[the_ad_group id=”107″]

ሊላሽቅ የሚገባው የኢትዮጵያውያን ልቅ ጀብዱ

ለመቆጠብ ያህል፣ የኢትዮጵያ ታሪክ በአብዛኛው የጦርነትና የመገዳደል፣ አንዱ አንዱን በጦርነት የማንበርከክና ማዋረድ ታሪክ ነው። ከሃይማኖታዊም ሆነ ከማኅበረ ሰባዊ መዋቅር የይሁንታ ቡራኬ የሚቸርለትና የማይነቀፍ አንድ የወል (common) ጉዳይ ቢኖረን፣ ሌላውን የመግደልና ሟችን በአደባባይ የማሳየት ጀብዱ ነው። በርግጥ ብዙ ሰዎች ያለፈ ድርጊት (ታሪክ) የመርሳት አባዜ (historical amnesia) የሚያጠቃቸው ቢሆንም፣ ቢያንስ በየአምሳ ዓመት ርቀት (interval) አንዱ ሌላውን በአሰቃቂ ሁኔታ ያላጠቃበትና ማጥቃቱን በጀብደኝነት በአደባባይ ያላሳየበት ጊዜ የለም ብዬ እከራከራሁ።

የነገሥታቱ፣ የመሳፍንትና ባላባቱ ታሪክ ይህን በግልጽ ያሳያል። በስላች መንገድ እና አደባባዮች ላይ “ጠላትን”፣ “ዐመፀኛን”፣ “ተጠርጣሪን”፣ “ጸጉረ ልውጥን” ገድሎ፣ ሬሳውን ማንጠልጠል የባለ ጊዜ የመንግሥትም (የጊዜውን ሕግ ያረቀቀ የትናንት “ሽፍታም”) ሆነ፣ የነገ መንግሥት (የዛሬ “ሽፍታ”) ተወዳጅ ተግባር አልነበር? የጀኔራል መንግሥቱ ንዋይን የተንጠለጠለ ሬሳ ፎቶ ያላየ አለ ብዬ አልመንና፣ ይህ ዐይነቱ “መቀጣጫ” በሰሜኑም ሆነ በደቡቡ፣ በምስራቁም ሆነ በምዕራቡ የሆነ ነው። እኛ በሽፍትነትም በመንግሥትነትም እንደዚያ ነበርን፤ ነን። ነፍስ ጠፍቷል፤ እህል ተዘርፏል፤ በእሳት ተቃጥሏል፤ ሌላ ባለ ጉልበት እስኪመጣና ያንኑ እስኪደግም ድረስ።

