[the_ad_group id=”107″]

“ማዝመር” እና “መዘመር”

በርእሱ ላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ቃላት “ማዝመር እና መዘመር” ወይም “አዝማሪነት እና ዘማሪነት” በዓለማዊ (Secular) በተሰኘው እና መንፈሳዊ በምንለው ክልል የዜማ እና የቅኔ ኪነ ጥበብ መገለጫ ስለ መሆናቸው፣ እንደውም በጋራ ተጨፈልቀው የተሠሩና ያለ ምንም ልዩነት አደባባይ የዋሉ ያህል ሲነገሩ ማድመጥ የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን የዜማና የቅኔ ጥበብ በተለይም የዝማሬው ኪነ ጥበብ የአንድ ዘመን የሰዎች የፈጠራ ግኝት ወይም በ“እከሌ ፍልስፍና” የተገኘ አለመሆኑን ከመንፈሳዊው ዓለም ታሪካዊ አስተምህሮ ተገቢ ትምህርት መቅሰም ይቻላል፡፡

ይህ መለኮት ነኩ የቅኔ እና የዜማ ጥበብ ግዑዙ ዓለም እንኳ ከመፈጠሩ በፊት እንደ ነበር ዋናው ማጣቀሻችንና ላቅ ያለው መረጃው መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ መንፈሳዊውን ኪነ ጥበብ በርዝመቱ ቢሆን በወርዱ፣ በስፋትና በጥልቀቱ፣ በምንም መልኩ ለልኬት ቀለል አድርጎ ማሰብ የማይቻል ነው፡፡

የረዥም ዘመን ዕድሜ ያለውና ለእግዚአብሔር ብቻ የነበረውንና የሆነውን ይህ የቅኔና የዜማ ኪነ ጥበብ እንዴት ነበር የቀጠለው? ኪነ ጥበቡ የውድቀት ፈር ቀዳጅ በሆነው በ“ሎሲፈር” በመርከሱ ሰበብ እስከ ዛሬም በዙሪያው ከፍተኛ ተግዳሮትና መወናበድ መኖሩ ግልጽ ነው፡፡ የጥበቡ ባላንጣ ዛሬም ድረስ ኪነ ጥበቡን በማያቋርጥና በማይገመት አሠራር፣ ልዩ ልዩ ዘዴና ዘይቤ እየተጠቀመ ይፈታተነዋል፡፡

ይህንኑ ጥበብ ዋነኛ መሣሪያው በማድረግ ማንኛውንም ክፉ ውጥኑን በሰዎች ሕይወት ላይ ለመፈጸም እየተጠቀመበትና እየተሳካለትም መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በሁለቱ ዓለማት መካከል (ዓለማዊው እና መንፈሳዊው) ጥበቡን “የእኔ፣ የእኔ” የሚል ከፍተኛ ትግል አለ፡፡ ከዚህ በመነሣት አንደኛው ወገን ይህን ጥበብ ለአጥፊው ዐላማ እንደ መሣሪያ ለሆነው “ለማዝመር” ወይም ለአዝማሪነቱ ሙያ ይጠቀምበታል፡፡

በተቃራኒው በመንፈሳዊው ክልል ያሉት ደግሞ “ነጋ ጠባ” ሳይሉ ለአምላክ ክብር ለመዘመር እያዋሉት መሆኑ እሙን ነው፡፡ እርግጥ የሳተ ሲያጋጥም፣ “ዘማሪ ሲስት አዝማሪ ይሆናል” ይሉትን ቢኂል ልብ ይሏል፡፡ ግለ ሰቡ ኪነ ጥበቡን አረከሰ ለማለት ነው፡፡

አሁን ላይ ስናስተውል ቤተ ክርስቲያን ይህ ጥበብ የገጠመውን አደጋ ልብ ያለች አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ቀደም ብለን እንዳነሣነው ኪነ ጥበቡ በሁለቱም ተጠቃሚዎች መካከል የአጠቃቀም ልዩነት ያልታየበት መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ለመረዳት መንፈሳዊውን አጉልቶ ማሳያ መነፅር ማጥለቅ የግድ ሳይል አይቀርም፡፡

የኪነ ጥበቡ አንዳንድ ባሕርያት ማለትም፣ ዜማዊ ቅኝቱ እና እንቅስቃሴው ዘይቤያዊ ተመሳስሎት አለው፡፡ ይህን ያህል የሚቀራረቡባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውና መመሳሰላቸው፣ አልያም መንትያ ተመስለው እስካይለዩ መደባለቃቸው ሰበብ ሆኗል፡፡ ይህ ደግሞ ስለ ኪነ ጥበቡ የተስተካከለ ግንዛቤ እንዳይኖር በሁሉ ዘንድ ሁሌም ውዥንብር እንደ ፈጠረ አለ፡፡

