
የልየታ መንፈስ ጥሪ!
ንጉሤ ቡልቻ በዚህ ጽሑፋቸው፣ ምስቅልቅል ለበዛበት የአማኞች አምልኳዊ ገቢር መፍትሔ እንዲመጣ፣ “የልየታ መንፈስ” ይፈስስ ዘንድ ለአምላክ ተማጽኖ፣ ለምእመናንም ምክሮች ይለግሳሉ።
[the_ad_group id=”107″]
ርእስ፡- የተመለሱና ያልተመለሱ ጥያቄዎች፡- ስለ እግዚአብሔር፣ ስለሰው፣ ስለክርስቶስ
ጸሐፊ፡- ሽመልስ ይፍሩ
አሳታሚ፡- አልተጠቀሰም
የታተመበትዓመት፡- 2006 ዓ.ም.
ዋጋ፡- 50 ብር
ገጽ፡- 279
ትምህርተ ክርስቶስ እጅግ መሠረታዊ ከሆኑ የክርስትና አስተምህሮዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክም ሆነ በዓለም ታሪክ ውስጥ አነጋጋሪ ከሆኑ ሰዎች መካከል ኢየሱስ ዋነኛው ነው፡፡ ገና ከጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ጊዜ ጀምሮ የኢየሱስ ማንነት አከራካሪ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ክርስቶስን በተመለከተ በያዙት የተለየ አቋሞች የተለያዩ ቤተ እምነቶች ሊፈጠሩ ችለዋል፡፡
ʻኢየሱስ የሚባል ግለ ሰብ በታሪክ ውስጥ ነበረ ወይ? ከኖረስ ኢየሱስ ሰው ነበር አምላክ? የመጽሐፉ ቅዱሱ ኢየሱስና በታሪክ ውስጥ የነበረው ኢየሱስን ተመሳሳይ ናቸውን?ʼ ከሚሉ ጥያቄዎች አንሥቶ፣ ʻኢየሱስ አንድ ባሕርይ ነው ወይስ ሁለት?ʼ እስከሚሉት ጥያቄዎች ድረስ ሙግት የተደረገባቸውና እየተደረገባቸው ያሉ ናቸው፡፡
ኢየሱስን በተመለከተ በስፋት የተሰራጩት አመለካከቶች መጽሐፍ ቅዱስን እንደ እግዚአብሔር አምነው በተቀበሉት ዘንድ ብቻ ሳይሆን፣ በማይቀበሉትም መካከል የሚስተዋል ነው፡፡
ጸሐፊው መጽሐፍ ቅዱስን እንደ እግዚአብሔር ቃል የሚቀበሉ ቤተ እምነቶች ኢየሱስን፣ እግዚአብሔርንና ሰውን በተመለከተ ያላቸውን የተለያዩ አመለካከቶችን ይዳስሳሉ፡፡ እነዚህ ልዩነቶች በዋነኛነት የሚመነጩት ከምንከተላቸው የተለያዩ የሥነ አፈታት ስልቶች ወይም መጽሐፍ ቅዱስን ከምናነብባቸው መንገዶች ነው፡፡
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በዋነኛነት በኢየሱስ ክርስቶስ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ፣ ነገር ግን እግዚአብሔርንና ሰውን የተመለከቱ ርእሰ ጉዳዮች ተዳሰዋል፡፡
መጽሐፉ በዋነኛነት የሚያጠነጥነው “ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ ሰው፣ ስለ ክርስቶስ” የተለያዩ ቤተ እምነቶች የያዙትን አቋም በመተንተን ላይ ነው፡፡ እነዚህ ሦስት ርእሰ ጉዳዮች እርስ በርሳቸው የተጋመዱ ናቸው፡፡ አንዱን በተመለከተ የምንይዘው አመለካከት በሌሎቹ የእምነት አቋሞቻችን ላይ ተጽእኖ ይፈጥራል፡፡ ለዚህም ይመስላል አቶ ሽመልስ እነዚህን ሦስት ርእሱ ጉዳዮች በአንድ ጥራዝ ያሰፈሯቸው፡፡
