[the_ad_group id=”107″]

የክርስቶስ ሞት ፋይዳዎች

Painting by: Salvador Dali, “Christ of Saint John of the Cross”

ብዙ ጊዜ የክርስቶስን ሞት ፋይዳ የምናስበው በዓመት አንድ ጊዜ በምናከብረው በዓል ነው። ሆኖም የዕለት ተ’ለት ሕይወታችን አካል ሊሆን የሚገባው ‘የጌታችን ሞት ፋይዳ ምንድን ነው?’ ብለን ማሰላሰል አለብን። በዚህ ዐጭር ጽሑፍ የክርስቶስን ሞት ዐምስት ፋይዳዎች አብራራለሁ።

1. የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያሳያል

መስቀሉ የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያሳያል። በሺሕ ከሚቈጠሩ ዓመታት በፊት እግዚአብሔር ልጁ በሆነው በመሲሁ በኩል ሊያደርግ ያለውን ፈጸመ። ይህም በዘፍጥረት መጽሐፍ (3፥15)፣ በተለያዩ የመዝሙረ ዳዊት ምንባባትና በነቢያቱ በኩል የተናገረው ነበር። በዚህም ለቃሉ ታማኝ አምላክ መሆኑን አሳይቷል። በተመሳሳይም፣ ኢየሱስ ተመልሶ እንደሚመጣ ተናግሯልና በዚህም ሙሉና ርግጠኛ የምንሆንበትን ተስፋ ይሰጠናል። መስቀሉ የታማኝነቱ ማሳያ ነው።

2. የማይገባንን ይቅርታ አገኘን

“በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን፤ እርሱም የበደላችን ስርየት።” (ኤፌሶን 1፥7)


በሞቱ የኀጢአታችንን ይቅርታ አገኘን። ነገር ግን፣ አምላካችን ቅድስናውንና ጽድቁን ሽሮ አይደለም ይህን ያደረገው፤ የምንድንበትን ምትካዊ መሥዋዕት ራሱ በማቅረብ እንጂ። ክርስቶስ በመስቀል ላይ በከፈለው መሥዋዕትነት ከእግዚአብሔር ቍጣ ተረፍን፤ ይቅርታንም አገኘን። እርሱ እንከን አልቦና ቅዱስ ሆኖ ሳለ፣ ፍጹም ኀጢአተኞች ለሆንነው ለእኛ በሞቱ ይቅርታን አስገኘልን። በእኛ ሊወርድ ይገባ የነበረው የእግዚአብሔር ቍጣ በአንድያ ልጁ ላይ ዐረፈ። ክርስቶስ ስለ እኛ ተቀጣ። ትንቢተ ኢሳይያስ ከምዕራፍ 52-53 ይህን አስቀድሞ ተናግሯል። በዚህም እኛን ኀጢአተኞቹን ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀን፤ በኢየሱስ መካከለኝነትም በድፍረት ወደ አብ መግባትን አገኘን። እንዴት ያለ ምሕረት፣ እንዴት ያለ ፍቅር፣ እንዴትስ ያለ ጽድቅ ነው!

3. ከአእምሮ የሚያልፈውን ፍቅሩን አሳየን

“ለጻድቅ የሚሞት ሰው ማግኘት እጅጉን ያዳግታል፤ ለደግ ሰው ሲል ሊሞት የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል። ነገር ግን ገና ኀጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞተ፤ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያሳያል።” (ሮሜ 5፥7-8)።
ይህ እንዴት ያለ ፍቅር ነው! እግዚአብሔር በልጁ አዳነን። ሰው ለጠላቱ አይሞትም፤ ክርስቶስ ግን በእርሱ ላይ ዐምፀን ጠላቶቹ ሳለን እኛን ሊያድን ሞተ። ይህ የእግዚአብሔርን ፍቅር፣ በማንም ታይቶ የማይታወቀውን ፍቅር ያሳያል። ሰውን ሁሉ ማጥፋት የሚችለው አምላክ ሊያድነን ሲፈቅድ ታይቶ በማይታወቅ፣ አእምሮን በሚያልፍ ፍቅሩ ወደደን። ዮሐንስ 3፥16 እንደሚናገረው፣ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” ኦ! ይህን ከአእምሮ የሚያልፍ፣ ደግሞም ልብን የሚያሳርፍ ፍቅር እግዚአብሔር ዕለት ዕለት ይግለጥልን፤ የሚያጸናም መልሕቅ ይሁነን!

