የእግዚአብሔርን ክብር ማየትና መጠማት
የኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻው ግብ1
ጆን ፓይፐር
ትርጉም አማረ ታቦር
ይህ የተፈጠረ ሁለንታ (universe) ምክንያቱ ለክብር ነው። የሰው ልጆች ልብ ውስጣዊ ምኞትና የሰማይ የምድር ውስጣዊ ምንነት በሚከተለው ሐረግ ሊጠቀለል ይችላል፤ የእግዚአብሔር ክብር። ሁለንታ የተፈጠረው ይህንን ለማሳየት ነው፤ የእኛም ህልውና ይህንኑ ለማየትና ለመጠማት ነው። ከዚህ ያነሰው ረብ የሌለው ይሆናል። ዓለም ሥርዐት የለሽና ተግባረ ቢስ የሆነችውም በዚህ ሳቢያ ነው። የእግዚአብሔርን ክብር በሌላ ለውጠነዋል (ሮሜ 1፥23)። “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ” (መዝ 19፥1)።
የሁለንታ መኖር ምክንያቱ ይህ ነው፤ ሁሉም ስለ ክብር ነው። “ኸብል” ተብሎ የሚጠራው ጠፈርን አቅርቦ የሚያሳይ መነፅር (Hubble Space Telescope)፣ ከወደ ዐሥራ ሁለት ቢሊዮን የፀሓይ ዓመታት (ስድስት ትሪሊዮን ማይል ሲባዛ በዐሥራ ሁለት ቢሊዮን) ርቀት ላይ የሚገኙ ለዐመል ያህል የሚታዩ ጋላክሲዎችን ታህተቀይ ምስሎችን ይልካል። በእኛ የወተት ጎዳና (Milky Way) ውስጥ እንኳን፣ ለመግለጥ እጅግ የሚከብዱ ከዋክብት አሉ፤ ለምሳሌ፣ ኢታ ካሪኔ (Eta Carine) የሚባለው ከእኛ ፀሓይ አምስት ሚሊዮን እጥፍ ብርሃናማ ነው።
ሰዎች አንዳንዴ ይህንን እጅግ በጣም መጠነ ሰፊንትን ከሰው ልጅ እጅግ አናሳነት ጋር በማዛመድ ይሰናከላሉ። ይህ እኛን በወሰን አልቦነት ትንሽ የሚያደርገን ይመስላል። ነገር ግን፣ የዚህ መጠን ፍቺ ብዙም ስለ እኛ ሳይሆን ስለ እግዚአብሔር ነው። የእግዚአብሔር ቃል፣ “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ” ይላል። ጠብታ የሆነውን የሰው ልጅ ለማኖር፣ በሁለንታ ላይ ይህ ሁሉ ቦታ “የባከነበት” ምክንያት፣ ስለ እኛ ሳይሆን ፈጣሪያችንን ለማሳየት ነው። “ዓይናችሁን ወደ ላይ አንሥታችሁ ተመልከቱ፤ እነዚህን [ከዋክብትን] የፈጠረማን ነው? ሠራዊታቸውን በቍጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፤ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ በኃይሉ ብዛትና በችሎቱ ብርታት አንድስ እንኳ አይታጣውም” (ኢሳይያስ 40፥26)።
ውስጣዊ የሰው ልጅ ልብ መሻት፣ የእግዚአብሔርን ክብር ለማወቅና በእሱም ደስ መሰኘት ነው። ጌታ አምላክ፣ “… ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፣ በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፣ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ” (ኢሳይያስ 43፥6-7) ይላል። የምንኖረው ይህንን ለማየት፣ ለመጠማት፣ እንዲሁም ለማሳየት ነው። እነዚህ ዱካቸው የማይገኝና በአእምሮ ሊገመቱ የማይቻሉ የሁለንታ መለጠጦች፣ የማያልቀው የእሱ “የክብሩ ባለጠግነት” (ሮሜ 9፥23) ምሳሌ ናቸው። ተፈጥሯዊው ዓይን መንፈሳዊውን ዓይን፣ “የነፍስህ መሻት ይህ ሳይሆን፣ ይህንን የሠራው ነው” የሚለው ይመስላል። ቅዱስ ጳውሎስ፣ “በእግዚአብሔር ክብርም ተስፋ እንመካለን” ይላል (ሮሜ 5፥2)። እንዲያውም በቀጥታ ሲናገር፣ እኛን “አስቀድሞ ለክብር ባዘጋጃቸው” ይለናል (ሮሜ 5፥2) ። የተፈጠርነውም ለዚህ ነው፤ ይኸውም፣ እሱ “ለክብር ባዘጋጃቸው በምሕረት ዕቃዎች ላይ የክብሩን ባለጠግነት ይገልጥ ዘንድ” (ሮሜ 8፥23) ነው።