ወደ አእምሮአችን ስንመለስ የዘመናዊ ታሪካችንን ምዕራፎች የሞሉት “የሥልጣኔ” ተግባራችን ሳይሆን፣ የመገዳደልና የደም መሆኑን እንረዳለን። የምኒልክ ጦር ራስ እና ደጃዝማቾች የገበረውን በሰላም እና በፍቅር፣ “እምቢኝ፤ አልገዛም” ያለውን ዲሂዩማናይዝ በሚያደርግ መልኩ መቀጣጫ አላደረጉምን? ይህ ሆኖ ሳለ “እግር ጡት አልቆረጡም”፣ “ጻድቃን ተዋጊዎች ነበሩ” መሰል ትርክት እስከ መቼ ልናንገዋልለው እንደወደድን ታያላችሁ። በተለይም ሥልጣን ያነጣጠረ ተራው ጦረኛ፣ ለጌቶቹ መታያና የግራዝማችነት ሹመት መቀበያ የሰውነት ክፍሎችን ከሬሳ ላይ አንሥቶ በአደባባይ በጀብደኝነት ማሳየት የተለመደ ቢሆንም፣ ይህንን በዚያ ዘመን ቅቡል የነበረ “ጠላትን ቅስም የመስበርያ” የጦርነት ስልት መሆኑን አምነን፣ ዛሬ ግን ሰብአዊነትን ባስቀደመው ዘመናዊ አስተሳሰብ ነቅፈን እና ተችተን ማለፍ ያቃተን ሰዎች ብዙ፣ ብዙ ነን።ይህ የታሪክን እውነታ መካድ የተጎዱትን ወገኖች ምን ያህል እንደሚያስከፋ፣ እንደሚያስቆጣ የተረዳን አይመስልም። ጡት፣እጅ የተቆረጠባቸው ኦሮሞዎች እና የደቡቡ ሕዝብም በተራቸው የማረኳቸውን የሰሜን አገሩን ምርኮኛ፣ በቁም መስለባቸውን፣ ቁዋንጃ መሳባቸውን፣ ሰዎቹ በሕይወት እያሉ በጭከና ቆዳቸውን ከላያቸው መግፈፋቸው፣ “የሌላውን ወኔ መግደያ” የጦርነት ስልት መሆኑን ብዙዎቻችን እስከ ዛሬ ልንቀበል የወደድን አይመስልም። የኦሮሞ (አክራሪ) ብሔረተኞች የመጀመሪያውን አጉልተው ይህንን ያለማንሣታቸው የተጠቂነት አመለካከት (victimhood mentality) አሁን ለተያዙት ትግል ስለሚጠቅማቸው፣ ኦሮሞው አምርሮ ሌላውን በተለይ አማራውንና ትግራዊውን እንዲጠላና እንዲያጠቃ የሚጠቀሙበት ካልሆነ በቀር፣ “አረመኔያዊ አገዳደል ኦሮሞ አይገድልም” ቢሉ በውስጣቸው ፈገግ እያሉ መሆን አለበት። ግን እውነታው የኦሮሞውም ሆነ ሌላው ጦረኛ ከሰሜናዊው ያልተናነሰ፣ በጉልበት ተስፋፊ ይህን በውዴታ አልቀበል ያለውን (ለዘመናዊው ሰው ሰቅጣጭ በሆነ መልኩ) ቅጣት ሰጪ፣ ቀማኛ፣ ገፋፊ፣ ገራፊ፣ ወዘተ. ነበር። ታሪካችን ይህ እና ያ ነው።

እንደ ጥንቱ ዛሬም የእኛ መገለጫ በዘር ጎሣ ርዕዮተ ዓለም የነዳቸው የጦርነቶች (በአረመኔያዊ ሁኔታም ጭምር) የመገዳደል ታሪክና ግዳይን በአደባባይ ማሳየት የተለመደ ነው። የቅርቡ 60ዎቹ የሰው ነፍስ ማርከስ የነጭ/ቀይ ሽብርስ ምን ነበር? ሰውን በጠራራ ፀሓይ ገደሎ ሬሳን በአደባባይ ለሌላው መቀጣጫ ለሚውል ትዕይንት ማሳያ ማድረግ የዛሬው ሰው ሊረሳው ቢችልም፣ የእኛነታችን ማኅተም ነው። በቅርቡ በቲቪ ይቀርብ የነበረው የየእስር ቤቶች ሰቆቃ ፈጻሚዎች የባለጊዜዎቹ “የማረሚያ ቤት” ትግራዊ አዛዦች ታሪክ ብቻ ሳይሆን፣ በውስጣችን የተሰነቀረ፣ ሌላውን ከሰውነት ተራ የማውጣት፣ የማዋረድና የማሰቃየት ጀብድ “የእኛ ጉዳይ” መሆኑን መስካሪዎች ናቸው፡፡