የተለያዩ የእምነት ክፍሎች፣ በጸሐፊው አገላለጽ “የመጽሐፉ ጎረቤቶች” እግዚአብሔርን፣ ክርስቶስንና ሰውን በተመለከተ የያዟቸውን የእምነት አቋሞች በዚህ መጽሐፍ ይፈተሻል፡፡ ይህንንም የሚያደርገው ሁለተኛ ምንጮችን (secondary sources) በማመሳከር ብቻ ሳይሆን፣ “ከፈረሱ አፍ” እንደ ወረደ በመቅዳት ነው፡፡ ጸሐፊው ቤተ እምነቶቹን ይወክላሉ ያሏቸውን ግለ ሰቦች ቃለ መጠይቅ አድርገዋል፡፡ “የመጽሐፉ ጎረቤቶች” አድርጎገው የወሰዷቸውም፡- የይሖዋ ምስክሮች፣ የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የካቶሊክና የወንጌላውያን አማኞች ናቸው፡፡ (በነገራችን ላይ የመጽሐፉ ጸሐፊ የወንጌላውያን እምነት ተከታይ መሆናቸውን ልብ ይሏል) ከእነዚህ አምስት ቤተ እምነቶች ለተውጣጡ የእምነቱ ተከታዮችና አገልጋዮች ቃለ መጠይቅ በማድረግ አንባቢያን በመጽሐፉ ርእስ ላይ በተጠቀሱት ነገረ መለኮታዊ አስተምሮዎች ላይ ቤተ እምነቶቹ ያሏቸውን አቋሞች ይፈነጥቁልናል፡፡
የይሖዋ ምስክር እምነት ተከታዮች የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የማይቀበሉ፣ ʻቃል ያልነበረበት ጊዜ ነበር፣ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ እግዚአብሔር ተግባራቱን የሚፈጽምበት ኀይል ነውʼ የሚሉ ናቸው፡፡ ይህ አመለካከታቸውም ትምህርተ ሥላሴን እንዳይቀበሉ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህ እምነት መሠረት “እግዚአብሔር አንድነት ብቻ እንጂ ሦስትነት የለውም ይላሉ”፡፡ በዚህ ክፍል ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ለኀምሣ ዓመታት በዚሁ ቤተ እምነት ውስጥ አገልጋይ የሆኑት አቶ ማሞ ብርሃኔ ናቸው፡፡ የይሖዋ ምስክርች ትምህርተ ሥላሴን፣ ትምህርተ ክርስቶስን፣ ትምህርተ ድነትን፣ ወዘተ … ላይ ያሏቸውን አመለካከቶች የሚያስቃኙ የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል፡፡
ጸሐፊው ቃለ መጠይቅ ተደራጊው ለሚያነሡዋቸው ጉዳዮች የተለያዩ የሙግት ጥያቄዎችን ያቀርባሉ፡፡ አንዳንድም ቆጣ ብለው ይሞግቷቸዋል፡፡ ከጥያቄዎቹ አንጻር ሲታይ ሽመልስ የይሖዋ እምነት ተከታዮችን የእምነት አንቀጽ ጠንቅቀው የሚያውቁ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን በትምህርተ ሥላሴ የማያምኑ ሲሆኑ፣ አንዱ እግዚአብሔር በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ መልኮች ራሱን ገልጧል የሚል አስተምህሮን ያነገቡ ናቸው፡፡ በዚህም አስተምህሮ መሠረት እግዚአብሔር ራሱን በብሉይ ኪዳን እንደ “አብ”፣ በአዲስ ኪዳን እንደ “ወልድ”፣ አሁን በቤተ ክርስቲያን ዘመን ደግሞ “መንፈስ ቅዱስ” አድርጎ ገልጧል ይላሉ፡፡ በዚህ ክፍል የተጠቀሱት ቄስ አበራ አልበጆ ሲሆኑ፣ በአንድ አጥቢያ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ናቸው፡፡ ሊነሡ የሚገባቸው ወሳኝ ጥያቄዎች ተነሥተዋል፡፡
