[the_ad_group id=”107″]

የፈውስ ቀውስ

የዚህ ጽሑፍ ዋና ዐሳብ ከዓመታት በፊት ከጻፍኩት መንፈስ ቅዱስና ካሪዝማዊ ቀውሶች[1] ከተሰኘ መጽሐፍ ምዕራፍ አራት የፈውስ ቀውስ በሚል ንዑስ ርእስ ከጻፍኩት በክፍል የተወሰደ ነው። የዚያ መጽሐፍ አራት ንጥር ዐሳቦች፥ 1. መንፈስ ቅዱስ ማን ነው? 2. የመንፈስ ቅዱስ የመነቃቃት ሥራዎች በታሪክ ውስጥ ነበሩ ወይ? መቼና የት? 3. የጸጋ ስጦታዎች (ካሪዝማታ) ዐላማ፥ ግብ እና አገልግሎቶቻቸው ምንድር ናቸው? 4. በጸጋ ስጦታዎች ስም የሚፈጸሙት ቀውሶችስ ምን ምን ናቸው? የሚሉ ሲሆኑ፣ ከተዘረዘሩት ቀውሶች ውስጥ አንዱ የፈውስ ቀውስ ነው። ይህ ጽሑፍ ከዚያኛው ዋናው ዐሳብ የተወሰደበት ብቻ እንጂ ክለሳ አይደለም።

በዘመናችን ክርስትና ውስጥ ከመንፈሳዊው ስርጸት ይልቅ ወደ ሥጋዊውና ስሜታዊው ያዘመመና ያዘነበለ ብቻ ሳይሆን ከማዝመምና ማዘንበል አልፈው በሥጋዊነትና ስሜታዊነት ላይ ተደፍተው የወደቁ ልምምዶች ይስተዋላሉ። ከእነዚህ አንዱ ፈውስ ነው። የፈውሰኞች አገልግሎቶች ባለማቋረጥ ከድጡ ወደ ማጡ እየሄዱ ይገኛሉ። ዛሬ የፈውስ አገልግሎት፥ አገልግሎቱ ራሱ ፈውስ የሚያስፈልገው ሆኖአል።

ይህ ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር ፈዋሽነት ደምቆ መነገር አለበት። እንደ አስጠንቃቂ የምጽፈው የፈውስ ተቃውሶ ላይ ቢሆንም፣ ከዚህ የእግዚአብሔር ፈዋሽነት መንደርደር እፈልጋለሁ። እግዚአብሔር ፈዋሽ አምላክ ነው። እርሱ ራሱ ለእስራኤል፥ እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና” ያለ አምላክ ነው (ዘጸ. 15፥26)። በብሉይ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር ያለ ምንም አማካይ በቀጥታና በቃሉ፥ እንዲሁም በአማካይ፥ በሰዎችና በመድኃኒት ፈውሶአል። በቀጥታ ያለ ምንም አማካይ ከፈወሰባቸው ጊዜያት ለምሳሌ፥ ጸሎት ዘፍ. 20፥17፤ 2ዜና 30፥20፤ መዝ. 107፥20 ይገኛሉ። በአማካይ ከፈወባቸው ጊዜያት ለምሳሌ፥ በዮርዳኖስ ውኃ፥ 2ነገ. 5፤ በበለስ ጥፍጥፍ፥ 20፥7፤ ወዘተ.።

አካላዊ ደዌ

በአዲስ ኪዳን መድኃኒታችን ኢየሱስም ሆነ ሐዋርያቱ በርካታ ጊዜ ፈውስ አድርገዋል። ስቃዮቹም ፈውሶቹም በግልጽ የሚታዩ የደዌ፥ የሕማም፥ የተለያዩ ስቃዮች አካላዊ ፈውሶች ናቸው። አንዳንዶቹ በሽታዎች ውስጣዊ ቢሆኑ እንኳ ውጪያዊ ምልክቶች አሏቸው። ከአጋንንት ጋር በቀጥታ የተያያዙት ሳይጠቀሱ፥ እነዚህ በሽታዎች ከተገለጡባቸው ቃላት መካከል፥ ደዌ፥ ሕማም፥ ስቃይ፥ በጨረቃ የሚነሣባቸው፥ ሽባዎች፥ እጁ የሰለለች፥ ደም የሚፈስሳት፥ አንካሶች፥ ዕውሮች፥ ዲዳዎች፥ ጉንድሾች፥ በሽተኞች፥ ለምጻሞች፥ የሆድ መነፋት፥ ንዳድ ይገኛሉ።

በጌታና በሐዋርያቱ የተፈጸሙት ፈውሶች መኖራቸውም፥ መጥፋታቸውም የማይታወቁ ሕመሞችና ፈውሶች አይደሉም። ሕመሞቹ እውነት፥ ፈውሶቹም ድንቅ ናቸው። የጌታና የሐዋርያቱ ፈውሶች በጉባኤ ሞቅታ ወቅት በስሜት ግለትና ጡዘት ውስጥ የተፈጸሙ የመሰሉ፥ ግን ከቶም ያልኖሩ ፈውሶች አልነበሩም።

የሕክምናና የሥነ ልቡና ጠበብት psychosomatic pain የሚሏቸው በሽታዎች አሉ። Psychosomatic ማለት አእምሮ ወለድ አካላዊ ማለት ነው። Psychosomatic painም በአእምሮ ውስጥ የተፈጠረ እንጂ በአካል ውስጥ የሌለ ሕመም ማለት ነው። ሕመሙ የለም፤ ግን ሰዎቹ ያለ ይመስላቸዋል። ወይም በፈውስ ጉባኤዎች ስሜታዊ መነዳት ውስጥ ያለ እንዲመስላቸው ይደረጋሉ። ተመርምረው መኖሩ አልተረጋገጠም። ከዚያ ‘ሲፈወሱ’ ቀድሞም ያልነበረ በሽታ ፈውስ ተቀዳጀሁ ብለው እንዲያምኑና በመድረክ ላይ በየዋኅነትም፥ በድፍረትና በእርግጠኛነትም እንዲመሰክሩ ይደረጋሉ።

