
ወርኀ ጽጌ ወስደት
“ወርኀ ጽጌ ወስደት” የተሰኘው ይህ ጽሑፍ፣ በወንጌላውያኑ ዘንድ ብዙ ትኩረት ስለማይሰጠውና ጌታ ኢየሱስ በሕጻንነቱ ወራት ከእናቱ ማርያምና ከዮሴፍ ጋር ወደ ግብፅ የተሰደደበትን ታሪክ መነሻ በማድረግ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ ሁነቱ ያለውን ትርክት ያስቃኛል።
[the_ad_group id=”107″]
እንደሚታወቀው የመንፈስ ቅዱስን ስጦታዎች በሚመለከት በወንጌላውያኑ ዘንድ ሁለት የተለያዩ ቡድኖች ተፈጥረዋል። የመንፈስ ቅዱስን ስጦታዎች በሚመለከት ከሚኖረን አቋም የተነሣ በአንዱ ቡድን ውስጥ መመደባችን የማይቀር ቢሆንም፣ ሌላኛውን ቡድን ማውገዝና በእምነቱ ላይ መፍረድ ግን ተገቢ አይደለም። በሁለቱም ጎራ ውስጥ ቤተ ክርስቲያንን በብዙ ያነጹና የጠቀሙ ወገኖች እንዳሉ ዐውቃለሁ። በአቋማቸው ከእኛ ስለተለዩ ብቻ ሌሎችን ማግለልና ከእነሱ ምንም ዐይነት በጎ ነገር እንዳልተቀበሉ በመካድ በተቃራኒው መንገድ ለብቻ ለመሮጥ መሞከር አላስፈላጊ አካሄድ ይመስለኛል። ስለ ሁሉም ነገር ፍጹም የሆነ ዕውቀት ስለማይኖረንና የሁል ጊዜ የቃሉ ተማሪዎች እንደ መሆናችን መጠን የራሳችንን እምነት ዘወትር በትሕትና የመፈተሽና ለራሳችን ጊዜን የመስጠት ባሕል ብናዳብር በብዙ እናተርፋለን፤ ከሌሎችም ለመማር አቅሙ ይኖረናል።
በየሚዲያው የሚታዩት የግራ ቀኝ ክርክሮች ግልጽና ሳቢ አይደሉም። አንዳንዶቹም ከተራ ብሽሽቅና ስም ማጉደፍ ሲዘሉ አይታዩም። በእነዚህ ክርክሮች መካከል ከሁሉም ይልቅ የሚጎዳው የዳር ተመልካቹ መሆኑ ግልጽ ነው። ከዚህ የሚዲያ ሰልፍና ግርግር ውስጥ መውጣት ለአንዳንዶቻችን ይከብዳል፤ ነገር ግን፣ ብንሞክረውና ምንም ነገር ከማድረጋችን በፊት መረጋጋትንና ሰከን ማለትን ብንመርጥ ራሳችንንና የሚሰሙንን እናድናለን። ይህ ወንድማዊ ምክር ራሴንም የሚያጠቃልል መሆኑን እያጸናሁ ወደ ዋናው ዐሳቤ ልግባ።
እኔ እንደማስበው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ከተቀመጡት አስተምህሮዎች መካከል አንዱ ስለ መንፈስ ቅዱስ የሆነው አስተምህሮ ነው።
ስለ መንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ቀጣይነት ሳስብ ወደ አእምሮዬ ፈጥኖ የሚመጣውና ግራ የሚያጋባኝ ነገር ቢኖር፣ ስጦታዎችን በተመለከተ በእኛ መካከል ልዩነቶች መፈጠር መቻሉ ጕዳይ ነው።
ይህ የግል ግርምታዬን ወደ ጎን ላድርገውና ልዩነቶችን እንዴት ማስተናገድ እንዳለብን ጥቂት ልበል። ልዩነቶች መፈጠር አልነበረባቸውም ወይም ግልጽ በሆኑ አስተምህሯዊ ልዩነቶች ሊፈጠሩ አይችሉም የሚል ግትር አቋም የለኝም። ነገር ግን፣ በእኛ መካከል የሚፈጠሩ ልዩነቶችን በማስተዋልና በዕውቀት በመያዝ አንዳችን ከሌላችን ለመማር በሚፈልግ ሰፊ ልብ ልንኖር ይገባናል። ስጦታዎችን በተመለከተ የሚፈጠሩ ልዩነቶችን የጠብና የመለያያ ምክንያት አድርገን መውሰድ የለብንም። እንዲሁም የአዋቂና የአስተዋይ ምላሽ ከማቅረብ ይልቅ ሌሎችን ለመስደብና ለማንጓጠጥ መድፈር ከማናችንም አይጠበቅም። በተጨማሪም የማይገናኙ ዐሳቦችን በማያያዝ፣ “እንዲህ የሆነው፣ እንዲህ ስለ ሆነ ነው” ከሚል የአስተሳሰብና የሙግት ሕጸጽ ልንጠበቅ ይገባናል።
በተለያዩ ርእሰ ጕዳዮች ላይ በየሚዲያው የሚደረጕትን ክርክሮች አበጥሮና ፈትኖ በመገንዘብ፣ የራሱን አቋም መውሰድ ይችል ዘንድ በቍጥር የሚበዛውን የእምነት ማኅበረ ሰብ በጥቂቱ ለመርዳት የራሴን እምነት በሚከተለው መልኩ አቅርቤያለሁ።
ስለ መንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች መቀጠልና መቈም ብዙ የተጻፉ፣ የተባሉና የተነገሩ ነገሮች አሉ። ስለ መቀጠሉ ከማምንበት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል የመጨረሻው ዘመንን የሚመለከተው አንዱ ነው። በተቋርጧላውያን (Cessationist) አመለካከት፣ መንፈስ ቅዱስ ከክርስቶስ የመዋጀት ሥራ ጋር ዐብሮ የሚሄድና ልክ እንደ ክርስቶስ የመዋጀት ሥራ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተፈጸመ ተደርጎ ይወሰዳል። ከዚህም የተነሣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ዘመነ ፍጻሜያዊ ሳይሆን፣ ንዑስ ዘመነ ፍጻሜያዊ ባሕርይ ስላላቸው ከሐዋርያዊው ተልእኮ ጋር ዐብረው ተፈጽመዋል በማለት ዐሳባቸውን ያቀርባሉ። ለዚህ ዐሳባቸው እንደ ማስረጃ የሚያቀርቧቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት በድነት ትርክት ማዕቀፍ ውስጥ አስቀምጠው ይተረጕሟቸዋል። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የተጻፈውም በመዋጀት ታሪክ አወቃቀር (Redemptive-Historical Structure) መሆኑ ለሙግታቸው መሠረት ሆኗቸዋል።
መንፈስ ቅዱስ ዘመነ ፍጻሜያዊ መሆኑ በስጦታዎቹ ቀጣይነት ከሚያምኑት ይልቅ መቈማቸውን ለሚያምኑት ጠንካራ መከራከሪያ እንደ ሆነ ይታሰባል። የዚህ ምክንያት ደግሞ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን፣ በተለይም የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የማይደገም የድነት ታሪክ ጅማሬ ማሳያ ተደርጎ በመወሰዱ ነው። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ በበዓለ ኀምሳ ቀን ለቤተ ክርስቲያን መሰጠቱ የመቤዠትን ሥራ ሙሉ ከማድረግ በቀር፣ በቀጣዮቹ የቤተ ክርስቲያን ዘመናት የማይደገም ኹነት ይሆናል ማለት ነው። በዓለ ኀምሳ በድነት ታሪክ ውስጥ የመጨረሻው ነውና አይደገምም። ከድነት በኋላ የሚመጣ ሁለተኛ ልምምድ አይደለም። ስለዚህ የኢየሱስ ሞት፣ ትንሣኤና የመንፈስ ቅዱስ መውረድ የማይነጣጠሉ ከመሆናቸውም በላይ፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተፈጸሙ ናቸው። ከዚህም አተረጓጐም የተነሣ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ የምናገኛቸው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎቸ መሰጠት በሐዋርያዊው የወንጌል ተልእኮ ማዕቀፍ ውስጥ የሚታዩ እንጂ፣ በዓለ ኀምሳ በሌሎች መደገሙን አያሳይም። ነገር ግን፣ አንዴ የመጣው መንፈስ ቅዱስ ስላለ አማኞች የተለያዩ ልምምዶችን ሊለማመዱ ይችላሉ። ይህ አመለካከት የተቋርጧላውያን (Cessationist) ነው።
