[the_ad_group id=”107″]

ማኅበራዊ ፍትሕ

የክርስትና ሌላኛው ገጽታ

“ሰው ሆይ፤ መልካም የሆነውን አሳይቶሃል፤ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትን ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?” (ሚክያስ 6፥8)

በኢትዮጵያ ውስጥ የወንጌላውያን ክርስትና ማኅበራዊ ፍትሕን በተመለከተ ጉልሕ ውይይት ወይም ጥረት ሲደረግ አይስተዋልም። ይህ ማለት ግን ፍትሕን እና ሰላምን በተመለከተ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ቤተ እምነቶች የሉም ማለት አይደለም። የዘመናችን ክርስትና በብልጥግና ወንጌል እና በእምነት እንቅስቃሴ ተጽእኖ ሥር የወደቀ ይመስላል። ትኩረቱ ሁሉ ምድራዊ እና በራስ ላይ ብቻ ያነጠነጠነ እየሆነ ነው። ከዚህ በተቃራኒው ያሉት ደግሞ ይህን ዓለም ቸል ብለው ሌላኛውን ዓለም ብቻ የሚሰብኩ ናቸው። እነዚህ ሁለት ጽንፎች ለማኅበረ ሰብ ለውጥ ግድ የማይላቸው ምእመናንን እየፈጠሩ ይገኛሉ። ከዚህም የተነሣ ቤተ ክርስቲያን በማኅበረ ሰብ ላይ ልታመጣ የምትችለውን አዎንታዊ ተጽእኖ እንዳታመጣ እያደረጋት ነው። በተቃራኒው የቤተ ክርስቲያንን ምስል እያበላሸ ነው። ይህ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን በማኅበረ ሰቡ ውስጥ የሚኖራትን ፋይዳ እና ተቀባይነት ያኮስሰዋል። ቤተ ክርስቲያን ከዚህ በዘለለ መልኩ በምትኖርበት ማኅበረ ሰብ ውስጥ አዎንታዊ የሆኑ ተጽኖዎችን መፍጠር አለባት። ከእነዚህ ተጽእኖዎች መካከል አንዱ ማኅበራዊ ፍትሕን የሚመለከት ነው።

የዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ በአንድ የካቶሊክ ገዳም ውስጥ የዳቦ ማሸጊያ ላይ ያነበብኩት ጽሑፍ ነው፤ “May those with hunger have bread and may we with bread have a hunger for justice.” (የተራቡት ዳቦን ያግኙ እኛም የጠገብን ፍትሕን እንራብ።) ይህ ትልቅ መልእክት ያለው ጸሎት/አባባል ነው። የክርስቲያኖች ትልቁ ዓላማ ተደላድሎ በምቾት መኖር ሳይሆን ለሌሎች መኖርና ማሰብን የሚጠይቅ መሆኑን ከማመላከቱ በተጨማሪ፣ ክርስቲያኖችን ወደ ተግባራዊ ሕይወት የሚጋብዝ ነው።


ማኅበራዊ ፍትሕ ምንድን ነው?

ማኅበራዊ ፍትሕ የሚለው ቃል ፖለቲካዊ አንድምታ ስላለው በአንዳንድ ወግ አጥባቂ ወንጌላውያን ዘንድ ተወዳጅ አይደለም። ሆኖም ግን መጽሐፍ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ከድኾች፣ ከመበለቶችና አቅም አልባ ከሆኑት ጋር እንድትወግን ያስተምራል (ኤር. 7፥5-3)። ይህ የማኅበራዊ ፍትሕ አንድ አካል ነው። አንዱ የክርስቲያን ኀላፊነታችን ርኅራኄያችንን እና ፍቅራችንን ተግባራዊ በሆነ መንገድ ለሰዎች ሁሉ መግለጽ ነው። ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ እና የተጠና ማኅበራዊ ተሳትፎን ይጠይቃል።

“ማኅበራዊ ፍትሕ” የሚለውን ቃል የፍልስፍና እና የፖለቲካ ተማሪዎች በተለያየ መልኩ ሊፈቱት ይችላሉ። ማኅበራዊ ፍትሕ ማኅበራዊ ችግሮችን መረዳት፣ የችግሮችን መነሾ መገንዘብ እና መፍትሔን መሰንዘርን ያካታል። ማኅበራዊ ፍትሕ ተጓደለ የሚባለው ሰዎች ከማኅበረ ሰባቸው ሊያገኙት የሚችሉትን ነገር ማግኘት ሳይችሉ ሲቀሩ ነው። ማኅበራዊ ፍትሕ የሚተገበረው ግለ ሰቦች ወይም ቡድኖች ባሉበት ማኅበረ ሰብ ውስጥ እኩል በሆነ መልኩ መጠቀም ሲችሉ ነው። በተቃራኒው ደግሞ ኢ-ፍትሃዊነት ኀይልን በአግባብ አለመጠቀምን፣ የተወሰኑ የማኅበረ ሰብ ክፍሎችን ዝቅ አድረጎ መመልከትን ወይም ከተጠቃሚነት ማጉደልን ያካታል።