በጌታ አገልግሎት ውስጥ በግልጽና በነጠላ የተጠቀሱ ሕሙማንና ደዌዎች እንደ ነበሩ ሁሉ በጥቅሉ ሰዎች በጀማና በብዛት የተጠቀሱባቸው ስፍራዎችም አሉ፤ ለምሳሌ፥ ማቴ. 4፥23-24፤ 8፥16-17፤ 9፥35፤ 14፥14፤ ወዘተ.። ስቃይና ደዌ ይዞ ወደ ጌታ መጥቶ ሳይፈወስ ቀርቶ ወደ ቤቱ የተመለሰ ሕሙም በወንጌላት ውስጥ ባናገኝም ጥቅል ፈውሶች ማለት ግን የጅምላ ፈውስ ማለት አይደለም። ጌታ ጸጋን አያባክንም። እንኳን ጸጋን የምግብ ትራፊንም እንዳያባክኑና እንዲሰበስቡ ሲያደርግ ታይቶአል። በግል የፈወሳቸውን ሰዎች ሁኔታ ስናይ አካላዊና ስሜታዊ ትሥሥርን እናያለን። ይህ ስሜታዊ ትሥሥር በዘመናዊ ፈውሰኞች ውስጥ ተፈልጎ የማይገኝ ነገር ስለሆነ ላብራራው።

አካላዊና ስሜታዊ ትሥሥር

ሕሙማኑ የተፈወሱባቸውን ሁኔታ ስንመለከት እነዚህንና እነዚህን የመሰሉ ሐረጎች እናገኛለን፤ “ወደ እርሱ አመጡ፥ ወደ እርሱ ቀረቡ፥ በእግሩ አጠገብ ጣሉአቸው፥ እጁን ጫነባቸው፥ ዳሰሱት፥ የልብሱን ጫፍ ዳሰሱት፥ ዳሰሳቸው፥ ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው፥ ኃይል ከእርሱ ወጣ”፥ ወዘተ። በነዚህ ቃላት ውስጥ አካላዊም፥ አካላዊ ብቻ ሳይሆን ስሜታዊ ተራክቦም አለ። “አዘነላቸው”፥  “እወዳለሁ ንጻ አለው”፥ “በቁጣ አያቸው”፥ “አነባ”፥ ወዘተ.። አካላዊ መነካካት ብቻ ሳይሆን ስሜታዊ ቁርኝትም አለ። ጌታ ከርቀት፥ በሽተኛው በሌለበት ቃል ብቻ ተናግሮም ፈውሶአል (ለምሳሌ፥ ማቴ. 8፥13፤ ዮሐ. 4፥50)። መደበኛ ሆኖ የሚታየው ግን ፈውስን የሚሹትና ለፈውስ የሚጸልዩት ንክኪ ሲኖራቸው ነው።

በተቃወሱ የፈውስ ልምምዶች ፈውሰኛውና ሕሙሙ ምንም አካላዊ ግንኙነትና ቅርርብ ወይም ስሜታዊ ቁርኝት አይታይባቸውም።  የማየው የሚያሳዝን ነገር ቢሆንም አልፎ አልፎ ፈውሰኞች በሚያገለግሉባቸው ጉባኤዎች እገኛለሁ። በቅርብ የተካፈልኩት ከጥቂት ወራት በፊት ነው። ከቀድሞዎቹም ከቅርቡም እንዳየሁት በሁሉም ስፍራዎች የማየው የፈዋሾቹ ስሜት እንደ ወታደር ዩኒፎርም አንድ ዐይነት ነው። ፈውሰኛና ሕመምተኛ አይነካኩም። የአዛኝነት፥ የርኅራኄ፥ የመጨነቅ፥ የመንሰፍሰፍ ስሜት አይታይባቸውም። አንዳንዶቹ ፈውሰኞች ሸቃጮችና ቸርቻሪዎች ናቸው። ሳይፈወስ የሚመለስ ሰው ሊኖር እንደሚችል አያስቡም። ከኖረም ያ ሰው ስላላመነ ነው ብለው ተምረዋልና ኅሊናቸውን አይኮሰኩሳቸውም።

በዊልቸር የሚመጡ ከኖሩ መኖራቸውም አይታሰብም። ዘይት ቀብቶ መጸለይና እጅ መጫን ጊዜው ያለፈበት አሮጌ ፋሽን ሆኗል። መዳሰስም ከቀረ ቆየ። አሁን የሚደረገው በሆሊውድና ዲዝኒላንድ የወጣቶች ፊልሞች ላይ እንደሚታየው የእጅ መዳፋቸውን ሲዘረጉ ጨረር እየወጣ ጠላቶቻቸውን አሽቀንጥሮ እንደሚዘርረው መዳፍ መዘርጋት ነው። ማይክሮፎን ላይ እፍፍፍፍ እያሉ አሸባሪ ድምፅ እየፈጠሩ በሽታን ማስደንገጥ ነው። ወይም በሽተኞችን ማስበርገግ ነው። ወደሚያሳዝን የፈውስ ልምምድ ዘመን ከደረስን ብዙ ዘመን ተቆጠረ።

ፈውስ ስጦታ ነው ጠበል?

