[the_ad_group id=”107″]

ልዩ ወንጌል

ልዩው ወንጌል እና መገለጫዎቹ

ሕንጸት ቁጥር 1 ዕትም፣ በአውራ ነገር ዐምድ ሥር “የወንጌላውያኑ መንታ መንገድ” በሚል ሐተታዊ ጽሑፍ ተስተናግዶ ነበር፡፡ ጽሑፉ በዋናነት ከመቶ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የወንጌላውያን ክርስትና በኢትዮጵያ ይዟቸው ስለመጣው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦች በማተት፣ አማኝ ማኅበረ ሰቡ ስላበረከታቸው በጎ አስተዋጽዖዎች በመጠቆም ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይህንን በጎ ተጽእኖውን ማስቀጠል በማይችልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰና ለዚህም ምክንያቱ ልዩ የሆነ አስተምህሯዊ አቋምና ልምምድ በቤተ ክርስቲያን መተዋወቁ እንደ ሆነ ይጠቁማል፡፡ ይህ ልዩ አስተምህሮና ልምምድ ደግሞ በ“እምነት እንቅስቃሴ” ወይም በ“ብልጽግና ወንጌል” የተጠመቀ “ክርስትና” ወደ አማኝ ማኅበረ ሰቡ መዝለቁ ነው፡፡

በዚህኛው ዕትም “የእምነት እንቅስቃሴ” አጀማመርና አጎለባበት እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ ራሱን የገለጠባቸውን ማሳያዎች ለማሳየት ጥረት ተደርጓል፡፡ “የእምነት እንቅስቃሴ”፣ “የብልጽግና ወንጌል”፣ “ሦስተኛው ሞገድ” የተሰኙት መጠሪያ ስያሜዎች እንቅስቃሴውን ለመግለጽ በተለዋዋጭነት በሥራ ላይ የዋሉ ናቸው፡፡ አንድ የወል ስም ለመስጠት ደግሞ “ልዩ ወንጌል” የሚል መጠሪያ ተሰጥቷል፡፡

የጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ

በአሜሪካን አገር በምትገኘው የካንሳስ ግዛት፣ ቶፔካ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ቤተል መጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ ተማሪ የነበረችው አግነስ ኦዝማን እ.አ.አ ጃንዋሪ 1 ቀን 1901 “በማይደመጥ ልሣን” (በግሪክ glosolalia) መናገር ጀመረች፡፡ አግነስ ወደዚህ ልምምድ የመጣቸው የኮሌጁ አስተዳዳሪ የነበሩት ቻርልስ ፎክስ ፓርሃም እጃቸውን ጭነው የመንፈስን ኀይል እንድትቀበል ከጸለዩላት በኋላ ነበር፡፡ ይህም ቀን በዘመናዊው ዓለም የጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ ጅማሬ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡[1] ይሁን እንጂ፣ ከአምስት ዓመታት በኋላ በዚያው አሜሪካ፣ ሎስ አንጄለስ ከተማ፣ አሱዛ ጎዳና የሆነው ክስተት ለእንቅስቃሴው መስፋፋት ቀዳማይ ድርሻ እንዳለው ይነገራል፡፡ ክስተቱ ዊሊያም ሰይሞር የተሰኘው መጋቢ ይመራት የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ “በማይደመጡ ልሳኖች” በሚናገሩ ምእመናን መሞላቷ ነበር፡፡ ይህም በወቅቱ እንደ ትልቅ ትንግርት ይታይ እንደ ነበር የታሪክ ጸሓፍት ይተርካሉ፡፡

በርግጥ የጴንጤቆስጤ ልምምድ ጆን ዌስሊ ካስተዋወቀው “የቅድስና እንቅስቃሴ” በኋላ በጊዜ ሂደት እንደ መጣ ብዙ አጥኚዎች ይስማማሉ (ምንም እንኳን በወቅቱ በርካታ “የቅድስና እንቅስቃሴ” መሪዎች ጴንጤቆስጤን ባይቀበሉትም)፡፡ አስተምህሮው አማኞች ከሥጋዊ ፈቃድና መሻት በመላቀቅ በቅድስና የሕይወት መርሕ መመላለስ እንዳለባቸው የሚያስተምር ነበር፡፡ በሌላ አገላለጽ፣ ክርስቲያኖች ፍጽምናን በምድር ሳሉ መለማመድ እንደሚችሉ አጽንኦት ይሰጣል፡፡ ይህንንም ለመፈጸም የመንፈስ ቅዱስ ዕርዳታ ወሳኝ በመሆኑ ምእመናን የእርሱን ኀይል በመጠማት ይጸልዩ ጀመር፡፡ በሂደትም ቀስ በቀስ የጴንጤቆስጤ መገለጫ ነው ወደሚባለው በልሣን የመጸለይ ልምምድ ውስጥ ገብተው ራሳቸውን አገኙት፡፡ እንደ ጴንጤቆስጤያውያን እምነት የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትም ሁለተኛው ጥምቀት ሲሆን፣ ይህም በልሣን በመናገር ይገለጣል የሚለው ዐይነተኛ የትምህርቱ መገለጫ ሆነ፤ በተጨማሪም ሌሎች የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች በአማኝ ሕይወት ውስጥ በሥራ ላይ እንደሚውሉ አስተምረዋል፡፡ ይህ የጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ አጀማመርና አጎለባበት የመጀመሪያው ሞገድ (The First Wave) የሚል መጠሪያ ስም ተሰጥቶታል፡፡

እንቅስቃሴው በ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ ዓመታት ከወንጌላውያኑ ጋር ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ገብቶ እንደ ነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡ በተለይም፣ ከድነት (conversion) በኋላ ሁለተኛ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት መኖር፣ በልሣን መጸለይ እንዲሁም ፈውስን ጨምሮ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች በዚህም ዘመን ይሠራል የሚለው አስተምህሯዊ አቋም የልዩነቱ መነሻ ነበር፡፡ በርግጥ በርካታ ጴንጤቆስጤያውያን ከ“ቅድስና እንቅስቃሴ” አራማጆች በተለየ፣ የቅድስና/የፍጽምና (sanctification) ሕይወት በሂደት የሚያድግ ተግባር (progressive work) እንደ ሆነ ያስተምራሉ፡፡

የጴንጤቆስጤ አስተምህሮና ልምምድ ከዐርባ ዓመታት በላይ በእኛም አገር በቤተ እምነት ደረጃ ተስፋፍቶና ተጽእኖውን አንሰራፍቶ የቀጠለ የኢትዮጵያ “ወንጌላውያን” ክርስትና አንድ አካል ነው፡፡ እንደ ገነት ቤተ ክርስቲያን፣ ሙሉ ወንጌል፣ ጉባኤ እግዚአብሔርና ሌሎች ቤተ እምነቶች በዚህ አስተምህሮ ውስጥ ያሉ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡

የካሪዝማቲክ እንቅስቃሴ

በዘመኑ የጴንጤቆስጤ እንቅስቃሴ ከቀደምት ቤተ እምነቶች (mainline denominations) ውጪ የተስፋፋ ቢሆንም፣ ሁለተኛው ሞገድ (The Second Wave) የተሰኘው የካሪዝማቲክ እንቅስቃሴ ቀደምት ቤተ እምነቶችን ጭምር ያጥለቀለቀ ሆነ፡፡ እንቅስቃሴው በወንጌላውያኑ ብቻ የተገደበ ሳይሆን፣ ወደ ካቶሊካውያኑ ዘንድም የተሻገረ እንደ ነበረ፣ ብሎም በቫቲካኑ መማክርት ላይ አጀንዳ ሆኖ መቅረቡን ታሪካዊ አጎለባበቱን ያጠኑ ይጽፋሉ፡፡

የካሪዝማቲክ እንቅስቃሴ ከጴንጤቆስጤ የሚለይበት ዋነኛ አቋሙ፣ በልሣን መናገር/መጸለይ ብቸኛ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት መገለጫ አይሆንም ብሎ ማመኑ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ በልሣን መናገርን ጨምሮ በ1ቆሮ. 12፥8-10 ያሉ የጸጋ ስጦታዎች ዛሬም እንደሚሠሩ ያምናል፤ ይለማመዳል፡፡ ዛሬ ይህ አስተምህሮ/ልምምድ በዓለም ደረጃ በቀደምቶቹም ሆነ በአዳዲሶቹ ቤተ እምነቶች በስፋት የሚስተዋል ሲሆን፣ ʻወግ አጥባቂʼ ወንጌላውያን ናቸው የሚባሉ ቤተ እምነቶች ሳይቀሩ ከሞላ ጎደል በዚህ ልምምድ ውስጥ መግባታቸው ይነገራል፡፡ በአገራችንም ቢሆን፣ ይኸው ልምምድ በከፍተኛ ደረጃ ተስፋፍቶ የክርስትናው አንዱ መገለጫ ሆኗል፡፡ የሉተራንና የመጥምቃውያን የአስተምህሮ መሠረት ያላቸው ቤተ እምነቶች እንኳ ሳይቀሩ በዚሁ ልምምድ ውስጥ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ምናልባትም ለኢትዮጵያውያኑ ከዚህ ልምምድ ውጪ መሆን የማይታሰብ ሳይሆን አይቀርም፡፡

ሦስተኛው ሞገድ (The Third Wave)

ይህ እንቅስቃሴ ወጥነት የሌለው ወይም መልከ ብዙ ሲሆን፣ ይሄ ነው ለሚባል ማዕከላዊ አካል ተጠሪነት የማያውቀው ወይም በየትኛውም መዋቅራዊ አደረጃጀት ተጠየቅ የሌለበት ነው፡፡ የእንቅስቃሴው አራማጆችም ተመሳሳይ የሆነ አስተምህሮም ሆነ ልምምድ የላቸውም፡፡ በርግጥ በጴንጤቆስጤአውያንም ሆነ በካሪዝማቲካውያን የሚታዩ ልምምዶች  በእንቅስቃሴው አራማጆች ዘንድ ሲተገበሩ ይስተዋላል፡፡ ምንም እንኳ “ሦስተኛው ሞገድ” እየተባለ የሚጠራው ይህ እንቅስቃሴ እ.አ.አ ከ1980ዎቹ በኋላ ባሉት ዓመታት ይስፋፋ እንጂ፣ የእንቅስቃሴው መነሻ ግን በሃያኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያዎቹ ዐሥርት ዓመታት በአንድ ግለ ሰብ አነሣሽነት በኩል እንደ ሆነ ይታመናል፡፡ “ሦስተኛው ሞገድ” በውስጡ፣ “የእምነት እንቅስቃሴን (Faith Movement) እና የዚያ ዐይነተኛ ማሳያ የሚባለውን “የብልጽግና ወንጌል”ን (Prosperity Gospel) ዐቅፎ የያዘ ነው፡፡

የወደኋላ ታሪኩ እንደሚያሳያው ከሆነ፣ “የእምነት እንቅስቃሴ”ን ጀምሮ አስፋፍቶታል የሚባለው ኤሴክ ዊሊያም ኬንዮን (1867-1948) ሲሆን፣ ይህም “አዲስ አስተሳሰብ” (New Thought) በተባለው የወቅቱ ንቅናቄ የተጠመቀ ነበር፡፡ ካትሪን ቦውለር “Blessed: A History of the American Prosperity Gospel” በሚል ርእስ ለፒ.ኤች.ዲ. ማሟያ ባቀረበችው ጥናት፣ ለኀምሣ አምስት ዓመታት የዘለቀው የኬንዮን “አገልግሎት” ለእንቅስቃሴው ቀጣይነት መደላደል ፈጥሮ እንዳለፈ ጽፋለች፡፡ ኬኒዮን “ተጽእኖ አምጪ እምነት” ብሎ በሰየመው አስተምህሮው፣ “ክርስቲያኖች ትክክለኛውን መለኮታዊ መርሖዎች በመጠቀም የእግዚአብሔርን ሀብት መበዝበዝ” እንደሚችሉ ያስተምር ነበር፡፡

በክርስቶስ ዳግም የተፈጠረው ሰው፣ በመንፈሳዊው ዓለም ብቻ ሳይሆን በምድራዊው ዓለምም ላይ ትልቅ ሥልጣን እንዳለው፣ ይህም ብቻ ሳይሆን ክርስቲያኖች የኀጢአት ሸክም የሌለባቸውና በጥቂቱ ከመላእክት አንሰው የሚገኙ እንደሆኑ  ይናገር ነበር፡፡ በተለይም፣ የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የአማኞችን ሥነ ኑባሬያዊ ደረጃ (ontological status) ቀይሮታል፤ ይህም በተሰወሰነ ደረጃ በፍጥረት ላይ የባለቤትነት ድርሻና የተጠቃሚነት ጸጋ አጎናጽፏቸዋል ባይ ነው፡፡ እንደውም በመንፈስ የተሞሉ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ጋር ካላቸው ሙሉ ተመሳስሎት/ውሕደት የተነሣ ሰው ብቻ ናቸው ብሎ ማሰብ እንደሚያስቸግር ይሰብክም ነበር፡፡ “ዓለም ዛሬ ላዕለ ሰብ (superman) በዕቅፏ ይዛ እንደምትኖር አላወቀችም” የሚለው ኬኒዮን፣ “ሰው መንፈስ” ብቻ ሳይሆን “እኛ ትንንሽ እግዚአብሔሮች ነን” ለሚለው ትምህርቱ መነሻ ይኸው አመለካከቱ ነበር፡፡

ዛሬ ይህ እንቅስቃሴ በሰሜን አሜሪካ፣ በደቡብ ኮርያና በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት ተስፋፍቶ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳን ከቀደምት ወንጌላውያን፣ ጴንጤቆስጤውያን እና ካሪዝማቲካውያን ቤተ እምነቶች የጠነከረ ተቃውሞ ቢደርስበትም፣ የእምነት እንቅስቃሴ/የብልጽግና ወንጌል የመዳከም ምልክት አይታይበትም፡፡ በአንጻሩ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ደኻ አገሮች እግሮቹን እያስገባ መጪ ዘመኑን የሚያራዝም ይመስላል፡፡

“የእምነት እቅስቃሴም ሆነ የብልጽግና ወንጌል” ስለ ምን ስሕተት ሆነ?

