
Ordinary and Extraordinary: A Day at the Asbury Awakening
“As a historian of American religious history with an interest in revivals and revivalism, I was excited to experience firsthand what a revival of this magnitude felt like.” Doug Hankins
[the_ad_group id=”107″]
ርእስ፡- በዚያን ጊዜ (ሁለተኛ ዕትም)
ጸሐፊ፡- ተስፋዬ ጋቢሶ
የታተመበት ዓመት፡- 2002 ዓ.ም.
አሳታሚ፡- የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲንያን
ገጽ፡- 134
ዋጋ፡- አልተጠቀሰም
“በዚያን ጊዜ” የተሰኘው የመጋቢ ተስፋዬ ጋቢሶ መጽሐፍ እርሱ ራሱ በመግቢያው እንዳለው “ተመጥኖ የቀረበ”፣ በ134 ገጾች የተቀነበበ የታሪክ ማስታወሻ ነው። የፊት ሽፋን ጨለማ ከብርሃን ጋር የሚያደርገውን ብርቱ ፍልሚያ እየጠቆመ የብርሃንን አይቀሬ ድል ያበሥራል።
በአምስት ምዕራፎች የተዋቀረው ታሪክ የውቅሩ አነዳድ የሁነቶችና የቦታ ቅደም ተከተል ስልት ይዞ የሚሄድ ነው። ከይርጋለም ሙሉ ወንጌል ምሥረታ ጅማሬ ተነሥቶ ወዲያው የጀመረውን ስደትና መከራ በዚያው ከተማ ቀበሌ፣ ኋላም በወኅኒ ቤቱ፣ የኋላ ኋላም በቦረና ነገሌ ማረሚያ ቤት፣ ተመልሶ በይርጋዓለም እየዞረ ቀይቶ የእስራቱ ቀንበር እስከተሰባበረበት የመጨረሻው ሰዓት ድረስ ይዘልቃል። የማያምታታ ግልጽ አከፋፈል ነው፤ የየምዕራፍ መካከል ቅንጣቶቹም ገላጭ፣ መሳጭና ዕቅጭ ናቸው።
በአራት ሰዎች የቀረቡ ሰባት ገጾች ያህል የፈጁ “መግቢያዎች” አሉ፤ ለመጽሐፉ የገጽ ዐቅም አልበዛም እንዴ ሊያሰኙ የሚያስቃጡ። ይሁን አንጂ በእርጋታ ላነበባቸው እንዲያውም ለመጽሐፉ ጉልበት የጨመሩ፣ ድልዳል የሰጡ በጣም አስፈላጊ መግቢያዎች ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። “ስለዚህ ወቅት” የሚለው አጭር መግለጫ የዘመኑን መልክ፣ የዚያን ጊዜይቱን ኢትዮጵያንና መሪዎቿን የሚያሳይ የታሪክ መቆናጠጫ ነው። “ስለዚህ መጽሐፍ” የተሰኘው ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን አንጻርና ከተስፋየ ጋቢሶ የትመጣ ጋር የተያያዘ ጥሩ ማዋዣ ነው። “መቅድም” ተብሎ የቀረበው ደግሞ ይህን የአንድ ዘመንና የአንድ ቦታ ስደት ከጠቅላላው ዓለም አቀፍ የክርስትና ታሪክ ጋር ይያያዛል። በመጨረሻም፣ የራሱ የጸሐፊው መግቢያ መጽሐፉ የተጻፈበትን ዓላማ ጥርት አድርጐ በማሳየት በጨዋነትና በትሕትና ወደ ታሪኩ ድግስ ይጋብዘናል።