ፈውስን በተመለከተ የቃል-እምነት ወይም ቃለ እምነት[2] (Word-Faith or Word of Faith) ትምህርቶች አንዱ ስሕተት ‘ሰው መንፈስ ነው’ እና ‘ሰው አምላክ ነው’ የሚለው አሳች ትምህርት ነው። ከሕመምና ፈውስ ጋር የተቆራኘው የዚህ ትምህርት ስሕተትም፥ ‘ሰው መንፈስና አምላክ ስለሆነ መታመም አይኖርበትም። እንዲያው በሆነው ምክንያት ቢታመም እንኳ ፈውስ በመስቀሉ የተገኘ ዋስትና ነውና ፈውስን መቀበል መብቱ ነው።’ የሚል ነው። ሁለቱም፥ ማለትም አለመታመምም፥ ፈውስም ካልሠሩ የወቀሳው ድፍድፉም አተላውም በበሽተኛው ላይ ይደፋል። ፈውስ መብት ሆኖ ካልሠራ እግዚአብሔር ሊወቀስ አይችልም። እርሱ ፍጹም አምላክ ነውና። ፈውሰኛውም አይወቀስም፤ አቀብሎአልና። ሕመምተኛው ግን እምነት የለውም ይባላል። ይህ ሌላው የፈውሰኞች ክፉ ጭካኔ ነው።

ለመሆኑ የፈውስ ስጦታ የሚባል ነገር አለ? የሚለውን ጥያቄ ላንሣ። Cessationists የሚባሉ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ፈውስ እና ሌሎች ምልክታዊ ስጦታዎች ከሐዋርያት ጋር ቆመዋል ይላሉ። የሐዋርያነት ምልክቶች በሐዋርያቱ እጅ ተደርጎአል። ከምልክቶቹ መካከል ፈውሶችም ነበሩ። ዛሬ ግን ሐዋርያቱ ስለሌሉ ፈውሱም የለም። ይህ ትምህርታቸው ነው።

እርግጥ ነው፤ ዛሬ ሐዋርያት የሉም። ያዕቆብ ወይም ጴጥሮስ ሐዋርያ እንደሆኑት የሆኑ ሐዋርያት የሉም። የእምነታችን መሠረቱ በሐዋርያትና ነቢያት ላይ አንዴ ተመሥርቶአል። ሲመሠረት አይኖርም። ስለዚህ በዘመናችን ራሳቸውን ሐዋርያት እና ነቢያት ያሉም ሆኑ ሌሎች የሰየሟቸው ቢኖሩ ከቀድሞዎቹ መደዳ የሚሰለፉ ከቶም አይደሉም። የዘመናችን ሐዋርያት ሐዋርያት ከተባሉ እንደ ቃሉ ትርጉም ቤተ ክርስቲያን ወንጌል ሊሰብኩ ባርካ የላከቻቸው ‘የተላኩ’ ናቸው ማለት ነው። ከሆኑ ስፍራቸው ወንጌል ያልሸተተበት ጠፍ ወረዳ እንጂ ጨውና ብርሃን በተከማቸበት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መተራመስና መንጎራደድ መሆን የለበትም። የዘመናችን ሐዋርያት ፈውሰኞች ሲሆኑ ከቀደሙት ኦርጅናሌዎቹ ሐዋርያት ጋር ራሳቸውን ማመሳሰላቸው ከሆነ ትልቅ ስሕተት ውስጥ ናቸው። ገና በመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት ዘመንም ይህ የፈውስ ጉዳይ እየመነመነ፥ እየደበዘዘ እንደ መጣ ይታያል። ለዚህም ነው ሰሴሽኒስቶች  ስጦታው ቆሞአል የሚሉት።

እኔ ሰሴሽኒስቶች አይደለሁምና በአጭር ቃል፥ ‘የፈውስ ስጦታ ዛሬም አለ’ እላለሁ። 1ቆሮ. 12፥9 ይህን ይናገራል። እዚያው 1ቆሮ. 1፥7 ጌታ እስኪመጣ ድረስ የጸጋ ጎዶሎዎች እንደማይሆኑ ለቆሮንቶስ ሰዎች ተጽፎአል። ፈውስና የፈውስ ስጦታ አለ። ይህ ይሁን እንጂ ፈውስ የፈዋሽ ፈቃድ የለም። ላብራራው። ስጦታው እንደ ስብከት ወይም ማስተማር በፈለጉት ጊዜና ቦታ አይፈጸምም። ቅዳሜ ማታ  እንደሚያስተምር አስተማሪ ወይም እሑድ ጠዋት እንደሚሰብክ ሰባኪ ፈዋሹ ማክሰኞ ማታ ወይም ረቡዕ ቀን የፈውስ ጊዜ ተብሎ ታውጆ አይፈውስም። ወይም ሰባኪ እመንገድ ዳር ቆሞ እንደሚሰብክ ፈዋሽ ነኝ የሚል ወደ ጥቁር አንበሳ ወይም ዳጃች ባልቻ ሆስፒታል ሄዶ ሕሙማንን ወደየቤታቸው አይልካቸውም። ስለዚህ ፈውስ በፈዋሹ ጌታ ፈቃድ ላይ ብቻ የተመሠረተ የጸጋ መፍሰስ ነው። ያም ለዚያ ድውይ ሰው፥ በዚያን ጊዜ ካስፈለገው የሚደረግ ቸርነት ነው። ጌታና ሐዋርያት ማክሰኞ ፈውስ፥ ቅዳሜ ትምህርት እያሉ ቀናትን ከፋፍለው አላገለገሉም። ከተማርን ከእነርሱ ነው መምማር ያለብን። ጌታና ሐዋርያት የፈውስ ፕሮግራም እያዘጋጁ አልፈወሱም።