ለመጽሔት በሚሆን ፍጆታ የእምነት እንቅስቃሴና የብልጽግና ወንጌል ስሑት የሚሆኑባቸውን ጥቂት ነጥቦች ነጥሎ ማውጣት አስፈላጊ ነው፡፡ ዴቪድ ደብሊው ጆንስ እና ሩሴል ዉድብሪጅ “Health, Wealth, and Happiness” ብለው በሰየሙት መጽሐፋቸው የብልጽግና ወንጌል ከትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ የሚለይባቸው ናቸው ያሏቸውን እዚህ መጥቀሱ ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ጆንስ እና ዉድብሪጅ የእንቅስቃሴውን አስተምህሯዊ ዝንፈት ያሳያል ብለው የጠቀሷቸው ነጥቦች አምስት ሲሆኑ፣ እነዚህም፡- የአብርሃም ኪዳን ምድራዊ/ቁሳዊ ባርኮትን ያካትታል ስለመባሉ፣ የክርስቶስ ስርየት ለሥጋዊ ጉስቁልና መነሻ የሆነውን ኀጢአት ሙሉ ለሙሉ በማስወገዱ አማኞች ከጉስቁልና ነጻ የሆነ የምድር ሕይወት መለማመድ ይችላሉ ስለመባሉ፣ መስጠት/ልግስና መልሶ የማግኛ/የማትረፊያ መንገድ ነው ስለመባሉ፣ እምነት በራስ የሚመነጭ መንፈሳዊ ኀይል ሲሆን፣ ይህም ወደ ብልጽግና ጎዳና ይመራሉ ስለመባሉ እንዲሁም ጸሎት እግዚአብሔር እንዲያበለጽገን የምናስገድድበት መሣሪያ ነው የተሰኙት ናቸው፡፡

እንደ “ብልጽግና ወንጌል” እምነት ከሆነ እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባው ኪዳን ቁሳዊ ሀብትን ያካትታል፡፡ በኦሪት ዘፍጥረት ምእራፍ 12፣ 15፣ 17 እና 22 የምናገኛቸው ኪዳናዊ ምንባባት ክርስቲያኖችም ምድራዊውን/ቁሳዊውን ሀብት የአብርሃም የሥጋ ልጆች እንደሆኑት እስራኤላውያን ሁሉ፣ ገንዘባቸው ማድረግ ይችላሉ፤ ምክንያቱ ደግሞ ክርስቲያኖች የአብርሃም የመንፈስ ልጆች መሆናቸው ይላል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም፣ በገላቲያ 3፥14 “…የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ ይደርስላቸው ዘንድ” የሚለው ጥቅስ እንደ ተጨማሪ ማጠናከሪያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በአንጻሩ ግን፣ በክርስቶስ በማመን የአብርሃም የመንፈስ ልጆች የሆኑ ክርስቲያኖች ከአብርሃም የሥጋ ልጆች ጋር የሚካፈሉት ምድራዊ ውርስ/ብልጥግና የለም፡፡ እንዲያ ቢሆን የዓለሙ ክርስቲያን ሁሉ መኖሪያ መሰባሰቢያው መካከለኛው ምሥራቅ በሆነ ነበር፡፡ ይህም እውነት በመሆኑ፣ ጳውሎስ በገላቲያ መልእክቱ አሕዛብ መንፈሳዊ ስለሆነው ባርኮት፣ ይህም ድነትእንደ ሆነ ከመልእክቱ መረዳት ያን ያህል አያዳግትም፤ “የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል … ” ሲል ባርኮቱ መንፈሳዊ መሆኑን ያው ቁጥር አስቀድሞ ይናገራልና፡፡

በሁለተኝነት የሚነሣው ስሕተት የኢየሱስ ክርስቶስ ስርየት ለቁሳዊ ጉስቁልና ምክንያት የሆነውን ኀጢአት ያካትታል ብቻ ሳይሆን፣ አማኞች ከጉስቁልና ነጻ የሆነ ሕይወት መለማመድ ይችላሉ የሚለው ነው፡፡ ይህ አመለካከት ተለጥጦ ሄዶ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ የተቀማጠለ ሕይወት እንደ ነበረው፣ አማኞችም ያንኑ ፈለግ በመከተል መኖር እንደሚችሉ “የልዩው ወንጌል” ሰባኪያን ያስተምራሉ፡፡ ጆን አቫንዚኒ፣ “ኢየሱስ በጣም የሚያምር ትልቅ መኖሪያ ቤት ያለው፣ ብዙ ገንዘብ ይይዝ የነበረ፤ ይለብሰው የነበረውም ልብስ በምርጥ ዲዛይነር የተዘጋጀ” እንደ ነበረ ማስተማሩ አንዱ የትምህርቱ መዛነፍ ማሳያ ነው፡፡ በዚህም የታላቁን የክርስቶስ የማስተሰረይ ተልእኮ፣ ነፍስን ከማዳንና የመንፈስ ጉስቁልና ከመዋጀት ክብር አውርዶ፣ በምድራዊው/ቁሳዊ ስኬትና ድል መተካቱ ነው፡፡

ከዚሁ ጋር በተጓዳኝነት የሚነሣውና በ“ልዩ ወንጌል” አራማጆች እስኪያሰለች የሚነገረው ዲስኩር፣ አማኞች ቁሳዊ ባርኮትን ለማግኘት መስጠት/መለገስ አለባቸው የሚለው ነው፡፡ በርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ መስጠትን ያበረታታል፤ ይሁን እንጂ የብልጽግና አስተማሪዎች በሚሉት “የካሳ ሕግ” ደግሞ አይደለም፡፡ ʻስጦታ/ልግስና ከግራ ኪስ አውጥቶ በቀኝ እንደማስቀመጥʼ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ አንድ ተገቢና መሠረታዊ ጥያቄ መነሣት አለበት፡- ʻለመሆኑ ምእመናን ለማን እንዲሰጡ ነው በአጽንዖት የሚነገራቸው?ʼ በተጨባጭ እንደሚስተዋለው፣ ምእመናንን በ“ስጡ ይሰጣችኋል” ስሌት በማማለል ስጦታቸውን የሚቀበሏቸው ሰባኪያኑ/አስተማሪዎቹ ወይም እነሱ በባላይነት የሚመሯቸው አካላት ናቸው፡፡ ስጦታው የሚያበለጽገውም እነዚህኑ ሰባኪያን/አስተማሪዎችን ነው፡፡ ሰጪዎቹ ግን ከዛሬ ነገ እናገኛለን በሚል አይጨበጥ ተስፋ ይዋትታሉ፤ “የካሳ ባርኮቱም” ሳይመጣ ይቀራል፡፡ ʻለምን?ʼ ብሎ የሚጠይቅ ደፋር ካለ፣ ʻበሙሉ ልብህ ስላላመንክ ነውʼ ወይም ʻመስጠት የሚገባህን ያኽል ስላልሰጠህ ነውʼ የሚል ዙር አክራሪ መልስ ይሰጠዋል፡፡

