[the_ad_group id=”107″]

መስቀሉ

ሲሞን ቬይ

ገዛኸኝ ዘበነ እንደ ተረጐመው

ሰይፍን የሚያነሡ በሰይፍ ይጠፋሉ። ሰይፍን የማያነሡ በመስቀል ይጠፋሉ።

ክርስቶስ የታመሙትን ፈውሷል፣ ሙታንን አስነሥቷል፣ ወዘተ.። ይህ ከተልእኮው ሁሉ እጅግ ትንሹና የሰው አእምሮ የሚረዳው ተግባሩ ነበር ማለት ይቻላል። ልዕለ ተፈጥሯዊው ተልእኮው፣ [የጌተሴማኔው] የደም ላቡ ነው፤ ለሰው ልጆች መጽናናት የነበረው ገና ያልረካ መሻቱ ነው፤ ጽዋው ከእርሱ ታልፍ ዘንድ መለመኑ ነው፤ በእግዚአብሔር የመተው ስሜት የተሰማው መሆኑ ነው።

ሰይፍን የሚያነሡ በሰይፍ ይጠፋሉ። ሰይፍን የማያነሡ በመስቀል ይጠፋሉ። 

በዚያች ቀውጢ ሰዓት፣ በስቅለቱ ሰዓት በአባቱ ተተው። በሁለቱም በኩል የተገለጠው ፍቅር እንዴት ያለ ጥልቅ ነው!

“አምላኬ፣ አምላኬ፣ ስለ ምን ተውኸኝ?”

ክርስትና አንዳች መለኮታዊ ነገር ስለ መሆኑ እነሆ ትክክለኛ ማስረጃ!

ፍትሓዊ መሆን እርቃን መቅረትንንና መሞትን የግድ ይጠይቃል፤ ከምንገምተው በላይ። ለዚያ ነው የፍትሕ ምሳሌ እርቃንና ሞት መሆን ያለበት። መስቀሉ ለዐሳባዊ ምስስሎሽ ክፍት አይደለም።

ክፍት እንዲሆን እግዚአብሔርን መምሰላችን ነገር የቃላት ጒዳይ ብቻ ሊሆን አይገባም። እርሱን ሊመስል የሚችል ጻድቅ ሰው ሊኖር ይገባል። ያ እንዲሆን ደግሞ እግዚአብሔርን መምሰል ምርጫችን ማድርግ ፈጽሞ የማንችል መሆኑን ሳንወድድ በግዳችንም ቢሆን ልናውቅ ግድ ይላል። ሰው መስቀልን ሊመርጥ አይችልማ!

ሰው ይብዛም ይነስም ምናኔን ወይም ጀግንነትን ሊመርጥ ይችላል፤ መስቀልን ግን በፍጹም አይመርጥም። መስቀል እኮ የቅጣት ስቃይ ነው።

ስቅለቱን ከመሥዋዕት አንጻር ብቻ የሚርዱት ሰዎች በውስጡ ያለውን የፈዋሽነት ምስጢር እና መራራ ፈዋሽነት አሽቀንጥረው ይጥላሉ። ሰማእትነትን መመኘት በእጅጉ ትንሽ ነው። መስቀሉ እልፍ ጊዜ ከስማእትነት ይልቃል።

የቅጣት ስቃይ፣ ከስቃዮች ሁሉ መራራው ስቃይ ነው። ለእውነተኛነቱም ማረጋገጫው ይኸው መራራነቱ ነው።

መስቀሉ። የኀጢአት ዛፍ፣ እውነተኛ ዛፍ ነበር፤ የሕይወት ዛፍ የዕንጨት ወጋግራ ነበር። ፍሬ የማይሰጥ አንዳች ነገር፤ ግን ዝም ብሎ ብቻ ሽቅብ ወደ ላይ የሚያድግ። “የሰው ልጅ ከምድር ከፍ ከፍ ማለት አለበት፤ ከምድር ከፍ ከፍ ባለም ጊዜ ሰዉን ሁሉ ወደ ራሱ ይስባል።” ጕዟችንን ሽቅብ ብቻ እየቀጠልን በውስጣችን ያለውን የንቃት ኀይላችንን ልንገድል እንችላለን። ብቸኛ ፍላጎታችን [እንድሚያጋሽብ ተክል] ሽቅብ ወደ ላይ መውጣት ከሆነ ቅጠልና ፍሬ ከንቱ ልፋት ናቸው።  

