[the_ad_group id=”107″]

ድምፃዊ ተፈራ ነጋሽ:- "ታንክ ቢመጣ ወደኋላ አልመለስም"

5 አልበሞች ለአድማጭ አድርሷል፤ ከእነ አረጋኸኝ ወራሽና ሌሎች ድምፃውያን ጋር የሠራቸው ስብስብ ሥራዎችም አሉት። “ደህና ሁኝ ልበልሽ በእንባ እየታጠብኩኝ”፣ “ምነው ቀዘቀዘ ፍቅራችን”፣ ከሥራዎቹ መካከል ጎልተው የሚጠቀሱት ናቸው። ሰሞኑን በታክሲ ሾፌርነት መታየቱ ተሰምቶ አነጋግረነዋል።


Originally posted at BBC Amharic

 • ዘፈንን ትተህ መንፈሳዊ ዓለምን ከተቀላለልክ ስንት ዓመት ሆነህ?

ተፈራ ነጋሽ፦ አሁን 13 ዓመት ጨርሼ 14 ዓመት ሊሞላኝ አንድ ወር ይቀረኛል።

 • ያኔ ይህንን ውሳኔ ስትወስን አድናቂዎችህ ምን ይሉ ነበር?

ተፈራ ነጋሽ፡-የተለያየ ዓይነት አስተያየት ነበር። የሚደግፉ አሉ። እንደገና ደግሞ በዛው ብቀጥል የሚፈልጉና የራሳቸውን ሐሳብ የሚሰጡም አሉ። እንዲሁ ደግሞ የሚቃወሙም ነበሩ። ዞሮ ዞሮ ውሳኔው ግን የራስ ስለሆነና ሕይወት ስለሆነ፣ መንፈሳዊ ነገር አንተ ለራስህ የሚገለጥልህ ነገር ስለሆነ፣ አንተ የተሰማህን ወይንም ደግሞ የተገለጠልህን ነገር ነው የምትኖረው።

 • ወደ መንፈሳዊ ሕይወት ከገባህ በኋላ የቀድሞ ሥራዎችህን ስትሰማ የሚፈጠርብህ ስሜት ምንድን ነው?

ተፈራ ነጋሽ፡- እውነቱን ለመናገር ከሆነ የውሳኔህ ሁኔታ ነው የሚወስነው። እኔ ስወስን ምንም ነገር ሳልጨብጥ አይደለም የወሰንኩት። የሆነ ነገር ገብቶኝ በትክክል መንፈሴ ላይ የተረዳሁት ነገር ስለነበረ፣ ያ የተረዳሁት ነገር ደግሞ ከአእምሮ በላይ የሆነ ትልቅ ስለሆነ፣ ከምንም ነገር ጋር አላነፃፅረውም። እና በቀጥታ ወደዚህ ወደ መንፈሳዊው ዓለም ስመጣ በፊት የነበሩኝ ልምዶች እንዴት እንደሆነ ሳላውቅ ከኔ ተለይተው ነው ያገኘኋቸው። እና ሙዚቃውም ዘፈኑም አብሮ ወዴት አንደሄደም አላውቅም። ፍላጎቱ ጠፍቷል። አሁን የድሮ ሥራዎቼን በምሰማበት ጊዜ እውነቱን ለመናገር ከሆነ ምንም ስሜት አይሰጠኝም።የኔ እስከማይመስሉኝ ድረስ ነው ውስጤ የተለወጠው ልልህ ፈልጌ ነው።

 • ያንን ድምፅ ስትሰማ፣ ሙዚቃውን ስትሰማ እንደሌላ ሰው ነው የምታስበው?

ተፈራ ነጋሽ፡- እውነት ነው፤ ምክንያቱም ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ከሄድን ምን ይላል፣ “ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው” ይላል። አዲስ ፍጥረት የሚለው ነገር እውነት ነው። ወደዚህ አዲስ ማንነት ስመጣ ውስጤ ለውጥ ተካሄዷል። በዐይን የማይታይ ግን መለኮት የሚሠራው ውስጣዊ ለውጥ ተከስቷል። ያ ለውጥ ዘፈንን ብቻ አይደለም፤ ሌሎች ማንኛቸውንም ነገሮች በተለይ ኀጥያት ተኮር የሆኑ ነገሮች ወዴት እንደሄዱ አላወቅሁም።

