በተራራቀ መልክአ ምድር ኾኖ መረጃ መለዋወጥ እንደ አኹኑ ዘመን ቀላል አልነበረም። በአካል ተራርቀው የሚኖሩ ሰዎች ተግባቦት ለመፍጠር ይጠቀሙ የነበረው ጥንታዊው ዘዴ፣ ከቦታ ወደ ቦታ በሚንቀሳቀሱ ሰዎች አማካኝነት የቃልና የጽሑፍ መልእክቶችን በዐደራ መልክ መላክ ነበር። መልእክተኞችም በእግርና በፈረስ ረጅምና አድካሚ ጕዞ በማድረግ ዐደራቸውን ከተባሉበት ሥፍራ ያደርሳሉ። ከተቀባዩ ወገን ምላሽ ለማግኘትም ቀናትና ሳምንታት፣ ዐለፍ ሲልም ወራትን መጠበቅ የግድ ነበር።
ይኽን አዝጋሚ የመልእክትና የመረጃ ልውውጥ ታሪክ ወደ ዐዲስ ምዕራፍ ያሻጋገረ የቴክኖሎጂ ግኝት እውን የኾነው በዐሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ገደማ ነበር። ሳሙኤል ሞርስ የተባለ አሜሪካዊ በገመድ አማካኝነት መልእክት ለመለዋወጥ የሚያስችል የቴሌግራፍ ማሽን ሠርቶ ለዓለም ሲያበረክት፣ መረጃና መልእክት የመለዋወጥ ታሪክ ወደ ሌላ ዐዲስ ምዕራፍ ተሸጋገረ። ከዚያም በኋላ ለተመሳሳይ ዐላማ የተሠሩ ዐዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ተከታተለው እውን መኾን ጀመሩ። በ1876 ዓ.ም. አሌክሳንደር ግርሃም ቤል የሠራው የገመድ ስልክ፣ በ1895 ዓ.ም. ጉሌርሞ ማርኮኒ ያሳካው የሬዲዮ ቴክኖሎጂ፣ በ1927 ዓ.ም. ደግሞ በቋሚና በተንቀሳቃሽ ምስሎች የታጀበው የቴሌቭዥን ዘመን ተከተሉ።
በዘመኑ የታየው የመረጃ ልውውጥ ቴክኖሎጂዎች ዕድገት እጅግ ፈጣን ነበር ማለት ይቻላል። ቀድሞ በጽሑፍ መልእክቶች መነጋገርና መተሳሰር የጀመረው ዓለም አኹን በድምፅና በምስል ጭምር መተሳሳር ቻለ። በተለይ ቴሌቭዥን ምስላዊ ገጽታ ተላብሶ መከሠቱ፣ መረጃን በማቅረቡ ረገድ፣ ከእርሱ በፊት ከነበሩት አማራጮች ኹሉ የበለጠ ተጽዕኖ ፈጣሪ አድርጎታል።
ከዚህ ቀጥሎ የመጣው የዲጅታል ሚዲያ ዘመን ነው። ዲጂታል የሚለው ቃል ዲጅተስ (digitus) ከሚለው የላቲን ስርወ ቃል የተገኘ ሲኾን፣ ትርጓሜውም “ጣት” ማለት ነው። ስያሜው የዲጅታል ቴክኖሎጂ መሣሪያዎች፣ በጣቶቻችን የምንዘውራቸው ከመኾናቸው ጋር የተያያዘ ነው። እንደ ቤን ፒተርስ ገለጻ፣ የሰው ልጅ በዕለተ ተዕለት የተግባቦት ሕይወቱ ጣቶቹን ለመቍጠር፣ ለመጠቈምና በተለያዩ ምልክቶች ለመግባባት ሲጠቀምበት የኖረ ዲጅታል ፍጡር ነው[1] ። ዲጅታል ቴክኖሎጂ ይኽ የሰው ልጅ ልማድ በዕድገት የደረሰበት ከፍተኛው ደረጃ መገለጫ ነው ማለት ይቻላል።
ከ1990ዎቹ በኋላ የታየው የበይነ መረብ መስፋፋትና የተንቀሳቃሽ ስልኮች መፈጠር፣ ዲጅታል ሚዲያዎች እንዲጠናከሩና ዐዲስ የተግባቦት ባሕል እንዲፈጥሩ አስችሏል። ይኽም ዓለምን እንደ አንድ መንደር ያስተሳሰረ ክሥተት ነው[2] ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዲጂታሉ መድረክ ከተዋወቅናቸው አገልግሎቶች መካከል ታዲያ፣ ተጠቃሚዎች የራሳቸውን ይዘት እንዲፈጥሩና ለብዙዎች ማጋራት እንዲችሉ ያበቁ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ወይም ማኅበራዊ ሚዲያዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ።
ማኅበራዊ ሚዲያ፣ በተራራቀ ክፍለ ዓለማት የሚኖሩ ሰዎች በቀላሉ ተግባቦት መፍጠርና ልዩ ልዩ ዐሳቦችን መለዋወጥ የሚችሉበትን መልካም ዕድል ፈጥሯል። በመድረኮቹ ንቁ ተሳታፊዎች ኾነው የታዩት ክርስቲያኖችም፣ እርስ በርስ መበረታታት፣ መንፈሳዊ ይዘት ስላላቸው ኹነቶች ዐሳብ መለዋወጥ፣ የአገልግሎት ሸክሞቻቸውን መጋራት፣ የሐሰት አስተምህሮና ልምምድን ማጋለጥና መመከት ዐብረው መቆም፣ በችግር ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እኅቶችን ተባብረው ማገዝና ሌሎችንም መልካም አገልግሎቶች በዚሁ መድረክ መስጠት እንዲችሉ አገናኛ ድልድይ ኾኗቸዋል፤ እየኾነም ነው።
የዲጅታሉ ዘመን ይዟቸው የመጣቸው እነዚህና ሌሎችም መልካም ዕድሎች እንደ በረከት ሊቈጠሩ የሚችሉ ናቸው። ይኹን እንጂ በረከትነታቸው ተጠብቆ የሚቈየው በጥበብ መያዝ እስካወቅንበት ድረስ ነው። ግንኙነቶቻችንን ቀላልና ፈጣን በማደረጉ አመስጋኞች የኾንንበት መድረክ፣ (አንዳንድ ጊዜ) ግንኙነቶቻችን በማሻከሩ የምናዝንበት መድረክ ሲኾን ተስተውሏልና።
እንደ ቴክኖሎጂ ባለሙያው ዣሮን ላኒየር አባባል ከኾነ፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎች አሉታዊ ስሜቶችና ዐሳቦች ከአዎንታዊዎቹ ይልቅ ገንነው ይወጣሉ፤ የብዙዎችንም ትኵረት ይስባሉ[3] ። አጥፊ በኾኑ ድርጊቶች የሚሳተፉ ሰዎችን የሚታገሡ ብቻ ሳይኾን፣ በንቃት የሚያበረታቱና የሚደግፉ ሚሊዮኖች መኖራቸው በመድረኮቹ በጕልህ ታይቷል፤ ይኽ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ገጽታ በቀላሉ ልናስወግደው የምንችለው አይመስልም።
