[the_ad_group id=”107″]

በግ አንበሳው

የኢየሱስ ክርስቶስ ልዕቀት 

በግ አንበሳው1

የኢየሱስ ክርስቶስ ልዕቀት2

“እንደ ታረደ በግ
ቆሞ አየሁ፥
ሰባትም ቀንዶችና
ሰባት ዓይኖች ነበሩት”
ራእይ 5:6

አንበሳን ያስከበረው አስፈሪ ጒልበቱና ንጉሣዊ ገጽታው ነው። በግን የሚያስከብረው የዋህነቱና በአገልጋይነት ሐር ለልብሳችን መስጠቱ ነው። ከዚህ በላይ አስደናቂው ግን፣ አንበሳ መሳይ በግ እና በግ መሳይ አንበሳ መሆን ነው። ጆናታን ኤድዋርስ ከ250 ዓመታት በፊት እንዳስተዋለው፣ ክርስቶስን ከሁሉ የላቀ እንዲሆን ያደረገው፣ “የልዩ ልዩ ታላቅነቶች ድንቅ ውሕድ” መሆኑ ነው።

ለምሳሌ ያህል፦ ክርስቶስን በምጥቁነቱ እናደንቀዋለን፤ ከዚህ በላይ የሚያስደንቀን ግን፣ ልዕቀቱ ለእግዚአብሔር ከመገዛቱ ጋር መዋሐዱ ነው። አይበገሬ ፍርዱ ከምሕረቱ ጋር መደባለቁ፣ በእርሱ እንድንደነቅ ያደርገናል። ግርማው የየዋህነት ጣፋጭ ሽታ መዓዛ አለው። ከእግዚአብሔር ጋር አንድ መሆኑ ውስጥ፣ ጥልቅ የሆነ እግዚአብሔርን ማክበር አለ። መልካም የሆነው ሁሉ ይገባው የነበረ ቢሆንም፣ በክፋት መሰቃየትን ታገሠ። በዓለም ላይ ያለው ሉዓላዊ ገዢነቱ፣ የመታዘዝና የመገዛት መንፈስን የተላበሰ ነው።

በጥበቡ የኲሩ ጻፎችን አፍ ያስያዘ፣ በሕፃናት ግን ሊወደድ የሚችል ቀሊል ነበር። እርሱ በቃሉ ማዕበልን ጸጥ ማድረግ የሚችል፣ ሳምራውያኑን ግን በመብረቅ ያልመታ፣ ከመስቀሉም ላይ ራሱን ያላወረደ ነው።

የክርስቶስ ክብር ተራ ነገር አይደለም። በአንድ ሰው ውስጥ ሆኖ በጣም በተለያዩ ድንቆች የሚገለጥ ነው። ይህንን በአዲስ ኪዳን፣ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ እናየዋለን፦ “እነሆ፤ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ፣ እርሱም የዳዊት ሥር መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ፣ ሰባቱንም ማኅተም ይፈታ ዘንድ ድል ነሥቷል” (5:5) በሚለው። እዚህ ላይ፣ ድል የነሣው አንበሳ መሳዩ ክርስቶስ፣ የታሪክን መጽሐፍ ሊዘረጋ ተዘጋጅቷል።

ሆኖም፣ በሚቀጥለው ቊጥር ምን እናያለን? “በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች መካከልም፣ በሽማግሌዎችም መካከል እንደ ታረደ በግ ቆሞ አየሁ፤ ሰባትም ቀንዶችና ሰባት ዓይኖች ነበሩት፤ እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው” (ቊጥር 6) ። ስለዚህ አንበሳው በግ ነው፤ ደካማና የማይጎዳ፣ ትሑትና በቀላሉ የሚያጠቁት እንዲሁም እኛ እንለብስ ዘንድ ራቁቱን የተሸለተና ለምግባችን የተገደለ እንስሳ! ስለዚህም፣ ክርስቶስ በግ መሳይ አንበሳ ነው።