አራተኛው የስሕተት ማሳያ ደግሞ እምነት ከራስ የሚመነጭ መንፈሳዊ ኀይል ሲሆን፣ ይህም እምነት ወደ ብልጽግና እና ወደ ከፍታ ሕይወት የሚመራ ጉልበት ነው መባሉ ነው፡፡ ይህም እምነት በእግዚአብሔር የሚሰጥና እግዚአብሔር ተኮር የሆነ ሳይሆን፣ በሰው ልጅ ጥያቄና መሻት ላይ ተመሥርቶ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ነው፡፡ በሌላ አባባል፣ እምነት ከላይ ከአምላክ ዘንድ ለሰዎች በሚሰጠው መለኮታዊ ትእዛዝ ውስጥ የሚቀነበብ ሳይሆን፣ ሰዎች ባላቸው የእምነት መጠን እግዚአብሔርን አስደምመው የሚፈልጉትን የሚያገኙበት ስልት ነው፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ በአማኞች ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሚና የሚኖረው የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅድና ሐሳብ ሳይሆን፣ የሰዎች ጊዜያዊና ተለዋዋጭ ፍላጎት ይሆናል፡፡ በመሆኑም፣ የግንኙነት አቅጣጫው ከላይ ወደታች ሳይሆን ከታች ወደ ላይ የተንጠራራ ሆኖ ይታያል፡፡

ʻጸሎት ብልጽግናን ለማግኘት እግዚአብሔርን የምናስገድድበት መሣሪያ ነውʼ የሚለው የልዩው ወንጌል ሰባኪያን/አስተማሪያን ሌላኛውና ዐይነተኛው መገለጫ ነው፡፡ ጆንስ እና ዉድብሪጅ የሚጠቅሱት ክሬፍሎ ዶላር የተሰኘ የብልጽግና ሰባኪ እንዲህ ብሏል፡- “ስንጸልይ የጠየቅነውን እንደተቀበልን አምነን በመሆኑ እግዚአብሔር ጸሎታችንን ከመመለስ ውጪ ሌላ አማራጭ የለውም…፡፡” የቱንም ያህል ብናምን እግዚአብሔር የጠየቅነውን ሁሉ ይመልሳል? እውን ጸሎት ከእግዚአብሔር ሉዓላዊ ፈቃድና ምርጫ በላይ ጉልበት አለው? ከቶ ነገር እግዚአብሔርን ማስገደድ ይቻላል እንዴ?

ልዩው ወንጌል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን

የእምነት እንቅስቃሴ በተለይ፣ ከሰማንያዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ቀጥተኛ በሆነ መልኩ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን ክርስትና እምነት ተከታዮች መካከል መስተዋል እንደ ጀመረ ይታመናል፡፡ በወቅቱም ከቀደምት አብያተ ክርስቲያናት ጋር ትልቅ ግጭት ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ የእንቅስቃሴው መገለጫ ባሕርያት ከሆኑት መካከል፣ የሌሎች አብያተ ክርስቲያናትን መንጋ ማስኮብለልን እንደ ዋና ሥልት ስለሚቆጥረውና ሃይማኖታዊ ልምምዱን ማስረፅ የሚፈልገው በዚሁ አማኝ ማኅበረ ሰቡ ውስጥ በመሆኑ በወቅቱ ከፍተኛ ቀውስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፈጥሮ ነበር፡፡

ይኸው አካሄድ በጊዜ ሂደት እየደከመ ሲመጣ፣ ተጋፍጭነቱን በመተው/በመቀነስ የተለሳለሰ አካሄድን ለመከተልና ራሱን በተዘዋዋሪ መንገድ ለማስረፅ ጥረት አድርጓል፡፡ ታዲያ፣ ይኼኛው ስልት ከመጀመሪያው ይልቅ ውጤታማ ሳያደርገው አልቀረም፡፡ በቀደምት አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ያሉ በርካታ አገልጋዮች በዚህ በሁለተኛው አካሄድ ወጥመድ ውስጥ መግባታቸውን ማስተዋል ይችላል፡፡ በተለይም እንቅስቃሴው ከብልጽግና ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው በመሆኑና አብዛኞቹ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮች የኑሮ ደረጃ ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሣ፣ ይዞት በመጣው አዲስ ሥልት ብዙዎችን ሳይረታ እንዳልቀረ መገመት አያዳግትም፡፡ ቀደም ሲል እንደተጠቆመው፣ እንቅስቃሴው በጴንጤቆስጤም ሆነ በካሪዝማቲክ ዐውድ ውስጥ መገለጥ የሚችል በመሆኑ፣ እንደ “ትንቢት ስጦታ” የመሳሰሉና ሌሎች የጸጋ ሥጦታዎችን በመጠቀም የአማኞችን ልብ ሊማርክ ቻለ፡፡ በዚህም የአማኞችን ንጽረተ እምነት ከሰማያዊው ወደ ምድራዊው በቀላሉ ያንሸራትተው ጀመር፡፡ በመሆኑም በርካታ አገልጋዮች በድንገት “የትንቢት ሥጦታ” እንዳላቸውና “ምስጢራት እንደሚገለጡላቸው” ሳይታክቱ ማወጅ ጀመሩ፤ “ለአገልግሎት” ስያሜውም የሞት ሽረት ትግል አደረጉ፤ በዚህም የበርካቶችን (ይልቁንም ደግሞ የባለ ጸጎችን) ትኩረት ማግኘት ቻሉ፡፡ በምላሹም “ነቢይ” ነን ያሉ የብልጽግናውን ሕይወት ተያያዙት፤ ዘማሪው እንዳለው “ምናምን” ካልተሰጣቸው “ትንቢት” አይናገሩምና፡፡

ዛሬ እንቅስቃሴው ከሃያ ዓመት በፊት እንደ ነበረው ከማንም ጋር መጋጨት አላስፈለገውም፤ በገዛ ቤተ ክርስቲያናችን፣ በገዛ መድረካችን፣ በገዛ አገልጋዮቻችን በአዲስ ልብስ አጊጦ፣ እንዳይነቀል ራሱን ተክሎ “መገለጫችን” የሆነ መስሏል፡፡ በዚህ ዘመን የወንጌላውያን ክርስትና ከ“ብልጽግና”፣ ከ“ከፍታ”፣ ከ“ድል ሕይወት” ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ሆኗል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ምእመናንም መስማት የሚፈልጉት ይህንን የ“ከፍታ ሕይወት” ብቻ ይመስላል፡፡ ለመሆኑ የእምነት እንቅስቃሴ በአሁን ጊዜ በምድራችን ራሱን እየገለጠባቸው የሚገኙ ናቸው የሚባሉ ማሳያዎች ምንድን ናቸው?

