[the_ad_group id=”107″]

እግዚአብሔርን የመፍራት በረከት

ምሳ. 23፥17

..ነገር ግን ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑር

በእውነት ፍጻሜ አለህና

ተስፋህም አይጠፋምና

የምንኖርበትን ዓለም በትዝብት መነፅር ብንመለከት የሰው ልጅ ሕይወት ውጣ ውረድና ትግል የበዛበት በመሆኑ ፍቅርና ጥላቻን እንዲሁም በእምነትና በክህደት መካከል ያለው የነፍስ ፍትጊያ እንዴት እንደ ሆነ ለመረዳት አንቸገርም። ሰው በዚህ ምድር ላይ ሲኖር ራሱን ከሌላው የተሻለ አድርጎ ለሌሎች ለማሳየት ወይም ከሌላው ሰው በልጦ ለመታየት የማይምሰው ጉድጓድና የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። የተፈጥሮ ሕግን ተከትሎ ጊዜው ሲመሽና ሲነጋ የሰውም ሕይወት አንዴ ሲጨልም፣ አንዳንዴ ደግሞ ፍንትው ብሎ ፀሓይ እንደወጣችለት ቀን ሲበራ ይታያል። አንዱ ለመማር፣ ሌላው ለመነገድና ጠቀም ያለ ትርፍን ለማግኘት፣ ወዘተ. በማሰብ ይሮጣል፤ ይማስናል። ባለው ጊዜ በጉልበቱም ሆነ በአእምሮው ኀይል እየተጠቀመ በፊት ከነበረው ሕይወት ወደ ተሻለና ወደ ላቀ የኑሮ ደረጃ ለመድረስ ይፍጨረጨራል። ታዲያ በዚህ የሕይወት ትንቅንቅ ውስጥ የሚያሳዝነው ተግባር አንዳንዱ ሰው ሌላው ወገኑን ወደ ታች በመርገጥ እርሱ ብቻ ለመበልጸግ መሞከሩ ነው። ያለምንም እፍረት ከሌሎች ላይ በግፍና በቅሚያ መንትፎ የያዘውን ʻእዩልኝʼ ብሎ ደረቱን ነፍቶ ወደ አደባባይ በኩራት ይወጣል። በአንጻሩ ደግሞ ፈሪሓ እግዚአብሔር ያላቸውና ጽድቅን አንግበው በእውነተኛው መንገድ ላይ የሚጓዙ ጥቂት የማይባሉ ሰዎችም አሉ። እነዚህ ሰዎች ለሰውም ሆነ ለፈጣሪ ሕግ ራሳቸውን አስገዝተውና ጽድቅን የሙጥኝ ብለው የሚኖሩ በመሆናቸው ምድራዊው ሕይወት እንደ ትልቅ ተራራ ከፊታቸው ተጋርጦ ሁልጊዜ በብርቱ ትግልና መፍጨርጨር ኑሯቸውን ለማሸነፍ የሚታገሉ ናቸው።

የጽድቅን መንገድ የመረጡ እውነተኞች ለበርካታ ዓመታት የደከሙበት ነገር መዳፍ የማይሞላ ሆኖ እያለ፣ በአንጻሩ ደግሞ ሌሎች በሐሰተኛ ሚዛን እውነትን ሸጠው እየኖሩ በቀላሉ ተሰፍሮ የማያልቅ ብልጽግናና ሀብትን ያከማቻሉ። ታዲያ በዚህን ጊዜ የጽድቅን አማራጭ ብቻ ይዘው በብዙ ድካምና ልፋት የኑሮን ተራራ ለመግፋት የሚውተረተሩ ጻድቃን ልባቸው በእነዚህ ሰዎች ይቀናል። እንዲህም በማለትም ይናገራሉ፡- “እኔ ዐመፃን ጠልቼ በጽድቅ ሕይወት ብቻ መኖሬ ምን አተረፈልኝ? ሕይወት ፊቷን አዙራብኝ ዘወትር በልፋትና በመማቀቅ መኖሩ ሰልችቶኛል።” እነርሱም እንደ ሌሎቹ በግፍና በሐሰት ኑሮ ለመሳተፍ ልባቸው ይከጅላል።

የሁሉ ፈጣሪ የሆነው እግዚአብሔር የሰውን ልቦና በትክክል የሚመዝን በመሆኑ፣ በተለይም እርሱን የሚያውቁት በትክክለኛው መንገድ ላይ እየተራመዱ ሠርተው ባገኙት ጥቂት ነገር ብቻ ረክተውና በጌታቸው ታምነው እንዲኖሩ እንጂ የኀጥአንን ቅጽበታዊ ስኬት ተመልክተውና ከቆሙበት የጽድቅ መንገድ ተንሸራትተው እንዳይወድቁ ያስጠነቅቃል። አዎን፤ እርሱን በመፍራት መኖርና በጽድቅ መንገድ መመላለስ ትልቅ በረከት አለው። ለመሆኑ እግዚአብሔርን የመፍራትና በጽድቅ መንገድ መኖር ያለው ብድራት ምንድነው? በመጽሐፈ ምሳሌ 23፥17 ላይ ሁለት ዐበይት ቁም ነገሮችን እንመለከታለን።