መጽሐፉ መጠኑ ትልቅ አይደለም፤ ይሁን እንጂ እምቅ ነው። ብዙ የሁነቶች ንብርብር፥ የስሜቶች ውጣ ውረድ፥ ብርቱ ብርቱ መልእክቶች፥ ክርስቲያኑን ማኅበረ ሰብ የሚያበለጽጉ ሁነኛ ጭብጦች የታመቁበት መዝገብ ነው። ጸሐፊው ራሱ በመግቢያው እንደጠቀሰው ዐልቦ ግነት ትረካ መተረክ ፈልጓል። ምንም የተጋነነ ነገር የለም። ግነት ያለ እንደሆን ልዑሉን ፈጣሪ የማግነን ሥራ ነው። በመላ መጽሐፉ ውስጥ ውዳሴ አምላክ ሳይሰሰት ቀርቧል። የመከራን በርኖስ የተከናነቡበት ሁነቶች በደማቅ የምስጋና መጎናጸፊያ ሲያሸበርቁ ይታያል።
የመጽሐፉ ዕይታ ወይም ግምገማ በቅርጽ ጉዳይ ላይ ብቻ ሲማስን በውል ፋይዳው እጅግም በመሆኑ በተለይ የክርስቲያን ጽሑፍ ደግሞ እጅጉን ባለ ይዞታ መሆን ስለሚያስፈልገው የእኔም ትኩረት ወደዚያ እንዲያጋድል አድርጌአለሁ። መጽሐፉ ላይ ጎልተው የወጡ ጭብጦች ወይም ልቡናችን ውስጥ የሚዘልቁ መልእክቶች ምንድን ናቸው?
በጽኑ መከራ ውስጥ፥ በድብደባ፥ በግርፋት፥ በዛቻ፥ በርግጫ፥ በንቀት በስድብ በብርቱ እንግልት ውስጥ በርትተው ሊቆሙ የቻሉበትን ምስጢር ከምንም ሁኔታ ጋር አያገናኙትም። መጽሐፉ በተደጋጋሚ የእግዚአብሔር ጸጋን ድጋፍ ያትታል፣ ያከብራል። “… ልቤ በታላቅ ደስታ ስለተሞላ የምሆነውን አጣሁ:: በጸሎት መቀጠል አልቻኩም። ተነሥቼ አንዳንድ ነገር ልጽፍ ብሞክር፣ ደስታው አላሠራህ አለኝ።” ገጽ 107 (ገጽ 40-41 ገጽ 80 እንዲሁም ገጽ 107 ናሙናዎች ናቸው)። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጠው የመንፈስ ቅዱስ ጉልበት ሰጪ ጸጋ መከራ ተቀባዮቹን ጸጋማ (gracious) አድርጓቸዋል። ለሚያሰቃይዋቸው ይጸልያሉ፣ ለአገራ ቸው መልካሙን ይመኛሉ፣ አለቆችን በርኅራኄና በበጎ መንፈስ ያናግራሉ፣ ጸጋ ይናኛሉ።
ታሪኩ የከፍተኛ መሥዋዕትነት ምስክር ነው፤ ሁላቸውም ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ሲያልፉ በሚያስገርም ጽናት ነበር። አንዱ ለሌላው ራሱን አሳልፎ እስኪሰጥ ድረስ (ገጽ 18-19) በምርመራ ጊዜ በኅብረት ጽናት ቆሙ (ገጽ 45)። ከጠያቂዎቻቸው የሚሰጣቸውን ጥቂት ምግብ ሳይበቃቸው ለሌች እስረኞች ያካፍሉ ነበር (ገጽ 42)። በዚያ የችግር ቦታ ብዙ ጊዜ ይጦሙ ነበር። ለክፉ ቃለ መጠይቆች ሕይወት የሚያስከፍል ቀጥተኛ መልስ ይሰጡ ነበር። (ገጽ 109-114)