ከዚህ አመለካከታቸው የተነሣ በ1ቆሮንቶስ 12፥9-10 እንደተዘረዘሩት ዐይነት ስጦታዎች ዛሬም ስለመኖራቸው ይጠራጠራሉ። እነዚህ ስጦታዎች ከሐዋርያዊ የወንጌል ተልእኮ ጋር ተፈጽመዋል እንጂ አልቀጠሉም የሚል አቋም ይይዛሉ (ዕብራውያን 2፥3-4)። እንዲሁም እነዚህ ስጦታዎች የእውነተኛ ሐዋርያት ምልክቶች ናቸው እንጂ (2ቆሮንቶስ 12፥12)፣ ከሐዋርያት ዘመን በኋላ ስለ መቀጠላቸው አዲስ ኪዳን ማስረጃ አይሰጠንም ይላሉ። ከሁሉም በላይ ተቋርጧላውያን ቈሟል የሚሉት የመናገር ስጦታዎችን ነው። እነዚህም ትንቢት፣ ልሳንና ዕውቀትን የመናገር ስጦታዎች ናቸው (1ቆሮንቶስ 12፥8-10፤ ሮሜ 12፥6-8)። ይህ አመለካከት እነዚህን ስጦታዎች ከሐዋርያትና ከነቢያት አገልግሎት ጋር ዐብረው እንደ ተፈጸሙ ያስባል። ምክንያቱም ክርስቶስ፣ ሐዋርያትና ነቢያት የቤተ ክርስቲያንን መሠረት ከመጣል ጋር ስለሚያያዙ ነው (ኤፌሶን 1፥20-22፤ 4፥8-10፡ 13)።
የዚህ አመለካከት መሠረቱ ድነታዊ የሆነው ትርክት (redemptive-historical) ማዕቀፍ ነው። በዚህም ማዕቀፍ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ሙሉ የድነት ትርክትን ይዟል። ስለዚህም የመናገር ስጦታዎች ከሐዋርያትና ነቢያት ተልእኮ መጠናቀቅና ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና መዘጋት ጋር ዐብረው ተፈጽመዋል። መቀጠላቸውን ከተቀበልን የመጽሐፍ ቅዱስን ቀኖናና በቂነቱን ማመቻመች ተደርጎ ይወሰዳል።
የመጀመሪያው የክርስቶስ መምጣት ዘመንን “የመጨረሻውና የሚመጣው ዘመን” በሚል ለሁለት ከፍሎታል። ይህ የሁለት ዘመን ንድፍ (model) በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ በስፋትና በግልጽ ተገልጦ እናገኘዋለን። ይህ የሁለቱ ዘመናት ዐሳብ ስለ መጨረሻው ዘመን ያለንን አረዳድ በእጅጉ ከመወሰኑም በላይ፣ የምንይዘውን ግንዛቤ መልክና ቅርጽ እንዲኖረው ያደርገዋል። የአሁኑን ዘመን በሚመለከት (ማቴዎስ 12፥32፤ ሉቃስ 16፥8፤ 20፥34፤ ሮሜ 12፥2፤ 1ቆሮንቶስ 1፥20፤ 2፥6፤ 3፥18፤ 2ቆሮንቶስ 4፥4፤ ኤፌሶን 1፥21፤ 2፥7፤ 1ጢሞቴዎስ 6፥19) መመልከት ይቻላል። ከዚህም የሁለት ዘመናት አከፋፈል የተነሣ መጽሐፍ ቅዱስ እውነታዎችን በሚመለከት ከሁለቱ በአንዱ አድርጎ ያቀርብልናል። ከሁለቱ ዘመናት ውጪ ሌላ ዘመን አልነበረም፤ አይኖርምም። ጊዜ በሁለቱ ዘመናት ተጠቃልሏል። የሰዎችም ታሪክ ከሁለቱ ዘመናት ውጪ ሊሆን አይችልም። በሁለቱ ዘመናት መካከልም ሌላ ዘመን የለም። ከሚመጣው ዘመንም ቀጥሎ ሌላ ዘመን አይኖርም። የሚመጣው ዘመን ዘላለም ነውና።
አዲሱ ዘመን ለመጀመሩ ማብሰሪያው የክርስቶስ የመጀመሪያው መምጣትና የመንፈስ ቅዱስ መሰጠት ነው።
ያለንበት የመጨረሻው ዘመን በጊዜ ሂደት ተሻሽሎና ተለውጦ የሚመጣውን አዲስ ዘመን አይሆንም። በመጨረሻውና በሚመጣው ዘመናት መካከል ሰፊ ልዩነት አለ (ሉቃስ 20፥27-40)። አዲሱን ዘመን መቀላቀል የትንሣኤን ሕይወት መካፈል ነውና፣ በመጨረሻው ዘመን ሆኖ ወደ አዲሱ ዘመን ለመግባት ሁለቱን ዘመናትን የከፈለውን የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤን መቀበልን ይጠይቃል። የክርስቶስ መምጣት የአሮጌው ዘመን መጨረሻ፣ የአዲሱ ዘመን ንጋት ምልክት ነው። አሮጌው እያለፈ አዲሱ ደግሞ እየነጋ ነው (1ቆሮንቶስ 2፥6፤ 10፥11፤ 1ዮሐንስ 2፥17፤ ዕብራውያን 9፥26)። ነገር ግን፣ ሁለቱ ዘመናት እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ ትይዩ ሆነው ይቀጥላሉ። ከዚህም የተነሣ ሁለቱ ዘመናት ተነባብረው ይጓዛሉ ማለት ነው። ስለዚህም የሚመጣውን ዘመን በረከቶች አሁን ባለንበት ዘመን እውነታዎች ውስጥ እየተለማመድናቸው እንኖራለን። ትንሣኤን፣ አዲስ ፍጥረት መሆንን፣ መጽደቅን ወዘተረፈ አግኝተናል። ደግሞም ከአሁኑ ዘመን ክፉ ነገሮች ጋር እየታገልንና በዚህም ምክንያት እየቃተትን እንኖራለን።
ይህ የሁለቱ ዘመናት መልክ (ሞዴል) ስለ መንፈስ ቅዱስ ያለንን አረዳድ ይወስነዋል። የአሁኑን ዘመን የቤተ ክርስቲያን ቈይታ በሚመለከት ለማሰብም ለመናገርም የሚቻለው ከመንፈስ ቅዱስ አንጻር ብቻ ነው። መንፈስ ቅዱስ ከክርስቶስ ቀጥሎ ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠ ስጦታ ነው (ገላትያ 4፥4-6)። እግዚአብሔር አባት ልጁን ላከ፤ ቀጥሎም መንፈሱን። ይህ የታሪክ እውነታ ያለንበትን ዘመን አስረጅቶ አዲስን ዘመን በእኛ ውስጥ እንዲጀምር አድርጎታል። አዲሱ ዘመን ለመጀመሩ ማብሰሪያው የክርስቶስ የመጀመሪያው መምጣትና የመንፈስ ቅዱስ መሰጠት ነው።
ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል አጋንንትን ማስወጣቱ የእግዚአብሔር መንግሥት በእርሱ ሁኔታ ለመምጣቷ ምልክት እንደ ነበረው ሁሉ በቤተ ክርስቲያንም መንፈስ ቅዱስ መሥራቱን መቀጠሉ የመንግሥቱ መምጣት ከክርስቶስ ዐልፎ ለተቀበሉት ሁሉ እንደ ሆነ ማስረጃ ይሆናል።
የክርስቶስ የመጀመሪያው መምጣት የሚመጣውን ዘመን በአሁኑ ክፉ ዘመን እንዲጀምር አድርጎታል። አዲሱ ዘመን የጀመረው አሮጌው እያለ ነው። ይህን “የተፈጸመና የሚፈጸም” ወይም “የመጣና የሚመጣ” ወይም “የሆነና የሚሆን” ብለን የምንጠራው የዘመን ፍጻሜ (“already, but not yet” aspect of eschatology) እውነታ ነው። ለምሳሌ የሙታን ትንሣኤ የአሁኑ ዘመን ሲያልቅና ሲፈጸም የሚሆን እውነታ ነው። ነገር ግን፣ ኢየሱስ በአሮጌው ዘመን መካከል ከሞት ተነሥቷልና ትንሣኤ ሆኗል። በክርስቶስ በሆኑትም ዘንድ በመንፈስ የሆነ ትንሣኤ ተከናውኗል (ሮሜ 6፤ ኤፌሶን 2)። ከዚህ የመጀመሪያው የአማኞች ትንሣኤ ጋር የመንፈስ ቅዱስ መምጣት የዘመን ፍጻሜ ምልክት ወይም መለኮታዊ ክንውን ነው። ጳውሎስ ትንሣኤንና መንፈስ ቅዱስን አያይዞ የሚጠቅሳቸው ከዚህ የተነሣ ነው (ሮሜ 8፤ 1ቆሮንቶስ 15)። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚያሳየን ኢየሱስን ከሞት ያስነሣው መንፈስ እኛንም ከሞት እንዳስነሣን፣ እንዲሁም በውስጥ ሰውነታችን እያደሰን እንደምንሄድ ነው።
አዲሱን ዘመን መቀላቀል የትንሣኤን ሕይወት መካፈል ነውና፣ በመጨረሻው ዘመን ሆኖ ወደ አዲሱ ዘመን ለመግባት ሁለቱን ዘመናትን የከፈለውን የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤን መቀበልን ይጠይቃል። የክርስቶስ መምጣት የአሮጌው ዘመን መጨረሻ፣ የአዲሱ ዘመን ንጋት ምልክት ነው።