ፍጹማዊ የአንድ ሰው አመራር

ምንም እንኳን ግለ ሰቦች በቤተ ክርስቲያን አመራር ወይም በአጠቃላይ አገልግሎት ውስጥ ጉልሕ ድርሻ ሊኖራቸው ቢችልም፣ የእምነት እንቅስቃሴ አራማጆች ወይም በዚህ እንቅስቃሴ ተጽዕኖ ያደረባቸው ሰዎች፣ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ የአንድ ሰው ገደብ የለሽ አመራርን (autocratic leadership) የሚከተሉ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትን የሚያውቃቸው (ከኢትዮጵያ መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን በስተቀር) በማኅበራት ምዝገባ ደንብ መሠረት እንደ ሆነ ይታወቃል፡፡ የማኅበራት የአመራር አወቃቀር ደግሞ ክትትልንና ቁጥጥርን ግምት ውስጥ ያስገባና ላዕላይ ተጠሪነቱን ለመንግሥት ያደረገ ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ ይህ ዐይነቱ አሠራር ሕይወት የማይዘራባቸው “ቤተ ክርስቲያናት” ቁጥራቸው ጥቂት የሚባል አይደሉም፡፡ ከሕግ አስገዳጅነት የተነሣ የክትትልና የቁጥጥር አሠራር የዘረጉ ቢመስሉም፣ ስለ ተግባራዊነቱ ግን ጥያቄ ማንሣት ይቻላል፡፡

ግለ ሰቦቹ (መሪዎቹ) በዙሪያቸው የሚያስቀምጧቸው ሰዎች ፍጹም ታዛዥ የሆኑ፣ የቤተ ዝምድና ትሥሥር ያላቸው፣ የግለ ሰቡ ኅልውና የእነሱ ኅልውና እንደ ሆነ የሚያምኑ ወይም በጥቅም የተያዙ፣ ወዘተ… ዐይነት ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ለመሪዎቹ ምቹ ሁኔታን ይፈጥርላቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ለግለ ሰቡ የሚሰጠው መንሳፈዊ ሰብዕና በአሠራሩም ሆነ በአስተምህሮው ላይ ጥያቄ ለማንሣት አዳጋች የሥነ ልቦና ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው፡፡ ግለ ሰቡ በተከታዮቹ ዙሪያ ሊከስት የሚፈልገው ምስል ከመለኮትነት ያነሰ፣ ከሰብዓዊነት የገዘፈ የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው፡፡ ለራሱ የሚሰው “የማዕረግ” ስያሜ (ለምሳሌ፡- “ዐቢይ ነቢይ”፣ “የእግዚአብሔር ሰው”፣ “የእግዚአብሔር መልኣክ”፣ “ሐዋርያ”፣ “ነቢይ”፣ “የተቀባ”፣ ወዘተ…) ከሌላው ሰው ለየት ብሎ እንዲታይ ያደርገዋል፡፡ ይህንኑ የሚያራግቡ፣ ግለ ሰቡን በተከታዮቹ አእምሮ ውስጥ በፍጹማዊነት ደረጃ የሚያሰርፁና ዐይነተኛ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ የሚሠሩለት አጃቢዎች በዐይነትና በቁጥር ይኖሩታል፡፡ እነዚሁ አጃቢዎች መሪው ተጋብዞ በሚሄድባቸው ሌሎች ቦታዎች ሁሉ አብረውት በመሄድ ለመድረክ አገልግሎቱ ድጋፍ የሚያሰጡና ሕዝብ የሚያጯጩኹ ናቸው፡፡

በመሆኑም፣ መሪው በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ምትክ አልባ ሰው ተደርጎ ይቆጠራል፤ የሚፈጽማቸውም ማናቸውም ተግባራት ሕገ ወጥ የሆኑትን ጨምሮ ያለ ተጠየቅ ይፈጸማሉ፡፡ “በተቀባው ላይ እጅህን አታንሣ” የሚለው ያለ ጥያቄ የሚቀነቀንበት ስፍራ ቢኖር እዚህ ነው፡፡

ሀብት ማጋበስ

የእምነት እንቅስቃሴ ራሱን በኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች መካከል ከገለጠባቸው ባሕርያቱ አንደኛው መሪውና በዙሪያው ያሉ ሰዎች ለራሳቸው የሚያከማቹት ሀብት ነው፡፡ ከላይ የተገለጸው ፈላጭ ቆራጭ አመራር ከሚያጎናጽፋቸው “ትሩፋት” መካከል የንዋይ ክምችት አንዱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ባለው ነባራዊና ሕጋዊ የገንዘብ ማግኛ ሥርዐት፣ ይልቁንም ደግሞ የአማኝ ማኅበረ ሰቡን የገቢ አቅም ግምት ውስጥ አስገብቶ አንድ “አገልጋይ” በተጨባጭ በሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማካበት የሚያስችለው ምንም ዐይነት መንገድ የለም ማለት ጨለምተኝነት ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡ አሁን አሁን የምናየውና የምንሰማው ግን ይህንኑ ሆኗል፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት ድኽነት ያንገላታቸው የነበሩ “አገልጋዮች” ነጥቀውም ሆነ ገንጥለው በከፈቱት ቤተ ክርስቲያን መሪ በሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ በከተማችን ካሉ ባለጠጎች ጋር ሊያስደምራቸው የሚችል ሀብትን እንዴት ሊያገኙ ቻሉ? አንድ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጥ ሰውና አብዛኛውን ጊዜውንም ይህንኑ አገልግሎት ለመስጠት ሲዘጋጅ ለሚያሳልፍ ሰው ብር ያተመ እስኪመስል ድረስ እንዴት በትልልቅ የኢንቨስትመንት መስክ ሊሳተፍ ይችላል?

የሀብት ክምችት ስበቱ ከቦታ ቦታ፣ ከክልል ክልል፣ ከአገር አገር በተዋረድ የሚለያይ ሲሆን፣ ጥቂት የማይባሉ ግለ ሰቦች ግን ወደዚህ “መንፈሳዊ የሥራ ፈጠራ” ዘርፍ በከፍተኛ ፍጥነት እየገቡ መሆኑን መዘገብ “ከልማት ጋዜጠኞቹ” ጎራ ያስደምር ይሆን?

