[the_ad_group id=”107″]

የነቢያቱ “መደመር” እና የፈጠረው ስሜት

“ይህ በጣም ጥሩ የሆነ ጅማሬ ነው።” ይላል ሄኖክ ሚናስ፤ “ኅብረቱ አራት ነቢያትን ‘በአጋር አባልነት’ ተቀበለ” የሚለውን ዜና ከሕንጸት ድረ ገጽ ላይ ካነበበ በኋላ የተሰማው ምን እንደ ሆነ በጠየቅነው ጊዜ። ሄኖክ ሚናስ እንደ ብዙ ምእመናን ሁሉ ጉዳዩን በርቀት ሆኖ ሲከታተል የነበረና ይሄ ነው በሚባል የአገልግሎት መዋቅር ውስጥ የማይሳተፍ አማኝ ነው። “ኅብረቱ ያስቀመጠውን ጠንካራ መስፈርቶች ለመቀበል ትኅትና ያሳዩትን ወንድሞች ምሳሌነት ሳላደንቅ አላልፍም። ሌሎችም ፈለጋቸውን ሊከተሉት የሚገባ ርምጃ አድርጌ ነው የምወስደው።” ይላል።

ለሄኖክ ማናቸውም ዐይነት የስሕተት ትምህርቶችና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ልምምዶች ይህን በመስለና ወንድማዊነትን ማዕከል ባደረገ መንገድ ነው መቅናት ያለበት። ምክንያቱም ይህ አካሄድ፣ “የእግዚአብሔር መንግሥት መስፋትን ያረጋግጣልና” ይላል።

የሄኖክ ሚናስ አስተያየት ግን ይሄ ብቻ አይደለም፤ ነቢያቱ ይህን ያህል ዝቅ ብለው ከመጡ፣ ኅብረቱ በበኩሉ ሊሄድ የሚገባው መንገድ ደግሞ አለ። “እነዚህ ወንድሞች የጀመሩትን ለውጥ እንዲገፉበት ዕድል መስጠት ይገባል። ‘በየስድስት ወሩ ይገመገማሉ’ የሚል ዐይነት አስገዳጅ መስፈርት ማስቀመጥና ጫና ማድረግ አይጠቅምም።” ሲል ኅብረቱ በዚህ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ያሳስባል።

የሄኖክን ሐሳብ የሚጋሩና የነቢያቱን ወደ ኅብረቱ መቀረብ በደስታና በአዎንታዊ ጎኑ የተመለከቱት ብዙ ሰዎች ናቸው። በተለይ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ከዚህ ቀደም አገልጋዮቹን አቅርቦ መንገድ አላሳያቸውም፣ ከሩቅ ሆኖ ነው የሚያወግዛቸው ይሉ የነበሩ ወገኖች በአሁኑ የኅብረቱ ርምጃ የፍንጠዛ ያህል ደስ ተሰኝተዋል። በዘመኑ ቋንቋም ኅብረቱ “በመደመር ፍልስፍና” ውስጥ ገብቷል እያሉ የሚያቆለጳጵሱትም አልጠፉም።

ረቡእ መስከረም 9

ረቡእ መስከረም 9 ቀን 2011 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በ8፡30 በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ጽ/ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ረፋዱ ላይ ተነገረን። በተባለው ሰዓት ደርሰናል። ሁነቱን በቪዲዮ ቀርጾ ለማስቀረት የኅብረቱ ጽ/ቤት የቀጠራቸው የካሜራ ባለሙያዎች ሥራቸውን በመከወን ላይ ናቸው። ከደቂቃዎች በኋላ መጋቢ ጻድቁ አብዶ ጋዜጣዊ መግለጫው ወደሚሰጥበት ስብሰባ አዳራሹ ገቡ። እሳቸውን ተከትለው፣ ነቢይ ኤርሚያስ ሁሴን፣ ነቢይ ሱራፌል ደምሴና ባለቤቱ መክሊት ፊልጶስ ከመጋቢ ጻድቁ ቀኛና ግራ ተቀመጡ።

መጋቢ ጻድቁ “እንጸልይ” አሉና ጸሎቱን ራሳቸው መሩ። ጸሎቱ እንዳለቀም፣ “ዛሬ በእዚህ ስፍራ ከአራት አገልጋዮች ጋር ነው መገናኘት የወሰንነው።” ካሉ በኋላ፣ ባለፈው ሰኞ ከሰዓት በኋላ ከ150 በላይ ከሆኑ፣ የተመዘገቡና አስተምህሯቸው ከወንጌላውያን (በኢትዮጵያ ዐውድ፣ ካሪዝማቲክ ጴንጤቆስጤ ማለታቸው እንደ ሆነ ጠቆም አደረጉ) ያልራቀ፣ ነገር ግን የኅብረቱ አባል ለመሆን ደግሞ መስፈርቱን ከማያሟሉ ጋር መነጋገራቸውን ገለጹ። አያይዘውም፣ እነዚህን ቤት እምነቶች ኅብረቱ የሚያቅፍበትን መንገድ ከቦርድ እስክ ጠቅላላ ጉባኤ እየመከረበት መሆኑንና በቦርዱ የጸደቀ የመግባቢያ ሰነድ መዘጋጅቱንም ተናገሩ።

“ዛሬ በዚህ ስፍራ አራት ወንድሞች እንዲገኙ እንጠብቃለን።” ያሉት መጋቢው፣ ከአራቱ አንደኛው ግን እክል የገጠመው መሆኑን በመጨረሻ ሰዓት ላይ እንዳሳወቃቸው ገለጹ። ይህ ሰው አገልጋይ/ነቢይ ዮናታን አክሊሉ ነው።

መጋቢ ጻድቁ ኅብረቱ በተለያዩ የጸጋ ስጦታ እናገለግላለን የሚሉትንና የራሳቸው የቴሌቪዥን ጣቢያ ያላቸውን በሦስት ከፍሎ እንድሚያይ ማብራሪያ ወደ መስጠቱ ገቡ። በዚሁ መሠረትም፣ “አንደኛው ቡድን በአስተምህሮውም፣ በልምምዱም፣ በሞራል አቋሙም በጣም የራቀ ነው” አሉ። “ሁለተኛው ደግሞ የአስተምህሮም ሆነ፣ የሞራል ወይም የልምምድ ችግር ወይም ጥያቄ አለ ብለን የምናስበው ነው። ሦስተኛው ቡድን የአስተምህሮ ችግር የለበትም ወይም ሳያውቅ አንዳንድ አስተምህሮ ሊነካው ይችላል፤ ልምምድ አካባቢ ግን ችግር” ያለበት መሆኑን አስረዱ። እነዚህኞቹን ለማቅናትና ለመመለስ እንደሚሠሩ ከዚህ ቀደም ኅብረቱ ያወጣውን የአቋም መግለጫ ጠቅሰው አስታወሱ።