የይሁዳ አንበሳው ድል የመንሣት ምስጢር፣ በግ የመሆንንም ሚና ለመጫወት ዕሺ ማለቱ ነበር። በሆሳዕና ወደ ዙፋን እንደሚወጣ ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፤ በስቅለት ቀን ሊታረድ እንደተዘጋጀ በግ ከኢየሩሳሌም ወጣ። ግዳዩን እንደሚዘነጥል አንበሳ፣ ዘራፊዎችን ከመቅደስ አባረራቸው። በሳምንቱ ግን፣ ግርማዊ አንገቱን ለካራ ሰጠ፤ እነርሱም፣ የይሁዳ አንበሳውን እንደ መሥዋዕት በግ አረዱት።

ግን፣ ይህ ምን ዐይነት በግ ነበር? ራእይ 5:6 “እንደ ታረደ በግ ቆሞ አየሁ፤ ሰባትም ቀንዶች …” ይላል። ሁለት ነገሮች እናስተውል። በመጀመሪያ፣ በጉ “ቆሟል” ። እንደ ያኔው ደሙ እየተንዠቀዠቀ ወድቆ መሬት ላይ አልተዘረጋም። አዎ፤ ታርዷል፤ ነገር ግን አሁን ቆሟል፤ በውስጠኛው ዙሪያ ውስጥ ከዙፋኑ አጠገብ ቆሟል።

ሁለተኛ፣ በጉ ሰባት ቀንዶች አሉት። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ፣ ቀንድ የኀይልና የሥልጣን ምልክት ነው (12:3፤ 13:1፤ 17:3-12)፤ በብሉይ ኪዳንም እንዲሁ ነው (ዘዳ 33:17፤ መዝ 18:2፤ 112:9) ። ሰባት ቊጥር፣ ሙላትንና ፍጹምነትን አመልካች ነው። ስለዚህም፣ ይህ ተራ በግ አይደለም። ከሙታን መካከል ህያው ነው፤ በባለ ሰባት እጥፍ ጥንካሬው፣ ፍጹም ኀያል ነው። እርሱ፣ እውነትም አንበሳ መሳይ በግ ነው።

ይህንን ራእይ 6:16 ላይ ሰዎች፣ ተራሮችንና ዓለቶችንም፣ “በላያችን ውደቁ፤ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን፤” በማለታቸው ውስጥ በፍርሀት እየራድን እናያለን። እንዲሁም ራእይ 17:14 ላይ፣ “እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል” በሚለውም ውስጥ እናየዋለን።

ስለዚህ፣ ክርስቶስ በግ መሳይ አንበሳ እንዲሁም አንበሳ መሳይ በግ ነው። ክብሩ ይህ ነው፦ “የልዩ ልዩ ታላቅነቶች ድንቅ ውሕድ” ። ይህ ድንቅ ውሕደት ደምቆ የሚበራ ነው፤ ምክንያቱም ከእኛ ግላዊ ደካማነትና ትልቅ የመሆን መሻት ጋር በፍጹምነት ይስማማልና። ኢየሱስ፣ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፤ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” (ማቴ 11:28-29) ብሏል። የዚህ አንበሳ በግ መሳይ ገራምነትና የዋህነት፣ በብርቱ ድካማችን ውስጥ የሚደግፈን ነው። በዚህም ምክንያት እርሱን እንወድደዋለን። የሚመለምለን እንደ የባሕር ኮማንዶ ምልመላ ቢሆን ኖሮ፣ ተስፋ ቢሶች ሆነን በቀረን ነበር፤ ነገር ግን፣ ይህ የየዋህነት ባሕርይ ለብቻው ክብር አይሆንም። የበግ መሳዩ አንበሳ ገራምነትና ትሕትና፣ ከአንበሳ መሳዩ በግ ዘላለማዊ ሥልጣን ጋር የሚያንጸባርቅ ሆኗል። ትልቅ ለመሆን ካለን መሻታችን ጋር የሚስማማው ይህ ብቻ ነው። አዎ፤ እኛ ደካሞችና የዛልን፣ ሸክምም የከበደን ነን። ሆኖም፣ ሕይወታችን ለሆነ ታላቅ ነገር እንደሚውል የሚነግረን፣ ዐልፎ ዐልፎ የሚነድድ ሕልም በሁላችንም ልብ ውስጥ አለ። ለዚህ ሕልም ኢየሱስ፣ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ … ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴ 28:18-20) ብሏል።