አዳም እና ሔዋን በዛፉም በፍሬውም በኩል በሚገኝ ወሳኝ ኀይል መለኮትነትን በከንቱ ፈለጉ። መለኮትነት ግን የተዘጋጀልን በአንድ ውስን ቦታ ባለና ግንዝ ሬሳ በተንጠለጠለበት ሙት ዛፍ ላይ ነው። ከእግዚአብሔር ጋር የመዛመዳችንን ምስጢር በሟችነታችን ውስጥ ልንፈልገው ይገባል።

ወደ ሰው ነፍስ ለመድረስ እና ነፍስን ለመማረክ እግዚአብሔር በማይቈጠሩ ዘመናትና ስፍራዎች ራሱን አዝሏል፣ አድክሟል። ያቺ ነፍስ በእግዚአብሔር ከራሷ ፈጽማ ለመላቀቅ ንጹህ ልቡናን፣ ሙሉ ፈቃደኝነትን (ከብልጭታ ለፈጠነ ዐጭር ቅጽበት እንኳ ቢሆን) ያሳየች እንደ ሆነ፣ እግዚአብሔር ያቺን ነፍስ ያለ ጥርጥር ያሸንፋታል። ይህቺ ነፍስ ፍጹም የእርሱ ስትሆን ይተዋታል። ፍጹም ብቻዋን ይተዋትና፣ በተራዋም የወደዳትን ፍለጋ በዚያ በማይቈጠር ዘመንና ጎዳና እየዳከረች ትፈልገዋለች። ስለዚህ ይህች ነፍስ ከተቃራኒው ጫፍ ተነሥታ እግዚአብሔር ወደ እርሷ ለመምጣት ያደረገውን ያንኑ ጉዞ ታደርጋለች። ያ ጉዞ እንግዲህ መስቀል ይባላል።

እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር ሕመሙ ነው። መልካም የሆነው ክፉዉን ያለ ስቃይ እንዴት ሊወድድ ይቻለዋል? ክፉ የሆነውም መልካሙን በመውደዱ ፍዳውን ያያል። የእግዜሩም የሰዉም የጋራ ፍቅር፣ የስቃይ ፍቅር ነው።

ሰው እንደ ውሱን ፍጥረትነቱ በሁኔታ፣ በቦታ እና በጊዜ ተወስኖም እንኳ ቢሆን የሚያስብ ፍጥረት ከመሆኑ የተነሣ እግዚአብሔር ተሰቅሏል።

አንድ የሚያስብ ውሱን ፍጡር እንደ መሆኔ፣ የተሰቀለውን እግዚአብሔር እንደምመስል ላውቅ ይገባል።

እንደ እግዚአብሔር ልሆን ይገባል፤ ነገር ግን፣ እንደ ተሰቀለው እግዚአብሔር። ሁሉን ቻይ ሆኖ በሁኔታ እንደተወሰነው እግዚአብሔር።

ጵሮሚጠስ[2]፣ ሰውን አብዝቶ በመውደድ የተሰቀለ አማልክት ነው። ሂፖሊተስ[3] ደግሞ እጅግ ንጹሕ ሰው በመሆኑና በአማልክት እጅግ በመወደዱ እንደ ተቀጣ የሚነገርለት ነው። የሁለቱ መተባበር (የሰው እና መለኮት ኅብረት) ነው ቅጣቱን የሚያመጣው።

እኛ ከወዲያ ጽንፍ ከእግዚአብሔር እጅግ ርቀን ያለን ቢሆንም፣ ወደ እርሱ ለመመለስ ግን ፈጸሞ የማንችልበት ርቀት ላይ አይደለንም። ከማንነታችን እግዚአብሔር ተቈርጦ ወጥቷል። ስቅለቶቹ ነን። እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር ሕመሙ ነው። መልካም የሆነው ክፉዉን ያለ ስቃይ እንዴት ሊወድድ ይቻለዋል? ክፉ የሆነውም መልካሙን በመውደዱ ፍዳውን ያያል። የእግዜሩም የሰዉም የጋራ ፍቅር፣ የስቃይ ፍቅር ነው።