ሐዋርያው ጳውሎስ ከቀደመው እምነቱ በመውጣት ወደ አዲስ ሕይወትና ዘመን መሸጋገሩን የተረዳው ከሞት የተነሣውን ክርስቶስን በደማስቆ መንገድ ከተገናኘ በኋላ ነበር። ይህ ክስተት ለጳውሎስ የለውጥ ክስተት ነበር። በተገለጠለት ክርስቶስ እንደ አንድ አይሁድ ይጠብቃቸው የነበሩ ተስፋዎች እንደ ተፈጸሙ ተረድቷል። በክርስቶስ አንድ፣ ልዩና አዲስ ዘመን እንደ ጀመረ ዐውቋል። ከዚህም የተነሣ በክርስቶስ የሆነ ሰው ሁሉ አዲስ ፍጥረት መሆኑን አብስሯል። በመሆኑም፣ የመንፈስ ቅዱስ መሰጠት በጳውሎስ ነገረ መለኮት ውስጥ ጕልህ ስፍራ አለው። ለጳውሎስ ይህ አዲሱ ዘመን ወይም የሚመጣው ዘመን ጅማሬ የመንፈስ ቅዱስ ዘመን ጅማሬ ሲሆን፣ የተበሰረውም በክርስቶስ መምጣት ነው። ከቀድሞው ከሕጕ ዘመን በተለየ መልኩ በመንፈስ ቅዱስ ዘመን ያሉት በሚልቅ የሕይወት ምልልስ ይኖራሉ (ሮሜ 8፥1-11፤ 1ቆሮንቶስ 2፥10-16)። በመንፈስ የሆነው ሕይወት የአዲሱ ዘመን ልዩ ምልክት ነው። በመንፈስ ያሉት በክርስቶስ አእምሮ እንዲያስቡና የእግዚአብሔርን ነገር እንዲረዱ ያስችላቸዋል። በመንፈስ የሆነው ሕይወት መገለጫ ፍሬዎችም አሉት (ገላትያ 5፥16-26)።
በተጀመረው አዲስ ዘመን ውስጥ የሚኖረው በመንፈስ የሆነው መንፈሳዊ ሕይወት በሙላት የሚመጣው ዘመን ቅምሻ ነው። የሚሞተው በማይሞተው፣ የሚበሰብሰው በማይበሰብሰው ሲለወጥ፣ የእግዚአብሔር ልጆች መቃተት ሲያበቃ፣ ያን ጊዜ በቅምሻ መልኩ የተካፈልነው መንፈሳዊ ሕይወት በሙላት ይገለጣል። በአሁኑ ዘመን የእግዚአብሔርን የድነት ወንጌል ጥሪ ሰምተው ምላሽ የሰጡ ይጸድቃሉ። የጸደቁትም በመጨረሻ ይከብራሉ (ሮሜ 8፥28-29)። እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ለበጎ ያደርገዋል። ይህ በጎ ነገር የልጁን መልክ መምሰል ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ታላቅ ድርሻ አለው። ከመንፈስ ቅዱስ ሥራዎች አንዱና ትልቁም ሰዎችን ሕያው ማድረግ ነው (ዮሐንስ 3፥8)። ይህ የታምራት ሁሉ ታምር ነው። ለእግዚአብሔር ሙታን የነበሩ ሕያዋን ሲሆኑ ማየት ያስደንቃል። ይህ በሰው አመክንዮ፣ ማስተዋልና ዕውቀት የሚሆን ሳይሆን፣ በመንፈስ ቅዱስ ብቻ የሚከናወን ታምር ነው።
በቤተ ክርስቲያንና በአማኞች ሕይወት ውስጥ የሚሠራው መንፈስ ቅዱስ ራሱ ዘመነ ፍጻሜያዊ ነው። መንፈስ ቅዱስና ዘመነ ፍጻሜ ስላላቸው የጠበቀ ግንኙነት ባለፉት የቤተ ክርስቲያን ዘመናት ብዙም ባይባልም፣ አሁን ግን ሊለያዩ እንደማይችሉ በብዙ ምሁራን ዘንድ ስምምነት አለ። የአዲስ ኪዳን ጸሐፍት በተለይም ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ መንፈስ ቅዱስ ፍጻሜያዊ ባሕርያት በስፋት ጽፏል። አሁን ባለው በአሮጌው ዘመን ቤተ ክርስቲያን እየኖረችና የተጀመረውንና የሚመጣውን ዘመን እየተጠባበቀች በመንፈስ ቅዱስ ኀይል አዲሱን የትንሣኤ ሕይወት ትለማመዳለች። የሚመጣው ዘመን በሙላት ሲመጣ የምንኖረውን የትንሣኤ ሕይወት አሁን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት እንለማመደዋለን። ይህ እውነታ በቤተ ክርስቲያን አንድነትና በሕይወት ፍሬዎቿ ብቻ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችም በኩል ይታያል።
መንፈስ ቅዱስ ከክርስቶስ መምጣት ቀጥሎ በማይደገም መልኩ በመምጣቱና የመዋጀትም ሥራ ሙሉ ስለ ሆነ ብቻ ፍጻሜያዊ አልሆነም። ስጦታዎችን መስጠቱና ቤተ ክርስቲያንን በየዘመናቱ በኀይል እያበረታ እስከሚቀጥለው ዘመን መምጣት ድረስ መቀጠሉም ፍጻሜያዊ ያደርገዋል። በርግጥም በማይደገም መልኩ አንዴ ወደ ሰዎች ወይም ሥጋ ወደ ለበሱ መምጣቱ ስጦታዎችን ለመስጠቱ መሠረት ነው። ከክርስቶስ የመዋጀት ሥራ ቀጥሎ በሰዎች ዘንድ ሊያድርና ሊኖር መምጣቱንና ስጦታዎችን መስጠቱን ማምታታት የለብንም። አንድ ጊዜ መምጣቱ የአዲሱ ዘመን ጅማሮ ከክርስቶስ ቀጥሎ ሁለተኛው ማብሰሪያ ነው። ስጦታዎችን መስጠቱ ግን በቀጣይነት የሚሆን ነው። ስጦታዎቹ ግን የእርሱን ሉዓላዊ አገዛዝ የሚተኩና ሰውንና የሰውን ዐሳብ ከተገለጠው የወንጌል እውነት በላይ የሚያደርጕ አይደሉም። እርሱ በስጦታዎቹ ብቻ የሚወሰን አይደለምና።
ከላይ ለማሳየት የሞከርኩት የሁለቱ ዘመናት ቅርጽ (ሞዴል) እንዲሁም በሆነውና በሚሆነው፤ በተፈጸመውና በሚፈጸመው መካከል ቤተ ክርስቲያን ያለችበት ውጥረት ለስጦታዎች መቀጠል መሠረት ነው። በ1ቆሮንቶስ 13 ውስጥ ያለውን ዐሳብ ወስዶ እምነት፣ ተስፋንና ፍቅርን ብቻ ፍጻሜያዊ ማድረግና ስጦታዎችን ግን ንዑስ ፍጻሜያዊ ማድረግ ከክፍሉ ጸሐፊ ጋር በብዙ መልኩ መጋጨት ነው። የንባብ ክፍሉን ጸሐፊው ጳውሎስም ሆኑ ተደራሲያኑ በቆሮንቶስ የሚገኙ አማኞች የአዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ቀኖና እያሰቡ የሚተረጉሙት አይደለም። በክፍሉ ውስጥ እንደምናየው በድንግዝግዝ ማየት ፊት ለፊት ከማየት ጋር ተነጻጽሯል። ይህ ንጽጽር በትንቢት፣ በራእይ፣ በሌላም መንገድ በተዘዋዋሪ መልኩ የምናውቀውን ሙሉ ያልሆነ እውነትን ሙሉ ለሙሉ ፍጹም በሆነ መልኩ ከማወቅ ጋር የሚያያዝ ንጽጽር ነው። “ፍጹም የሆነ ሲመጣ” (ቁጥር 10) የሚለው ሐረግ የሚያሳየው ወደፊት የሚዘጋጀውን የአዲስ ኪዳን ቀኖናን ሳይሆን ከጌታችን ዳግመኛ መምጣት ጋር ተያይዞ
የሚመጣውን ፍጹም እውነታ (Eschatological Reality) ነው። ለዚህ ማስረጃው የጳውሎስ ነገረ ፍጻሜ ነው። ስለዚህ ክፍሉ እንዲያውም የስጦታዎችን መቀጠል ያሳያል። ስጦታዎች ልክ እንደ መስተዋት የሚመጣውን ፍጹም ዓለም እውነት የሚያሳዩ ናቸው እንጂ እስከ ተወሰነ ዘመን ድረስ ሠርተው ፍጹም በሆነ ነገር የተተኩ አይደሉም።
በአጭሩ ጳውሎስ በ1ቆሮንቶስ ምዕራፍ 13 የፍቅርን ቋሚነትና የስጦታዎችን ጊዜያዊነት እያነጻጸረ ነው እንጂ ከቅዱሳት መጻሕፍት በቀኖና መዘጋጀት ጋር ምንም ዐይነት ግንኙነት የለውም። በሐዋርያት ዘመን እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት የሚቆጠሩትስ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አይደሉምን? የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያንስ የተጻፈላት ጥቂት ደብዳቤዎች አልነበሯትምን? በመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን ይተላለፉ የነበሩት ትንቢቶች በሙሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖና ጋር የሚገናኙ አልነበሩም። በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባብ ክፍል ውስጥ ያለው ንጽጽር በስጦታዎች ወይም በስጦታዎች በተገለጠው እንደ መስተዋት በተገለጸው በተከፈለው እውነት እና ፊት ለፊት እንደ ማየት ተደርጎ በቀረበው ፍጹም የሆነው እውነት መካከል ሆኖ ሳለ የስጦታዎች መቋረጥን ከቀኖና መጠናቀቅ ጋር ማነጻጸሩ የመጽሐፍ ቅዱስን አተረጓጎም መሠረታዊ ሕግጋት መጣስና ለቃሉም ታማኝ አለመኾን ነው።
