[the_ad_group id=”107″]

ኢየሱስ የእግዚአብሔር ክብር ነው

የኢየሱስ ክርስቶስ መለኮትነት

ጆን ፓይፐር
ትርጉም በአማረ ታቦር

የክርስቶስ መሆናችን እኛን ልዩዎች ለማድረግ ሳይሆን፣ በእርሱ ልዩ መሆን ምክንያት እኛ እንድንደሰት ነው። የዚህ መጽሐፍ ዐላማ፣ የክርስቶስን ክብሮች ማወቅ የመጨረሻ ግባችን መሆኑን ማመልከት ነው። የክርስቶስ ክቡርነቱ፣ እኛ ባለጠጋ ወይም ጤነኛ እንድንሆን አይደለም። ክርስቶስ ክቡር የሆነው ሀብታም ብንሆን ወይም ድኻ፣ ታማሚ ወይ ጠንካራ፣ በእሱ ርካታን እንድናገኝ ነው። 

ክርስቶስ ዘላለማዊ መሆኑ ብቻ ሌላውን ሁሉ ክብሮች ደግፎ የያዘ ቀዳማዊና ልዩ ክብር ነው። ይህንን ማሰላሰል እንደሚገባን ብናስበው በነፍሳችን መርከብ ላይ ታላቅ ወጀብ ይመጣበታል። በፍጹማዊነት ውስጥ መሆን ምናልባት የምስጢሮች ሁሉ ቊንጮ ነው። እስቲ የህላዌን ገደብ የለሽነት እናሰላስል። መቼም ወደ መሆን ያልመጣ አንዳች ነገር መኖር አለበት። በጣም ወደ ኋላና እንደ ገናም ወደ ኋላ፣ ሩቅ ማለቂያ ወደ ሌላቸው ዘመናት አትኩረን እንመልከት፤ ይህም ሆኖ፣ ምንም የነበረበት ጊዜ መቼም አልነበረም። እዚያ በቀዳሚነትና ምንጊዜም የመሆን ክብር የነበረው አንድ ነበር። እርሱ በሆነ ጊዜ የሆነ ወይም የተፈጠረ አይደለም። በቃ ነበረ። ይህ ብቸኛና ፍጹም ክብር የማነው?

ለዚህ ጥያቄ መልሱ፣ “ክርስቶስ ነው” የሚል ነው፤ ዓለም “የናዝሬቱ ኢየሱስ” እያለ የሚያውቀው ሰው።

የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻውን መጽሐፍ የጻፈልን ሐዋርያው ዮሐንስ ወሳኝ የሆነ መገለጥን ተቀብሏል። እግዚአብሔር፣ “ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ። አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ይላል።” (ራእ 1፥8) ብሎ የተናገረውን ይጠቅሳል። ይህን የተናገረው ክርስቶስ አይደለም። ይህ ሁሉን የሚችል [ኀያሉ] አምላክ ነው። ራሱን፣ “አልፋና ዖሜጋ” (በግሪክ ቋንቋ የፊደል መጀመሪያና መጨረሻ ሆሄያት ናቸው) እኔ ነኝ ብሎ ይጠራል። በፊደሉ [ገበታ]፣ ከአልፋ በፊት ማንም አንዳች (ወይም ምንም) ሊናገር አይችልም። በፊደሉ፣ ከአልፋ “ፊት” የሆነ የለም። ከዖሜጋ በኋላም ማንም አንዳች (ወይም ምንም) ሊናገር አይችልም። በፊደሉ፣ ከዖሜጋ “በኋላ” የሆነም የለም። 

በእግዚአብሔርና በእርሱ እውነታ ዘንድ እንዲሁ ነው። ከአምላክ ከፊቱም ሆነ ከኋላው ምንም የለም። ምንም ያህል ወደ ኋላ ወይም ምንም ያህል ወደ ፊት ቢሄዱ፣ እርሱ በሙሉ ሙላት እዚያ አለ። የሙሉ ሙላቱ እውነታ እርሱ ነው። እርሱ እዚያ በመጀመሪያና ሁሌም በመሆን ከበረ። ይህ ብቸኛ ክብር የእርሱ ነው። 