አንበሳ መሳዩ በግ በመላው እውነታ ላይ ባለው ፍጹማዊ ሥልጣን እንድንጽናና ያደርገናል። ኀያል ሥልጣኑ፣ እስከ ዘመን ፍጻሜ ድረስ ዐብሮን እንደሚሆን ያስታውሰናል። የምንመኘው ይህንን አሸናፊ፣ አይበገሬ መሪ ነው። [እኛ] ሟቾች ብንሆንም ተራዎች ግን አይደለንም። የምናሳዝን፣ ነገር ግን ጥልቅና ኀያል ፍቅር ያለን ነን። ደካሞች ብንሆንም፣ ሕልማችን ድንቆችን ለማድረግ ነው። በልባችን ውስጥ ዘላለማዊነት የተጻፈብን ህልፈታውያን ነን። የእርሱ ልዩ ልዩ ታላቅነቶች ድንቅ ውሕደት ከውስብስብነታችን ጋር የተስማማ በመሆኑ ምክንያት፣ የክርስቶስ ክብር በሙላት ያንጸባርቃል።

ይህ በግ መሳይ አንበሳ አንዴ ተጨንቆና ተሠቃይቶ ነበር። በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም (ኢሳ 53:7) ። በመጨረሻው ቀን ግን እንዲህ አይሆንም። በግ መሳዩ አንበሳ፣ አንበሳ መሳይ በግ ይሆናል፤ በንጉሠ ነገሥትነት ሥልጣኑ በእሳቱና ባሕር ዳርቻ ቆሞ፣ ለንስሐ እምቢተኛ ጠላቶቹ፣ “በቅዱሳንም መላእክትና በበጉ ፊት … የሥቃያቸውም ጢስ ለዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ይወጣል” (ራእይ 14:10-11) ።

ጸሎት

ሁሉን ቻይና ምሕረትህ የበዛ አምላክ ሆይ፤ በልጅህ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በመንጸባረቁ እንፈነድቃለን። በእርሱ የአንበሳ መሳይ ኀይል ጥንካሬና በበግ መሳይ የዋህ ርኅራኄው ላይ ሀሴትን እናደርጋለን። አቻ በሌለው የልኂቀነቶቹ ውሕደት የልብ መጽናናትን እናገኛለን። ይህም፣ እርሱን የመሰለ አንዳች እንደሌለና እንደ ሌሎቹ ሰው ብቻ እንዳልሆነ ያረጋግጥልናል። በአስነዋሪ ምንገዶኝነታችን ውስጥ፣ በይሁዳ አንበሳው ፊት እንድንቀጠቀጥና በጽኑ ቅድስናው እግር ሥር በትሕትና እንድንወድቅ አድርገን። በስብራትና በፍርሀታችን ውስጥ፣ ከአንበሳ መሳዩ በግ ብርታትን ማግኘት እንድንችል ርዳን። አቤቱ፤ ክርስቶስ በሙላት ምንኛ ያስፈልገናል! የልዕቀቱን ሙላት ማየት እንድንችል ዓይናችንን ክፈትልን። አምልኳችንን የሚያሳንሱና ታዛዥነታችንን ሽባ የሚያደርጉትን፣ ስለ ልጅህ ማንነት ያለንን የተንጋደደና የተዛባ ምስል አስወግድልን። የአንበሳው ጥንካሬና የበጉ ፍቅር፣ በክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት የማይነቃነቅ ያድርገው። ስለዚህ፣ ከተራ ሕልሞችና ትናንሽ ሙከራዎች እንዲሁም ተቆራራጭ ዕቅዶች አድነን፤ አጀግነን፤ አጠንክረን። በጽኑና ትሑት ፍቅር መውደድ እንድንችል አስችለን። የይሁዳ አንበሳው እንደ በግ ለመሞትና በዘላለማዊ ደስታ እንዲነሣ ብርታት የሆነው ድፍረት ውስጥ፣ እኛም ድርሻ እንዲኖረን አድርገን። በዚህም ሁሉ፣ ሁሉም የክርስቶስን ክብር እንዲያይና በእርሱም አንተ እንድትከብር አድርግ።