‘ፈውስ ዛሬም አለ’ ስል ግን ፈውስ ሁሌም አለ ማለቴ አይደለም። እግዚአብሔር እንደ ወደደና እንደ ፈቀደ ይፈውሳል፤ ካልፈቀደ ደግሞ አይፈውስም። ፈውስንና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማጋጨት የሚያመጣው ጣጣ ከባድ ነው። ፈውስ በሰዎች መዳፍ ውስጥ አይደለችም። ይህንን የሚያስቡ ፈውሰኞች ፈውስን ከቦታ ጋር ማቆራኘት ትተው፥ ሕሙማንም ቅዳሜ ወይም ማክሰኞ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲመጡ መጋበዝና መጠበቅ አቁመው ወደ ጤና ጣቢያዎችና ወደ ሆስፒታሎች ወይም ወደ መንገድ ዳርና ወደ መንደር መሄድ አለባቸው። ሲሄዱ ግን አይታይም። ፈውስ በሰዎች ፍላጎትና እምነትን በመጭመቅ የሚመጣ ልምምድ ሳይሆን እግዚአብሔር ሲፈቅድ ብቻ የሚሆን ነው። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከስሌቱ ውስጥ ካወጣነው የፈውሰኞቹም የሕሙማኑም ቅሬታ የበዛ ይሆናል። የሕሙማኑ ቅሬታ ግልጽ ነው፤ የፈውሰኞቹ ቅሬታ የበዛ የሚሆነው ደግሞ ቅን ከሆኑ ነው። ተዋናዮችና የዝና ያለህ ባዮች ከሆኑ ቅርም፥ ቅምም አይላቸውም። የእግዚአብሔር ፈቃድ በአክብሮቱ በስፍራው ሲሆን ግን ቴያትሩና ተውኔቱ ይወገዳል። ፈውስ ያልሆነ ፈውስ አይኖርም።

በአዲስ ኪዳን ከወንጌላት ቀጥሎ ወዳሉት መጻሕፍት ስንመጣ ወይም ከጌታ አገልግሎት በኋላ ወደ ነበሩት ሐዋርያት ዘመን አገልግሎት ስንመጣ ፈውስ እንደ ጠበል ሲረጭ፥ እንደ ርችት ሲተኮስ አናይም። የፈውስ ጸጋ አለ? አዎን። የተፈወሱ ሰዎች አሉ? አዎን፤ አሉ። ፈውስ ሁሌም ነበረ? አልነበረም። በጳውሎስ እጅ ፈውስ ተፈጽሞአል? አዎን፤ ተፈጽሞአል። ከአካሉ ጨርቅ እንኳ እየተወሰደ አጋንንት ይወጡና ድውያን ተፈውሰው ነበር (ሐዋ. 19፥11-12)። ከጳውሎስ ጋር አብረው ያገለገሉ ሕሙማን ነበሩ? አዎን ነበሩ። አፍሮዲጡ ታምሞ እግዚአብሔር ማረው (ፊል. 2፥25-27)። “ማረው” የሚለው ቃል ፈወሰው ከሚለው የተለየ መሆኑን እናስተውል። ምሕረት አደረገለት፤ አዘነለት ማለት ነው። ጥሮፊሞስን ታሞ በሚሊጢን ተወው እንጂ አልፈወሰውም (2ጢሞ. 4፥20)። ለጢሞቴዎስ የሆድ ሕመም “ስለ ሆድህና ስለ በሽታህ ብዛት ጥቂት የወይን ጠጅ ጠጣ እንጂ፥ ወደ ፊት ውኃ ብቻ አትጠጣ” አለው እንጂ ከአካሉ ጨርቅ አልላከለትም (1ጢሞ. 5፥23)። “ስለ በሽታህ ብዛት”  በሚለው ሐረግ ‘ብዛት’ የሚለው ቃል ቅድምም አሁንም በተደጋጋሚ የሚሆን እንደማለት ነው። ራሱ ጳውሎስ እንዲወገድለት አጥብቆ የለመነበት የሥጋው መውጊያ ነበረው? አዎን ነበረው። እንዲያም ሆኖ ግን በእጁ ፈውስ ይፈጸም ነበር? አዎን ነበር። በአገልግሎቱ ማብቂያ ገደማ ወደ ሮም ሲሄድ መርከቡ በተሰበረበት መላጥያ ብዙ ፈውስ ተደርጎ ደግሞ ነበር (ሐዋ. 28፥8-9)። ይህ ከሆነ፥ ፈውስ እንደ ጌታ ፈቃድ የሚፈጸም እንጂ የሁሉና የሁሌ አይደለም ማለት ነው። ያኔ እንደዚያ ከሆነ ዛሬም እንደዚያው ነውና ፈውሰኞችና የቃል-እምነት የስሕተት አስተማሪዎች በስሕተታቸው አላዋቂዎችን ሊሸነግሉ የተገባ አይደለም።

አንድ ቀን ፍጹም ፈውስን እንቀዳጃለን? አዎን እንቀዳጃለን። ሕመም ከቶም የማይነካው መንፈሳዊ አካል እንለብሳለን። እስከዚያ ግን በጤና ከተባረክን ጌታን ከልብ እናመስግን። ጤናማ ባለመሆን ከተባረክንም ስለዚያም እናመስግን። ‘ጤናማ ባለመሆን መባረክ’ ስል የፌዝ ቃል መናገሬ አይደለም። እያንዳንዲቱ የልብ ትርታችንና እያንዳንዲቱ ወደ ሳንባችን ገብታ የምትወጣው ትንፋሻችንን እና መንገዳችንን በእጁ ከያዘ ከጌታ ጸጋና ምሕረት የተነሣ የተቸሩን በረከቶች እንጂ መብቶቻችን አይደሉም። እኛ በሕይወት ለመኖርም እንኳ መታደል ያልነበረብን ኀጢአተኞች ነን። ይህ በሕይወት መኖር የሆነልን ከመለኮታዊ መልካምነቱ የተነሣ ብቻ ነው። ከክርስቶስ ጋር ሕይወት የሰጠንና በጸጋው ያዳነን ደግሞ ከምሕረቱ ባለጠግነት የተነሣ ብቻ ነው (ኤፌ. 2፥1-5)። በጣም ብዙ የነጠሩ (በሕመምም ጭምር የነጠሩና የተቀመሙ) ክርስቲያኖች አውቃለሁ። እነዚህ ክርስቲያኖች አስገራሚ ሕይወት፥ ንጹሕ ፍቅር፥ ጉልሕ እምነት፥ የጌታ መውደድ፥ የቃሉ ሙላት፥ የጸሎት ተጋድሎ የበዛላቸው ሰዎች ናቸው።  ፈውስ መልካም ነው? እጅግ በጣም። ግን የፈቃዱ ስጦታ እንጂ መብት አይደለም።

ፈውስ ሥልጣንና መብት ወይስ ስጦታና ፈቃድ?