በብዙ አገራት፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት የተለኮሱ ግጭቶች ከፍተኛ ጥፋት አስከትለዋል። ፖለቲካዊ ልዩነትን፣ ሃይማኖታዊ ወገንተኝነትንና ማንነትን መሠረት ያደረጉ በርካታ የቅርብ ጊዜ ግጭቶች በእነዚህ ሚዲያዎች አቀጣጣይነት የተፋፋሙ ናቸው።[4] የክርስቲያኖችን የማኅበራዊ ሚዲያ ተሳትፎ ፈታኝ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል ታዲያ፣ ይኸው ከእግዚአብሔር መንግሥት ዕሴቶች በተቃራኒ የቆሙ መሰል ባሕርያት በሚንጸባረቁበት መድረክ መገኘታቸው ነው። ነውጠኛውንና ጠብ አጫሪውን በሚሸልመው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ፣ ሰላምን በመፈለግ ብፅዕና ሊኖሩ የሚወድዱ ክርስቲያኖች (ማቴ. 5፥9) የሚኖራቸው ተሳትፎ ፈታኝ መኾኑ እሙን ነው[5] ።
ይኽ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ገጽታ የቤተ ክርስቲያንን ዐጥር አልደፈረም ማለት አይቻልም። የብዙዎች ክርስቲያናዊ ፍቅርና አንድነት ጥያቄ ውስጥ እስኪገባ ድረስ የሚያደርሱ የኀይለ ቃላት ልውውጦች፣ ሐሜት፣ እርስ በርስ መፈራረድና ጎራ ለይቶ መቋሰል በየጊዜው የሚታዩ ነገሮች ናቸው ማለት ይቻላል። ርግጥ በአኹኑ ዘመን ፍጽምናን ሙሉ በሙሉ ባልተቀዳጀችው የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ፣ በአካላዊው መሰባሰብ ጊዜም ኾነ በእነዚህ መድረኮች በምናደርገው ተሳትፎ ወቅት የተለያዩ ግጭቶችና አለመግባባቶች በመካከላችን ሊከሠቱ ይችላሉ። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ የውስጥ አለመግባባቶችና ግጭቶች ያልነበሩበት ዘመን አልታየም። ዛሬም ከዚህ የተለየ አይኾንም። ይኹን እንጂ፣ በአማኞች መካከል በዐሳብ ከአለመግባባት የሚመነጩ ግጭቶች በሚኖሩበት ጊዜ፣ አለመግባባቶቹ የሚፈቱባቸው ክርስቲያናዊ መርሖዎች አሉ።
ክርስቲያኖች በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ እንዲተጉ (ኤፌ. 4፥3)፣ አለመግባባቶቻቸውን አደባባያዊ ገጽታ ሳያላብሱ በውስጥ እንዲፈቱ (1 ቆሮ. 6፥1-8) እና በውጪ ኾነው በሚያዩአቸው ፊት የጌታ መኾናቸውን በሚገልጥ ፍቅራቸው እንዲታወቁ ታዝዘዋል (ዮሐ. 13፥35)። ኾኖም፣ በስልኮቻችንና በኮምፒውተሮቻችን የምንተይባቸው ቃላት ከእነዚህ መርሖች ያፈነገጡ ሲኾኑ በተደጋጋሚ ይታያል።
ግለትና ክረት
በክርስቲያኖች መካከል በኦንላይን የሚስተዋለው አንዳንዱ አለመግባባት የዐሳብ ልዩነትን ተከትሎ የሚመጣ ነው። በማኅበራዊ ሚዲያ ዐሳብ ከሰነዘርን በኋላ የተለያዩ ምላሾች እንደሚጠበቁ የታወቀ ነው። በዐሳባችን የሚደሰቱና የሚያዝኑ፣ እንዲሁም የሚናደዱም ጭምር ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህን ምላሾች እንዴት ላስተናግድ የሚለው ትልቅ ጨዋነትንና መንፈሳዊነትን ይጠይቃል። ከዚህ ጋር ተያይዞ፣ መልካም ግንኙነቶችን የሚያበላሹ በርካታ አጋጣሚዎች ይስተዋላሉ።
አንዳንድ ጊዜ የዐሳብ ልዩነትን በምናሳይባቸው ጕዳዮች ላይ የምንነጋገርበት ድምፀት በመሬት ስንገናኝ ከምንነጋገርበት ፍጹም የተለየ ኾኖ ይታያል። አንዳንዴም የሚዲያው መስክ በመደበኛው ሕይወታችን መግለጥ እየፈለግን ያፈንነውን እኵይ ባሕርይ የምናንጸባርቅበት መድረክ መምሰሉ አልቀረም[6] ። መሬት ላይ ባለው ማኅበራዊ ሕይወታችን፣ በልባችን ብንቀየመው እንኳን በይሉኝታና በሐፍረት ምክንያት በሻካራ ቃላት የማንናገረውን ሰው፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲኾን በድፍረት እንናገረዋለን። ይኽ ዐይነቱን ምላሽ የምንሰጥበት ዋና ምክንያት፣ ሌሎች ዐሳባችንን ሲያናንቁብን በብዙኀኑ ፊት እያዋረዱን እንደ ኾነ ስለሚሰማን ሊኾን ይችላል። ያኔ፣ አዳማዊ ማንነታችን ከዛጎሉ ውስጥ ይወጣል። ኹኔታውን በአንክሮ የታዘቡት መጋቢ ሰሎሞን ጥላሁን፣ በአንድ ወቅት፣ “ነርቭህ ሲነካ፤ ኪቦርድ አትንካ!” የሚል ሸንቋጭ ማሳሰቢያ በዚሁ መድረክ እንደ ሰጡን አስታውሳለሁ።
አንዳንዴም የሚዲያው መስክ በመደበኛው ሕይወታችን መግለጥ እየፈለግን ያፈንነውን እኵይ ባሕርይ የምናንጸባርቅበት መድረክ መምሰሉ አልቀረም
