[the_ad_group id=”107″]

ለፈጣሪ መኖር ድጋፍ ከሳይንሱ ዓለም?

በባለፈው የፈረንጆች ዓመት ማብቂያ ላይ፣ ማለትም እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 25 2014 ኤሪክ ሜታክስስ የተባለው ዕውቅ ጸሐፊ በዎልስትሪት ጆርናል “Science Increasingly Makes the Case for God” በሚል ርእስ ሳይንስ ፈጣሪ ስለ መኖሩ የሚቀርቡ ሙግቶችን ዕለት ዕለት ይበልጥ እየደገፈ ስለ መምጣቱ ጽፏል።1 ይህ አነጋጋሪ ጽሑፍ እ.ኤ.አ. በ1966 በታይም መጽሔት “ፈጣሪ ሞቷል?” የተሰኘውን ጽሑፍ መነሻ በማድረግ የዘመኑ ሳይንስ የፈጣሪን አለመሞት፣ ብሎም ስለ መኖሩ ይበልጥ ርግጠኛነትን የሚያስጨብጥ ግኝት ላይ እንደ ደረሰ ይናገራል። ይህ ግኝት ምን እንደሆነና ከሜታክስስ ጽሑፍ ጋር የተገናኙ አንዳንድ ሐሳቦችን በዛሬው ጽሑፋችን ለመዳሰስ እንሞክራለን።

ታይም መጽሔት “ፈጣሪ ሞቷል?” የተሰኘውን ጽሑፍ ባወጣበት በዚያው ዓመት ካርል ሴጋን የተባለው የጠፈር ተመራማሪ አንድ ፕላኔት ሕይወት ያላቸው ነገሮችን ለማኖር ሁለት መስፈርቶችን ማሟላት እንደሚገባው ተናግሮ ነበር። ሴጋን እንደሚለው ከሁሉ አስቀድሞ ያ ፕላኔት ትክክለኛው ዐይነት ኮከብ ሊኖረው ይገባል። እንዲሁም ደግሞ ፕላኔቱ ከኮከቡ ትክክለኛ ርቀት ላይ መገኘት ይኖርበታል። ይህ ርቀት በጥቂት ሚሊ ሜትሮች እንኳ ከፍ ወይም ዝቅ ካለ ያ ፕላኔት ሕይወትን ማኖር አይችልም። ካርል ሴጋን ልክ ከሆነ፣ ከአንድ ኦክቲሊየን (ከ1 በኋላ 27 ዜሮዎች ሲከተሉ) ፕላኔቶች መካከል እነኚህን መስፈርቶች የሚያሟሉና ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ለማኖር ምቹ የሆኑ ሴፕቲሊየን (ከ1 በኋላ 24 ዜሮዎች ሲከተሉ) ፕላኔቶች ሊኖሩ ይገባል። ይህን አስደናቂ ግኝት ተከትሎ ከምድራችን ሌላ ሕይወት ሊኖርባቸው የሚችሉ ሌሎች ፕላኔቶችን ለማግኘት ብዙ ሙከራ ይደረግ ጀመር። ይሁንና ብዙ ዐሥርት ዓመታት ቢያልፉም ከምንኖርባት ዓለም ውጪ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች የያዙ ሌሎች ዓለማት ሊገኙ አልቻሉም። እንዲያውም ካርል ሴጋን እንዳሰበው መሟላት የሚገባቸው መስፈርቶች ሁለት ብቻ ሳይሆኑ፣ ሕያዋንን ለማኖር ከሁለት መቶ በላይ የሚያስፈልጉ ነገሮች እንዳሉ አሁን መታመን ጀምሯል። የመስፈርቶቹ ቁጥር እየጨመረ መምጣት እንዲሁም ደግሞ እያንዳንዱ መስፈርት በትክክል መሟላት ማስፈለጉ ሕይወት ሊኖርባቸው የሚችሉ ፕላኔቶችን ብዛት እጅጉን ይቀንሰዋል።

ሳይንስ ከደረሰባቸው ከእነዚህ አስገራሚ መስፈርቶች ባሻገር ሊሟላ የሚገባው ሌላም ነገር አለ። ጁፒተር ለእኛ ምድር እንደሆነው ሁሉ፣ ታላቅ የስበት ኀይል ያለው ግዙፍ ፕላኔት መስፈርቶቹን ሁሉ ከሚያሟላ አንድ ፕላኔት አቅራቢያ ሆኖ ከበራሪ ከዋክብት ፕላኔቱን ካልጠበቀ፣ ከዋክብቱ ፕላኔቱን ሊመቱትና ነዎሪዎቹን ሊያጠፉ ይችላሉ። ይህ ሁሉ ነገር፣ ሕይወት ያለበት ፕላኔት ምን ያህል ድንቅ እንደ ሆነ እንዲሁም ሕይወት እንዲኖር ከአእምሮ ያለፈ ዝግጅትና ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ያሳያል።