ፈውስና ሥልጣን የተቆራኙባቸው ስፍራዎች አሉ፤ ለምሳሌ፥ ማቴ. 10፥1፤ ማር. 3፥15፤ ሉቃ. 9፥1። በእነዚህ ስፍራዎች ይህ ፈውስና ሥልጣን ከ12ቱ ጋር አብሮ የተቆራኘ ነው። ከ12ቱ መደዳ ያለ የለምና ይህ የፈውስና የሥልጣን ቁርኝት ዛሬ የለም። ዛሬ ያለው ፈውስ እንደ ጌታ ፈቃድ የሚፈጸም የጸሎት መልስ የሆነ ፈውስ ነው።

ፈውስን እንደ መብት የሚያስተምሩ ሰዎች ይህን የሚያስተምሩት ከሁለት አቅጣጫ ነው። አንዱ እምነት ነው። ለመፈወስ እምነት ያስፈልግሃል የሚል ነው። ካልተፈወስክ፥ ወይም መጀመሪያውኑ ከታመምክ እምነት ጎድሎህ ነበር ይሉናል። የእምነት ጉድለት ያልተፈወሱ ሰዎች ማንኳሰሻና የፈውሰኞቹ ከክስና ከተጠያቂነት ማምለጫም ነው።

ሌላው ጃንጥላ የሆነና በእነዚህ ሰዎች መብት የሚሰኝ ቃል ነው። የዚህ ‘መብት’ ዋና ጥቅስ፥ ኢሳ. 53፥4-5 ነው።

4 በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው።

5 እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።

የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ዐውድ የሚሉት ነገር አለ። አንዲትን ጥቅስ ቆንጽለን ሳይሆን ቢያንስ ጠቅላላ ምዕራፉን ነው ማየት ያለብን። የኢሳ. 53 ጥቅል ዐሳብ የክርስቶስ ተውላጣዊ ሞት ነው።

በመስቀሉ ሞት የተፈወስነው ፈውስ አለ? አዎን አለ። ያ ፈውስ ፍጹም የሆነው ፈውስ ነው! በኃጢአት ፍዳ የወደቀብን መርገም የተፈታልን መፈታት ነው። ይህ ፈውስ የአካላችንን መዋጀትም የነፍሳችንን መዳንም የጨበጠና ያረጋገጠ ነው።

ቁጥር 4 ስለ ደዌና ስለ ሕመም ይናገራል። ፈዋሽነቱ በወንጌላት ውስጥና ለሐዋርያቱ በሰጠው ሥልጣን ውስጥም ታይቶአል። የዚያን ዐይነት ፈውስ ዛሬም ይፈውሳል። ጌታ ሥጋ በመልበሱና በመሞቱ ውስጥ ፈውስ አለ? አዎን አለ። በሽታ ራሱ በምድር መኖሩ የኀጢአት ወይም የውድቀት ውጤት ነው። የበሽታ ዐይነቶችን ሁሉ መጥራት እንችላለን፤ ከራስ ምታትና ከቁርጠት እስከ መነጽርና ማዳመጫ፥ እስከ ትልልቆቹ የካንሰር ዐይነቶች ድረስ ሁሉም የውድቀት መዘዝ ናቸው። ውድቀትና መርገም ባይኖር ኖሮ እነዚህ ሁሉ ባልኖሩም ነበር። ጌታ ሲመጣና ሲሞት ስለ ኀጢአታችንና የውድቀትና የመርገም መዘዝ ስለሆኑት ነገሮች ሁሉ ጭምር ነው። ደዌና ሕማም፥ በሽታና ሞት የውድቀት መዘዞች ናቸው።

ጌታ ፈዋሽ ነው? አዎን ፈዋሽ ነው። ጌታ ይፈውሳል? አዎን ይፈውሳል? ፈውስ መብት ነው? አይደለም። ሁሌም ይፈውሳል? እንደ ፈቃዱ ብቻ ይፈውሳል እንጂ ሁሌም አይፈውስም። እግዚአብሔርን ማስገደድ አንችልም። የእኛ ምርጫ የእርሱን ፈቃድ የሚያሸንፍ ከሆነ እግዚአብሔር ተገዳጅ እንጂ ሉዓላዊ አምላክ አይሆንም። እግዚአብሔርን ሁሌም የእኛን ትንንሽ ምኞትና ዐሳብ ሊያገለግል ታጥቆ የቆመ አገልጋይ አድርገን መገመት የለብንም። ፈቃዱ ደግሞ እርሱ የሚከብርበት እንጂ እኛ የመረጥነው ምርጫ አይደለም። እርሱ ከምን ይልቅ በምን፥ ከየትኛው ይልቅ በየትኛው ይበልጥ እንደሚከብር ያውቃል።

በጤንነትና በጤናማ አካል ሊከብር የሚችለውን ያህል ጤናማ ባልሆነ ወይም በስደትና በመከራ ውስጥ በሚያልፍ ሰው ሕይወትም እግዚአብሔር ሊከብር እንደሚችል መገመትና መቀበል ይቀፍፈናል። በስደትና በመከራ ውስጥ እያለፈ የሚያመሰግነውና የሚያከብረው ክርስቲያን ምስክርነት ሌሎችን ሊነካና አምላካቸውን ይበልጥ እንዲደነቅና እንዲከበር ሊያደርግ እንደሚችል መቀበል ያዳግተናል። እኛ ልናውቀው የተገባን ጉልሕ ነገር ግን አለ፤ ያም፥ እርሱ በሁሉም ነገርና በማንም ሰው ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለው፥ ክብሩን ለሌላ፥ ምስጋናውንም ለተቀረጹ ምስሎች የማይሰጥ መሆኑን (ኢሳ. 42፥8) ነው። እርሱ ከፈለገ ዲዳና ደንቆሮ፥ የሚያይና ዕውር ማድረግ ይችላል (ዘጸ. 4፥11)።