በርግጥም፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎች “አደባባያዊ ማሸማቀቂያ”[7] (public shaming) መሣሪያ የሚኾኑባቸው አጋጣሚዎች አሉ። ከእውነት የራቁ በሰብእናችን ላይ የሚከፈቱ እኵይ ጥቃቶችና የስም ማጥፋት ድርጊቶች በሚኖሩበት ጊዜ፣ በዝምታ ከማለፍ ይልቅ አስፈላጊውን ኮምጨጭ ያለ ምላሽ መስጠት ሊያስፈልግ ይችላል። ይኽን ስናደርግ ግን፣ በምላሾቻችን የሚንጸባረቀው ነገር መንፈሳዊ ሰዎች መኾንችንን ያሳያል ወይስ ሥጋዊነት የተጫነው ነው? የሚለውን አበክረን መጠየቅ ይኖርብናል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች፣ የሰርክ ልማድ እስኪመስል ድረስ እየታዩ ያሉት አንዳንድ ምልልሶቻችን፣ ለትልቅ ቅራኔ በር የሚከፍቱና አሉታዊ ስሜቶች ያየሉባቸው ናቸው። ከዐሳብ ይልቅ ሰብእናን ማጥቃትንና የተቃወመንን ኹሉ በተመጣጣኝ የመልስ ምቶች ማደባየትን ተክነናል። ከፉውን በመልካም የመመለስና በጸድቅ በልጦ የመገኘት ክርስቲያናዊ ዕሴት ያለን እስከማይመስል ድረስ፣ ለኹሉ በሰፈሩት ቍና የመስፈር ዓለማዊ ጥበብ ተጠናውቶናል። ዐሳቡን ያልገዛንለት ሰው ሲኖር፣ ሌሎች ሰዎች ለዚያ ሰው ያላቸው ክብርና ፍቅር እስኪሸረሸር ድረስ በሚዘልቅ ጥቃት እንከፋበታለን፤ የለየት ማጠልሸት ውስጥ እንገባለን።
አንዳንድ ጊዜ፣ የጥቂት ግለ ሰቦች አለመግባባት በዙሪያቸው ያሉ ወዳጆቻቸውን ጭምር በማሳተፍ የቡድን ወደ መኾን ያድጋል። በዚህ መልኩ የሚደረግ አደባባያዊ መካሰስና መናቆር ሰላምንና የመንፈስ አንድነትን ጠብቀው በንጽሕና መመላለስ የሚወድዱ ክርስቲያኖችን ክፉኛ ሲያሳዝን፣ ባላመኑት ዘንድም የክርስትናን ገጽታ ሲያጠለሽ ይታያል።
የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ፣ “እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ” (ሮሜ 12፥10) የሚለውን አምላካዊ ቃል ዕለት ዕለት ማስታወስንና መተግበርን ከምን ጊዜውም በላይ እየጠየቀን አለ” የሚሉት መጋቢ ሰሎሞን አበበ፣ ትዝብታቸውን፣ “በማኅበራዊ ሚዲያ አስተየየት ስንሰጥ፣ አክብሮትን ማስቀደም የለብንም ወይ?” በማለት ጠይቀው ይጀምራሉ፤
ቍጣና ክረት በሞላበት፣ ትሕትናና ፍቅር ጨርሶውኑ በማይታይበት አኳኋን፣ የነገር ወንጭፋችንን እያነሣን የምንወረውረው ምን ለማምጣት ነው? ሌላው ላይ ባስከተልነው ቍስል የምናገኘው ክብርና በላጭነትስ ምን ይጠቅመናል? ሌላው ቢቀር፣ አንድ ሰው በራሱ ቤት ግድግዳ (የማኅበራዊ ትስሰር ገጽ) የወደደውን የማድረግ መብት እንዳለው እንዴት እንረሳለን? ሌሎች ባጋሩት ልጥፍ ሥር ኼዶ ያልተገባ ነገር መናገር፣ የሰው ቤት አንኳኩቶ ገብቶ እንደ መሳደብ ያለ ተግባር ነው። መቼስ በእንዲህ ዐይነት ግለትና ንትርክ የምናስተላልፈው ነገር እግዚአብሔርን ያስከብራል፤ ቤተ ክርስቲያንን ደግሞ ያንጻታል ብለን እያሰብን ከኾነ እገረማለሁ! የክርስቶስ ልብ ያስፈልገናል። በእውነት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ከኾንን፣ እኛ በቆምንበት ቦታ ኢየሱስ ቢቆም ኖሮ ምን ያደርግ ነበር? ብለን እንጠይቃለን[8] ።
በርግጥም ምልልሳችንን ለሌሎች ያለንን አክብሮት በሚገልጥ መንገድ ለማድረግ ብዙ ርቀት መጓዝ ይጠይቀናል። እርስ በርስ መጐዳዳትንና መራራነትን የሚወልድ፣ ለበቀልና ለስም ማጥፋት በር የሚከፍት፣ ዐልፎ ተርፎም ያልተገባ ቡድንተኝነትን እየፈጠረ ያለው የኦንላይን ምልልሳችን የዘመኗን ቤተ ክርስቲያን የተለየ ትኵረት የሚሻ እጅግ አሳሳቢ ጕዳይ ይመስላል።
ዲጅታል ሐሜት
ቲም ኬለርና ዴቭድ ፖልሰን የሰዎችን ገጽታ በሚያጠለሹ ነገሮች መሳተፍን ከሐሜት ጋር ያያይዙታል። “ሐሜት፣ የግድ የውሸት መረጃ ማስተላለፍ ብቻ ላይኾን ይችላል፤ ከአንድ ሰው በተቃራኒ በመቆም፣ ያን ሰው ለማሳነስ፣ ለማዋረድና ለመጉዳት ከማሰብ የሚመነጭ ቃል መናገር፣ እንዲኹም በተቀነባበረ ክፋት መደሰትም ጭምር ነው”[9] ይላሉ። በውድቀት ምክንያት የመጣብን የሌላውን ድካም በመግለጥና በመስማት የሚደሰት አዘንብሎት አለን፤ “የሐሜተኛ ቃል እንደ ጣፋጭ ጕርሻ ነው፤ ወደ ሰው ውስጣዊ ክፍል ዘልቆ ይገባል” (ምሳ. 18፥8) እንዲል ጠቢቡ። ይኽ ባሕርያችን ከእኛ የባሰ ኀጢአተኛ ነው ብለን የምናስበውን ወይም በቅንዓት ዐይን የምንመለከተውን ሰው የማሰይጠን ዝንባሌ የተጠናወተው ነው። ድርጊቱ፣ በቀድሞው ዘመን ከባለቤቱ ጀርባ ይደረግ የነበረ ቢኾንም፣ አሁን በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመን ግን አደባባያዊ ገጽታ ተላብሶ የሌላውን ጕድፍ ለማነፍነፍና ለማሰራጨት እየዋለ ነው።
“ሐሜት፣ የግድ የውሸት መረጃ ማስተላለፍ ብቻ ላይኾን ይችላል፤ ከአንድ ሰው በተቃራኒ በመቆም፣ ያን ሰው ለማሳነስ፣ ለማዋረድና ለመጉዳት ከማሰብ የሚመነጭ ቃል መናገር፣ እንዲኹም በተቀነባበረ ክፋት መደሰትም ጭምር ነው”
