[the_ad_group id=”107″]

ውግዘቱና የተሰጠው ምላሽ

“እኔ ያልገባኝ በእነዚህ ሰዎች እግዚአብሔር ተጠቅሞ አያውቅም እያላችሁ ነው? እኔ ብዙ ሲሠራባቸው ስላየሁ አከብራቸዋለሁ፡፡ ምናልባት ትምህርት ሲያስተምሩ በሚመርጡት የአነጋገር ሥነ ሥርዐት፣ አንዳንዴም የእኔነት መንፈስ ሲታይባቸው እኔም በግሌ አይመቸኝም፡፡ ይህም ማለት ግን እግዚአብሔር በእነሱ የሚሠራውን ሥራ ያሳንሰዋል ማለት አይደለም፡፡ እርሱ መርጦ የሚጠቀምባቸውን እኛ ልናወግዝ ማን ነን? …”

******

“ስለ ነቢይ እስራኤል ዳንሳ ብዙ ባላውቅም፣ በጉባኤው ተገኝቼ አውቃለሁ፡፡ በአገልግሎቱም ብዙ ሰዎች ተጠቃሚ (በብዙ መልኩ) እንደ ሆኑ ገምቻለሁ፡፡ እኔ የሚደንቀኝ ግን፣ እነዚህ ማኅበር መሥርተው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዝም ብለው ቁጭ ያሉ፣ የማያስተምሩ፣ ሞትንም ይሁን ሕይወትን የማይተነቢዩ፣ በመንፈስ ሳይሆን በጎጥ የሚመሩ ሰነፎች፤ ራሳቸውን ብቻ የሚያኖሩ፣ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ሆነው ሰውን ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ የጠፋባቸው፣ ትምህርታቸው የማያድስ፣ የአድማጭ ማጣት ያንገበገባቸው፣ …”

******

“መግለጫው ደኅና ነው፤ ግን እስራኤል ብቻ ምን በወጣው፤ ሁሉም እኮ ነቢያት አይደሉም፡፡ ግን አንድ ነገር ልበል፤ ድሮ ቢሆን ሐሰተኛ ነቢይ በድንጋይ ተወግሮ ነበር የሚጠፋው፤ ግን ዛሬ ስለሆነ እግዚአብሔር ይመስገን ተርፈዋል፡፡ ቢሆንም ግን ፍጥረት እግዚአብሔርን እንዳይመለከት ስላሰሩት ፍርዳቸውን ከጌታ ይቀበላሉ፡፡ በተረፈ ይህንን ጠማማና ምልክትን የሚፈልግን ክፉ ትውልድ፣ እስከሚገባው ድረስ በሙሉ ይረሱት፡፡ ያኔ ምሕረት ወደ አምላኩ ይለምናል፡፡”

******

“እግዚአብሔር አምላክ ይባርካችሁ! እኔ ብቻዬን ስቃጠልበት የነበረውን ነገር በእናንተ በኩል መፍትሔ አግኝቷልና ደስ ብሎኛል፡፡ ከዚህ በኋላ የመሠረተ ክርስቶስ አባል እሆናለሁ፡፡ ጌታ ይባርካችሁ! እነዚህ ከጌታ ጋር የተለማመዱ ደፋሮች፣ ስንቶቹ ትክክለኛ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ትተው ትንቢትና መገለጥ ወዳለበት እንዲሮጡ አድርገዋል፡፡ ይህ ለእናንተ የተገለጠው፣ የሰው ልጅ ከጥፋት መንገድ እንዲመለስ የታየው መንፈስ ለሌሎች ቤተ ክርስቲያናትም ይታይ፡፡”

******

የመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን መሪዎችንና ጠቅላላ ጉባኤ ጌታ እግዚአብሔር ይባርካችሁ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪከ የመጀመሪያ ፈር ቀዳጅ ውሳኔ እንደ ቤተ እምነት መውሰዳችሁ በሁለት ቢላዋ ለሚበሉ ትልቅ ትምህርት ይሰጣል፡፡

******

እነዚህ አስተያየቶች የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት እና የመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ሐሰተኞች ሲሉ ያወገዟቸውን ግለ ሰቦች ተከትሎ፣ ሕንጸት በማኅበራዊ ሚዲያው ላስነበበው ዜና ከተሰጡ በርካታ አስተያየቶች መካከል የተወሰዱ ናቸው፡፡ አስተያየቶቹ፣ በተወሰነ ደረጃ አማኝ ማኅበረ ሰቡ ለውግዘቱ የሰጠውን ምላሽ የሚያነጽባርቅ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ውግዘቱ በሁሉም ዘንድ ሙሉ ድጋፍም ሆነ ሙሉ ተቃውሞ አላገኘም፡፡ ግለ ሰቦቹ ʻለምን ተነኩ?ʼ የሚሉ እንዳሉ፣ ʻአበጃችሁ!ʼ ያሉ አሉ፡፡ የነገረ ጕዳዩ ምንነት ያልገባቸው ወይም ለውግዘት ሐሳብ አዲስ የሆኑ ደግሞ ግራ በመጋባት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡ በተለይ ጕዳዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይመለከተናል ያሉ ግለ ሰቦች የብዙኀን መገናኛን ተጠቅመው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የ“ነቢይ” እስራኤል ዳንሳ መንፈሳዊ አባት እንደ ሆነ የሚናገረው  “ሐዋርያው” ይዲዲያ … ይገኝበታል፡፡ “ሐዋርያው” ይዲዲያ በቪዲዮ ባስተላለፈው መልእክቱ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ያወጣው የውግዘት መግለጫ ፈጽሞ የተሳሳተና “መጽሐፍ ቅዱሳዊ መንገድን ያልተከተለ” ነው ሲል ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡

ውግዘቱ

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት ዓርብ መስከረም 26 ቀን፣ 2010 ዓ.ም. በጽ/ቤታቸው ጋዜጠኞችን ጠርተው “እስራኤል ዳንሳ ሐሰተኛ ነቢይ ነው” ሲሉ በይፋ ተናገሩ፡፡ እንደ መጋቢ ጻድቁ አብዶ ከሆነ፣ ግለ ሰቡ በተለያዩ ጊዜያት የተናገራቸው ትንቢቶች አለመፈጸማቸው ብቻ ሳይሆን፣ ትንቢቶቹ በእግዚአብሔር ቃል ሲመዘኑም ስሕተት መሆናቸው ጭምር ነው ለውግዘት ያበቃው፡፡

በዕለቱ ለጋዜጠኞች የተበተነው የኅብረቱ መግለጫ እንደሚለው ከሆነ፣ “እስራኤል ዳንሳ፣ 2009 ዓ.ም. ከመጠናቀቁ አስቀድሞ” ይፈጸማሉ ብሎ የተነበያቸው ትንቢቶች በተባለው ጊዜ አለመፈጸማቸውን ያወሳል፡፡ እነዚህም፡- “የኢትዮጵያ ሥርዐት ነቢይ በሚያወጣው ቃል ይቀጥላል፣ የፓርላማ አባላትና ነቢያት በጋራ ሕግ ያረቅቃሉ፣ የእነዚህ ተግባራት ክንውኖች በመንግሥት ቴሌቪዥን ለሕዝብ ይተላለፋል፣ የሚጠለፉ አውሮፕላኖች አሉ፣ በአገር ደረጃ የነቢያቶችና የሐዋርያት ስብሰባ ይደረጋል፣ ከሕገ መንግሥቱ የሚሻር አንቀጽ መኖሩ፣ በ2009 ዓ.ም. ከመጠናቀቁ አስቀድሞ እነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜ ያገኛሉ፣ ትንቢቶቹ ተፈጻሚነት ካላገኙ እስራኤል ዳንሳ (አገልግሎት/ነቢይነት) ይለቅቃል” ሲል የተናገራቸው እንደ ሆነ መግለጫው ይዘረዝራል፡፡

አያይዞም፣ “በወርኀ ሚያዝያ 2009 ዓ.ም. በተነበየው ትንቢት 2009 ዓ.ም. ከመጠናቀቁ በፊት ʻመጋቢ በቀለ ወ/ኪዳን 13 ታላላቅ ነቢያትን በሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ ውስጥ ይቀባልʼ ሲል ተንቢዮአል፤ ይሁን እንጂ ያ ትንቢት እንዳልተፈጸመ ይታወቃል” ሲል፣ እነዚህ ሁሉ በእግዚአብሔር ስም በድፍረት የተነገሩ የሐሰት ትንቢቶች ናቸው፤ እንደ ኅብረቱ መግለጫ፡፡

የኅብረቱ መግለጫ ከመውጣቱ በፊት በወረኀ ነሐሴ ላይ ለስብሰባ ተቀምጦ የነበረው የመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ ጉባኤ፣ በስም የጠቀሳቸውን የዐሥራ ሦስት ሰዎች አገልግሎት አልቀበልም ሲል ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡ ይህ የመሠረተ ክርስቶስ ውግዘት እንደ ኅብረቱ ለመገናኛ ብዙኅን በተሰጠ መግለጫ የተላለፈ ሳይሆን፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ባላት የአደረጃጀት መዋቅር ለምእመናን እና አገልጋዮቿ እንዲደርስ የተደረገ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለራሷ ምእመናን ብቻ እንዲደርስላት በሚል ውሳኔ ብታሳልፍም፣ ውሳኔው ከተላለፈ ከሁለት ወር በኋላ የደብዳቤው የመጨረሻ ገጽ ብቻ በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ይሠራጭ ጀመር፡፡ በዚህም የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አመራር ደስተኛ አለመሆኑን ነው ሕንጸት ከታማኝ ምንጮቹ ማረጋገጥ የቻለው፡፡

የመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ ጉባኤ ያሳለፈው ውሳኔ አስተምህሯዊ ጭብጥን መነሻ ያደረገ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ፣ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ጋር የማይስማማ ትምህርትን የሚያስተምሩ ማናቸውም ሰዎች፣ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት አባል እንኳ ቢሆኑ፣ የትምህርትና ስብከት ዕድል እንዳይሰጣቸው ያዝዛል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን፣ አስተምህሯዊ ዝንፈት ውስጥ ናቸው የተባሉ ግለ ሰቦች አገልግሎት በቴሌቪዥን፣ በካሴት፣ በመድረክም በቡድንም ሆነ በግል እንዳይካፈሉ፣ የሚካፈሉም ሆነ ምእመናን እንዲካፈሉ የሚያደርጉ እንደ ሁኔታው ከአባልነት እስከ መሰረዝ የሚደርስ የሥነ ሥርዐት ርምጃ እንዲወሰድባቸው ያስገድዳል፡፡

በዚህ መሠረትም ቤተ ክርስቲያኒቱ አባላቷ እንዲጠነቀቋቸው በሚል ዐሥራ ሦስት ሰዎችን ስም ጠቅሳለች፡፡ እነዚህም፡- ኀይሉ ዮሐንስ፣ ታምራት ታረቀኝ፣ ብስራት ብዙአየን፣ ፒተር ማርዲን፣ በላይ ሽፈራው፣ ብርሃኑ ዳና፣ እስራኤል ዳንሳ፣ ኤርሚያስ ሁሴን፣ ዳዊት ሞላልኝ፣ በረከት ዮሴፍ፣ ዘላለም ጌታቸው፣ ዳንኤል ጌታቸው እና ኤልሻዳይ አበራ ናቸው፡፡

ይህ የመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የውግዘት ውሳኔ ከላይ በተጠቀሱት ግለ ሰቦች ብቻ የሚቆም ሳይሆን፣ በቀጣይም የሌሎችን የሚያካትት እንደ ሆነ ነው የተነገረው፡፡ በተመሳሳይ ኅብረቱ፣ ይህንኑ የማውገዝ ርምጃ ይገፋበታል ወይ የሚለው ቁርጥ መልስ አልተሰጠውም፡፡ በርግጥ ይህንን በተመለከተ የኅብረቱ ፕሬዚዳንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ሌሎች ግለ ሰቦችም ወደ ፊት ተመሳሳይ የውግዘት ርምጃ ሊጠብቃቸው እንደሚችል ፍንጨ ሰጥተው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ፣ መቼ ይሆናል የሚለው እስከ አሁን የታወቀ አይደለም፡፡

የፕሬዚዳንቱ “እስር”

መሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የዐሥራ ሦስት ሰዎችን ስም ጥቅሳ ʻአትከተሏቸውʼ ስትል ለምእመናን የላከችው ደብዳቤ የመጨረሻ ገጽ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከተሠራጨ ቀናት በኋላ፣ የየካ ክፍለ ከተማ፣ ኮተቤ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ የክስ ደብዳቤ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ዋና ጽ/ቤት ደረሰ፡፡ ደብዳቤው በቀጥታ ፕሬዚዳንቱ አቶ ቴዎድሮስ በየነን የሚመለከት ሲሆን፣ መጥሪያው የደረሳቸው ረቡዕ ጥቅምት 29 ቀን፣ 2010 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ነበር፡፡ ቃል እንዲሰጡ ቀጠሮ የተያዘላቸው ደግሞ ዓርብ ኅዳር 1 ቀን፣ 2010 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3 ሰዓት ተኩል ላይ ነው፡፡ በተባሉት ሰዓት በስፍራው የተገኙት አቶ ቴዎድሮስ፣ መጥሪያ ደብዳቤው በሚለው መሠረት ዋሳቸውን ይዘዋል፡፡ አቶ ቴዎድርስ በየነ ለክስ የበቁበት ምክንያት፣ ነቢይ ኤርሚያስ ሁሴን የተባሉ ግለ ሰብ ስም በማጥፋት ወንጀል ስለከሰሷቻ እንደ ሆነ ቃላቸውን የተቀበለቻቸው መርማሪ ፖሊስ እንደነገረቻቸው አቶ ቴዎድሮስ በተለይ ለሕንጸት ገልጸዋል፡፡

ከነዋሳቸው በፖሊስ ጣቢያው የተገኙት ፕሬዚዳንቱ የሚጠበቅባቸውን ቃል ቢሰጡም፣ ከጣቢያው ግን በቀላሉ መውጣት አልቻሉም፤ ተጨማሪ ሰዓታት በጣቢያው እንዲቆዩ ተደረጉ፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ተመሳሳይ ክስ ከሌሎች ግለ ሰቦች የቀረበባቸው መሆኑ ነው፡፡ “ሌሎቹ ከሳሾች እነማን እንደ ሆኑ ግን በግልጽ አልተነገረኝም” የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ በዚህ ሁኔታ በፖሊስ ጣቢያው ከስድስት ሰዓታት በላይ እንዲቆዩ ተገደዱ፡፡ በመጨረሻም፣ የፕሬዚዳንቱ ምስጋና የተቸረው የክፍለ ከተማው የፍትሕ አካል፣ ጕዳያቸው በተገቢው የክስ ሂደት እንዲታይና ዋስትናቸው እንዲጠበቅላቸው በማድረጉ ከጣቢያው እንዲወጡ ተደረገ፡፡

በቂ ምላሽ ያለማግኘት ያስከተለው ውግዘት ወይስ ሌላ?

