[the_ad_group id=”107″]

አቋራጭ ስሌቶች

የተስማማንበት ዳኛ

ሕይወት በርካታ አማራጮችን ‘እንካችሁ’ ይለናል፤ አማራጭ ባለበት ደግሞ መወሰን የግድ ይሆናል። ልጅነታችንን እየሻርን በበሰልን ቁጥር፣ በሌሎች ከመደገፍ (dependency) ይልቅ ከሌሎች ጋር በመደጋገፍ (interdependency) ወደ መወሰን እናድጋለን። ያደግንበት የጋርዮሽ ባህል (communal culture)፣ የቡድን ምርጫን (group identity) እንደማንቆለጳጰሱ፣ ‘ተከተል’ የሚለውን ማኅበራዊ ግፊት ተቋቁመን በራሳችን ለመወሰን መፍቀዳችን የአስተሳሰብ ልዕልናችንን ያሳያል። ግላዊ አመክንዮ በመካከላችን እስከ አሁን ብርቅዬ ከመሆኑ የተነሣ፣ የሐሳባችን ጭብጥ ምንም ይሁን ምን እስካሰብን ድረስ እሰየው ያሰኛል።

አመክንዮን ብርቅዬ እንስሳ ባደረገ ማኅበራዊ መስተጋብር፣ በሐሳብ ይዋጣልን የሚሉ ሰብእናዎች መታየታቸው ደስታችንን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል። በአመንክዮ የመፈንጠዛችን መነሾ፣ ገና የምንፈትሻቸው እልፍ ነገሮች ያሉን ከመሆናችን ጋር ይያዛል። አመክንዮን ጥበቃ ከሩቅ ማንጋጠጣችን የቱን ያህል እንደተጠማነው ምስክር ነው። የምንጠብቀው የተሻለ ነገ ምንም ቢዘገይም፣ የአመክንዮ መፈንጠቅ ተስፋችንን ያለመልመዋል። በአመክንዮ የሚያስቡ ሰዎች እንኳን ኖሩን፤ ይኑሩልንም! ለአመክንዮ ክብር ያላቸው ሰዎች አመንክዮ እንዲዳኛቸው ራሳቸውን ሰጥተዋልና ሲሳሳቱ አያስገርንን። 

አሰናካዮቹ

አመክንዮ በጎ ሆኖ ሳለ አመንክዮዎቻችን ሊሰናከሉ መቻላቸው ሂደቱን እንድንመረምረው ግድ ይለናል። አመክንዮ ይዳኘን ብለን እንደመነሣታችን፣ አመክንዮዋችን ሰንካላ፣ ተያይዞም ፍርዳችን አባይ እንዲሆን አንፈልግም። ከምኞታችን በተቃረነ ፍርሀታችን እውነት መሆኑን የሚያሳዩ አመክንዮ አምካኝ ቅኝቶችን በመካከላችን ማስተዋላችን አልቀረም፤ በአንዳንድ ፍርዶቻችን የአመንክዮዋችን ሰንካላነት እና የፍርዳችን አባይነት አደባባይ ታይቷል። የአመክንዮ መፋለስን፣ ተያይዞም የፍርድ መዛባትን፣ የሚያስከትሉ ጉዳዮች በርካታ ናቸው። ከእነዚህም መካከል፣ ውስጣዊ የልብ መነሣሣት (motivation) ችግር እና አቋራጭ መንገዶች (heuristics) በዋነኛነት ይነሣሉ። የልብ የመነሣሣት ተንሻፎ፣ መፍትሔው ንሰሓ እንደ መሆኑ፣ ለክስተቱ መነሾ ምክንያቶችን ከመጠቆም ባሻገር ምንም ልናደርገው የምንችለው ጉዳይ አይደለም። ሁሉን የሚገልጥ ጌታም ነገረን አደባባይ እስኪያወጣው መፈራረድም ቢያቃቅር እንጂ ማንንም አይጠቅምም። ለግል ሂስ ግን የልብን የመነሣሣት ተንሻፎ ምልክቶቹን መጠቆም ይቻላል። የልብ ጠማማነት፣ በአብዛኛው የሚከሰተው፣ በምናሰላስለው ጉዳይ ላይ ግላዊ ጥቅም ሲኖርና ጥቅማችንን እንዲጠበቅ ሌሎችን ጉዳዮች ለመሠዋት ስንጨክን ነው። በእንዲህ ዐይነቱ ፈተና ተጠላልፈን ራሳችንን እንዳናገኘው፣ ነገሩ የሚያስገኝልን ጥቅም ወይም የሚያሳጣን ነገር አለን ስንል ራሳችንን እንጠይቅ። ልባችን የመንሻፈፉ ምልክት የምንፈልጋቸውን ነገሮችን ዋጋ (values) ከሚገባው በላይ ማግነን መጀመራችንን እና አቋማችን ሊያስከትሏቸው የሚችሉ አደጋዎች (risks) በአንጻሩ በማቃለል መጠመዳችንን በመመልከት መገንዘብ እንችላለን።