ይኽ ልማድ በእኛ በክርስቲያኖች ዘንድ ሲታይ ይበልጥ የሚያሳፍር ነው። ግለ ሰባዊ ኀጢአትን ወይም የሥነ ምግባር ጕድለትን በተመለከተ፣ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ግልጽ መመሪዎች ተሰጥውናል። እርስ በርስ የተቀያየሙ ሰዎች ሲኖሩ ለብቻቸው በመወቃቀስና ይቅርታ በመስጠት እንዲሁም በመቀበል እንዲፈቱት፣ በእነርሱ ደረጃ መፈታት ካልተቻለም በቤተ ክርስቲያን ሥልጣን እንዲዳኝና ዕልባት እንዲያገኝ እንዲያደርጉ ቃሉ ያዝዘናል (ማቴ. 18፥15-18)። አንዳችን በሌላችን ላይ ያለብን ግላዊ ቅራኔ ፈጽሞ የማኅበራዊ ሚዲያ ሲሳይ ማድረግ አይገባም። ከግጭት ጋር ያልተያያዙ ከባድ ኀጢአቶች በሚኖሩበት ጊዜም አኹንም ቤተ ክርስቲያን የተግሣጽ እርምጃ እንድትወስድ ሥልጣን ተሰጥቷታል። በግለ ሰቦች ደረጃ ወይም በቤተ ክርስቲያን ሥልጣን ማዕቀፍ ሥር የሚያልቀውን ጕዳይ፣ ወደ አደባባይ ማውጣትና ‘የእገሌን ጉድ ስሙልኝ’ ማለት በቃሉ መርሕ ውስጥ የለም።
ይኽ አካኼድ፣ በግለ ሰቡ፣ በቤተ ሰቦቹ እንዲኹም በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያመጣውን ትርፍና ኪሳራ አስቀድሞ ማስላት የተሳነው ግድ የለሽ አካኼድ ነው። የምናዛምተው መረጃ እውነት እንኳን ቢኾን፣ “እውነትን ማጋለጥ” በሚል ስም በወንድም ላይ በአደባባይ መዝመት ከፍቅር ሕግ የተጣላ ድርጊት ነው። “ለእውነት ብንወግንም፣ ሰዎችን በፍቅር ማከም ካላወቅንበት ሳናቈስል አንመለስም። እንደ ቡጢ ሲሰጡት ብቻ በሚቀልለው “መካሪነትና ወጋጅነት” ብቻ ሩቅ መኼድ አይቻልም።”[10] በተገኘው መድረክ ኹሉ፣ በሆድ ያለን እያወጡ ፀሓይ ማስመታት ስንፍና ነው፤ “ሰነፍ የጥበብን ነገር አይወድድም፤ በልቡ ያለውን ብቻ መግለጥ ይወድዳል(ና)” (ምሳ. 18፥2)። ይኽ ልማድ የሚሰሙትን የሚያፈርስ፣ በእኛ የተጠራውንም የእግዚአብሔርን ስም የሚያሰድብ ነው።
ወንድሞቻችንን በአደባባይ እንድናሳፍራቸው ሳይኾን፣ የንስሓ ዕድል የሚያገኙበትን መንገድ እንድናሳያቸው ይጠበቅብናል።
ክርስቲያናዊው የፍቅር ሕግ የወንድምን በደል በፍቅር እንድንሸፍን ያዝዘናል፤ “ፍቅር የኀጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከኹሉ በፊት እርስ በርሳችኹ አጥብቃችኹ ተዋደዱ” ተብለናል (1 ጴጥ. 4፥8)። ወንድሞቻችንን በአደባባይ እንድናሳፍራቸው ሳይኾን፣ የንስሓ ዕድል የሚያገኙበትን መንገድ እንድናሳያቸው ይጠበቅብናል። ሐሜት የሌላውን በደል በመግለጥ ራስን የተሻሉ አድርጎ በመቍጠር ወይም እንደ ተሻሉ በማሰብ የሚገኝን ደስታ መሠረት ያደረገ ድርጊት ነው። ቀደም ባለው ዘመን በቤተ ሰብ፣ በባሕላዊ ሽምግልናና በሃይማኖት አባቶች በጥንቃቄ ተይዘው ዕልባት ይገኝላቸው የነበሩ የሰዎች ምስጢራዊ ጕዳዮች፣ በዘመናችን የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሰለባ እየኾኑ ነው። የምስጢር ጠባቂነትንና የገመና ሸፋኝነት ዕሴቶች አሽቀንጥሮ የጣለ ገጽታ ገዳይ ትውልድ የተፈጠረ ይመስላል።
ቅንዓትና ውድድር
የማኅበራዊ ሚዲያ ተሳትፎን ክረት የሞላበት ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል የቅንዓትና የውድድር መንፈስ አንዱ ነው። በእነዚህ ሚዲያዎች ንቁ ተሳትፎ ስናደርግ፣ እኛ በምንሳተፍበት ዘርፍ የሚሳተፉ ሌሎች ሰዎችን በዚሁ መድረክ ማግኘታችን አይቀርም። ለእነዚህ ሰዎች በጎ አመለካከት ሊኖረን እንደሚችለው ኹሉ፣ እኵይ ስሜትም ሊሰማን ይችላል። ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላልተፈለገ የውድድር መንፈስ የማጋለጥ ወይም ስሜቱን የማባባስ ሚና አላቸው። ይኽን አስመልከቶ በተሠራ አንድ ጥናት፣ ማርጋሬት የተባለች ታዳጊ፣ “ፌስቡክ ስጠቀም በቀላሉ ራሴን ከሌሎች ጋር በማወዳደር ፈተና ውስጥ እወድቃለሁ። እኔ ያገኘሁትን የላይክ ቍጥር ሌሎች ካገኙት ጋር ሳወዳድር ራሴን አገኘዋለሁ። እነዚህ ሰዎች ደስተኛ እንዳልኾን ያደርጉኛል። ለራሴ ያለኝ ግምት በዚህ ላይ የተመሠረተ ነው” ብላለች[11] ። ሚካኤል የተባለ ሌላ ወጣትም እንዲሁ፣ “ማኅበራዊ ሚዲያዎች ከሰዎች ጋር ትርጕም ያለው ተግባቦት ከመፍጠር ይልቅ ምን ያህል ደስተኛ ሕይወት እንዳለህ ለሌሎች የምታሳይበት መድረክ ነው። አንድ ሰው ፎቶ ለጥፎ 30 ላይክ ቢያገኝና አንተ 31 ብታገኝ ከዚያ ሰው የተሻልክ እንደኾንህ መቍጠር ትጀምራለህ”[12] ይላል።