“እነዚህ አራት አገልጋዮች በዕድሜያቸውም ወጣቶች ናቸው” ያሉት መጋቢ ጻድቁ፣ የመጡባቸው ቤተ እምነቶችም ከነባር ቤተ እምነቶች በመሆናቸው ጭምር፣ ምክርና ንግግር ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገለጹ። በዚሁ መሠረት፣ በተስማሙባቸው ነጥቦች ላይ ስምምነት እንደሚያደርጉና ስምምነቱ በየስድስት ወሩ የሚገመገም እንደሚሆን አብራሩ። አያይዘውም ሱራፌል፣ መስፍንና ዮናታን ከሐዋሳ መሆናቸውንና ከደቡብ ኅብረት ጋር በዚሁ ጉዳይ ላይ ምክክር ሲደርግ መቆየታቸውን ተናገሩ። በዚህ መካከል የነቢያቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሠራተኞች መግባት ጀመሩ። ከዚህ በኋላ የስምምነት ሰነዱ ላይ ያለውን የአጋር አባልት ግዴታና ኀላፊነት ምን እንደ ሆነ፣ በተመሳሳይም የኀብረቱ ግዴታና ኀላፊነት ምን እንደ ሆነ ገለጻ አደረጉ። ከዚያም የፊርማ ሥነ ሥርዐቱ ተከናወነ።

ነቢያቱ ምን አሉ?

የ“አጋር አባል” ስምምነት በተደረገ ዕለት ከአራቱ ሦስቱ ነቢያት በኅብረቱ ጽ/ቤት ተገኝተው አጋር አባል በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ በዚህ መልኩ ነበር የገለጹት።

ነቢይ ኤርሚያስ ሁሴን

“ስለ እኔ በጠለቀ ሁኔታ የማወቅና የማጣራት፣ ከሚነሡት አሰተያየቶች ጀምሮ፣ በግል ደግሞ እነሱ እስከሚያዩትና እስከሚረዱት ድረስ፣ ብዙ ዐይነት ሁኔታዎች፣ ክርክሮች፣ ተግሳጾች፣ ማቆናቶች፣ በጣም ደስ በሚል ሁኔታ ተካሄዷል። የአንድ ዓመት ጊዜ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ምን ያህል ወደ ቀናው መንገድ ለማምጣትና በትውልድ መኻል ክፍተት እንዳይኖር፣ የጠራና ግልጽ የሆነ የእግዚአብሔር ሥራ እንዲሠራ ምን ያህል እንደተጉ፣ እኛም ምን ያህል እንደ ተመከርን፣ እንደ ተገሰጽን፣ የሚያቀኑ ሐሳቦችን እንዳለፍን፣ ከዚህም ወረቀት በላይ የማቅናት፣ የማስተማር ጊዜ ነበር። እኔ በግሌ በጣም የቀና ነገር አሳልፌአለሁ።

“አበክሬ መናገር የምፈልገው፣ ዕድል እንዲሁም ደግሞ ዕውቅና ባለ ሰዓት ላይ ጎበጥ ብሎ ወደ ኅብረቱ ለመግባትና ከኮሚትመንት በላይ ድጋሚ ኮሚትመንት መግባት፣ ነጻነትን ለሚወድድ ሰው ወይም ነጻነትን በመውደድ ለሚያገለግል ሰው አይመችም። ይበልጥ መልካም የሆነ ቀንበር፣ ለነገ እንድንተርፍ፣ ለሕዝቡ እውነተኛውን የወንጌል አገልግሎት እንድናገለግል የሚያስችል ትልቅና በጎ ሥራ ተሠርቷል። ለእኔ ዕድል ነው፤ ለቤተ ክርስቲያኔ ዕድል ነው፤ ከሥሬ ላሉትም አገልጋዮች እንዲሁም ደግሞ ለኢትዮጵያ ቅዱሳን ትልቅ ዕድል ነው፤ ምክንያቱም ሕዝቡን ስናገለግል በተገራና ጥንቁቅ በሆነ መልኩ እንድናገለግል ዕድል ስለሚፈጥርልን።”

ነቢይ መስፍን በሹ

“የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረትንና ዋና መጋቢ የሆኑትን መጋቢ ጻድቁ በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ። እግዚአብሔር በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ አንተን ተጠቅሞ ዛሬ ለመሰብሰባችን ምክንያት ሆነሃል። መጽሐፍ እንደሚል “ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ መልካም ነው” ያላል። አባቶች መኻል ተቀላቅሎ ምክር ለመስማት፣ ተግሳጽን ለመስማት በመቻሌ እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል። በቀጣይ ደግሞ በአግልግሎታቸን፣ መንገዱን እያሳያችሁን፣ እየመከራችሁን አብረን በመተሳሰብና በመደጋገፍ ለማገልገል ጌታ እንደሚረዳን ተስፋ አደርጋለሁ። እዚህ ላይ የተነሡት ነጥቦች ጥሩ ናቸው። እጅ ለእጅ መያያዝ ብቻ ሳይሆን፣ ልብ ለልብ መያያዝ ያስፈልጋል። ይህ ትልቅ ዕድል ነው፤ ለእኔም ለቤተ ክርስቲያኔም። ቀጣይ እንዴት መውጣት፣ እንዴት መግባት፣ እንዴት ማገልገል፣ እንዴት መመላለስ እንዳለብኝ ተጠንቅቄ ያየሁበትን መንገድ የማውቅበት ነው። በተጨማሪም ሌላ ሸክም ውስጥ ነው የገባነው። በማስተዋል፣ እግዚአብሔርን በመፍራት፣ በቅድስና ለማገልገል (እስከ ዛሬ በቅድስና እያገለገልን አይደለም ለማለት ሳይሆን)፣ ከዚህ በኋላ ያለን አካሄድ እግዚአብሔርን በመፍራት፣ እግዚአብሔር አክብሮ የሰጠንን ሕዝብ በታማኝነት ማገልገል መሪ ጉዟችን ይሆናል። በእኔም፣ በቤተ ክርስቲያኔም ስም አመሰግናለሁ።”

