[the_ad_group id=”107″]

እኔነት የሚፈታተነው የክርስቶስ ማኅበር አንድነት

“ደሞዛችን አልደረሰም እንዴ?” ስትል ጠየቀችኝ። ጠያቂዋ ሚስቴ ስትሆን፣ ትዳር ከመሠረትን ሁለት ሳምንት ገደማ የሆነን ይመስለኛል። ለካንስ ላቤን አንጠፍጥፌ የማገኘው ደሞዝ፣ ከትዳር በኋላ ደሞዛችን ሆኗል! ላቤም የግሌ አይደለም ማለት ነው። ይሄን ማሰቡ ድንጋጤ ለቀቀብኝ። ባልና ሚስት አንድ አካል፣ አንድ አምሳል እንደሆኑ አልጠፋኝም፤ ክርስቲያናዊው ትዳር፣ “ባል በገዛ ሥጋው ላይ ሥልጣን የለውም፤ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ” በሚል መርሕ መታቀፉን ከማግባቴም በፊት ዐውቃለሁ (1ቆሮ. 7፥4)። የሥጋዬ የግል ንብረትነት አክትሞ፣ ሌላው ነገሬ የግሌ ሆኖ ሊቀጥል አይችልም። ታዲያ የተግባሩ ቀን ሲከሰትና “የእኔ” የሚለው የይዞታ ማረጋገጫ ቃል፣ “የእኛ” በሚል ሲቀየር ምን አስደነገጠኝ?

ጕዳዩ በዚህ ብቻ አልተገደበም፤ “የእኛ” የሚለው ቃል በሌሎች ነገሮችም ላይ ተፈታትኖኛል። በእጮኝነት ጊዜአችንም እኔ ከእርሷ በተለየ መልኩ “እኔ” በማለት አስብ እንደ ነበር አስታውሳለሁ። በርግጥ አሁን እንደዚያ ባልሆንም፣ ከእኔነት ሙሉ በሙሉ የጸዳሁ አይደለሁም። ከትዳር በፊት ከነበሩኝ አስተሳሰቦች እና ዝንባሌዎች፣ ወደ ትዳር ከገባሁ በኋላም እንኳ እንደ ጨጎጊት በላዬ ተጣብቆ ያስቸገረኝ ነገር ቢኖር ይኸው “እኔ” ነበር።

“እኔ” የብዙ ትዳሮች ክሽፈት ሰበብ እንደ ሆነ የተሳካ ትዳር ያላቸው ትልልቅ ሰዎች ይናገራሉ፤ ለነገሩማ ሌሎችም በቀላሉ ሊታዘቡት የሚችሉት ነገር ነው። ነገር ግን “እኔ” ሳንካነቱ ለትዳር ብቻ አይደለም፤ የመንፈሳዊ ሕይወት እና አገልግሎት ነቀርሳ ነው። የአገር ዕድገትና የዓለም ሰላም ጸርም ነው። እኔነት የግለኛነት መገለጫ፣ የግለኛነት ዜማ ነው። ግለኛነት ደግሞ፣ “ግላዊ መብት ከሁሉ ነገር የሚበልጥ፣ ግላዊ እንቅስቃሴም በኅብረት ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የሚልቅ አድርጎ የመውሰድ ዝንባሌ” ነው።1

ቤተ ክርስቲያን ለዚህ በሽታ መድኃኒትነት ቢጠበቅባትም፣ ራሷም ከዚህ ነጻ አይደለችም። ችግሩ በቤተ ክርስቲያን ውስጥም ሥር የሰደደ፣ በዕድሜ የክርስትና ታላቅ ነው፤ በጌታ ደቀ መዛሙርት መካከልም ይታይ ነበር። ከሐዋርያት መካከል ወንድማማቾቹ ያዕቆብ እና ዮሐንስ ወደ ጌታ መጥተው፣ “መምህር ሆይ፤ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንወዳለን” በማለት ንግግር የጀመሩት ለራሳቸው ክብር አስበው ነበር። ከዚያም፣ “በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝ አንዳችንም በግራ መቀመጥን ስጠን” ሲሉ ጠየቁት (ማር. 10፥35-38)። ጌታን ለመከተል የተጠሩት ደቀ መዛሙርት ውስጣቸው የተሞላው በ“እኔ” ነበርና ሌላው ቢቀር ራሳቸውን የሌሎቹ ደቀ መዛሙርት አካል አድርገው ማሰብ እንኳ ተሳናቸው። ቀሪዎቹ ደቀ መዛሙርትም ከደሙ ንጹሕ አልነበሩም። ጌታችን መከራና ሞት እንደሚጠብቀው የልቡን ሐዘንና ሸክም ሲያካፍላቸው፣ እኔነታቸው የመምህራቸውን ሐዘን ከመጋራት ገድቧቸዋል፤ ከመካከላቸው ማን ታላቅ እንደ ሆነ ለማወቅ ሙግት ላይ ነበሩና (ሉቃ. 22፥24፤ ማር. 9፥30-34)። እናታቸው ከጎናቸው ባለው ክፍል ውስጥ ለመሞት እያጣጣረች ሳለ፣ ʻከብር የተሠሩትን ዕቃዎች ማን ነው የሚወስደው?ʼ በማለት ጥል እንደሚፈጥሩ ልጆች፣ ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ በማይኖርበት ጊዜ መሪነቱን ማን እንደሚወስድ እየተከራከሩ ነበር።2 “እኔ”ን ማስቀደም ይህን ያህል ያስጨክናል። ሰው እኔነቱን ከዙፋን ካላወረደ ለአምላኩም አይበጅም።

የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን ለበረራ ክንፎቿን ስትዘረጋጋም እኔ ተኰር የሆኑ ሰዎች ገጥመዋት ነበር። ለምሳሌ፣ በሰማርያ ከተማ “እኔ ታላቅ ነኝ” በማለት ሕዝብን ያስገርም የነበረ ሲሞን የተባለ ጠንቋይ በፊልጶስ አገልግሎት ለወንጌል እጅ ሰጥቶ ነበር። ከዚያም ከፊልጶስ ጋር እያገለገለ በፊልጶስ እጅ በሚደረገው ምልክትና ተኣምራት መገረም ጀመረ (የሐዋ. 8፥9-13)። ነገር ግን ሲሞን ከታላቅነት ጥማት ልቡ አልጸዳምና ለሐዋርያቱ እጅ መንሻ በማቅረብ ጸጋቸውን እንዲያካፍሉት ሞከረ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ግን “ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ” በሚል የፍርድ ቃል ከሕይወት አሰናበተው እንጂ አልራራለትም (የሐዋ. 8፥14-24)። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዋና መሆንን እየፈለገ፣ ሐዋርያትን ግን የመስማትና የመቀበል ፍላጎት ያልነበረው የዲዮጥራጢስ ችግርም ተመሳሳይ ነበር (3ዮሐ. 9-10)። እኔነት ያለበት ሰው የአገልግሎት ጥማቱ እና ሩጫው ራሱን ለማግነን ከመፈለግ እንደሚመነጭ እነዚህ ታሪኮች ያመላክቱናል።

እኔነት ቡድናዊ መገለጫም አለው፤ ወገንተኝነትና ዘረኝነት የዚህ ነጸብራቆች ናቸው። የቀደመችው ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዐይነቱ ቍርቋሶም ትናጥ ነበር። በይሁዳ ይኖሩ የነበሩ አይሁድ ከተለያዩ የግሪክ ከተሞች የመጡ የአይሁድ መበለቶችን በእንጀራ ይበድሉ ነበር። መበለቶች ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሴቶች ናቸው። በዚያን ዘመን፣ አባወራ ሲሞት የቤተ ሰቡ ብቸኛ የገቢ ምንጭ ስለሚቋረጥ፣ በተለይም ልጅ ያልወለዱ ሚስቶች ባዶ እጃቸውን ይቀሩ ነበር፤ የዕለት ጉርስ እስከ ማጣት ይደርሳሉ። ቤተ ክርስቲያን ለእነዚህ መበለቶች እንጀራዋን ስትቈርስ ደግሞ፣ “የእኔ ብሔር፣ የእኔ ወገን፣ …” የሚሉ ጠባቦች አድልዎ ይፈጽሙ ጀመር። የጠባብነታቸው ማሳያም፣ ሁለቱም ወገኖች አይሁዳውያን ቢሆኑም በመካከላቸው ይህ መፈጠሩ ነው። ችግሩ ወዲያው መፍትሔ ባይበጅለት ኖሮ፣ ለለጋዋ ቤተ ክርስቲያን ዳፋው እጅግ ይከብድ ነበር (የሐዋ. 6፥1-6)።ወገንተኛነት የእኔነት መልክ እንዳለው ከዚህ እናስተውላለን። “እኔ፣ የእኔ ቡድን፣ የእኔ ዘር፣ …” የሚሉ ድምፆች አንድ ዐይነት ቅኝት ያላቸው ዜማዎች ናቸው፤ ትልቁን ቤተ ሰብ እንደ ሉካንዳ ሥጋ ቈራርጠው ያቀርባሉና!
የምድራችን ቤተ ክርስቲያን የምድራችን ቤተ ክርስቲያን ብዙ መልካም ነገሮች የተፈጸሙባትና እየተፈጸሙባት ያሉ ቢሆንም፣ በተሸከመቻቸው በርካታ ችግሮች ጀርባዋ ጎብጧል። ከጊዜ ወደ ጊዜም ሸክሟ እየከበደ መምጣቱ ግልጽ ቢሆንም፣ የችግሩ ጥልቀትና አሳሳቢነት ለሁሉ እየታየ አለመሆኑ ችግሩን አሳዛኝና አስፈሪ ያደርገዋል። የትስስራችን እና የአንድነታችን መላላት ምልክቶች ጎልተው እየታዩ ነው።