ታዲያ ይህን አስደናቂ ሳይንሳዊ ሐቅ ሲገነዘብ ኤሪክ ሜታክስስ ስለ ፈጣሪ መኖር ሳይንስ ራሱ ድጋፍ እንደሚሰጥ ጽፏል። ሜታክስስ እንደሚለው ሕይወትን ስለ ያዙ ፕላኔቶች ማውራት ብቻ ሳይሆን፣ ሕይወትን በያዘች ፕላኔታችን እየኖርን እንገኛለን። በዚህ ሁኔታ መኖር ያስቻሉን ነገሮች ረቂቅነት፣ መኖራችንን ዐቅዶና ፈቅዶ ሁኔታዎችን ሁሉ ስላሰነዳዳ ፈጣሪ የሚሉት አላቸው። በሌላ አነጋገር፣ ይህ ዓለም የተሰናዳና የተበጃጀ እንዲያውም በናኖ ሜትር ደረጃ እንኳን የሚመጡ ኢምንት ለውጦች እንዳልነበር የሚያደርጉት በመሆኑ፣ ይህንን ዓለም በዕቅድ የፈጠረው አካል መኖሩን ያስረዳል። በሚገባ የተሰናዳ ዓለም (a fine-tuned universe) ፈጣሪ ስለ መኖሩ አሳማኝ ሙግት ያቀርባል። ሜታክስስ እንደሚለው፣ “ከተበጃጀው ዓለም በስተጀርባ ፈጣሪ አለ” ብሎ ማመን፣ “ፈጣሪ የለም” ብሎ ከማመን እጅጉን የሚቀል እምነት ነው። ይሁንና ፈጣሪ ስለ መኖሩ ሙግት ስናቀርብ ሳይንሳዊ ግኝቶች ላይ ከተመረኮዝን ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ‘ለምን?’ ቢባል ሳይንስ ተለዋዋጭ ስለሆነ።

ዛሬ እንደ እውነት የተቆጠሩ ነገሮች ነገ ጉድለታቸው ወይም ስሕተታቸው ገንኖ ይወጣል። አዳዲስ ግኝቶች የትላንት እውነቶችን ለመፈተሽ የሚረዱ አመለካከቶችንና ሐሳቦችን ያስገኛሉ። እናም እያደገና እየዳበረ የሚመጣ ዕውቀትን ያስጨብጣል እንጂ ሳይንስ “ከአፈርኩ አይመልሰኝ” ዐይነት ስሕተቶቹን የሚደብቅ መስክ አይደለም። ስለዚህ ሥነ መለኮታዊ መረዳቶቻችንን ከሳይንሱ ዓለም በሚመጡ ተለዋዋጭ ግኝቶች ካስደገፍናቸው ችግር ላይ ልንወድቅ እንችላለን።

ከላይ እንዳየነው ፈጣሪ ስለ መኖሩ የሚሞግተው የኤሪክ ሜታክስስ ጽሑፍ የተመረኮዘው በዋናነት ሳይንስ በቅርቡ በደረሰበት አዲስ ግኝት ላይ ነው። ይህ ግኝት ቀደም ሲል (ከኀምሣ ዓመታት በፊት) እንደታሰበው ሳይሆን፣ ፕላኔቶች ሕይወት እንዲኖራቸው መሟላት የሚገባቸው መስፈርቶች ከሁለት መቶ በላይ እንደሆኑ አሁን መረጋገጡን የሚያሳይ ነው። ሜታክስስ የመስፈርቶቹን ብዛትና እያንዳንዱ ነገር በትክክል መሟላት ማስፈለጉን አስታክኮ ከፕላኔታችን በስተጀርባ ፈጣሪ መኖሩን ሞግቷል። እንበልና ከሳይንሱ ዓለም አዲስ ግኝት ቢመጣና የእነዚህ መስፈርቶች ቁጥር ዛሬ ከሚታመነው እጅጉን አንሶ ቢገኝ፣ ብሎም ሕይወት ያላቸውን ለምሳሌ ዕጽዋትንና በዓይን የማይታዩ ፍጡራንን የያዘ ፕላኔት ነገ ቢገኝ በሳይንስ ላይ የተመረኮዘው ሙግታችን አደጋ ላይ ወደቀ ማለት ነው።