ነቢይ ሱራፌል ደምሴ

“ለብዙ ዘመን ስንናፍቅ፣ ስንጸልይበት የነበረው ነገር ዛሬ እውን ሆኖ ስናይ፣ እግዚአብሔር ያደረገልንን ነገር ከፍ አድርገን እንድናመሰግን ያደርገናል። እንደ ፕረዘንስ ኦፍ ጋድ ኢንተርናሽናል ቸርች፣ እንደ ግል አገልጋይም ብዙ የሚያሳስበንና የሚያስጨንቀን የነበረው ነገር ይሄ ነው። ከኅብረቱ ብዙ በአካል አልራቅንም። አባቶቻችን ከጎናችን እየደገፉን፣ በደቡብ [ኅብረት]፣ በሐዋሳ ያሉ፣ እንዲሁም በዋናው ቢሮ ያሉ አባቶቻችን እየመከሩን እንዲሁም ከክልል አብያተ ክርስቲያናት ጋር፣ ከዞን ጋር፣ ከከተማ አብያተ ክርስቲያናት ጋር በቀረበ መንገድ እያገለገልን ነበር። ሆኖም ግን የምንሄድበት መንገድ ሁሉ ይፋዊ የሆነ መንገድ አልነበረም። የሚያሳስበን ነገር እሱ ነው። አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ካሉ ደንቦች ጋር፣ አሠራር ጋር፣ ካሉት ልሞዶች ጋር ሁሉ ተስማምተንና በፍቅር እየሠራን ነው ያለነው፤ ግን ይሄ ነገር ኦፊሺያል አይደለም የሚለው የእኔ ትልቁ ሐሳብ እሱ ነበር።

“እግዚአብሔር ይሄንን ዘመን እንዲሰጠን፣ የዜማ ጊዜ እንዲያደርግልን፣ አብረን የምንሠራበት ጊዜ እንዲያደርግልን፣ ያለመሳቀቅ፣ በነጻነት የምናገለግልበትን ዘመን ጌታ እንዲያመጣ ስንጸልይ ቆይተናል። ያም ደግሞ ዛሬ በመሆኑ፣ በአካል እዚህ ሁላችንም ተገኝተን ይሄ ነገር በመደረጉ በጣም ደስ ብሎኛል። እግዚአብሔር የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትን ኅብረት ይባርክ። እውነተኛ ነገር ያላቸው ሰዎች፣ ከኅብረቱ ጋር ደግሞ አብረው መሥራት ይችላሉ። እንዲሁም የሚቀና ነገር ያላቸውን ሰዎች አቃንቶ አብሮ ለመሥራት በሮቹን ስለ ከፈተ ኅብረቱን ማመስገን እፈልጋለሁ። ከዚህ በኋላ የሚኖረን አገልግሎት፣ ከዚህ በኋላ የሚኖረን ርምጃ በሙሉ የአባቶችን ኮቴ እየተከተሉ፣ ለወንጌል እንቅፋት ሳንሆን፣ የእግዚአብሔርም ስም በእኛ ሳይሰደብ በቅርብ እየተመካከርን እንሄዳለን። እጅ ለእጅ ብቻ ሳይሆን፣ ልብ ለልብም ተያይዘን ከዚህ በኋላ አብረን እንሠራለን።

“ሌላው ብዙ ቅዱሳን በዓለም ዙሪያ ይህንን ቀን ስትናፍቁ ነበር፤ በተለይ የማስታውሰውና ብዙ ጊዜ ይህ ዘመን እንዲመጣ የምናፍቅበት፣ አንድ ትልቅ የእግዚአብሔር ሰው፣ በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ያሉ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያናችን መምጣት፣ አገልግሎታችንን መካፈል፣ ከእኛ ጋር ኅብረት ማድረግ በጣም ፈለጉ። ነገር ግን ‘ይህን ነገር ኦፊሻል ሳይሆን ዝም ብለን ብንሄድ የሚፋለስ ነገር ነው የሚፈጠረው፤ ስለዚህ አገልግሎትህን ብወድደውም፣ ጸጋህን ባከብርም ኦፊሻል እስከሚሆን ድረስ፣ ዘመን እስከሚመጣ ድረስ እንጠብቃለን’ ብለው ነበርና እንደነዚህ ያሉ አባቶቻችችንን፣ እንደነዚህ ያሉ መካሪዎቻችን አሁን በነጻነት ከእኛ ጋር፣ እኛም ከእነርሱ ጋር የምንጸልይበት፣ የምንሠራበት ዘመን ይመጣልና፣ እግዚአብሔር ሁላችሁንም ይባርክ።

“እኔ በግሌ ብዙ ቦታ ሊሰጠኝ የማይገባ ሰው ልሆን እችላለሁ፤ በብዙ ነገር ታናሽ ልሆን እችላለሁ፤ ነገር ግን እንደ ታናሽ ብቻ ሳይሆን፣ ልቤ ውስጥ ያለውን፣ ቤተ ክርስቲያኔም ያላትን ራእይ ተመልክታችሁ ለዚህ ድል ደግሞ እግዚአብሔር ስላበቃን እናመሰግናለን።

“ሌላው በእኔ ሕይወት፣ በእኔ አገልግሎት፣ በእኔ ቤተ ክርስቲያን ምንም ዐይነት ጥያቄ ቢኖራችሁ፣ የትኛውም ዐይነት ጥያቄ ቢኖር፣ ያንን ጥያቄ ለመስማት፣ ለመመከር፣ ለመገሰጽ፣ ለመታረም ሙሉ ለሙሉ ፈቃደኛ መሆኔን ለማሳወቅ ነው የምፈልገው። ይሄ ዛሬ የጀመርኩት ወይም አብያተ ክርስቲያናት ስገባ የምጀምረው አዲስ ነገር ሳይሆን፣ የኖርኩት ኑሮ ስለሆነ፣ ከዚህ በኋላ በደንብ አብረን እናገለግላለን፣ አብረን እንሠራለን። ስለዚህ በአገልግሎቴ ዘመን ካሳየሁት ቅንነትና ትኅትና በላይ፣ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ይረዳኛል፣ እንደዚህ ዐይነት የነጻነት መንገድ ከመጣ፣ የእግዚአብሔርን ሥራ እጅ ለእጅ ተያይዘን የምንሠራበት ዘመን ከመጣ፣ ከዚህ በላይ ዝቅ ብዬ፣ ከዚህ ታዝዤ ለአባቶችም፣ ለሕዝቡም ጌታን ለማገልግል ቃል እገባለሁ። ስለዚህ ማንኛውም ጥያቄ ያለው ሰው፣ በግልም መጥቶ ሊያገኘኝ ይችላል። በቤተ ክርስቲያንም፣ እንደ ገና በአብያተ ክርስቲያናት በኩልም፤ አሁን አጋር አባል ሆነናል፤ ስለዚህ ማንም ሰው ጥያቄ ቢጠይቅ ተገቢውን መልስ ሊያገኝ፣ ተሳስቼም ከሆነ ልታረም እወድዳለሁ።