ስለዚህ የእግዚአብሔር ክብር ጥቂት ልበል። ‘እንዴት ነው በኔ ሕመም ወይም ስደትና ስቃይ እግዚአብሔር የሚከብረው?’ የሚለው ጥያቄ ይህን ትምህርት ባካፈልኩባቸው ቦታዎች በአንዳንዶች ከልብ፥ በሌሎች ደግሞ በማንጓጠጥና በነቀፋ በተደጋጋሚ ተጠይቄአለሁ። እግዚአብሔር በእነዚህ ነገሮች እንዴት እንደሚከብር በእርግጥ እኔ አላውቅም። ምናልባት ሁላችንም አናውቅም። ቁምነገሩ መክበሩን ማወቃችን እንጂ እንዴት እንደሚከብር መረዳታችን አይደለም። ይህንን የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነው።

ክብሩ ያንን ደዌ መፈወስ ሊሆን ይችላል። ወይም በዚያ ውስጥ እኛ ከእርሱ ጋር መጣበቃችንና እርሱን ከመቼም ይልቅ መማጸናችን ሊሆን ይችላል። ብዙዎቻችን ከእግዚአብሔር ጋር ቁርኝታችን ጥብቅና ጠንካራ የሚሆነው በምቾትና ድሎት ጊዜ ሳይሆን በጭንቅና ጥበት ጊዜ መሆኑን አልፈንበትና አይተን እናውቃለን። ይህ ለራሳችን ነው። መጽናታችንና እርሱን ማመናችን ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ጥንካሬ ሊሆንም ይችላል። እኛ ምናልባት ውጤቱን አይተን፥ ‘እውነትም ይህ ነገር ለበጎ ነበረ’ ልንል እንችላለን። ለዚህ ከብዙዎች መካከል ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ እማኞችን መጥራት እችላለሁ።

ዮሴፍ ከወንድሞቹ እጅ ጀምሮ በባዕድ አገርና በባዕዳን እጅ መከራን  መቀበሉ ለበጎ መሆኑን ያስተዋለው ከውጤቱ ተነሥቶ ነው (ዘፍ. 45፥4-7 እና 50፥20)። በኢዮብ ላይ ከደረሰው መከራ ተነሥተው የማያስተውሉ ሰዎች እግዚአብሔር ሰዎችን በመጭመቅና በማስጨነቅ የሚደሰት (በሥነ ልቡና ቋንቋ Sadist ይባላል) አድርገው የሚያዩት ሰነፎች አሉ። አንዳንድ የቃለ እምነት አስተማሪዎች ደግሞ ኢዮብ መከራ የደረሰበት ቀድሞውኑ ገና ለገና ይደርስብኛል ብሎ ይፈራ ስለ ነበር የደረሰበት መከራ ነው ይሉናል። ሰነፍ ደፋሮች! ‘ኋላ የደረሰለት ብዙ እጥፍ ሥጋዊና ምድራዊ በረከትስ? ይመጣልኛል ብሎ ስለተናገረ ነው?’ ሲባሉ መልስ ሊፈልጉ ይደናበራሉ። ኢዮብ በአዲስ ኪዳን አንዴ ሲጠቀስልን (ያዕ. 5፥11) ኢዮብ መታገሡንና ጌታም የሚራራ መሆኑን ነው የተነገረን።

ሥርዓቱን እንድናውቅ ልንጨነቅና ይህም ለመልካም ሊሆንልን ይችላል (መዝ. 119፥71)። ጳውሎስ በሮሜ 8፥28 እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን።” ይህን ጥቅስ ቀጥሎ ካለው ቁጥር፥ ከቁጥር 29 ለይቶ ማንበብ ትልቅ ስሕተት ነው። ሮሜ 8፥29 የሚለን ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤” ነው። የአብ ውሳኔ እኛ ልጆቹ በኵሩን ኢየሱስን እንድንመስል ነው። እርሱን እንድንመስል የሚያደርገንን ማናቸውንም ነገር ወደ ሕይወታችን ሊያመጣ ፈቃድም ሥልጣንም ያለው እርሱ ብቻ ነው። ይህንን የጻፈው ጳውሎስ ራሱ በብዙ እንግልትና በአካላዊ ጉስቁልናም ጭምር ነው ያገለገለው። ይህ ማለት በመከራና በእንግልት መኖርን መጥራት ነው? አይደለም። ማንም ጤናማ አእምሮ ያለው ሰው ጤናማ አካልን ይመኛል።

የሕመም ብዙ ምንጮች

ጤናማ አካል የእግዚአብሔር ቸር ስጦታ ነው። መከራና ሕማም ሁሉ ደግሞስ፥ ከእግዚአብሔር ነው? አንዳንዶች እግዚአብሔርን የመክሰሻ ፋይል ለመክፈት ይህን ዐሳብ ቢጠቀሙም ይህም እውነት አይደለም። በሽታና ደዌ ከተለያዩ ምክንያቶች የተነሣ ሊመጣ ይችላል። ዋና ዋናዎቹን ብንወስድ፥