1ቆሮንቶስ 1፥4-8 ባለው የንባብ ክፍል ውስጥ በሙላት የሚመጣውን ዘመን ከስጦታዎች መቀጠል ወይም ሳይጓደል መሰጠት ጋር ተያይዞ ቀርቧል። የቆሮንቶስ አማኞች የጌታን መምጣት እየተጠባበቁ ሳሉ ከመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች እንደማይጎድሉ ክፍሉ በግልጽ ይናገራል። በመጀመሪያው እና በሁለተኛው የጌታ መምጣት መካከል ያለችው ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ የጀመረችውን ጉዞ የምትጨርሰው በጸጋ በሚሰጣት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች እየታነጸች ለመሆኑ ይህ የንባብ ክፍል ማሳያ ነው። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ ፍጻሜያዊ ፋይዳ ያለው ወደ ሰዎች በአንድ ዘመን የመጣ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በቀጣይነትም እስከ ጌታ ዳግመኛ መምጣት ቀን ድረስ በስጦታዎቹ ከቤተ ክርስቲያን ጋር መኖሩ ነው። ከሐዋርያት የወንጌል አገልግሎት መፈጸም ጋር ዐብሮ የተፈጸመና ቀጣይነት እንዳይኖረው በመንፈስ ቅዱስ የተደረገ ስጦታ ስለመኖሩ አዲስ ኪዳን ምንም ማስረጃ አይሰጠንም። ወንጌል የተሰበከው በሐዋርያት ዘመን ብቻ ስላልሆነ መንፈስ ቅዱስ በስጦታዎቹ በኩል ዛሬም የወንጌሉን ስብከት ያጸናል። እንዲሁም በወንጌሉ ወደ አዲሱ ፍጻሜያዊ መንግሥት ለተቀላቀሉት ስጦታዎችን በመስጠት ያንጻቸዋል።
ታዲያ የስጦታዎችን አስፈላጊነትንና ተገቢ አጠቃቀም የነገራቸው መሠረት ከተጣለ በኋላ በተመሠረተው መሠረት ላይ እንዴት ማነጽ እንዳለባቸው መልእክት ለጻፈላቸው ለቆሮንቶስ አማኞች አይደለምን? በሐዋርያትና በነቢያት አገልግሎት መሠረት ከተጣለ በኋላ ስጦታዎች አያስፈልጉም ወይ ቈመዋል ማለት ከሐዋርያው የ1ቆሮንቶስ መልእክቱ ጋር አይጋጭምን? የሐዋርያትና የነቢያትን አገልግሎት መሠረት ከመጣል ጋር ብቻ ማያያዝስ ተገቢ ነውን? ቤተ ክርስቲያንን በማስተማርና በማነጽ ይተጉ የነበሩ ታምራትና ምልክቶች ስለ ማድረጋቸው ያልተጻፈልን እንደ በርናባስና አጵሎስ ዐይነት ሰዎች ነበሩ። ምንም ዐይነት ደብዳቤም ያልጻፉ ሐዋርያት ነበሩ። እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን የሚናገረው በቃሉ ብቻ ነው ብሎ መደምደም ይቻላልን?
ኤፌሶን 4፥11-13 የተሰጡት ስጦታዎች የተሰጡበትን ዐላማና የሚያሳኩትን ግብ እንዲኹም እስከመቼ ድረስ እንደሚቀጥሉ ይነግረናል። የስጦታዎቹ ግብ ቤተ ክርስቲያን ፍጹም ሰው እስክትሆን ድረስ የሚሰሩ ለመሆናቸው ክፍሉ “ሙሉ ሰውም ወደመሆን…ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ” በሚሉ ሐረጎች ያረጋግጥልናል። ይህ ከሐዋርያትና ነቢያት አገልግሎት እንዲሁም መሠረት ከመጣል የሚያልፍ ቤተ ክርስቲያንን የማነጽና ፍጹም የማድረግ አገልግሎት ነው። ፍጹም መሆንና ወደ ክርስቶስ ማደግ በአንድ ዘመን የተፈጸመ ወይም የተከናወነና በሌላ ዘመን የማያስፈልግ ስላልሆነ ስጦታዎች በቤተ ክርስቲያን ዘመን ሁሉ መሥራታቸውን ተገቢ ያደርገዋል። ከስጦታዎቹ መካከልም በወጣላቸው መለኮታዊ የጊዜ ሰሌዳ ምክንያት በመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን ዘመን ሚናቸውን ስለተወጡ ቈመዋል የሚባልበት አንዳችም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለም። የኤፌሶን መጽሐፍ እንደ ሚያሳየን የእግዚአብሔር ዐሳብ ሁሉን ነገር በክርስቶስ ጌትነት ሥር ማድረግና መጠቅለል ነው። ወደ ላይ የወጣው ሁሉን ለመሙላት ነውና የዚህ ግቡ ጅማሬ ቤተ ክርስቲያን ናት። የዕቅዱ የመጀመሪያው ማሳያ ኾና አሁን በምድር አለች። የእርሱ ሙላት በሆነችው በቤተ ክርስቲያን የዘመን ፍጻሜ ሥራው አሁን ይታያል።
ከዚህም አስደናቂ ግብ የተነሣ ስጦታዎችን ሰጥቷል። የእነዚህ የአገልግሎት ስጦታዎች ዐላማም ቤተ ክርስቲያንን ወደ ክርስቶስ ፍጹም ሙላት ማድረስ ነው። ቤተ ክርስቲያን ወደ ሙላቱ ልክ እስካልደረሰች ድረስ የመንፈስ ቅዱስ ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ቀጣይነትን በድፍረት መቀበል ካለመቀበል የተሻለ ምክንያታዊነት ነው። እርሱ ከስጦታዎቹም በላይ ራሱን ለቤተ ክርስቲያን ሰጥቷልና የስጦታዎቹን ቀጣይነት ማሰብ ከባድ አይሆንም።
ሐዋርያው ጳውሎስ በገላትያ 3፡5 እንደሚነግረን የገላትያ አማኞች ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸው ቃል ኪዳናዊ ግንኙነት የተመሠረተው በእምነት እንጂ በሕግ ሥራ አለመሆኑንና መንፈሱን መስጠቱና በእነርሱም መካከል ታምራትን ማድረጕ ከድነታቸው ቀጥሎ የሆነ ነገር እንደሆነ ያሳየናል። በመቀጠልም በገላትያ 3፥13-14 በክርስቶስ ሞት ምክንያት ለአብርሃም የተሰጠው ተስፋ እንደተፈጸመ ያረጋግጥልናል። ተስፋው መንፈስ ቅዱስ ሲሆን እግዚአብሔር ለሕዝቡ የገባው ተስፋ ሁሉ መጠቅለያው ይኸው መንፈሱ ነው። ስለዚህም የእግዚአብሔር ኪዳናዊ ተስፋዎች በሙሉ በመንፈስ ቅዱስ ማንነትና ሥራ የተጠቀለሉና የተፈጸሙ ናቸው። ይህ መንፈስ የገላትያ አማኞች በክርስቶስ ሥራ ከባርነት ወደ ልጅነት በተሸጋገሩበት ወቅት የተቀበሉት የልጅት መንፈስ ነው (ገላትያ 4፥1-7)። ከዚህ የገላትያ መልእክት ዐሳብ የተነሣ በክርስቶስ ሥራ ላይ ባለን እምነት መንፈስ ቅዱስን መቀበላችን ብቻ ሳይሆን በቀጣይነት የመንፈስ ቅዱስን ኀይል መለማመዳችን የተረጋገጠ ነው። አሁን ፍጻሜያዊ የሆነው መንፈስ በቤተ ክርስቲያን ለመኖሩም ሆነ ለመሥራቱ መሠረቱ የአዲሱ ኪዳን እውነታ ነው። በቀደመው ኪዳን የተገቡ ተስፋዎች የተፈጸሙበትና ሰው ሁሉ ያለ ልዩነት አንድ የሆነበት ኪዳን ነውና ለሰው ሁሉ መንፈስ ቅዱስ መሰጠቱና በሰው በኀይል መሥራቱ ፍጻሜያዊ መንፈስ ያደርገዋል። ይህ የመንፈስ ሕልውና ግን የሕይወት መንፈሳዊ ፍሬ ከማፍራት ጋር ብቻ ያልተወሰነ ነው።
የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችም እግዚአብሔር ለጀመረው የዘመን ፍጻሜ ሥራው ማሳያ ናቸው።