ማኅበራዊ ፍትሕ የሰውን ሁለንተናዊ የሕይወት ገጽታ የሚመለከት ሲሆን፣ ይህም ማኅበራዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንዲሁም ምግባራዊ ተግባርን የሚያቅፍ ነው።


መጽሐፍ ቅዱሳዊ እና ነገረ መለኮታዊ መሠረት

የማኅበራዊ ፍትሕ አስተምህሮ መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ ነው። እግዚአብሔር በባሕርይው ጻድቅና የፍትሕ አምላክ ነው (ዘዳ. 10፥17-18፤ መዝ. 89፥14፤ ኤር. 9፥23-24)። ይህ እግዚአብሔር ራሱን ሥሉስ አደርጎ መግለጹ በባሕርዩ ኅብረትን ፈላጊ (communal and social) ያደርገዋል። እኛም ይህን ባሕርይ እንጋራለን። ለዚህም ነው ባልንጀራችንን መውደድ ያለብን። ከማኅበረ ሰቡ ራሳችንን ገንጥለን መመልከት አንችልም። በመሠረቱ ማኅበራዊ ፍትሕ ከዕብራውያን ነቢያት የመነጨ ነው። እግዚአብሔር ለድኾችና ለተገፉት የተለየ ፍቅር አለው። ይህ አስተምህሮ በኢየሱስ ትምህርት ላይ የበለጠ ተጠናክሮ ቀርቧል (ሉቃ. 4፥18-19)። ኢየሱስ ከዝቅተኞች ጋር ራሱን አወዳጅቷል።

መጽሐፍ ቅዱስ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል በመፈጠሩ ክቡር እንደ ሆነ ያስተምረናል (ዘፍ. 1፥27)። ይህ የሰው ክብር ደግሞ ከእግዚአብሔር የሚመነጭ እንጂ ሰዎች በብቃታቸው ወይም በሥራቸው የሚያገኙት አይደለም። ይህ ከእግዚአብሔር የተቸረን ክብር ነው እንግዲህ ለማኅበራዊ ተሳትፎ መሠረት የሚሆነን። ወንዶችና ሴቶች በእግዚአብሔር አምሳል ነው የተፈጠሩት። ኀጢአት ሰዎች እርስ በርሳቸው እና ከተፈጥሮ ጋር ያላቸውን የሠመረ መስተጋብር አበላሽቶታል። ከዚህም የተነሣ በምንኖርበት ዓለም ኢ-ፍትሓዎ የሆኑ ነገሮች በስፋት ይሰተዋላሉ።

እምነታችን የሰውን ሁሉ ክቡርነት እንድንቀበል፣ ለሰብአዊ መብት እንድንቆም፣ ለሰላም እና ለጋራ ጥቅም እንድንሠራ ይጠይቀናል። ማኅበራዊ ኢ-ፍትሓዊነት የኀጢአት ውጤት ከመሆኑ የተነሣ እኩይ ከኢ-ፍትሓዊነት ጋር እንዲገናኝ ምክንያት ይሆናል። ለዚህም ነው አንዳንድ ጊዜ እኩይ ተቋማዊ ገጽታ (institutional-structural) የሚኖረው። እግዚአብሔር እኩይን ይጠላል፤ ወደፊትም ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ያስወግደዋል። እንግዲህ ይህ ሥነ ፍጻሜአዊ ተስፋ ነው ክርስቲያኖች ሠናይን እንዲሹ የሚያበረታታቸው። ይህ እስኪሆን ግን እኩይ ራሱን በተለያየ መልኩ መግለጹን ይቀጥላል።