በዚህ የመከራ ታሪክ ውስጥ በጉልሕ እንዲታይ የተደረገው የአንድ ወይም የጥቂት ግለ ሰቦች ልዩ ጀግንነት ሳይሆን፣ የክርስቶስ ማኅበረ ሰብ ጽኑ የወንጌል ምስክርነትና የወገኖች ሁሉ ሥቃይ ተካፋይነት ነው። የመጽሐፉ ዋና ተውላጠ ስም “እኔ” ሳይሆን “እኛ” የሚለው ነው። ይህም “እኛ” የታሰሩትን ዐሥርና ሃያ ሰዎች ብቻ ሳይሆን የነበሩበትን ቤተ ክርስቲያን፣ ከዚያም አልፎ ብሔራዊዋን የአማኞች ማኅበረ ሰብ በሙሉ ይጠቀልላል። በተያያዥ መከራውም ደስታውም የሁሉ መሆኑ ይፋ ተደርጓል። ለአብነት ዜናው ሲሰማ በሚል ንዑስ ሥር የተጻፈውን ይመልከቱ (ገጽ 128)።
ይህ መጽሐፍ “ድሩም ማጉም” እንደሚባለው በየዝርዝር ትዕይንትና በየቃለ ምልልሱ በእግዚአብሔር ቃል የተሞላ ነው። ቃሉ የመከራው ተርጓሚ፣ የጸሎት መነሻ፣ የመጽናኛ ገበታ፣ የጥያቄዎች መልስ፣ የስደት ዘመን ምሪት፣ የስደት ፋታ ተስፋ ሆኗል ወዘተርፈ… በሚያስገርም ሁኔታ “ቃሉ በሙላት ይኑርባቸው” የሚለው የጳውሎስ ምክር በገቢር የታየበት ትንሽ ትልቅ መጽሐፍ ነው። አተረጓጎሙ የሚያመረቃ ነው። (ለምሳሌ ገጽ 36፣ 91፣ 43፣ 54፣ 75)
እዚህ መጽሐፍ ውስጥ ብዙ ጸሎቶች፣ ጥልቅ ጸሎቶች፣ ቅኖች ጸሎቶች ተመዝግበዋል። በሚሰማ አምላክ ላይ የነበራቸው ተአምኖ፣ የጌታና ሎሌ አክብሮታዊ ቋንቋ፣ የአባትና ልጅ ፍቅራዊ ቋንቋ፣ የሲቃና የምጥ፣ የምስጋናና የሐሴት ቋንቋ የተሞሉ ጸሎቶች ተመዝግበዋል። ምሪት ጥየቃ፣ ጸጋ ልመና፣ የነፍስ ዐደራ ሁሉ በጸሎት የተሄዱ መንደሮች ናቸው።
ከጸሎት ሌላ መጽሐፉ በመዝሙር ዜማ የደመቀ ነው። በየምዕራፉ ላይ መዝሙር አለ፤ “ከጨለማ ጋር ብርሃን ሲዋጋ (ገጽ 10)፣ “የመከራ ጉም”፣ “አትሸበር በርታ”፣ (ገጽ 47)፣ “እግዚአብሔር ሲረዳ” (ገጽ 85)፣ “መጻተኛው ተጽናና” (ገጽ 81)። እስር ቤት ውስጥ ብዙ መዝሙር ተጻፈ፣ ተዘመረም፤ ቢያንስ 40 መዝሙሮች (ገጽ 127)። ከፍተኛ የአመስጋኝነት ጸጋ የተገለጠባቸው ሰባት የታሪክ ዓመታት ነው። መጽሐፉ ታሪክ እየተረከ፥ ስለ ሰዎች እያወራ፥ የዚያን ዘመን ሽታ እያሸተተን ትልልቅ ዘመን ተሸጋሪ ትምህርቶችን ይሰጠናል። ይህ አስተማሪነት ከትረካ ቋንቋ ዘልሎ ወጥቶ፣ ከዚያ ዘመን ችንካር ተፈትቶ ስለ አሁን ስለ እኛ ሁኔታ ብርቱ መልእክት ሆኖ በማጠቃለያው ገጽ ላይ ቀርቧል (ገጽ 133-34)።