በተፈጸመውና በሚፈጸመው መካከል ባለ ልዩነት መንፈስ ቅዱስን ለመረዳት በክርስቶስ የመጀመሪያውና የሁለተኛው መምጣት መካከል ያለውን ልዩነት መረዳት ተገቢ ነው። በመጀመሪያው መምጣት አዲስ ኪዳን ሆኗል። በሁለተኛው መምጣቱ ኪዳን ሙሉ ለሙሉ ይፈጸማል። መንፈስ ቅዱስ የአዲሱ ኪዳን ማኅተምና ማረጋገጫ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ መሢህና ጌታ መሆኑን ያጸናው የመንፈስ ቅዱስ መምጣት ነው። አዲስ ፍጥረትና ትንሣኤ ለመሆኑ ማሳያው የመንፈስ ቅዱስ መምጣት ነው። የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችም እግዚአብሔር ለጀመረው የዘመን ፍጻሜ ሥራው ማሳያ ናቸው። ክርስቶስ በአካል ያደርገው የነበረውን መንፈስ ቅዱስ በስጦታዎቹ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል ይቀጥለዋል። እስከ መቼ? ከተባለ እስከ ኢየሱስ መምጣት። በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የተበሰረው አዲስ ኪዳን እስካልተፈጸመና የተጀመረው አዲሱ ዘመን እስካልመጣ ድረስ አንዳንድ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ቈመዋል ብሎ ማሰብና ማመን መሠረት የለውም።
በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ እንደምናየው ለመጀመሪያ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ከመጣበት ከበዓለ ኀምሳ ቀን ጀምሮ፣ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ በሙሉ ስጦታውንም ይለማመዱ የነበረ ሲሆን፣ ይህ ክስተት በእነርሱና በዚያ ዘመን ብቻ የተወሰነ እንደ ነበረ የሚያመላክት አንዳችም ማስረጃ የለም። ለምሳሌ በሮም (ሮሜ 12፥4-8)፣ በቆሮንቶስ (1ቆሮንቶስ 1፥5-7፤ 12-14)፣ በሰማርያ (ሐዋርያት ሥራ 8)፣ በቂሣሪያ (ሐዋርያት ሥራ 10)፣ በአንጾኪያ (ሐዋርያት ሥራ 13፥1)፣ በኤፌሶን (ሐዋርያት ሥራ 19)፣ በቂሣርያ የነበሩት የወንጌላዊው የፊልጶስ አራት ሴት ልጆች (ሐዋርያት ሥራ 21፥9)፣ በተሰሎንቄ (1 ተሰሎንቄ 5፥19-20 እና በገላትያ (ገላትያ 3፥5) በእነዚህ በተጠቀሱት ምንባባት ውስጥ አማኞች የመንፈስ ቅዱስን ስጦታዎችን ይለማመዱ እንደ ነበር ለማየት እንችላለን።
መንፈስ ቅዱስ አንድ ነው። ስጦታዎቹ ግን ብዙ ናቸው። ከብዙ ስጦታዎቹ መካከል በቅደም ተከተል ወይም በተወሰነ ጊዜ የሚሠሩና የማይሠሩ ብሎ መከፋፈል አይቻልም። እያንዳንዱ ስጦታ ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ እስከ ተሰጠ ድረስ በቤተ ክርስቲያን ዘመን ሁሉ ይሠራል የሚለው ድምዳሜ ተገቢና ምክንያታዊ ነው።
ይህ የሚያስረዳን በወቅቱ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎችን መለማመድ በመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን የተለመደ ነገር እንደ ነበረ ነው። የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ጸሐፍት በመንፈስ ቅዱስ የሆነውን የአማኞችን ልምምድ ምን ሊመስል እንደሚችል ከዚህ በላይ በሆነ ግልጽነት እንዴት ሊያስረዱን ይችላሉ? ከመንፈስ ቅዱስ መምጣትና በቤተ ክርስቲያን በሥራዎቹ ከመገለጡ በላይ የመጨረሻው ዘመን ስለማርጀቱና አዲሱ ዘመን ስለ መንጋቱ ማስረጃው ምንድን ነው? ከስጦታዎቹ መካከል የመናገርና ታምራት የማድረግ ስጦታዎች ቈመዋል ለማለት የሚቀርበው ምክንያታዊው ማስረጃስ ምንድን ነው?
የመናገርና ታምራት የማድረግ ስጦታዎች ከሐዋርያት የወንጌል አገልግሎት ጋር ተፈጽመዋል። ስለዚህ ቀጣይነት የላቸውም የሚለው ሙግት አሳማኝ ያልሆነበት አንዱ ምክንያት ስጦታዎቹ የተሰጡት የሐዋርያትን የወንጌል አገልግሎት ለማጀብና በወንጌልን የሆነውን ድነት ለማጽናት ብቻ ተብለው ያልተሰጡ መኾናቸው ግልጽ ስለሆነ ነው። በርግጥ የክርስቶስም ሆነ የሐዋርያት አገልግሎት በእግዚአብሔር ምስክርነት የታጀበ ነበር (ዕብራውያን 2፥3-4)። ነገር ግን፣ ከስጦታዎቹ መካከል ጥቂቱን መርጦ የተሰጡበትን ዐላማና የሚሠሩበትን ጊዜ ወስኖ ለመናገር የሚያስደፍር ምን ማስረጃ አለ? እንዲውም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች የተሰጡበት ዐላማ በግልጽ በብዙ የንባብ ክፍሎች ተቀምጦልናል። ስጦታዎች የሚጠቅሙት የወንጌሉን ስብከት ለማጀብ ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽም ጭምር ነው (1ቆሮንቶስ 12፥7፤ 14፥3፡ 26)። መንፈስ ቅዱስ አንድ ነው። ስጦታዎቹ ግን ብዙ ናቸው። ከብዙ ስጦታዎቹ መካከል በቅደም ተከተል ወይም በተወሰነ ጊዜ የሚሠሩና የማይሠሩ ብሎ መከፋፈል አይቻልም። እያንዳንዱ ስጦታ ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ እስከ ተሰጠ ድረስ በቤተ ክርስቲያን ዘመን ሁሉ ይሠራል የሚለው ድምዳሜ ተገቢና ምክንያታዊ ነው።
በመሠረቱ ዕብራውያን ምዕራፍ 2 በምልክቶችና በታምራት የወንጌል ምስክርነት መረጋገጡን በዐላፊ ጊዜ መናገሩ በሌላ ጊዜ ሊደገም አይችልም ማለት አይደለም። ምልክቶች ወደ አንድ እውነት ጠቋሚዎች ናቸው። ታምራትም ወንጌልን ለማጽናት ብቻ ሳይሆን በተለየዩ ምክንያቶች ተደርገዋል። ዐላማና ግባቸው ይለያል። ጌታ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስላዘነ ታምራትን አድርጓል (ማቴዎስ 8-9)። ታምራት እንዲያደርግ ቢጠየቅም መጥፎና ጠማማ ትውልድ ምልክትን ይሻል (ማቴዎስ 16፥1-4፤ ሉቃስ 4፥23) ብሎ ለጥያቄያቸው ምላሽን ሰጥቷል። አንድ ሰው ፒያኖ የሚጫወተው ጣቶች እንዳሉት ለማረጋገጥ አይደለም። ፒያኖ የሚጫወተው ሙዚቃ ስለሚወድድ ነው። ፒያኖ የሚጫወተው ግን ጣቶች ስላሉት መሆኑ ግልጽ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር ምልክቶች የሚሰጠውና ታምራትን የሚያደርገው የወንጌልን እውነት ለማጽናት ብቻ ሳይሆን፣ ለሰው ያለውን መልካምነቱንና ፍቅሩን ለመግለጥም ጭምር ነው። በአንድ ዘመን ለነበረ ሕዝብ ብቻ የወንጌልን እውነት ለማረጋገጥና ለማጽናት ምልክቶችና ታምራት ካስፈለጉ፣ በሌላ ዘመን ላለ ሕዝብ የወንጌልን እውነት ለማረጋገጥና ለማጽናት ምልክቶችን ታምራት አያስፈልጉም ማለት ነውን? ወይስ ከመጀመሪያው ክፍለ ዘመን በኋላ ያለው ትውልድ የወንጌልን እውነት ለመቀበል መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ይበቃዋል ማለት ነውን?