ይህ የጋራ ፍቅር እንዲሰምር በእኛ እና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን ርቀት መገንዘብ ያሻል። ይህ እግዚአብሔርም የተሰቀለ ባሪያ ሊሆን ግድ ይላል። ከላይ ወደታች ካልሆነ በቀር ርቀቱን መረዳት አንችልምና። ሁሌም ቢሆን በተሰቀለው ክርስቶስ ፈንታ ራሳችንን ከማስቀመጥ ይልቅ በፈጣሪው አምላክ ፈንታ ማስቀመጥ ይቀልለናል።

የክርስቶስ ፍቅር ስፋቱ፣ እግዚአብሔር ከፍጥረቱ የሚርቀውን ርቀት ያህላል።

የመካከለኝነት ሥራው በራሱ እጅግ የሰፋ መለያየትን ያመለክታል።

ለዚህ ነው እጅግ የሰፋ ልዩነት ሳይኖር የእግዚአብሔርን ወደ ሰው መውረድንም ሆነ የሰው ወደ አምላክ መቅረብን በአእምሯችን መረዳት የሚያቅተን።

ኅልቆ መሳፍርት የሌለውን ጊዜና ቦታን ተሻግረን መሔድ ይገባናል። የመንገዱ ቀድሞ ጀማሪ እግዚአብሔር መሆን አለበት፣ ቀድሞ ተሻግሮ የመጣው እርሱ ነውና። እግዚአብሔርን እና ሰውን ከሚያገናኙ መሥመሮች ሁሉ ትልቁ ፍቅር ነው። ይህ ፍቅር ልንሻገረው የሚገባንን ገደል ያህል የሚረዝምና የሚሰፋ ትልቀት ያለው ነው።

ስለዚህ ፍቅር የቻለውን ያህል ይተልቃል፤ ርቀቱም የቻለውን ያህል ይርቃል። ለዚህ ነው ክፉ ከገደብ በላይ ሆኖ መልካሙ ነገር የሚያቆጠቁጥበት ዕድልን እስኪያጠፋ ድርሰ የሚደርሰው። እኵይ እዚህ ጥግ እንዲደርስ ተፈቅዶለታል። አንዳንዴም ከዚህ የተሻገረም ይመስላል።

ይህ ላይብኒዝ[4] ያስበው ከነበረው ፍጹም ተቃራኒ ነው። ያለንብት ክፋት የተንሰራፋበት ዓለም ያለ ጥርጥር ከእግዚአብሔር ታላቅነት ጋር የበለጠ የሚገጥም በመሆኑ እንጂ፣ ላይብኒዝ እንደሚለው እግዚአብሔር በፈጠረው ከዓለማት ሁሉ የሚሻል ዓለም ውስጥ ብንሆን ኖሮ እርሱ ሊያደርግ የሚችለው ነገር ጥቂት በሆነ ነበር።

እግዚአብሔር ዓለምን የሞላውን ድቅድቅ ጨለማ አልፎ ወደ እኛ ተሻግሮ ይመጣል።

የክርስቶስ የመስቀል ላይ ሕመምና ስቃይ በምስጢር የተከናወነ የእግዚአብሔር ፍጹም ፍትሕ መኖሪያ ነው። ፍትሕ በመሠረቱ ስለመብቱና ጥቅሙ የሚያስፈልገውን ሁሉ ፍልሚያ የሚያደርግ አይደለም። ወይ ከቁሳዊው ዓለም የተሻገረ በመለኮት ዘንድ ብቻ ያለ፣ አልያም ሕመም መሆን አለበት።

የክርስቶስ ስቃይ ያለ ጥርጥር ልዕለ ተፍጥሯዊ ፍትሕ ነው። ያሉትን የርኅራኄ ርዳታ ሁሉ ፍጹም የከለከል ፍትሕ ነው፤ የእግዚአብሔር አብ ፍቅር እንኳ እንዳይራራለት ያደረገ ፍትሕ ነው።

የቤዝዎት ስቃይ የመከራን እርቃን አውጥቶና ወደ ንጽሕናው አምጥቶ ህልውና የሚሰጠው ነው። ይህም ህላዌን፣ ፍጥረትን ሁሉ ያድናል።

እግዚአብሔር የኅብስት ቊራጭ አድርገን በምንቀበለው በቅዱስ ሥጋ ወደሙ በኩል እንደሚገኝ ሁሉ፣ በመስቀል ላይ ባለው እጅግ ክፉ በሆነ ስቃይ ውስጥም ይገኛል።

