[the_ad_group id=”107″]

የመጽሐፍ ቅኝት

“የትሩፋን ናፍቆት”

ርእስ፡- “የትሩፋን ናፍቆት”
ጸሐፊ፡- ሰሎሞን አበበ ገብረ መድኅን
አሳታሚ፡- ሰሎሞን አበበ ገብረ መድኅን
የታተመበት ዓመት፡- 2006 ዓ.ም. 
ገጽ፡-264
ዋጋ፡- 55.00 ብር

መግቢያ

ይህ ግምገማ በሦስት ክፍሎች የሚከፈል ሲሆን፣ የመጀመሪያው ክፍል መጣጥፎችን ለመገምገም እንደ ሐሳብ ማዕቀፍ የሚያገለግሉንን ጥያቄዎች የሚያስተዋውቅ ነው። በሁለተኛው ክፍል በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ በመመሥረት “በትሩፋን ናፍቆት” ውስጥ የተሰባሰቡትን መጣጥፎች የሚመለከት ሲሆን፣ በመጨረሻም መደምደሚያ ይሆናል።

1. የግምገማው የሐሳብ ማዕቀፍ

በትሩፋን ናፍቆት ውስጥ የተካተቱትን መጣጥፎች ጸሐፊው ከቀረጸለን ዓለም (narra ve world) አንጻር ለመረዳት የሚያግዙ ሦስት ሥነ ጹሑፋዊ ጥያቄዎች ለዚህ ግምገማ ማዕቀፍ ሆነው ያገለግሉናል።

ሀ. የመጀመሪያውጥያቄጸሐፊውመጣጥፎችንለመጻፍ የተነሣበት መነሻ፣ መድብሉ ተደራሽ ሊያደርገው የፈለገው አካል፣ ጸሐፊው የሚያነሣቸውን ጉዳዮች የሚያይበትን ዕይታ ለማየት ይሞክራል፤

ለ. ሁለተኛው ጥያቄ የመጣጥፎቹን ይዘት እና የሚያነሡት የመከራከርያ ነጥቦች ላይ ያጠነጥናል፤

ሐ. ሦስተኛው እና የመጨረሻው ጥያቄ ጸሐፊው ሐሳቡን ለማጐልበት የተጠቀመባቸውን የቋንቋ እና ሥነ ጹሑፋዊ ሥልቶች እንዲሁም የመጽሐፉን መዋቅር እና የሐሳብ ፍሰት ይፈትሻል።

2. ግምገማ

ሀ. “የትሩፋን ናፍቆት” ከጸሐፊው ዓላማ፣ ዕይታ እና ተደራሽ ከአደርገው አካል አኳያ

ጸሐፊው “መሿለኪያ” ብሎ በሰየመው መግቢያ ላይ በመድብሉ ውስጥ የተካተቱት ጽሑፎች የተጻፉበት ዋነኛ መንሥኤ “ክርስቶስን ከማክበር፣ መንግሥቱን ከመናፈቅና እናንተን ውዶቹን ከመውደድ ውስጥ የተመዘዘ” እንደ ሆነ ይነግረናል። ከእዚህም በመነሣት የዚህ መድብል ተደራሽ ክፍል በክርስቶስ ቤተ ሰብ ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች እንደሆኑ እንረዳለን። ይህን ዕሳቤ የሚያጠነክረውም ጸሐፊው “ትሩፋን” የሚለውን እና በመጽሐፉ ርእስ ውስጥ የተጠቀመበትን ቃል ዐውዳዊ አፈታት ሲያቀርብ “ቅሬቶች፣ እምነታቸው የጸና፣ ምግባራቸው የቀና፣ ከብዙኀኑ በተለየ መንገድ ለኪዳኑ ታማኝ በመኾን የሚጸኑ” እንደ ሆኑ ትርጓሜ ይሰጣል። በእነዚህ መጣጥፎች ውስጥ ግልጽ የሚሆንልን አንድ እውነታ በጸሐፊው ዕይታ ትሩፋን አንድን ቤተ እምነት ወይም የሃይማኖት ጐራ የሚወከሉ ሳይሆኑ የእግዚአብሔርን ቃል የተጠሙ፣ የክርስትናን ህዳሴ የሚመኙ፣ በማንኛውም ክርስቲያናዊ ቤተ እምነት ታዛ ሥር የሚገኙ ግለ ሰቦች መሆናቸውን ነው። ከዚህም የተነሣ ጸሐፊው በተለያዩ መጣጥፎች ውስጥ በሚነሡ ጉዳዮች ላይ ከኦርቶዶክሳዊውም ሆነ ከወንጌላዊው ዐውድ ያስተዋላቸውን እክሎች መሳ ለመሳ ያቀርብልናል። ይህ የመጣጥፎቹ ጠንካራ ጐን ብዬ ከምፈርጃቸው አበረታችና ይበል የሚያሰኙ ገጽታዎች አንዱ ነው።

