[the_ad_group id=”107″]

መስቀሉ

አዲስ ኪዳን እውን የሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ በመስቀል መሥዋዕትነቱ፣ በፈሰሰው ክቡር ደሙ ነው። ይህ የመስቀል መንገድ ለዓለም ሞኝነት ሆኖ ቢቈጠርም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን የመለኮት ጥበብና ኀይል ነው።

የቃል ሥጋ መሆንና በመካከላችን ማደሩ ያነጣጠረው መስቀሉ ላይ፣ የመስቀሉ ክስተት ላይ ነበር። “ልጆቹ በሥጋና በደም እንደሚካፈሉ እርሱ ራሱ ደግሞ ያንኑ ተካፈለ፤ ይኸውም በሞት ላይ ኀይል ያለውን ዲያብሎስን በሞቱ ኀይል እንዲደመስስ ነው። እንዲሁም በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በሞት ፍርሀት የታሰሩትነ ነጻ እንዲያወጣ ነው።” (ዕብ 2፥14-15)።

በብሉይ በእንጨት ላይ የሚሰቀል በእግዚአብሔር የተረገመ፣ እግዚአብሔር የተጸየፈው ነው። እንደ ሮማውያን አመለካከት ሰውን በመስቀል መግደል እጅግ አሰቃቂ ነው። ስለሆነም ማንንም የሮማ ዜጋ መስቀል፣ በስቅላት መግደል በሮም መንግሥት የተወገዘ ነበር።

ሐዋርያቱ የመስቀል መሥዋዕትነቱን የድነታችን መሠረት መሆኑን መልእክታቸውን አጠንክረው አውጀዋል። በራእይ መጽሐፍም እንደምንመለከተው አራቱ ሕያዋን ፍጡራን፣ ሃያ አራቱ ሽማግሌዎች ለታረደው በግ ቅኔ ተቀኝተው፣ ተደፍተው መስገዳቸው የመስቀሉን ሥራ ክቡርነት ከፍ አድርጎ የሚያሳይ ነው (ራእይ 5፥9፡10፡12)።

መጽሐፉን ልትወስድ፣
ማኅተሞቹንም ልትፈታ ይገባሃል፤
ምክንያቱም ታርደሃል፤ …
10 ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት
አድርገሃቸዋል፤
እነርሱም በምድር ላይ ይነግሣሉ። …
12 የታረደው በግ ኀይልና ባለ ጠግነት፣
ጥበብና ብርታት፣
ክብርና ሞገስ፣ ምስጋናም፣
ሊቀበል ይገባዋል።”

መስቀል የሰውን ስቃይ እግዚአብሔር አምላክ የተካፈለበት፣ የኢዮብ ጥያቄ “አንተ የሥጋ ዐይን አለህን?” የሚለው ፍንትው ያለ ምላሽ ያገኘበት፤ ስቃይ ለእግዚአብሔር ባዕድ እንዳልሆነ የተመሠከረበት፣ “የእግዚአብሔር ፍቅር ስፋቱ፣ ከፍታው፣ ጥልቀቱ ከመታወቅ ያለፈ ነው” የሚለው ምናባዊ ሆኖ እንዳይቀር በመስቀሉ ሞት እግዚአብሔር ሰውን ማፍቀሩ በገሃድ የተገለጠበት ታሪካዊ እውነታ ነው።

የመለኮት ጥምር ባሕርያት በአንድ ሁኔታ የተገለጠበት፣ ማለትም ምሕረቱና ፍርዱ፣ ሰው አፍቃሪነቱ እና ኀጢአት ጠልነቱ የታየበት፣ ጥበቡ የተንጸባረቀበት፣ ሞትና ሕይወት የተገናኙበት፣ ሽንፈትና ድል የተቃቀፉበት፣ መተውና መታቀፍ የተቆራኙበት፣ ውርደትና ክብር የተጨባበጡበት፣ መፍረስና መታነጽ የተተካኩበት፣ ሰውና እግዚአብሔር የተገዳደሉበት (“አሮጌው ሰው” እንዲሉ፣ “እግዚአብሔር ወልድ” እንዲሉ) ፍጥረት የታደሰበት አዲስ የሆነበት ነው።

ትላንትና ነገ የተሸረቡበት፣ ምድርና ሰማይ የተጋጠሙበት፣ ሰማይ የተከፈተበት፣ “ምድር” ወደ “ሰማይ የወጣበት”፣ “ሰማይ” ወደ “ምድር የወረደበት”፣ የጥል ግድግዳ የፈረሰበት፣ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ የሆነው የክርስቶስ ኢየሱስ መስቀል ነው።

ከአምልኮተ ባዕድ ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ዘወር የሚባልበት፤ ከባይተዋረ እግዚአብሔርነት፣ ከአምላክ ጠልነት ወደ አምላክ ቤተ ሰብነት፣ ወደ አምላክ ወዳጅነት የሚገባበት፤ ከጨለማው አገዛዝ፣ ከመንግሥተ እኔ ግዞት ነጻ ተወጥቶ ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር፣ ወደ ሰማያዊ ዜግነት መፍለስ የተቻለበት ነው፡፡

በመስቀሉ ላይ የፈሰሰው ደም የኀጢአትና የበደል ስርየት መቀበያ፣ ጽድቅን መታደያ፣ ከሕግ ርግማንና ከከንቱ ኑሮ መዋጃ፣ በኀጢአት ኀይል በሞት ኀይልና በጨለማው ሥርዐት ላይ ድል መጎናጸፊያ፣ ከእግዚአብሔር ጋር መታረቂያ ነው። መስቀሉ የወንጌል እምብርት የመስቀሉም መንገድ የኑሯችን መርሕና ዘይቤ ነው፤ ማለትም በመስጠት ማግኘት የሚስተናገድበት፣ ከሁሉ ኋላ በመሆን ከፊት ገጭ የሚባልበት፣ በድካም ብርታት የሚታፈስበት፣ በውርደት ክብር የሚለበስበት ጣይ አንሽ ቅኝት ነው።

“… እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ መሰናክል፣ ለአሕዛብ ደግሞ ሞኝነት ነው።”
(1ቆሮ 1፥22-23)

ተኣምረ ማርያም፣ ገድላትና ድርሳናት ምን ይኹኑ?

መምህር አግዛቸው ተፈራ፣ ሰሞኑን መነጋገሪያ በሆኑት ድርሳናትና ገድላት ጕዳይ ላይ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት፣ በሊቃውንት ጕባኤ በኩል ተገቢው ማስተካከያ እንደሚሰጥ መናገራቸውን ተከትሎ የሚከተለውን ዐሳብ አጋርቷል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.