የክርስቶስ ስቃይ ያለ ጥርጥር ልዕለ ተፍጥሯዊ ፍትሕ ነው። ያሉትን የርኅራኄ ርዳታ ሁሉ ፍጹም የከለከል ፍትሕ ነው፤ የእግዚአብሔር አብ ፍቅር እንኳ እንዳይራራለት ያደረገ ፍትሕ ነው። 

የሰው ስቃይ ለእግዜሩ ሆነ። ግን ደግሞ ለካሳ ወይ ለማጽናኛ እንዲሆን አይደለም። ዘመድ ሊሆነን እንጂ።

ሁሉ ነገር ለበጎ እየተለወጠ ወደ እግዚአብሔር እንዲቀርቡ የሚያግዛቸው ሰዎች አሉ። ለእኔ ግን ሁሉም ነገር ከእግዚአብሔር ያርቀኛል። በእኔ እና በእርሱ መካከል የመላለሙን ግዝፈት የሚያህል ርቀት አለ። በዚያ ርቀት ላይ ደግሞ መስቀልን የሚያህል ነገር ተጨምሮበታል።

ስቃይ ለኀጢአት አልቦነት ፍጹም እንግዳ ነው፤ እንዲሁም በተመሳሳይ የኀጢአት አልቦነት መሠረታዊው ጠባዩ ስቃይ ነው።

በኻጫ በረዶ ላይ ያለ ደም። ንጹሕ እና እኵይ። እኵይ ራሱ ንጹሕ መሆን አለበት። ሊነጻ የሚችለው ደግሞ ፍጹም ንጹሕ በሆነ ሰው ስቃይ ብቻ ነው። የስቃይን ፅዋ የሚጎነጭ ንጹሕ ማንነት በእኵዩ ላይ የድኅነትን ብርሃን ያበራል። እንዲህ ያለው ሰው፣ የንጹሕ አምላክ የሚታይ ምሳሌ ነው። ለዚህ ነው ሰውን የሚወድድ አምላክ፣ አምላክን የሚወድድ ሰው መሰቃየት ያለበት።

ደስተኛ የሆነ ንጽሕና። ይህም ሌላ ድንቅ ነገር ነው። ነገር ግን፣ በቀላሉ የሚወድቅና የሚሰብር፣ በዕድል ላይ የተመሠረተ ደስታ ነው። ልክ እንደ አንድ ጣፋጭ የፍሬ ዛፍ አበባ ነው። ደስታ ከንጽሕና ጋር የጠበቀ ትሥሥር የለውም።

ፍጹም ንጹሕ መሆን ማለት የመላለሙን ቀንበር መሸከም ማለት ነው። እንዲሁም ያንን ቀንበር መሸከሚያ የሚሆን ተጻራሪ ዐቅምንም አሽቀንጥሮ መጣል ማለት ነው።

እግዚአብሔር፣ ለሰው ልጆች እንደ ጽኑ ኀያልም፣ ኀጢአት እንደ ሌለበት ንጹሕ ሰውም ራሱን ሰጥቷል። ከሁለቱ መምረጥ የሰው ልጆች ፈንታ ነው። 

ራሳችንን ባዶ በማድረግ ውስጥ፣ በዙሪያችን ላለው ለመላለሙ ጫና ራሳችንን እናጋልጣለን።

እግዚአብሔር፣ ለሰው ልጆች እንደ ጽኑ ኀያልም፣ ኀጢአት እንደ ሌለበት ንጹሕ ሰውም ራሱን ሰጥቷል። ከሁለቱ መምረጥ የሰው ልጆች ፈንታ ነው።