የአምልኮ ጉባኤ፣ አባላት ዘምረውና መባ ሰጥተው፣ ከዚያም ስብከቱ እንዳለቀ ሮጠው የሚወጡበት ሆኗል፤ የአንድ ተራ እድርን ያህል መረዳዳትና መደጋገፍ በአማኞች መካከል አይስተዋልም። ለብዙ ዓመታት የሚተዋወቁና አጠገብ ለአጠገብ ቆመው የሚዘምሩ አማኞች አንዱ የሌላውን ሸክምና ጭንቀት አያውቅም። ሰላም መባባል የአምልኮው አካል መሆኑ ተረስቷል (ሮሜ 16፥16፤ 1ቆሮ. 16፥20፤ 2ቆሮ. 13፥12፤ 1ተሰ. 5፥26፤ 1ጴጥ. 5፥14)፤ ስለዚህም በሰላምታና ትኵረት በማግኘት ብቻ የሚፈወሱ ምስኪኖች ከነሕመማቸው ይመለሳሉ። መጋብያኑም (ሁሉንም ማለት አይደለም) ከምእመኑ ርቀው አይደረሴ ሆነዋል።

በአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች መካከልም ራስን ልዩ የማድረግና የማግነን ጥማት ሰዎችን ማለቂያ በሌለው የመጠሪያ ስምና የማዕርግ ሽሚያ ውስጥ ከቷቸዋል። እኔነት ዘውድ ጭኗል። እነርሱ የሚመሯት ቤተ ክርስቲያን ትደግና ትበልጽግ እንጂ የሌላው ቤተ ክርስቲያን ውድቀት ግድ የማይሰጣቸው፣ የወንጌሉ አካሄድ የማያስሳባቸው እረኞች በዝተዋል። ማኅበረ ምእመናን ዘርን ቈጥሮ በመቧደን ይታመሳሉ። ይህ ሁሉ ትርምስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ እኔነት ሲቀድምና እኔነት ሲከተል የሚፈጠር አይቀሬ ውጤት ነው። እኔነትና ራስ ወዳድነት ከነገሠ፣ ኅብረትና ፍቅር ዋጋ ያጣል። ይህ ደግሞ ያለ ጥርጥር ኀጢአትን ይፈለፍላል። ራስ ተኰርነት ሲበዛ በአማኞች መካከል የሕይወት ዝቅጠት ይንሰራፋል። ለምሳሌ፣ ትዕቢት ʻየራሴን ፍለጋ እከተላለሁ፤ እኔ የተሻለ ዐውቃለሁ፤ እኔ ከሌላው እበልጣለሁʼ ማለት አይደለምን? ምሬትስ ʻበእኔ ላይ ያደረሱብኝን በደል ተመልከቱʼ ማለት እንጂ ምንድን ነው? ይቅር አለማለትስ ቢሆን ʻበእኔ ላይ የተፈጸመብኝን ግፍ እናንተ አታውቁትምʼ ማለት አይደለምን? ስግብግብነት፣ ስስትና አይጠግቤነትም ʻእኔ የበለጠ ማግኘት አለብኝ፤ ሂደቱ ማንንም ይጕዳ ማንንም ግድ የለኝምʼ ከማለት አይርቅም። ምቀኝነት፣ ሐሜት፣ ስድብ፣ ስም ማጥፋት፣ ጠብ፣ ክርክር፣ጦርነት … ሰልፋቸው እዚሁ ሰፈር ነው፤ ለራስ እንጂ ለኅብረት ያለ ማሰብ። እኔነት የኀጢአት ዐውራ ነው!

ግለኛነትና ብቸኛነት የቅርብ ጎረቤቶች ናቸው። ብቸኛነት ደግሞ ፉርጎው ብዙ ነው፤ የልብ ሰው እያሳጣ ሰዎችን ለሐዘንተኛነት፣ ለተስፋ ቢስነት፣ ለሆደ ባሻነት፣ … ይዳርጋል። ኅብረት ሲታጣ እነዚህ እና ሌሎችም መንፈሳዊ በሽታዎች ብቅ ብቅ ይላሉ። ግለኛነት እግዚአብሔር ካስቀመጠው መስፈርት እያጐደለ ጕዳት ያመጣል። አማኞች ከኅብረት ሲነጠሉ ለተለያዩ መንፈሳዊ ጥቃቶች ይጋለጣሉ። ለጠላት ምቹ ዒላማ ይሆናሉ። አንበሳ፣ ነብር ወይም ሌሎች አራዊት በኅብረት ከተሰባሰቡ እንስሳት ይልቅ ነጠል ብሎ የሚገኝን እንስሳ ማደን እንደሚቀልላቸው ይታወቃል። ከመንጋው የተነጠለ ታዳኝ ሲታጣም ረብሻ ፈጥረው መንጋውን ይበታትኑና በግርግሩ ምክንያት ተነጥሎ የሚወጣው እንስሳ ላይ ይረባረቡበታል። በመንፈሳዊው ዓለምም እንደዚሁ ነው። ሊውጠን ፈልጎ ዙሪያችንን የሚዞረው አንበሳ ሥራው ይኸው ነው!
ግራ ቀኛችንን ስናጤን የኅብረት መታጣት ልዩ ልዩ መንሥዔዎች ይታዩናል። አንዳንዶች በአማኞች መካከል በሚፈጠሩ አጓጉል ድርጊቶች አዝነው ራሳቸውን ከኅብረት ያገልላሉ። በደረሰባቸው ስብራት ያኮረፉም ራሳቸውን ከኅብረት ይነጥላሉ። ተገፍተው እና ተገፍትረው ከኅብረት ውጭ የሚደረጉ አማኞችም አይታጡም። እጅ ለእጅ መያያዛችን እና ልብ ለልብ መቀራረባችን መንፈሳዊ ቅስም ይሰጠናል። “ከአንድ፣ ሁለት መሆን ይሻላል፤ አንዱ ቢወድቅ፣ ባልንጀራው ደግፎ ያነሣዋል። … አንድ ሰው ብቸኛውን ቢያጠቃውም፣ ሁለት ከሆኑ ይመክቱታል” የተባለው ለጋብቻ ብቻ አይደለም (መክ. 4፥9-12፤ አ.መ.ት)። ይህን የሚያውቀው ባላጋራችን በሰበብ አስባቡ የኅብረት መውጫ በሩን ያመላክተናል። ይህን ግብዣ እንደ ጥሩ አማራጭ የተቀበለ ለጠላቱ መሣሪያ ያቀብላል። የምድራችን ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዐይነቱ ጥቃት እየተደቆሰች ይመስላል።

ኅብረት ምትክ የለውም፤ ከአማኞች መቀራረብና መያያዝ ውጭ እግዚአብሔር ሌላ አማራጭ አላዘጋጀልንም። ቤተ ክርስቲያንም ከአማኞች ኅብረት ውጭ ተራ ተቋም ናት! ስለዚህም የቤተ ክርስቲያን የቅድስና ቀለም እና ብርታት እንዲመለስ ከፈለግን፣ ስለ ኅብረት መነጋገር፣ ስለ ፍቅር መማማር፣ ለኅብረትና ለፍቅር መሥራት ይኖርብናል። ፍቅር የጐደለው፣ ለኅብረት ግድ የሌለው፣ ራሱን የሚያስቀድም ሰው እግዚአብሔርን አያውቅም፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ የኅብረትና የፍቅር ሰው ይሆናልና። ለመሆኑ ኅብረት ምናችን ነው?