“ቅድም ፓስተርም ስለ ገስት ሐውስ አንሥተዋል፣ እንኳን ገስት ሐውስ አይደለም ቱታ ለብሰህ አገልግል ብባል አገለግላለሁ። ምክንያቱም ትርፌ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ማገልገል ስለሆነ ማለት ነው። ስለዚህ ገስት ሐውስ ወይም እንትን ብዬ የማስቀምጠው የራሴ ነገር የለኝም። የውሃ ሽያጭ፣ የቲሸርት ሽያጭ፣ ቁሳቁስ ተጸልዮበት የሚደረግ ሽያጭ በቤተ ክርስቲያናችን ተደርጎ አያውቅም። ገስት ሐውስ ግን አለን፤ እሱም ከውጭ አገር ለሚመጡ ሰዎች ከመንገላታት፣ በአንድ ስፍራ ሆነው ሁሉም እንዲያመልኩ፣ እንዲጸለይላቸው በማሰብ ብቻ እንጂ ሌላ ዐላማ የለውም። ስለዚህ ይሄ ከመርዳት የመነጨ ስለሆነ እሱም መቅረት ካለበት የትኛውንም ነገር የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደገናም ደግሞ አብያተ ክርስቲያናት የሚሉትን ነገር በሙሉ ለመታዘዝ ባለሙሉ ፍቃድ ነኝ። በሕይወቴ ምንም ዐይነት ነቀፋ እንዲኖር አልፈልግም። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ታዝዤ ማገልገል እፈልጋለሁ።

“ጌታ ይህን ጊዜ ስላመጣ፣ ይሄ ‘ወርቃማ ዘመን ነው’ ብዬ ነው የምጠራው። ጌታ ይህን ዘመን ካመጣ እጅግ ብዙ ሥራ በእኛ ሊሠራ እንዳለ ነው የማየው። እግዚአብሔር ይባርካችሁ። ፓስተር ስላደረከው ነገር፣ ስለመከርከን፣ ብዙ ነገር ስላስተማርከን እግዚአብሔር ይባርክህ። ሁላችሁንም ጌታ ይባርካችሁ።”

ነገሩ እንዴት ተጀመረ?

ከአንድም ዓመት በፊት መሠረት ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ዐሥራ ሦስት ግለ ሰቦችን ማውገዟን ተከትሎ፣ ውግዘቱ የደረሰባቸው ነቢይ ኤርሚያስ ሁሴንና ቢሾፕ ዳዊት ሞላልኝ ቅሬታቸውን ይዘው ወደ የኢትዮጵያ ሃይማኖቶች ጉባኤ ይሄዳሉ። በዚያ ያሉ ሰዎች ጉዳዩን ወደ ኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ይመልሱታል። በወቅቱ የኅብረቱ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ጌቱ ግዛው ሂደቱን ለሕንጸት ሲያስረዱ፣ “ዳዊት የነበረውን ቅሬታ ከገለጸ በኋላ ብዙም ሳይገፋበት ቀረ። ኤርሚያስ ግን ጉዳዩን ወደ ኅብረቱ ይዞት መጣ። በሂደትም በመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያና ላይ ክስ መመሥረቱና ፕሬዚዳንቱን ማሳሰሩ ተገቢ አለመሆኑን አውቆ፣ ‘አጥፍቻለሁ’ ብሎ ይቅርታ ጠየቀ።” ይላሉ።

አቶ ጌቱ እንደሚሉት ከሆነ፣ ይኸው ግንኙነት አድጎ ‘ለምን ኅብረቱ መጋቢያዊ ድጋፍ አይሰጥም?’ የሚል ሐሳብ ይነሣና፣ የኅብረቱ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት መጋቢ ዘሪሁን ደጉ፣ ምክትል ሰብሳቢው ራሳቸው አቶ ጌቱ ግዛው፣ የኅብረቱ የቦርድ ጸሐፊ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ በየነ እና የኅብረቱ ፕሬዚዳንት መጋቢ ጻድቁ አብዶ ጉዳዩን እንዲከታተሉ በቦርዱ ኀላፊነት ይሰጣቸዋል።

“በዚህ ሂደት ነው እንግዲህ እነዚህን አራት ግለ ሰቦች ኅብረቱ ማነጋገር የጀመረው” ይላሉ አቶ ጌቱ። ከነቢይ ኤርሚያስ ሁሴን በቀር ሦስቱ ግለ ሰቦች ግን በራሳቸው ተነሳሽነት ‘ምከሩን’ ብለው እንደመጡም ያስታውሳሉ። ይህ ግንኙነት የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ለአራቱ ግለ ሰቦች መጋቢያዊ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው፣ አሉባቸው ከሚባሉ ማናቸውም ችግሮች እንዲወጡ፣ የአባቶችን ምክርና ተግሳጽ እንዲያገኙ በሚል ለአንድ ዓመት ሙሉ ተደጋጋሚ ውይይትና ምክክር ሲደረግ የቆየ ነው። አቶ ጌቱ የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው እስከቆዩበት የኅብረቱ የመጨረሻ ጠቅላላ ጉባኤ ድረስ፣ ይህ ግንኙነት ግለ ሰቦች ለኅብረቱ ተጠያቂ (accountable) የሚሆኑበትንና ሕይወታቸውን የሚገሩበት ግንኙነት እንጂ፣ በአባልነት ደረጃ እነሱን ስለመቀበል የተደረገ ምንም ዐይነት ድርድርም ሆነ ንግግር አልነበረም።