[i] ሲሞን ቬይ (1909 -1943) ከለዘብተኛ አይሁድ ቤተ ሰብ የተገኘች ፈረንሳያዊት ፈላስፋ፣ ምስጢራዊ (mystic) እና የግራ ዘመም አክራሪ ፖለቲካ አክቲቪስት ነበረች። ለሠራተኛው መደብ ካላት አዘኔታ የተነሣ አብዛኛውን ጊዜዋን በፖለቲካ ትግል ውስጥ አሳልፋለች። “Oppression and Liberty” የሚለው ዝናኛ ፖለቲካዊ መጽሐፏን ጨምሮ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጒዳዮች በርካታ ዐጫጭር ጽሐፎችን ለተለያዩ መጽሔቶች አበርክታለች። በፍልስፍናዋ የጥንቱ የግሪክ ፈላስፋ የአፍላጦ (Plato) ፍልስፍና በእጅጉ ይስባት ነበር። ሲሞኖ ቬይ፣ ምንም እንኳን በኢአማኒ ቤተ ሰብ ውስጥ ያደገች ቢሆንም፣ በሕይወቷ ዘመን ሁሉ በክርስትና እምነት (በተለይ በካቶሊክ ሚስቲሲዝም) በእጅጉ የምትሳብ ነበረች። ጉስቷቭ ቲብን የሚባል ወዳጇም፣ በእርሱ ዘንድ በዐደራ መልክ ያስቀመጠቻቸው መንፈሳዊና ምስጢራዊ (mystical) የጽሐፍ ስብስቦቿን እንደገና የአርትዖት ሥራውን በመሥራት፣ “Gravit and Grace” በሚል ርእስ እንዲታተሙ አድርጓል። አሁን እዚህ ተተርጒሞ የቀረበው ጽሐፍም፣ “The Cross” በሚል ርእስ በዚህ የስብስብ ጽሑፍ መድብል ውስጥ የተካተተ ነው። ሲሞን ቬይ፣ በሕይወት በነበረችበት ወቅት ከተወሰኑ የግራ ዘመም ፖለቲካ አስተሳሰብ አራማጅ ከነበሩ ሰዎች ውጪ ምንም ዐይነት ዕውቅና ያልነበራት ቢሆንም፣ ከሕልፈቷ በኋላ፣ በተለይም በ1960ዎች የበርካታ ፈላስፎችን፣ የሥነ ጽሑፍ ሰዎችን፣ የፖለቲካ ሳይንቲስቶችን እና የነገረ መለኮት ምሑራንን ቀልብ የሳበች፣ በአያሌዎቹም ላይ ተጽዕኖ ያሳረፈች ሆናለች። ለአብነት ያህል ቲ. ኤስ. ኤሊዮት፣ አልበርት ኮመስ፣ የካቶሊኩ ፖፕ ፖል ስድስተኛ እና የካንተርበሪ ሊቀጳጳስ የነበረው ሮወን ዊልያም መጥቀስ ይቻላል። አልበር ኮመስም፣ “የዘመናችን ብቸኛ ድንቅ መንፈስ ሲል ነበረች” ሲል ያሞካሻታል።

[2] በግሪክ ሚቲዮሎጂ ውስጥ “የእሳት አምላክ” ተብሎ የሚታውቅ ነው። በብልህነቱና ሰው ወዳድ በመሆኑ ይታወቃል። ከዚህ ፍቅሩ የተነሣ ከሌሎች አማልክት ጋር ከባድ ፊልሚያ በማድረግ፣ ከእነርሱ እሳት ሰርቆ ለሰው ልጆች እንደ ሰጠ ይታመናል። ይህም እሳት የሰው ልጅ አእምሮ እንዲከፈትና ሥልጣኔን እንዲያመጣበት አደረግ ይላሉ።

[3] ዕውቊ የግሪክ ቲያትር ጸሐፊ ኢሩፒዲየስ (484-407 ዓ.ዓ.) የደረሰው “ሂፖሊተስ” የተባለ ትራጄዲ ቲያትር ገጸ ባሕርይ ነው።

[4] ጋትፍሊድ ዊልኸልም ላይብኒዝ (1646-1716 ዓ.እ.)፣ ጀርመናዊ ሒሳብ አዋቂ እና ፈላስፋ ነው። ከዚያ ባለፈ ሥነ መለኮታዊ፣ ሥነ ምግባራዊ፣ ፓለቲካዊ፣ ሕግ፣ ታሪካዊ እና ሥነ ልሳናዊ በሆኑ ጒዳዮች ላይም ጽፏል። አውንታዊነት (Optimism) በሚባለው ፍልስፍና እና ሥነ መለኮታዊ ጽንሰ ሐሳቡ ይታወቃል። በዚህ ፍልስፍና እግዚአብሔር የፈጠረው ይህ ዓለም፣ ሊፈጥራቸው ከሚችለው ሁሉ የተሻለው ዓለም ነው የሚል ሙግት ያቀርባል። 

Gezahegn Zebene

ገዛኸኝ ዘበነ የመጀመሪያ ድግሪውን በ Construction Technology and Management ከዲላ ዩንቨርሲቲ ያገኘ ሲሆን፣ በግል ሥራ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል። መጻሕፍትን የመተርጐም ዝንባሌ አለው። የናዚ ሰለባ የነበረው ጀርመናዊ መጋቢ ዲትሪክ ቦንሆፈር ሥራ የሆነውን Life together የተሰኘውን መጽሐፍ “ሕያው ማኅበር” በሚል ርእስ ወደ አማርኛ ቋንቋ በመመለስ ለንባብ አብቅቷል።

Share this article:

እግዚአብሔር – አለ!