በእያንዳንዱ ሰው ልብ ውስጥ ያለው ውጋት (ሕመም) ይህ ነው። ሆኖም ይህንን እኛ አፍነነዋል፣ በእውቀታችንም እግዚአብሔርን ለማወቅ የበቃን አንመስልም (ሮሜ 1፥28)። በዚህም ምክንያት፣ ፍጥረት ሁሉ ሥርዐት የለሽነት ውስጥ ገባ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሁሉ ጎልቶ የሚታየው ምሳሌ፣ የወሲባዊ ሕይወታችን ሥርዐት የለሽነት ነው። ጳውሎስ የተመሳሳይ ጾታ (እንዲሁም የተቃራኒ ጾታ) ግንኙነት ሥርዐት የለሽነት ሥረ መሠረት፣ የእግዚአብሔርን ክብር ለሌላ በመለወጡ ነው ይላል። “ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ …” (ሮሜ 1፥26-27) ። የእግዚአብሔርን ክብር በትናንሽ ነገሮች ከለወጥን፣ እሱም የብሉሹነታችን (depravity) ምሳሌ ለሆኑ ዐላፊ ነገሮች አሳልፎ ይሰጠናል፤ ሌሎቹ ልውጠቶች በስቃያችን ውስጥ፣ የራሳችንን የመጨረሻ ኪሳራ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው።
ዋናው ነጥብ የሚከተለው ነው፤ እኛ የተፈጠርነው ከሁሉም ነገሮች በላይ የእግዚአብሔርን ክብር ለማወቅና እርሱንም እንደ ክቡር መዝገብ ለመያዝ ነው፤ ይህንን ክቡር መዝገብ ለሌሎች ነገሮች ስንለውጠው፣ ሁሉም ነገር ሥርዐት የለሽ ይሆናል። የእግዚአብሔር ክብር ፀሓይ በነፍሳችን የሕዋ ሥርዐት እምብርት ላይ እንዲያበራ ተደርጎ የተቀመጠ ነው። ይህ ሲሆን የሕይወታችን ፕላኔቶች ሁሉ በትክክለኛው መሥመራቸው (ምህዋር) ላይ ይሆናሉ። ፀሓይ ቦታውን ሲለቅቅ ግን ሁሉ ነገር ይፈረካከሳል። የነፍስ ፈውስ ከመካከል ሆኖ ሁሉን ነገር ወደ ራሱ ወደሚስበው የእግዚአብሔር ክብር በመመለስ ይጀምራል።
ሁላችንም የተራብነው እራሳችንን ሳይሆን የእግዚአብሔርን ክብር ነው። ማንም ሰው ወደ ግራንድ ካኒየን (Grand Canyon) የሚሄደው የራሱን ክብር ለመጨመር አይደለም። ታዲያ ወደዚያ (የእግዚአብሔር ክብር) የምንሄደው ለምንድን ነው? የዚህ ምክንያቱ እራስን ከመመልከት ይልቅ፣ የእሱን ውበት በማየት ለነፍስ ትልቅ ፈውስ እዛ ውስጥ በመኖሩ ነው። በእውነቱ፣በዚህ መጠነ ሰፊና እጅግ አስደናቂ ሁለንታ ውስጥ፣ ከዚህች መሬት በተባለች ጠብታ ላይ ሆኖ አንድ ሰው በመስታወት ፊት ቆሞ ከራሱ ምስል ትልቅነትን ከመፈለግ የሚበልጥ ቀልድ የት ይገኛል? የዘመናዊው ዓለም ወንጌል እንደዚያ መሆኑ ግን በጣም ያሳዝናል።
ይህ የክርስቲያን ወንጌል አይደለም። በማይረባው በራስ የመጠመድ ጨለማ ላይ፣ “የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው” (2ኛ ቆሮንቶስ 4፥4) አደረገ። የክርስቲያን ወንጌል ስለ ክርስቶስ ክብር እንጂ ስለ እኔ አይደለም። በሌላ አንጻር አይተነው ስለ እኔ ሲሆን ቁም ነገሩ ያለው ብዙም እኔ በአምላክ መሠራቴ ላይ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር አድርጎ በምሕረቱ ለዘላለም በእርሱ በብዙ እንድደሰት እኔን ማስቻሉ ላይ ነው።
ኢየሱስ በፍቅሩ ሊያደርግልን የሚችለው ከሁሉ የላቀው ነገር ምን ይሆን? የወንጌሉ ጥርዘት (ወይም መጨረሻ ነጥብ)፣ ከሁሉ የላቀው መልካምነት የቱ ጋር ነው? መዋጀት? ይቅርታ? መጽደቅ? መታረቅ? መቀደስ? ልጅነት? እነዚህ ታላላቅ ድንቆች፣ አንድ ሌላ የበለጠን ነገር አያሳዩምን? ኢየሱስ አባቱ እንዲሰጠን የለመነውን? “አባት ሆይ፤ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ።” (ዮሐንስ 17፥24)።
