[the_ad_group id=”107″]

ቴክኖሎጂ እና ክርስትና

ስለ ቴክኖሎጂ ሲነሣ በአብዛኛው ወደ ሰው አእምሮ አስቀድሞ የሚከሰተው የቴክኖሎጂ ፈጠራ ኮምፒውተር፣ ገመድ አልባ (ተንቀሳቃሽ) ስልክ ወይም በይነ መረብ (Internet) ነው፡፡ ነገር ግን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ዘርፍ ብዙ ሲሆን፣ ለምሳሌ አውቶሞቢል፣ ባቡር፣ አውሮፕላን፣ ራዲዮ፣ ቴሌቭዥን፣ መገናኛ አውታሮች፣ ኅትመት እና ሌሎችም… ናቸው፡፡ ዛሬ የምንነጋገርበት ጉዳይ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች በክርስትና ላይ ያሳረፉትን እና እያሳረፉ ያሉትን በጎ ተጽዕኖ ነው፡፡

“ቴክኖሎጂ” የሚለው ቃል የተለያየ ትርጓሜ አለው፤ ከእነዚህም ውስጥ የዌብስተር መዝገበ ቃላት (Webster Dictionary 9th edition) ካስቀመጣቸው ትርጉሞች መካከል፣ “ሳይንሳዊ መንገድ እና ዕውቀትን በመከተል ለአንድ ለታቀደ ዓላማ ተግባራዊ መፍትሔን ማግኛ መንገድ ነው” የሚለው በተሻለ እንደሚገልጸው ዐስባለሁ፡፡ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች የተለያዩ ዓላማዎችን ይዘው፣ በተለያዩ ጊዜያት ለሰው ልጆች ተዋውቀዋል፡፡ እነዚህም ፈጠራዎች በሰው ልጆች የዕለት ዕለት አኗኗር ላይ ያሳደሩትን ተጽዕኖ ስንመለከት ብዙ ጥያቄዎች ልናነሣ እንችላለን፡፡ በእርግጥ እያንዳንዱ የቴክኖሎጂ ፈጠራ በተፈበረከበት ዓላማ በሰው ልጆች አኗኗር ላይ የራሱን ቅርጽ በመፍጠር፣ ለተለያዩ ችግሮች መፍትሔን በማምጣት እና አኗኗር ዘይቤያችንን በማቅለል ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡ ሆኖም ከኤሌክትሪክ ኀይል፣ ከአውቶሞቢል፣ ከባቡር፣ ከአውሮፕላን፣ ከመገናኛ አውታሮች፣ ከኮምፒውተር፣ ከበይነ መረብ፣ ከዘመናዊ ሕክምና … የአንበሳውን ድርሻ የሚወሰደው የትኛው የቴክኖሎጂ ፈጠራ ነው?

ጥያቄው ቴክኖሎጂ በክርስትና ላይ ካሳደረው ተጽዕኖ ወይም ከፈጠረው ቅርጽ አቅጣጫም ሊታይ ይችላል፡፡ ቴክኖሎጂ ታላቁን ተልዕኮ ለሰው ልጆች ሁሉ ማድረስ የምንችልባቸውን አውታሮች ማስፋቱ በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ከዚህም የተነሣ የወንጌል ሥርጭት ዐቅምን በማገዝ ክርስትናን በማስፋፋት ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ አሳርፏል፡፡ ከዚህም የተነሣ የክርስትና ዕድገት ከቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር ቀጥተኛ ተዛምዶ እንዳለው ይታመናል፡፡

ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ዘመናት የተፈበረኩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ቀዳሚ ተጠቃሚ ነበረች፡፡ የሮማውያን አገዛዝ የፈጠረው ጊዜያዊ ሰላም (Pax Romana) እና ጠንካራ ወታደራዊ አስተዳደር ለማስፈን የተዘረጋው የመጓጓዣ መሠረተ ልማት መስፋፋት ለዚህ በማስረጃነት ይቀርባሉ፡፡ የሮማ አስተዳደር የተለያዩ አገራትን በአንድ ሕግ፣ ቋንቋ እና ባህል ሥር ለማዋል ያደረገው እንቅስቃሴ ከዚህ ጋር የተሳሰረ ነበር፡፡ ይህንን የመጓጓዣ መሠረተ ልማትም በመልካም አጋጣሚነት በመጠቀም የክርስትና እምነትን በተለያዩ አካባቢዎች ማዳረስ ተችሏል፤ ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ እና የአገልግሎት ባልደረቦቹ የዘመኑን ፈጣን የመጓጓዣ መንገድ፣ ማለትም መርከብን በመጠቀም የምሥራቹን በሮማውያን አገዛዝ ሥር ለነበሩ ሕዝቦች በፍጥነት አሠራጭተዋል፡፡