እንደ እግዚአብሔር ሕዝብ የመታነጽ አስፈላጊነት በቤተ ክርስቲያን ዘመን ሁሉ ያለ ስለ ሆነ የስጦታዎች አስፈላጊነት አጠያያቂ ሊሆን አይችልም። በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የነበረችው ቤተ ክርስቲያን መታነጽ ያስፈለጋትን ያህል ዛሬም ያለችው ቤተ ክርስቲያን መታነጽ ያስፈልጋታል። ስጦታዎች ለቤተ ክርስቲያን ጅማሬ አስፈላጊ እንደ ነበሩ ሁሉ፣ ለቀጣይ እድገቷና ፍጽምናዋ ያስፈልጋሉ። በዚህም ምክንያት ልዩ ልዩ ስጦታዎች ተሰጥተዋታል። የተሰጧት ስጦታዎች ከሐዋርያት ማለፍ ጋር ዐልፈዋል ወይም ቈመዋል የሚባሉበት ምንም ምክንያት የለም። ሐዋርያት ባይኖሩም ስጦታዎቹን የሚሰጠው መንፈስ ዛሬም በቤተ ክርስቲያን ስለሚኖር፣ ስጦታዎችን የማይሰጥበት ምክንያት ወይም የተወሰኑትን ስጦታዎች ብቻ የሚሰጥበት ምክንያት አይኖርም።
ሕንጻ ሲሠራ መሠረቱ ቀድሞ ይሠራል። ለመሠረቱ የሚያስፈልገው መሣሪያም የተለየ ነው። መሠረቱ ከተጣለ በኋላ ግን መሠረቱን ለመጣል ከፍተኛ ሚና የነበራቸው መሣሪያዎች አያስፈልጉም። ይህ ለአንዳንድ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች መቈም አስረጂ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ዛሬም ቢሆን በየትኛውም ዘመን ወንጌልን ለመስበክና ቤተ ክርስቲያን በሌለችባቸው ስፍራዎች ቤተ ክርስቲያንን ለመትከልም ሆነ የተተከለችውን ለማሳደግና ለማነጽ ስጦታዎች ከፍተኛ ሚና አላቸው። መሠረቱ አንዴ የመጣው ክርስቶስ ጌታ ነው። ሌላ መሠረት የለንም። ስለ መሠረቱ የምንሰጠው ምስክርነት ግን ዛሬም በመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ይታጀባል። የመናገርና የታምራት ስጦታዎች ከሐዋርያት አገልግሎት ጋር የተቈራኙና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን የማይመለከቱ አድርጎ መውሰድ በምን አግባብ ይቻላል? ሰጪው እንደ ወደደ የሚሰጣቸውን ስጦታዎች ከተወሰኑ ሐዋርያትና ነቢያት ጋር ብቻ አጣብቈ በተወሰነ ዘመን ውስጥ እንደ ቈሙ መደምደም ከሰጪው ፈቃድና ስጦታዎችን ከሚሰጥበት ግብ ጋር መጋጨት ይመስለኛል።
ሐዋርያው ጴጥሮስ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ምዕራፍ 2 እንደተናገረው፣ የመንፈስ ቅዱስ መምጣት የአዲሱ ኪዳን ዘመን ልዩ ባሕርይ መሆኑን ያሳየናል። የመንፈስ ቅዱስ መምጣት የአዲሱን ዘመን ጅማሬ ማብሰሪያ ብቻ አልነበረም። የመንፈስ ቅዱስ መውረድ የሚመለከተው የመጀመሪያውን የጰንጠቈስጤ ቀን ብቻ ሳይሆን፣ እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ መምጣት ድረስ ያለውን ረጅም ዘመን የሚያካትት ነው። ስለዚህም ይህ በመጀመሪያውና በሁለተኛው የጌታ መምጣት መካከል ያለው ዘመን የመንፈስ ቅዱስ ዘመን ነው። በዚህም መንፈስ ቅዱስ ፍጻሜያዊ ባሕርይ አለው። በዚህ ዘመን መጀመሪያ ላይ ካልሆነ በቀር በቀጣዮቹ የቤተ ክርስቲያን ዘመናት መንፈስ ቅዱስ ራሱን በተወሰኑት ስጦታዎቹ ብቻ ገድቦ ይኖራል ማለት የሚቻልበት ምንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለም። ስለዚህም የልሳን፣ የትንቢትና ዕውቀትን የመናገር ስጦታዎች የአዲስ ኪዳን ማብሰሪያ ምልክቶች ወይም የሐዋርያቱ እውነተኛነት ማረጋገጫዎች ብቻ እንደ ሆኑ መደምደም ልክ አይደልም። ዘመኑ የመጨረሻ ዘመን ነውና መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ይኖራል። እንዲሁም በተለያዩ ስጦታዎቹ እየሠራ ቤተ ክርስቲያንን ወደ ፍጻሜው ቀን ያደርሳታል።
ሐዋርያው ጳውሎስ በ1ቆሮንቶስ 13፥8-12 “ፍጹም” የሆነው እስከሚመጣበት ቀን ድረስ ፍጹም የሆነ ዕውቀት ባይሰጡንም ስጦታዎች እንደሚቀጥሉ ያስረዳናል። በስጦታዎች በኩል የምናገኘው መንፈሳዊ ዕውቀት ልክ በመስተዋት እንደ ማየት ነው። ፍጹም የሆነው ሲመጣ ግን በከፊል ያወቅናቸው ነገሮች ሙሉ ይሆናሉ። ያን ጊዜ በመስተዋት (በድንግዝግዝ) ሳይሆን፣ ልክ ፊት ለፊት እንደ ማየት ነውና። ነገር ግን የሚጠበቀው የጌታ ቀን ወይም የሚመጣው አዲስ ዘመን እስከሚመጣ ድረስ በመስተዋት ማየታችን ይቀጥላል። የፍጹሙ መምጣት የድነት ዕቅድ መቋጫ (consummation)፣ የተጀመረው ኪዳን መደምደሚያ፣ የአዲሱ ዘመን የመጨረሻ መጀመሪያ ነውና፣ እስከዚያው ቀን ድረስ ክርስቶስ ሙላቱ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያንን በመንፈስ ቅዱስ ኀይል መባረኩንና ማስታጠቁን ይቀጥላል። ነገር ግን፣ ይህን ክፍል ተጠቅሞ በመስታወት ማየት የቻሉት የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት ነበሩ ማለት ትልቅ የአተረጓጎም ስሕተት መፈጸም ነው።
ይህን ከፊል ዕውቀት የሚያገኙት የተወሰኑ ሰዎች ብቻ እንዳልሆኑ በሌሎች የቆሮንቶስ የንባብ ክፍሎች ውስጥ ማየት እንችላለን (1ቆሮንቶስ 12-14)። ስለዚህ ትንቢትንም ልሳንንም እንዲሁም ዕውቀትን የመናገር ስጦታን መለማመድ ለሁሉም አማኝ የተሰጠ መሆኑንና ልምምዱ እንደሚቀጥል ከብዙ የአዲስ ኪዳን የንባብ ክፍሎች መረዳት ይቻላል።
ተቋርጧላውያን ስለ አቋማቸው ከሚያቀርቡት ማስረጃ አንዱና ዋነኛው ታምራት የማድረግ፣ የልሳን፣ የትንቢትና ዕውቀትን የመናገር ስጦታዎች የሐዋርያትን ትክክለኛነት ለማረጋገጥና ለማጽናት ተብለው መሰጠታቸውንና ከሐዋርያት ማለፍ ጋር ስጦታዎቹም ዐብረው እንዳለፉ የሚያነሡት ዐሳብ ነው (ዕብራውያን 2፥4፤ 2ቆሮንቶስ 12፥12)።
በርግጥ የእውነተኞቹ ሐዋርያት አገልግሎት በምልክቶች የታጀበ መሆኑ ምንም ጥያቄ የሚያስነሣ አይደለም። ስለ እውነተኛ ሐዋርያት እንደ ማስረጃ ምልክቶቹ ቢቀርቡም፣ የምልክቶቹ ግብ ግን ይኸው ብቻ ነበር ብሎ መደምደም ስሕተት ነው። የሐዋርያነት ምልክት የተደረጉት በዋናነት ታምራትና ድንቆች እንጂ ሁሉም ስጦታዎች አይደሉም። ምልክቶችና ድንቆች ስለ ኢየሱስ መሢህነትና ስለ ኢየሱስ መሢህነት የመሰከሩትን የሐዋርያት ምስክርነት አረጋግጠዋል። ከኢየሱስና ከሐዋርያት ውጪ በነበሩ ብዙ ሰዎች አገልግሎት ምልክቶችና ድንቆች ታይተዋል። ለምሳሌ እስጢፋኖስን (ሐዋርያት ሥራ 6፥8) እና ፊልጶስን (ሐዋርያት ሥራ 8፥5-8) መጥቀስ እንችላለን። ይህን ወጥነት ባለው መልኩ ሊያብራራ የሚችል የተቋርጧላውያን አመለካከት የለም።