“ነጻነታችን ኃላፊነት በተሞላ መንገድ እንጠቀምበት። … መናኛ ጉዳዮችና ያለ ልክ በመዝናናት የምናጠፋው ጊዜ የለንም። ደስታችን … በታላቁ የወንጌል ተልእኮ መሳካት ይሁን። … እግዚአብሔር እስከ ዛሬ ድረስ በጸጋው ረድቶናል። እስከ ፍጻሜውም ይረዳናል።” (ገጽ 134) በሚል ቃል ያነቃቃል።
የመጋቢ ተስፋ መጽሐፍ አነሣሡም ድምድማቱም በዚያን ዘመን የነበረችይቱ የክርስቶስ ማኅበርና የጥቂት አባሎቿ የመከራና ድል ትውስታ ነው። ይሁን እንጂ ያች ማኅበር የነበረችበት ኅብረተ ሰብ ቀለም፣ አብዮት የተባለው ተዐብና የአመለካከት ዝመትና የመሪዎቿ ነገረ ሥራ ሳይጠቀስ ለማለፍ አስቸጋሪ በመሆኑ በመጠኑ ተተርኳል።
የፍልስፍነው መሠረት ቁስ አካላዊነት የነበረው ማርክሲዝም-ሌሊንዘም ለመንፈሳዊ ነገር ቁብ የለሽ ብቻ ሳይሆን እንዲውም ይሁነኝ ብሎ በተጀራጀ መልክ “በባህለ አብዮት” ቃና አምላክ የለሽነትን የሚሰብክ ነበር። በእስር ቤት ውስጥ እነ ተስፋዬ በተደጋጋሚ የቀረቡላቸው ቃለ መጠይቆች እንደሚያሳዩት፥ የመፈታታቸው ወቅት ሲደርስ በግድ ይሰሙት የነበረው ዲስኩር ሁሉ ጸረ እምነት እንደ ነበረ ግልጽ ተደርጓል። (ገጽ 124)
ሰብአዊ መብትና የእምነት ነጻነት እንደሚያከብር፣ ዐይኑን ሳያሽ በሚናገረው አገዛዝ፣ ለጆሮና ለዐይን የሚዘገንን የጭካኔ ተግባር ይፈጸም እንደ ነበረ መጽሐፉ ፍንተው አድርጎ ያሳያል። በራቁት ጉልበት በአስፋልት መንገድ ላይ በእምብርክክ እያስኬዱ፥ በቁርና በራብ ሰብአውያንን በሚያሰቃይ ቦታ ደጅ እያሰሩ፥ በርግጫ በጥፊ እየደበደቡ፣ ያለ ምንም ፍርድ ሰባት ዓመታት ያህል በወህኒ እየማቀቁ ሰዎችን እንደ ከብት የነዱ የዚያ መንግሥት አለቆች የተባለው አብዮት ፍሬዎች ነበሩ።
ያ አብዮት የፈጠረው የሰው ዐይነት እርስ በራሱ የተፈራራ፥ የተጠላላ እውነታን ግግም ብሎ የሚክድ፥ በጭካኔ ብርታት ጫፍ ለመድረስ ፉክክር የያዘ አስፈሪ ትውልድ ነበረ። ይህ “መጽሐፉ በየገጹ ይህን ነፍስ አልባ የቆመ ሠራዊት በመጠኑም ቢሆን ገለጻ ዐሳይቷል። (ገጽ 44፣ 51-56፣ 88፣ 124)
“ካነጋገር ይፈረዳል፤ ካያያዝ ይቀደዳል” እንዲሉ ምንም እንኳ የ“በዚያን ጊዜ” መጽሐፍ ትልቁ ዋጋ ይዘቱ ቢሆንም፣ ለቡናው ጀበና ማህቶት ማረፊያ እንደሚያስፈልገው ሁሉ፣ የጽሕፈት ዘይቤው ይዞታውን ማቅረቢያ መሣሪያ ነውና ቸል ተብሎ አይታለፍም። የእውነተኛ የታሪክ ዘገባ በመሆኑ ይህ መጽሐፍ የልብ ወለድ ታሪክ በሚታይበት ቴክኒክ ሙሉ በሙሉ ሊፈተሸ አይገባም፤ አካሄዳቸው እየቅል ነውና። ይሁን እንጂ ደግሞ ሁለቱም ትራኬዎች በመሆናቸው በቀጭን ደምም ቢሆን ይዛመዳሉ። ስለዚህ ተመሳሳይ መሥፈሪዎች ላንሣ፡-