በማኅበራዊ ሚዲያዎች የተለያዩ ይዘቶችን በማጋራት የምንሳተፍ ወንድሞችና እኅቶች፣ በዚህ ረገድ ያለን ተመክሮ ምን ይመስላል? ከእኛ የበለጠ ሙገሳና ተከታይ የሚያገኙ ወዳጆቻችንን ስንመለከትስ ምላሻችን ምን ይኾናል? ከትሕትና ዐሳብ ይልቅ በልጦ የመገኘት የእኔነት ዐሳብ የሚበረታብን ከኾነ፣ የሌላው ሰው ተቀባይነት ማግኘት ሽብር ውስጥ ይከትተናል። በተለይ ከእኛ የተለየ ዐሳብ ኖሮት ቅቡል መኾን የቻለ ሰው ስንመለከት፣ ዐይናችን ደም ሊለብስና የዚያን ሰው ገጽታ ለማበላሸት እንቅልፍ ዐጥተን ልናድር እንችላለን። “ጤናማ ያልኾነ ውድድር ቅንዓትን ይወልዳል”[13] ። የአንዳንድ ግጭቶች መንስኤ የዚህ ስሜት ውልድ ነው።
ራስን ከሌሎች ጋር ማወዳደር፣ የሰው ልጅ ኹሉ የሚፈተንበት ፈተና ሳይኾን አይቀርም። ከጨቅላ ዕድሜያችን ጀምሮ በመልክ፣ በአለባበስ፣ በቤተ ሰብ ደረጃ፣ በትምህርት ስኬትና በሌሎችም ነገሮች ከጓደኞቻችን ጋር ያለንን ልዩነት እናሰላለን። ተሽሎ በመገኘትም የተሻለ ትኵረትና ተቀባይነት ለማግኘት አንፈልጋለን። ይቀናቀኑናል ብለን በምናስባቸው ላይ የቅንዓት ስሜት ያድርብናል። ይኽ ዝንባሌ በሚዲያ ተሳትፎም ላይ ጐልቶ ይታያል። ኹሉም ሰው እንዲህ ያለ ያልተፈለገ ስሜት ይሰማዋል ብሎ መደምደም ባይቻልም፣ ፈተናው እውን ነው። ይኽ ዐይነቱ ሥጋዊነት በክርስቲያን ወንድሞችና እኅቶች ዘንድ ሲታይ፣ መንፈሳዊ ሕይወትን የሚያቀጭጭ፣ ለብዙዎችም መሰናክል የሚኾን ነው።
“በዚህ መድረክ እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ትልቁ ተግዳሮት፣ አገልጋዮቹ እኔ ከፊት ኾኜ ሪቫኑን ካልቈረጥኩ የሚል መንፈስ የሚታይባቸው መኾኑ ነው”
መጋቢ ሰሎሞን ጥላሁን በማኅበራዊ ሚዲያ መንፈሳዊ አገልግሎት እንሰጣለን በሚሉት ላይ ጭምር ይኽ ነገር የሚስተዋል እንደ ኾነ ሲያነሡ፣ “በዚህ መድረክ እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ትልቁ ተግዳሮት፣ አገልጋዮቹ እኔ ከፊት ኾኜ ሪቫኑን ካልቈረጥኩ የሚል መንፈስ የሚታይባቸው መኾኑ ነው”[14] ይላሉ። በርግጥም፣ በተደጋጋሚ የአገልግሎቱን ሜዳ ሲያውከው የሚታየው ይኸው እኵይ ባሕርይ ይመስላል።
ከኹሉ የከፋው አደጋ ከሌላው ጋር ራስን ማወዳደርና በልጬ ልገኝ ማለቱ ብቻ አይደለም፤ ይቀናቀነናል ብለን የምናስበውን ሰው መጥላትና በዚያ ሰው ላይ ክፉ ነገር መጐንጐን ውስጥ ልንገባ የምንችል መኾኑ ጭምር ነው። ሌላው ሰው ከእኔ የተሻለ ዕውቅና እያገኘ ነው ከሚል ደኅንነት የማጣት ስሜት (insecurity) የሚመነጭና ያ ሰው ይንቀኛል ከሚል ፍርሐት የሚወለድ ጭካኔ አለ። ይኽም የምንሠጋውን ሰው ገጽታ የማጠልሸት ተግባር ውስጥ ሊያስገባን ይችላል።[15] ነገሩ በግለ ሰብ ደረጃ ተወስኖ የሚቆይም አይደለም፤ እንደ ሥጋት የቈጠርነውን ሰው ከማይወድዱ ሰዎች ጋር ቡድን መፍጠር፣ ስሕተቱን አድፍጦ መጠበቅ፣ ጕድለት ሲገኝበት በተደራጀ መንገድ ማጥቃትና ውንጀላ ውስጥ መግባትንም ያስከትላል።
ክርስትና ወንድሜ ከእኔ ይሻላል በሚል መንፈስ የታነጸ የፍቅር ሕይወት ነው (ፊልጵ. 2፥3)። ራስን በማላቅ ምኞት ውድድር ውስጥ አይገባም። የአንድ አካል ብልቶች ሊነቃቀፉና ሊናናቁ አይችሉም። ባለፉት ዓመታት፣ የዐሳብ ልዩነትን ካለመታገሥና ምናልባት በልባችን ወስጥ ካደባ የውድድርና የቅንዓት መንፈስ በመነጨ የምንጭረው ቅዱስ ያልኾነ እሳት (እኔን ጨምሮ) ብዙዎቻችንን ለብልቦናል። የአንድ አባት ልጆች መኾናችንን እስክንዘነጋ ድረስ በማኅበራዊ ሚዲያ የምናፋፍመው ፍቅር አልባ ጦርነት መልካም ዕሴቶቻችን በማስጣል ለማኅበራዊና መንፈሳዊ ኪሳራ ዳርጎናል።
ይኽን አሳዛኝ እውነታ የታዘበው ወንድም ፋኑኤል ብርሃኔ፣ “የዕቅበተ ዕምነት ሠራተኞች ነን የምንለውን ባሰብኹ ጊዜ….” በማለት የቂሳሪያው ባስልዮስ የተናገረውን ንግግር ተርጕሞ በፌስቡክ ገጹ ላይ አስፍሮ ተመልክቻለሁ። እንዲህ ይነበባል፡-
አንዳችን ሌላችንን እናጠቃለን፤ እርስ በርሳችንም እንጐዳዳለን። ጠላት ቀድሞ ባይመታን እንኳን ከእኛ ወገን የኾነው ወታደር አስቀድሞ አቍስሎናል። ይኽም ብቻ አይደለም፣ ከእኛ ወገን የኾነው አንዱ ተመትቶ ቢወድቅ ሌላው ጓድ ሬሳው ላይ ይረማመዳል። አንድ የሚያመሳስለን ነገር ቢኖር የጋራ ጠላታችንን መጥላታችን ብቻ ነው፤ ይኹን እንጂ ጠላቶቻችን ዘወር ሲሉ እርስ በርስ እንደ ጠላት መሻኮታችንን እንቀጥላለን”[16]
ትዝብቱ ከአደባባይ የዋለ እውነት ነው። በመሰል ድካም ውስጥ የተገኘን፣ በሐሜት፣ በፍርድና በቡድንተኝነት የሚያፈርስን መንገድ በመኼድ የታማን ኹሉ፣ ከያዝነው እምነትና ሕይወት ከሚጣረሰው ከዚህ ከንቱነት መመለስ ለነገ የምናሳድረው ጕዳይ ሊኾን አይገባም። ቅንዓትና የውድድር መንፈስ ያለመብሰል ፍሬዎች ናቸው። በጣቶቻችን የምንተይበውና የምንለጥፈው ኹሉ ለሚሰሙን፣ ለሚያዩንና ለሚያነብቡን ጸጋን የሚሰጥ እንዲኾን በጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል (ኤፌ. 4፥29)።
ዕቅበተ እምነትስ?