እዛው መግቢያው ላይ ጸሐፊው ይህን መድብል ሲያዘጋጅ ዓላማው “ራሳችንን ዐይተን ለመታዘብ፣ ከጉድለታችን ለመታረም እንጐተጐት” (ገጽ 17) ዘንድ እንደ ሆነ ይነግረናል። ከዚህም በመነሣት በመጣጥፎቹ ውስጥ የተካተተው ማኅበረ ሰባዊ ሂስ የቀረበበት ዕይታ ገለልተኛ ከሆነ እና ከማኅብረ ሰቡ ውጭ ሆኖ ነገሮችን የሚያጠና (e c) ሳይሆን፣ የማኅበረ ሰቡ አካል በሆነ እና ከማኅበረ ሰቡ ዕቅፍ ውስጥ ምልካታውን የሚያካፍል (emic) እንደሆነ ለመረዳት እንችላልን። ይህ አመለካከትም በተለያየ መልኩ ተንጸባርቆ ይገኛል። ከሁሉም “እኛ” የሚለው ድምፅ ጉልሕ እንደ መሆኑ ጸሐፊው ከታዘባቸው እክሎች ራሱን ንጹሕ ለማድረግ እንዳልሞከረ ስለሚያመላክት መፍትሔውም በእኛ እጅ እንዳለ ሲጠቁመንም ለመቀበል አያዳግተንም። በርግጥ የተወሰነ ገለልተኝነት መፍጠር ካልተቻለ በአንድ ማኅበረ ሰብ ውስጥ ሆኖ ሂስን ማቅረብ የዕይታ መጥበብን ሊያስከትል ይችላል።

በተለያዩ መጣጥፎች ውስጥ ተንጸባርቀው የምናስተውላቸው የጸሐፊው ጠንካራ ስሜቶች የሚመነጩትም ከዚሁ ዕይታ እንደ ሆነ መገመት ይቻላል። ለምሳሌም ያህል “ባለቤት የናቀው አሞሌ” በተሰኘው ጽሑፍ ውስጥ በአንድ ወቅት ተነሥተው የነበሩ የተሓድሶ እንቅስቃሴዎች ያጋጠማቸውን እክል በማውሳት ጸሐፊው የራሱን እማኝነት የሚያካፍልበት ክፍል ማውሳት ይቻላል (ገጽ 37)።

በተወሰነ መንገድ በጽሑፎቹ ውስጥ የምናየው ጥልቅ ስሜት ጸሐፊው ላነሣቸው ጉዳዩች የሰጠውን ጉልሕ ስፍራ እንድንረዳ ብቻ ሳይሆን፣ እኛ አንባቢዎች ጽሑፎቹን እንደ ቀዝቃዛ ማኅብረ ሰባዊ ሂሶች ወይም ትንታኔዎች ብቻ እንዳናነባቸው ያደርገናል። ሆኖም ግን በአንዳንድ ስፍራ ይሄ ጠንካራ ስሜት የምሬት ወይም የፍረጃ ቃና ሲይዝ እናስተውላለን። ጸሐፊው ከሚያነሣቸውም ምሳሌዎች (ለምሳሌ ገጽ 208 – 13) ጀርባ ያለው ሃቅ ባያጠራጥርም ምናልባትም አብዛኞቹ የአንድ ማኅበረ ሰብ እክል ሳይሆኑ መንሥኤው የሰው

ዘር የጋራ ሊባሉ የሚችሉ ችግሮች ከመሆናቸው አንጻር የጸሐፊው ምልከታ ጥልቅ ቁጣ እና ትዝብት የፈጠረው ምሬት ውጤት ይሆን ብለን እንድናስብ ያደርገናል።