የሻሸመኔውም ድርጊት ፈጻሚዎች የጀብደኝነት ደስታ ስካር የማንነታችን ሌላው ገጽታ ነው። ባዕድ አይደለም። ሁላችንም በድርጊቱ ለጊዜው ልንደነግጥ ችለን ይሆናል እንጂ፣ መገረማቻን ግን የውሸት ነው። የማንነታችን መገለጫ ምን ያስገርማል? በአንዳንድ ፌስ ቡክ ገጾች መልእክት ላይ የድርጊቱን ጀስቲፍኬሽን ከአንዳንድ የኦሮሞ መብት ተከራካሪዎች ብትሰሙ አትገረሙ፤ ይህ የሆነው አረመኔነት የእኛ በመሆኑ ብቻ ነው።

ሁኔታው የሚያሳየው ነገም የጉጂው/ጌዲኦው፣ ሱማሌው፣ የሻሸመኔው ዐይነት የአረመኔ ድል ሌላውን በአደባባይ የመግደልና ለሕዝብ ዕይታ የማቅረብ “ሥርዐት” (“rituals”) ከእኛ ርቆ የትም አይሄድም፤ ላይናድ ውስጣችን የተቀረቀረ ነውና፤ አሳፋሪ ታሪካችንም ከእኛ ጋር ይኖራል። እየተደመምን፣ እየተደነቅን፣ እየደነገጥን ሳንለወጥ ወደ ሌላ የግድያ ታሪክ እናልፋለን። ይህ ጽሕፍ ከተጻፈ በኋላ እንኳ የእኛው 37 ኦሮሞዎች በእኛው ሱማሌዎች ተገድለናል፤ እኛ የምስራቅ ወለጋ ኦሮሞዎች የእኛን 2 ትግራውያንን በድንጋይ ጨፍጭፈን ገድለናል፤ ወደ ወገኖቻችን የትግራይ ነዋሪዎች (በርግጠኝነት ትገሬ ብቻ የማይበላውን) እህል በጠራራ ፀሓይ ከመኪና ላይ ዘርፈን ተከፋፍለናል።

መፍትሔ ዐልባ ግን አልነበርንም

  • ነውረኛነታችንን እንመን፤ የታሪካችንን ጥሬ ሃቅ መጋፈጥ እኮ የግል/የማኅበረ ሰብ አብሮ የመኖርን ማነቆ ለመፍታት የሚደረግ ጥረት በብርቱ ይረዳ ነበር፤ የጭካኔያችንን መነሻ ማወቅና ‘ችግሩን እንዴት እንፍታ?’ ለሚለው ጥያቄ (ብቸኛው ባይሆንም) አንዱ መንደርደሪያ ነበር።
  • ዛሬ እኛን የገደለን ትናንት ገላውን በጭከና የቦጫጨቅነው መሆኑን እንመን።
  • በተለይ፣ በተለይ ግን ተነጻጻሪ ሁኔታን ከአውሮፓ መካካለኛው ዘመን ታሪክ የምናነብበውን አሰቃቂ የአገዳደል እና የመገዳደል ድርጊቶችን በእኛ ዘንድ እንዳለ ሳይቀየር መኖሩን ማወቅ ቀጣይ ምን እናድርግ ለሚለው መንደርደሪያ ነው። እነርሱ ያንን አረመኔነት ከጫንቃቸው ላይ ሊጥሉ ቆረጡ። የ18ኛው ክፍለ ዘመን ትልቁ ድል ታዲያ፦ 1) የሕግ የበላይነትን ማስፈን ነበር። ይህንንም ለማድረግ በቅድሚያ የሕግ አስፈጻሚ አካላትን ከሃይማኖት፣ ከሕዝቦች (ዘሮች) ጥቅምና ተጽእኖ ማላቀቅ አንዱ መሥመር ነው። አሁኑኑ በእጃችን ያለው ተግባር ይህ በሆነ፣ የጀግናና የሌላውን ተልትሎ ገዳይ አወዳሽም ሆነ “ለዚህ” ወግኖ፣ “ያንን” በጭፈና የማጥቃት የጀብደኝነት ማንነታችን በሕግ የበላይነት ማለስለስ ያስፈልጋል። 2) ኢንዱስትሪን ማስፋፋት፤ ሥራን መፍጠርና ሠራተኛን መሸለም፤ ወጣቱን ወደ ሥራ መግፋት። 3) ዘመናዊ ትምህርትን አሁንም ጨከን ብሎ (ከጥራት ጋር) ማስፋፋት።
  • ሰብአዊነትን ማስቀደም፤ ጀግንነት፣ ይልቁኑ ጀብድ የሚነዳውን ማንነት (ኢትዮጵያዊነት፣ ኦሮሞነት፣ ትግራዊነት፣ …) ዕሳቤን ከአእምሯችን ፍቀን፣ በሌላ ማንነት ለመለወጥ ሐሳብ አቅርቦ መወያየት፤ አብሮን የኖረ የእኛነታችን፣ የጀብዱ ማኅተምን በሌላ ሰብአዊ ማኅተም (symbol and metaphor) መቀየር። የዶ/ር ዐቢይ “መደመር” እና “ፍቅር” ረቀቅ፣ ሰፋ፣ ተንተን ቢልና በሁሉም ዘንድ (ወደ ሁሉም ክልሎች ቢደርስና) ቢሠርጽ አንድ አማራጭ ነበር።