ጭብጦች

ቤተ ክርስቲያን በማኅበረ ሰብ ውስጥ የሚኖራት ተሳትፎ ማኅበራዊ ተግባርን ያካትታል። በዚህም ተሳትፎ የማኅበረ ሰቡን ችግሮች ለመቅረፍ ከሌሎች ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው ተቋማት ጋር በመሆን የበኩሏን አስተዋጽኦ ታደርጋለች። በዚህ ሂደት ውስጥ የተለመዱ ጥያቄዎችን መጠየቅ ተገቢ ነው፡- “ሥራ አጦች ለምን ብዙ በዙ?”፣ “የሥነ ምኅዳር ችግር በአካባቢ ሙቀት ላይ ምን ዐይነት ችግር እያስከተለ ነው?”፣ “ጾታዊ ጥቃት በቤተ ክርስቲያን እና በምንኖርበት ማኅበረ ሰብ እያስከተለ ያለው ችግር ምድን ነው?”፣ ወዘተ. እነዚህ እና ሌሎች ያልተዘረዘሩ ማኅበረ ሰባዊ ችግሮች የቤተ ክርስቲያንን ተሳትፎ የሚጠይቁ ናቸው።

በማኅበራዊ ፍትሕ ረገድ ጉልሕ ተሳትፎ ያላት ቤተ ክርስቲያን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲን ነች። ከዚህ በመቀጠል ቤተ ክርስቲያኒቱ ትኩረት የምትሰጥባቸውን የተወሰኑትን ርእሰ ጉዳዮች ጠቅሰን እናልፋለን። ወደፊት ከእነዚህ ርእሰ ጉዳዮች መካከል ተወሰኑትን ሰፋ ባለ መልኩ እንመለከታቸዋለን። እነዚህ ርእሰ ጉዳዮች ከማኅበራዊ ፍትሕ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውና ማኅበራ ፍትሕ እንዲሰፍን ቤተ ክርስቲያን ልትይዛቸው የሚገቡ ዕሴቶችና ልትጫወተው የሚገባትንም ሚና የሚያመላክቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ነጥቦች ናቸው።