 • ራሴ ነፃ ሆኜ፣ ፍላጎቴ ተቀይሮ፣ ሌላ ሰው ሆኜ ነው ራሴን ያገኘሁት።

ለምሳሌ አንድ ነገር ልንገርህ፤ ጫት እቅም፣ መጠጥም እጠጣ ነበር። ግን ይህንን ውሳኔ በወሰንኩ በማግሥቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ነው ትዝ ያለኝ። ውስጤን ሳዳምጠው የለም። ልክ እንደዚህ ዘፈኑም አብሮ ሄዷል። ስለዚህ ይህ ውስጣዊ ለውጥ ነው፤ ይሄ የማንነት ለውጥ ነው።

 • ሥራዎችህ ከውሳኔህ በኋላ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ተከፍተው ሲደመጡ ቅር ይልሃል?

ተፈራ ነጋሽ፡- እንደዛ አላስብም፤ ተቃውሞም አላሰማም። ምክንያቱም ሥራዎቹ የብቻዬ አይደሉም። የሙዚቃ ባንዱ፣ ገጣሚያን፣ ዜማ ደራሲያን አሉ። ብቻዬን የሠራሁት ሥራ ስላልሆነ እነኛም ሰዎች መብት አላቸው። ሌላው ቢሰሙም ላለፈው ነገር እኔ አልጠየቅም። የዛን ጊዜ ትክክል ነበርኩ፤ አሁን ደግሞ የበለጠ ትክክል ነኝ። በዛን ወቅት ጥፋት አጥፍቼ ቢሆን አሁን በምሕረት ወጥቼያለሁኝና ያንን ነገር እግዚአብሔር ረስቶልኛል። ወደ ኋላ ተመልሼ ይህ ለምን ሆነ? ለምን ዘፈንኩ? ብዬ አልፀፀትም። በሌላ መንገድ ካየነው ሥራዎቹ ሲሰሙ አንድም ሰዎች መነጋገሪያ ሊያደርጉትና ሰዎች ራሳቸውን ውሳኔ መምረጫ እንዲያደርጉት መንገድ ሊፈጥር ስለሚችል ለምን የኔ ሥራ ተከፈተ፣ በሚዲያ ላይ መደመጥ የለበትም የሚል አቋም የለኝም።

 • ሰሞኑን ከራይድ ጋር መሥራት መጀመርህን ሰማን፤ እንዴት ወደዚህ ሥራ ልትገባ ቻልክ?

ተፈራ ነጋሽ፡- ከዛ በፊትም የተለያየ ሥራ እሠራ ነበር። ለመኖር መሥራት አለብኝ። አሁን ራይድ ሲመጣ መኪናው እጄ ላይ ስላለ በቀጥታ ሰሌዳውን ወደ 3 ቁጥር አዙሬ፣ የንግድ ፍቃድ አውጥቼ፣ ከድርጅቱ ጋር ተስማምቼ መስራት ጀምሬያለሁ። ሥራው ጥሩ ነው። በጣም ተመችቶኛል። ይህንን ውሳኔ የወሰንኩበት ምክንያት ደግሞ ምንም አይነት ሥራ ስትሠራ በቀዳሚነት የአእምሮ እረፍት ታገኛለህ። ሌላው ደግሞ የሚያስፈልግህን ነገር ታሟላለህ። ሌላ ሰውንም የምትደግፍበት የምታግዝበት አቅም ታገኛለህ። ለመንግሥትም ግብር ትከፍላለህ። ስለዚህ ይህንን ሥራ ሳገኝ ምንም አላቅማማሁም፤ አላመቻመችኩም።

 • ራይዶች እነርሱ ጋር ልትሠራ ስትሄድ ምን ዓይነት ስሜት ነበራቸው?

ተፈራ ነጋሽ፡- የሚመዘግቡት ልጆች የሚያውቁኝ አይመስለኝም። ያን ጊዜ የነበረኝን የታዋቂነት መንፈስ ትቼዋለሁ። ነገር ግን የራይድ ሥራ አስኪያጅ ስታገኘኝ ደስ የሚል ነገር አይቼባታለሁ። ጥሩ አድርጋ አስተናግዳኛለች። እኔ ራሴን እንደ ማንኛውም ተራ ሰው ነው የምቆጥረው። የድሮው ስሜት የለኝም።

 • ደንበኞችህስ? አንተ መሆንህን ሲያውቁ ምን ይላሉ?