መጽሐፉ በትዕይንት የተሞላ ነው፣ ከቦታ ቦታ የሚዞር ታሪክ ነው። የገለጻን አስፈላጊነት አጉልቶታል። በሁሉ ስፍራ የሚበቃ ገለጻ ባናገኝም፣ የተገኙት ግን በምስል ከሳችነትም ሆነ በአግባብነት የሚመሰገኑ ናቸው። ለምሳሌ ገጽ 50 የሜዳው ላይ ስፖርት፣ ገጽ 61- 62 የእስር ቤት ገለጻ፣ ገጽ 84-85 የቦረና ጉዞ በጥሩ ምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው።
በታሪኩ ውስጥ የተጠቀሱ በቀኝም በግራም ብዙ ሰዎች አሉ። የእነዚህ ሰዎች ምስል ባያሌው ቀርቧል ለማለት ባያስደፍርም፣ አንዳንዶቹ ግን በዐይነ ኅሊናችን እንዲታዩ ተደርገዋል (ገጽ 52)። ዋናዎቹ ባለ ታሪኮች በደንብ ቢሳሉልን ኖሮ የበለጠ ይጣፍጥ ነበር።
የመጽሐፉ አንድ ደማቅ ቀለም ዝርዝራቸው የተጠበቀ፥ የስሜት ሙቀታቸው የሚሰማን በአብዛኛው በእስረኞችና በአሳሪዎቻቸው መካከል የነበሩ ምልልሶች ናቸው። ለታሪኩ የበለጠ ሕይወት ሰጥተውታል። ከአምስት ያላነሱ ምልልሶች ተመዝግበዋል። (ገጽ 37፣ 45፣ 109፣ 111-114)
ታሪኩ በአብዛኛው በዐራት ግድግዳ ውስጥ የተፈጸመ ቢሆንም ያለ ወንጀል የታሰሩ፣ ያለ ፍርድ የሚሰቃዩ፣ በሕግ ሳይሆን በአለቆች አምባ ገነን ፈቃድ የየዕለት እንቅስቃሴአቸው የሚነዳ ስለ ነበር ብዙ የማይታወቁ ’ነገ ምን ሊሆን ነው?’ የሚያሰኙ ልብ የሚያንጠለጥሉ ሁነቶች ሞልተውበታል። ደራሲውም እነዚህን ልብ ሰቃዮች በታሪኩ ውስጥ አስገብቷቸዋል። (ለምሳሌ ገጽ 44፣ ገጽ 47፣ ገጽ 76)
መጽሐፉ የመከራ ዘገባ ቢሆንም ፈገግታ ግን አልተለየውም። በሥቃይ መካከልም ሣቅ እንዳለ ያሳያል። ለትረካው ደስ የሚል ቃና ሰጥቶታል። ገጽ 51 “ካልሲው ጫማ መሰለ”፣ ገጽ 55 “እንክትክት ብሏል’ኮ”፣ ገጽ 57 “እንደ ንጉሡ አጎንብስን” ያንብቡ።
ደራሲው ለታሪክ ሐቅ ያለው ጥንቃቄ ትልቅ ነው፤ ይህም የሁነቶች ቀናት በዝርዝር መያዙ፣ የንግግር ቃላት በትክክል በመቅረባቸው፣ ውሳኔዎች፥ ደብዳቤዎች የሰዎች ስሞች፥ ማዕረጎች ሁሉ ሳይዛነፉ በመጻፋቸው ይታያል። ይሁን እንጂ ይህ ጥንቃቄ አንዳንዴ የትረካውን ሂደት የፖሊስ ዘገባ ወይም የጋዜጠኛ ሪፖርት ገጽታ የሰጠው ይመስላል። ይህ እንዳይሆን በእሳት ዳር የቀረበ ወግ እንዲመስል አንዳንድ ዝርዝሮች ዐውቆ መተው ተገቢ ነበር። ለምሳሌ ልዩ ምክንያት ከሌለ “በ11/10/75” ሳይባል ይልቁን “በዚያ ዓመት የክረምር መባቻ ሰሞን” እየተባለ ቢተረክ። እንደዚህ የመሳሰሉ ዘገባዊ ገለጻዎች ተቀንሰው ቢሠፍሩ ፍሰቱ የተሻለ ሆኖ ይሄድ ነበር።