ከዚህም በመቀጠል በ1400 አጋማሽ የተፈበረከው የኅትመት ቴክኖሎጂ ለክርስትና መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የኅትመት ቴክኖሎጂ እውን ከመሆኑ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ የሚጻፈው በእጅ ነበር፤ በዚህም አካሄድ የዘፍጥረትን መጽሐፍ እንኳ ለመጻፍ አንድ ሰው በአማካይ ሁለት ወራት ይወስድበታል፡፡ በዚህም ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ በውስን ቁጥር፣ እርሱም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብቻ ነበር የሚገኘው፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን ለማግኘት እና ለማጥናት የግድ ቤተ ክርስቲያን ድረስ መሄድ ይኖርበት ነበር፡፡ የኅትመት ቴክኖሎጂው እውን መሆን ግን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በብዛትና በአጭር ጊዜ ውስጥ መታተም እንዲችሉ እና ለብዙ ሕዝቦች እንዲዳረሱ አስችሏል፡፡

ዊልያም ቲንዴል መጽሐፍ ቅዱስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተርጉሞ ለኅትመት ካቀረበ በኋላ፣ በ1500 መጀመሪያ ላይ ማርቲን ሉተር የተለያዩ አነስተኛ ጽሑፎችን በማሳተም የመጽሐፍ ቅዱስ ምልከታውን እና አስተምህሮቱን ወደ አውሮፓ በቀላሉ ማስረጽ ችሏል፡፡ ሉተር በተጨማሪም፣ መጽሐፍ ቅዱስን በጀርመንኛ ቋንቋ በመተርጐም አሳትሞ ማሠራጨት ችሎ ነበር፡፡ ይህንን ዕትም ጀርመኖች መደበኛ የትርጉም መጽሐፋቸው አድርገው እስከ አሁን ይጠቀሙበታል፡፡ በ1644 የእንግሊዝ ፓርላማ ʻየኅትመት ቴክኖሎጂው አደገኛ የሃይማኖት አስተምህሮዎችን እያስፋፋ ነውʼ በማለት የቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) ሕግ በማውጣቱ፣ የክርስትና አስተምህሮዎችን የያዙ ኅትመቶች በብዛት እና በፍጥነት እንዳይዳረሱ እንቅፋት በመፍጠር በክርስትና መስፋፋት ላይ ተጽዕኖ አሳድሮአል፡፡ ይሁን እንጂ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ይዘው የመጡት ብሌይዝ ፓስካል፣ አይዛክ ኒውተን እና ሳሙኤል ሞርስ በፈጠራ ሥራቸው ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮዎችን መልሶ በማነቃቃት እና በማዳረስ ትልቅ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው የቴሌግራፍ ፈጠራ ባለቤት የሆነው ሳሙኤል ሞርስ ለመጀመሪያ ጊዜ በቴሌግራፍ የላከው መልእክት “What hath God wrought” የሚል ነበር፡፡