በመሠረቱ ʻእንዴት ሀብት ማጋበስ ቻላችሁ?ʼ ለሚለው ጥያቄ በአብዛኛው የሚሰጠው ምላሽ አመክንዮ በደረሰበት የማይደርስ ነው፤ ብሎም ጠያቂን ለማሞኘት የሚዳዳው ነው፡፡ ʻእገሌ የተሰኘ አፍሪካዊ/አሜሪካዊ አገልጋይ ወይም እገሊት የምትሰኝ አገልጋይ የግል አውሮፕላንን ጨምሮ እንዲህና እንዲያ አለው/አላት፤ ታዲያ የእኛ ምን ያስገርማል? እኛ እኮ የንጉሡ አምባሳደሮች ነን!ʼ ከሚለው ጀምሮ፣ ነገሩን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስመስሎ ለማቅረብ እስከሚደረገው ጉንጭ አልፋ ክርክር ድረስ ይዘልቃል፡፡

ከሞላ ጎደል እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ሀብት የሚያጋብሱበት ዐይነተኛው መንገድ ምእመናን ገንዘብ እንዲሰጧቸው በማግባባት/በማማለል፣ በዐሥራትና መባ ላይ ከፍተኛ አትኩሮት በማድረግ፣ አንዳንዴም ምእመናን ካልሰጡ እንደማይባረኩና “ነገሮቻቸው” ሁሉ እንደሚያዙባቸው በማስፈራራት ጭምር ነው፡፡ አሁን በቅርቡ እየተስተዋለ የመጣ እንግዳ ልምምድ ደግሞ፣ “ለተገለጠልህ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቅርብ” በሚል ሰባኪው ለተናገራቸው ንግርቶች ገንዘብ እንዲሰጥ የሚደረገው ዲስኩር ነው፤ በደረቁ አሜንታ አያዋጣም እንደ ማለት ነው፡፡

መሠረታዊ አስተምህሮዎችን ማናጋት

የእምነት እንቅስቃሴ አራማጆች የሚገለጡባቸው ሌላኛው ባሕርያት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱትንና በአባቶች የጸኑትን መሠረታዊ የክርስትና አስተምህሮዎችን (biblical and historical doctrines) ማናናቅና ከመሠረታቸው መናድ ነው፡፡ እነሱ ʻገባንʼ የሚሉት “ልዩ መገለጥ” መጽሐፍ ቅዱሳዊውንና ታሪካዊውን አስተምህሮ በግለ ሰቡ “መረዳት” ላይ እንዲመሠረት ያደርጉታል፡፡ በሌላ አባባል ላለፉት 2000 ዓመታት የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ያልተረዳችው “ልዩ አብርሆት” በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላሉት ለእነሱ ብቻ እንደበራ ያምናሉ፡፡ ከዚህም የተነሣ፣ የክርስትና እምነት የተመሠረቱባቸውንም ሆነ ለእምነቱ አስፈላጊ የሆኑትን አስተምህሮዎች አይቀበሏቸውም፡፡

እንደ ምሳሌ ለማንሣት ያህል፣ ሰውን ወደ መለኮትነት ደረጃ የሚያልቀው ትምህርት አንዱ ነው፡፡ “ሰው መንፈስ ነው”፣ “እኛ ትንንሽ አማልክት ነን”፣ “እግዚአብሔር ያለ ሰው ፈቃድ በምድር ላይ ሊሠራ አይችልም” እና የመሳሰሉት ትምህርቶቻቸው ከታሪካዊውና መጽሐፍ ቅዱሳዊው አስተምህሮ ለማፈንገጣቸው ማሳያዎች ናቸው፡፡ እንደውም የሰውን ታላቅነት ለማሳየት የእግዚአብሔርን ማንነት ማሳነስ የቀለላቸውም ጊዜ አለ፡፡ በየቴሌቪዥን ጣቢያው ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ የመለኮት ማንነት እንዳልነበረው፣ መለኮትነትም በጊዜ ሒደት በእግዚአብሔር የተሰጠው እንደ ሆነ በግልጽ ሲያስተምሩ እየሰማን ነው፡፡ የዚህ ዐይነቱ ትምህርት ዋናው አስፈላጊነት፣ ኢየሱስን ዝቅ አድርጎ ሰውን በማተለቅ የአምላክነት ደረጃ እንዲያገኝ ለማድረግ ነው፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ አስተምህሯዊ መሠረቶችን ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ሥርዐቶችንና የአመራር አካሄዶችን በክፉ ይኮንናሉ፤ አማኞችም እነዚህን ሥርዐቶች እንዳይቀበሉ ያሳምፃሉ፡፡ በሌላ አባባል ቀደምት አብያተ ክርስቲያናት በወግና በሥርዐት የተተበተቡና ለለውጥ ክፍት ያልሆኑ አድርገው ካቀረቡ በኋላ ለዚህ ችግር መፍትሔው እነርሱ ጋር ብቻ እንዳለ በመስበክ ምእመናን “ጮቤ ያስረግጣሉ”፤ የሚመጣውም “ተሃድሶ” በእነሱ አዝማችነት ምድሪቱን እንደሚያጥለቀልቅ “ያበሥራሉ”፡፡ ይህን የመሰለው ስልት ሥራ ላይ ከዋለ ዐሥርት ዓመታት ቢያልፉም፣ የሚባለው “ተሃድሶ” እስካሁን ሊታይ ግን አልቻለም፡፡ ምናልባት ታየ የሚባል ለውጥ ካለ የአማኞች ኪስ እየተራቆተ የእንቅስቃሴው መሪዎች መደለቡ ነው፡፡ “ተሃድሶ” የሚሉት ይህንን ይሆን እንዴ?!

ለክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር እና ለቅድስና ሕይወት ደንታ ቢስ መሆን

“የእምነት እንቅስቃሴ” አራማጆች አትኩሮት ምድራዊ ስኬት ላይ በመሆኑ ለመንፈሳዊው/ሰማያዊው ዕሴት የሚሰጡት ስፍራ ኮስሶ ይታያል፡፡ ስኬቱ የሚመዘንበት መለኪያም “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” ዐይነት ከመሆኑ የተነሣ፣ የአማኞች ሕይወት በሥነ ምግባርና በጽድቅ እንዲጎለበት ብዙ ምክር አይሰጠውም፡፡ በርግጥ፣ የእንቅስቃሴው አራማጆች ስለ ፍቅር ሲናገሩ ይደመጣል፤ ስለ እግዚአብሔር ያላቸው ሥዕልም በፍቅሩና በምሕረቱ ላይ ብቻ የተንጠላጠለ ይመስላል፡፡ በአንጻሩ ግን ስለ ጽድቁና ፈራጅነቱ ሲናገሩ አይደመጡም፡፡ ከዚህ የተነሣ የእንቅስቃሴው ተከታዮች መሆን ወይም መምሰል የሚፈልጉት “ክርስቶስ”፡- “ሀብታም የሆነውን”፣ “በሽታ የማያውቀውን”፣ “በስኬት ጎዳና ላይ የሚንጎራደደውን” ዐይነት ነው፡፡ አንድ አማኝ እግዚአብሔርን በመምሰል የሕይወት ጎዳና ላይ “የድል ሕይወት” ብቻ ሳይሆን፣ መገፋት እንደሚደርስበት፣ ስለ ስሙ መከራ እንደሚቀበልና መስቀሉን በመሸከም ሒደት ውስጥ የመፃተኛ ሕይወት እንደሚኖር አይነገረውም፤ እንዲህ ያለው ትምህርትም ጤነኛ “የክርስትና” ሕይወት ተደርጎም አይቆጠርም፡፡