የአቋራጭ ተጓዦች

አቋራጭ አድካሚውን መንገድ ትተን፣ በፍጥነት ያደርሳናል በሚል የምንመርጠው ርምጃ ቀናሽ መንገድ ነው። ይሁን እንጂ ይህ መንገድ ሁልጊዜ የጤና አይሆንምና መጠንቀቅ ብልህነት ነው። ለጥልቅ አሳቢያን ዐሥርት ዓመታት የወሰዱ ጉዳዮችን፣ በአንድ ቀን የቁም አሰላስሎ ወይም በአንድ ሰው የመጽሐፍ መግቢያ ንባብ የምንደመድም የአቋራጭ መንገድ አፍቃሪያን አለን። ጥራዝ ነጠቅነታችን አንደበተ ርትዑነትን ከእውቀት ጋር ያምታታል። በርግጥ የማኅበረ ሰባችን ውጤት ነንና፣ ሰሚ ባገኘን ቁጥር ራሳችንን አዋቂ፣ በደፈርን ቁጥር ራሳችንን አማኝ የማድረጉ አባዜ በቀላሉ ላይለቅቀን ይችላል። የአቋራጭ ተጓዥነታችን፣ ሌላው ምስክር፣ ለድምዳሜ እኛውኑ ማቻኮሉ ሳይበቃ፣ የመሪነት ዘንጉን ለመጨበጥ ባለን ፍላጎት ውስጥ ይበልጡኑ ይገለጣል። ከእኛ ምልከታ ውጭ ያሉትን ሁሉ ለአሳር ማለታችን መልሶ ትዝብት ላይ የሚጥለን እኛውኑ መሆኑም አልቀረም። ሌሎች ከትዝብት ይልቅ፣ “ልጅ ነውና ያድጋል” በሚል ርኅራኄ መመልከታቸውን ልብ ያላልንባቸው ጊዜያትም አሉ። የአንዳንዶቻችን ልበ ሙሉነት እንወክለዋለን የምንለውን ማስደንገጡም ሆነ ማሳፈሩ አልቀረም። አቋራጭ መንገደኞቹ ልብ ያላልነው ነገር፣ አንዳንድ ውሳኔዎቻን የቅድመ እሳቤዎቻችን ውጤቶች እንጂ መረጃዎቻችን አብጠርጥረን የደረስንባቸው ድምዳሜዎች አለመሆናቸው ነው። ከእንዲህ ዐይነት ከአቋራጭ መንገዶች ስሕተት እንድንድን፣ የአቋራጭ መንገድ ዐይነቶችን እና አደጋቸውን መመልከት ሁላችንንም ይጠቅማል።

“ለጥልቅ አሳቢያን ዐሥርት ዓመታት የወሰዱ ጉዳዮችን፣ በአንድ ቀን የቁም አሰላስሎ ወይም በአንድ ሰው የመጽሐፍ መግቢያ ንባብ የምንደመድም የአቋራጭ መንገድ አፍቃሪያን አለን።”

