
[the_ad_group id=”107″]
በባለፈው ዕትም ጽሑፋችን ቴክኖሎጂ ከክርስትና ጋር ያለውን ቁርኝት እና አውንታዊ ተጽእኖዎችን ለማየት ሞክረን ነበር። በዛሬ ጽሐፋችን ደግሞ የቴክኖሎጂን አሉታዊ ገጽታዎችን በመመልከት እንዴት አድረገን ከአደጋ በፀዳ መልኩ ከክርስትና አስተምህሮ ጋር አጣጥመን መጠቀም እንደምንችል እንመለከታለን። በታሪክ ውስጥ የቴክኖሎጂ ፈጠራ እና ዕድገት በጣም ፈጣን እንደ ሆነ በአብዛኛው ሰው ዘንድ ያታመናል። የፈጠራው ዕድገት እና ፍጥነት የሰው ልጆችን አኗኗር ዘይቤ በማቅለል እና በማሳለጥ አካላዊ፣ ማኅብረ ሰባዊ እንዲሁም መንፈሳዊ ተጽእኖዎችን እያሳረፈ ይገኛል። ከእነዚህ ተጽእኖዎች ተነሥተን ልናነሣቸው የምንችላቸው ጥያቄዎች ይኖራሉ፤ ይኸውም እንደ አንድ ክርስቲያን ራሳችንን በምን ያህል መጠን ከቴክኖሎጂ ጋር ማጣመር ይኖርብናል? ከሺህ ዓመታት በፊት የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ የዚህ ዘመን ክስተት ከሆነው ከቴክኖሎጂ ጋር እንዴት መኖር እንዳለብን ያስተምረናል? የቴክኖሎጂ ውጤቶች በመንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖ ምን ያህል ነው? የሚሉት ከሚነሡት ጥያቄዎች መካከል ናቸው።
አንዳንድ ክርስቲያኖች ቴክኖሎጂን እና ክርስትናን አጣምረው ማየት ሲቸገሩ ወይም ቴክኖሎጂ ኢ-መንፈሳዊ ወይም ለመንፈሳዊ አኗኗር አደጋው የበዛ እንደ ሆነ ሲሞግቱ ያታያል። ለዚህም እንደ ምክንያት ከሚያነሡአቸው አሉታዊ ተጽእኖዎች መካከል፣ አሁን በምንኖርበት ዘመን የቴሌቪዥን፣ ኮምፒዩተር፣ በይነ መረብ፣ ተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ በተለይ የተራቀቁ ተንቀሳቃሽ ስልኮች (Smart phones) ጋር ያለን ጥብቅ ቁርኝት በዕለት ውስጥ ብዙ ሰዓታትን በእነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ ተጠምደን እንድናሳልፍ እያደረጉ ይገኛሉ የሚለው ነው። ከዚህም ባለፈ በእነዚህ ቴክኖሎጂ አውታሮች ውስጥ የምናገኛቸው ለመዝናናት የሚመስሉ፣ ነገር ግን በውስጣቸው የያዟቸው መልእክቶች ሰዎችን ወደ ኀጢያት የሚያንደረድሩ፣ ማለትም በቀልን የሚያስተምሩ፣ ልቅ ወሲብን የሚያነሣሡ፣ መልካም ሥነ ምግባርን የሚያንቋሽሹ፣ መንፈሳዊነትን ዋጋ የሚያሳጡ እና ሌሎችም አሉታዊ ገጽታዎች እንዳሉት ምስሌ አድርገው ያቀርባሉ።
በተለያየ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ሰዎች ከቴክኖሎጂ ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ ከፍተኛ እንደ ነው። በፈረንጆቹ የዘመን አቆጣጠር በ2010 በእንግሊዝ አገር የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ፣ በቀን ውስጥ አንድ ሰው በሥራ ላይ ከሚያሳልፈው ግማሹን ሰዓት የሚወስደው በይነ መረብ በማሰስ፣ ስልክ በማውራት ወይም ቴሌቪዥን በመመልከት እንደ ሆነ ይጠቁማል። በጥናቱ መሠረት አንድ ለአቅመ አዳም ወይም ሔዋን የደረሰ ሰው በቀን ውስጥ ከእንቅልፍ ውጭ ከሚያሳልፈው ጊዜ ውስጥ 45% ከቴክኖሎጂ ጋር ነው። ይህንን የሚደግፍ ሌላ ጥናት ባለፈው ዓመት 2013 ላይ ተደርጎ የነበረ ሲሆን፣ ሰዎች ከቴክኖሎጂ ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ የበለጠ እያደገ መምጣቱን ነው የሚያረጋግጠው። ይኸውም አንድ ሰው በቀን ውስጥ ለአምስት ሰዓታት ያህል በይነ መረብ እያሰሰ ሲቆይ፣ ለአራት ሰዓት ከሠላሳ አንድ ደቂቃ ያህል ደግሞ ቴሌቪዥን በመመልከት ጊዜውን እንደሚያሳልፍ ተነግሯል። በእኛም አገር ከበይነ መረብ መሰፋፋት፣ ተንቀሳቃሽ ስልክ እና ቅንጡ ስልኮች በቀላሉ እና በአነስተኛ ዋጋ መገኘት፣ የቴሌቪዥን ስርጭት አማራጮች መብዛት ከቴክኖሎጂ ጋር ያለንን ቁርኝት ይበልጥ አሳድጎታል።
ታዳጊዎች እና ወጣቶች ከቴክኖሎጂ ጋር ያላቸው ቁርኝት በተለየ መልኩ ተጽእኖው የጎላ ነው። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በምናባዊ ማንነት ውስጥ አዝፍቆ ያልሆኑትን መሆን እንደቻሉ በማድረግ (Fantasy) እና ጥልቅ ሱስ ውስጥ በመክተት ከቤተ ሰብ እና ማኅበረ ሰብ ጋር በሚኖራቸው መስተጋብር ላይ የሚባል ችግርን ያስከትላል። በተጨማሪም፣ በይነ መረብ ላይ ያለው ሰፊ መረጃ እና ልቅነት ቤተ ሰብ በልጆቻቸው አስተዳደርግ ላይ ሊያስቀምጡ የሚፈልጉትን መሠረት በማናጋት ልጆች ከወላጆቻቸው ሰምቶ ከማር ይልቅ የበይነ መረብ መረጃዎችን እንደ ዋና የመረጃ እና የእውቀት ምንጭ በማድረግ መሥመርን የሚያስቱ ጐዳናዎች ውስጥ ሲከቷቸው ይታያሉ። የበይነ መረብ ክፍት የመረጃ ምንጭነት የሚያመጣውን አደጋ በተለይም ልጆች ያልተገቡ መረጃዎችን በመፈለግ ወደ አልተፈለገ አስተሳሰብ ውስጥ እንዳያስገባቸው ወላጆች መጠበቂያን ማስቀመጥ ያገባቸዋል። ይህንንም ለማድረግ በአብዛኛው ኮምፒዩተሮች ላይ “Parental controls” በማስቀመጥ የልጆችን አጠቃቀም መቆጠር ይቻላል። በቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ የመጠመድ ተጽእኖ እየሰፋ ሲመጣ በየዕለት ኑሮአችን ማድረግ የሚገባንን ኀላፊነቶች እና ግዴታዎች መወጣት እስኪያቅተን ሊያደርሰን ይችላል። ከዚህም የተነሣ የሥነ አእምሮ ባለሙያዎች ከአልኮል መጠጥ እና አደንዛዥ ዕፀ ሱስ ውስጥ የሚካተት አዲስ ችግር እንደ ሆነ እና ከዚህም የቴክኖሎጂ የበዛ ተገዥነት ለመላቀቅ ሥነ አእምሯዊ እርዳታ ሊያስፈልግ እንደሚችል ይናገራሉ።
ይህንን ሐሳብ የሚሞግቱ ደግሞ የቴክኖሎጂ አቅም ከፍተኛ መሆኑን ለማሳየት የበያነ መረብን ሰፊ ጥቅም ያስረዳሉ። ከበይነ መረብ የተነሣ የተለያየ አገር እና ቦታ ካሉ ጋር ብዙ ጓደኞችን እና ወዳጆችን በተለያዩ ማኅበረ ሰባዊ ገጾች ማፍራት መቻላቸውንና ከእነዚህም ሰዎች ጋር በቀላሉ ሐሳብ ለመለዋወጥ እና ኅብረት ለማድረግ እንዳሰቻላቸው ይናገራሉ። በዚህ ሐሳብ የቴክኖሎጂ አሉታዊ ጎኑ ይበዛል የሚሉትም ቢስማሙም፣ አጠቃቀማችን እና ቁርኝታችን በመንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ ምንም ተጽእኖ ሊያሳርፍ በማያስችል መልኩ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ።
በተጨማሪም፣ ኒዩሮሳይንቲስቶቹ ማንፍሬድ ስፒትዘር እና አዳም ጋዘሊ እንደሚሉት ወላጆች በልጆቻቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች አጠቃቀም ላይ ጥንቃቄ ሊያደረጉ ከሚገባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ በሕፃናት የአእምሮ ዕድገት እና የመማር ሂደት ላይ ትልቅ ችግር ማስከተል መቻሉ ነው። ከሚያስከትላቸው የአእምሮ ዕድገት እና የመማር ሂደት ችግሮች ዋነኛው የተለያዩ ሥራዎችን በአንድ ጊዜ በመሥራት ሰዎች በራሳቸው አእምሮ ጥልቅ የሐሳብ ምርምርን እንዳያደርጉ መገደቡ እንደ ሆነ ያመለክታሉ።