በሦስተኛ ደረጃ የሰፈረው አመለካከት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አቋም ነው፡፡ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው የኔታ “ገብረ ወልድ” ይሰኛሉ፡፡ ይህ ስም የቃለ መጠይቅ ተደራጊው ትክክለኛ ስም ሳይሆን የብእር ስም ነው፡፡ በዚህ ክፍል በዋነኛነት ትኩረት የተሰጠው ኢየሱስ አንድ ባሕርይ ወይስ ሁለት ባሕርይ አለው? ኢየሱስ ያማልዳል ስንል ምን ማለታችን ነው? ወዘተ… የሚሉና ኦርቶዶክሳውያን ከሌሎች አማኒያን በሚለዩባቸው የእምነት አቋሞች ላይ ነው፡፡
ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ዶ/ር አባ ዳንኤል አሰፋ ሲሆኑ፣ በፍራንሲስኮስ ገዳም የነገረ መለኮት መምህር ናቸው፡፡ የኦርቶዶክስ፣ የካቶሊክ እና የወንጌላዊያን አማኞች መሠረታዊ በሆነው ነገረ ክርስቶስ ላይ ስምምነት ያላቸው ቢሆን፣ በአንዳንድ አገላለጾች ላይ ግን ልዩነቶች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ፡- የኢየሱስ አንድ ባሕርይ ወይስ ሁለት ባሕርይ በሚለው ጉዳይ ላይ አለመስማማቶች አሉ፡፡
ከወንጌላዊያን አማኞች ለቃለ መጠይቅ የቀረቡት መምህር በልሁ ደለለኝ ናቸው፡፡ በልሁ በመሠረተ ክርስቶስ ኮሌጅ መምህር ናቸው፡፡ አንዳንድ አቋማቸው ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ጋር የሚመሳሰል ሲሆን፣ በተለይም ክርስቶስ በተዋሕዶ አንድ ባሕርይ ነው የሚለው የአቶ በልሁ አቋም ሆኖ ይታያል፡፡
በመጨረሻው ክፍል ላይ ጸሐፊው የራሳቸውን ብይን እና መደምደሚያ አስቀምጠዋል፡፡ ጸሐፊው ከኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክና ፕሮቴስታንቶች ጋር እግዚአብሔርን በተመለከተ ባለው አቋም እንደሚስማሙ በመግለጽ የይሖዋ ምስክሮችና የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ለእግዚአብሔር አሐዳዊነት ዘብ ለመቆም ሲሉ ትልቅ የሆነን ስሕተት ፈጽመዋል በማለት ይደመድማል፡፡
የተለያዩ የእምነት ክፍሎች የራሳቸው የሆነ የእምነት አንቀጽ አላቸው፡፡ እነዚህን በአካባቢያችን የሚገኙ የተለያዩ የእምነት ክፍሎችን መረዳት ጠቀሜታው እጅግ የላቀ ነው፡፡ ሌሎች ምን ያምናሉ የሚለውን መጠየቅ ከሌሎች ጋር ተቀራርቦ ውይይት (dialogue) ለማድረግ፣ የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመሥራት፣ ሌሎችን ያለ አግባብ ላለመፈረጅ ይጠቅማል፡፡ በሌሎች አገራት ውስጥ ተመሳሳይነት ያላቸው ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ ጸሐፊው እንደዚህ ዐይነት ባህልን በኢትዮጵያ ውስጥ ስላስተዋወቁ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል፡፡
ጸሐፊው የተለያዩ ቤተ እምነቶች ነገረ እግዚአብሔርን፣ ነገረ ሰብን እና ነገረ ክርስቶስን በተመለከተ የያዟቸውን አመለካከቶች ማስቃኘቱን በተወሰነ መልኩ ለርእሰ ጉዳዩ ታሪካዊ ዳራን በመስጠት ቢያፋፉት መልካም ነበር፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ታሪካዊ አመጣጥ ስላላቸው ለአንባቢያኑ አጠር ባለ መልኩ ታሪካዊ ዕድገታቸውን ቢያስቃኙ መልካም ነበር፤ ሙሉ የሆነውንም ምስል ይሰጥ ነበር፡፡