ተፈራ ነጋሽ፡- እስካሁን በጎ ምላሽ ነው ያለው። አንዳንድ ከልብ አድናቂዎች ደንገጥ የማለት ነገር ታይባቸዋለህ። ብዙ ሰዎች ውሳኔዬን ያከብራሉ ያደንቃሉም። ምክንያቱም የተሻለ እንደሆነ ያስታውቃል። እንዴት ያስታውቃል ካልከኝ ዝም ብለህ ሰውን ፊቱን ስታየው ሰላሙን ታይበታለህ። እኔ ደግሞ አሁን ያለኝ አቋም ከዕድሜዬ ጋር እንኳ አይገናኝም። 56 ዓመቴ ነው ግን የ40 ዓመት ጎልማሳ ነው የምመስለው። እንደውም አንዳንድ ሰዎች ‘እሸት መሰልክ’፣ ‘ገለፈፍክ’፣ ‘ለመለምክ’ የሚሉኝ አሉ። በውስጤ የሚታየው ሰላም ፊቴ ላይ ስለሚታይ፣ ከማንም ጋር የመግባባቱን ፀጋ ደግሞ እግዚአብሔር ስለሰጠኝ፣ ከብዙ ሰዎች ጋር እናወራለን። የሚፈልጉትን ይጠይቁኛል፤ እኔም እንደሚገባው ከዚህኛውም ከዛኛውም እያጣቀስኩ መልስ እሰጣቸዋለሁ።

 • በአንተ ታክሲ በመገልገላቸው የተለየ ደስታ የተሰማቸው ወይንም የተከፉ አሉ?

ተፈራ ነጋሽ፡- ደስ እንዳላቸው የሚነግሩኝ አሉ። እንደውም ስልኬን ወስደው እንደዘመድ የምንጠያየቅም አሉ። ከጀመርኩ ሦስት ወር ከአስራ አምስት ቀን ቢሆነኝም በዚህ አጭር ጊዜ በርካታ ሰው አግኝቻለሁ። የተለያየ ዕውቀት፣ ልምድ ያላቸው ሰዎች አግኝቻለሁና በጣም ደስ ይላል።

 • አዲሱ የሥራ መስክ ተመቸህ?

ተፈራ ነጋሽ፡- ወድጄዋለሁ። ጭቅጭቅ የለውም። ድካም የለውም። ሥራው አንተ ያለህበት ድረስ ነው የሚመጣልህ። የምታገኛቸው ሰዎችም አሪፎች ናቸው። ወድጄዋለሁ።

 • የተለያዩ ሥራዎችን መሞከርህን ነግረኸን ነበርና ምን ምን ሥራዎችን ነው የሞከርከው?

ተፈራ ነጋሽ፡- የኮሚሽን ሥራዎችን ሞክሬያለሁ። ቤት ሠርቶ ለመሸጥም ሞክሬያለሁ።

 • ኮሚሽን ስትል ድለላ ማለትህ ነው?

ተፈራ ነጋሽ፡- አዎ። ግን አጭር ጊዜ ነው የሠራሁት። መሬት ስለነበረኝ ቤት ሠርቼ ነው የሸጥኩት፤ እሱ ሁለት ሦስት ነገር ወጣው። አሁን ሌላ ቤት ጀምሬ ቆሟል። ያው የሕንፃ መሣሪያ ውድነት አለ፤ በዚህ ሰዓት ላይ። እሱ ሥራ ውስጥ ለመግባት ሐሳብ አለኝ። ሌላው ደግሞ አገልግሎት ላይ ነኝ። በነገራችን ላይ ሙዚቃውን አልተውኩም። የመንፈሳዊ ሙዚቃ ላይ በዝማሬ አገለግላለሁ።

 • አንዳንድ ሰዎች ወደ ታክሲ ሹፌርነት የገባው ተቸግሮ ነው የሚሉ አሉ። አንተ ኑሮህ ዝቅ ብሎ ነው ወደ እዚህ ሥራ የገባኸው?