  1. ከላይ በተደጋጋሚ የተወሳው ውድቀት ወይም መርገም አንዱ ምክንያት ነው። አንዱ ሳይሆን ዋናው ምክንያት ነው ማለት ይቻላል። ማናቸውም ዐይነት ኀጢአትና ጉስቁልና በቀጥታ የዚያ ውጤት ናቸው። ደዌና ሞትም የዚያ ውጤት ነው።
  2. ጢአት ውጤት ሊሆን ይችላል። ከላይ የተጠቀሰው ጠቅላላ ኀጢአት ወይም ከአዳም የወረስነው ውድቀት የምንለው መርገም ሲሆን ይህኛው ግን በግል የሚደረግ ኀጢአት ነው። እግዚአብሔር በቃሉ እንዳናደርግ የሚከለክለንን ነገር ተላልፎ በማድረግ ሰዎች በአካላዊ፥ በሥነ ልቡናዊና በአእምሮአዊ በሽታዎች ሊጠመዱ ይችላሉ።
  3. ንዝኅላልነትና የንጽሕና ጉድለት በሽታን ማምጣትም ማሰራጨትም ይችላል።
  4. የውርስ ደዌ ሊኖር ይችላል። ወደ ሐኪም ዘንድ ስንሄድና ሲመረምሩን፥ ‘እንዲህ ያለ ሕመም፥ እንዲህ ያለ በሽታ በወላጆችህ ኖሮ ያውቃል? ወዘተ. እያሉ የሚጠይቁን ያለ ምክንያት አይደለም። እኛ የእግዚአብሔር ፍጡራን ብንሆንም የወላጆቻችን ልጆችና ማንነታችን ከእነርሱ የተገኘ ፍሬዎች ነን። እንደ ቆዳ ቀለማችን ከቆዳችን በታች ያለውንም እኛነት ወርሰናል። በዚያ ውስጥ የተበላሹ የደዌ ጂኖችም ሊኖሩ መቻላቸው እውነት ነው።
  5. የተፈጥሮ ሕግን መጣስ። ተአምር የተፈጥሮ ሕግ ሲፋለስ ነው። ግን እንዲህ ያለ መፋለስ በሌለበት ስሜታዊ በሆነ መፋነን መንጎድ ሕጉን መጣስ ነው። ሰውነት የተፈጠረባቸውና የሚንቀሳቀስባቸው የተፈጥሮ መሥመሮች አሉ። በቅርብ አንድ አጓጉል አፍሪቃዊ ካሪዝማዊ ሰባኪ ጉባኤውን ነዳጅ ጋዝ ሲያጠጣና ሲያስታውኩ የተቀረጸውን ተመልክቼ ነበር። የሚገድልም ነገር ቢጠጡ አይጎዳቸውም፤” የሚለው የማር. 16፥18 ቃል ከጥራዝ ተነጥቆ ተወስዶ መሆኑ ይሆን? የሰውነት አፈጣጠር ጋዝ ለመጠጣት አይደለም።
  6. ሰይጣን አካላችንን ሊጎዳ ይፈልጋል። ቢችል ዒላማው ነፍሳችን ናት። ነፍሳችንን ለማጎሳቆል መተላለፊያ መንገድ አድርጎ የሚጠቀመው ቢሆንለት ሥጋችንን መጉዳት ነው። መልካሙ ነገር በጌታ ፈቃድና ክልል ውስጥ እስከሆንን ድረስ ካልተፈቀደለት ሊነካን አለመቻሉ ነው። ከላይ ያየነው ኢዮብ የዚህ ምስክር ነው። በሉቃ. 13፥10-17 የተፈወሰችው የድካም መንፈስ ያደረባት የተባለችው ሴት ሰይጣን ያሰራት እንደ ነበረች ጌታ ተናግሮአል።
  7. እግዚአብሔር በመለኮታዊ ፈቃዱ ማናቸውንም ክብሩን ሊያሳይ የሚፈቅደውን ነገር በሕይወታችን ሊያደርግ ይችላል። ከላይ እንዳልኩት ክብሩ ፈውሱም ሊሆን ይችላል። በታማሚው ሕይወት ወይም ከዚያ ሰው ጋር ቁርኝት ባላቸው ሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚፈጠር ወይም የሚፈጸም ጉዳይም ሊሆን ይችላል። በዮሐ. 9፥3 የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ የተባለለትን ዕውር ፈውስ እናያለን።

ጌታ ሥጋ በመልበሱና በመሞቱ ውስጥ ፈውስ አለ? ከላይ እንዳልኩት አዎን አለ። የፈውሰኞች ጉልሕ ስሕተት ግን ይህ ነው፤ ከመስቀሉ በኋላ የተገኙት በረከቶች ሙሉ በሙሉ፥ ሁሉም፥ እያንዳንዳቸው ከመንግሥተ ሰማያት ወዲህ የሚታጨዱ አይደሉም። አንዳንዱን በረከት ከሞት ወዲያ ማዶ እንጂ ከሞት ወዲህ አናገኘውም። ለምሳሌ፥ ወደ ፊት የምንለብሰው ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ የነበረውን የሚመስለው ሰማያዊ አካል በዚህች ምድር የማንቀዳጀው በረከት ነው። አለመሞትም እንደዚያው። አለመሞት ከመቃብር ወዲያ የምንቀዳጀው በረከት ነው። ከሞት በኋላ ነው የማንሞተው እንጂ ከሞት ወዲህ ሁላችንም እንሞታለን። የውድቀትና የመርገም አንዱ ቅጣት ሞት ነው። ለዚህ ነው በመስቀሉ የተገኙት በረከቶች ሁሉ በዚህች ምድርና በዚህ ሥጋ ውስጥ ሆነን የምናጭዳቸው ሰብሎች ያልሆኑት።