የመጨረሻ ግባችን የክርስቶስን ክብር ማየትና መጠማት በመሆኑ ምክንያት፣ የክርስቲያን ወንጌል “የክርስቶስ ክብር ወንጌል” ነው። ይህ ምንም ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር ክብር ነውና! “እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ [ነው]” (ዕብራውያን 1፥3)። “እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው” (ቆላስይስ 1፥15)። የወንጌሉ ብርሃን በልባችን ሲበራ፣ “በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ” ነው። “በእግዚአብሔር ክብርም ተስፋ” ስንመካ (ሮሜ 5፥2) ተስፋችን፣ “የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም [የእኛን] የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን” ነው (ቲቶ 2፥13)። የክርስቶስ ክብር የእግዚአብሔር ክብር ነው (የዚህ መጽሐፍን ምዕራፍ 2 ይመልከቱ)። በአንድ አንጻር፣ ክርስቶስ ሲመጣ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ወደ ጎን አስቀምጦ ነው፤ “አሁንም አባት ሆይ፤ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ” (ዮሐንስ 17፥5)። በሌላ አንጻር ደግሞ፣ በመምጣቱ የእግዚአብሔርን ክብር ጠብቋል፣ “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ ዐደረ፤ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን” (ዮሐንስ 1፥14) ። ስለዚህም፣ በወንጌሉ “በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት” (2ኛ ቆሮንቶስ 4፥6) የሚለውን እናያለን፣ እንጠማለንም። የዚህ ዐይነት “ማየት”፣ ለሥርዐት የለሹ ሕይወታችን ፈውስ ነው። “እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን” (2ኛ ቆሮንቶስ 3፥18)።
ጸሎት
የክብር አባት ሆይ፤ ከክብር ወደ ክብር እንድንለወጥ፣ በትንሣኤ፣ በመጨረሻው መለከት ሙሉ በሙሉ የልጅህ የኢየሱስ ክርስቶስ የጌታችንን መልክ እስክንመስል ድረስ የልባችንን ጩኸት ስማ። እስከዛው ድረስ ግን፣ በጌታችን ጸጋና እውቀት፣ በተለይም በክብሩ እውቀት ማደግን እንናፍቃለን። ይህንን ፀሓይ በግልጽ ፍንትው ብላ እንደምትታየን ለማየትና እንደ ትልቅ ፍላጎታችን በጥልቀት መጠማትን እንሻለን። አንተ ቸር አምላክ ሆይ፤ ልባችን ወደ ቃልህ እና ወደ አስደናቂው ክብርህ እንዲያዘነብል አድርግ፤ ከዋጋ ቢስ ነገሮች መጠመድ እስር አውጣን። የተፈጠረው ሁለንታ ስለ ክብርህ የሚነግሩንን ነገሮች ዕለት ተዕለት እንድናይ የልባችንን ዓይኖች ክፈትልን። የልጅህን ክብር በወንጌሉ እንድናይ አእምሮአችንን አብራልን። አንተ፣ በሁሉ የላቅህ ክቡር ነህ፤ እንዳንተ ዐይነት ማንም የለም። አለማመናችንን እርዳው። ለትናንሽ ነገሮች ያለንን ፍቅርና ለእነሱ ከመጠን በላይ ቦታ በመስጠታችን ይቅር በለን። ስለ ክርስቶስ ማረን፤ የአንተ ታላቅ አሳብ የሆነውን የጸጋህን ክብር እንድንፈጽም አድርገን። በኢየሱስ ስም ጸለይን። አሜን።
1. John Piper, “Seeing and Savoring Jesus Christ“, Desiring God Foundation (2004), p.13-18
1 comment
Thats good and change my life. Thank you so much.