ተፈራ ነጋሽ፡- እኔ ይህኛውን አባባል አልደግፈውም። ይህንን ሥራ እኔ የምሠራው ምንም ነገር አጥቼ አይደለም። በቤተ እምነት ውስጥ አገልግሎት አገለግላለሁ፤ እርሱ ለኑሮ አያንስም። በዛ ላይ የሚከራይ ቤትም አለኝ። አሁን በጣም ድሃ የመሆን ጉዳይ ሳይሆን ወደ ዚህ ያመጣኝ የጊዜ መኖር ጉዳይ ነው። እኔ የማገለግለው በሰንበት ወይንም በአዘቦት ቀናት ማታ ማታ ነው። ስለዚህ ቀን ቀን በከንቱ የሚያልፈውን ጊዜ ብጠቀምበት ጥሩ ነው። በተጨማሪም ሰው አገኝበታለሁ፤ ከዚህ ሁሉ ባሻገር ደግሞ ገንዘብ አገኝበታለሁ። የሚገኝበት ገንዘብ ቀላል አይደለም። በወር ውስጥ 30 ሺህ ሊያገኝ የሚችል ብዙ ሰው አለ ብዬ አላምንም። ከዚህ ሥራ በቀን ከሺህ ብር በላይ ታገኝበታለህ። እና ገቢው ራሱ በጣም ዝቅተኛ የሚባል አይደለም። እና ትልቁ ነገር ጤና ኖሮህ ሠርተህ የምታገኘው ነገር ነው። ይህንን ነገር እንድሠራ ያደረገኝ የዝቅታና የከፍታ ነገር አይደለም። እግዚአብሔር ይመስገን በከፍታ ውስጥ ነኝ፤ ከክርስቶስ ጋር።

 • ወደ ዓለማዊ ሙዚቃ የምትመለስበት አጋጣሚ ይኖራል?

ተፈራ ነጋሽ፡- ሐዋሪያው ጳውሎስን ታውቀዋለህ?… እነ ጴጥሮስን ታውቃቸዋለህ?… አልተመለሱም ።ለምን እንዳልተመለሱ ታውቃለህ? …ያዩት ምድራዊ ነገር አይደለም። ሰማያዊ ነገር ነው ያዩት።… ታንክ ቢመጣ ወደኋላ አልመለስም። ወደኋላ ከምመለስ ሞት ይሻለኛል።

Originally posted at BBC Amharic

Hintset's Pick

Hintset's Pick is a collection of hand-picked articles from different websites.

Share this article:

ጕራማይሌው የቴሌቪዥን አገልግሎት

ይህ ያለንበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን የአስተሳሰብና የባህል ሽግግር/ለውጥ እጅግ በጣም ፈጣን የሚባል ነው፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ በአንድ አካባቢ ያሉ አስተሳሰቦች፣ ፍልስፍናዎች፣ ሃይማኖታዊ ተዋስኦዎች፣ ወዘተ. ወደ ሌላው አካባቢ ለመድረስ ዓመታትን፣ ምናልባትም ዘመናትን የሚያስቆጥሩበት ረጅሙ ጊዜ አሁን አጥሯል፡፡ ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች ቢሰጡም፣ የብዙኀን መገናኛ ሚና ግን ጉልሕ ሥፍራ የሚይዝ እንደ ሆነ ከብዙዎች የተሰወረ አይደለም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

ጋሽ በቀለ ይናገራል

መጋቢ በቀለ ወልደ ኪዳን ለአብዛኞቹ አንባቢዎቻችን የምናስተዋውቃቸው ዐይነት ሰው አይደሉም። በአጭሩ ለዐርባ ዓመታት ያህል በዘለቀው አገልግሎታቸው፣ መጋቢ ከሆኑባት የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ባሻገር ብዙዎቹን አብያተ ቤተ ክርስቲያናት፣ ከተማ ገጠር፣ አገር ቤት ውጪ አገር ብለው ያገለገሉ መሆናቸው፣ በወጣቱም ሆነ በቀደሙት ዘንድ ታዋቂ አድርጓቸዋል። ለዚህ ነው የምናስተዋውቃቸው ዐይነት ሰው አይደሉም ማለታችን። መጋቢ በቀለ በብዙዎች ዘንድ “ጋሽ በቄ” በሚል ስም ነው የሚጠሩት።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.