ሁንም ከመሿለኪያው ሳንወጣ ጸሐፊው በማያሻማ መልኩ መጣጥፎቹ ያዘሉት ሂስ ያነጣጠረበትን ማኅበረ ሰብ “ድሪቶ በለበሰ … ክፋት ኅሊናን በሚኮሰኩስበት ዘመን” ውስጥ መገኘቱን ከዚህም በመነሣት መፍትሔዎች በመፈለግ ሂደት ውስጥ የበኩሉን ሊያበረክት እንዳለ ይናገራል። በዚህም ረገድ ጸሐፊው ልንሄድባቸው የሚገቡንን መንገዶች ይጠቁመናል፤ ይህንንም የሚያጠነክሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እና ሌሎች ማስረጃዎችን ያቀርብልናል እንጂ፣ ‘እኔ የያዝኩት መፍትሔ ፍቱን መድኃኒት ነውና ያለማቅማማት ተጋቱት’ ብሎ አይሰብከንም። ይህም ጸሐፊው ለአንባቢው ያለውን ክብር እንዲሁም ደግሞ ያነሣቸው ጉዳዮችን ውስብስብነት መረዳቱን ያሳየናል።

ለ. “የትሩፋን ናፍቆት” ከጽሑፎቹ ይዘት እና መከራከርያ ነጥቦች አኳያ

ምንም እንኳን በ“ትሩፋን ናፍቆት” በተካተቱ መጣጥፎች ውስጥ አያሌ ጉዳዮች ቢነሡም በእኔ ዕይታ እነዚህ ጉዳዮች በሦስት ዋነኛ ጭብጦች ዙሪያ ያጠነጥናሉ። እነዚህም ቤተ ክርስቲያናዊ ተሓድሶ፣ ግለሰባዊ ተሓድሶ እና ብሔራዊ ተሓድሶ ናቸው።

ቤተ ክርስቲያናዊ ተሓድሶ፡- ቤተ ክርስቲያን በሞራላዊ እና መንፈሳዊ ተሓድሶ አልፋ በኅበብረተ ሰቡ ውስጥ በሚጠበቅባት ሥፍራ ላይ መቀመጧ የመጀመሪያው “የትሩፋን ናፍቆት” ነው ብንል የምንሳሳት አይመስለኝም። በአንባቢ ልብ ውስጥ ምኞትን የሚያጭሩ፣ የተሻለ ክርስቲያናዊ ተሞክሮን ከአድማስ ባሻገር እንድናይ እና ያን ናፍቆት እንድንጋራ የማድረግ ኀይል ያላቸው ትዝብቶችን ከምናስተውልባቸው መጣጥፎች መካከል “ስሙን መልሱልን” እና “ማፍረስም መሥራት ነው” በዐበይትነት የሚጠቀሱ ናቸው።

ቤተ ክርስቲያናዊ ተሓድሶን በተመለከተ ጸሐፊው በእነዚህ ጽሑፎች ውስጥ እና በሌሎች ሥፍራዎች ላይ የሰነዘራቸው ትችቶች የኢትዮጵያ ክርስትና እዚያም ቤት እዚህም ቤት የደረሰበትን መንታ መንገድ የሚያመለከቱ እና አስፈላጊ የሆነ የተሓድሶ መሥመሮችንም በሰከነ መልክ በመጠቆም የትሩፋንን ድርሻ የሚያመላክቱ ናቸው።

ግለ ሰባዊ ተሓድሶ፡- በትሩፋን ናፍቆት ውስጥ የምናገኛው ሁለተኛ መሪ ጭብጥ ግለ ሰባዊ ተሓድሶ ነው። “እንከራከር ወይስ ́እንጋደል ́?”፣ “የበርናባስ ብፅዕናዎች”፣ “መንገዱም ቢጠብ፣ ጠብን እንጠብ”፣ “ሕልም አንሸጥም” የተሰኙት መጣጥፎች በተለያየ መንገድ እያንዳንዳችን ወደ ራሳችን መለስ ብለን ነገሮችን እንድንቃኝ የሚጋብዙ ናቸው።