1. ያማረና የተቃና ፍጻሜን ማግኘት

ይሄ ክፍል በዋናነት የሚናገረው እግዚአብሔርን ስለ መፍራት ነው። “ቀኑን ሙሉ እግዚአብሔርን በመፍራት ኑር” የሚለው አባባል ሰው በማንኛውም ጊዜ፣ ማለትም በደስታና በኀዘን፣ በማግኘትና በማጣት፣ በብቸኝነትና በአጀብ እንዲሁም በክብርና በውርደት ውስጥ ሁሉ እግዚአብሔርን በመፍራት መኖር እንደሚገባው የሚናገር ነው። ሰው በማንኛውም ጊዜ እግዚአብሔርን በመፍራት የሚኖር ከሆነ ፍጻሜው ያማረና የተቃና ይሆናል። ይህንን ስንል ግን በሰው የሕይወት ጎዳና ላይ ሁልጊዜ ፈጣሪውን እያሰበና እየፈራ ሊኖር የማይችልባቸው አጋጣሚዎች አይኖሩም ማለት አይደለም። ሆኖም ግን፣ በእነዚህ ጊዜያት እንኳን የራሱን ስሜትና ፈቃድ ሳይሆን የአምላኩን ሐሳብ ለመኖር የሚጥር መሆን አለበት ማለታችን ነው። የሰው ፍጻሜ በፈጣሪ እጅ ብቻ ያለ በመሆኑ ሰው ነገን በተመለከተ ʻእንዲህ ይሆናልʼ ብሎ ፈጽሞ መገመት አይችልም። በሕይወት ዘመኑ እግዚአብሔርን በመፍራት ለሚኖር ጻድቅ ግን ፍጻሜው የጥፋትና የኀዘን ሳይሆን፣ የተድላና የክብር እንደ ሆነ ከአምላኩ ዘንድ መለኮታዊ ማረጋገጫ ተሰጥቶታል። ምንም እንኳን ኀጥእ ለጊዜው በቅሚያና በዝርፊያ በሰበሰበው ቁሳዊ ነገሮች የተደሰተ ቢመስለውም፣ ፍጻሜው ግን የጥፋት ነው። በመንገዱ እግዚአብሔርን በመፍራት የሚመላለስ ሰው አምላኩ በማይከብርበት ነገር ውስጥ ስለማይገባ ጌታውን አስደስቶ የሚኖር ነው። እግዚአብሔርን በመፍራት የሚመላለስ ሰው መለኮታዊ ለሆነው የኑሮ መለኪያ የሚመጥን ኑሮን የሚኖር ነው። ከዚህ የተነሣ አምላኩ ፍጻሜውን ውብና ግሩም አድርጎ ይሰጠዋል።

ዛሬ በዙሪያችን ያለውን የኀጢአተኞች ጊዜያዊ ተድላ ተመልክተን ጌታን መፍራታችንን ችላ ልንለው አይገባም። ጌታን በመፍራት በጽድቅ መንገድ ላይ ስንጓዝ ይህች ዓለም ለእኛ የተገባችን ባለመሆኗ ሊደላን አይችልም። ሆኖም ግን ዛሬ በምናልፍበት በማንኛውም የሕይወት መንገድ በሕያው መንፈሱ እየተጽናናን ሊገለጥ ያለውን የፍጻሜአችንን ክብር ልናስብ ይገባል፤ የዘላለም መኖሪያችን በዚህ አይደለምና። ፍጻሜአችንም በዙሪያችን እንዳሉ ጌታን እንደማያውቁ ሰዎች የጥፋት ሳይሆን የክብር ነው። አሁን ያለንበት ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ፈጽሞ የጠፋበትና ዐመፅ የገነነበት፣ እንደውም እግዚአብሔርን በመፍራት በጽድቅ መንገድ ብቻ የሚሄዱ ሰዎች እንደ ኋላ ቀር ሰው የሚቆጠሩበት ጊዜ ነው። ይሄ ደግሞ በውጭ ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያንም ውስጥም በስፋት መታመኑ የሚያስገርም ነው። ዛሬ በቤተ ክርስቲያን በግልጽ የምናየው ነገር አገልግሎት በገንዘብና ጠፊ በሆነው ቁሳቁስ መለወጡ ነው። በጣም የሚደንቀው ነገር መድረኩ ጠብቦት ʻአገልግሎት በዛብኝ፤ መተንፈሻ ጊዜ አጣሁʼ የሚለው አገልጋዩም ከወንጌል ይልቅ ለክብርና ስም እንዲሁም ለቁሳቁስ ሲጋደል ማየታችን ምን ያህል ፍጻሜአችንን እንደዘነጋን አመላካች ነው።