ኢሳ. 53ን ብቻ ሳይሆን ጠቅላላውን መጽሐፍ ቅዱስና በተለይም አዲሱን ኪዳን ስናይ የመሢሑ ሥጋ መልበስ ዋና ዐላማ ኀጢአታችንን ተሸክሞ ሊሞትና በሞቱም እኛን ሊያድን ነው። ይህ ደኅንነት ነው፤ ይህ እውነተኛው ፈውስ ነው! መሢሕ የቆሰለው ስለ መተላለፋችን፥ የሞተውም ስለ በደላችን ነው። በኢሳ. 53 የተጻፈው የጌታ ፈውስ ስለ ዘላለማዊቱ ነፍሳችን ድነት እንጂ ስለ አካላዊ ሥጋችን ፈውስ አድርጎ ማስተማር የስቃዩንና የመስቀሉን ዋጋ ማርከስ ነው። መስቀሉ ለሥጋ ፈውስ አለመሆኑን የሚያረጋግጥልን ማቴ. 8፥16-17 ነው። ይህ ክፍል ይህንን በኢሳ. 53፥4 የተጻፈውን በመጥቀስ፥ ‘የታመሙትን ሁሉ ፈወሰ’ ማለቱ ነው። ጌታ ሕማምንና ደዌን ለመፈወስ መሰቀል አላስፈለገውም። ነፍስን ለማዳን፥ ለኀጢአት ስርየት ግን ደሙ መፍሰስ ነበረበት! መሞት ነበረበት። የመስቀሉ ግብ ይህ ነው።

ይህ ክፍል በጴጥሮስም ተጠቅሶአል (1ጴጥ. 2፥22-25)። ለኀጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር በሥጋው ኀጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ። ጌታ ከዚህ ላነሰ ነገር አልተሰቀለም፤ አልሞተም። ከዚያ ያነሰውን ነገር ለማድረግ መሰቀልና መሞት የለበትም። ስለዚህ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ ሲል ስለ ሥጋዊ ሕመም ፈውስ አለመሆኑ ቁልጭ ብሎ የሚታይ ነው። ጌታ የሥጋችን ጠባቂና እረኛ ቢሆንም ጴጥሮስ የሚለን፥ ‘ወደ ነፍሳችሁ ጠባቂና እረኛ ተመልሳችኋል’ ነው። የሥጋ ፈውስን ከሞቱ በፊት ከፈወሰ፥ እርሱ ብቻ ሳይሆን ሐዋርያቱም ተልከው በሥልጣን ከፈወሱ፥ የመስቀሉ ሞት ለሥጋ ፈውስ አይደለም ማለት ነው። ይህ ግልጽ ነው። እጅግ በጣም ግልጽ ነው። የመገረፉ ቁስል ለእኛ ደሙ የመፍሰሱ ቁስል ነው። የሥጋ ፈውስን ሳይገረፍና ሳይቆስልም ፈውሷል።

ጌታ በመስቀል ላይ ሳይሰቀል እርሱም ሐዋርያቱም ከፈወሱ መስቀልና የሥጋ ፈውስ አይቆራኙም። መቆራኘትም የለባቸውም። የፈውስ በረከት እንደ ጌታ ፈቃድ ቢኖርም የጌታን የመስቀል ሥቃይና ሞት ከአካላዊ ፈውስ ጋር የሚያቆራኙ ሰዎች ግዙፍ ስሕተትን በቃሉ ላይ እየፈጸሙ ያለ ሰዎች ናቸው። ከዚህ ስሕተት ተጠንቅቀን ልንጠበቅ መትጋት አለብን። የጌታን የመስቀል ሞት ከደኅንነታችን፥ ከዘላለማዊት ነፍሳችን መዳን ላነሰ ለምድራዊና ለሥጋዊ ጥቅም ማውረድ እጅግ ግዙፍ ስሕተት ነው።

ሳጠቃልል፥ ውሸታም ፈውስ አለ? አዎን አለ። ሐቀኛ ፈውስስ አለ? አዎን አለ። ፈውስ ግን ‘ፈዋሽ’ ወይም ‘ተፈዋሽ’ አምጠው የሚወልዱት ነገር አይደለም። ጌታ እግዚአብሔር ሲፈቅድና እርሱ ሲፈቅድ ብቻ የሚፈጸም በረከት ነው። አንድ ቀን ደዌና ሕማም የማይነካው ለዘላለም ጌታ እግዚአብሔርን እያከበረ የሚኖር መንፈሳዊ አካል ይኖረናል። ይህ በመስቀሉ በኩል ያገኘነውና የሚሆንልን የመዳናችን ቁንጮ ነው።

እግዚአብሔር ከአርያም ይባርካችሁ።


[1] መንፈስ ቅዱስና ካሪዝማዊ ቀውሶች፤ ቃለ ሕይወት ሥነ ጽሑፍ አገልግሎት፤ አዲስ አበባ፤ 1996። ዐሳቡ የተወሰደበት ገጽ፤ 212-24። መጽሐፉን ከኢንተርኔት ለማግኘት ወይም አውርዶ ለመጫን ከ http://www.good-amharic-books.com/library?id=107 ማግኘት ይቻላል።

[2] ቃል-እምነት ወይም ቃለ እምነት የሚሰኘው የስሕተት ትምህርት ዋና ማጠንጠኛ የምንናገረው ቃል ነገሮችን የመፍጠር ወይም የመከሰት ውስጣዊ ኃይል አለው የሚል ነው። ልክ እግዚአብሔር ቃልን ተናግሮ እንደ ፈጠረ እኛም የምንናገረው ቃል ፈጣሪና ተከናዋኝ ነው ይላሉ።

Zelalem Mengistu

ፍቅር፣ ፍትሕ እና ሰላም የኢየሱስ መንገድ

በዚህ ልዩ ዕትም፣ ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆነው እስክንድር ነጋ የሕንጸት ዕንግዳ ሆኖ ቀርቧል። አገራችን ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶችና ዴሞክራሲ የሚከበሩባት አገር እንድትሆን መሥዋዕትነትን የጠየቀ ትግል አድርገዋል ከሚባሉት ግለ ሰቦች መካከል አንዱ እስክንድር ነው። በዚህም፥ ከዘጠኝ ጊዜያት በላይ ደጋግሞ ለእስር የተዳረገው እስክንድር፣ በአጠቃላይ ከዘጠኝ ዓመታት በላይ በእስር አሳልፏል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.