በተለይም ደግሞ “ቢዘገይም አይዘገይም” የተሰኘው መጣጥፍ ትንቢተ ዕንባቆም ላይ የተመረኮዘ ክሽን ያለ አብራሪ ስብከት (expository preaching) ላይ በመመሥረት የእግዚአብሔር ሰው፣ በዙሪያ በሚመለከተው ነገር ግራ እንደማይጋባ፣ ይልቁንም ወደ እግዚአብሔር ቀርቦ በማድመጥ እና በማምለክ ተሓድሶ እንደሚያገኝ ይነግረናል (ገጽ 75)። ከመጽሐፉ አጠቃላይ ዐውድም እንዲህ ያለው ሰው የዘመኑን ግራ መጋባት ከእግዚአብሔር ልዕልና እና ግርማ አኳያ በማየት በእምነት እግዚአብሔርን ከሚጠባበቁት ትሩፋን ወገን ይሆናል።

ብሔራዊ ተሓድሶ፡- “ሴት ምናችን ናት” እና “በስሜት ስንከንፍ እውነትን እንዳንገድፍ” የተሰኙት መጣጥፎች ቀጥተኛ ማኅበረ ሰባዊ ትችቶች ሲሆኑ፣ ብሔራዊ ተሓድሶ (እዚህ ጋር በደፈናው የግብረገብ ነገር እንጂ መንፈሳዊውን ብቻ አያመለክትም) ያልነውን ጭብጥ ምሳሌ ሆነው ያገለግላሉ። ጸሐፊው ሥር ሰደድ ማኅበረ ሰባዊ እክል የሆነውን በሴቶች ላይ የሚደርስ አካላዊ ጥቃትን እንደ መነሻ በመያዝ በማኅበረ ሰባችን ውስጥ ስለ ሴቶች ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን እንዲሁም ደግሞ በእነርሱ ላይ የሚደርሱ በደሎችን በማውሳት ሞራላዊም ሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊም ትችት ይሰጠናል። እንዲሁም ደግሞ “በስሜት ስንከንፍ እውነትን እንዳንገድፍ” በሚለው ጽሑፍ ውስጥ ሚዛናዊነት ስለ ጐደለው ቲፎዞነት ይወቅሰናል። እነዚህ ሁለት ጽሑፎች ላነሷቸው ሐሳቦች በሚመጥን፣ ቅልብጭ እና ጥርት ባለ የሐሳብ ፍሰት የመከራከሪያ ነጥባቸውን ያቀርባሉ። በተጨማሪም፣ ጸሐፊው ከቤተ ክርስቲያን ዐውድ ውጭም ሰፊውን ማኅብረ ሰብ ያማካሉ ጉዳዮች ላይ ያለውን የበሰለ ዕይታ በጨረፍታ እንድናይ ያደርገናል።

ከዚህ በዘለለ፣ ብሔራዊ ተሓድሶ ብለን ከፈረጅነው ጭብጥ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የሚመስሉ ሐሳቦች “ባለቤት የናቀው አሞሌ”፣ “እንከራከር ወይስ ‘እንጋደል’?” እና “የኔን መልክ ያያችሁ” በሚሉት መጣጥፎች ውስጥ እናገኛለን። ምንም እንኳን የተነሡት ትችቶች ተገቢ እና በተወሰነ መልክ አገራዊ ውይይቶች ላይ ያሉ ሐሳቦችን የሚያስቀጥሉ ቢሆንም ጸሐፊው ተደራሼ ብሎ ከያዘው ማኅበረ ሰብ እና ለጽሑፎቹም ከያዘላቸው ዋነኛ ዓላማ ውስኑነት የተነሣ ሊነኩት የሞከሩትን ይህን ጭብጥ በወጉ መሸከም የከበዳቸው ይመስላሉ። ለምሳሌም ያህል፣ “ባለቤት የናቀው አሞሌ” ያነሣው የባህል እና የማንነት ቅየጣ ጉዳይ ከዕለት ወደ ዕለት አሳሳቢነቱ እያየለ የመጣ ብሔራዊ ችግር እንደ ሆነ አያጠራጥርም። ጸሐፊው ምናልባትም ይህን 