የጅምላ ጭፍለቃ

አንደኛው የአቋራጭ መንገድ ዐይነተኛ ምልክቱ በተወሰኑ የማመሳሰያ ሚዛኖች ላይ የተመሠረተ (representative bias) የጅምላ ጭፍለቃ መኖሩ ነው። ጭፍለቃ ነገርን በማመሳሰል የተጠመደ ቅኝት ነው። እንዲህ ዐይነቱ አተያይ በቀደምት ፍረጃዎች ውስጥ ነገሮችን ሁሉ መጠቅጠቅ ይቀናዋል፤ ልዩነቶችን ተመልክቶ አዳዲስ ምድቦችን የማዘጋጀት አቅምም ሆነ ፍላጎት የለውም። በአቋራጭ መንገድ የተደረሰ ትንተና ነገርን በማመሳሰል የተካነ ነው። እንደምንለያይ በርግጠኝነት የምናውቀውን በሙሉ በአንድ ላይ ደምሮ “ያው ናችሁ” በማለቱ ይለያል። ትንታኔው እኛነታችንን በትክክል ስለማይገልጽ ልብን አይነካም፤ ፍጻሜውም ‘ምን እናድርግ?’ በሚል አይቋጭም። የዚህ አስተሳሰብ ችግሩ ለነገሮች ሁሉ አስቀድሞ የተዘጋጀ መልስ ያለውና ማዳመጡ የይስሙላ መሆኑ ነው። ሌላው መገለጫው እንደ እርሱ የማያስቡ ሁሉን፣ ልበ ደንዳኖች ብሎ ይቆጥራል፤ ይሳለቃልም። የቀደሙ ግንዛቤዎች (prior conceptions) አስተሳሰቦችንን ለማቀናበር ያገለገሉ የማዋቀሪያ ንድፎች (conceptual grids) መሆናቸውን ዘንግቶ እንደ አምላካዊ መገለጥ ሙጭጭ በማለቱ ይታወቃል።

አቁማዳው ካልበቃ፣ የሚሆን ሌላ አቁማዳ ማዘጋጀት እንጂ የጅምላ ፍረጃ አያስፈልግም። የጅምላ ፍረጃ፣ ቀርቦ ተመልካች ስላልሆነ፣ በቀላሉ የማይታዩ ልዩነቶች (nuance) እና የነገሮች ውስብስብነቶች (complexity) መመልከት አይችልም። የጅምላ ጭፍለቃ ነገሮች ሁሉ ጥቁር እና ነጭ እንዲሆኑ ካለው ጉገት እንጂ ከነገሮች መልክ እንዳለመመንጨቱ፣ ነገሮች ሁሉ ጥቁር አሊያም ነጭ ናቸው ሲል ችክ ማለቱ አይገርምም። ችኮነቱ አለማወቁን ያጋልጣል። እንዲህ ዐይነቱ የአቋራጭ መንገድ ስሌት፣ አዳዲስ መረጃዎችን የሚመትረው ቀድሞ ከሚያውቃቸው ነገሮች ጋር ያላቸውን ስምምነት በመመልከት ይሆናል። በእነዚሁ ውስን የተመሳስሎ ሚዛን ተመሥርቶም፣ ልዩነቶችን ሳያገናዝብ ለድምዳሜ የሚፈጥን ችኩል እና አቻኳይ መሆኑ አይቀርም። ነገርን በጥቂት ተመሳስሎ በአንድ ጎራ መመደብ ባልከፋ ነበር። ችግሩ ቅድመ እሳቤያችን ተግዳሮት እንዳይገጥመው በሚል ማመሳሰሉ ወሳኝ የሚባሉ ልዩነቶችን ማቃለሉ ነው። በአመሳስሎ ውስጥ ከቅደመ እሳቤዎቻችን ጋር የማይሄዱ መረጃዎች ወደ ጎን ይተዋሉ። የስሌቱ ግድፈት፣ ገሸሽ ያደረግናቸው ነገሮች ለሚዛናዊ ዳኝነት ያላቸው ሚና ትልቅ ከመሆኑ ጋር ይያዛል። ቅድመ እሳቤያችን (pre-conception) ከሚምታታ (confusion)፣ ልዩነት እንደሌለ ተደርጎ ልዩነቱ ቢዘነጋ መመረጡ የአመክንዮአችን መሰናከል ጅማሬ ነው። የብስለት ምልክቱ መረጃ አግላይነት ከሚፈጥረው ሰላም ይልቅ፣ መረጃ ማካተት የሚፈጥረው ጊዜያዊ መምታታትን (temporal confusion) ለመቀበል በመምረጡ ይታወቃል። አግላይ ሰላም፣ ገፊ እና ካጅ እንደ መሆኑ፣ የሚደረጅ እና የሚያድግ አይደለም። አካታች መምታት የተከፈተ ልብ ስለሚኖረው፣ መምታታቱን በእድገት ማረቁ (resolve) አይቀርም። መረጃን ክዶ ርግጠኛ ከመሆን፣ መረጃን ይዞ መወጠር የተሸለ ጥበብ፣ ትሕትና እና እረፍት ነው።