የተስፋዬ ጋቢሶ መጽሐፍ ደራሲውን መምሰሉ አይቀርም። ብዙ አንባቢዎች ሳይሉት ያልቀረው ነገር ‘ምነው ባጭር ባጭሩ አቀረብኸው? የሆነው ነገር ብዙ አንተ የጻፍከው ጥቂት ለምን ሆነ?’ የሚል ነው። ርግጥ ነው ገና ከመጸሐፉ መግቢያ እንደነገረን ጸሐፊው የደለበ ታሪክ ሳይሆን ምጥን ምስክርነት ሊሰጠን መፈለጉ አይካድም። የደራሲው የጽሕፈትም የንግግርም መርሖ ፈረንጆቹ “Do not break the silence unless you improve it” “የተሻለ ነገር የማታቀርብ ከሆነ ዝምታን አትስበር” የሚል ይመስላል። መርሖው ድንቅ ነው! ይሁን እንጂ አንዳንድ ዝምታ ለጨዋታም ሲባል፣ መኖራችንንም ለመፈተሽ ሲባል ቢሰበር ምንም አይደል። በጥቂቱ የተገለጹ ሰፋ ተደርገው ቢቀርቡ ተነባቢነትን የማያደናቅፉ፣ ይልቁን የሚጨምሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ቀደም ተብሎ እንደተገለጸው የባለ ታሪኮችን ገጽ በጉልሕ እንድናየው በዝርዝር ቢሳሉልን፥ ስሜቶች በበቂ ቃላት ቢተነተኑ፥ የኅብረተ ሰቡ አኗኗርና የሃይማኖት አቋሙ ዘለግ ተደርጎ ቢወራ፥ ወዘተርፈ።
በዚህ ታሪክ የቀረቡት እኅቶችና ወንድሞች ጠንካራ የእምነት አቋም፥ የጸሎት ትጋትና የመንፈስ ጽናት እጅግ የሚያስገርም በተመስጦ ለሚያነበው የሚያንጽ የክርስቶስ ደቀ መዝሙርነት አርአያ ነው። ነገር ግን አንባቢው ’አንዳንድ ጊዜ ከዘመዶች ወይም ከወዳጆች ጫና የተነሣ ልባችሁ አልተፈታምን? ከመከራው ጽናት የተነሣ ጥሎ ለመሄድ የተፈተነ ሰው አልነበረምን? እርስ በርስ የተቀያየማችሁበት ጊዜ አልነበረምን? ሌሎችስ ያነከሱ ነገሮች አላጋጠሙዋችሁምን?’ የሚሉ ትያቄዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ወደ ታሪኩ ማብቂያ አካባቢ ከባድ የልብ ማመንታት የነበረበት ወቅትን ጸሐፊው አስፍሯል (ገጽ 116፣ 118)። ይህን መሳይ ሁኔታዎች በግልም በማኅበርም የነበሩ ከሆነ ቢጻፉ አንባቢው የበለጠ ቅርብ እንዲሆን፣ ከራሱም ጋርም ለማዛመድ ይጠቅመው ነበር።