በክርስቶስ ስም ጸለይን፣ አሜን።


  1. ወንድም ሰሎሞን ጥላሁን በአንድ ስብከቱ ውስጥ ውስጥ ሲናገር ከሰማሁት የተወሰደ።
  2. John Piper, “Seeing and Savoring Jesus Christ,” Desiring God Foundation (2004), p.28-33

     

Amare Tabor


አማረ ፈቃደ ታቦር የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በስታትስቲክስ፣ ሁለተኛውን በኮምፒውተር ሳይንስ የሠሩ ሲሆን፣ መጻሕፍትን የማንበብ ልምድና የመተርጎም ዝንባሌ አላቸው። በተለይ በክርስትና ዙሪያ የተለያዩ መጣጥፎችን በመጻፍና በመተርጎም ይበልጥ ማገልገልን ይሻሉ። 
E-mail: taboramare@gmail.com

Share this article:

ጴንጤቆስጣዊ – ካሪዝማቲካዊ

የኢትዮጵያ ወንጌላዊው ክርስትና ካሪዝማዊነት እና ጴንጤቆስጣዊነት ዐይነተኛ መለያው ይመስላል። በአመዛኙ በልምምድ ላይ ትኩረቱን ያደርጋል እየተባለ የሚወቀሰው ይህ ክርስትና፣ ወደ ኢትዮጵያ የመጣበትን ታሪካዊ አጎለባበትና ያመጣውን ትሩፋት እንዲሁም አሁን እየተፈተነበት ያለበትን ዐደጋ ሚክያስ በላይ እንደሚከተለው ያስቃኛል።

ተጨማሪ ያንብቡ

የነቢያቱ “መደመር” እና የፈጠረው ስሜት

ኅብረቱ ከአራት ነቢያት “የአጋር አባልነት” ስምምነት ማድረጉን ተከትሎ፣ በርካታ አስተያየቶች በመሰጠት ላይ ናቸው። የስምምነቱ ይዘት፣ ነቢያቱ የተረዱበት መንገድ፣ የሂደቱን አጀማመር እና ስምምነቱ አለበት የተባሉትን ክፍተቶች ሚክያስ በላይ የተለያዩ ሰዎችን አነጋግሮ እንደሚከተለው አቅርቦታል።

ተጨማሪ ያንብቡ

እንዴት እንድትተይቡ ተጠንቀቁ!

“በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች፣ የሰርክ ልማድ እስኪመስል ድረስ እየታዩ ያሉት አንዳንድ ምልልሶቻችን፣ ለትልቅ ቅራኔ በር የሚከፍቱና አሉታዊ ስሜቶች ያየሉባቸው ናቸው። ከዐሳብ ይልቅ ሰብእናን ማጥቃትንና የተቃወመንን ኹሉ በተመጣጣኝ የመልስ ምቶች ማደባየትን ተክነናል። ከፉውን በመልካም የመመለስና በጸድቅ በልጦ የመገኘት ክርስቲያናዊ ዕሴት ያለን እስከማይመስል ድረስ፣ ለኹሉ በሰፈሩት ቍና የመስፈር ዓለማዊ ጥበብ ተጠናውቶናል። ዐሳቡን ያልገዛንለት ሰው ሲኖር፣ ሌሎች ሰዎች ለዚያ ሰው ያላቸው ክብርና ፍቅር እስኪሸረሸር ድረስ በሚዘልቅ ጥቃት እንከፋበታለን፤ የለየት ማጠልሸት ውስጥ እንገባለን።” አሳየኸኝ ለገሰ

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.