2. የማይጠፋና የማይቋረጥ ተስፋን ማግኘት

እግዚአብሔርን በመፍራት መኖር የሚያስገኘው ሌላው ብድራት መቼም የማይጠፋና የማይቋረጥ ተስፋን ይሰጣል። እግዚአብሔርን በመፍራት በጽድቅ መንገድ ላይ የሚራመዱ ቅዱሳን ምንም እንኳን በዚህ ምድር ላይ በኑሮአቸው ባይደላቸውም ሁልጊዜ ግን ነፍሳቸው የምትረካበት የማይጠፋ ጽኑ ተስፋ አላቸው። በእንግድነት ዘመናቸው በዚህ ምድር ላይ ሲኖሩ የሚገጥማቸው ምድራዊ የሕይወት ሳንካ ተስፋቸውን አያናውጠውም። በሚቆረቁር ነገር ላይ ሆነው ሕመም አልባ የሆነውን የወደፊት ኑሮአቸውን አትኩረው ይመለከታሉ። ጌታን በመፍራት ለሚኖሩ ጻድቃን የተሰጠው ተስፋ ከዘመን ጋር የሚያከትም ጊዜያዊ ሳይሆን ዘላለማዊ ነው። መቼም ተስፋን ስናስብ ተስፋ ሰጪውንም ማሰባችን አይቀሬ ነው። እግዚአብሔርን የሚፈሩ የጻድቃን ተስፋ ምድራዊና ነገ ወደ አፈር በሚገባ ሥጋ ለባሽ የተሰጠ ሳይሆን፣ ዘላለማዊና ሕያው ከሆነው ከእግዚአብሔር የተሰጠ ነው። ጌታን የሚፈራ ጻድቅ በዚህ ምድር ላይ ሲኖር በግፍና በዐመፃ የተጀቦነውን የኀጥአንን ቅጽበታዊ ስኬት በመመኘት ጊዜውን አያባክንም። ነገ እንደ ጉም በንኖ በሚጠፋው ምድራዊ ብልጽግና ላይም ልቡን አይጥልም። ሆኖም ግን፣ በልቡ ላይ የሚያነግሠው አምላኩን ብቻ ነው። ስለሆነም፣ ሁልጊዜ ከጌታው በተሰጠው የማይቋረጥ መለኮታዊ ተስፋ ነፍሱ እፈነደቀች በዚህ ምስቅልቅሉ በወጣ ዓለም ውስጥ አምላኩን እያከበረ ይኖራል። በማይመች ሁኔታ ውስጥ ደስ እንዲለውና በጌታው ላይ ያለውን መታመን እንዲጨምር የሚያደርገው ከጌታው የተሰጠው መለኮታዊ ተስፋ ነው። ታዲያ ይሄንን ተስፋ ለአፍታ እንኳን አይዘነጋውም፤ ያስበዋል፤ ያሰላስለዋል ይኖረውማል።

ዛሬ ልባችን ላይ የነገሠው ምንድነው፤ መለኮታዊ ተስፋ ወይንስ ጠፊ የሆነ ምድራዊ ቁሳቁስ? በአሁኑ ጊዜማ አብዛኛው አማኝ ተስፋውን የሚያያይዘው ከሚበላና ከሚጠጣ ነገር ጋር ሆኗል። ልቡ ምድራዊው ላይ ተሰክቶ ምን በወጣውና ሰማያዊውን ነገር ያስባል? የነቢያቱም ተደጋጋሚ የልብ ምት የሚያቀነቅነው ሰማያዊውን ሳይሆን ʻትወጣለህ፣ ትሻገራለህ፣ ትንሳፈፋለህ ወዘተ.ʼ በሚል ምድራዊ ብልፅግና ላይ ያረፈ ሰዋዊ የሆነ የምኞት ስንቅ ነው። የአማኝ ተስፋ በዚህ ምድር በሆነ ጠፊ ነገር ላይ ሳይሆን ከሰማይ የሆነ ሰማያዊ ነው። ስለሆነም፣ ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በመፍራት እየኖርን የማይጠፋውን መለኮታዊ ተስፋችንን አትኩረን እንመልከት። ሕያው አምላክ በማያልቀው ቸርነቱ ልቡናችንን ወደ ራሱ ይመልስልን። አሜን!

Share this article:

ቅዱስ መንፈስም ይለያል!

በደግም ቀን ሆነ በክፉዉም ዘመናት ክርስቶስን እና እውነተኛ ትምህርቱን የሚገልጠው መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ሊሆን ይገባል ስንል በብዙ ምክንያቶች ነው። አንድም ዙሪያችን በብዙ እንቅስቃሴዎች የተሞላ በመሆኑ በተፈጥሮውም ሆነ በመንፈሳዊው ዓለም ብቻችንን አይደለንምንና ነው። አንድም በአንዱ መንፈስ ቅዱስ የማይገዛ ሕይወት፣ ትምህርት እና አገልግሎት ለሌሎች ብዙ መንፈሶች ጥቃት ስለሚጋለጥ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ

እውነተኛ ንስሐ

በደልና ዐመፅ ባየለበት፣ አንዱ ሌላው ላይ በሚጠቁምበት፣ ሌላውም ለምን ተነካሁ በሚልበት፣ ሁሉም ራሱን ባጸደቀበት በዚህ አስቸጋሪ ዘመን፣ ስለ ንስሓ እውነቶች፣ “እውነተኛ ንስሓ” በሚል ንጉሤ ቡልቻ ይህንን ያካፍሉናል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.