በርግጥ አንድ ወዳጄ እንዳለው፣ ከአዲሱ ግኝት ጋር እንዲስማማ አድርገን አዲስ ሙግት መቀመር እንችል ይሆናል፤ ነገር ግን አላስፈላጊ ሥነ መለኮታዊ ጂምናስቲክ ምን አሠራን? ስመ ጥሩው ክርስቲያን ሳይንቲስት ፍራንሲስ ዋትሰን እንዳለው “የስንዱ ዓለም ሙግት (the fine-tuning argument)፣ እንደ ብዙ የዐቃቤ እምነት ሙግቶች በአዳዲስ ሳይንሳዊ ግኝቶች ሊዳከም የሚችል በመሆኑ እግዚአብሔር ስለ መኖሩ ማረጋገጫ ተደርጎ መወሰድ የለበትም።”2 በእርግጥ ሕይወት እንዲኖር ለማድረግ በጥንቃቄና በትክክል መሟላት የሚገባቸው ነገሮች አስደናቂ ናቸው። ይሁንና ሳይንስ ስለ ቁሳዊው ዓለም ዕውቀት ለማስጨበጥ የሚካሄድ ጥረት በመሆኑ ስለሚታየው ዓለም ያለንን መረዳት በየጊዜው በአዳዲስ ግኝቶች ያሻሽልልናል። ስለ ፈጣሪ ያለንን ግንዛቤ በእነዚህ ተለዋዋጭ ግኝቶች ላይ የምናስደግፍ ከሆነ ግን ሥነ መለኮታችን ደካማ ይሆናል።
ስለዚህ ፈጣሪ ስለ መኖሩ ከሳይንሱ ዓለም ድጋፍን ካሻን የሳይንሳዊ ግኝቶችን ተለዋዋጭ ባሕርይ ባገናዘበ መልኩ ሙግቶቻችንን እንቀይስ።

የግርጌ ማስታወሻ

  1. Science Increasingly Makes the Case for God
  2. Francis Collins and Karl Giberson, The Language of Science and Faith (Downers Grove: InterVarsity Press, 2011), 195.

Sofanit Abebe

የጌታ የሆኑትን ማሳደድ ራሱን ጌታን ማሳደድ ነው

የማኅበረ አኀው የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የአርባ ምንጭ አጥቢያ፣ ከየካቲት 8-10 የሥልጠናና የአምልኮ ጊዜ አዘጋጅታ ነበር። በዚህ የሦስት ቀናት መርሓ ግብር የመጨረሻው የአምልኮ ጊዜ ላይ፣ ‘ስለ ወንጌል ቀንተናል’ ያሉ ወገኖች ወደ ጉባኤው ገብተው፣ ድብደባና ዘረፋ መፈጸማቸው ተነግሯል። ይህ የዲያቆን አግዛቸው ተፈራ ዐጭር ጽሑፍ፣ የጌታ የሆኑትን ማሳደድ ክርስቶስ ራሱን ማሳደድ መሆኑን ያመለክታል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ኢትዮጵያ የ“አረማዊ ደሴት”?


የእሬቻ በዓል በክርስቲያኑ ማኅበረ ሰብ መካከል መነጋገሪያ ሆኖ እንደ ሰነበተ ተከብሮ ዐልፏል። በዓሉ ተከብሮ ይለፍ እንጂ፣ መነጋገሪያነቱ አልቆመም፤ ምናልባትም ለመጭዎቹ ዘመናት እንዲሁ መነጋገሪያ እንደ ሆነ ይቀጥል ይሆናል። ባንቱ ገብረ ማርያም፣ “ኢትዮጵያ የ ‘አረማዊ ደሴት’?” ሲሉ የሰየሙት ይህ ጽሑፍ፣ በሮም ግዛት ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች፣ እንዲህ ላለው የአደባባይ በዓል የሰጡትን ምላሽ በታሪክ መነፅር እያስቃኙ፣ ለዛሬ ክርስቲያኖች መልእክት ያቀብላሉ። የባንቱ ገብረ ማርያም ጽሑፍ፣ የእሬቻ በዓልን በሚመለከት ለሚካሄደው ውይይት መፋፋት የራሱ ፋይዳ አለው በሚል እንደሚከተለው ለንባብ በቅቷል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.