
የካታኮምብ ዋሻዎች
“የጥንት ሮማዊያን እንደ እነዚህ ያሉ ቦታዎችን የሠሯቸው ሞትን ከመጥላትና ከመፍራት የተነሣ፣ ስለ ሞት ላለማሰብ በሚል ነበር። እነዚህን ስፍራዎች ግን ክርስቲያኖች በአንጻራዊ ነጻነት የማምለኪያ ስፍራ አድርገው ይጠቀሙበት ነበር።”
[the_ad_group id=”107″]
ሳይንስ እና ክርስትና የእግዚአብሔርን ሕልውና በሚመለከት የሚቃረኑ አስተምህሮዎችን እንደሚያራምዱ ብዙዎች ያስባሉ፡፡ አንዳንዶች፣ “ሳይንስ ያለውን ይበል፤ እኔ ግን መጽሐፍ ቅዱሴን አምናለሁ” ሲሉ፣ በተቃራኒው ያሉት ደግሞ “ሳይንስ የእግዚአብሔርን አለመኖር በበቂ ሁኔታ አረጋግጦታል” በማለት ይናገራሉ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ሳይንስ እግዚአብሔርን “ዜሮ እንደማያወጣው” እና አምላክ አለመኖሩን እንደማያረጋግጥ ሳይንሳዊ ግኝቶችን ተመርኩዘን ለማየት እንሞክራለን፡፡
የእግዚአብሔር ቃል ለሳይንሳዊ ሐሳቦች በቂ ምክንያት የሚሆኑ መሠረታዊ መርሖችን ይዟል፡፡ ለምሳሌ፣ ምድር ጅማሬ እንዳላት ዘፍጥረት 1፥1 ያትታል፤ ሳይንስም ቀጥለን እንደምናየው ስለ ምድር ጅማሬ ይነግረናል፡፡ እንደዚሁ ደግሞ ምድር በቅጡ እንደ ተበጃጀች እና ለመኖር ምቹ እንደሆነች መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል (ዘፍ. 1፥3-31)፡፡ ሳይንስም ይህንኑ እውነታ “fine tuning” በማለት የሚገልጽልን ሲሆን፣ የዚህን አስተምህሮ ፍሬ ሐሳብ በሌላ ዕትም በዝርዝር የምንመለስበት ይሆናል፡፡ በተጨማሪም የምድር ሥርዐት ወደ መቃወስ እንደሚያመራና ምድርም አንድ ቀን እንድምትጠፋ መዝሙር 102፥25-26 ሲነግረን፣ ሳይንስም ይህንኑ እውነታ “entropy” በተሰኘው ሰፊ ሐሳብ ውስጥ ያስቀምጥልናል፡፡
እነዚህን ሐሳቦች ያነሣኋቸው ለናሙናነት እንጂ ክርስትና እና ሳይንስ እንደማይቃረኑ የተሟላ ማረጋገጫ እንደሚሆኑ በማሰብ አይደለም፡፡ በርግጥም የተነጠሉ ምሳሌዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ነቅሶ በማውጣት “ክርስትና እና ሳይንስ ይስማማሉ፤ ብሎም አንዱ የሌላውን እውነተኛነትና አመዛዛኝነት ያረጋግጣል” ማለት ከመጽሐፍ ቅዱስ ሥነ አፈታት መርሖዎች አንጻር ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ የጽሑፋችንን የሙግት ሐሳብ፣ ማለትም ሳይንስ የእግዚአብሔርን አለመኖር እንደማያረጋግጥ በምክንያትነት ለማስደገፍ የመረጥኩት ለእግዚአብሔር መኖር የቀረቡ ሳይንሳዊ ሙግቶችን በመተንተን ነው፡፡ በዚህ ዕትም አንዱን ሙግት ብቻ፣ ማለትም ሥነ ፍጥረታዊ ሙግትን (the Cosmological argument) እንመለከታለን፡፡
የዚህ ሙግት መደበኛ አመክንዮ በሁለት የመነሻ አቋሞች (premises) ላይ ተመርኩዞ አጽናፈ ዓለሙ (Universe) መነሻ እንዳለው ማመላከት ነው፡፡ ይህም በቀላሉ እንደሚከተለው ሊቀርብ ይችላል፡-
