግንብ አጥራለሁ’ ባሉበት ወቅት በቅድሚያ ፍርሀት መንዛት ነበረባቸው። ትውልደ ስፓኒሽ እና ነጭ ዘር የሌለበትን ስደተኛ ሽብር ፈጣሪ፣ ሴት ልጅ ደፋሪ፣ ነፍሰ ገዳይ፣ ዕፅ ወሳጅ ብለው ፈረጁ።[2] ነጮች በመኻንነትና በውርጃ መስፋፋት ከሠላሳ ዓመት በኋላ አናሳ እንደሚሆኑ ታውቋል። የሕፃናት ንግድ የተጧጧፈው አንዱም ለዚህ ነው! በቊጥር አናሳነት ፍርሀት የተናወጠውን የአሜሪካን ገጠሬና ነጭ ወንጌላውያንን የኖረ ጥላቻ ቀሰቀሱ። ፕሬዝዳንቱ የእነዚህን ድጋፍ ሳያገኙ ማሸነፍ እንደማይችሉ አውቀው ነበር። በዚህ ወቅት ነበር ግሩደም ብቅ ያሉት፤ ሕዝበ እስራኤል ከጠላቶቻቸው ጥቃት ለመዳን ከተሞቻቸውን በግንብ አጥረው ነበር አሉ።[3] የትረምፕን እጅ በዘረኛ ሥነ መለኮት ቅባት ቀብተው አበረቱ። አሜሪካኖችን ሕዝበ እስራኤል፣ ምድራቸውንም ከነዓን አስመሰሉ!

ከላይ የጠቀስናቸው የተሓድሶ መምህራን፣ ሰው ሁሉ በአምሳለ እግዜር የተፈጠረ ስለ ሆነ ክቡር ነው ብለው የሚያስተምሩ ናቸው። በአንጻሩ፣ የስደተኞች ልጆች ከእናቶቻቸው ተነጥቀው እንደ አውሬ በሽቦ አጥር ውስጥ ሲቆለፍባቸው፣ ሲታመሙና ሲሞቱ እንዲሁም ሴቶቻቸው ሲደፈሩ ምንም ያላሉ ናቸው። ኢየሱስ ወደ ግብፅ ሲሰደድ የኢሚግሬሽን ሕግ አልጣሰም፤ ሕግ የሚጥሱ ቢታሠሩ ቢባረሩ ትክክል ነው አሉ![4] ምኑን ከምኑ አገናኙ? የእግዚአብሔርን ቃል አስተካክሎ የማያውቀውን ምእመን ለማሳመን ግን በቂ ነበር።

እውነቱ ምንድነው? እውነቱ ጥቁር መሆን ወንጀል አይደለም! አሜሪካ ስደተኛ የገነባት፣ የስደተኛ መጠጊያ ነች፤ “ስደተኞች ነበራችሁና ስደተኛውን አትበድለው” (ዘፀአት 22፥21)፤ “እንግዳ” ሆኜ መጥቼ ነበር (ማቴዎስ 25፥35፡ 45)፤ “እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ በዚህ አንዳንዶች ሳያውቁ መላእክትን እንግድነት ተቀብለዋል፤ ከእነርሱ ጋር እንደ ታሰረ ሆናችሁ እስሮችን አስቡ፥ የተጨነቁትንም ራሳችሁ ደግሞ በሥጋ እንዳለ ሆናችሁ አስቡ” (ዕብራውያን 1፣2፡ 3)።

ማንኛውም አስተምህሮ (ነገረ መለኮት) በጠንሳሹ ባሕልና ዕሳቤ የተቀለመ ነው!