ይህ በብሉይ ኪዳን ያህዌ (ጀሆቫ) ለሚለው ስም ዐቢይ ትርጉም ነው። ስሙ የተዋቀረው “ነኝ” በሚለው ግሥ ነው። ሙሴ አምላክን ስሙን ሲጠይቅ፣ “እግዚአብሔርም ሙሴን ‘ያለና የሚኖር እኔ ነኝ’ አለው፤ እንግዲህ ለእስራኤል ልጆች፣ ‘ያለና የሚኖር ወደ እናንተ ላከኝ ትላለህ’ አለው” (ዘፀ 3፥14)። ይህ “እኔ ነኝ” ኢሳይያስ ላይ በእግዚአብሔር ፍጹምና ዘላለማዊ (ያለፈና የወደ ፊት) ህላዌነት እዳለው አመልካች ሆኖ ተገልጿል። “ ‘ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፥ እናንተ፣ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም፤ ከእኔም በኋላ አይሆንም’ ” (ኢሳ 43፥30)። “እኔ ነኝ” መሆን፣ በፍጹማዊነት የመጀመሪያና የመጨረሻ መሆን ነው። “ከፊቱ” ማንም፣ “ከኋላ” እንዲሁ ምንም አይኖርም። በቃ “እኔ ነኝ”።

እግዚአብሔር ይህንን ኢሳይያስ 44፥6 ላይ ግልጽ ያደርገዋል፤ “የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር፥ የሚቤዥም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እኔ ፊተኛ ነኝ፥ እኔም ኋለኛ ነኝ፥ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም።’ ”  ደግሞም፣ “ያዕቆብ ሆይ፥ የጠራሁህም እስራኤል ሆይ፥ ስማኝ፤ እኔ ነኝ፤ እኔ ፊተኛው ነኝ፥ እኔም ኋለኛው ነኝ” ብሎ ይደግመዋል (ኢሳ 48፥12)። ስሙ ይህ ነው፦ ያህዌ፤ እርሱ በፍጹማዊነት፣ በዘላለማዊነት እንዲሁም በአይገበሬነት የሆነ ነው። እርሱ ሁሌም፣ ምንም ባልነበረበት ጊዜ፣ ከሁሉ የተለየ ስምና ለእርሱ ብቻ የሚገባው ክብር ያለው ነው። አምላክ መሆን ማለት እንደህ ነው።

ታዲያ፣ ይህ እኛ “የናዝሬቱ ኢየሱስ” ብለን ከምናውቀው ክርስቶስ ጋር ምን ግኑኝነት አለው?

በሁሉ አንጻር ይገናኛል። ሐዋርያው ዮሐንስ በራእዩ መጨረሻ ላይ፣ ክርስቶስ “እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ … አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ” (ራእ 22፥12-13) ብሎ የተናገረውን ይጠቅሰዋል። ይህን የሚናገረው ክርስቶስ እንጂ፣ እግዚአብሔር አባት አይደለም። እንግዲህ፣ አንድ ካልሆኑ በስተቀር፣ ሁለቱም “አልፋና ዖሜጋ” ሊሆኑ አይችሉም። አንድ ካልሆኑ በስተቀርም፣ ሁለቱም “መጀመሪያውና መጨረሻው” ሊሆኑ በፍጹም አይችሉም። ሆኖም ግን ክርስቶስ (ራሱን ኢየሱስ ብሎ የሚጠራው)፣ ሁሉን ቻዩ ኀያሉ አምላክ ያለውን አንድ ዐይነት ስምና ክብር ለራሱ ይገባኛል ይላል (በተጨማሪ ራእ 1፥17-18፤ 2፥8 ይመልከቱ)። 

ኢየሱስ “እኔ ነኝ” የሚለውን የእግዚአብሔር ብቻ የሆነውን ድንቅ ስም ለራሱ ወስዷል። “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ” (ዮሐ 8፥58)። ኢየሱስ ሕይወቱ የምታልፍበት ጊዜ ሲቀርብ፣ “በሆነ ጊዜ እኔ እንደ ሆንሁ ታምኑ ዘንድ፥ ከአሁን ጀምሬ አስቀድሞ ሳይሆን እነግራችኋለሁ” ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ ይነግራቸዋል (ዮሐ 13፥19፤ 8፥24 ይመልከቱ)። ማንም ሰው ከዚህ የሚበልጥ አንዳች ነገር ስለራሱ ሊናገር አይችልም። እውነታው ይህ ነው፤ ከዚህ ውጭ ያለው የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ አንሥቶ መሳደብ ነው የሚሆነው። ክርስቶስ መለኮት ነው፤ ወይም አምላክ የለሽ ነው።