የመጀመሪያው የመነሻ አቋም ምንም ነገር ያለ ጅማሬ እንዲሁ እንደማይመጣ ይናገራል፤ ይህን ደግሞ ሳይንስም ሆነ የግል ተሞክሮዎች ያረጋግጡልናል፡፡[1]አጽናፈ ዓለሙ ካለመሆን ወደ መሆን ለመምጣቱ ዋነኛው ሳይንሳዊ ማረጋገጫ የተገኘው እ.ኤ.አ. በ1929 ኸብል (Hubble) በተባለ የከዋክብት (የሥነ ፈለክ) ተመራማሪ ነው፡፡[2] የኸብልን ግኝት ለመረዳት በአገራችን የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የፊዚክስ ሥርዐተ ትምህርት ወደተካተተው “Doppler Effect” የተሰኘ የፊዚክስ ኀልዮ እንሂድ፡-
አንድ አምቡላንስ እኛ ወደቆምንባት ቦታ እየመጣ እንደ ሆነ እናስብ፡፡ አምቡላንሱ በቀረበን ቁጥር የአደጋ ጊዜ ደወሉ ድምፅ እየጨመረ ይመጣል፤ ዐልፎን ሲሄድ ደግሞ ድምፁ ይቀንሳል፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያት መኪናው ወደኛ እንዲመጣ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ የተነሣ ሲሆን፣ ይህም የድምፁን ሞገድ (wave length) እየቀነሰ፣ ድግግሞሹን (frequency) ግን ይጨምረዋል፡፡ መኪናው ዐልፎን ሲሄድ ደግሞ ሞገዱ እየረዘመ፣ ድግግሞሹ ደግሞ ይቀንሳል፡፡ ረጃጅም ሞገዶች ወይም ዝቅተኛ ድግግሞሾች ደግሞ ወደ ዝቅተኛ የድምፅ ኖታዎች ስለሚመሩ፣ አምቡላንሱ በራቀን ቁጥር ድምፁም እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ ብርሃንም ከድምፅ ጋር ተመሳሳይነት አለው፤ በውስጡ ከያዛቸው የተለያዩ ሞገዶች ያሏቸው ቀለማት የተነሣ ተለዋዋጭነት ይታይበታል፡፡ ይህም በተለይ በከዋክብት ክምችቶች (galaxies) ላይ በተደረገው ጥናት ተስተውሏል፡፡ እንደ ጥናቱ ከሆነ በርቀት ያሉ የከዋክብት ክምችቶች እየተቀራረቡ በመምጣት ፋንታ እርስ በርስ እየተራራቁ ይሄዳሉ፤ ርቀታቸውም ሲጨምር የግስገሳ ፍጥነታቸውም ይጨምራል፡፡ ኸብል ይህን ያጤነው የከዋክብት ክምችቶቹ ከሚያፈልቁት ብርሃን በመነሣት ነው፡፡ እናም በዚህ አስተውሎት ላይ በመመርኮዝ አጽናፈ ዓለም እየተለጠጠ መሆኑን መረዳት ተቻለ፡፡[3]
እንዲሁም ደግሞ አጽናፈ ዓለም እየተለጠጠ እንደ ሆነ ኸብል የደረሰበትን ድምዳሜ የሚያረጋግጥ ሌላ ሳይንሳዊ ግኝት በ1965 ተፈጠረ፡፡[4] በየአቅጣጫው ተመሳሳይ መጠን ያለው ኀይለ መንፈስ (energy) በጨረር እየተረጨ እንዳለና ይህም ኀይለ መንፈስ ደግሞ አጽናፈ ዓለሙ እየተለጠጠ እንዲመጣ ካደረገው የመጀመሪያው ፍንዳታ የተለቀቀ መሆኑ ታመነበት፡፡ ስለ Big Bang theory መነጋገር የዚህ ጽሑፍ ትኩረት አይደለም፡፡ ለጊዜው በ1929 እና በ1965 በሳይንቲስቶች የተስተዋሉት እነኚህ ሁለት ግኝቶች ምድር እየሰፋች እንዳለችና ጅማሬዋ ደግሞ ከፍንዳታው እንደ ተነሣ ለማየት በቂ መረጃ መስጠታቸውን ማስተዋሉ ይበቃል፡፡ ይህ ማለት ሁሉም ቁስ (matter) እና ኀይለ መንፈስ ጊዜን እና ጠፈርን (space) ጨምሮ መነሻ አለው ማለት ነው፡፡