ማጠቃለያ
ቴክኖሎጂ በክርስትና ሕይወት እና በየዕለት ኑሮአችን ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ጐን ትኩረታችንን ከእግዚአብሔር ላይ አንሥቶ በቴክኖሎጂው ውጤቶች ላይ እንድንጠምድ በማድረግ ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረንን ጊዜ ማሳጣት ነው። ቴክኖሎጂ በተለያየ መልኩ ባዘመነው ጊዜ ውስጥ መኖራችን የፈጠረውን መልካም ዕድል በመጠቀም የተጠራንበት ዓላማ ለመፈጸም እንድንችል ራሳችንን ከአሉታዊ ጐኑ በመጠበቅ በአግባቡ መኖር ይጠቅብናል። ከክርስትና ዕይታ የአንድ ቴክኖሎጂ አሉታዊም ሆነ አውንታዊ ጐኑ የሚታየው፣ የቴክኖሎጂው ፈጠራ የተሠራበት ዓላማ ላይ ይወድቃል። አካባቢን እና የሰው ልጅን ለመጥቀም የተፈበረከ ሊሆን ይችላል፤ ወይም በተቃራኒው አካባቢንም ሆነ የሰው ልጅን የሚያጠፋ ይሆናል። የቴክኖሎጂ ፈጠራ ለሰው ልጅ የሚያስፈልግ እንደ ምግብ፣ ጤና መገናኛ፣ መጠለያ ወዘተ… ማቅረብ የምንችልበትን ዕድል ሊፈጥር እንደሚችል ሁሉ የሰው ልጅን ሊያጠፋ የሚችል እንደ ጦር መሣሪያና በሸታ የመሳሰሉትን ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።
በአጠቃላይ ቴክኖሎጂ ላይ ሊኖረን የሚገባ ጥንቃቄ ቁርኝታችንን በመወሰን ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረንን ጊዜ በማያሳጣ መልኩ መሆን ይኖርበታል። የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም የተለያዩ ሥራዎቻችን እና አኗኗራችን በቀላሉ፣ በቅልጥፍና እና ውጤታማ በሆነ መንገድ መከወን መቻላችን በራሳችን ጥረት እና እውቀት መስሎ እንዳይሰማን፣ ይልቁኑ የቴክኖሎጂ ፈጠራ አእምሮ መከፈት ምክንያቱ ከእግዚአብሔር እንደ ሆነ መዘንጋት የለብንም።
Share this article:
“የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” (ማቴ. 5፥9)
አማረ ታቦር Seeing and Savoring Jesus Christ ከተሰኘው የጆን ፓይፐር መጽሐፍ መግቢያ የተወሰኑ አንቀጾችን ተርጉሞ እንደሚከተለው አቅርቧቸዋል።
የሥነ መለኮት ጥናት በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን አጭር ዕድሜ ያለው ነው፡፡ የዕድሜው ዕጥረት ከወንጌላውያን ክርስትና አጀማመር ጋር የራሱ ቁርኝት አለው፡፡ የአብያተ ክርስቲያናቱ የቆይታ ዘመን በአንጻራዊነት ከታየ አጭር የሚባል ነውና፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በርካታ ቤተ ክርስቲያናት፣ አጋር ቤተ ክርስቲያናትና ግለ ሰቦች የመጽሐፍ ቅዱስ ት/ቤቶችን መክፈት ጀምረዋል፡፡ በመሠረቱ ይህን መሰሉ ጥረት ሊበረታታ ይገባል እንላለን፡፡ ይሁን እንጂ ጥረቱን ማበረታታት እንዳለ ሆኖ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በዋናነት ከትምህርት ጥራት ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
Add comment