ከግላዊና ቡድናዊ አለመግባባቶች ቀጥሎ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ከሚያናጉ ነገሮች አንዱ የሐሰት አስተምህሮ ነው። ኑፋቄ በባሕርዩ አማኞችን የሚከፋፍል ነው (ቲቶ 3፥10)። በርግጥ በኑፋቄ ምክንያት የሚከሠት መለያየት ኹል ጊዜ ክፉ አይደለም፤ በተለይ እውነትን ካጸኑ በኋላ በእውነት ላይ ከሚያምጹ ሰዎች ጋር ግልጽ መሥመር አኑሮ መለያየቱ የቤተ ክርስቲያንን ኹለንተናዊ ጤንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ ነው። አንድ ሰው እንደ ተናገሩት፣ “እውነት አንዳንድ ጊዜ ሰዎችን ትለያያለች። በተለይም በክርስትና መሠረታዊ የሚባሉት እውነቶች ሰፊ ልዩነት ያስከትላሉ። የክርስትና ግብም ቢኾን በሮችን አስፍቶ ኹሉም ሰው እንዲገባና ምቾት እንዲሰማው ማድረግ ሳይኾን፣ ቀጥተኛውን የእውነት ወንጌል መስበክና እውነትን በሚወድዱና በማይወድዱ መካከል ልዩነት መፍጠር ነው።”እውነት ሰዎችን እንደምትከፋፍል ጌታም ተናግሯል፤ እውነትን በመረጡና በእውነት ላይ ባመጹ የአንድ ቤተ ሰብ ሰዎች መካከል እንኳን ልዩነት ሊፈጠር ይችላል (ሉቃስ 12፥51-53)።
በርግጥ በኑፋቄ ምክንያት የሚከሠት መለያየት ኹል ጊዜ ክፉ አይደለም፤ በተለይ እውነትን ካጸኑ በኋላ በእውነት ላይ ከሚያምጹ ሰዎች ጋር ግልጽ መሥመር አኑሮ መለያየቱ የቤተ ክርስቲያንን ኹለንተናዊ ጤንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ ነው።
ይኽን ተከትሎ ሊፈጠር የሚችልን መለያየት አንዳንዶች ከፍቅር አልባነት ጋር ሲያያይዙት ይታያል። በሐሰት አስተምህሮ ዙሪያ በተለያዩ መድረኮች የሚደረግን ሙግትና እንደ እግዚአብሔር ቃል የሚተላለፍን የተጠንቀቁ መልእክት ከጥላቻ የሚፈርጁ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነት እንዲጠበቅ የሚሞግቱ ድምፆችንም በክርስቲያኖች መካከል ክፍፍልን ይፈጥራሉ ብለው የሚሠጉ አሉ። ይኽን የታዘቡት ሀንክ ሀኔግራፍ፣ “Christianity in Crisis” በሚለው መጽሐፋቸው፣ ስሕተትን በግልጽ መቃወም እንዲያውም ምእመናንን ከመከፋፈል ይልቅ አንድ የማድረግ ሚና እንዳለው ይሞግታሉ[17] ። ትምህርታቸውን ወደ ብዙኀኑ ጆሮ ስላደረሱ የሐሰት መምህራንና ስለ ትምህርቶቻቸው፣ ክርስቲያናዊ ጨዋነትን በተላበሰ መልኩ ሰሚዎችን ማስጠንቀቅ ተገቢ ነው። ተግባሩ የቤተ ክርስቲያንን በእውነት ላይ የቆመ አንድነት መጠበቅ እንጂ ማፍረስ አይደለም።
ሐዋርያቱና የጥንቷ ዘመን ቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ስሕተት እንዳይስፋፋ የኑፋቄን ትምህርት ይከላከሉና መናፍቃንንም ያወግዙ ነበር (1ጢሞ. 1፥18-20፤ 2ጢሞ. 1፥15፤ 4፥9-10፤ 2ጢሞ. 2፥16-18። በእነዚህ ክፍሎች በስም ጭምር እየጠሩ ማውገዛቸውን እንመለከታለን)። የ16ኛው ክፍለ ዘመን የቤተ ክርስቲያን ሐዳሲያን፣ የቤተ ክርስቲያንን ሕልውና ቃሉ በቀጥተኛነት ከመሰበኩ ጋር አገናኝተዋል። ቃሉ በርቱዕነት የማይሰበክበት ሥፍራ፣ የቱንም ያህል ፍቅር የሰፈነበት ቢመስልም በዚያ ሥፍራ ቤተ ክርስቲያን አለች ማለት አይቻልም። እውነተኛ ክርስትና “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ለተሰጠች እምነት እንጋደል” (ይሁዳ 3) የሚልን ጥሪ ያነገበ ነው። ይኽ በእኛም ዘመን እውነት ነው።
በሐሰት አስተምህሮ ዙሪያ በተለያዩ መድረኮች የሚደረግን ሙግትና እንደ እግዚአብሔር ቃል የሚተላለፍን የተጠንቀቁ መልእክት ከጥላቻ የሚፈርጁ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነት እንዲጠበቅ የሚሞግቱ ድምፆችንም በክርስቲያኖች መካከል ክፍፍልን ይፈጥራሉ ብለው የሚሠጉ አሉ።
በማኅበራዊ ሚዲያ በሚሰጠው የዕቅበተ እምነት አገልግሎቱ የሚታወቀው መጋቢ ቴዎድሮስ ተጫን፣ በማኅበራዊ ሚዲያ እየተሠራ ያለው የምካቴ ክርስትና ሥራ ብዙዎችን ለማንቃትና ለማስጠንቀቅ እንደ ቻለ ይመሰክራል። በዚህ መድረክ የሚቀርበውን አገልግሎት እጅግ አስፈላጊና አማራጭ የሌለው ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ፣ የሐሰት መምህራን ትምህርታቸውን ለማሰራጨት በዋናነት የሚጠቀሙት እነዚህኑ መድረኮች መኾኑ ነው ይላል። “ብዙኀኑ እየተገኘ ያለው በዚህ መድረክ ስለ ኾነ፣ በዛው መድረክ ያስተማሩትን ትምህርት የማፍረስ ግዴታ አለብን” በማለትም ቤተ ክርስቲያንና የዕቅበተ እምነት ሸክም ያላቸው ወገኖች የተለየ ትኵረት ሰጥተው እንዲጠቀሙ ያበረታታል[18] ።
የተጽዕኖ አድማሱ በአንዲት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ብቻ የተገደበና በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥልጣን ሥር የሚዳኝ ካልኾነ በቀር፣ በተለያዩ መንገዶች የተስፋፋና የተሰራጨን ኑፋቄ በማኅበራዊ ሚዲያም ኾነ በሌሎች መንገዶች በአደባባይ መመከት፣ እንዲኹም የተጠንቀቁ መልእክት ማስተላለፍ፣ ለአንድ አገልጋይ ጥሪው ራሱ የሚጠይቀው ግዴታ ነው። ጤናማውን የክርስትና ትምህርት መከላከል የእያንዳንዱ አማኝ ኀላፊነት ጭምር በመኾኑም፣ በቂ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ዐቃብያነ እምነት በዚህ አገልግሎት መሳተፍና ማስጠንቀቅ ይችላሉ።
ለዚህ አገልግሎት የተለየ ሸክም ያለን አገልጋዮች ብንኖር ሥራችንን በብዙ አክብሮትና በጥንቃቄ ማከናወን አለብን። አገልግሎቱን ከፍቅር ዕጦት ማያያዝ፣ አገልጋዮቹንም እንደ ከፋፋይና በጥላቻ ያበዱ አድርጎ መፈረጅ አይገባም ስንል ግን፣ የአገልግሎቱ አቀራረብ ግድ የለሽ ይኹን ማለት አይደለም።
ጤናማውን የክርስትና ትምህርት መከላከል የእያንዳንዱ አማኝ ኀላፊነት ጭምር በመኾኑም፣ በቂ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ዐቃብያነ እምነት በዚህ አገልግሎት መሳተፍና ማስጠንቀቅ ይችላሉ።