“የሰላም መረበሽና የፍትሕ ቀውስ እየከረረ በመጣበት በዚህ ዘመን፣ እንደ ክርስቲያን ተስፋ የምናደርገው የታሪክን አቅጣጫ በልጓም የያዘውን ልዑል እግዚአብሔርን ነው።” መጋቢ ግርማ በቀለ (ዶ/ር) “እግዚአብሔር አለ!” በተሰኘው በዚህ ዐጭር አጽናኝ መልእክት ያስተላለፉትን ያንብቡ።

ተጨማሪ ያንብቡ

ወንድሞችና እኅቶች ተስማምተው በአንድነት ሲኖሩ እንዴት መልካም ነው!

የአንድና የብዙ ጉዳይ የዓለም አፈጣጠር ምሥጢር ነው። የአንድና የብዙ ሁኔታ የብዙ ጠቢባን፣ የብዙ ፈላስፋዎች ጥያቄ ነው። አንዳንዶቹ በአሐዳዊው ላይ ሌሎቹ ደግሞ በብዙው ላይ ያተኩራሉ። ሆኖም ብዝኃነትን ያለ ኅብረት፣ አንድነትን ያለብዝኃነት ማሰብ ይቻል ይሆን? ብዝኃነት ውበት የሚሆነው መቼ ይሆን? አንድነትስ አስደሳች የሚሆነው መቼ ይሆን? 

ተጨማሪ ያንብቡ

7 comments

Your email address will not be published. Required fields are marked *

 • “ሁሌም ቢሆን በተሰቀለው ክርስቶስ ፈንታ ራሳችንን ከማስቀመጥ ይልቅ በፈጣሪው አምላክ ፈንታ ማስቀመጥ ይቀልለናል።”
  ለአሰላስሎት በሚሆኑ ሃሳቦች የተሞላ ነው። ገዝሽ እናመሠግናለን!! በርታ!
  በ”ኅያው ማሕበር” ተጠቅመናል። ብዙ እንደምትጠቅመን አምናለሁ።

 • It is a wonderful and touching message gezsh. God bless you for sharing it with us.It is a message that should be remember daily.

 • “ከእግዚአብሔር ጋር የመዛመዳችንን ምስጢር በሟችነታችን ውስጥ ልንፈልገው ይገባል”።ገዝሽ ተባረክ እንድናሰላስለው የሚያደርገንን ሃሳብ ነው ይዘህልን የመጣኸው፡፡

 • “የክርስቶስ የመስቀል ላይ ሕመምና ስቃይ በምስጢር የተከናወነ የእግዚአብሔር ፍጹም ፍትሕ መኖሪያ ነው። ፍትሕ በመሠረቱ ስለመብቱና ጥቅሙ የሚያስፈልገውን ሁሉ ፍልሚያ የሚያደርግ አይደለም። ወይ ከቁሳዊው ዓለም የተሻገረ በመለኮት ዘንድ ብቻ ያለ፣ አልያም ሕመም መሆን አለበት።”

 • “እግዚአብሔርን እና ሰውን ከሚያገናኙ መሥመሮች ሁሉ ትልቁ ፍቅር ነው። ይህ ፍቅር ልንሻገረው የሚገባንን ገደል ያህል የሚረዝምና የሚሰፋ ትልቀት ያለው ነው።” አስደናቂ ጽሑፍ ነው። እናመሰግናለን!!

 • Gezesh God bless you, and thank you!
  … እግዚአብሔር የኅብስት ቊራጭ አድርገን በምንቀበለው በቅዱስ ሥጋ ወደሙ በኩል እንደሚገኝ ሁሉ፣ በመስቀል ላይ ባለው እጅግ ክፉ በሆነ ስቃይ ውስጥም ይገኛል።

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.