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት በመጋቢት 2009 ዓ.ም. ላይ አካሂዶት በነበረው 32ኛ መደበኛ ስብሰባው፣ በአስተምህሮ ዝንፈት፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ባልሆኑ ልምምዶችና በሞራል ውድቀት ላይ የአቋም መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ በዚያ መግለጫ ላይ፣ “የአስተምህሮ፣ የልምምድና የሞራል መንገድ ውስጥ ያሉ ቤተ እምነቶች፣ መገናኛ ብዙኀን እንዲሁም ግለ ሰቦች፣ ካሉበት የሳተ አካሄድ እንዲመለሱ በራችንን ክፍት አድርገን በክርስቲያናዊ ፍቅር ጥሪ እናደርጋለን” የሚለው መግለጫው፣ “ነገር ግን ይህን ለማድረግ ፈቃደኞች በማይሆኑትና በስሕተት መንገዳቸው ለመቀጠል በፈቀዱት ላይ ተገቢውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርምጃ” እንደሚወስድ አስታውቆ ነበር፡፡ 

አሁን ኅብረቱም ሆነ የመሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የወሰዱት የውግዘት ርምጃ፣ የቀዳሚው መግለጫ ተግባራዊ ርምጃ አካል ሆኖ እንዲታይ የተፈለገ ሳይሆን እንደማይቀር የሚያምኑ ወገኖች አሉ፡፡ በተለይ ኅብረቱ እስራኤል ዳንሳን “ሐሰተኛ ነቢይ ነው” ብሎ ባወገዘበት ዕለት፣ መጋቢ ጻድቁ አብዶ የቀደመውን የአቋም መግለጫ አስታውሰውት ነበር፡፡

የመጀመሪያው መግለጫ መውጣቱን ተከትሎ፣ ቊጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ʻለምን የግለ ሰቦቹ ስም በግልጽ አልተጠቀሰም?ʼ ሲሉ ይጠይቁ ነበር፤ መግለጫው በተሰጠበት ዕለትም ተመሳሳይ ጥያቄ ከጋዜጠኞች ቀርቦ ነበር፡፡ ለዚህ ጥያቄ ይሰጥ የነበረው መልስ፣ ʻየእርምት ርምጃ እንዲወሰድ ዕድል ለመስጠት ነውʼ የሚል ነበር፡፡ የመግለጫው አንቀጽ ተራ ቊጥር 8 ይህንኑ የሚገልጽ ይመስላል፤ “… ካሉበት የሳተ አካሄድ እንዲመለሱ በራችንን ክፍት አድርገን በክርስቲያናዊ ፍቅር ጥሪ እናደርጋለን”፡፡

እዚህ ላይ አከራካሪ ሆኖ ይቀርብ የነበረው ሐሳብ፣ “በራችንን ክፍት አድርገን በክርስቲያናዊ ፍቅር ጥሪ እናደርጋለን” በሚለው ጥሪ ተግባራዊነት ላይ ነው፡፡ ʻግለ ሰቦቹም ሆነ ቤተ እምነቶቻቸው ወደ ኅብረቱ መጥተው ከሳተው መንገዳቸው መመለሳቸውን እንዲታወቅ የሚያደርጉበት መንገድ እንዴት ያለ ነው? ኅብረቱስ ለጥሪው አዎንታዊ ምላሽ እንዲኖር ምን ተጨማሪ ጥረት አድርጓል?ʼ የሚል፡፡

ከኅበረቱ ጽ/ቤት አካባቢ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ፣ መግለጫው ከወጣ በኋላ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ፕሬዚዳንት፣ በኅብረቱ ካልታቀፉ ሌሎች ቤተ እምነቶች ጋር በጕዳዩ ላይ ውይይት ማድረጋቸውን፣ አንዳንዶችም አሁን ባለው እንቅስቃሴ ደስተኞች አለመሆናቸውን እንደነገሯቸው ተወርቷል፡፡ የውይይት መድረኩም እንዲቀጥል በሁለቱም ወገኖች መካከል ፍላጎት እንዳለም ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ከዚያ ስብሰባ የተገኘ ተጨባጭ ለውጥ ስለመኖሩ ከሁለቱም ወገኖች በይፋ የተነገረ ነገር የለም፡፡

ከሁሉም በላይ ግን፣ የኢትዮጵያ ቪዥነሪ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ ሚያዚያ 23 ቀን፣ 2009 ዓ.ም. የሰጠው አጸፋዊ መግለጫ፣ ኅብረቱ ተጨማሪ መንገድ እንዳይሄድ እንዳደረገው የሚያምኑ አሉ፡፡ ምንም እንኳን ኅብረቱ ለዚህ አጸፋዊ መግለጫ የሰጠው ይፋዊ መልስ ባይኖርም፣ ተጨማሪ የምክክርና የውይይት ጥረት እንዳያደርግ ተስፋ ሳያስቆርጠው አልቀረም፡፡ ይህንንም ተከትሎ ኅብረቱም ሆነ አባል ቤተ እምነቶቹ የራሳቸውን ርምጃ መውሰድ እንዲጀምሩ አድርጓቸዋል፡፡ አንዳንድ ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ፣ መሠረተ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን ተከትሎ፣ በኅብረቱ ውስጥም ሆነ፣ ከኅብረቱ ውጪ ያሉ ቤተ እምነቶች ተመሳሳይ ርምጃ ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡

መግለጫው ግቡን መትቶ ይሆን?