ድንቆችና ምልክቶች የተሰጡት የሐዋርያትን መልእክት ትክክለኛነትና እውነተኛነት ብቻ ለማረጋገጥ መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ ለማረጋገጥ ከተቻለ፣ የተቋርጧላውያን አመለካከት ተገቢ የሚሆንበት ሰፊ ዕድል አለ። ነገር ግን፣ የምልክቶችንና የታምራትን ዐላማ የሐዋርያትን መልእክት እውነተኛነት ከማረጋገጥ ጋር ብቻ ገድቦ የሚያሳየን አንድም የአዲስ ኪዳን የንባብ ክፍል አናገኝም። እንዲያውም ምልክቶችና ታምራት ብዙ ዐላማ እንዳላቸው እናያለን። ከሐዋርያቱ ማንነት ጋር ባልተገናኘ መልኩም ምልክቶችንና ታምራት ተገልጠዋል።
ለምሳሌ እግዚአብሔርን ለማክበር (ዮሐንስ 2፥11፤ 9፥3፤ 11፥4፡ 40፤ ማቴዎስ 15፥29-31)፣ ለወንጌል ተልእኮ (ሐዋርያት ሥራ 9፥32-43) እና የአማኞችን ሕይወት ለማነጽ (1ቆሮንቶስ 12፥7፤ 14፥3-5፡ 26)። ስለዚህ ስጦታዎች ለተለያየ ዐላማ ስለሚሰጡ ከተወሰኑ ሰዎችና ዘመን ጋር ቈይታቸውን ከመወሰን ይልቅ፣ ቢያንስ ቢያንስ ለሌላም ዐላማ ሊሰጡ እንደሚችሉ መረዳት የተሻለ ድምዳሜ ጋር ለመድረስ ያስችላል።
ተቋርጧላውያን ከሚያነሧቸው ነጥቦች መካከል ሌላኛው ዋና መከራከሪ ዐሳብ፣ የመናገር ማለትም የትንቢት፣ የልሳንና ዕውቀትን የመናገር ስጦታዎችን ቀጣይነትን መቀበል የቅዱሳት መጻሕፍትን በቂነትና (sufficiency) የመጨረሻ ባለ ሥልጣንነትን (finality) ማሳነስ ነው የሚል ነው። ይህ ዕሳቤ በእነዚህ ስጦታዎች የሚገኘውን መንፈሳዊ ዕውቀት ከቅዱሳት መጻሕፍት ስሕተት ዐልቦ እውነትና ሥልጣን ጋር እኩል አድርጎ ከማየት የሚመጣ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው። ቅዱሳት መጻሕፍት በተለየ መልኩ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፉ ናቸው። ስጦታዎች ግን በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ለቤተ ክርስቲያን መታነጽ ተብለው የተሰጡ ናቸው እንጂ፣ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተገለጠው የወንጌል እውነት ዐይነት ባሕርይ ያላቸውና ከቅዱሳት መጻሕፍት እውነት ጋር በእኩል ደረጃ የሚቀመጡ ስሕተት ዐልቦ እውነቶች የምናገኝባቸው ልምምዶች አይደሉም። ይህ ማለት ግን በስጦታዎቹ በኩል የምንረዳው መንፈሳዊ እውነት የለም ማለት አይደለም። ነገር ግን፣ በባሕርይና በሥልጣን ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር የሚተካከል ሌላ ተጨማሪ እውነት የምናገኝባቸው አይደሉም።
የመናገር ስጦታዎች በተለይም ትንቢትን የመናገር ስጦታ፣ ልዩ በሆነ መልኩ ይሠራ የነበረው በቤተ ክርስቲያን በመጀመሪያዎቹ ዓመታት መሠረቷን ከመጣል ጋር ብቻ ተያይዞ እንደ ነበር ተደርጎ መቅረቡ ስሕተት ነው። በአንጻሩ በአዲስ ኪዳን የንባብ ክፍሎች እንደምናየው፣ ይህ ስጦታ ከሐዋርያት መሠረት ከመጣል አገልግሎት ባሻገር ይሠራ ነበር። የሐዋርያት ዘመን ማለፍም ሆነ የቤተ ክርስቲያን መሠረት መጣል የትንቢት ስጦታ ለመቈሙ ማስረጃ ሆነው መቅረብ አይችሉም።
በስጦታዎች መቀጠል ለማመን በቂ ምክንያት ባይሆንም፣ በቅርበት የምናያቸውን እውነተኛ ልምምዶች እንደ ተጨማሪ ማስረጃዎች ማየቱ ተገቢ ነው። በዐይኖቻችን ፊት የተደረጉ ብዙ ታምራትና ምልክቶች እንዲሁም የተፈጸሙ ትንቢቶችን የተመለከትን የዐይን ምስክሮች ብዙ እንደሆንን ዐስባለሁ። ልምምዶችን በማየት ብቻ ለስጦታዎች መቀጠል ማስረጃ አድርጎ ማቅረብ ተገቢ ባይሆንም፣ ልምምዶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ጋር በማስተያየት ትክክለኛነታቸው ማረጋገጥ ግን ስጦታዎች ከመስራት ቈመዋል ከሚል ድምዳሜ ይጠብቀናል። ስለዚህ ልምምዶች የማይናቅ ዋጋ አላቸው። እንዲያው በሰው ፈቃድና ኀይል የሚሆኑ አይደሉም። ነገር ግን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኘውን እውነት በሚያረጋግጡና በሚያሳዩ መልኩ በቤተ ክርስቲያን ካየናቸው ዋጋ ልንሰጣቸውና ለተሰጡበት ዐላማ መዋላቸውን ልናረጋግጥ ይገባናል።
ስጦታዎች የተሰጡት ለፍጹማን ሰዎች ሳይሆን፣ ድካም ላለባቸው ሰዎች መሆኑን ከቆሮንቶስ አማኞች መረዳት እንችላለን።
ግለ ሰቦች ከመንፈስ ቅዱስ የተሰጣቸውን ስጦታ በተለያየ ምክንያት በአግባቡ ላይጠቀሙበትና ለተሰጠበት ዐላማ ላያውሉት ይችላሉ። ነገር ግን፣ የግለ ሰቦቹ ድካም የስጦታዎቹን አለመኖር አያሳይም። ስጦታዎች የተሰጡት ለፍጹማን ሰዎች ሳይሆን፣ ድካም ላለባቸው ሰዎች መሆኑን ከቆሮንቶስ አማኞች መረዳት እንችላለን። በርግጥም ስጦታዎች በአግባቡ ላይያዙ ይችላሉ። አንዳንድ ተቋርጧላውያን በጰንጠቆስጤያውያንና በካሪዝማውያኑ ዘንድ ያለውን የስጦታዎች አጠቃቀም በጥርጣሬ ስለሚመለከቱትና በስጦታዎቹ በሚያገለግሉት ሰዎች ያልተገባ ሁኔታ ስለሚረበሹ የአንዳንድ ስጦታዎችን መቈም ለማስረጃነት ይጠቀሙበታል። እንደ ምሳሌነትም ተነግረው ያልተፈጸሙ ትንቢቶችን፣ ያልተሳኩ የፈውስ እወጃዎችንና ሌሎችንም ነገሮች ያነሣሉ። እነደዚህ ዐይነት ነገሮች በመኖራቸው ምክንያት ስጦታዎችን ከነአካቴው ካለመቀበል ይልቅ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መመሪያ መከተል ይሻላል። የሚደረጉ ነገሮችንና የሚነገሩ ትንቢቶችን መፈተሸ እና መመርመር ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠ ኀላፊነት ስለ ሆነ ስጦታዎችን ከማዳፈንና ካለመቀበል ይልቅ፣ የተሰጠበትን ኀላፊነት በአግባቡ መወጣት ላይ ብናተኵር ይሻላል።
የስጦታዎችን አጠቃቀም በተመለከተ የሚሰነዘሩ ተገቢም እና ተገቢ ያልሆኑ ነቀፌታዎች አሉ። በርግጥ የመጀመሪያዋም ቤተ ክርስቲያን ከዚህ ነቀፌታ የነጻች አልነበረችም። በአንጻሩ አላስፈላጊ ከሆኑ የስጦታዎች ልምምድና እውነተኛ ካልሆኑ ልምምዶች የተነሣ ብዙ ጥፋቶችና ጕዳቶች ይፈጠራሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ የስጦታዎችን ተገቢ ያልሆነ አጠቃቀም ለማረም የስጦታዎችን አላስፈላጊነት በመናገር ባልተገባ መንገድ አልሄደም። የስጦታዎችን ትክክለኛ ዐላማና አጠቃቀም በማሳየት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁሉ ነገር በሥርዐት እንዲከናወን አሳሰበ እንጂ (1ቆሮንቶስ 14፥40)።