ነገር ግን ቆመንም ሆነ ተቀምጠን የነገሩን ልዩነት ለመረዳትና የተቀደሰውን የኪነ ጥበብ አጠቃቀም ለመከተል፣ ከሳተበትም ለመመለስ “የቁርጠኝነት ያለህ!” የሚል ጥሪ ደጃችንን እያንኳኳው ነው፡፡ ጥበቡን ለመቀደስ ብንወድ ልብ ማለት ያለብን ማዝመርንና መዘመርን በየራሳቸው መለየት ነው፡፡ “ማዝመር” ኪሩብ የነበረውና “የወደቀው ዘማሪ” ወይም ሰይጣን የመዝሙርን ጥበብ ለመተካት ከነበረው ዐሳች ዐላማ በማደናገሪያ ዘዴነት እየተጠቀመበት ያለው አደገኛና ገዳይ መርዙ ነው፡፡ ይህም እርሱ ራሱ የፈበረከውና ያረከሰው የጥበብ ሥራው ዘርፍ ሲሆን፣ ዜማውን፣ ቅኔውንና መሣሪያውን ታግዞ ሰዎችን ወደሚፈልገውና ወደሚፈልጉት ለመንዳት፣ ለእርኩሰት የሚቀሰቅስበትና ወደ ራሱ አጥፊ ግብ የሚያጐርፍበት የተበከለ ጥበባዊ ጐርፉ ነው፡፡

ያኔ ከጥንት ጀምሮ የውድቀት አውራ የሆነው ኪሩብ ድንቁን የዜማ ኪነ ጥበብ በማን አለብኝነት ወይም በትዕቢት እንዳረከሰው ብዙዎች ሲያስገነዝቡ ዛሬ ላይ መድረሳችንን ያስተውሏል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይህን በቅኔና በዜማ የታገዘ ጥበብ ከግንዛቤና ከተሳሳተ አጠቃቀም የተነሣ የቤተ ክርስቲያን ሰዎችም ጭምር ለጊዜያዊውና ለፍላጐታዊ ስሜታችን ማነሣሻነት፣ ላላስፈላጊ ቡረቃ እንዲጋብዝ ብቻ መፈለጉ አሳሳቢ ነው፡፡ ሰይጣን በጥበቡ ተሸፍኖ እኛንም እንኳ ሁለንተናን እንደ ልብ ፈትቶ በዓለም ያለውን “ዓለምዬ ሶራ” የተሰኘ ዐይነት ድለቃ የቤተ ክርስቲያንን ሰዎች ማስጠናት የጀመረ ሲሆን፣ ይህን በኮንፍራንስ ቦታዎቻችንና በሠርግ ድግሦቻችን “ዝማሬ” ያልነውን የዜማ ሥራ ማየት ይበቃል፡፡ ተረቱስ፣ “የዘፈን ዳር ዳሩ እስክስታ ነው” አይደል!?

ዝማሬ በቤተ ክርስቲያን መድረኮችና ከመድረኮችም በታች በየትኛውም ሥፍራ ዓውዱን እየጠበቀ የሚከወን ተግባር ነው፡፡ የእግዚአብሔር መልእክት የሆነው ወንጌል ለሰዎች ሁሉ መዳን ከሚገለጥባቸው መንገዶች አንዱ ይህ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ነው፡፡ ዝማሬ የእግዚአብሔርን ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ማስተዋወቂያ ብቻም ሳይሆን፣ ዳግመኛ መገለጡን ማብሰሪያ ጥበብ ጭምር ነው፡፡ መዝሙር የሰዎችን ነፍስ በእምነትና በእውነት በማጠንከር መንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸውን ለጽድቅ ቁርጠኝነት፣ ለክፋት ጠበኝነትን በማላመድ ማትጋት የጥበቡ የማይለወጥ እና የማይናወጥ ዐላማና ባሕርይ ነው፡፡