“ይህንንም ሥርዐት ባለው መልኩ ለማድረግ የመግባቢያ ሰነድ እንደሚዘጋጅና ግለ ሰቦቹ በዚሁ መሠረቱ ከኅብረቱ መጋቢያዊ አገልግሎት ለማግኘትና ለኅብረቱ ተጠሪ/ተጠያቂ ለመሆን መፍቀዳቸውን የሚመሰክር ሰነድ ላይ እንደሚፈርሙ ነው የማውቀው።” ሲሉ “አጋር አባል” (Affiliated Members) የሚል ሐሳብ ቀድሞ እንዳልነበረ ያስረዳሉ።

በርግጥ የኅብረቱ ፕሬዚዳንት በስምምነት ፊርማ ሥነ ሥርዐቱ ላይ ሂደቱ ይህን ይመስል እንደ ነበር ከሞላ ጎደል ተናግረዋል። መጋቢ ጻድቁ በዕለቱ አጽንኦት ሰጥተው ሲናገሩ የነበረው፣ “አሁን የተቀበልናችሁ እንደ አጋር አባል እንጂ እንደ ሙሉ ወይም ተባባሪ አባል አይደለም። አባል ለመሆንም መተዳደሪያ ደንቡ የሚጠይቀውን መስፈርት አታሟሉም” ብለዋቸው ነበር። ነቢያቱ በንግግራቸው መካከልም “አባል” የሚል ቃል ሲጠቀሙም በመኻል እየገቡ “አጋር አባል” ናችሁ ብለው ዕርማት ሲሰጡም ተስተውሏል። ምንም እንኳን መጋቢ ጻድቁ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጡም፣ በነቢይ ሱራፌል ደምሴ የፌስቡክ ገጽ ላይ፣ “ዘ ፕረዘንስ ኦፍ ጋድ ኢንተርናሽናል ቤተ ክርስቲያን [የ]ኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረትን ተቀላቀለ” የሚል ዜና ከመለጠፍ ግን አላስቆመም (አሁን ከፌስቡክ ገጹ ላይ ተነሥቷል)።

“አጋር አባል” ሲባል ምን ማለት ነው?

ኅብረቱና አራቱ ነቢያት የፈረሙት የመግባቢያ ሰነድ፣ ከኅብረቱ ጋር በመተባበር ማገልገል ከሚፈልጉ አብያተ ክርስቲያናትና አገልግሎቶች ጋር ሊኖር ስለሚገባ ግንኙነትና፣ ከግንኙነቱ ስለሚመነጩ ጉዳዮች ያብራራል። በዚህ ሰነድ ላይ ስለ አጋር አባል (Affiliated Members) ትርጓሜ ተሰጥቷል። በዚህም፣ “‘አጋር አባል’ የሚለው መጠሪያ፣ መተዳደሪያ ደንቡ በሚፈቅደው መሠረት አብያተ ክርስቲያናቱ የኅብረቱ አባል እስኪሆኑ በሚኖረው የጊዜ ገደብ፣ ከኅብረቱ ጋር በቅርበት መንፈሳዊ ኅብረት ለማድረግ የተስማሙትን የሚመለከት ይሆናል።” ይላል።

ይህ ስያሜና ትርጓሜ ዜናው ከተሰማበት ቅጽበት ጀምሮ ጥያቄ እየተነሣበት አለ። ጥያቄው የተነሣው ግለ ሰቦቹና ቤተ እምነቶቻቸው በተባለው መንገድ የኅብረቱ አጋር አባላት መሆናቸው ያስደሰታቸውም ሆኑ፣ ያልተቀበሉት የሚተቹት ሆኗል። ‘አባል ከተባለ ሙሉ አባልነት ነው፤ አጋርነቱን ምን አመጣው? ስለዚህ እንደ ሙሉ አባል ሊታዩ ይገባል’ ከሚሉት ጀምሮ፣ ‘አጋር አባል የሚባል አሠራር ኅብረቱ ከየት ያመጣው ነው?’ እስከሚሉት ድረስ የዘለቀ ነው።

“ይህን ጉዳይ፣ አይደለም የፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት፣ ቦርዱ እንኳ ሊወስነው አይችልም። ቤተ እምነቶችን የመቀበል ወይም ያለመቀበሉ ሙሉ ሥልጣን ያለው ጠቅላላ ጉባኤው ነው” ይላሉ የቀድሞ የኅብረቱ የሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጌቱ ግዛው።

የዓለም አቀፉ የወንጌላውያን ተማሪዎች ኅብረት (IFES-EPSA) የአፍሪካ ዋና ጸሐፊ የሆነው ዘላለም አበበ በበኩሉ፣ “እኔ እስከማውቀው ድረስ፣ አንድ ቤተ እምነት የኅብረቱ አባል የሚሆንበት የራሱ አሠራር አለ። ይህንን ‘አጋር አባል’ የሚለውን ከየት እንዳመጡት አላውቅም” ሲል ደንቡን ያልጠበቀ አካሄድ ኅብረቱ ሄዷል ሲል ይተቻል።

መጋቢ ጻድቁ አብዶ በበኩላቸው፣ ንግግሩ እየተደረገ ያለው ከአራቱ ነቢያት ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ቁጥራቸው 150 ከሚደርሱ ሌሎች ቤተ እምነቶች ጋር ጭምር መሆኑን ያስረዳሉ። “ከወንጌላውያን ጋር የሚስማማ አስተምህሮና ልምምድ ያላቸው፣ ነገር ግን የኅብረቱን መሥፈርት የማያሟሉ አሉ። እነሱን እንዴት ነው ማቀፍ ያለብን በሚለው ላይ በቦርድ ደረጃ እየተመከረበት ነው።” ይላሉ። ሆኖም ይህን ፍልጎት ሊያሟላ የሚያስችል አሠራር (modalities) መዘጋጀት እንደነበረበትና የተደረገውም ይኸው መሆኑን ነው የሚገልጹት። አያያዝውም፣ ባለፈው ዓመት በተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ስለ አራቱ ግለ ሰቦችና ቤተ እምነቶቻቸው ሪፖርት ማቅረባቸውንና ጉዳዩ በቦርድ ደረጃ እንዲያዝና ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ዳር እንዲደርስ ከጠቅላላ ጉባኤው ሥልጣን ማግኘታቸውንም ጭምር አብራርተዋል።

ለምን አሁን ይፋ ሆነ?