“ጠበብ ባለ ትርጕሙ አንድ ግለ ሰብ፣ ቡድን ወይም ተቋም በአንድ ሐሳብ፣ ዕቅድ፣ ዝግጅት ወይም ተግባራዊ እንቅስቃሴ በተመለከተ ያለውን ወይም የሚኖረውን ሐሳብ፣ እምነት፣ ውሳኔ፣ የሚያንጸባርቅበትና በጕዳዩ ላይ ያለውንና የወሰደውን አቋም ይፋ በማድረግ የሚያሳውቅበት መንገድ ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡” በሚል ለአቋም መግለጫ ትርጓሜ የሚሰጡት በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ባለሙያ የሆኑት አቶ አስፋው በላይ ናቸው፡፡ እንደ አቶ አስፋው ከሆነ፣ የአቋም መግለጫ በአብዛኛው በቀጣይ ለሚወሰድ ተግባራዊ ርምጃ መነሻ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ነው፡፡ “በሌላ አነጋገር ለተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲተባበሩት የሚፈልጋቸውን ወገኖች ለዐላማው አሰባስቦና አስተባብሮ ውጤቱን ለማምጣት እንዲችል የዐላማውን ምንነትና ከግቡም ለመድረስ የወሰደውን ቁርጠኝነት በመግለጽ አጋሮቹን፣ ደጋፊዎቹን በሐሳብ አስተሳስሮ ወደ ተግባር የሚገባበትና የሚያስገባበት መረማመጃ ነው፡፡” ይላሉ አቶ አስፋው፡፡

ይህንን የአቶ አስፋውን ብይን መነሻ አድረገን፣ ʻኅብረቱ ከዘጠኝ ወራት በፊት ያወጣው የአቋም መግለጫ የሚፈለገውን ውጤት አምጥቷል ወይ?ʼ የሚለውን ጥያቄ የምናነሣበት ጊዜ ላይ ሳንደርስ አንቀርም፡፡ በርግጥ መግለጫው በአማኝ ማኅበረ ሰቡ ዘንድ ትልቅ መነጋገሪያ ርእስ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ የመግለጫውን መውጣት ተከትሎ በተለያዩ ወገኖች ይሰጡ የነበሩ የተቃውሞና የድጋፍ ምላሾች አማኝ ማኅበረ ሰቡን ቢያንስ ለሁለት ከፍለውት ሰንብተዋል፡፡ ልዩነቱን በራሱ እንደ ግብ አድርገው የሚመለከቱ ወገኖች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ፣ የተፈጠረው ልዩነት በአንድ ቤተ እምነት ውስጥ ያሉ ምእመናንን/አገልጋዮችን ከመክፈል አልፎ፣ በአንድ ቤተ ሰብ መካከል የከረረ ጠብ ካስነሣ፣ መግለጫው የያዘው ዐቢይ ጭብጥ ወይም መነሻ ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ ለአማኝ ማኅበረ ሰቡ የደረሰበትን መንገድ መፈተሽ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡

“የአቋም መግለጫን ማውጣት ብቻ ሳይሆን፣ መግለጫው ከመውጣቱ በፊትም ሆነ ከወጣ በኋላ ለፍሬያማነቱ መሠራት ያለባቸው ነገሮች ትልቁን ስፍራ ይይዛሉ፡፡” የሚሉት አቶ አስፋው፣ “የአቋም መግለጫ በተጠና፣ በእውቀት ላይ በተመሠረተ፣ የችግሮችን መነሻ፣ የሚያስከትሉትን ጉዳት፣ አቋሙን የሚቃወሙ ክፍሎች ቢኖሩ ሊሄዱበት የሚችሉበትን ርቀትና በአፈጻጸም ላይ ችግሮች ቢከሰቱ የሚተገበረውን ተለዋጭ አካሄድ፣ የመሳሰሉትን ያከተተ ግልጽ የሆነ ዕቅድ” ሊኖረው እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡

ይህንንም ለማድረግ በራሱ በአብያተ ክርስቲያናት ኅብረት አመራር መካከል በጕዳዩ ላይ ጽኑ የአቋም አንድነት እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ከኅብረቱ ውጪ ያሉና በአገሪቱ የወንጌል ሥራ ላይ ጉልሕ ድርሻና ተሰሚነት ካላቸው አብያተ ክርስቲያናት ጋር በቅርበት መሥራት፣ ቢቻል እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ጕዳዩን በባለቤትነት እንዲይዙት ሁኔታዎችን ማመቻቸት ተገቢ ነው፡፡ ምእመናን ስለተወሰደው ርምጃ ተገቢውን ግንዛቤ እንዲያገኙ ባሉት የብዙኅን መገናኛ ዘዴዎች ተከታታይ የሆኑ መልእክቶችን ማቅረብ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ በተለይም፣ ጕዳዩ ይመለከተናል በሚሉና አሉታዊ ምላሽ በሚሰጡ ቡድኖች ለሚነሡ ተገቢነት ያላቸው ጥያቄዎች ትዕግስት በተሞላው መልኩ ምላሽ መስጠት ብዥታን ለማጥራት ዐይነተኛ መንገድ ይሆናል፡፡ በተቻለ መጠን ጕዳዩ የአንድ ግለ ሰብ ወይም የተወሰኑ ቡድኖች ብቻ ሆኖ እንዳይታይ፣ የተለያዩ ቤተ እምነት መሪዎችንና አገልጋዮችን በማሳተፍ የበለጠ ወደ ሕዝብ እንዲደርስ ማስቻል ተገቢነት አለው፡፡ ምን ጊዜም ቢሆን ስለ ጕዳዩ ፍቅርንና ርኅራኄን በተላበሰ መልኩ ለማስረዳት መሞከር፣ የሚወሰዱ ርምጃዎች በሙሉ ለምእመናን ደኅንነት ሲባሉ እንደሚደረግ ምእመናን እንዲረዱት ማድረግ፣ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን መካከል የሚፈጠሩ አላስፈላጊ ክፍተቶች እንዲጠብቡ ያደርጋል፡፡

ከውግዘት ባለፈ…

ከቶ ነገር ቤተ ክርስቲያን እዚህ ቅርቃር ውስጥ እንዴት ልትገባ ቻለች? የሆነው ሁሉ ለምን ሆነ? መግለጫና ውግዘትስ ችግሩን ያስቀረው ይሆን? በርግጥ እነዚህ ሰፊና ጥልቅ ትንታኔ የሚሹ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ፣ መሠረታዊ የሆኑት ችግሮቻችን ደግሞ ያን ያህል የረቀቁና የተሰወሩ ደግሞ አይደሉም፡፡

“አሁን ያለው እንቅስቃሴ ጅማሬው አሁን አይደለም፤ ምናልባት አሁን በከፍተኛ ደረጃ እየተባዛ መጣ እንጂ” የሚለው በኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን፣ ጎተራ አጥቢያ በመጋቢነት የሚያገለግለው መጋቢ ዮሐንስ አፈወርቅ ነው፡፡ እንደ መጋቢ ዮሐንስ አመለካከት፣ አሁን ተንሰራፍቶ ያለው ችግር ሊመጣ እንደሚችል ቀድሞ ምልክቶች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያን ቀድማ ልትሠራው የሚገባትን ሥራ ባለመሥራቷ ብዙ ጥፋት መምጣቱን ነው መጋቢ ዮሐንስ አጽንኦት የሚሰጠው፡፡ “የተለያዩ ትምህርቶች ሲነሡ፣ አብያተ ክርስቲያናት የነበራቸውን ሕዝብ፣ የነበራቸውን የተደማጭነት አቅም፣ የነበራቸውን የሰውም ሆነ የቊስ ሀብት በመጠቀም፣ ነገሩ ሥር ሰድዶ ሌላ ፍሬ እንዳያፈራ የሠሩት ሥራ አልነበረም፡፡ ሁልጊዜም ማውገዝ ነው፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተለመደ ነገር ነው፤ ማውገዝ ብቻ ነው፡፡” ይላል፡፡

“አንድ ትክክል ያልሆነን ነገር ማወቅ፣ የእኛን ትክክለኛነት አያሳይም” የሚለው ደግሞ፣ በኤጳፍራ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በዋና መጋቢነት የሚያገለግለው ቸርነት በላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ይህን መሰሉ ችግር ውስጥ የገባችው ከእግዚአብሔር የተሰጣትን ዐቢይ ተልእኮ ስለዘነጋችው ወይም በሌላ ስለተካችው ነው፡፡ “ያወጣነውን መመለስ አለብን፡፡ የወጣው በቦታው መመለስ አለበት፡፡ ከየአገልግሎታችን ውስጥ ያወጣነውን እውነት፣ ቦታው ላይ መመለስ አለብን፤ ያም የክርስቶስ ወንጌል ነው፡፡ እሱን ስንመልሰው የሚስተካከል፣ (ሙሉ ለሙሉ የሚሰተካከልና የሚጠፋም ባይሆንም) ቤተ ክርስቲያንን ወደ ነበረችበት አቋሟ፣ ወደ ነበረችበት መልክ የሚመልሳት ይሆናል፡፡” ይላል መጋቢ ቸርነት በላይ፡፡