የሰው ልጅና ኅብረት

ቅዱሱ መጽሐፍ እግዚአብሔር ፍቅር መሆኑን በተደጋጋሚ ይናገራል። የእግዚአብሔር ፍቅርነት የሚጀምረው ግን ሰውንም ሆነ ሌሎቹን ፍጥረታት ካስገኘ በኋላ አይደለም። እርሱ ሁሌም ፍቅር ነው! ለፍቅርነቱ ጅማሬ የለውም። የዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ሥሉስ አምላክነት ነው። አብ ወልድን ይወድዳል፣ መንፈስ ቅዱስንም ይወድዳል። ወልድ አብን ይወድዳል፣ መንፈስ ቅዱስንም ይወድዳል። መንፈስ ቅዱስ አብን ይወድዳል፣ ወልድንም ይወድዳል። ስለዚህም የክርስቲያኑ አምላክ ካልሆነ በቀር የትኛውም አምላክ ማንነቱ (ባሕርይው) ፍቅር ሊሆን አይችልም። እግዚአብሔርን ፍቅር ያሰኘው ይሄ በራሱ በእግዚአብሔር አካላት (Godhead) መካከል ያለው እውነተኛ ፍቅር ነው። ተፈቃሪ ከሌለ ፍቅር ትርጕም የለውምና። ያም ፍቅር ሲትረፈረፍ፣ ያ ሕይወት ሞልቶ ሲፈስስ ሰውን አስገኘ። እግዚአብሔር በብቸኝነት ስለ ተጠቃ ወይም አምላኪ ስላስፈለገው አይደለም ሰውን የፈጠረው፤ ይሄንን ሕይወት እና ፍቅር የሚካፈልን ፍጥረት ስለ ፈለገ እንጂ። ሰው በአርአያ ሥላሴ መፈጠሩን ቅዱሱ መጽሐፍ ይናገራል፤ እግዚአብሔር አምላክ፣ “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” በማለት ሰውን ከምድር ዐፈር አበጀው (ዘፍ. 1፥26-27)። ታዲያም ሰዎች በእግዚአብሔር መልክ የመፈጠራቸው አንዱ ማሳያ እርስ በርስ መዋደድ እና እርስ በርስ መያያዝ ያለባቸው መሆኑ ነው። ግለኛነት የእግዚአብሔር መልክ አይደለም። “እኛ” የሚል አምላክ ፈጥሮናልና፣ እኛም “እኛ” ባዮች መሆን ይጠበቅብናል። እግዚአብሔር አንድን ሰው ከመፍጠር ይልቅ ሁለት ሰዎችን የፈጠረው ለዚህ ነው።3 አንዳችን ከሌላኛችን እንድንተሳሰር፣ እንድንዘማመድ ተደርገን ነው የተፈጠርነው። ሰው ብቻውን ቢሆን መልካም አለመሆኑ የተገለጠው ኀጢአትም ሆነ ውድቀት ከመከሰታቸው በፊት ነው፤ ሁሉ መልካም በሆነበት ገነት ውስጥ። ስለዚህ ብቻነት የእግዚአብሔር ዕቅድ አይደለም። ከእኔነት ይልቅ እኛነት ተፈጥሯዊ ባሕርያችን ነው። የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሞያዎች፣ ማኅበራዊ ፍጥረት መሆናችንን በማተታቸው አልተሳሳቱም።

የኅብረት ውድቀት እና ተሓድሶ

ማኅበራዊነት የሰው ሁሉ ተፈጥሮ ቢሆንም፣ የሰው ልጅ በኀጢአት በመውደቁ ግን ይህ ኅብረት መናጋት ጀመረ። በሰው ላይ ያለው የእግዚአብሔር መልክ ተበላሸ። ባል ከሚስቱ ራሱን አስቀደመ፤ አዳም ሚስቱ የጥፋቱ መንሥኤ መሆኗን አሳብቆ ራሱን ሊያድን ሞከረ። እኔነት የሰውን ዘር በከለ። እኛነት በእኔነት ተቀደመ። ቅናትም ተንሰራፋና የአምልኮ ተቀባይነት ማግኘትና አለማግኘት እንኳ ነፍስን ለማጥፋት ሰበብ እስከ መሆን ደረሰ። እናም ዕፀ በለስ በመቀንጠስ የተጀመረው ኀጢአት ወንድም የወንድሙን ሕይወት ወደሚቀነጥስበት እርከን ለመሻገር ከአንድ ትውልድ በላይ መጓዝ እንዳላስፈለገው ቃየን እና አቤል ምስክሮቻችን ናቸው (ዘፍ. 4)።

ክርስትና ደግሞ የዕደሳ ወይም የሕዳሴ መንገድ መሆኑ ይታወቃል። በክርስቶስ የመጣው ቤዝዎት አስቀድሞ የነበረውንና የተበላሸውን የፍጥረት መልካምነት የሚያድስ ነው። ከሚታደሱት ነገሮች አንዱ ኅብረት ነው። በርግጥ ብዙ ጊዜ እንደሚስተዋለው ሰዎች ወደ ጌታ ሲመጡ፣ “እኔ”ን እያሰቡ ነው የሚመጡት። የግል ጥቅማቸውን ብቻ አስበው ጌታን “ይቀበላሉ”፤ ከዚያም በኋላ የክርስትና ጕዟቸውን የሚለኩት የግል ምቾታቸውን በማሰብ ብቻ ሆኖ ይቀራል። ወደ አገልግሎት ከሚመጡትም መካከል “እኔ”ን ማግነን የአገልግሎት መነሻቸው የሆነላቸው ሞልተዋል።

በርግጥ ለምን እንደምናዘወትረው ባይገባኝም፣ “ጌታን እንደ ግል አዳኝ” አድርጎ መቀበሉ ከዚህ ችግር ጋር ተያያዥነት ሳይኖረው አይቀርም። ፈረንጆች የነገሩንን እንደ በቀቀን እንደግማለን እንጂ “እንደ” የሚለው ቃልማ ጭራሹኑ አላስፈላጊ ነው፤ የጌታን እውነተኛ ጌትነት ወይም አዳኝነት ያልተቀበልን ያስመስላል። ሐዋርያቱ፣ “እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል?” ለጠየቃቸው፣ “በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እመን፤ አንተና ቤተ ሰዎችህም ትድናላችሁ” (የሐዋ. 16፥30-31) ሲሉ የመለሱለት ለምንድን ነው? “ጌታን እንደ ግል አዳኝህ አድርገህ ተቀበል” ለምን አላሉትም?

ጌታን ስንቀበል ወይም ጌታ ሲቀበለን በክርስቶስ አካል ውስጥ ቦታ እናገኛለን እንጂ ተነጥለን አንቆምም። “ለተቀበሉት ሁሉ ግን፣ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው” (ዮሐ. 1፥12) የሚለው ቃል እንደሚነግረን፣ የጌታ ኢየሱስን ማንነቱን፣ መልእክቱንና ሥራውን የተቀበሉ ሁሉ የአንድ አባት ልጆች ሆነዋል። በክርስቶስ ደም ተዘማምደዋል። እያንዳንዳችንን የአንድ አባት ልጆች ያደረገን ሂደት፣ እርስ በርስም ለመወናደም (ወንድም ለመደራረግ) አብቅቶናል። ከእግዚአብሔር ጋር ያስተሳሰረን ገመድ፣ ወደ ጎንም አስተሳሰሮናል። አንድ ቤተ ሰው ሆነናል። በመሆኑም “እግዚአብሔር አባቴ” የሚል ሁሉ፣ “እግዚአብሔር አባታችን” መሆኑን ለመቀበል ግድ አለበት፤ ከእግዚአብሔር ጋር ለመጣላት ካልሆነ በቀር፣ ሌሎች አማኞችን ሊወግድ መብት አይኖረውም!
ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን የአንድ አካል ብልቶች አድርጎ የሚያቀርባቸው ለዚህ ነው (1ቆሮ. 10፥17፤ 12፥12-27)። የጤናማ ሰው አካል ብልቶች በኅብረት እና በአንድነት እንደሚሠሩ ሁሉ፣ አማኞችም ይህን አሠራር መቀበል ብቻ ሳይሆን ማስቀጠልም ይኖርባቸዋል። በዚህ አካል ላይ ዐይን፣ ʻጆሮ ካልሆንኩʼ ብትል፣ ጆሮም እጅነት ቢያምራት፣ እግር፣ ʻከእጅ ጋር አብሬ አልኖርምʼ ብትል አካሉ ጤና ያጣል። ከሌሎች ብልቶች ጋር ሳልማከር በራሴ እንቀሳቀሳለሁ የሚል ብልት ሁሉ ነቀርሳ ያለበት ነውና አካሉን እንዳይመርዝ ባለቤቱ ቈርጦ ይጥለዋል። ክርስቶስ አንድ አካል እንጂ ብጥስጣሽ አካላት የሉትምና!

ስለዚህ ጌታን ለመከተል ስንወስን ወደዚህ አካል፣ ወደዚህ ቤተ ሰብ፣ ወደዚህ ኅብረት እንጨመራለን። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረን ሰዎች ሲድኑ ወደ መሢሓዊ ማኅበረ ሰብ ነው የሚጨመሩት። ዘር፣ ቀለም፣ ጾታ፣ ሀብት የልዩነት ሰበብነታቸው ያከትማል (ገላ. 3፥26-29)። ቶም ራይት የተሰኙ የአዲስ ኪዳን መምህር እንደሚናገሩት፣ “እግዚአብሔር ሲያጸድቀን ለግለኛነት ምሥረታ ፈቃድ መስጠቱ አይደለም፤ የቃል ኪዳን ማኅበረ ሰብ አባል መሆናችንን ማወጁ እንጂ።”4
አማኞች እና ኅብረት ተፈጥሯዊ ባሕርያችን የሆነው ኅብረት በተለይ በቤተ ሰባችን ውስጥ እና መንፈሳዊ ቤተ ሰብ በሆነችው በቤተ ክርስቲያን መካከል ጥልቀት ይኖረዋል።5 ሰዎች በክርስቶስ ሲያምኑ የክርስቶስ አካል ይሆናሉ፤ ከሌሎች አማኞች ጋር ቤተ ሰባዊነትን ይመሠርታሉ። እኔነታቸው እየተሻረ ይሄዳል። ስለዚህም በክርስቶስ ጸድቀናል የሚሉ ሰዎች ብቻቸውን መጓዝ አይጠበቅባቸውም። የዳኑ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት አላቸው፤ ከጌታ ጋር በመንፈስ አንድ ይሆናሉ (1ቆሮ. 6፥17)። ወደ ላይ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ያላቸው ደግሞ፣ ወደ ጎን ከሌሎችም የኪዳኑ ሕዝቦች ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው ግድ ነው።

ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ጌታ ራት ምስጢር ለቆሮንቶስ ከተማ ክርስቲያኖች ሲናገር ይህንኑ ነው የሚጠቍመው። “የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቈርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? አንድ እንጀራ ስለ ሆነ፣ እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን፤ ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና” (1ቆሮ. 10፥16- 17)። አንዱን ጽዋ እና አንዱን ሕብስት በጋራ የምንካፈለው ኅብረት ወይም አንድነት ስላለን ነው። በአንዳንድ ዘመነኞች በፈሊጥነት እንደ ተያዘው ቅዱስ ቍርባንን በግል ማዘጋጀትና መውሰድ መጽሐፍ ቅዱሳዊም ታሪካዊም መሠረት የሌለው ለዚህ ነው።

ቤተ ክርስቲያን ስትመሠረት በሰዎች መካከል እውነተኛ ኅብረት እንደ ተመሠረተ፣ “ያመኑትም ሕዝብ አንድ ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው” የሚለው ዘገባ ምስክራችን ይሆናል (የሐዋ. 4፥32)። ይህ ደግሞ ዛሬም እኛኑ የሚመለከት ነው። በፍቅር በመመላለስ እግዚአብሔርን እንድንመስል ተጠርተናል። እግዚአብሔር ዛሬም ፍቅር ነው (ኤፌ. 5፥1-2፤ አ.መ.ት)። ባሕርይው አልተለወጠም። ፍቅር የኅብረት መሠረት በመሆኑም አማኞች ሁሉ እንድንዋደድ ታዝዘናል (ዮሐ. 13፥34-35፤ ኤፌ. 4፥2)። ፍቅር ሳይኖር ስለ ኅብረት ማውራት ጉንጭ ማልፋት ነውና።

ከመዳናችን ቀጥሎ እርስ በርሳችን እንድንደጋገፍ በርካታ ተያያዥ ኀላፊነቶች ተሰጥተውናል። እርስ በርስ እግር እንድንተጣጠብ (ዮሐ. 13፥14)፣ እንድንተናነጽ (ሮሜ 14፥19)፣ እንድንቀባበል (ሮሜ 15፥7)፣ እንድንገሣሠጽ (ሮሜ 15፥14)፣ ሰላምታ እንድንሰጣጥ (ሮሜ 16፥16)፣ እንድንተሳሰብ (1ቆሮ. 12፥25) አንዱ ሌላውን በፍቅር እንዲያገለግል (ገላ. 5፥13 – አ.መ.ት)፣ አንዱ የሌላውን ሸክም እንዲሸከም (ገላ. 6፥2)፣ ይቅር እንድንባባል (ኤፌ. 4፥32)፣ በጥበብ እንድንማማር (ቈላ. 3፥16 – አ.መ.ት)፣ እርስ በርስ እንድንጽናና (1ተሰ. 4፥18)፣ እንድንመካከር (ዕብ. 3፥13)፣ ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንድንነቃቃ (ዕብ. 10፥24 – አ.መ.ት)፣ አንዳችን ለሌላኛችን ኀጢአታችንን እንድንናዘዝ (ያዕ. 5፥16)፣ እንድንጸላለይ (ያዕ. 5፥16)፣ በእንግድነት እንድንቀባበል (1ጴጥ. 4፥9)፣ መከባበርና ትሕትናን እንድንላበስ (1ጴጥ. 5፥5 – አ.መ.ት)…።

ኅብረት/አንድነት በክርስቶስ ደም የተመረቀው አዲሱ ኪዳን የሚጥልብን ኀላፊነት ነው። ስለዚህም የአዲሱን ኪዳን ቃል ፈጸምን የሚባለው ሁላችንንም የሚመለከቱ እነዚህን የጋራ ኀላፊነቶች ስንወጣ ብቻ ነው።6 እነዚሁ ሁሉ ትእዛዛት የተሰጡን የቤተ ሰባዊነት ምልክት በመሆናቸው ነው። የምልጃ ጸሎት ዋና ምሰሶም ቤተ ሰባዊነት ነው። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን “የሐዋርያት ጸሎት” በሚል የምናውቀው ጌታ ያስተማረው ጸሎት ነው። ይህ ጸሎት ኅብረትን ከግምት ያስገባ ነው። ጸሎቱ ሲጀምር “አባታችን [የእኛ አባት] ሆይ” በማለት መጀመሩ ይህን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፤ የምንጸልየው “ለእኛ” እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም። እያንዳንዱ ጥያቄም፣ ብዙ ጊዜ ትኵረት የማንሰጠውን “እኛ” የሚል ቃል አዝሏል፤ የዕለት እንጀራዬን ሳይሆን የዕለት እንጀራችንን፣ በደሌን ሳይሆን በደላችንን፣ ወደ ፈተና አታግባኝ ሳይሆን አታግባን፣ ከክፉ አድነኝ ሳይሆን አድነን። እነዚህ ሁሉ ቤተ ሰባዊነትን ያሳያሉ።

ሮናልድ ደን ስለዚህ ጕዳይ ሲያስተምሩ፣ “አንዱ ልጅ ሲጸልይ መላው ቤተ ሰብ እንደሚጸልይ ይታሰባል” ይሉና “ይህ ራስ ወዳድነት የሌለበት ምልጃነው።የቤተሰቡአባልስለራሱብቻ አይደለም የሚጸልየው፤ ስለ እያንዳንዱ የቤተ ሰብ አባልም እንጂ። ለራሱ የሚፈልገውን ለመላው ቤተ ሰብም ይፈልጋል። እንደ አንድ የእግዚአብሔር ቤተ ሰብ አባል፣ አንድነቱ እንደ ተዋቀረበት አካል፣ እያንዳንዱ አባል እንዲኖረው የማልፈልገውን ነገር ለራሴ የመጠየቅ መብት የለኝም። በመጨረሻ ጸሎቱ ምንም ዐይነት ቢሆን፣ ከሌሎች ቀድሜ እንድደራጅ፣ ከሌሎች የሚበልጥ ይዞታ እንዲኖረኝ፣ በአብ ፊት ከሌሎች የተሻለ ቅርበት እንድይዝ፣ ቤተ ክርስቲያኔ እዚያ ማዶ ካለችው ቤተ ክርስቲያን ይበልጥ እንድታድግና እንድትበለጽግ ማድረጊያ መንገድ አይደለም።”7 ሲሉ ይመክራሉ።

ኮይኖንያ

ይህ ክርስቲያናዊ ኅብረት አዲስ ኪዳን ውስጥ ኮይኖንያ (Koinonia) በሚል የግሪክ ቃል ተጠቅሷል፤ ይህም በብዙ ትርጕሞች ውስጥ ኅብረት ተብሎ ነው የቀረበው። ኮይኖንያ የሚለው ስም ኮይኖስ (Koinos) – “የጋራ” ከሚለው ቅጽል የተገኘ ነው። የኮይኖንያ ቃል በቃል ሲተረጐም፣ “አንድን ነገር በጋራ መያዝ” የሚል ትርጒም ይሰጣል። ሁለት ወይም ከሁለት የሚበልጡ ሰዎች የጋራ ነገር ሲኖራቸው፣ ኮይኖንያ አላቸው ማለት ነው። ምንም የማይጋሩባቸው ጒዳዮች ካሉ ደግሞ በእነዚህ ጒዳዮች ኮይኖንያ የላቸውም ማለት ነው። በቀደመችዋ ቤተ ክርስቲያን “ማንም ሰው ‘ይህ የእኔ ነው’ የሚለው ነገር አልነበረውም፤ በመካከላቸውም ሁሉ ነገር የጋራ ነበር” (የሐዋ. 4፥32 – የ1997 ትርጒም)። ይህ ኮይኖንያ ነው።8 ለኮይኖንያ ፍጹም ምሳሌ የሚሆነን በአብ እና በወልድ መካከል ያለው ግንኙነት ነው። በዮሐንስ 10፥30 ላይ ጌታ ኢየሱስ፣ “እኔና አብ አንድ ነን” ብሎ ተናግሯል። ይህ በአብና በወልድ መካከል ያለው ኅብረት የኮይኖንያቸው መሠረት ነው። የኮይኖንያ ውጤትም ኢየሱስ በዮሐንስ 16፥14-15 ላይ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሲናገር፣ “ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል” ያለው ነው። ወዲያውኑ ቀጠል አድርጐም፣ “ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው” ይላል። በሌላ አነጋገር ጌታ ኢየሱስ ʻእኔ ያለኝ ነገር በሙሉ በራሴ ያገኘሁት ሳይሆን ከአብ ጋር ባለኝ ኅብረት ያገኘሁት ነውʼ ማለቱ ነው። በዮሐንስ 17፥10 ላይም ጌታ ኢየሱስ ወደ አባቱ ሲጸልይ፣ “የእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ የአንተውም የእኔ ነው …” በማለት ይህንኑ በይበልጥ ያረጋግጥልናል።ይህ በሥሉስ አምላክ አካላት ውስጥ ያለው ፍቅር ደግሞ አማኞች እንዲኖራቸው የታሰበው ዐይነት አንድነት ወይም ኅብረት መሆኑን ጌታ ኢየሱስ ባደረገው ጸሎት ውስጥ ተገልጿል። ጌታችን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የጌታ እራትን ከበላ በኋላ፣ “ቅዱስ አባት ሆይ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው፤ … አንተ አባት ሆይ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፣ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ። እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ … በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ …” ሲል ጸልዮአል (ዮሐ. 17፥11፤ 21-23)። ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በጴንጠቆስጤ ቀን ነው፤ መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ላይ በወረደ ቀን። ይህ ቅዱስ መንፈስ በየግላቸው በቆሙ አማኞች ላይ ሳይሆን፣ በአንድነት በሚጸልዩ አማኞች ላይ በአንድነት መውረዱ የኅብረትን ፋይዳ ይነግረናል።10 መንፈስ ቅዱስ ተነጣጥለው የሚሮጡ ግለኛ አማኞችን ሳይሆን፣ ተያይዘው የክርስቶስ አካል የሚሆኑ ብልቶችን ነው የሚያበጀው።