በ1939 ቲዮደር ኢፒፒ የራድዮ ሞገድ ሥርጭት ቴክኖሎጂን በመጠቀም “Back to the Bible” የሚል ትልቅ ሥርጭት ጀምሮ ብዙ ሕዝቦችን መድረስ ችሎአል፤ ይህ በ800 ጣቢያዎች በ8 ቋንቋዎች ይተላለፍ የነበረው ሥርጭት ከፍተኛ ተደማጭነት ነበረው፡፡ ቢሊ ግራሃምም የቴሌቭዥን ቴክኖሎጂ ሥርጭትን በመጠቀም ታላላቅ የጀማ ስብከተ ወንጌልን በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሕዝቦች ማድረስ ችለዋል፡፡ ሲሞን ጄንኪንስ እና ስቲቭ ጎዳርድ የተሰኙ ሁለት ሰዎችም የበይነ መረብ ቴክኖሎጂ ውጤትን በመጠቀም በእንግሊዝ አገር የሚገኙ አካል ጉዳተኞች ባሉበት ስፍራ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያገኙበትን መንገድ አመቻችተዋል፤ ይህም “Church of Fools” በመባል ይታወቃል፡፡ የበይነ መረብ ቴክኖሎጂም የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እና አስተማሪዎች መልክእክታቸውን በቀላሉ እና በፍጥነት ለብዙዎች እንዲያደርሱ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የዘመኑ ምዕራባውያን ቤተ ክርስቲያናት የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች በአንድ ቦታ ሆነው ማምለክ እንዲችሉ፣ መልእክቶችን በተለያዩ ቋንቋዎች በመተርጎምና በገመድ አልባ የጆሮ ማዳመጫ (head phone) በመጠቀም አገልግሎቱን መቋደስ የሚቻልበት መንገድ እውን አድርገዋል፡፡

ዘርፈ ብዙው የቴክኖሎጂ ፈጠራ የሰው ልጆችን አኗኗር በማቅለል እና በማገዝ በጐ ተጽዕኖዎችን ማሳረፍ ችሏል፤ ቤተ ክርስቲያንም እጆቿን አርዝማ፣ ከቅጥሯም ርቃ በመሄድ ወንጌል ማድረስ የሚትችልበትን ትልቅ አቅም ፈጥሮላታል፡፡ በጐ የሚባሉ ተጽዕኖዎችን አጠቃልለን ስንመለከት በመጀመሪያ ደረጃ፤ ወንጌልን በማዳረስ ሥራ ላይ የነበረው የቁጥር ገደብ ከመቶ እና ከሺህ ተነሥቶ በአጭር ጊዜ ሚሊዮኖችን መድረስ የሚቻልበት ዕድል ተፈጥሮአል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ፤ የኅትመት ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስን እና የተለያዩ የማስተማሪያ መጻሕፍትንና ሌሎች የኅትመት ውጤቶችን በብዛት እና በጥራት ለብዙ ሕዝቦች በፍጥነት ማድረስ ተችሏል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ፤ የወንጌል ተልዕኮ ማዳረሻ አማራጮች ተስፋፍተዋል፡፡ በአራተኛ ደረጃ፤ ቤተ ክርስቲያን አባላቷን በመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ በፍጥነት እና በቀላሉ ለማበረታት፣ ለማነጽ፣ ለመገሠጽ እና ደቀ መዝሙር በማድረግ ሂደት ውስጥ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሰፊ አማራጮች ሆነዋታል፡፡ በአምስተኛ ደረጃ፤ እያንዳንዱ ክርስቲያን የተሰጠውን ጸጋ ተጠቅሞ ሌሎችን ባሉበት ዐውድ በቀላሉ መድረስ የሚችልበት ዕድል ተፈጥሮለታል፡፡

እውን ክርስቲያኖች ሳይሞቱ ለዘላለም ሊኖሩ ይችላሉ?

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቴሌቪዥን መስኮት ብቻ እናውቃቸው የነበሩ አንዳንድ አፍሪካውያን “አገልጋዮች” በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ መታየት ጀምረዋል። በቅርቡ የተከሰቱ ሁለት ኩነቶችን እንኳ ብንመለከት “ሜጀር ሼፐርድ ፕሮፌት” ቡሽር ከማላዊ፣ “ነቢይ” ኮቦስ ቫን ሬንስበርግ ከደቡብ አፍርካ ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ልብ ይሏል።

ተጨማሪ ያንብቡ

መስቀሉ

“መስቀል የሰውን ስቃይ እግዚአብሔር አምላክ የተካፈለበት፣ የኢዮብ ጥያቄ “አንተ የሥጋ ዐይን አለህን?” የሚለው ፍንትው ያለ ምላሽ ያገኘበት፤ ስቃይ ለእግዚአብሔር ባዕድ እንዳልሆነ የተመሠከረበት፣. . . ነው።” በሰሎሞን ከበደ

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.