“ቤተ ክርስቲያን ይህን ዐቢዩን መልእክት እንዴት በሌላ ቀየረችው?” ለሚለው ጥያቄ ምላሹን የሚሰጠው መጋቢ ቸርነት፣ ነገሩ በአንድ ጊዜ የሆነ ሳይሆን ቀስ በቀስ፣ በሂደት እንደ መጣ ነው የሚያስረዳው፡፡ “እንደ ቀልድ ነው የወጣው፡፡ ከዚህ በፊት በነበረው የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ፖለቲካ፣ ሰዎች የራሳቸውን ልምምዶች፣ የራሳቸውን ስሜትና ፈቃድ ማንጸባረቅ ሲጀምሩ ዋናው ቀስ እያለ” ወጣ ይላል፡፡ አክሎም፣ “…በሎዶቂያ የሆነው እኮ ይኸው ነው! ʻአለኝ፤ አግኝቻለሁ፤ ባለ ጠጋ ነኝ፤ አሁን ሁሉም ነገር አለኝ፤ አንዳች ነገር አያስፈልገኝምʼ ማለት ስትጀምርና ቀስ እያለች የማይሆን ነገር ስታስገባ ኢየሱስ ወጣ፡፡ ʻእነሆ፤ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁʼ ያለው እኮ ለቤተ ክርስቲያን ነው እንጂ፣ በውጪ ላሉት ሰዎች አይደለም፡፡ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ምድራዊ ነገሮች ስትያዝ፣ ዓለማዊ በሆኑ ነገሮች ስትያዝ፣ በሰዎች ፍላጎቶች ስትያዝ፣ የሰዎችን ምኞትና ፍላጎት ለመሙላት መንቀሳቀስ ስትጀምር፣ የእግዚአብሔር የልብ ሐሳብ የሆነውን ክርስቶስን ከቤተ ክርስቲያን እንድታወጣው ምክንያት ሆኗል፡፡” ሲል ችግሩ እንዴት ዘልቆን እንደ ገባ ያብራራል፡፡

በሁለቱ መጋቢያን የተሰጡት የችግሩ መንሥኤዎች ሙሉእ ላይሆኑ ይችሉ ይሆናል፤ በእነዚህ ላይ ርእቱ የሆኑ ሌሎች መንሥኤዎች ሊታከሉበት ይችላሉና፡፡ ይሁን እንጂ፣ ሁሉንም እውነት ፈላጊ ሊያስማማ የሚችል መሠረታዊ ጕዳይ ደግሞ አለ፤ ይህም የእግዚአብሔር ቃል በቤተ ክርስቲያን ተገቢውን ስፍራ ማግኘት መቻሉ ነው፡፡ “ወንጌላዊ ነኝ” የሚለው ይህ አማኝ ማኅበረ ሰብ፣ ልምምዱንም ሆነ አስተምህሮውን የሚመሠርተው በመጽሐፍ ቅዱስ ፍጹም ባለ ሥልጣንነት ላይ ቆሞ ነው፡፡ ከሌሎች ቀደምት የክርስትና ቤተ እምነቶች ለቀቅ ወደዚህኛው የሚፈልሰውም፣ ʻአስተምህሮዎችና ልምምዶች ከእግዚአብሔር ቃል አንጻር አፈንግጠዋልʼ እያለ ነው፡፡ ታዲያ፣ እዚያ የማይሠራው፣ እዚህ ሲመጣ እንዴት ሊሠራ ይችላል?

ነህሚያ ገጥሞት የነበረውን መንፈሳዊ ችግር ለመፍታት የወሰደው ርምጃ፣ ወደ እግዚአብሔር ቃል የሚያመለክት እንደ ነበር የሚያስታውሰው መጋቢ ቸርነት፣ ዛሬም እኛ ማድረግ የሚገባን ተመሳሳዩን እንደ ሆነ ያሠምርበታል፡፡ “መጽሐፍ ቅዱሳችን በእነ ነህሚያ ጊዜ የነበረውን ችግር ለማስተካከል የተሾሙት ሰዎች ራሳቸው የችግሩ ምክንያት ሆነው ተገኝተዋል፡፡ የቅጥሩ መሠራት በነህሚያ ከተፈጸመ በኋላ፣ ትልቁን የበግ በር የሠራው ኤልያሴም ካህን ሆኖ በታላቁ ቤተ መቅደስ ተሹሞ የነበረ ነው፡፡ ይህ ሰው ነው እንግዲህ ከጦቢያ ጋር የተወዳጀው፡፡ … ኤልያሴብ ያደረገው ʻታላቁን ጓዳ ለጦቢያ ለቀቀለትʼ ይላል፡፡ … ነህሚያ ሲመጣ፣ ʻጦቢያ ያደረገውን ነገር አስተዋልሁʼ ይላል፤… ከዚያም ʻየታላቁ መጽሐፍ ይከፈትʼ አለ፡፡ የሕጉ መጽሐፍ ሲከፈት፣ ʻሞዓብ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባʼ የሚል ተጽፎ አገኘ፡፡ ከዚያ እንደ እግዚአብሔር ቃል መሠረት፣ በሕጉ መሠረት ትክክለኛ ርምጃዎችን ሲወስድ እናያለን፡፡ አሁንም ለተፈጠሩት ችግሮች መፍትሔ የሚሆነው መጽሐፍ መክፈት ነው፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል ከፍተን፣ እንደ እግዚአብሔር ቃል ያልሆኑት ነገሮች በሙሉ ለማስወጣት ርምጃ መውሰድ አለብን፡፡ … ʻጦቢያን አወጣሁ፣ ጣልኩኝ፤ ከዚያ የወጡትን ዘማሪዎችና ካህናት መለስኩኝ፤ ከዚያ የማንጻት ሥራ ሠራኹʼ ይላል፡፡ በዚህም ርምጃ የጠፋው የቤተ መቅደሱ ሥርዐት እንደ ገና ተመልሶ ሲቆም እናየዋለን፡፡ … ስለዚህ ሁሉም ሰው ወደዚህ እውነት መመለስ አለበት ብዬ ነው የማምነው፡፡” ይላል መጋቢ ቸርነት በላይ፡፡