እግዚአብሔር ሁላችንንም የጠራን የልጁን መልክ እንድንመስል መሆኑ በቅዱሱ መጽሐፍ ተደጋግሞ የተገለጠ እውነት ነው (ሮሜ 8፥29፤ 1ቆሮ. 15፥49፤ ቈላ. 3፥10፤ 1ዮሐ. 3፥2)። የእርሱ መልክ ደግሞ ፍቅርን፣ ትሕትናን፣ አንዱ ለሌላው መኖርን፣ ወዘተ. ያካትታል። የመንፈስ ፍሬዎች ልንላቸውም እንችላለን። እነዚህ ደግሞ ኅብረትን የግድ ይላሉ።

ሰዎች ከሰዎች ጋር ኅብረት ከሌላቸው ግን ፍቅርን እንዴት ነው የሚገልጡት? የሚወደድ በሌለበት ፍቅር አይኖርምና! ከሰዎች ተነጥለው በዋሻ የሚኖሩና እግዚአብሔር ወደሚፈልገው መንፈሳዊ ብቃት ለመድረስ የሚያልሙ ሃይማኖተኞች ወይም በሰዎች መካከል እየኖሩ ግለኝነትና ራስ ተኰርነት የተጠናወታቸው ሰዎች ፍቅርን ሊያፈሩ አይችሉም። ከምእመኖቻቸው የራቁና የሚደበቁ መጋብያንም ፍቅርን አያውቁትም። ፍቅር የግለኛነት ዝማሬ አይደለም።
ትሕትናም ሌሎች ሰዎች በሌሉበት ወይም ለሌሎች የሚሆን ቦታ በሌላቸው ሰዎች ዘንድ የሚገለጥ ትሩፋት አይደለም። የሚታዘዙት እና ዝቅ የሚሉለት ሰው በሌለበት እንዴት ትሑት ይኮናል? መከባበርም ኅብረትን ይሻል። ግለኛነት በመንፈስ ፍሬ እጦት ክፉኛ የመራቆት ሕይወት ነው። ስለዚህም አይደረሴና አይነኬ አገልጋዮች ክርስቶስን የማይመስሉና የደረቁ ዛፎች ናቸው። ግለኛ ሰው መንፈሳዊ አይደለም። ከግለኛነቱ ካልተላቀቀም የመንፈሳዊነት ተስፋ የለውም።
ክርስትና እግዚአብሔር ፍቅር መሆኑን ማወጅን ብቻ ሳይሆን፣ በፍቅርና በኅብረት መኖርንም ግድ ያደርገዋል። ሆኖም መንገዱን የሚያሰናክሉ ጋሬጣዎች አይታጡም። ከእነዚህም መካከል አንድ ዐይነትነትን መፈለግ፣ ራስን መውደድ፣የጥገኛነት ሥጋት፣ የግለ ሰቦች ቲፎዞነት፣ አንድነትን ከተቋማዊ አንድነት ጋር ማምታታት ይገኙበታል። እነርሱን ከዚህ ቀጥለን እናያቸዋለን።

አንድ ዐይነትነትን መፈለግ

አንድነት አንድ ዐይነትነት እንዳልሆነ በብዙ ይታወቃል፤ ከፍጥረት መጀመሪያም እንደዚሁ ነበር። “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” ተብሏልና (ዘፍ. 1፥26)። እግዚአብሔር አዳምና ሔዋን በትዳር ጥምረት እና አንድ ሥጋ በመሆን የምድርን ቤተ ሰብ፣ ማኅበረ ሰብ፣ ኅብረተ ሰብ እንዲያስገኙ ቢፈልግም፣ አንድ ዐይነት አድርጎ አልቀረጻቸውም። የአዳም ጕድለት በሔዋን፣ የሔዋን ጕድለት በአዳም ይሟላል። አዳምና ሔዋን የሚሳሳቡት (የሚፋቀሩት) አንድ ዐይነት ስለሆኑ አልነበረም። አዳምን የሔዋን ሴትነት ወደ እርሷ ሲስበው፣ ሔዋንን ደግሞ የእርሱ ወንድነት ይስባታል። እግዚአብሔር በዚህ ድርጊቱ አንድነት ከአንድ ዐይነትነት እንደማይመነጭ አስተምሯል። ይህ የክርስቲያናዊ ትዳር ዐምድ ሲሆን፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ትዳር ደግሞ የክርስቶስና የአካሉን ግንኙነት ተምሳሌትነቱ ይታወቃል (ኤፌ. 5፥32)። አንዳችንም ፍጹማን አይደለንምና አንድ ዐይነት ብንሆን ኖሮ የአንዳችን ጕድለት በማን ነበር የሚሞላው?

ስለዚህም አንድ አካል እና አንድ ቤተ ሰብ ለመሆን አንድ ዐይነትነት አይጠበቅብንም። ሲ.ኤስ.ሌዊስ “Mere Christianity” በተሰኘ መጽሐፉ ይህንን በጥሩ ምሳሌ ይገልጸዋል። ስድስት ሽልንጎችን በአንድነት ወስደን ብናያቸው አንድ ዐይነት ናቸው፤ አንዳችም ልዩነት አናገኝባቸውም። አንድነት ግን የላቸውም። የአንድ ሰው አፍንጫ እና ሳንባ ግን አይመሳሰሉም፤ ነገር ግን የአንድ ሰው አካል ብልቶች ናቸውና አንድነት አላቸው።11 የአማኞች አንድነትም ይህን ይመስላል። ቅዱስ ጳውሎስ እንኳ የሚያገለግላቸውን ሰዎች “እኔን ምሰሉ” ያላቸው፣ እግዚአብሔርን የሚመስልባቸውን ጕዳዮች ከዘረዘረ በኋላ ብቻ ነው። በሌላ አገላለጽ፣ ክርስቶስን ምሰሉ ማለቱ ነው (1ቆሮ. 10፥32 – 11፥1)። ጳውሎስ ክርስቶስን በማይመስልባቸው ጕዳዮች በወቅቱ የነበሩ ምእመናንም ሆኑ እኛ እርሱን መምሰል አይኖርብንም። እኛኑ መሳይ ምእመናንን ለማፍራት የምናደርገው ጥረት ይህን ከግንዛቤ መውሰድ አለበት።

ሰዎች ሁሉ የመልካችንን ያህል ማንነታዊ እና ሥነ ልቡናዊ ልዩነቶች አሉን። ከአንድ አባትና እናት በተወለዱ ልጆች መካከልም ልዩነቱ አለ፤ ይህም የሳምንታት ዕድሜ ባላቸው ሕፃናት ላይ እንኳ ሊስተዋል ይችላል። ስለዚህ የሰዎችን ማንነታዊ ባሕርይ (Personality) ለመለወጥ መጣር መልክን ለመለወጥ እንደ መጣር ነው። ክርስቲያን ወደ መሆን ስንመጣ፣ ገጽታችንን ወይም መልካችንን ልንለውጥ እንደማያስፈልገን ሁሉ፣ ማንነታዊ ባሕርያችንም እንዲለወጥ አያስፈልግም። እውነተኛ ማንነት በሌለበት እውነተኛ ኅብረት አይኖርም። የሚታየውም ሆነ የማይታየው መልካችን ከእግዚአብሔር የተቀበልናቸው ቀለሞቻችን ናቸውና አንድ ዐይነት ለመሆን የምናደርገው ጥረት አንድነታችንን ያጠፋዋል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ከጳውሎስ ጋር፣ ጳውሎስ ከጢሞቴዎስ ጋር፣ ዮሐንስ ከጴጥሮስ ጋር አንድ ዐይነት ማንነት እንዳልነበራቸው መጽሐፍ ቅዱስን ያነበበ ሁሉ የሚገነዘበው ነው። ገጣሚውም፣“አንድ ዐይነት ለመሆን ስንለፋ፣ አንድነታችን ጠፋ።” ይለናል።12

ራስን መውደድ

በዚህ ዘመን ራስን ስለ መውደድ አግባብነት ከቤተ ክርስቲያን ምስባክ ጭምር ይደመጣል። ራስን ወውደድ በጥሩ ምግባርነት ይሞካሻል። ብዙውን ጊዜም፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው ትእዛዝ ለዚህ መሠረት ተደርጓል። እውነቱ ግን ከዚህ ይርቃል። በርግጥ ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ በብሉዩም ሆነ በአዲሱ ኪዳን ውስጥ የቀረበ ትእዛዝ ነው (ዘሌ. 19፥18፤ ማቴ. 19፥19፤ ሉቃ. 10፥27፤ ገላ. 5፥14)። ሐሳቡ ግን ራስን መውደድን የሚያጸድቅ እንዳልሆነ ጆን ስቶት ሦስት ነጥቦችን በማንሣት ያስተምራሉ።አንደኛ፣ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የተባለው፣ “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” የሚለውን ወርቃማ ትእዛዝ በአስረጅነት ነው (ማቴ. 7፥12፤ ሉቃ. 6፥31)። ሁላችንም ራሳችንን መውደዳችን የማይታበል ነው። መጽሐፉም፣ “ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል” ካለ በኋላ፣ “ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና” ይለናል። ስለዚህም፣ “የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል” (ኤፌ. 5፥28-29)። ሰዎች በምን መልኩ ቢያከብሩን፣ ቢጠነቀቁልን፣ ቢወድዱን፣ ቢንከባከቡን ተገቢ እንደሚሆን እናውቃለን፤ ይህ ደግሞ ሌሎች ሰዎችን እንዴት መንከባከብ፣ መውደድና ማክብር እንዳለብን ማሳያ ይሆነናል። ስለዚህም ራስን መውደድ ልንከተለውና ልንደርስበት የተገባ ትሩፋት አይደለም። ሌላውን ምን ያህል መውደድ እንዳለብን ለማሳየት የገባ መስፈርት ነው።