ይህ ከመሆኑ የተነሣም፣ እንቅስቃሴው ተጽዕኖውን ያሳደረባቸው “ቤተ ክርስቲያናት” በበርካታ የሥነ ምግባር ችግሮችና በብልሹ የሕይወት ጎዳና ውስጥ የሚኖሩ ምእመናን ከማፍራት ውጪ ሌላ አማራጭ ሊኖራቸው አልቻለም፡፡ በሥነ ምግባር ጉድለትና በጽድቅ ሕይወት ዕጦት የቤተ ክርስቲያን ግሳፄ ደርሶባቸው ሕይወታቸውን እንዲመረምሩ የተደረጉ “አገልጋዮች”፣ ያለ ምንም ጥያቄ መድረክ እንዲያገኙ ይደረጋል፤ ጀብድ ፈጽመው እንደ መጡ የወንጌል ዐርበኞችም የክብር ስፍራ ይዘጋጅላቸዋል፡፡ በመሆኑም፣ የክርስትና እምነት መገለጫ የሆነው የጽድቅና የቅድስና ሕይወት “በአማኙ” ሕይወት ውስጥ ድርሻ ያጣል፡፡

ፍጹማዊ ጤና እና የብልጽግና አቀንቃኝነት

“የእምነት እንቅስቃሴ” ግንባር ቀደም መገለጫ ነው ከሚባለው መካከል ʻክርስቲያን አይታመምም፤ ድኽነትና ጉስቁልናም ከቶ አያውቀውምʼ የሚለው አመለካከት ነው፡፡ ለዚህ እንደ ማሳያ የሚሆን ንግግር እንውሰድ፡-

አንድ ኢትዮጵያዊ ሰባኪ እንዲህ ብለው ነበር፡-

“እኔ የእምነት ቃል አስተማሪ ነኝ … ክርስቶስ ያመጣውን በረከት ሁሉ የምናገኘው በእምነት ነው፡፡ … ኢየሱስ የኢያኢሮስን ሴት ልጅ ከሞት ሲያስነሣ ʻተኝታለችʼ ነው ያለው፤ ይህም ኢየሱስ ሞታለች የሚለውን ክዶታል፡፡ ተኝታለች ብሎ በመናገሩ ሪያሊቲውን ስለካደ ልጅቱ አልሞተችም፤ ነገር ግን ተኝታለች፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ የሞተውን ሰው ሳይሆን ያስነሣው ያንቀላፋውን ሰው ነው፡፡ ያስነሣው … ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ በሥጋ ይኖራል … አካል ነኝ የሚል ሰው ሥጋዊ ክርስቲያን ነው … እኔ በጭቃ ቤት ውስጥ የምኖር እንጂ ጭቃ አይደለሁም … በጭቃ ቤት ውስጥ የምኖረው ኀይሉ ነኝ … እኔ መንፈስ ነኝ … አካሌ ደግሞ ድንኳን ነው … የጭቃ ቤት ነው … ቁርበት ነው …፡፡ ዳግም የተወለድነው በመንፈስ ነው፤ የሥጋ ቋንቋ ደግሞ የስሜት ሕዋሳት ናቸው፡፡”[1]

ሌላ የውጪ አገር ሰዎች የሆኑ ባልና ሚስት ካሳተሙትና ወደ አማርኛ ከተመለሰው አነስተኛ መጽሐፍ ላይ የተወሰደ፡-

“… ሃይማኖታዊ ክርስትና ብዙዎችን ኪሳራ ውስጥ አስገብቷቸዋል … የገንዘብ ብልጽግና በክርስቶስ ያገኛችሁት መብታችሁ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ደግሞ በክርስቶስ የተፈቀደላችሁን የብልጽግና ሕይወት ወደ ገሃዱ ዓለም በማምጣት ሊገዛችሁ፣ ሊመራችሁ፣ ስፍራን ሊሰጣችሁ ይችላል፡፡ በቃሉ ስትጸኑ እግዚአብሔር ባቀደላችሁ መስመር ላይ እንድትገቡ ያደርጋችኋል፡፡ በዚህ መንገድ ድህነት የለም፡፡ … ሃሳባችሁና ንግግራችሁ ብልጽግና ይሁን ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ለእናንተ ነው፡፡ ʻእግዚአብሔር እረኛዬ ነው የሚያሳጣኝም የለም (መዝ 23፥1)ʼ… ቃሉ የእናንተን ብልጽግና ይመሰክራልና፡፡ ይህን እንደ እውነት ወስዳችሁ ብልጽግናን አንዱ የህይወት ጎዳናችሁ አድርጉ እንጂ ወደ ኋላ አታፈግፍጉ፡፡”[2]

የመጀመሪያው ጥቅስ ሕመምን መካድ ብቻ ሳይሆን፣ የክኅደት መሠረቱ ሰው መንፈስ መሆኑን ከማወቅ እንደሚጀመር ያስረዱበት ሲሆን፣ የክርስትና ጎዳናው ብልጽግና ነው የሚለው ደግሞ ሁለተኛው ነው፡፡

የተንሰራፋ ተጽዕኖ መፍጠር (Charismatic Dominianism)

ይህ እንቅስቃሴ በቅርቡ በአሜሪካ ምድር እንደ ተጀመረ ይነገራል፡፡[3] ታላቁ ተልእኮ ወንጌልን መስበክ ብቻ ሳይሆን፣ ኅብረተ ሰባዊ ለውጥ ማምጣት እንደ ሆነ የሚያምነው እንቅስቃሴ፣ ቤተ ክርስቲያን የወንጌል ስብከትንና ኅብረተ ሰባዊ ለውጥን በእኩል ደረጃ እንድትይዝ ኀላፊነት እንደ ተሰጣት ያምናል፡፡ በዚህም መሠረት፣ ቤተ ክርስቲያን ልትቆጣጠራቸው የሚገቡ “7 ተራሮች” አሉ፤ እነዚህም፡- መንግሥት፣ ሃይማኖት፣ ኪነ ጥበብና መዝናኛ፣ የመገናኛ ብዙኀን፣ ንግድ እና ቤተ ሰብ ናቸው፡፡ እነዚህም ተቋማት የሚመሩት በ“ሐዋርያት” እና በ“ነቢያት” ሲሆን፣ ለዚህም የሚሆኑ ሰዎች በመዘጋጀት ላይ እንደ ሆኑ ይነገራል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን እንቅስቃሴው እነዚህ 7 ተቋማት በ“ሐዋርያቱ” እና “ነቢያቱ” እስኪያዙና ኅብረተ ሰባዊ ለውጥ በምድር ሁሉ ላይ እስኪፈጸም ድረስ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምፅዓት እንደማይሆን የእንቅስቃሴው አመራሮች ያምኑበታል፡፡