  1. የሰው ልጅ ክቡርነት፤ ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር አምሳል ከመፈጠራቸው የተነሣ ክቡር ናቸው። ለዚህ ነው በጾታ፣ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በሀብት፣ ወዘተ. የሚደረጉ አድሎዎች ተቀባይነት ሊኖራቸው የማይገባው። የሰው ሕይወት ክቡርነት የትኛውም ማኅበረ ሰብ ለሚኖረው ምግባሪዊ ዕይታ (moral vision) መነሻ ነው። የሰው ሕይወትን ክቡርነት የሚፈታተኑ ብዙ ነገሮች በምንኖርበት ዓለም እየተከሰቱ ነው። ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን ልትሠራባቸው ከምትችልባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የሰውን ክቡርነት ማስተማር ነው።
  2. ወንድማማችነት (Solidarity)፤ ሁላችንም አንድ ቤተ ሰብ ነን። በየትኛውም ጊዜ እና በየትኛውም ሥፍራ ብንኖር የወንድሞቻችን እና የእኅቶቻችን ጠባቂዎች ነን። ባልንጀራችንን መውደድ ዓለም አቀፋዊ ገጽታ አለው፤ በዚህም መልኩ ሊገለጽ ይገባዋል። ሙሉ የሆነ የሰው ልጅ ዕድገት የግል፣ ማኅበራ፣ ኢኮኖሚዊ እና ፖለቲካዊ መብቶችን ማስፋፋትን ያካታል። ለዚህ ነው ቤተ ክርስቲያን በየትኛውም የማኅበረ ሰብ ክፍል ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ማኅበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ መሥራት ያለባት። ‘እኛን አይመለከተንም’ የምንለው የትኛውም ዐይነት ማኅበራዊ ችግር ሊኖር አይገባም።
  3. ሰብአዊ መብት፤ የሰው ልጅ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ሊከበርና መብቱ ሊጠበቅለት ይገባዋል። ይህ ‘የሰው ሕይወት ክቡር ነው’ ከሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ የሚመነጭ ነው። ከላይ እንደተመለከትነው በዘር፣ በኢኮኖሚ፣ በሃይማኖት፣ ወዘተ. ብንለያይም፣ ሰዎች ሁሉ አንድ ቤተ ሰብ ነን። ሰዎች የመኖር መሠረታዊ መብት አላቸው። ከዚህም በተጨማሪ ምግብ፣ መጠለያ፣ አልባሳት፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ወዘተ. የማግኘት መብት አላቸው። እነዚህ መብቶች ግዴታም አላቸው፤ የሌላውን መብትን መገንዘብና ማክበርን ይጠይቃሉ። ባርነት፣ ያለ አግባብ መታሰር፣ ተስማሚ ያልሁኑ የሥራ ቦታዎች፣ ሕጋዊ ያልሆነ የሰዎች ዝውውር እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ ችግሮች የሰውን መብት የሚጥሱና የሰውን ክብር ዝቅ የሚያደርጉ ተግባራት ናቸው። እንደዚህ ዐይነት ችግሮች በማኅበረ ሰባችን ውስጥ ሲስተዋሉ ቤተ ክርስቲያን ድምጿን ማሰማትና ለመፍትሔውም መሥራት አለባት።
  4. ባላደራነት፤ ተፈጥሮን በመንከባከብ ለፈጣሪያችን ያለንን አክብሮት እናሳያለን። ከተፈጥሮ ጋር ተገቢ የሆነ መስተጋብር ሊኖረን ያስፈልጋል። በተፈጥሮ ውስጥ የምናገኘው መልካም ነገር በሙሉ ከእግዚአብሔር የተቸረን ሥጦታ ነው። ዓለም ስለ አካባቢ ሙቀት መጨመር፣ ስለተፈጥሮ ሀብት መመናመን በሚያወራበት በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያን እጇን አጣጥፋ መቀመጥ አትችልም፤ ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ግዳጆቿን መወጣት አለባት። በተለያዩ ተግባራት ተፍጥሮን መንከባከባችን እና መውደዳችንን ማሳያት አለብን። ይህም ከእግዚአብሔር የተሰጠንን ባላደራነት የምንወጣበት መንገድ ነው።
  5. ለድኾችና ለተጠቁት መወገን፤ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ለድኾች ትኩረት እንደሚሰጥ ይነግረናል። እኛም ለድኾች ትኩረት መስጠት እንዳለብን ያሳስበናል። ሰዎች ሁሉ ለኑሮ የሚያስፈልጋቸው መሠረታዊ ነገር እንዲሞላላቸው መሥራት ያስፈልጋል። ይህ ራስን አሳልፎ መስጠትን የሚጠይቅ ነው። የአንድ ማኅበረ ሰብ ምግባር መፈተኛ ድኾችን እና ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረ ሰብ ክፍሎችን እንዴት ይመለከታቸዋል የሚል ነው። የእነዚህ የማኅበረ ሰብ ክፍሎች ችግር የሁሉም የማኅበረ ሰብ ክፍል ችግር ነው። ጤናማ ማኅበረ ሰብ የሚፈጠረው እነዚህ የማኅበረ ሰብ ክፍሎች ትኩረትን ሲያገኙ ብቻ ነው። ቤተ ክርስቲያን ለድኾች የተሰጠች መሆን አለባት። ተስፋን ብቻ የምትሰብክ ሳትሆን አሁን ያለውን የሰዎችን ሁኔታ ለመለወጥ የምትጥር መሆን አለባት። ይህ አመለካከት በተወሰነ መልኩ ከዐርነት ነገረ መለኮት (liberation theology) አስተምህሮ ጋር ይሄዳል።
  6. የጋራ ጥቅም (common good)፤ “ባልንጀራህን ውደድ” የሚለው ትእዛዝ ሰፊ የሆነ ማኅበረ ሰባዊ አንድምታ አለው። ለማኅበረ ሰብ ዕድገትና ማበብ እያንዳንዱ ሰው አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት። የሰው ልጅ ማኅበራዊ ፍጡር ነው። የሰው ክብሩ እና መብቱ የሚረጋገጠው በኅብረተ ሰብ ውስጥ ባለው ግንኙነት ነው። ሰዎች የሚያድጉት፣ ዓላማቸውን የሚፈጽሙጽ በኅብረተ ሰብ ውስጥ ነው። የሰዎችም መብት የሚከበረውና የሚጠበቀው በኅብረተ ሰብ ውስጥ ነው። ማኅበረሰባችን ፖለቲካን፣ ኢኮኖሚን፣ ሕግን እና የመሳሰሉ ጉዳዮችን ያዋቀረበት መንገድ በቀጥታ ከሰዎች ክብር ጋር የተገናኘ ነው። ማኅበራዊ ፍትሕ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት ነው። ማኅበዊ ተቋማትን ለጋራ ጥቅም (common good) እንዲሠሩ ያበረታታል። አንድ ማኅበረ ሰብ የሚያብበው ለጋራ ጥቅም የሚሠሩ የተለያዩ ተቋማት በመተባበር ለለውጥ ሲሠሩ ነው። ይህ ካልሆነ ማኅበረ ሰብ ይታመማል፣ ይከፋፈል፤ ውጤቱም ቀውስና በችግር ውስጥ መዘፈቅ ይሆናል። ቤተ ክርስቲያንም የክፍፍል መሣሪያ ሳትሆን ለማኅበረ ሰብ የጋራ ጥቅም የምትሠራ መሆን አለባት።