ሁለተኛ፣ በዚሁ ቦታ ጥቅም ላይ የዋለው “አጋፔ” የሚለው የግሪክ ቃል፣ “ሌሎችን ለማገልገል ራስን መሥዋዕት ማድረግ” የሚል ትርጓሜ ነው ያለው። ስለዚህ ራስ ተኰር ሊሆን አይችልም። ራስን ለማገልገል ራስን መሥዋዕት ማድረግ ስሜት የማይሰጥ ነገር ነው። ስለዚህ ጥቅሱ ራስን ስለ መውደድና ራስን ስለ ማገልገል ተገቢነት አይናገርም።

ሦስተኛ፣ ራስን መውደድ መጽሐፍ ቅዱስ ኀጢአትን ለማመልከት የሚጠቀምበት ማስረጃ ነው። በሉተር አገላለጽ፣ ኀጢአት ራስን ራስ ውስጥ መጠቅለል ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ ተነበየው ከሆነ፣ ከመጨረሻው ዘመን ምልክቶች አንዱ ሰዎች ራሳቸውን የሚወድዱ መሆናቸው ነው። ሰዎች እግዚአብሔርን እና ባልንጀራቸውን ከሚወድዱበት ፍቅር ቀንሰው ራስ ወዳድ ይሆናሉ (1ጢሞ. 3፥2-4)። ስለዚህ ራስን መውደድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማበረታቻ የለውም።የራስ ወዳድነት ማርከሻው ጌታን መምሰል ነው። ሰው የሆነው አምላክ በጌቴሴማኒ ያደረገው ጸሎት ከራሱ ፍላጎት ይልቅ የአባቱን ፈቃድ ያስቀደመበት መሆኑ ለዚህ ትልቅ መልእክት አለው (ማቴ. 26፥39)።

የጥገኛነት ሥጋት

ሁላችንም ወደዚህ ዓለም ስንመጣ በሌሎች ላይ ጥገኛ ሆነን ነው። ሲርበን በሚመግቡን፣ ሽንት ጨርቃችንን በሚቀይሩንልን፣ ስንንከባለል ወደ ቦታችን በሚመልሱን፣ ሲበርደን በሚያሞቁን ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ላይ ጥገኛ ነበርን። ጌታችንም ሰው ሆኖ ሲመጣ በጥገኛነት ዐልፏል። መስቀሉ ላይ ሳለም ጥገኛ ነበር፤ የሚጠጣውን ነገር ወደ አፉ የሚያስጠጉለት እንኳ ያስፈልጉት ነበር። ስለዚህም ዕውቁ ወንጌላዊ ጆን ስቶት እንደሚናገሩት፣ “ክርስቶስ ራሱ በሌላው ላይ ሸክም የመሆንን ክብር ተካፍሏል። በዚህ ግን በጭራሽ የመለኮትነት ከበሬታውን አላጣም። በሌሎች ላይ ተደጋፊ መሆን ሰዎችን የማንነት ክብራቸውን እና እውነተኛ ዋጋቸውን እንደማያሳጣቸው እኛም በክርስቶስ ተምረናል። ለመላ ዓለሙ አምላክ ጥገኝነት ተገቢ ከሆነ፣ በርግጥ ለእኛም ነው።”14 ጆን ስቶት እንደሚገልጹት፣ የሌላውን ድጋፍ መሻት እኩይ ነገር አይደለም። እግዚአብሔር ያበጀን በዚሁ መልክ ነውና። አስቀድመንም እንዳልነው፣ ሁላችንም ወደዚህ ምድር የመጣነው በሌሎች ፍቅር፣ እንክብካቤ እና ጥበቃ ላይ በጥገኛነት ነው። ከዚያ ደግሞ ሌሎች በእኛ ላይ ጥገኛ ወደሚሆኑበት የሕይወት እርከን ልንመጣ እንችላለን፤ ምናልባት ይህ አስቀድመን ጥገኛ የሆንንባቸውን ወላጆቻችንን ሊጨምር ይችላል። አብዛኞቻችንም ይህችን ዓለም ለቅቀን የምንወጣው በሌሎች ፍቅር እና እንክብካቤ ላይ ጥገኛ ሆነን ነው። ሆኖም በሌላው ላይ ሸክም ወይም ጥገኛ ከመሆን፣ የሌላውን ሰው ድጋፍ ከመሻት፣ ሞት የሚመርጡ ሰዎች ይኖሩ ይሆናል። ይህ ግን ስሕተት ነው።

ከመጀመሪያውኑ እግዚአብሔር ያበጀን በሌላው ሰው ላይ እንድንደገፍ አድርጎ ነው፤ ለሌሎች ሸክም እንድንሆን ነው። የቤተ ሰብ ሕይወት፣ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ሰብ የዚህ ዐይነቱ “እርሰ በርስ መሸካከም” መገለጫ መሆን አለበት። መጽሐፍ እንደሚል፣ “አንዱ የሌላውን ከባድ ሸክም ይሸከም፤ በዚህ ሁኔታም የክርስቶስን ሕግ ትፈጽማላችሁ” (ገላ. 6፥2 – አ.መ.ት)።15 ከዚህ ውጭ ያለው ትዕቢት ነው።

የግለ ሰቦች ቲፎዞነት

እግዚአብሔር ሰዎችን ከጨለማው ግዛት እየታደገ በሕይወት የሚያኖረው፣ ሕያዋን እርስ በርስ ሲገጣጠሙ የሚያስገኙት አዲስ አካል በመኖሩ ነው። ቤተ ክርስቲያን የምትገነባው ከሕያዋን ድንጋዮች ወይም ጡቦች ነው (1ጴጥ. 2፥5፤ ኤፌ. 2፥20-21)። ጡቦች ወይም ብሎኬቶች ለየብቻቸው ቢቆሙ ሕንጻ አይኖርም። ለዚህ ሥራ ደግሞ እግዚአብሔር የተለያዩ ሠራተኞችን ሰጥቷል። እዚህ ጋ መስተዋል ያለበት ነገር ቢኖር ሠራተኞቹ ለቤተ ክርስቲያን የተሰጡ እንጂ፣ ቤተ ክርስቲያን ለሠራተኞቹ የተሰጠች አለመሆኗን ነው። ቤተ ክርስቲያን ባለቤት አላት፤ እርሱም ክርስቶስ ነው። በተለያዩ ወቅቶች ግን ይህን የማያስተውሉ መሪዎች እና ምእመናን ብቅ ይሉና ብዙ ጥፋት ያስከትላሉ።ለዚህ በናሙናነት የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያንን መውሰድ እንችላለን። ከቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች መካከል በንግግር ጥበብ የተካኑ እና ጎልተው የሚታዩ ሌሎች ክኅሎቶች የነበሯቸው ነበሩ። ይህም ያልበሰሉቱን ምእመናን ከሚያደንቁት አገልጋይ ጀርባ እየተሰለፉ፣ “እኔ የጳውሎስ ነኝ”፣ “እኔ ደግሞ የአጵሎስ ነኝ”፣ “የለም፤ እኔ የኬፋ ነኝ” እንዲሉ አደረጋቸው (1ቆሮ. 1፥11- 13፤ 3፥1-4)። ማንኛቸውም በእነዚህ አገልጋዮች ስም አልዳኑም፤ በእነርሱም ስም አልተጠመቁም። የዳኑትም ሆነ የተጠመቁት በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። ታዲያ ክርስቶስ ተከፍሏልን? ይህ የሐዋርያው ጳውሎስ ጥያቄ ነበር (1ቆሮ. 1፥13)። ሰዎቹ ድርጊታቸው ሕንጻውን እንደሚንድ እና የሕንጻው ባለቤትም በቸልታ እንደማያልፋቸው አላስተዋሉም። ይህ እኛንም ይመለከታል። ቅዱስ ጳውሎስ በመጀመሪያዪቱ የቆሮንቶስ መልእክት በምዕራፍ ሦስት እንደሚያስረዳው ከሆነ፣ አገልጋዮች እንደየ ጥሪአቸው የእግዚአብሔርን ዕርሻ የሚኮተኩቱ፣ ውሃ የሚያጠጡ፣ አረም የሚነቅሉ ናቸው እንጂ፣ ተክሎቹን የሚያሳድጋቸው የዕርሻው ባለቤት ነው። አገልጋዮቹ እግዚአብሔር ለሚያስገነባው ሕንጻ መሠረት የሚጥሉ፣ ግድግዳ የሚያቆሙ፣ ጣራ የሚገጥሙ፣ ቀለም የሚቀቡ የቀን ሠራተኞች ናቸው እንጂ፣ የሕንጻው ባለቤት እግዚአብሔር ነው። ሠራተኞቹ ዐላማቸው ወይም ግባቸው አንድ በመሆኑ ለየጎጣቸው መሥራት የለባቸውም፤ አሊያ ሕንጻው ሕንጻ አይሆንም። ሠራተኞቹ ይህን የሚያደርጉት ግን በብላሽ አይደለም። ደሞዝ አላቸው። ደሞዛቸውን የሚያገኙት ግን የቤተ መቅደሱ ግንባታ ተያይዞ እንዲቀላጠፍ የሚያደርጉት ጥረት ተመዝኖ ነው። እግዚአብሔር በሚመጣው ዓለም ለአገልጋዮቹ የሚከፍለው ዛሬ ለኅብረት ባደረጉት አስተዋጽኦ ነው። ለሕንጻው ተገጣጥሞ መቆም ሠራተኞቹ ምን ያደርጉ እንደ ነበር የእያንዳንዳቸው ሥራ የሚገለጥበት ቀን ይመጣል። ለሕንጻው አንድነት የሠሩ በወርቅ፣ በብርና በከበረ ድንጋይ እንደ ገነቡ ይቈጠርላቸዋል። ከሕንጻው አንድነት ይልቅ የየራሳቸውን ጎጥ ሲያስቀድሙ የነበሩቱ ደግሞ አይረቤ እና ምናምንቴ ቁሳቁሶችን ሲጠቀሙ የኖሩ ናቸው። ትኵረታቸውን በራሳቸውና በቡድናቸው ላይ ያደረጉ አገልጋዮች ልፋታቸው መና ይቀራል፤ የሠሩትም ይቃጠላል። የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሰዋልና ቅጣት አይቀርላቸውም።

“ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር ያፈርሰዋል” ተብሏልና (1ቆሮ. 3፥16-17)። ብዙዎች እንደሚያስቡት፣ ቅጣቱ የራሱን አካል (ሥጋ) በአግባቡ የማይንከባከብን ሰው እንደሚመለከት አድርጎ መውሰድ የምዕራፉን ጠቅላላ ሐሳብ መሳት ነው፤ ምክንያቱም በዚህ ዐውድ መሠረት፣ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የምንሆነው በጋራ እንጂ በነፍስ ወከፍ አይደለም። የምዕራፉ ጭብጥ ኅብረት ነው። ኅብረት ከሌለ መቅደስነት የለም። የእግዚአብሔርን ኅብረት የሚያፈርሱትን እግዚአብሔር ራሱ ያፈርሳቸዋል።16 ከአማኞች ኅብረት በተቃራኒ ሠርቶ ያለ ቅጣት ማምለጥ የማይቻል ነው። እግዚአብሔር የመሠረተውንና የሚሳሳለትን ኅብረትን ያህል ነገር ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የሚንዱ ጨካኞች በራሳቸው ላይ ፍርድን ያከማቻሉ።

አንድነትን ከተቋማዊ አንድነት ጋር ማምታታት የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የመንፈስ አንድነትና ተቋማዊ አንድነትን የሚምታቱባቸው ይመስላል። ይህም በሁለት ጽንፎች ሲገለጥ ይስተዋላል። አንደኛው ጽንፍ፣ ተቋማዊ አንድነት ከሌለ ጭራሹኑ አንድነት እንደ ሌለ መቍጠር ነው። ለምሳሌ፣ የቤተ ክርስቲያናቸው አባል የሌላኛዪቱን ቤተ ክርስቲያን አባል እንዳያገባ በድፍረት የሚያከላክሉ መጋብያን ብቅ ብቅ ብለዋል። አንዱ ተቋም የሌላኛውን ፍላጎት (ቤተ ክርስቲያንንም ይጨምራል) ያጣጥላል። ከአንደኛዋ ቤተ ክርስቲያን በኀጢአቱ የተገሠጸ ወይም እርምጃ የተወሰደበት አገልጋይ በሌላኛዪቱ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት አንዳችም ችግር አይገጥመውም። ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት የአንድ ቤተ እምነት አጥቢያዎች ካልሆኑ፣ የእርምት ውሳኔው በሌላኛዪቱ ዘንድ ተፈጻሚነት አይኖረውም።

ዛሬ ዛሬ የእግዚአብሔርን ገንዘብ እያባከኑ፣ በአመንዝራነት የብዙዎችን ሕይወት እየበከሉ፣ ጋብቻን እና ፍችን እያደራረቡ የሚዞሩ ሰዎች ሃይ ባይ ያጡት ለዚህ ነው። ይህ ደግሞ አብያተ ክርስቲያናት ኀጢአትን እንዳይገሥጹ ዐቅም እያሳጣቸው ሲሆን፣ ለእውነት የሚቆሙ ሰዎችንም ቅስም ይሰብራል። በመጨረሻም ትብብርን በማዳከም እና መበቃቀልን በመውለድ የክርስቶስን ወንጌል ያዳፍናል። የዚህ ሁሉ ምንጭ ደግሞ ተቋማዊ አንድነት ከሌለ አንድነት እንደ ሌለ ማሰብ ነው። በሌላኛው ጽንፍ ደግሞ፣ ተቋማዊ አንድነት ለአንድነት መኖር በምትክነት ይወሰዳል። ተቋማዊ አንድነትን ለማምጣት መሥራትም አንድነትን ለማምጣት እንደ መሥራት ይታያል። ከመንግሥት ለውጡ ወዲህ በትልልቅ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ውስጣዊ ችግሮች ገንፍለው ፍርድ ቤት መሯሯጥ መበራከቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ከእነዚያ መካከል ብዙዎቹ በሕግ ጡንቻና በሽምግልና ጥረት ተቋማዊ አንድነታቸው ተመልሷል። የችግሩን አስኳል ግን አንዳንዶቹ አለባብሰው ዐልፈውታል። ከእነዚሁ መካከል ቀድሞውኑም የጠቡ መንሥዔ በነበረው በዚያው የዘር ችግር ውስጣቸው የሚታመስና ለመፈንዳት ጊዜውን የሚጠብቅ ፈንጅ የተቀበረባቸው አብያተ ክርስቲያናት አሉ። መሪዎቹ በተቋማዊ አንድነታቸው ደስታ ተውጠው ከበሮ ከመደለቅ ይልቅ፣ የእውነተኛ አንድነታቸው ጠር ለሆኑት ጕዳዮች እውነተኛ መፍትሔ ለማበጀት መትጋት ነበረባቸው።

የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረትንም በተጨማሪ ማስረጃነት ማጤን ይቻላል። የትኛውም ማኅበር አባላቱ ከሉዐላዊነታቸው ላይ ሸርፈው እንዲሰጡት እስከ መጠየቅ ይደርሳል። አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ግን ይህ እንኳ ቢቀር ከጥቅማቸው ወይም ከክብራቸው ላይ ጥቂቱን ከማጋራት ኅብረቱን ትቶ መውጣትን ይመርጣሉ። ስለዚህም የአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ከዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላም የጕልምስና ዐቅም የለውም። ቀድሞውኑም የራስን ጥቅም ብቻ እያሰቡ ማኅበር መቀመጥ ፋይዳ አልነበረውም። ከኅብረቱ አባላት መካከል አንዳቸው የሌላኛቸውን ፈቃድና ፍላጎት ከቁም ነገር የሚወስዱም አይመስሉም፤ አብረው ስብሰባ ቢያካሂዱና ጽዋ ቢጠጡም፣ በጋራ የወሰኑትን ውሳኔ በተናጠል ለማፍረስ የሚሠሩ አሉ።
ተቋማት አስፈላጊ ናቸው፤ ተቋማዊ አንድነትም እንዲሁ። አንድነታችን ግን በፍቅር ላይ እንጂ፣ በተቋም አንድነት ላይ አልተመሠረተም። እማሆይ ቴሬሳ እንዳሉት፣ ተቋማት አስደናቂ ሥራ ቢኖራቸውም፣ ክርስቲያናዊ ፍቅርን መግለጥ የተቋማት ሳይሆን የሰዎች ኀላፊነት ነው።17 ስለዚህም፣ አንድነታችን ከተቋማዊነት ጋር በጭራሽ አንድ አይደለም። ጌታ ኢየሱስም አንድ እንድንሆን ሲጸልይልን ተቋማዊነትን አስቦ አይደለም (ዮሐ. 17፥11)። ጌታ የተናገረው አንድነት እኛ የምንፈጥረው አንድነትም አይደለም፤ በክርስቶስ ስናምን ወዲያውኑ የተፈጠረ ነው። የጌታም ጸሎት አንድነት እንዲፈጠር ሳይሆን፣ በአንድነታችን እንድንቀጥል የሚያትት ነው።18 ተቋማዊ አንድነት ኖረም አልኖረ፣ የመንፈስ አንድነቱ አለ። ሁለቱን ማምታታት ከቀጠልን ግን የመንፈስ አንድነታችን አደጋ ውስጥ ይወድቃል።