ዮሐንስ የትኛው እንደ ሆነ አውቋል፤ “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። ይህ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። … ቃልም ሥጋ ሆነ፤ … አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ [አንዳንድ ትርጉሞች “እቅፍ”፣ “የተወለደ” ይላሉ]” (ዮሐ 1፥1፡ 14)። “ቃል” የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ—የሆነ ጊዜ ሳይሆን ለዘላለም በአባቱ “ዘንድ የነበረ” እንጂ የተፈጠረ አይደለም። ሁለት አምላኮች ያልሆኑ፣ በአንድ የሚቆሙ ሁለት አካላት—በአብ ዘንድ የነበረ “ወልድ”፣ አንድ ዐቢይ መለኮት። መሆን እንደሚገባውም ይህ ታላቅ ምስጢር ነው፤ ሆኖም፣ እግዚአብሔር ስለ ራሱ የገለጠው ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስም ለክርስቶስ ብቻ ስለሚገባው ልዩ ክብር አውቋል። እርሱ፣ “… ከእነርሱም ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥ እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው፤ አሜን” (ሮሜ 9፥5)። ይህም ሆኖ ግን፣ “እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ [እርሱ] ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ” (ፊል 2፥6-7)። ስለዚህም፣ “በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና” (ቆላ 2፥9፤ 1፥19 ይመልከቱ)። እናም፣ እኛ ክርስቲያኖች አሁን እየጠበቅን ያለነው ሰው ብቻ የሆነውን ሳይሆን፣ “የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ” ነው (ቲቶ 2፥13፤ 2ኛ ጴጥ 1፥1 ይመልከቱ)። 

የዕብራውያን ጸሐፊም በድፍረት የሚናገረው፣ ሁሉም መላእክት ለክርስቶስ ይሰግዳሉ እያለ ነው። በመላእክት መካከል ሆኖ፣ ለእግዚአብሔር የሚሰግድ ሊቀ መላእክት አይደለም። በሁሉም መላእክት እንደ አምላክ ይሰገዱለታል። “ደግሞም [እግዚአብሔር] በኵርን ወደ ዓለም ሲያገባ፥ ‘የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ ይላል’ ”(ዕብ 1፥6)። እርሱ የሁሉ ፈጣሪ ነው፤ እርሱ ራሱም አምላክ ነው፤ “ስለ ልጁ ግን፣ ‘አምላክ ሆይ፥ ዙፋንህ እስከ ዘላለም ድረስ ይኖራል’ … ደግሞ። ‘ጌታ ሆይ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ’ ” (ዕብ 1፥8፡ 10) እያለ አብ ስለ ወልድ መለኮትነት ይመሰክራል። “እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በሥልጣኑ ቃል እየደገፈ” (ዕብ 1፥3) ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ የሁለንታ (ዩኒቨርስ) ፈጣሪ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ አልፋና ዖሜጋ፣ የመጀመሪያውና የመጨረሻው ነው። አካል የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ መጀመሪያ አልነበረውም። እርሱ ፍጹም [ወሰን/ገደብ የለሽ] እውነታ ነው። እርሱ የመጀመሪያና ሁሌም ሆኖ፣ ምሳሌ የሌለው የከበረ ስምና የእርሱ ብቻ የሆነ ክብር አለው። እርሱ ለዘላለም ያለ [የተወለደ] ነው። “እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ” (ዕብ 1፥3)፣ አብ በልጁ አካል ለዘላለም ተደስቶበታል። 

ይህንን ክብር ማየትና መጠማት፣ የደኅንነታችን መጨረሻ ነው። “አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወድዳለሁ።” (ዮሐ 17፥24)። ይህንን ለዘላለም መመገብ፣ የመፈጠራችንና የመዋጀታችን ዐላማ ነው።