ነጭ የተሓድሶ መምህራን ድርጊታቸው ከወንጌል አስተምህሮ ጋር አልተስማማም። ዝሙት ይቃወማሉ፤ ዝሙት የሚፈጽሙትን ለመሪነት ያጫሉ። ዘረኝነትን ይቃወማሉ፤ ለዘረኛ መሪዎች ድጋፍ ይሰጣሉ፤ ምእመን ድጋፍ እንዲሰጥ ይሰብካሉ። ሐሰት መናገር ስሕተት ነው ይላሉ፤ ሐሰት የሚዘሩትን፣ በሐሰት የሚመሰክሩትን ይሾማሉ፤ ሐሰቱን እውነት ይላሉ። በሌላ አነጋገር፣ ነጭ ያልሆነን ማጥላላትና መግፋት የመጣው የነጭ የበላይነት እንዲያንሠራራ ነው። ለዚህ አንደኛው ስልት መጽሐፍ ቅዱስን መጥቀስ ነው! የተሓድሶ ዶክትሪን በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ መጠናከር ዋነኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው አንርሳ! አውሮጳውያን አፍሪካ እና ኤዥያን ቅኝ የገዙት በዚሁ ዶክትሪን ተንተርሰው እንደ ሆነ አንርሳ! ጥቊር ሕዝቦች ሙሉ ሰው ስላልሆኑ (ከእንስሳ ብዙም ስለማይሻሉ) ቢያንስ ቢያንስ ነፍሳቸውን እናድን፣ ከአውሬነት እናላቅቃቸው የሚል ነበር ግቡ! ቅኝ መግዛት ጥቊሩን ሕዝብ ከአውሬነቱ ለማላቀቅ የታሰብ የጽድቅ ሥራ መሆኑ ነው! ማንኛውም አስተምህሮ (ነገረ መለኮት) በጠንሳሹ ባሕልና ዕሳቤ የተቀለመ ነው! የእኛንም አገር ጨምሮ! ተሓድሶ በመሠረቱ ጥሩ አስተምህሮ ነው፤ አማንያን ካህናት ናቸው፤ መዳን በኢየሱስ በማመን ብቻ በጸጋ ብቻ ነው። (ኤፌሶን 2፥8፤ 1ኛ ጴጥሮስ 2፥9) መርምሮና መርጦ መውሰድ ግን ግድ ነው! የተሓድሶ አስተምህሮ መሠረቱ አውሮጳዊ ነው። ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን የተገኘችበት ቀዳሚ ባሕልና ታሪክ ደግሞ አሁዳዊ፣ ሮማዊና ግሪካዊ ነው። የኋለኛው ለቀደመው እርምት እንደ ሰጠ ሁሉ፣ በቀደመው የኋለኛውን መመርመር እና ማረም ግድ ነው!  


ይህ ጽሑፍ “ተሓድሶ ወይስ ተሓድሶ?” በሚል ርእስ ሜይ 15/2020 ETHIOPIANCHURCH.ORG ካተመው ላይ የተወሰደ ነው።

[1] https://prospect.org/power/liar-racist-cheat-president-america-cpac-seal-approval/

[2] https://www.bbc.com/news/av/world-us-canada-37230916

[3] https://www.christianpost.com/news/wayne-grudem-trump-border-wall-morally-good-bible-cities.html

[4] https://www.vox.com/2018/7/11/17561950/trump-evangelical-ally-jesus-immigration-law

Share this article:

ለሚድን በሽታ የሚገድል መድኃኒት መውሰድ ይብቃ! (ደወል 3 ዘ ኢትዮጵያ)

“አንዱ በብሔሩ ዘረኛ ሲሆን፣ ሌላኛው በዜግነቱ ዘረኛ ይሆናል። አንዱ ብሔሩን ሲያስቀድም፣ ሌላኛው ዜግነቱን ያስቀድማል። አንዱ የብሔር ዘረኛ የራሱን ብሔር ለብቻው ሊያገንን ሲፈልግ፣ ለኢትዮጵያ ዐብሮነት መሠረት ውጋት ይሆናል። እንደዚሁም የዜግነት ዘረኛ ኢትዮጵያን ለብቻዋ እንድትገን ሲፈልግ፣ በጨለማ ላለ ጥቁር አፍሪካ ሕዝብ አንድነት ውጋት ይሆናል።