የ“ዶሚኒዮኒዝም” እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ እግር ማስገባቱን የሚያምኑ ሰዎች አሉ፡፡[4] አንዳንድ ግለ ሰቦችና የሚመሯቸው ቤተ ክርስቲያናት ለዚህ እንቅስቃሴ ተገቢውን ዝግጀት በማድረግ ላይ እንዳሉም ይወራል፡፡ የተወሰኑትም በዚሁ ዓለም አቀፍ የ“ሐዋርያት” እና የ“ነቢያት” መማክርት ውስጥ የተመዘገቡ እንደ ሆነ ይነገራል፡፡

ማጠቃለያ

ይህን እንቅስቃሴ ለመከላከል በሚያስቸግር መልኩ በየቤተ ክርስቲያናችን ተንሰራፍቶ፣ በምእመናን አእምሮም ተሰግስጎ ይገኛል፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ “እነሱ” እና “እኛ” የምንልበት ጊዜው አልፏል፡፡ ጉዳቱ ደግሞ እውነተኛውንና ትክክለኛውን ወንጌል በሐሰተኛው በመቀየር ሰዎች በቅዠት ዓለም እንዲዋኙ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን፣ ቀጥተኛ በመሆነ መልኩ በአማኞች ሕይወት ላይ ጉዳት የሚያስከትል ጭምር ነው፡፡ እንቅስቃሴው የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎችን የመታከክ ስልት ያለው በመሆኑም፣ በትንቢትና በመገለጥ ስም ብዙዎችን አራቁቷል፤ ትዳር አስፈትቷል፤ አእምሮ አስጥሏል፤ ወዘተ…፡፡ በዚሁ ከቀጠለም፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች በፍጹም የስሕተት አካሄድ ውስጥ ላለመውደቃቸው ምንም ዋስታና አይኖርም፡፡

በመሆኑም፣ አብያተ ክርስቲያናትና ያገባናል የሚሉ ሁሉ ፍጥነትን የሚጠይቀውን ተገቢ ርምጃ መውሰድ አለባቸው፡፡ ካልሆነ ግን፣ በሥራ ሥነ ምግባር ከማመን ይልቅ በማይጨበጥ ተስፋ የሚኖር ተላላ ሕዝብ፣ ለማኅበራዊ ፍትሕና እኩልነት ደንታ የሌለውና ያንቀላፋ ዜጋ፣ የሞራልም ሆነ የሥነ ምግባር ልዕልና የጎደለው የሃይማኖት ማኅበረ ሰብ ለማየት ሩብ ክፍለ ዘመን አይፈጅም ማለት ነቢይ አያሰኝም፡፡

[1] Hailu Yohannes, Birth Right #1-#4 http://www.hyfm.org/Videos.16.htm

[2] ክሪስ እና አኒታ (2005). ራፕሶዲ ኦፍ ሪያሊቲ አማርኛ፤ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ላቭ ወርልድ ፐብሊሺንግ፤ ገጽ 50-51፡፡

[3] ዶ/ር ቴዎድሮስ አየለ፤ “ካሪዝማዊ ሁለን ገዝ ሥርዐት (Charismatic Dominionism) እና ኅብረተ ሰባዊ ለውጥ (Transformation)”፡፡ ቤተር ላይፍ ኢትዮጵያ ለአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች፣ ለሚኒስትሪዎችና ለሚመለከታቸው ግለ ሰቦች ባዘጋጀው ዐውደ ጥናት ላይ የቀረበ፤ መጋቢት 2004 ዓ.ም.፡፡

[4] ዝኒ ከማሁ

[1] Sinclair B. Ferguson and David F. Wright, eds. (2003). New Dictionary of Theology. Inter-Varsity press, Leicester, England.

Share this article:

ኢትዮጵያ የ“አረማዊ ደሴት”?


የእሬቻ በዓል በክርስቲያኑ ማኅበረ ሰብ መካከል መነጋገሪያ ሆኖ እንደ ሰነበተ ተከብሮ ዐልፏል። በዓሉ ተከብሮ ይለፍ እንጂ፣ መነጋገሪያነቱ አልቆመም፤ ምናልባትም ለመጭዎቹ ዘመናት እንዲሁ መነጋገሪያ እንደ ሆነ ይቀጥል ይሆናል። ባንቱ ገብረ ማርያም፣ “ኢትዮጵያ የ ‘አረማዊ ደሴት’?” ሲሉ የሰየሙት ይህ ጽሑፍ፣ በሮም ግዛት ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች፣ እንዲህ ላለው የአደባባይ በዓል የሰጡትን ምላሽ በታሪክ መነፅር እያስቃኙ፣ ለዛሬ ክርስቲያኖች መልእክት ያቀብላሉ። የባንቱ ገብረ ማርያም ጽሑፍ፣ የእሬቻ በዓልን በሚመለከት ለሚካሄደው ውይይት መፋፋት የራሱ ፋይዳ አለው በሚል እንደሚከተለው ለንባብ በቅቷል።

ተጨማሪ ያንብቡ

በሚድን በሽታ ተይዛ በሽታው እየገደላት ያለች አገር፦ኢትዮጵያ

“የሁሉንም ጆሮ ቀልብ ይዞ አንድን ዐሳብ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ማድረስ ካልተቻለ፣ እየተነጋገርን አይደለም ማለት ነው። እስካልተነጋገርን ድረስ ደግሞ መግባባት ፈጽሞ አንችልም። ካልተግባባን ደግሞ የሚድን በሽታችንን ማከም ስለማንችል፣ በሽታችን የምንኖር እስኪመስለን እያታለለን ወደ ሞት ይወስደናል። ታዲያ ምን ይሻላል?” ዘላለም እሸቴ (ዶ/ር)

ተጨማሪ ያንብቡ

የማንነት ስምምነት ካልቀደመ እየሠሩ ማፍረስ ይቀጥላል

አገራችንን በዚህ ጊዜ እየተፈታተናት ያለው ጉልሕ ችግር፣ በማንነት ላይ ያሉ ጥያቄዎቻችን ምላሽ ስላላገኙ ነው፤ ይህንንም በተገቢው መንገድ እስካልፈታን ድረስ ውጥረቶች መቀጠላቸው አይቀርም ይላል በሰላም ግንባትና በእርቅ ላይ ተመራማሪ የሆነው ሰሎሞን ጥላሁን።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.