መዝሙርን ከማዝመር የሚለየው ጤናማው ባሕርዩ እንጂ ቅኔውና ቃላቶቹ አለመሆናቸውን ማወቅ ትልቅ ኀላፊነት ነው፡፡ መዝሙር ዛሬ ዛሬ በአንዳንድ ቦታና ሁኔታ ለእግዚአብሔር ደስታንና ክብርን ከማቅረቡ ይልቅ፣ ደስታና ቡረቃውን ለማላመድ ሆን ተብሎ ለሕዝብ የሚቀርብ፣ ክብሩን ለዘማሪው የማድረጊያ መንገድ ሆኗል፡፡

መዝሙርን ከማዝመር የሚለየው ጤናማው ባሕርዩ እንጂ ቅኔውና ቃላቶቹ አለመሆናቸውን ማወቅ ትልቅ ኀላፊነት ነው፡፡

ይህ ደግሞ የሁሉ ሳይባል የበርካቶቹ የዘርፉ አገልጋዮች ከፍተኛ ስሕተት ሆኗል፡፡ የመንፈሳዊ ዝማሬ ልዩነት የመልእክት፣ የዐላማ ብሩክነት እና ዋና መንፈሱ ወንጌል ላይ ማተኮር መቻሉ እንደ ሆነ ይሠመርበት፡፡

የመዝሙር ጥበብ በዜማና በቅኔ፣ በግጥምም ተዋዝቶ የሰዎችን የሕይወት እንቆቅልሽ ለመፍታት፣ የሰውን መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ግምት ውስጥ በማስገባት በዜማ ሊያስተጋባ የሚችል ጥበብ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ሁሉን ተደራሽ በሚያደርጉ በድምፅ ዜማ የታገዙ መልእክቶችን አንግቦ አላዋቂውን ሁሉ ሊያስተምር፣ አጥፊውን ሊገስጽ፣ በክፉ የታሰረውን ነጻ ሊያወጣ፣ ሐዘንተኛውን ሊያጽናና፣ ተፍገምጋሚውን ሊያቆምና ሊያጸና፣ ሊያንጽም አቅም ያለው ነው፡፡

የመዝሙር ጥበብ ጥንካሬ፣ ግለትና ሙቀቱ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሻጋሪነቱ፣ ውበትና ማራኪነቱ፣ አስተማሪነቱ፣ አራሚነቱ ከክፋት ነጣቂነቱ፣ አራቂነቱ በዋናነት የሕይወት ጥራት ዘይቤው፣ የማንነት እውነታው ጭብጥነት፣ የሥነ ምግባር ልዕቀት ምሳሌነቱ ነው፡፡  

ከመዝሙረኛው ዳዊት ቤት የተገኙ፣ ከአሳፍ ቤት የወጡ፣ ከሌዊ ወይም ከቆሬ ቤት የተቀዱ፣ በአጠቃላይ ከእሥራኤል ቤት የተንቆረቆሩ ዝማሬዎች ምስክሮች ናቸው፡፡ የዘርፉ ሰዎች ጥበቡን ስለ ማወቃቸው፣ ለጥበቡ ሥራ ተገቢውን ክብር ለማጐናጸፍ ስለ ነበራቸው ከፍተኛ ጥረት፣ በመልእክቶቻቸው መታየቱ ለአንባቢያን ግለጽ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ስለ ፍጹምነታቸው ለመስበክ ሳይሆን፣ በሕይወትም፣ በማንነትም፣ በሥነ ምግባርም ያረጋገጡት እውነት በመሆኑ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ለዚህ ዘመን የዘርፉ አገልጋዮች ለማሳያነት የእነዚያን መልእክቶች በመረጃነት ከመጽሐፍ ቅዱስ ለማጣቀስ ይቻላል፡፡

በተለይ ዛሬ ላይ ብዙዎቻችን ስለ ዘማሪው ዳዊት “… ዳዊት እርቃኑን ዘለለ፤ ጨፈረ…”  የሚለውን ነቁጣ የምታክል ዐሳብ፣ ለያውም በስሕተተኛው አተረጓጎም እናስተጋባልን፡፡ ዳሩ ግን ዳዊት ምን ያህል ጊዜያት በአምላኩ ፊት በመንፈሳዊ ማኅሌትና ቅኔ፣ የትንቢታዊ፣ የውዳሴ፣ የንስሐ፣ የምልጃ፣ የልመና እና የምስጋና ይዘት ያዘለውን ዝማሬ እያዜመ እንደ ከረመ እንዘነጋለን፡፡

ንጉሡ በትሕትና በመቅደስ ይወድቅና ይነሣ፣ እራሱምን ይጥልና ይጎነብስ እንደ ነበር ለማወቅ ስንቶቻችን እንደ ፈቀድን ጌታ ይወቅ!? በርካቶቻችን በርካቶቹን የዳዊትን የሕይወት ልምምዶችና የአገልግሎት ተሞክሮዎች ያወቅንም የተከተልንም ስለ መሆኑ በርግጠኝነት መናገር እንዴት ከባድ ነው!?