ከጥፋቶችና ከስሕተቶች የተነሣ የስጦታዎችን መኖር ከመካድ ይልቅ፣ የስጦታዎችን ተገቢ አጠቃቀም ማሳየት እጅግ የተሻለ ነው። ሐሰተኛ ልምምድ ስላለ እውነተኛውን ልምምድ ማዳፈን ተገቢ አይደለም። ሐሰተኞች ምድሪቱን ስለሞሏት እውነተኞች የሉም ከሚል ድምዳሜ መቆጠብ አለብን። አንዳንድ ጊዜ የስጦታዎችን መኖር ተቀብለን ብዙ ዋጋ ከመክፈልና ከመጎዳት ከነጭራሹ ስጦታዎች የሉም ብንል የሚቀለን ይመስለናል። ፍርሀታችንና ስጋታችን ግን እውነታውን ሊቀይሩት አይችሉም። ሁሉም ነገር በቤተ ክርስቲያን በሥርዐት እንዲከናወን ማድረግ ከተቻለና የክርስቶስ ጌትነት ዕውቅና ከተሰጠው፣ ከብዙ ጥፋትና ጉዳት እንድናለን፤ ቤተ ክርስቲያንም በብዙ ትታነጻች፤ ሐሰተኛ ልምምድም ሆነ ሐሰተኛ ሰው ስፍራ ያጣሉ።
የማስተማር ስጦታ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚያንጽ እንዲሁም በሰዎች ድካምና አለመብሰል ምክንያት ስሕተት እንደሚገኝበት ሁሉ፣ የትንቢትም ሆነ ሌሎች ስጦታዎች ቤተ ክርስቲያንን ያንጻሉ። እንዲሁም በሰዎችም ድካምና አለመብሰል ምክንያት ስሕተት ሊኖርባቸው ይችላል። ከምናያቸው ድካሞችና ስሕተቶች ወይም ያልተገባ የስጦታዎች አጠቃቀም ተነሥተን ግን፣ በቤተ ክርስቲያን የምናያቸውን የስጦታዎች ልምምድ በሙሉ ከሰይጣን ወይም ከሰው የመነጩ አድርጎ መቍጠርና እውነተኛው ስጦታ አሁን እንደማይሠራ መደምደም ስሕተት ነው። ስለዚህ ያለ አንዳች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክንያት ስጦታዎች ተቋርጠዋል ብሎ ማለት መሠረት የሌለው ድምዳሜ ነው ብዬ ዐስባለሁ። ሐሰተኛ ነቢያት በሕዝቡ መካከል ይኖራሉ ተብለን በተነገረን ልክ፣ እውነተኛ ነቢያት አይኖሩም አልተባልንም። የሐሰተኞች መኖር የእውነተኞችን አለመኖር አያረጋግጥልንም። ሁሉንም ትንቢት የሐሰት፣ ሁሉንም ነቢይ ሐሰተኛ ብሎ ማለት እንዴት ልክ ሊሆን ይችላል? ሐሰተኞች እውነተኞችን ቢመስሉ እንጂ መሆን አይችሉም። የሐሰት ትንቢትም የእውነት ትንቢት መሆን አይችልም። ሁለቱም ግን በቤተ ክርስቲያን ዘመን ይኖራሉ። መፈተሸና መመርመር ለቤተ ክርስቲያን የተሰጣት ነጻነትና ኀላፊነት ነው። ስለዚህም ስጦታዎችን ፍጹም በሆነ መልኩ መጠቀም አለመቻል ስጦታዎቹ ላለመኖራቸው ማስረጃ ሊሆን አይችልም።
በመጨረሻም አንድ አማኝ ተቋርጧላዊ (Cessationist) ሆኖ መንፈሳዊ ሊሆን እንደሚችል አምናለሁ። ማንም በክርስቶስ አምኖ መንፈስ ቅዱስን የተቀበለ ሁሉ መንፈሳዊ የሚሆንበትን ኀይል አግኝቷል። ተቋርጧላዊ መሆን ከድነትና ከመንፈሳዊ ብስለት ጋር የሚያያዝ አይደለም። ተቋርጧላዊ ያልሆኑ የተሻሉ አማኞች ናቸው ብሎ መደምደም ተገቢ አይደለም። የጽሑፌም ዐላማ ይህን ማስረዳት አይደለም። ተቋርጧላዊ ሆነው ቤተ ክርስቲያንን በተሻለ መልኩ የሚያገለግሉ ብዙ ሰዎች ዐውቃለሁ።
እንዲያውም አቋማቸውን ከማይቀበሉ ሌሎች ወገኖች ጋር በቃለት ከመዋጋት ይልቅ በተለያየ መልኩ ኅብረት ሲያደርጉ ለመታዘብ ችያለሁ። ተቋርጧላውያን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ሙሉ ለሙሉ ተቋርጠዋል ወይም ቈመዋል አይሉም። መንፈስ ቅዱስ መጋቢ እንጂ ሐዋርያ ሊሰጠን አይችልም ወይም የመምከር ስጦታ እንጂ የልሳን ስጦታ አይሰጠንም ብለው ሊሉ ይችላሉ። ስለዚህም ተቋርጧላውያን መንፈስ ቅዱስ ስለሚሠራበት መንገድ ወሰንና ገደብ በማበጀት ለተወሰኑት ስጦታዎች ብቻ ዕውቅና ይሰጣሉ እንጂ፣ ሙሉ ለሙሉ ስጦታዎች ቈመዋል የሚል እምነት የላቸውም።
አንዳንዴም ተቋርጧላውያን እግዚአብሔር የወደደውን ሊሠራ እንደሚችል ይናገራሉ። ከፈለገ የታመመን ሊፈውስ፣ ካሻውም ምልክትን ሊያሳየንና ታምራን ሊሠራ እንደሚችል ያስባሉ። ነገር ግን፣ ለታመሙና በአጋንንት ለታሰሩ ለመጸለይ ሲደፍሩ አንመለከታቸውም። በዕውቀት ደረጃ የሚያስቡትን በተግባር ሲለማመዱት አይታዩም። በተግባራዊ መልኩ ሲታዩ “እግዚአብሔር የወደደውን ማድረግ ይችላል፤ ነገር ግን ታምራን ሲያደርግና የታመሙትን ሲፈውስ አይታይም” በሚል በሁለት ዐሳብ የሚያነክሱ ናቸው። እግዚአብሔር መፈወስና ታምራት ማድረግ መቻሉን ካመንን ያለ አንዳች አሳማኝ ምክንያት ስጦታዎችን መስጠት ማቈሙን ማመን ለምን አስፈለገ? ካደግንበት ባሕልና የቤተ ክርስቲያን ሥርዐት የተነሣ እጅግ ጥንቁቅ መሆናችን ስጦታዎችን እንዳንቀበል አድርጎን ይሆን? ወይስ ብዙ ማወቃችን ወስኖን ይሆን? ብዬ በአክብሮት እጠይቃለሁ።
ስለዚህ አንድ ሰው ተቋርጧላዊ ሆኖ “በሆነውና በሚሆነው” ወይም “በተፈጸመውና ወደ ፊት በሚፈጸመው” (“already, but not yet”) ፍጻሜያው ማዕቀፍ ውስጥ የአንዳንድ ስጦታዎችን መቈም ሊከራከር ይችላል። ክርክሩና የሚያቀርባቸው ዐሳቦች ግን በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት፣ በተለይም በሐዋርያው ጳውሎስ የተገለጠውን የዚህን ፍጻሜያዊ ማዕቀፍ አንዳንድ ገጽታዎች መጨፍለቃቸውና ማሳነሳቸው አይቀሬ ነው።
Share this article:
“ወርኀ ጽጌ ወስደት” የተሰኘው ይህ ጽሑፍ፣ በወንጌላውያኑ ዘንድ ብዙ ትኩረት ስለማይሰጠውና ጌታ ኢየሱስ በሕጻንነቱ ወራት ከእናቱ ማርያምና ከዮሴፍ ጋር ወደ ግብፅ የተሰደደበትን ታሪክ መነሻ በማድረግ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ ሁነቱ ያለውን ትርክት ያስቃኛል።
በርእሱ ላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ቃላት “ማዝመር እና መዘመር” ወይም “አዝማሪነት እና ዘማሪነት” በዓለማዊ (Secular) በተሰኘው እና መንፈሳዊ በምንለው ክልል የዜማ እና የቅኔ ኪነ ጥበብ መገለጫ ስለ መሆናቸው፣ እንደውም በጋራ ተጨፈልቀው የተሠሩና ያለ ምንም ልዩነት አደባባይ የዋሉ ያህል ሲነገሩ ማድመጥ የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን የዜማና የቅኔ ጥበብ በተለይም የዝማሬው ኪነ ጥበብ የአንድ ዘመን የሰዎች የፈጠራ ግኝት ወይም በ“እከሌ ፍልስፍና” የተገኘ አለመሆኑን ከመንፈሳዊው ዓለም ታሪካዊ አስተምህሮ ተገቢ ትምህርት መቅሰም ይቻላል፡፡
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
Add comment