የትውስታችን አቅርቦት

የትውስታዎችን እቅርቦት (availability heuristic) ሁለተኛው የአቋራጭ ስሌቶች ዋንኛ ችግር ነው። እኛ ሰዎች ኑሯችንን በትውስታዎች ላይ መመሥረታችን ሀቅ ነው። ባናስታውስ ኖሮ በእያንዳንዳችን ላይ ጉድ በፈላብን ነበር። ነገርን ደጋግመን ከጅምሩ መማር ስለሚኖርብን፣ የቅርብ ወዳጆቻችንን ጭምር እንደገና ለመተዋወቅ እየተገደድንን፣ ሕይወታችን እጅጉን በከበደ ነበር። የትውስታችን መኖር ሕይወታችንን ያቀልናል። ነገሩ እንዲገባን ከፈለግን በአልዛይመር በሽታ የተጠቁ ሰዎችን እናስታውስ። አመክንዮዋችን የሚሰናከለው፣ ትውስታችን አንዳንዶቹ ለማስታወስ እንደሚቀለው እና ሌሎቹን ለማስተዋል እንደሚቸግረው መገንዘብ ሲያቅተው ነው። የትውስታን ችግር ያልተገነዘበ አመክንዮ፣ ለሚዛናዊነት ተጨማሪ መረጃዎችን ከትውስታችን የውስጠኛ ክፍል መፈለግ እንዳለበት ይዘነጋና ድምዳሜውን ትውስታችንን በሚያጣብቡ ክስተቶች ይመሠርታል።

አንዳንድ ነገሮች ከሌሎች ይልቅ ለትውስታችን የሚቀርቡበት ምክንያት ብዙ ነው። የቅርብ ጊዜ ክስተቶች ከሩቅ ነገሮች ይልቅ ይታወሳሉ፤ በቅደም ተከተላዊ ክስቶች መካከል ከሆነው ይልቅ የመጀመሪያውና የመጨረሻው የመታወስ እድላቸው ከፍተኛ ነው። ስሜቶቻችንን የነኩ ነገሮች አንዳች ነገር ካልጫሩብን ክስተቶች በበለጠ ይታወሳሉ። ሚዲያ አንሥቶ ያራገባቸው ያልተለመዱ ክስተቶቹ በየዕለት ተዕለቱ ከሚደረጉት ተደጋጋሚ ክስተቶች ይልቅ ለትውስታዎቻችን ቅርብ ናቸው። ይህ ማለት ግን ለውሳኔ የሩቅ ክስተቶች፣ በመካከል የሆኑ ጉዳዮች፣ ስሜታችን ያልተኮረከረባቸው ጊዜያት እና ዕለታዊ ክስተቶች፣ ለሚዛናዊ ፍርድ የማይጠቅሙ ግብአቶች ናቸው ማለት አይደለም። አቋራጭ መንገድ ግን እነዚህን አውነታዎች አይገነዘብም።