ማጠቃለያ

ሰዎች ማኅበራዊ ገጽታ አለን። ስለዚህም በጋራ እንደ ማኅበረ ሰብ የጋራ ጥቅምን በመሻት ሂደት ውስጥ የመሳተፍ መብትና ግዴታ አለብን። እንደ ክርስቲያን ኀላፊነት የሚሰማውና ሕግ አክባሪ ዜጎች የመሆን ግዴታ አለብን። በተመሳሳይ መልኩም ቤተ ክርስቲያን እንደ ተቋም ልትጫወታቸው የሚገቡ ኀላፊነቶች አሉ። መልካም ነገሮች በእኩይ ሲሞሉ ድምጿን ልታሰማ ይገባታል።

ቤተ ክርስቲያን የትኛውም ማኅበረ ሰብ ይዞት የሚመጣውን ራእይ የምትደግፍና የምታበረታታ እንዲሁም ሂስን የምትሰነዝር መሆን አለባት። የወንጌላውያን አማኞች በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሁም በዓለም ቀደፍ ደረጃ ምን ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ? የሚለውን ጥያቄ እንደ ማጠቃላያ ማንሣት ተገቢ ነው። ማኅበረ ሰቡን በተመለከተ ሊያበረኩቱት የሚገባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

የነገረ መለኮት ትምህርት ቤቶች በትምህርት ሥርዐታቸው ውስጥ እነዚህን ነገሮች በማካተት አገልጋዮችን ማሠልጠን አለባቸው። ወንጌል መመስከር የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ እንደ ሆነ ሁሉ ማኅበራዊ ተሳትፎም የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። በኅብረተ ሰቡ ውስጥ የሚታዩትን ኢ-ፍትሓዊ የሆነ ሥርዐትን እና ልምምዶችን መቀየር እንችላለን? እንደ ግለ ሰብ ብዙ ማድረግ ላንችል እንችል ይሆናል፣ ሀኖም ግን ለውጥ ለማምጣት ከሌሎች ጋር አብሮ መሥራትን ይጠይቃል። ለሁሉም ጠቃሚ የሆነ ሥርዐትን ለመፍጠር መተባበር ያስፈልጋል። ይህን በማድረግ የማኅበራዊ ፍትሕን ዕሴቶችና ፍቅርን መለማመድ አለብን።

Share this article:

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተጋፈጠቻቸው የኑፋቄ አስተምህሮዎች

የክርስትና እምነት ገና ከጅማሬው እውነተኛውን የክርስትናን አስተምህሮ በሐሰት ለመበረዝ በሚጥሩ የኑፋቄ ትምህርት መምህራን ከፍተኛ ተግዳሮት ይደርስበት እንደ ነበር ከመጽሐፍ ቅዱስን እንረዳለን፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙ መጻሕፍት መካከል አንድ ሦስተኛውን ስፍራ የሚወስደው ለመናፍቃን ትምህርት የተሰጠ ምላሽ እንደ ሆነ በዘርፉ ምርምር ያደረጉ የሥነ መለኮት ምሁራን ይጠቁማሉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

ለፈጣሪ መኖር ድጋፍ ከሳይንሱ ዓለም?

በባለፈው የፈረንጆች ዓመት ማብቂያ ላይ፣ ማለትም እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 25 2014 ኤሪክ ሜታክስስ የተባለው ዕውቅ ጸሐፊ በዎልስትሪት ጆርናል “Science Increasingly Makes the Case for God” በሚል ርእስ ሳይንስ ፈጣሪ ስለ መኖሩ የሚቀርቡ ሙግቶችን ዕለት ዕለት ይበልጥ እየደገፈ ስለ መምጣቱ ጽፏል።1 ይህ አነጋጋሪ ጽሑፍ እ.ኤ.አ. በ1966 በታይም መጽሔት “ፈጣሪ ሞቷል?” የተሰኘውን ጽሑፍ መነሻ በማድረግ የዘመኑ ሳይንስ የፈጣሪን አለመሞት፣ ብሎም ስለ መኖሩ ይበልጥ ርግጠኛነትን የሚያስጨብጥ ግኝት ላይ እንደ ደረሰ ይናገራል። ይህ ግኝት ምን እንደሆነና ከሜታክስስ ጽሑፍ ጋር የተገናኙ አንዳንድ ሐሳቦችን በዛሬው ጽሑፋችን ለመዳሰስ እንሞክራለን።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.