አንዳንድ ጊዜ ጸሐፊው የራሳቸውን አቋም ይዘው ስለሚጠይቁ ሞጋች/ተጋፋጭ አካሄድን እንዲከተሉ አድርጓቸዋል፡፡ ለምሳሌ፡- “ከሐቁ ለመሸሽ እየሞከሩ ነው” (42)፣ “ኢየሱስንማ እየሰበካችሁ አይደለም!”፣ “የይሖዋ ምስክሮች አባል መሆንን ብቸኛው የደኅንነት መንገድ በማስመሰል እንደ እናንተ የተካነ አለ እንዴ?” የሚሉ የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ይወክላሉ ተብለው የቀረቡት የኔታ “ገብረ ወልድ” በተወሰነ መልኩ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አቋም የሚቃረኑ ይመስላሉ፡፡ “ገብረ ወልድ” የሚለው ስም በጸሐፊው የወጣላቸው መሆኑ ብቻ ሳይሆን ግለ ሰቡ በትክክለኛ ስማቸው አለመጠራታቸው በአንዳንዶች በኩል ለሚነሣ የተኣማኒነት ጥያቄ መደላደል ይሰጣል፡፡ ʻጸሐፊው በትክክል የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን አቋም የሚያንጸባርቅ ሰው ቃለ መጠይቅ ቢያደርጉልን ይሻል ነበር?ʼ የሚል ጥያቄ እንድናነሣ ሳያስገድዱን አልቀሩም፡፡
ጸሐፊው አፍላቂነታቸው በታየበት መልኩ የተለያዩ ቤተ እምነቶች ክርስቶስን በተመለከተ ያሏቸውን አመለካከቶች አቅርበውልናል፡፡ ሽመልስ ይፍሩ መሳጭና ቀላል በሆነ አማሪኛ እያዋዙ ማስተላለፍ የሚፈልጉትን መልእክት በትክክል አድርሰዋል ለማለት እደፍራለሁ፡፡
የተለያዩ ቤተ እምነቶች እግዚአብሔርን፣ ክርስቶስን እና ሰውን በተመለከተ ያሏቸውን አቋም ማወቅ የሚፈልግ ሰው ይህን መጽሐፍ ቢያነበው ብዙ ይማርበታል፡፡ መጽሐፉ በተለያዩ ቤተ እምነቶች መካከል ያለውን ልዩነት ብቻ ሳይሆን የሐሳብ መመሳሰልንም አጉልቶ ያሳየናል፡፡
Share this article:
ንጉሤ ቡልቻ በዚህ ጽሑፋቸው፣ ምስቅልቅል ለበዛበት የአማኞች አምልኳዊ ገቢር መፍትሔ እንዲመጣ፣ “የልየታ መንፈስ” ይፈስስ ዘንድ ለአምላክ ተማጽኖ፣ ለምእመናንም ምክሮች ይለግሳሉ።
የስሜትና የሐሳብ ቁርኝት የፍቅር አካላት ሆነው ይነሣሉ። ያልተነጣጠለ አብሮነታቸውም አንደኛው ከሌለ የሌላው ሕልውና ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ ያደርጋል። ለነገሩ፣ ፍቅርን ከተያያዥ ስሜትና ሐሳብ አፋቶ ትርጉም ባለው መልኩ ማሰብስ ማን ይችላል? ተፈቃሪን በምናብ አጣምሮ ራስን ማብገንን ሆነ የመጨረሻዋ ተጠባቂ ሰከንድ አምልጣን ዘላለምን የተቀላቀለች ይመስል በቁንጥንጥ “ውዳችንን” መጠበቃችን በምንስ ይብራራል? በእርግጥም ከፍቅር ጋር ተያይዞ የምናሳየው መሰጠት፣ ሐዘኔታ፣ ቅናት፣ መረበሽ ከስሜትና ከሐሳብ ትሥሥር ጋር ይዛመዳሉ። የስሜቶቻችን እና የሐሳቦቻችን ቁርኝት ከሌሎች ተደምሮ ባዕድነትን ገፎ ተፈቃሪያችን በአንድት የሚገምድ ምስጢር ነው (ዘፍ. 2፥23-24)።
ናኦል በፈቃዱ፣ የሰሞኑ መነጋገሪያ ከሆነው ትጥቅ የመፍታትና አለመፍታት ፖለቲካዊ ውዝግብ ባሻገር፣ ሌላ ትጥቅ አስፈቺ እንዳለ ያስታውሰናል። ክርስቲያኖችም የትጥቅ ትግል እንዴት ሊያዩት እንደሚገባም ሐሳብ ያቀብላል።
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
Add comment