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት መሥራች አባላቱ ከነበሩትና አሁን በኅብረቱ ውስጥ ከሌሉት ሁለት ትልልቅ ቤተ እምነቶች ጋር ያለውን ክፍተት አስቀርቶ፣ ዳግሞ ኅብረት ሊጀምር ነው እየተባለ ባለበት በዚህ ጊዜ ለምን ይህንን ስምምነት ይፋ ማድረግ አስፈለገው የሚለው ሌላኛው ጥያቄ ነው።

ኅብረቱ ስምምነቱን ይፋ ያደረገበት ጊዜ እንደሚያሳስበው የሚናገረው፣ የዲዳስኮ ክርስቲያናዊ ሚኒስትሪ መሥራችና ዳይሬክተር እንዲሁም የሥነ መለኮት መምህር የሆነው እንዳሻው ነጋሽ ነው። “ኅብረቱ ይህንን ውሳኔ ይፋ ያደረገበት ወቅት ጊዜውን የጠበቀ አይመስለኝም። የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ወደ ኅብረቱ ልትመለስ መሆኑ በተገለጠበት እና የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ወደ ኅብረቱ እንድትመለስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ይህ ውሳኔ ይፋ መደረጉ ጥረቱን ወደ ኋላ እንዳይመልሰው የሚል ስጋት ፈጥሮብኛል።” ይላል።

በተለይ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ከኅብረቱ ለመውጣት እንደ አንድ ምክንያት ታስቀምጠው የነበረው የአስተምህሮና የልምምድ ጉዳይ እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህ ውሳኔ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሄደችበት የዕርቅ መንገድ እንዳይመልሳት ነው የእንዳሻውም ሆነ የሌሎቹ ስጋት።

ኅብረቱም፣ እነዚህ ግለ ሰቦችም ሆኑ ቤተ እምነቶቻቸው በእውነተኛ የንስሓ ፍሬና የአገልግሎት ንጽሕና ውስጥ መዝለቅ የሚችሉ መሆናቸው በተግባር መታየት ነበረበት የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም።

የገቡት ስምምነት ሕይወታቸውንና አገልግሎታቸውን ለመግራት ይቻል ዘንድ ኅብረቱ መጋቢያዊ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው የሚገልጽ እንጂ፣ “አባል” እንደሆኑ አድርገው ይፋ የሚያደርጉበት አለመሆኑ የኅብረቱ ፕሬዚደንትን ጨምሮ ጉዳዩን የሚያውቁ ሰዎች እየተናገሩ ነው። ይሁን እንጂ፣ አንዳንዶቹ በማኅበራዊ ሚዲያና በራሳቸው የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ አባል እንደ ሆኑ አድርገው ማቅረባቸው የግለ ሰቦቹን የንስሓ ፍሬ ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል የሚል ሐሳብ እየተሰነዘረ ነው።

“‘ለመመለስ ቃል እንገባለን’ የሚል ስምምነት ፈርመው ያሉትን ነገር የሚያደርጉት መሆኑ በተግባር መታየት አለበት። አንድ ዓመትም ሊሆን ይችላል፤ ከዚያም የሚበልጥ ጊዜ ተሰጥቶ እነዚህ ሰዎች ፍሬ ማፍራታቸውንና መመለሳቸውን የሚያረጋግጥ ነገር ሳይታይ በእንደዚህ መልኩ ይፋ ማድረግና በዚህ ደርጃ ሕዝቡን ግርታ ውስጥ መክተት በጣም ልክ አይደለም ብዬ ነው የማምነው።” ይላል ዘላለም አበበ።

የንስሓ ፍሬ ይጠበቃል!

“በመጀመሪያ ደረጃ መታወቅ ያለበት ነገር፣ በትክክለኛው መንገድ ላይ የማይሄድ ሰው፣ ‘አጥፍቷል፤ የምንለው ሰው፣ ሐሰተኛ አስተማሪ የሆነ ሰው፣ እኛን የማይወክል ሰው፣ በማንኛውም ጊዜ ልክ አለመሆኑ ገብቶት፣ ያበላሸው ነገር እንዳለ ተረድቶ መመለስ ከፈለገ፣ ‘አትመለስም’ ብለን የምንዘጋበት ምንም ምክንያት የለም።” የሚለው ዘላለም አበበ፣ ይሁን እንጂ የንስሓ ፍሬ መኖሩ በጊዜ ሂደት መታየት እንዳለበት ደግሞ አበክሮ ያሳስባል። “አምስት ዓመት፣ ስድስት ዓመት፣ ሰባት ዓመት ሰው የፈለገውን ሲያደርግ ቆይቶ የሆነ ጊዜ ላይ ‘በቃ ትቻለሁ’ ቢል፣ ‘በቃ ከእኛ ጋር ከዚሁ ቀጥል’ ይባላል ወይ?” ሲል ይጠይቃል።

ይህንኑ ጥያቄ የሚያነሣው የሥነ መለኮት አጥኚው እንዳሻው ነጋሽ ነው። “ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች በእስካአሁኑ የአገልግሎት ጉዟቸው ላጠፉት ጥፋት በግልጽ ንስሓ ገብተዋል? ‘የታሸገ ዘይት ሽጠናል፣ ፎቷችን ያለበት ጨርቅና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ሽጠናል፣ “አትሞቱም” ብለናቸው ብዙ ሰዎች ሞተዋል፤ ትዳር አፍርሰናል፤ ንብረት ዘርፈናል’ ብለው የንስሐ ፍሬ አፍርተዋል?” ወይ ሲል ይጠይቃል። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ አጋር አባል ማድረግ “ኅብረቱን ራሱ በጥያቄ ውስጥ የሚጥል ይሆናል።” ሲል የኅብረቱ መሪዎች ይህንን ውሳኔ እንደ ገና በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊመለከቱት እንደሚገባ ይመክራል።

የተቀባ የእግዚአብሔር ቃል ቤተ ክርስቲያን መጋቢ ሚካኤል ወንድሙ በበኩሉ፣ የግለ ሰቦቹና የቤተ እምነቶቻቸው አስተምህሮና ልምምድ እንዲሁም መንፈሳዊ ሕይወት በቅድሚያ ሊታይ እንደሚገባ ነው የሚያሳስበው። “ይህንን ማረጋገጥ ስንችል ነው ከእነርሱ ጋር ኅብረት ማድረግ የምንችለው” ይላል መጋቢ ሚካኤል።

የመሠረተ ክርስቶስ ውግዘትስ?