እሰቲ ፈቃዳችን ቢሆን ለዳዊት ዝላዩን ባስከተለለት ዐላማና ሕይወት ላይ እናተኩር፡፡ ዳዊት እኮ እንደ እኛ እራሱ ባስጨበጨበው ጭብጨባ ሊሞቀው ይቅርና፣ “እልፍ ገደለ” ተብሎ በተጨበጨበለትም ጊዜ ራሱን ይደብቅ የነበረ ሰው ነው፡፡

ለአገልግሎቱ ክብር ሲባል ስለ ሕይወት ጥራት፣ ስለ መስቀሉ፣ ሲያልፍ ደግሞ በርካታ ሥነ መለኮታዊ ቁም ነገሮችን አንሥቶ መዘመር በሚጠበቅበት በዚህ ጊዜ አገልጋዩ ከዚህ ርቋል፡፡ ከዚህ ይልቅ ለሰዎች ስሜት ብቻ የሚመጥን ዝማሬ መሰል በሆነ የዜማ ጩኸት ጊዜን በማባከን መክረማችን አሳፋሪ ሳይሆን አይቀርም፡፡

ዘማሪው እንደ መልእክተኛ በብዙ ስደትና እንግልት፣ መከራና ስቃይ እጦትና መራቆት ውስጥም ሆኖ እንኳ በመንፈሱ ሳይከስምና ሳይጠወልግ ጸንቶ ሊያገለግል መለኮታዊ ጥሪ አለበት፡፡ በቅድስና፣ በጸሎት ትጋትና በቃሉ መረዳት በአገልግሎት አተገባበር ጽናት እንዲቆምና በጉልሕ መንፈሳዊ የሕይወት ልምምዶች እንዲሁም የአገልግሎት መርሖዎች ሥር ተገዢ ሆኖ መመላለስ የግድ ይላል፡፡

ያለ በቂ የሕይወት ጥራት የሚገኙም ሆኑ ለሕዝብ የሚቀርቡ መንፈሳዊ ዜማዎች ወይም ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች፣ ዘማሪ የተቀበላቸው መልእክቶች ሳይሆኑ፣ አዝማሪ የሠራቸው ስንኩል ሥራዎች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡

በዝማሬው አገልግሎት ውስጥ የግለ ሰቡ ባሕርይ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጠው አውራ ጉዳይ ነው፡፡ ዜማዊ አገልግሎቱ የሚጠይቃቸው የማንነት መገለጫ የሆኑ ባሕርያት በርከት ያሉ ናቸው (በርግጥ እነዚህ ባሕርያት ለዘማሪው ብቻ የተተዉ ናቸው ለማለት አይደለም)፡፡ ከእነዚህም መካከል ትእግሥት፣ ትሕትና፣ በጎነትና ርኅራኄ፣ ሐቀኝነት (Integrity)፣ ወዘተ. የመሳሰሉት ወሳኞቹ ናቸው፡፡ በተለይም ሰይጣን ጥበቡን ያበላሸውና ያረከሰው በትዕቢት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬም የብዙ አገልጋዮችን ሕይወት ቁልቁል የሚናዳበት የኀጢአት መሣሪያው መሆኑን ልብ ማለት ተገቢ ይመስለናል፡፡

ያለ በቂ  የሕይወት ጥራት የሚገኙም ሆኑ ለሕዝብ የሚቀርቡ መንፈሳዊ ዜማዎች ወይም ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች፣ ዘማሪ የተቀበላቸው መልእክቶች ሳይሆኑ፣ አዝማሪ የሠራቸው ስንኩል ሥራዎች መሆናቸውን መዘንጋ ትየለብንም፡፡

ዘማሪ ደግሞ ትኁት በመሆን የኪነ ጥበቡን ንፅሕና እና ቅድስና የመጠበቅ አላፊነት አለበት፡፡ ታላቁ የቤተ ክርስቲያን አባት ቅዱስ አውግስጢኖስ፣ “ተዓብዮ ትልቅ መኾን አይደለም፤ የማንነት ያለ አገበብ ማበጥ እንጂ፡፡ ዕብጠት ሲያዩት ትልቅ የሚመስልበት ጊዜ ባይጠፋም እውነቱ ግን በሽታ መኾኑ ነው፡፡” ብሎ ነበር፡፡