በመጨረሻ

ግለኛነት፣ ሰው ታማኝነቱና አገልጋይነቱ ለራሱ ብቻ እንዲሆን ያስተምራል፤ ደስታም የሚገኘው ለራስ በመኖር መሆኑን ይሰብካል። ዛሬ ዛሬ የተለያዩ መገናኛ ብዙኀንና ራስ ተኰር መጽሐፎችም ይህንኑ ነው የሚያራግቡት። ስለዚህም የትኛውም ነገር ለራሳችንና ለቡድናችን ጥሩ ከሆነ፣ ለሌሎች ጥሩ ቢሆንም ባይሆንም ግድ ወደ ማጣት ደርሰናል። ለእኛ የተመቸ፣ ለሌላውም እንደሚመች እናስባለን። የልከኝነትና የትክክለኝነት መለኪያው እኛ ሆነናል። ከየባለሞያው የሚደመጠው ምክር፣ “ልብህን ስማው”፣ “ልብሽ የሚልሽን አድርጊ”፣ “ልባችሁን ተከተሉ” የሚል ብቻ ሆኗል፤ ጌታ ግን “ተከተለኝ፣ ተከተዪኝ፤ ተከተሉኝ” ነበር ያለው። ዘመነኛው ወንጌልም ግለ ሰብ እና ግለ ሰቡ የሚያገኛቸው በረከቶች ላይ ያተኵራል። በእምነት ስም ራስ ተኰርነትና ራስ ወዳድነት ይበረታታል። አማኞች ኢየሱስን የሚከተሉት ለሥጋቸው ፈውስ፣ ለገንዘባቸው በረከት፣ ለሥራቸው ስኬት፣ ለራሳቸው ሞገስ፣ ደስታ፣ ርካታ፣ ወዘተ. ፍለጋ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ሳለ ለተመሳሳይ ነገር የፈለጉት ሰዎች ግን መልእክቱ ጠንከር ማለት ሲጀምር ትተውት ሄደዋል። ርግጥ ነው፣ ክርስትናችን የግል ለውጥን እርባና ማሳነስ የለበትም፤ ሆኖም የግል ለውጥ በቂ አይደለም። የደቀ መዝሙርነት ሕይወት ለሌላው መኖርን ይመለከታል። ጥሪአችን ለመለኮታዊ ተልእኮ እና አገልግሎት ሲባል ራስን መተውን ይጨምራል፤ ይህ በማኅበረ ሰባችንም ቢሆን ተቀባይነት ያለው ዕሴት ነው። የምንለውና የምናደርገው ነገር በሌሎች ላይ የሚፈጥረውን ጫና እና ተጽእኖ ማጤን ይኖርብናል። በአጭሩ ለመናገር፣ ሌሎችን ማስቀደም አለብን። ራስን መካድ፣ በየዕለቱ መስቀላችንን መሸከምና ጌታን መከተል ትርጕሙ ይሄ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ “ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቍጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት … አንዳች አታድርጉ” ሲል የሚመክረን ከኀጢአት እንድንጠበቅ ነው (ፊል. 2፥3-4)።
በሌላ አንጻር ኅብረት ላይ ስናተኵር ግን ግላዊ መልካችን እና ቀለማችን ይጥፋ ማለት አይደለም። መልካችንን እንደ ያዝን እንያያዝ። ለራሳችን ምንም አንፈልግ ማለትም አይደለም። ለራሳችን የምንፈልገውን መልካም ነገር ለሌላውም እንፈልግ፣ በራሳችን እንዲደርስ የማንፈልገው ደግሞ በሌላው ላይ እንዳይደርስ እንትጋ። ሁልጊዜም ቢሆን ልንዘነጋ የማይገባን ነገር ቢኖር አማኞች ሁሉ የአንድ አካል ብልት መሆናችንን ነው። ይህም አንዳችን ለሌላኛችን እንደምናስፈልግ ያስተምረናል። የአንዱ ስኬትም ሆነ ውድቀት፣ ሥቃይም ሆነ ዕረፍት የጋራ ነው። የጋራ ሆነ ማለት ደግሞ የአካሉም ሆነ ማለት ነው። “አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ፤ በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ” (2ቆሮ. 5፥14-15)። ጌታ በመስቀል የሞተው ለራሳችን እንዳንኖር ነው። ጌታችን ከሰማይ የወረደው በሰማይ ያለው አንድነትና ኅብረት በምድርም እንዲንሰራፋ ነው።
ሁላችንም ልባችንንና ሐሳባችንን እንፈትሽ። መንፈስ ቅዱስ ውስጣችንን እንዲመረምርና ራስ ተኰርነታችንን እንዲገልጠው እንፍቀድለት። ለውጡን ማየት ከፈለግንም ከቅርባችን እንጀምር። ከእኛ ይልቅ የትዳር ጓደኞቻችንን ጥቅምና ደስታ እናስቀድም። ጎረቤቶቻችንን፣ ባልንጀሮቻችንን እንደ ራሳችንን እንውደድ። የሌላዪቱን ቤተ ክርስቲያን ዕድገት እንደ ራሳችን ቤተ ክርስቲያን ዕድገት፣ የሌላውን የኑሮ እመርታ እንደ ራሳችን የኑሮ እመርታ እንውሰድ። የሌላኛውን ብሔር አባላት ክብርና ደኅንነት እንደ ራሳችን ብሔር አባላት ክብርና ደኅንነት እንመልከት። አብያተ ክርስቲያናትም ጤናማ እና ሚዛናዊ ትምህርትን ከማስተማር ባሻገር የአባላትን እርስ በርስ መቀራረብ የሚያግዙ እንቅስቃሴዎችን ቢነድፉ መልካም ነው።
ያ ሲሆን ቤትም ሆነ ቤተ ሰብ ጤና ያገኛሉ። ማኅበራትና ማኅበረሰ ሰቦች ስምም ይሆናሉ። እኔነት ዝቅ ሲል፣ ከራሳችን ይልቅ ሌላውን ስናስቀድም ስምረት በምድር ይሰፍናል፤ ሰላምም በየቦታው ይበዛል፤ ጌታም ይከብራል። እውነተኛ የጌታ ደቀ መዝሙርነታችንም በሁሉ ዘንድ ይገለጣል (ዮሐ. 13፥35)።


ማስታወሻ

1. J. A. Ryan, “Individualism,”The Catholic Encyclopedia (New York: Robert Appleton Company, 1910).
2. ሮናልድ ደን (ተርጓሚ ጳውሎስ ፈቃዱ)፤ የወዳጅ ፍላጻ (አዲስ አበባ፣ 2002 ዓ.ም) ገጽ።
3. Wayne Grudem, Systematic Theology: An Introduction to Biblical Doctrine (Grand Rapids: Zondervan, 1994), 455.
4. Tom Wright, “Justi cation: The Biblical Basis and Its Relevance for Contemporary Evangelicalism,” in The Great Acquittal, ed. Gavin Reid (London: Collins, 1980), 36. 5. Grudem, Systematic, 454.
6. ዴሪክ ፕሪንስ (ተርጓሚ ጳውሎስ ፈቃዱ)፤ የጋብቻ ኪዳን (አዲስ አበባ፣ 1994 ዓ.ም) ገጽ 48-49።
7. ሮናልድ ደን (ተርጓሚ ጳውሎስ ፈቃዱ)፤ የጸሎት ኀይል (አዲስ አበባ፣ 2005 ዓ.ም) ገጽ 160።
8. ፕሪንስ፤ የጋብቻ ኪዳን፣ ገጽ 51።
9. ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 52።
10. Vladimir Lossky, Image and Likeness of God (Crestwood: St. Vladimir’s Press, 1976), 177.
11. ሲ. ኤስ. ሌዊስ (ተርጓሚ አዲስ አሰፋ)፤ ክርስትና ለጠያቂ አእምሮ (አዲስ አበባ፤ 2007) ገጽ 160-61።
12. ዳዊት ጸጋዬ፤ አርነት የወጡ ሐሳቦች (አዲስ አበባ፤ 2003) 41።
13. John Stott, The Cross of Christ (Downers Grove: IVP, 2006), 269.
14. John Stott, The Radical Disciple: Some Neglected Aspects of Our Calling (Downers Grove: IVP, 2010), 111
15. ዝኒ ከማሁ፤ 110።
16. Gordon D. Fee and Douglas Stuart, How to Read the Bible for All Its Worth (Grand Rapids: Zondervan, 2003), 65-66.
17. Eric Metaxas, Seven Women and the Secret of Their Greateness (Nahiville, Neslson Books, 2015), 183. 18. NIV Study Bible (Grand Rapids: Zondervan, 2002), 1663.

Share this article:

ሊላሽቅ የሚገባው የኢትዮጵያውያን ልቅ ጀብዱ

የታሪክ አጥኚው አፈወርቅ ኀይሉ (ዶ/ር) በዚህ ጽሑፉ፣ ኢትዮጵያዊነት “ጨዋነት” ብቻ አለመሆኑን፤ ይልቁን ጸያፍ የሆነ “የጀብደኝነት” አመለካከት ከማንነታችን ጋር የተጋባ መሆኑን ከታሪካችንና ከአሁኑ ሁናቴ ጋር ያዛምደዋል። “ልቅ” የተባለው ይህ “ጀብደኝነት” በቶሎ ካልላሸቀ ያጠፋናል ይላል ዶ/ር አፈወርቅ።

ተጨማሪ ያንብቡ

ርብቃ – የእስራኤል እናት

በዚህች አጭር መጣጥፍ እስራኤልን እስራኤል ስላደረገች እናት ለማየት እንሞክራለን። እስራኤላውያን ጠንካራ ሕዝቦች ናቸው። በየቀኑ በዜና ስለ እነሱ ሳንሰማ ማደር አንችልም። አባታቸው ያዕቆብ እግዚአብሔር በሚገርም መልኩ መርጦ የታላቅ ወንድሙ የዔሳው የበላይ ያደረው የእግዚአብሔር ሰው ነበር።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.