ጸሎት

የዘላለም አባት ሆይ፤ አንተ ጅማሬ ኖሮህ አያውቅም። መቼም ቢሆን መጨረሻ አይኖርህም። አንተ አልፋና ዖሜጋ ነህ። እኛ ይህንን ያመንነው፣ አንተ ስለገለጥህልን ነው። አባት ሆይ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ የአንተ ዘላለማዊና መለኮታዊ ልጅ ሆኖ የተወለደ እንጂ፣ ያልተፈጠረ እንደ ሆነ እንዲሁም አንተ አባታችን እና ልጅህም አንድ አምላክ እንደሆናችሁ ዓይናችንን ከፍተህልን እንድናይ ስላደረግኸን፣ ልባችን በምስጋና ወደ ላይ ይዘልላል። እነዚህ እጅግ አስገራሚ የሆኑ እውነቶችን በከንፈሮቻችን አድርገን፣ በጠወለጉና ብቃት በሌላቸው ቃላት እንዳናዋርድህ በመስጋት በፍርሀት እንርዳለን። ሆኖም፣ ልናመሰግንህ ስለሚገባን፣ መናገር ይኖርብናል። ዝምታ ያዋርደናል፤ ድንጋዮቹ እንኳን ይጮኻሉና! አንተው በሠራኸው ዓለም ላይ፣ በአንተነትህ ልትወደስ ይገባሃል። እንዲሁም፣ የልጅህን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር እንድንቀምስና እንድናይ ስላደረኸን ልናመሰግንህ ይገባናል። አቤት እርሱን ማወቅ! አባታችን ሆይ፤ እርሱን ልናውቀው እንናፍቃለን። ስለ ክርስቶስ አሳንሰን የምናስባቸው ነገሮችን ከአእምሯችን አስወግድልን። ነፍሶቻችንን በክርስቶስ መንፈስና በታላቅነቱ ሙላት ሙላልን። አንተ በእርሱ ውስጥ ለእኛ በሆንኸው የመርካት አቅማችንን አስፋልን። ሥጋና ደም ኀይል የለሽ በሆኑበት፣ ክርስቶስን ገልጠህልን አትኩሮታችንን እና ፍቅራችንን ፍጹም ወደሆነው ድንቅ ልጅህ እንዲሳብ አድርግ። እንዲሁም፣ ባለጠጋ ብንሆን ድኻ፣ ሕመምተኛ ወይም ጤነኛ በእርሱ ተለውጠን፣ የእርሱ ልኂቅነት አስተጋቢ ድምፆች እንድንሆን አድርገን። በኢየሱስም ስም ጸለይን፤ አሜን።

Share this article:

የነገረ መለኮት ነገር

ክርስትና በአፍሪካ ውስጥ በስፋት በመስፋፋት ላይ እንደ ሆነ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ሆኖም ግን ʻእየተስፋፋ ያለው ክርስትና ምን ዐይነት ገጽታ አለው?ʼ የሚለው ትኩረት የሚያሻው ጥያቄ ነው። የቁጥር ዕድገት ቤተ ክርስቲያን በማኅበረ ሰቡ ውስጥ ያላትን መገኘት በማግዘፍ የሚኖራትን ሚና ያጎላዋል። በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ ዕድገቱ የተለያዩ ተግዳሮቶችን ይዞ ይመጣል። ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ዕድሎች የማትጠቀም ወይም ለተግዳሮቶች ምላሸን የማትሰጥ ከሆነ በምትኖርበት ማኅበረ ሰብ ውስጥ ያላት ፋይዳ እጅግ አናሳ ይሆናል።

ተጨማሪ ያንብቡ

መንፈስ ቅዱስ በታሪክ ውስጥ

በዘመናችን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምስባኮች ላይ መንፈስ ቅዱስ የሚለው ስም መጥራት የተለመደ ቢሆንም፣ ሕዝበ ክርስትያኑ ስለ መንፈስ ቅዱስ ማንነት ጠንቅቆ ያውቃል ለማለት አስቸጋሪ ይመስላል። መንፈስ ቅዱስን አስመልክቶ ግልጽ አስተምህሮ ያለም አይመስልም። ለአንዳንዶች መንፈስ ቅዱስ ተአምራት ማድረጊያ ኀይል፣ እንዲሁም በጨርቅ ተደርጎ እና በጠርሙስ ታሽጎ የሚወሰድ ትንግርት መፍጠሪያ ሲሆን፣ ለሌሎች ደግሞ ማነቃቂያ እና ተሃድሶ የሚያመጣ እሳት ወዘተ. ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.