መቼም ተተናኳይ እና ተናቋሪ፣ ʻአትንኩኝ፤ ከነኩኝ…ʼ የተሰኘ አስጊና አስፈሪ ማንነት ተጐናጽፎ መዘመር ተወዳጁን ኪነ ጥበብ ማሳነስ ብቻ ሳይሆን፣ መሥዋዕቱን ማርከስና ከመሠዊያው በታች አፈሩ ላይ አንከባሎና አቆሽሾ እንደ ማቅረብ ነው፡፡ ስለሆነም ማንነታችንን የመረዳት አቅም ካለን የምር እያዘመርን ወይም እየዘመርን ለመሆናችን ኅሊናችን ብቻውን የሚዳኘው ይሆናል፡፡

በየዘመናቱ የሥነ ምግባር ክፍተት ይኖር እንደ ነበር የታሪክ መስታይት ፍንተው አድርጎ ያሳየናል፡፡ ዛሬም ቢሆን በኪነ ጥበቡ ዕድገት ሰበብ መሥመር የሳቱና

ያሳቱ ነገሮች በመኖራቸው፣ በተለይም በዜማውና በቅኔ ጥበቡ ዙሪያ “የሥነ ምግባር ያለ!” በሚል የሚስተጋባው ኀይለኛ የቁጭት ጩኸት አድማጭ ያጣ ይመስላል፡፡

የመዝሙር አገልግሎት፣ ሥነ ምግባር በተለየውና ገንዘብ መሰብሰቢያ እንዲሁም እውቅናና ክብር ማግኛ ማድረግ ወይም መጠቀም ያለ ጥርጥር በጥበቡ ላይ ሉሲፈር የፈጸመውን ጥበቡን የማርከስና የማንኳሰስ ስሕተት ወይም ጥፋት እንደ መድገም፣ አልያም የጥፋቱ ተባባሪ እንደ መሆን ይቆጠራል፡፡

“ዘማሪ” በሕይወት ጨለምተኝነት ሰበብ፣ በማንነት መሸርሸር ዳፉ፣ በሥነ ምግባር ጉድለት ሥር ሆኖ የጥበብ ሥራውን ከማርከስና ከማሰደብ መመለስ ይገባዋል፡፡ ኪነ ጥበቡ ለምን ዐላማ እንደ ተፈጠረና በእንዴት ባለ ጽድቃዊ አካሄድ እንደሚከወን ሊጠፋውም አይገባም፡፡ የተጠራንለት ጥበብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ልክ በሌለው ስድ አካሄድ እየተተገበረ መሆኑንና አለመሆኑን መፈተሸ አለብን፡፡ በጥበቡ ዙሪያ የተሰባሰቡ ሁሉ የጥበቡን ባለቤት ባለ መፍራት እንዳይበድሉ – ዐደራ!

እውነተኛ አገልጋይ ማነው?

የምንኖረው እጅግ በዘመነ ትውልድ ውስጥ ነው። በዘመኑ ውስጥ በዓይናችን የምናያቸውና በልቡናችን የምናስተውላቸው በርካታ ነገሮች አሉ። በተለይም በብዙ አቅጣጫ ውሸተኞች ሆነው ሳሉ ነገር ግን እውነተኛውን መስለው የሚገለጡ ነገሮችን እናስተውላለን።

ተጨማሪ ያንብቡ

ሚሲዮናዊ ተልእኮ ባ’ገር ልጅ

በወንጌላውያን የሚሲዮን ታሪክ ፋና ወጊ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው በዐፄ ፋሲል ዘመነ መንግሥት (1625 – 1660 ዓ.ም.) እንደ መጣ የሚታመነው ጀርመናዊው ፒተር ሄይሊንግ ነው። ፒተር በኢትዮጵያ ቆይቶ በ1644 አካባቢ ወደ አገሩ ለመመለስ በመንገድ ሳለ፣ ቱርኮች አግኝተው እስልምናን እንዲቀበል ቢያስገድዱትም አሻፈረኝ በማለት አንገቱን ቀልተው ገደሉት። ይህ ሚሲዮናዊ በኢትዮጵያ ሳለ የአማርኛ ቋንቋን አቀላጥፎ መናገር ችሎ የነበረ ሲሆን፣ የዮሐንስ ወንጌልን ወደ አማርኛ በመመለስ ለሕዝቡ እንዳበረከተ ታሪክ ዘግቦታል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.