እንደ ዘማሪ ዶ/ር ለዓለም ጥላሁን እምነት፣ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚቀርበውን አገልግሎት ውጤታማነት የሚወስኑ ኹለት ነገሮች አሉ፤ የመጀመሪያው ከብቃት ጋር ይያያዛል። አገልግሎት የዕውቀት ዝግጅት የሚፈልግ በመኾኑ፣ በዚህ መድረክ አገለግላለሁ የሚል ሰው መልእክቱን በሚያስተላልፍበት ጕዳይ ላይ ጥልቀት ያለው ዕውቀት ታጥቋል ወይ የሚለው የመጀመሪያው ቍልፍ ነገር ነው። አንድ ስሑት ትምህርት ወይም ልምምድ አደባባያዊ ማጋለጥና ማስጠንቀቂያ የሚያስፈልገው ኾኖ ሲገኝ፣ በትምህርቱ ላይ በቂ መረጃ ማሰባሰብና አስፈላጊ ሙግት ማደራጀትን ይጠይቃል።
ኹለተኛው፣ ከአገልጋዩ መልካም የሕይወት ምስክርነትና ምሳሌነት ያለው ሕይወት ጋር የሚያያዝ ነው። የአንድን አገልግሎት ውጤታማነት የሚወስነው፣ መልእክቱ ብቻ ሳይኾን አቅራቢውም ጭምር ነው። በዚህ መድረክ የምናገለግል ሰዎች፣ ብንሳሳት ለመታረምና ብናጠፋ ለመስተካከል ፈቃደኝነቱ አለን ወይ? አገልግሎታችንን የምናቀርብበት መነሻ ምክንያትስ ንጹሕ ነው? እነዚህን ነገሮች ርግጠኛ መኾን ከቻልን አዎንታዊ ውጤት ልናይ እንችላለን[19] ።
ዕቅበተ እምነታችንን ለነቀፋ ከሚያጋልጡት ነገሮች አንዱ የአቀራረባችን ከክርስቲያናዊ ዕሴቶች ጐድሎ መገኘት ነው።
ዕቅበተ እምነታችንን ለነቀፋ ከሚያጋልጡት ነገሮች አንዱ የአቀራረባችን ከክርስቲያናዊ ዕሴቶች ጐድሎ መገኘት ነው። አስተማሪውንም ኾነ የትምህርቱን ተከታዮች በስሜት መዝለፍ፣ ንግግሮችን እየመዘዙ ማንጓጠጥና ክብረ ነክ ቃላትን መናገር ከሚታዩት ጕድለቶች መካካል ይጠቀሳሉ። ይኽ ዐይነቱ አቀራረብ በትምህርቱ የሳቱትን ከማቅናት ይልቅ የሚያፈርስ፣ ሰሚዎችንም ግራ የሚያጋባ ነው። ሰይፋችን ስተዋል በምንላቸው ላይ ብቻ ሳይኾን፣ ዐብረውን በተሰለፉት ላይ ሳይቀር የሚመዘዝባቸው ጊዜያትም ብዙ ናቸው። የዕውቀት ብልጫን ለማሳየት የሚደረግ የሚመስል፣ ጥቃቅን ልዩነቶችን ሳይቀር መታገሥ የማይችልና “ሌላው እንደ እኔ ለምን አላሰበም?” በሚል ዕብሪት የተለወሰ አካኼድ ይታያል። በዚህ ኹኔታ የሚደረግ “ዕቅበተ እምነት” የተከበረውን አገልግሎት የሚያሰድብና የሚያስንቅ ነው። ‘የዕውቀት ማሥመሪያ እኔ ነኝ’ በሚል መንፈስ ሌሎች እንዲሰሙን የምንጮኸው ጩኸት፣ በትዕቢት ተወግቶ የቈሰለ በመኾኑ ሰሚውን ከማቅናት ይልቅ ይሰብራል። “የቃለ እግዚአብሔር መልእክት ትርጕም የሚሰጠውና ሌሎችን የሚያክመው እውነትና ፍቅር ከሕይወት ጋር ተዳምረው ሲቀርቡበት ነው።”[20] አገልግሎቱ ሊያክመን ሲገባ ተጨማሪ ቍስል የሚያመጣብን እንዳይኾን ከፍ ያለ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል።
እንዴት እንደምንተይብ እንጠንቀቅ!
ጌታችን “ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ኹሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል” (ማቴ. 12፥36) በማለት ተናግሯል። ፍቅርን የማይገልጡ ሻካራ ቃላት፣ ፌዝና ሥላቅ፣ ስድብና ማንጓጠጥ ኹሉ በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ፊት መልስ እንድንሰጥ ሊያቆመን እንደሚችል ማወቅ አለብን። መዘዙን በጥንቃቄ ሳናስተውል የምንተይበው ቃል ለአንዱ ሣቅ ሲያጭር፣ ለሌላው ዐጥንት የሚሰብር ሊኾን ይችላል። ስለዚህ ነገር እግዚአብሔር የሚፈርድ ነው።
መንፈሳዊ ሰው፣ ከሰዎች ጋር በሚኖረው ተግባቦቱ የመንፈስ ፍሬዎች በኾኑት ትዕግሥት፣ የውሃትና ራስን መግዛት ተለይቶ ይታወቃል። ንግግራችን በጥበብ ካልተገራ ትልቅ ጫካ እንደሚያጋይ እሳት የማጥፋት ዐቅሙ ከፍተኛ ነው (ያዕ. 3፥1-2)። ሰው የዐሳብና የተግባቦት ድካም ቢኖርበት እንኳ መልካም ነገሩን ሊያጠለሽ በሚችል ደረጃ መክፋት ክርስቲያናዊ አይደለም።
ርግጥ ሰላማዊና የሚያንጽ ንግግር ለማድረግ የማይመቹና ከመቀራረብ ይልቅ መለያየትን ዘወትር የሚፈጥሩ ሰዎች ይገጥማሉ። ይኽ በሚኾንበት ጊዜ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ለእምነት ልጁ ለቲቶ፣ “አንድ ጊዜ ኹለት ጊዜም ከገሠጽኸው በኋላ እንዲህ ከሚመስል ሰው ራቅ” (ቲቶ 3፥10) በማለት ያዘዘውን መተግበር አስፈላጊ ሊኾን ይችላል። በማኅበራዊ ሚዲያ የሚደረገውን አላስፈላጊ መዘላለፍና መጐዳዳት ማስቀረት ባንችል አንኳ፣ የእኛን ተሳትፎ መቀነስና የችግሩ አካል ላለመኾን መወሰን እንችላለን።
ርግጥ ሰላማዊና የሚያንጽ ንግግር ለማድረግ የማይመቹና ከመቀራረብ ይልቅ መለያየትን ዘወትር የሚፈጥሩ ሰዎች ይገጥማሉ። ይኽ በሚኾንበት ጊዜ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ለእምነት ልጁ ለቲቶ፣ “አንድ ጊዜ ኹለት ጊዜም ከገሠጽኸው በኋላ እንዲህ ከሚመስል ሰው ራቅ” (ቲቶ 3፥10) በማለት ያዘዘውን መተግበር አስፈላጊ ሊኾን ይችላል።
ይኽ ሲባል ብዙኀኑን የሚጠቅም እንደ ኾነ በታመነበት ርእሰ ጕዳይ ላይ አደባባያዊ ክርክር ልናደርግ የምንችልባቸው አጋጣሚዎች የሉም ማለት አይደለም። ያን ደግሞ፣ የሙግቱን ተሳታፊዎች ማዋረድና ዐሳባቸውን ማጣመም ሳያስፈልግ በጨዋ ደንብ ልናደርገው እንችላለን። ከብዙ ጥንቃቄ ጋር ከተደረገ፣ ከተለያየ የዕይታ መነጽር ሊታሰቡ የሚችሉ ጠቃሚ ዐሳቦችን መለዋወጡ ቢጠቅም እንጂ ጕዳት የለውም።
“በማኅበራዊ ሚዲያ የምናስተላልፈው መልእክት ዘር ነው፤ መብቀሉ አይቀርም። ያ ነገር ቢበቅል እግዚአብሔርን ያስከብራል? ቤተ ክርስቲያንን ያንጻል? ለአገር ይበጃል? ማኅበራዊ ተግባቦትን ያመጣል? እኛ ሳናልፍም ኾነ ዐልፈን ልጆቻችን ሲያዩት በዚያ ነገረ ደስ ይሰኛሉ? ብለን እንጠይቅ። ከመጻፋችንና ከማጋራታችን በፊት ደጋግሞ ማሰብ ወሳኝነት አለው።”[21]
ይኽን ዕርምት ለመውሰድ የምንቸገር እንደ ኾነስ?