ተጨማሪ ያንብቡ

እግዜር እንግዳ ሆኖ ሲመጣ

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን በምናስብበት በዚህ ሰሞን፣ “እግዜር እንግዳ ሆኖ ሲመጣ” ሊኖረን ስለሚችልና ስለሚገባ ምላሽ የሚከተለውን ጽሑፍ ሰሎሞን ጥላሁን ያስነብበናል።

ተጨማሪ ያንብቡ

“የክርስቲያን ሚዲያዎች ሲታዩና ተግባራቸው ሲገመገምም አብዛኛዎቹ አንባቢውንም ሆነ ተመልካቹን የማይመጥኑ…ሆነው እናገኛቸዋለን” – ቃለ መጠይቅ ከዶ/ር ንጉሤ ተፈራ ጋር

ሚክያስ በላይ ከዶ/ር ንጉሤ ተፈራ ጋር ባደረገው ቆይታ፣ አማኝ ማኅበረ ሰቡን በሚመለከት ስለ ኮሙኒኬሽንና የመገናኛ ብዙኅን አጠቃቀም፣ አብያተ ክርስቲያናት ከኅብረተ ሰቡ ጋር ስላላቸው መስተጋብር እንዲሁም በአጠቃላይ ከቤተ ክርስቲያንን አመራር ጋር ሊያያዙ በሚችሉ ጭብጦች ዙሪያ ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ተጨማሪ ያንብቡ

5 comments

Your email address will not be published. Required fields are marked *

  • I really don’t understand the point the author is trying to make. I could not see the coherence. Can anyone please explain what he’s trying to say? I have difficulty connecting the paragraphs. Is he talking about the reformation in general? Or the Reformed Church? Are the Eastern Churches free from the allegations the author made about the ‘reformation teachers’? What is he trying to conclude?

    • It could be your Amharic is not there yet (because you live abroad). It could also be you are expecting the article to read a familiar way and it is not. Both cases do happen. The remedy for that is to talk it over with someone else.

  • ይህ ፅሁፍ በራሱ ሲነበብ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል! የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትና የፓን አፍሪካኒዝም እርሾ ተጫጭኖታል! የአሜሪካንን የውስጥ ፖለቲካም በአግባቡ ያለመረዳት ችግር ይስተዋልበታል! በአጠቃላይ ስለተሀድሶ ስናወራ መፅሀፍ ቅዱሳዊ የአስተምህሮ እውነቶችን ከስህተት የማፅዳት ጉዳይ እስከሆነ ድረስ መመዘን ያለበት በራሱ በመፅሀፍ ቅዱስ ነው:: በጊዜው የነበረው የምዕራባውያን መሀበራዊ ሁናቴ የወንጌል አረዳዳቸውን እንዴት ቀርፆታል የሚለው ጥያቄ ግን ወሳኝ ነው! ጥሩ ሪሰርችም ያስፈልገዋል:: ይህ ግን ሲደረግ እኛም ከዚሁ የሀገራዊና ማህበራዊ ተፅእኖ እንዴት የወንጌል አረዳዳችን ላይ ተፅእኖ እንዳመጣ የራሳችንንም መሀበራዊ እውነታና በአድ ልምምዶቻችንን ማጥናት አለብን!

    • “የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትና የፓን አፍሪካኒዝም እርሾ ተጫጭኖታል! የአሜሪካንን የውስጥ ፖለቲካም በአግባቡ ያለመረዳት” ያልከውን ልታብራራ ልትጠቁም ትችላለህ? ሁለቴ አንብቤ አልታይ ብሎኛል።

    • ወንድም ብሩክ፣ ስለ ፓን አፍሪካኒዝም እና ስለ አሜሪካ ፖለቲካ ብዙ መረዳት እንደሌለህ ያስታውቃል ። በጽሑፉ ውስጥ የሌለ ነገር ነው።

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.