አሁን ያለውን የተበላሸ አካሄድ ለማረቅ “አንድ ንቅናቄ (movement) ያስፈልገናል ብዬ ነው የማስበው” የሚለው የጎተራ ሙሉ ወንጌል መጋቢ የሆነው መጋቢ ዮሐንስ አፈወርቅ ነው፡፡ “ኢየሱስ ክርስቶስ በጣም በገዘፈ የሃይማኖት ሥርዐት ባለበት ዓለም ውስጥ ነው የመጣው፡፡ ልክ እኛ እንዳለንበት ዘመን፣ ፈሪሳውያኑ አሉ፤ ቀናተኞቹ አሉ፤ ሰዱቃውያኑ አሉ፤ ብዙ ዐይነት ጎራዎች (sects) ነበሩ፤ በእነዚህ ጎራዎች መካከል መጥቶ ያንን ለማደስ አይደለም ብዙ ሥራ ሲሠራ የሚታየው፡፡ ከዚያ ሥርዐት ውጪ የሆነ ንቅናቄ ነው የፈጠረው፡፡ እኛም ጋ ቅሬታዎች አሉ፤ በመካከል ያሉ፤ እውነተኛው፣ ትክክለኛው ወንጌል፣ ጸጋ ስጦታዎችን በትክክለኛው መንገድ መሄድ አለባቸው፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታዎች መቀጠል አለባቸው የሚሉ አሉ፡፡ እነዚህን ተከትሎ የሚሄድ ንቅናቄ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ትንሽ ሊሆን ይችላል፤ ለጊዜው እንቅስቃሴው በጣም ዋጋ የሚያስከፍል ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ፣ እንዲህ ያለው ንቅናቄ ይመስለኛል ይህንን በውግዘት የማናፈርሰውን ሥርዐት (system) ሊጥልልን የሚችለው፡፡” ይላል መጋቢ ዮሐንስ፡፡

የማይቀረው “እነሱ” እና “እኛ” እየመጣ ይመስላል

ውግዘት ካለ መለየት አለ፡፡ ʻአንተ አትወክለኝም፤ እኔን አትመስልም፤ ስለዚህም አንድነት/ኅብረት የለንምʼ ማለት አለ፡፡ ለበርካታ ዐሥርት ዓመታት የቤተ እምነት ልዩነት እጅግም ጎልቶ ያልታየበት የኢትዮጵያ ወንጌላዊው ክርስትና፣ አሁን በሌላ አቅጣጫ እየተጓዘ ያለ ይመስላል፡፡ በርግጥ ለዚህ አዲስ “የልዩነት ጕዞ” ምን ያህሉ አማኝ ዝግጁ እንደ ሆነ ማወቅ ባይቻልም፣ መጪው ጊዜ ግን ከዚህ ውጪ ሌላ አማራጭ ያለው አይመስልም፡፡ “በእናንተ ዘንድ ያለውን መንጋ ጠበቁ” የተባለውን ታላቅ ኀላፊነት ለመወጣት ጥረት በሚያደርገው አካልና ነባሩን በሌላ ለመተካት ላይ ታች በሚለው መካከል የሚኖረው ፍትጊያ በመጪዎቹ ዘመናት ሊቀጥል ይችላል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ሲቆለጳጰስ የኖረው የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች አንድነት/ኅብረት፣ “የጫጕላ” ጊዜውን ጨርሶ ይሆን?

Mikyas Belay

ሚክያስ በላይ የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር መሥራችና ዳይሬክተር ሲሆን፣ የሕንጸት ሚዲያ ዋና አዘጋጅ ነው። በኢቫንጄሊካል ቲዎሎጂካል ኮሌጅ በሥነ መለከት ጥናት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካ ጥናት የማስተርስ ዲግሪ ሠርቷል።

Share this article:

“እግዚአብሔር፣ ያልተቀደሰች ቤተ ክርስቲያንን ፈጽሞውኑ መኖርያው አያደርግም” – ቻርልስ ሀደን ስፐርጀን

ግርማ በቀለ (ዶ/ር)፣ የታዋቂውን እንግሊዛዊ የወንጌል ሰባኪና አስተማሪ ቻርልስ ሀደን ስፐርጀንን ግለ ታሪክ መነሻ አድርገው ባቀረቡት በዚህ ጽሑፍ፣ ስፐርጅን ያለፈበትን አስቸጋሪ የሕይወት ትግል፣ ስለ ወንጌል ንጽሕና ሲል የተጋፈጣቸውን ዕቡያን እንዲሁም፣ በጽናት የተደመደመውን የድል ሕይወት ያስቃኙናል።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.