የሽፋኑ የኋላ ገጽ አስቀድመው ባነበቡት ሰዎች አስተያየት ታጭቋል። ዘርዘር ቢል ምናልባት የሁለት ሰዎች ብቻ አስተያየት ቢቀርብበት ወይም የአምስቱም በአንዳንድ መሥመር ብቻ ቢጻፍ ለዐይን ዘና፣ ለንባብም የተመቸ ያደርገው ነበር። ፊቱም ቢሆን የተሸለ የአቀላለም ዘይቤ ሊከተል ይችል ነበር። አንዳንድ አርእስት በማይሆን ቦታ በገጽ ግርጌ መጀመሩ ተገቢ ካለመሆኑ በተጨማሪ ከንዑስ ምዕራፍ ወደ ሌላው ሲሸጋገር ከጊዜ ማያያዣ ይልቅ ሌላ መግለጫ ቢሰጥ ይሻል ነበር (ገጽ 21)። ለአንዳንድ አርእስት የተሰጠ አሰያየም ብርቱ አይደለም፤ ለምሳሌ “ተጨማሪ ሁነቶች” (ገጽ 65)። ሌላው መጠቀስ ያለበት የፎቶ ግራፍ ጥራት ችግር ሲሆን ምናልባት በዚያን ጊዜ ከነበረው ዝቅተኛ የቴክኒክ ሁኔታ የተከሰተ ሊሆን ይችላል።
የተባለው ሁሉ ተብሎ ይህ መጽሐፍ የክርስቶስ ወንጌል አሸናፊነት፣ የልዑል እግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት ሳያቅማማ ይመሰክራል፤ “ማን ያርዳ የቀበረ ማን ይመስክር የነበረ” እንዲል።
Share this article:
“As a historian of American religious history with an interest in revivals and revivalism, I was excited to experience firsthand what a revival of this magnitude felt like.” Doug Hankins
ሚክያስ በላይ ከዶ/ር ንጉሤ ተፈራ ጋር ባደረገው ቆይታ፣ አማኝ ማኅበረ ሰቡን በሚመለከት ስለ ኮሙኒኬሽንና የመገናኛ ብዙኅን አጠቃቀም፣ አብያተ ክርስቲያናት ከኅብረተ ሰቡ ጋር ስላላቸው መስተጋብር እንዲሁም በአጠቃላይ ከቤተ ክርስቲያንን አመራር ጋር ሊያያዙ በሚችሉ ጭብጦች ዙሪያ ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል።
ቤተ ክርስቲያን ከ2000 ዓመታት በላይ ባስቈጠረው ዕድሜ ዘመኗ፣ በተለያዩ ባህሎች እና ወጎች ውስጥ አልፋም እንኳ ቢሆን ታላቁን የክርስቶስን የማዳን መልእክት ይዛ ስለ መቀጠሏ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ ይህ ሲባል ግን በዘመናቱ መካከል ከዚህ መሠረታዊ መልእክት የተለየ ያስተላለፈችባቸው ጊዜያት የሉም ማለት አይደለም፡፡ ዛሬም እንኳ ስሑት የሆነ መልእክት የምታስተላልፍበት አጋጣሚ እንዳለ እናስተውላለን፡፡ (“ስሑት” የምንልበት ሚዛናችን መጽሐፍ ቅዱሳዊው ክርስትና መሆኑን እዚህ ላይ ጠቊሞ ማለፉ ተገቢ ይሆናል፡፡) ይህ ታላቁ መልእክት በንጽሕናው እንዳይተላለፍ እንቅፋት እየገጠማቸው ካሉ ሕዝቦች መካከል ደግሞ አፍሪካውያኑ ይገኙበታል፡፡
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
Add comment