አገራዊ ጉዳይ ከክርስትና ዕይታ አንጻር ሊያየው ሞክሮ እንደ ሆነ ክርስትና የኢትዮጵያ የባህልና የትውፊት አካል ከመሆኑም በላይ ቤተ ክርስቲያንም በብሔራዊ ታሪክ ላይ በጐም ክፉም አሻራዎቿን እንደማኖሯ ይበል የሚያሰኝ ነው። ሆኖም ግን በአንዳንድ ስፍራ ላይ አገራዊ የሆነውን ጉዳይ ቤተ ክርስቲያናዊ በሆኑ ማስረጃዎች ለመደገፍ ሙከራ አድርጓል። ይህ ደግሞ ምሳሌዎቹ (ገጽ 33፡ 43፡ 44) የብሔራዊውን ጉዳይ ለማሳየት አቅም እንዲያንሳቸው ምክንያት ሆኗል። ይህ በመሆኑም የነገረ ሐሳቡን ጠንካራ ጎን የሚገባውን ያህል እንዳናስተውል እክል ፈጥሯል።

3. “የትሩፋን ናፍቆት” ከቋንቋ፣ መዋቅር፣ እና ሐሳብ ፍሰት አኳያ

“የትሩፋን ናፍቆት” እየተረሱ የመጡ እና በአንዳንዶቻችን ዘንድ ፍጹም የማይታወቁ ቃላትን ማስታወስ እና ማስተዋወቁ አስደሳች ቢሆንም፣ ከመጽሐፉ ተደራሽ አካል አንጻር በአንዳንድ ሥፍራዎች ላይ ቀላል እና በሰፊው የተለመዱ ቃላት ሊያገለግሉ ሲችሉ ከበድ ያሉ እና በተወሰነ ጠባብ ዐውድ ውስጥ የተለመዱ ቃላት በጥቅም ላይ መዋላቸው ለአንባቢ ሊያዳግት ይችላል። ብሎም መጣጥፎቹ ወቅታዊ እና ማኅበረ ሰባዊ ጉዳዮችን ለሰፊው አንባብያን ለማድረስ፣ መፍትሔም ለመጠቆም የታቀዱ እንጂ ምሁራዊ ውይይት ወይም ጥናት አለመሆናቸው ቋንቋውን ለመረዳት ቀለል ያለ ቢሆን ኖሮ ተመራጭ ያደርገው ነበር።

“የትሩፋን ናፍቆት” ጠንካራ ጐን ተብሎ ሊወሳ ከሚገባቸው ነገሮች መካል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በጥቅም ላይ የዋሉበት ውበት ነው። ጸሐፊው የጽሑፉን ፍሰት ላለመረበሽ ከወሰደው ጥንቃቄ ባሻገር ጥቅሶች

ከሞላ በጐደል በትክክለኛ ስፍራ በተገቢ ሁኔታ ይህ ቀረህ በማይባል የአፈታት ብቃት ቀርበዋል። ይበልጡንም ደግሞ በአብዛኞቹ መጣጥፎች ውስጥ (በተለይም “ቢዘገይም አይዘገይም” እና “የበርናባስ ብፅዕናዎች”) የምናገኘው አብራሪ ስብከት አንባቢው ቃሉን በሕይወቱ መተግበር እንዲያስችለው የሚያግዝ ምክር ወይም ተዛምዶ አክሎ ማቅረቡ የጽሑፎቹን ጠቃሚነት እና ጥራት ከፍ ያደርጋል።

ጸሐፊው ከመጽሐፍ ቅዱስ ለጥቆም ምሳሌያዊ ትረካዎችን፣ ግለ ታሪኮችንና አባበሎችን እንዲሁም ከተለያዩ ምንጮች የተወሰዱ ምሳሌዎች እና ማብራሪያዎች በመጠቀም ጽሑፉን ያበረታል። ከእዚህ ጋር በተያያዘ ልንጠቅሰው የሚገባን በአንዳንድ ሥፍራዎች ላይ የቀረቡ ማብራሪያዎች ምንም ያህል ቁም ነገር ቢያዝሉ ወይም አስተማሪ ቢሆኑም የሐሳቡን ፍሰት የሚያቋርጡ እና ከጽሑፉ ጭብጥ ለማፈንገጥ የሚታገሉ በመሆናቸው በግርጌ ማስታወሻ ላይ፣ አልያም ለብቻ እንደ ተጨማሪ ማብራሪያ ቢቀርቡ ተመራጭ ይሆን ነበር።