የተጋመድናቸው መነሾዎች

ሦስተኛው፣ የተጋመድናቸው መነሾዎች (anchors) ተጽእኖ በትንተናችን ላይ አሉታዊ ሚና ሲኖረው የሚከሰት ነው። ማናችንም ነገር መመርመር ስንጀመር፣ አእምሮዋችን ያለ ቅድመ እሳቤ አይጀምርም። ሁላችንም፣ ስንጀምር ከሆነ ቦታ መነሣታችን እና ጅማሮዎቻችን ከአዳዲስ መረጃዎች ይልቅ ማመናችን ተፈጥሮዋዊ ነው። ይህንን የተገነዘቡ ሰዎች መጀመሪያ ቀን የሚጫረው እሳቤ (first impression) በቀጣይ ቀናት የሚኖረንን ግንዛቤ እንደሚወስን በማወቅ፣ በመጀመሪያው ቀን ልባችንን ሊገዙት ይጥራሉ። ቅድመ እስቤያችን ላይ ለመድረስ የተጠቀምንባቸው የማጣቀሻ መነሾዎች፣ ሳናውቃቸው እንጋመዳቸውና ራሳችንን በረጅም ርቀት ማስተካከል ስንቸገር እንገኛለን። የመጀመሪያ መነሿችን የነገር ሁሉ መደምደሚያ ነው ብለን ካሰብን በአመክንዮዋችን መሳት አይቀርልንም፤ በአዳዲስ መረጃ ቀደምት አሳቦቻችን ለማስተካከል ያለንን ዝግጁነት እጅጉን ይቀንሱታል። መነሾዎቻችን፣ አቅጣጫ ካሳቱን፣ ድምዳሜያችን በአዲስ መረጃዎች የመስተካከሉ እድሉ ያንኑ ያህል አናሳ ይሆናል። ተስተካከልን ያልን ጊዜ እንኳ ማስተካከያዎቻቸን ከፊል (partial) መሆናቸው አይቀርም። የአቋራጭ መንገዶችን አደጋን በመገንዘብ አመክንዮቻችን እንታደግ።

ቸር እንሰንብት!

Share this article:

“የውጭ ወራሪና የውስጥ ቦርቧሪ ያልናቸውን ትምህርቶች መግረዝ ይችላሉ ባይ ነኝ”

ተስፋዬ ሮበሌ ለትምህርት ከኢትዮጵያ እስኪወጣ ድረስ የተስፋ ዐቃቢያነ ክርስትና ማኅበርን በዳይሬክተርነት አገልግሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በዕቅበተ እምነት ርእሰ ጒዳዮች ላይ የተለያዩ መጻሕፍትንም ጽፏል፡፡ ከእነዚህም መካከል “የይሖዋ ምስክሮችና አስተምህሮአቸው በእግዚአብሔር ቃል ሲመዘን”፣ “ውሃና ስሙ፡- ʻየሐዋርያት ቤተ ክርስቲያንʼ የድነት ትምህርት በቃለ እግዚአብሔር ሲመዘን”፣ “ዐበይት መናፍቃን” እንዲሁም “የዳቬንቺ ኮድ፡- ድርሳነ ጠቢብ ወይስ ድርሳነ ባልቴት?” ይጠቀሳሉ፡፡ ተካልኝ ዱጉማ በዕቅበተ እምነት ጕዳዮች ዙሪያ ከተስፋዬ ሮበሌ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

የጳውሎስ መልእክት ወደ ቲቶ ጤናማ ትምህርት – ጤናማ ኑሮ (ክፍል 2)

በአንድ ወቅት ከአንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ጋር በታክሲ እየተጓዝን፣ ከቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች መካከል አንዱን አገኘን፡፡ ይህም ሰው ሞቅ ያለ ሰላምታ ከሰጠኝ በኋላ አብሮኝ የነበረውን አገልጋይ ስሙን በመናገር ለመተዋወቅ ሞከረ፡፡ በዚህ ጊዜ ግራ የተጋባው ወዳጄ ስሙን በመጥቀስ “እከሌ እኮ ነኝ” በማለት ሊያስታውሰው ሞከረ፡፡ የሚያሳዝነው ግን የቤተ ክርስቲያን መሪው ሊያስታውሰው አልቻለም፤ በድፍረትም እንደማያውቀው ተናገረ፡፡ እኔም በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አብረው እያገለገሉ ያሉ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌንና በብዛት የእሑድ አምልኮ ፕሮግራም ይመራ የነበረውን ወንድም ለማስተዋወቅ ተገደድሁ፡፡ ይህ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ የተደራረበ ሥራ ያለው ከመሆኑ የተነሣ ከቅዱሳን ጋር ኅብረት ለማድረግ ወደ እሑድ አምልኮ ፕሮግራም ከሚመጣበት የማይመጣበት ጊዜ ይበዛ ነበር፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.