ጥያቄዬ ግን፣ ‘በዘመኔ ሰብአዊነትን የረገጠ ልቅ ጀብድም ሆነ ጀግንነት ሲላሽቅ ማየት እችል ይሆን?’ የሚል ነው።

Share this article:

ለዋጭ ለውጦች!

አድማጭ የሚሹ ብዙ ጩኸቶች እዚህም እዚያም አሉ። የሰው ልጅ የስኬት ብቻ ሕይወት የለውም፤ ውድቀትም አንዱ የኑሮ ገጽታ ነው። በውድቀት ውስጥ ብዙ ሕመሞች በሰዎች ልብ ውስጥ ተቀርቅረው ይገኛሉ። እነዚህ ሕመሞች እንዲታከሙ የሚያስችሉ አድማጭ ጆሮ ያላቸው መካሪዎች በእጅጉ ያስፈልጉናል ይላል ይህ የተካልኝ ነጋ (ዶ/ር) ጽሑፍ።

ተጨማሪ ያንብቡ

ዊክሊፍ:- የታላቁ ለውጥ አጥቢያ ኮከብ

የፕሮቴስታንት ተሓድሶ በሚታወስበት በዚህ ሰሞን፣ ለማርቲን ሉተርና ለሌሎቹ ተሓድሷውያን ነገረ መለኮታዊ መደላድል አስቀድሞ ሠርቶ አልፏል ስለሚባልለት ጆን ዊክሊፍ እንድናስታውስ፣ ፍቅረየሱስ ሁንዴሳ ይህን ዝክር እንደሚከተለው ያስነብበናል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ፍቅርን የመግለጫ መንገዶች

በፍቅር የተጋመዱ ጥንዶች ትሥሥራቸውን አስመልክቶ ጥያቄዎችን ማንሣታቸው አይቀርም። አንዳንዱ ጥያቄ የሚሰነዘረው ለአፍቃሪው ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ መልስ ከተፈቃሪው ይሻል። ከሚነሡት ጥያቄዎች መካከል አንደኛው “የፍቅር ጥያቄ” ነው። ራሳችንን፣ “በርግጥ አፈቅራታለሁኝ?”፣ “እሷስ ከልቧ ታፈቅረኛለች?” እንላለን። መነሾው ቢለያይም፣ በደስታ መኻል ስንቅር የሚል ጥያቄ እንደ መሆኑ ያስጠላል፤ ያስፈራልም። ሲ. ኤስ. ሊዊስም፣ “ፍቅር በሕይወታችን ካለ ጽኑና ቀጣይ ደስታ ከዐሥሩ የዘጠኙን እጅ ድርሻ ይወስዳል” እንደ ማለቱ ጥያቄው አይናቅም።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published.

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.