4. የእግዚአብሔር ሕዝብ፣ የእግዚአብሔር ቤተ ሰብ አባል አደረገን

“አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።” (ገላትያ 1፥28)

የክርስቶስ ፍቅር አንድ አደረገን። በክርስቶስ ደም ይቅርታን በማግኘት እኛ ሩቅ የነበርነውን አሕዛብ፣ እኛ የእግዚአብሔር ሕዝብ ያልተባልነውን፣ የእግዚአብሔር ሕዝቦች አደረገን። በአሮጌው ኪዳን እስራኤል የእግዚአብሔር ሕዝብ ነበር፤ እኛም አሕዛብ፣ መፃተኞች/እንግዶች ነበርን። አሁን ግን ሩቅ የነበርነውን፣ ከእግዚአብሔር ተለይተን የቈየነውን ሕዝቦች በክርስቶስ ይቅርታን በመስጠት ሕዝቡ አደረገን። የክርስቶስም ሞት አይሁድና አሕዛብ አንድ የሆኑበትን ቤተ ክርስቲያንን መሠረተ። የክርስቶስ ሞት በእግዚአብሔርና በእኛ በአሕዛብ፣ እንዲሁም በእኛ እና በአይሁድ የነበረውን የጥል ግድግዳ አፈረሰ። ሁላችን በክርስቶስ አንድ ሆንን፤ ባሪያም ጨዋም፣ አይሁድም ግሪክም፣ ሴትም ወንድም። በዚህም የእግዚአብሔር ሕዝብ፣ የእግዚአብሔር ቤተ ሰብ አባል አደረገን።

5. ከኀጢአት ባርነት አዳነን

“አሁን ግን ከኀጢአት ነጻ ወጥታችሁ የእግዚአብሔር ባሮች ሆናችኋል፤ የምትሰበስቡትም ፍሬ ወደ ቅድስና ያመራል፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው። የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።” (ሮሜ 6፥22-23)

በክርስቶስ ሞት ከኀጢአት ባርነት አርነት ወጥተናል። ከዚያ ቀደም ግን፣ ለኀጢአትና ለሰይጣን ባርያ ነበርን። ስሜታችን፣ ፈቃዳችን፣ ዐሳባችንም ለሰይጣንና ለኀጢአት ባሪያ ነበር። ምንም አልቀረልንም፤ በግልጽና በግብዝነት ለእነዚህ ገዦቻችን ተንበረከክን። እርሱ ግን እስራኤልን ከፈርዖን እጅ እንደታደገ ሁሉ (ዘዳግም 7፥8፤ 9፥26)፣ በቤዛነቱ ከኀጢአትና ከሰይጣን ባርነት ነጻ አወጣን። ቈላስይስ 1፥13-14 እንዲህ ይላል፦ “እርሱ ከጨለማ አገዛዝ ታደገን፤ ወደሚወደው ልጁ መንግሥትም አሻገረን፤ በእርሱም መዋጀትን በደሙ አግኝተናል፤ ይህም የኀጢአት ይቅርታ ነው።”

ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን!

Share this article:

ለክቡር ጥሪ የሚመጥን ክቡር ሕይወት

አንዳንዶች ሰዎች በሕይወታቸው ትርጉም ላለው፣ ብሎም ዓላማቸው ላደረጉት ጉዳይ እስከ ሞት ሊደርስ በሚችል መከራ ውስጥ ያልፋሉ፡፡ ማዕበሉ የሚንጥና የሚያንገላታ ቢሆንም፣ የሕይወት ምስቅልቅሎሹ ቢበረታም ዓላማቸውን ግን የሙጥኝ ይላሉ፡፡ በእውነቱ እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች ተፈትነው ያልተረቱና የማይናወጥ ጠንካራ ሰብዕናን የተላበሱ ናቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

ጥልቅ ዐሳቢው ጳጳስ

ስመ ጥር ካደረጉትና ዝናን ካጎናጸፉት መጻሕፍቱ መካከል፣ “ኑዛዜ” የተሰኘውን ጥራዝ ሳይጠቅስ የሚያልፍ ጸሐፊ አለ ለማለት ያስቸግራል፤ “ጌታ ሆይ፤ ለራስህ ስትል ስለ ፈጠርከን ልባችን በአንተ ላይ እስኪያርፍ ድረስ የትም ይባክናል” የተሰኘውና ተደጋግሞ የሚነሣው ኀይለ ቃልም ከዚሁ መጽሐፍ ነው ተመዞ የወጣው።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.