በዚህ ረገድ ያለብን ድካም በቀላሉ የማናስወግደው እንደ ኾነ ከተረዳን፣ ከመድረኩ መራቅ አንደ አንድ አማራጭ ሊታሰብ ይችላል። ጊዜ ወስደን ራሳችን ላይ መሥራት እንድንችል ከፈተናው ሜዳ ለጥቂት ገለል በማለት በእግዚአብሔርና በቃሉ ፊት በቂ ጊዜ መውሰድ ያስፈልጋል። በዕድሜና በአገልግሎት የበሰሉ ሰዎችን ማማከርም ሊጠቅም ይችላል። ከዚህ ውጪ በለመድነው መንገድ የምንጓዝ ከኾነ ግን፣ ከኹሉ በፊት ራሳችን እንጐዳለን፤ ቀጥሎም ሌላውን እናቈስላለን።[22]
ማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ እኛ የእግዚአብሔር ልጆች በፍቅራችን የምናበራባቸውና ሰላምን የምንሰብክባቸው መድረኮች ይኹኑልን!
ከሰማይ የኾነችው ጥበብ ሰላም ወዳድ ናት (ያዕ. 3፥17)!
[1] Benjamin Peters, ed., Digital Keywords: A Vocabulary of Information Society and Culture (Princeton, NJ: Princeton University Press, 2016), 93
[2] Gabriele Balbi and Paolo Magaudda, A History of Digital Media: An Intermedian and Global Perspective (Routledge, New York, 2018), 29.
[3] Jaron Lanier, Vox podcast interview with Ezra Klein from January 16, 2018, Accessed December 23, 2023 https://www.vox.com/2018/1/16/16897738/jaronlanier-interview
[4] በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶችን አያያዝ የሚያጠና የምርመራ ቡድን እንዳረጋገጠው፣ በ2017 ዓ.ም. በማይናማር ለተከሠተውና ለብዙዎች ሞት እንዲሁም ወደ ሰባት መቶ ሺሕ ለሚጠጋ ሕዝብ መፈናቀል ምክንያት ለኾነው ግጭት፣ በፌስቡክ ይሰራጩ የነበሩት የጥላቻ ንግግሮች የአንበሳውን ድርሻ ስለመውሰዳቸው ሮይተርስ በዘገባው ገልጾ ነበር። Reuters, Accessed January 29, 2023, https://www.reuters.com/article/us-myanmar-rohingya-facebook/u-n-investigators-cite-facebook-role-in-myanmar-crisis-idUSKCN1GO2PN ፤ እንዲኹም፣ ሲ ኤን ኤን ጥቅምት 25፣ 2021 ይዞ በወጣው ተመሳሳይ ይዘት ያለው ዘገባ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በሰሜኑ ክፍል ለተቀሰቀሰው ግጭትና ጦርነት መስፋፋት፣ በፌስቡክ ይሰራጩ የነበሩት ግጭት አባባሽ መልእክቶች አስተዋጽ እንደ ነበራቸው፣ ይኽም ሲኾን ድርጅቱ እያወቀ እንዳላስቆመ በዘገባው ላይ ተመላክቷል። CNN, Accessed January 29, 2023, https://edition.cnn.com/2021/10/25/business/ethiopia-violence-facebook-papers-cmd-intl/index.html
[5] Gavin Ortlund, Digital Discipleship: Faithful Christian Living in the Digiatla Age, Accessed December 1, 2022, https://www.thegospelcoalition.org/landing/digital-discipleship-ebook/
[6] ዝኒ ከማሁ
[7] ዝኒ ከማሁ
[8] ሰሎሞን አበበ (መጋቢ)፣ በግል የተደረገ ቃለ መጠይቅ፣ ታኅሣሥ 8፥ 2015 ዓ.ም።
[9] Tim Keller and David Powlison, “Should You Pass on Bad Reports?” Accessed November 30, 2022, https://www.thegospelcoalition.org/blogs.justin-taylor/keller-and-powlison-should-you-pass-on/
[10] ሰሎሞን አበበ ገብረ መድኅን፣ የተቈረሱ ነፍሶች (አዲስ አበባ፣ ርኆቦት ዐታሚዎች፣ 2009 ዓ.ም.)፣ 77።
[11] Donna Freitas, The Happiness effect: How Social Media is Driving a Generation to Appear Perfect at Any Cost (USA:Oxford University Press፣ 2017), 19.
[12] Ibid, 21.
[13] Digital Discipleship, 24.
[14] ሰሎሞን ጥላሁን (መጋቢ)፣ በግል የተደረገ ቃለ መጠይቅ፣ ኅዳር 1፥ 2015 ዓ.ም.
[15] Digital Dscipleship, 24
[16] ፋኑኤል ብርሃኔ፣ በGospel Coalition ገፅ ያገኘውን የቂሣርያው ባሲልዮስን (330-79 ዓ.ም) ንግግር በመተርጐም፣ በጥቅምት 23፥ 2022 በፌስቡክ ገጹ አጋርቶ ያገኘሁት ነው፦ https://www.facebook.com/100000257538309/posts/pfbid02eMBAVMgoCJhV1F7kxrpkf1vzaC2j6MZqmUTmrfQytKqBeyXJsStwwdua3VUroQUJl/?app=fbl
[17] Hank Hanegraaff, Christianity in Crisis (Eugene, Oregon: Harvest House Pub., 1993), 47.
[18] መጋቢ ቴዎድሮስ ተጫን፣ በግል የተደረገ ቃለ መጠይቅ፣ ጥቅምት 11፥ 2015 ዓ.ም.
[19] ለዓለም ጥላሁን (ዶክተር)፣ በግል የተደረገ ቃለ መጠይቅ፣ ጥቅምት 30፥ 2015 ዓ.ም.
[20] ሰሎሞን አበበ፣ የተቆረሱ ነፍሶች፣ 79
[21] ሰሎሞን አበበ (መጋቢ)፣ በግል የተደረገ ቃለ መጠይቅ
[22] ሰሎሞን አበበ (መጋቢ)፣ በግል የተደረገ ቃለ መጠይቅ
1 comment
በጣም ምርጥ ጽሑፍ ነው። አስተማሪ ብቻ ሳይሆን፣ ራሳችንን እንድንመለከት የሚጋብዝ ገሳጭ መልእክት አለው። ራሴን ተመልክቼበታለሁ። ደጋግመህ ጻፍ።