ክርስትና የምድርን ጅማሬ ከእግዚአብሔር የመፍጠር ሥራ ጋር ያያይዘዋል፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት ምድር ሁሌም አልነበረችም ማለት ነው፡፡ ሳይንስ “የፍንዳታውን መንሥኤ ይህ ነው” ባይለንም፣ “ምድር እና ሞላዋ” ጅማሬ እንዳላቸው ከላይ ባየነው መልኩ ያረጋግጥልናል፡፡ ይህም፣ ነገርን ሁሉ ወደ መሆን ያመጣ ፈጣሪ አለ ብሎ የማመንን ሥነ ፍጥረታዊ ሙግት ሙሉ በሙሉ ባያረጋግጠውም ምክንያታዊነቱንና አመክንዮአዊ ጎኑን ያጠናክረዋል፡፡ በሌላ አነጋገር ብዙዎች እንደሚገምቱት ሳይንስ የእግዚአብሔርን አለመኖር አያረጋግጥም ማለት ነው፡፡
በተከታይ ጽሑፍ እስክንገናኝ ቸር ያሰንብተን፡፡
[1] William Lane Craig, “The Existence of God and the Beginning of the Universe,” Truth: A Journal of Modern Thought Vol. 3 (1991): 85-96.
[2] Stephen Hawking, History of Time (NY: Bantam Books, 1988), 39.
[3] ዝኒ ከማሁ፡፡
[4] ዝኒ ከማሁ፤ 45፡፡
Share this article:
“የጥንት ሮማዊያን እንደ እነዚህ ያሉ ቦታዎችን የሠሯቸው ሞትን ከመጥላትና ከመፍራት የተነሣ፣ ስለ ሞት ላለማሰብ በሚል ነበር። እነዚህን ስፍራዎች ግን ክርስቲያኖች በአንጻራዊ ነጻነት የማምለኪያ ስፍራ አድርገው ይጠቀሙበት ነበር።”
“የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” (ማቴ. 5፥9)
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society is a faith-based society founded in June 7, 2013 by a group of Christians who are committed to the expansion and edification of the Evangelical Churches of Ethiopia. The Ge’ez word ‘Hintset’, which means ‘to edify’ or ‘to build’, is intended to describe this commitment.
“ከመልእክተ ሕንጸት” በስተቀር፣ በድረ ገጹ ላይ የሚቀርቡ ማናቸውም ዝግጅቶች የሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር አቋምን ላይወክሉ ይችላሉ።
With the exception of “Hintset’s Editorial”, any pubication presented on the Website may not necessarily represent the position of Hintset Christian Society.
Hintset Christian Society
Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.
2 comments
[…] ደግሞ ሳይንስም ሆነ የግል ተሞክሮዎች ያረጋግጡልናል፡፡[1]አጽናፈ ዓለሙ ካለመሆን ወደ መሆን ለመምጣቱ ዋነኛው ሳይንሳዊ […]
[…] [2] Stephen Hawking, History of Time (NY: Bantam Books, 1988), 39. […]