ከቅርጽ እና የሐሳብ ፍሰት ጋር በተያያዘ የዐረፍተ ነገሮችን ጉዳይ ማንሣት ግድ ይሆንብናል። ይህን መድብል በዘፈቀደ በማንኛውም ገጽ ላይ ብንከፍተው ከአንድ በላይ የሚሆኑና ዐራት መሥመሮችና ከእዚያ በላይ ርዝመት ያላቸው ዐረፍተ ነገሮችን ማግኘታችን አየቀሬ ነው። አንዳንድ ስፍራ ላይ አንድ ዐረፍተ ነገር አንድ አንቀጽ ሆኖ እናገኘዋለን። ይህ የአንባቢን መረዳት የሚገዳደር እና ጸሐፊው ያነሣውን ነጥብ ለመረዳት የሚያዳግት ስለሆነ ከጽሑፎቹ ደካማ ጐኖች ይመደባል።

በመጨረሻም፣ “የትሩፋን ናፍቆት” የግርጌ ማስታወሻ እና የዋቢ መጽሐፍት አጠቃቀም እና አቀራረብ ማመስገን ግድ ይላል። ብሎም ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ ጸጋዬ ገ/መድኅን፣ ጌታቸው ኃይሌ፣ ከበደ ሚካኤል የመሳሰሉ አያሌ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት በአግባብ ጥቅም ላይ ውለው እና በዋቢ መጽሐፍት ዝርዝር ላይ በጉልሕ ተቀምጠው መገኘታቸው አስደሳች ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ጥናትም በር ከፋች ነው።

መደምደሚያ

በእዚህ ግምገማ ለማሳየት እንደሞከርሁት “የትሩፋን ናፍቆት” የመጣጥፎች መድብል ጸሐፊው በምድራችን ቤተ ክርስቲያናዊ፣ ግለ ሰባዊ እና ብሔራዊ ተሓድሶ አስፈላጊ እንዲሆን ያደረጉትን ማኅብረ ሰባዊ ሕጸጾች ያሳየናል። የእግዚአብሔርን ቃል፣ እማኝ ታሪክን፣ ባህላዊም ሆነ ዘመናዊ አስተሳሰብን ግብዓት አድርጐ ለእነዚህ እክሎች መፍትሔ ያለውንም መንገድም ይጠቁመናል። ከእዚህም በመነሣት ምንም እንኳን በየትኛውም መጣጥፉ ላይ በግልጽ ባይሰፍርልንም “የትሩፋን ናፍቆት” ሁሉን አቀፍ ተሓድሶ ናፋቂ እንደ ሆነ መገመት እንችላለን።

ቃል፤ ምጡቅ፣ ፈጣሪ ኵሉ፣ ሥግው

በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ። ዘፍ. 1፥1

በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። እርሱም በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ። ዮሐ 1፥1-2

በመጀመሪያ ነበርና ከሁሉ በፊት ቃል ኖሯል፤ መጽሐፉ ብሏል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

ዳገትና ተስፋ

ልጆች ሳለን በሚነገሩን ጣፋጭ ተረቶች በኩል አጮልቀን የምናያቸው የሕልም ዓለማት ነበሩን። (ርግጥ፣ በነ “አያ ጅቦ” ታሪክ ብቻ ላደገ ልጅ ይህ አባባል አይሠራም።)

ተጨማሪ ያንብቡ

ጋሽ በቀለ ይናገራል

መጋቢ በቀለ ወልደ ኪዳን ለአብዛኞቹ አንባቢዎቻችን የምናስተዋውቃቸው ዐይነት ሰው አይደሉም። በአጭሩ ለዐርባ ዓመታት ያህል በዘለቀው አገልግሎታቸው፣ መጋቢ ከሆኑባት የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ባሻገር ብዙዎቹን አብያተ ቤተ ክርስቲያናት፣ ከተማ ገጠር፣ አገር ቤት ውጪ አገር ብለው ያገለገሉ መሆናቸው፣ በወጣቱም ሆነ በቀደሙት ዘንድ ታዋቂ አድርጓቸዋል። ለዚህ ነው የምናስተዋውቃቸው ዐይነት ሰው አይደሉም ማለታችን። መጋቢ በቀለ በብዙዎች ዘንድ “ጋሽ በቄ” በሚል ስም ነው የሚጠሩት።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.