ከአንድ ዓመት በፊት የመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ ጉባኤ ዐሥራ ሦስት ግለ ሰቦችን በአስተምህሯቸው፣ በልምምዳቸውና በሞራል ሕይወታቸው ለምእመናን ምሳሌ መሆን የማይችሉ ናቸው በሚል ማወገዟ ይታወሳል። ውሳኔውም ቤተ ክርስቲያኒቱ ባለት መዋቅር መሠረት ወደ አጥቢያዎችና የወንጌል ሥርጭት ጣቢያዎች እንዲላክ ተደርጎ ምእመናንና አገልጋዮች እንዲያውቁት ተደርጎ ነበር።

ስማቸው ከተጠቅሱት ዐሥራ ሦስት ግለ ሰቦች መካከል ነቢይ ኤርሚያስ ሁሴን አንዱ ነው። ይህንን መነሻ አድርገን፣ ‘ኅብረቱ የወሰደው ርምጃ በመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በኩል ተቀባይነት አለው ወይ? ከሆነስ ቤተ ክርስቲያኒቱ በነቢይ ኤርሚያስ ላይ የያዘችውን አቋም ይቀየራል?’ ስንል ለቤተ ክርስቲያኒቱ ጥያቄ አቅርበን ነበር። ያገኘነው ምላሽም፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በኅብረቱ አደራዳሪነት ከነቢይ ኤርሚያስ ጋር ውይይት መጀመሯንና ውይይቱ ያልተቋጨ መሆኑ፣ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያኒቱ በነቢይ ኤርሚያስ ሁሴን ላይ የያዘችውን አቋም እስካሁን ያልለወጠች መሆኗ ተነግሮናል።

የኅብረቱ ቀጣይ ፈተና

ኅብረቱ አራቱንም ግለ ሰቦችና ቤተ እምነቶቻቸው አዲስ ስያሜ በሰጠው “የአጋር አባል” ስምምነት በኩል ተቀብያለሁ ማለቱ ያስደሰታቸውን ያህል፣ ውሳኔው ያስደነገጣቸውና ያስቆጣቸው በርካቶች ናቸው። ይኸው የተቃውሞ ድምፅ ከራሱ አባል ቤተ እምነቶች ጭምር የሚመጣ እንደ ሆነ ይጠበቃል። እንዴት ያስታርቀው ይሆን?


(ኅብረቱ ከነቢያቱ ጋር የተፈራረመው ሙሉው የመግባቢያ ሰነዱ ከዚህ በታች ማግኘት ይችላሉ።)

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት

ከኢ.ወ.አ.ክ.ኅብረት ጋር በመተባበር ማገልገል ለሚፈልጉ አብያተ ክርስቲያናትና አገልግሎቶች ጋር ሊኖረው ስለሚገባ ግንኙነትና ከግንኙነቱም ስለሚመነጩ ጉዳዮች የሚሆን የመግባቢያ ሰነድ፤

I. አጭር ርእስ

ትርጉም፦ የአጋር አባልነት (Affiliate membership)

በዚህ የመግባቢያ ሰነድ፣ “አጋር አባል” የሚለው መጠሪያ፣ መተዳደሪያ ደንቡ በሚፈቅደው መሠረት፣ ቤተ እምነቶቹ ወደ ፊት የኅብረቱ አባላት ለመሆን የሚያስችላቸውን መመዘኛዎች እስከሚያሟሉ ድረስ በሚኖረው የጊዜ ገደብ፣ ከኅብረቱ ጋር በቅርበት መንፈሳዊ ኅብረት ለማድረግ የተስማሙትን የሚመለከት ይሆናል።

II. የመግባቢያ አሳብ

የመግባቢያ ሰነዱ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ አዳዲስ ቤተ እምነቶችን በአባልነት ለመቀበል ያወጣውን መስፈርት ሊያሟሉ ያልቻሉ አብያተ ክርስቲያናትን በአጋር አባልነት ለመቀበል ያዘጋጀው ሰነድ ሲሆን፣ የሰነዱን ዝርዝር ነጥቦች የሚቀበል ቤተ እምነት የኅብረቱን ራእይ፣ ዓላማ፣ ተልእኮ፣ መተዳደሪያ ደንብ፣ እንዲሁም የኅብረቱ ጠቅላላ ጉባኤው በተለያዩ ወቅቶች ያሳለፋቸውን የአቋም መግለጫዎች ተቀብሎ ተግባራዊ የማድረግ ኀላፊነት አለበት።

III. የአጋር አባላቱ (Affiliate members) ግዴታና ኀላፊነት

በኅብረቱ መተዳደሪያ ደንብ ከሌሎች ተባባሪ አባላት የሚጠበቁ ግዴታዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣

  1. የኢትዮጵያ ሕግ በሚጠይቀው መሠረት፣ በሕግ አግባብ የተመዘገቡ፣
  2. በአስተምህሮ፣ በልምምድና በሞራል ወይም በቅድስና ከኅብረቱ ጋር ተመሳሳይ ወይም አንድ ዓይነት አቋም ያላቸው፣
  3. የወንጌላውያንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረታዊ አስተምህሮ፣ የኅብረቱን መተዳደሪያ ደንብና የእምነት አንቀፅ የሚቀበሉ፣
  4. ሥልተ አመራራቸው የአገልጋይ/ሎሌነት መርሕን የሚከተልና በተግባር የሚገለጽ ሲሆን፣
  5. የኅብረቱን ራዕይ፣ ዓላማና ተልዕኮ የሚቀበሉ ወይም በተፃራሪ የማይቆሙ፣
  6. የኅብረቱን ምክርና እገዛ እንዲሁም የእርምት ሀሳብ የሚቀበሉ መሆናቸውን በይፋ የሚያስታውቁ፣
  7. በአገልግሎታቸውም ሆነ በአመራራቸው ክርስቶስንና ወንጌሉን ማዕከላዊ አድርገው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን በተግባር የሚያሳዩ፣
  8. ከኅብረቱ መሥራች ቤተ እምነቶች ጋር መልካም ግንኙነት የሚያደርጉ፣
  9. በአስተምህሮአቸው፣ በልምምዳቸውና በተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው በኅብረቱ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸውን፣ ከርቱዕ ክርስትና አስተምህሮ ያፈነገጡ በማለት ኅብረቱ ካገለላቸው ተቋማት ጋር የተለየ ግንኙነት የሌላቸው መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን ኅብረቱ በአጋር አባልነት ይቀበላቸዋል፣
  10. የጸጋ ስጦታዎች አጠቃቀምን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱሳዊ በተለይም አዲስ ኪዳናዊ መርህ የሚከተሉና በጸጋ ስጦታዎች ስም የማይነግዱ መሆናቸው ማለትም፣ የተጸለየባቸው ናቸው፣ ፈውስን ይሰጣሉ ብሎ የተለያዩ ቁሳቁሶችን መሸጥና ሌሎች ባዕዳዊ ልምምዶችን የማይፈጽሙ መሆናቸው ሲረጋገጥ፣
  11. ኑፋቄያዊ ተክለ ሰውነት የማይገነቡ ማለትም ክርስቶስን እንጂ ራሳቸውን የማይሰብኩ፣
  12. በየትኛውም ደረጃ ካለ ኅብረት ማለትም የክልል፣ የዞንና የከተማ ኅብረት ጋር በሚደረግ የጀማ ስብከተ ወንጌል፣
    ሀ. የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ዋና ቢሮ ሳያውቅ ማስታወቂያዎችን በኅብረቱ ስም በማንኛውም ሚዲያዎቻቸው ወይም ቻናሎች የማያስተላልፉ፣
    ለ. ከተለመደውና ሰው በፈቃዱ ከሚሰጠው መባ ውጭ በማናቸውም መንገድ ለራሳቸውም ሆነ ፕሮግራም ለአዘጋጀው (የክልል፣ የዞን ወይም የከተማ ኅብረት) ክፍል ገንዘብ ላይሰበሰቡ (fundraise) የሚስማሙ ሲሆንና ይህንንም ሲያረጋግጡ በአጋር አባልነት ይቀበላል፣
  13. በእስካሁኑ የአገልግሎት ጉዟቸው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ላጠፉት ጥፋት በግልጽ ይቅርታ ለመጠየቅ የተዘጋጁ መሆን።

IV. የኅብረቱ ግዴታና ኀላፊነት

ኅብረቱ ለሌሎች ተባባሪ አባላት የሚያደርገው ድጋፍ እንደተጠበቀ ሆኖ በአጋር አባልነት የሚቀበላቸው አብያተ ክርስቲያናት ለሙሉ አባልነት የሚያበቃቸው መስፈርት ላይ እስኪደርሱ ድረስ፣

  1. ለተባባሪ አባላት በደንቡ መሠረት የሚደረገውን ትብብርና ድጋፍ ያደርጋል፣
  2. ሥልጠናዎች፣ ወርክሾፖችና ምክክሮች ያዘጋጅላቸዋል፣
  3. ኅብረቱ የሚያዘጋጃቸው የተለያዩ ሥልጠናዎችና ዐውደ ጥናቶች ላይ በተወሰነ ቁጥር በውክልና እንዲሳተፉ ያደርጋል፣
  4. ለሕወታቸውና ለአገልግሎታቸው ስምረት የሚቻለውን በጎ አስተዋጽዖ ያደርጋል፣
  5. ግንኙነት በዚህ መግባቢያ ሰነድ መሠረት በአግባቡ እየተፈጸመ መሆኑን በጋራ በየስድስት ወሩ የሚታይና የሚገመገም ይሆናል።

V.  የግንኙነት መቋረጥ ምክንያቶች

  1. ከላይ እንደ ግዴታ የተዘረዘሩት ጉዳዮች በከፊል ወይም በሙሉ ከተጣሱ ኅብረቱ እውቅናውን ይነሳል፣ መንሳቱንም በግልጽ ያሳውቃል፤
  2. መሠረታዊ የክርስትና አስተምህሮ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ልምምዶችና የሞራል እና የቅድስና ጉድለቶች ሲፈጸሙ ምክር መስጠት ቅድሚያ ቢሆንም ምክርና ተግሳጽ ተቀብሎ ለማስተካከል የማይፈልጉትን በይፋ እውቅና ይከለክላል ወይም እውቅናውን ያነሳል።

Share this article:

ልዩ ወንጌል

በሕንጸት ቁጥር 1 ዕትም፣ በአውራ ነገር ዐምድ ሥር “የወንጌላውያኑ መንታ መንገድ” በሚል ሐተታዊ ጽሑፍ ተስተናግዶ ነበር፡፡ ጽሑፉ በዋናነት ከመቶ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የወንጌላውያን ክርስትና በኢትዮጵያ ይዟቸው ስለመጣው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦች በማተት፣ አማኝ ማኅበረ ሰቡ ስላበረከታቸው በጎ አስተዋጽዖዎች በመጠቆም ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይህንን በጎ ተጽእኖውን ማስቀጠል በማይችልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰና ለዚህም ምክንያቱ ልዩ የሆነ አስተምህሯዊ አቋምና ልምምድ በቤተ ክርስቲያን መተዋወቁ እንደ ሆነ ይጠቁማል፡፡ ይህ ልዩ አስተምህሮና ልምምድ ደግሞ በ“እምነት እንቅስቃሴ” ወይም በ“ብልጽግና ወንጌል” የተጠመቀ “ክርስትና” ወደ አማኝ ማኅበረ ሰቡ መዝለቁ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

“ዘመነ ነቢያት” በእግዚአብሔር ቃል ሲፈተሽ

ባለፈው ዕትም የ“ነቢይ” ቡሽሪን የኢትዮጵያ አገልግሎት አስመልክቶ አንድ መጣጥፍ አቅርቤ ነበር፡፡ የእኚህ ሰው “አገልግሎት” በሐሰት የተሞላና ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር የሚጣረስ መሆኑን አሳይቻለሁ፡፡ እንዲህ ዐይነቱ የስህተት አስተምህሮ እንደ ቡሽሪ ባሉ ከውጭ ሀገር በሚመጡ አገልጋዮች ላይ ብቻ የሚታይ ሳይሆን በእኛ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት እየተስተዋለ የመጣ ችግር ነው፡፡ የዛሬው መጣጥፍ የትኩረት አቅጣጫም ይህ ይሆናል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

ጌታን ተቀበሉ!

ዘሪቱ ከበደ በዚህ “ጌታን ተቀበሉ!” በተሰኘው ጽሑፍ ስለ የምስራቹ ቃልና ይህን የምስራች እንዲያደርሱ በእግዚአብሔር ስለ ተጠሩ አማኞች ታብራራለች፤ “እኔም እኅታችሁ በእግዚአብሔር ጸጋና መልካም ፈቃድ፣ የዚህ ሕይወት የሆነው ጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል አብስሪነት ዕጣ ወደቀብኝ።” ስትል የሕይወት የጥሪ አቅጣጫዋን ታመለክታለች። ተጨማሪ ያንብቡ።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.