[the_ad_group id=”107″]

በዓለ ጰራቅሊጦስ

መንደርደሪያ

በኢትዮጵያ ከ1555-1585 ዓ.ም. የነገሠው የዐፄ ሠርጸ ድንግል ዜና መዋዕል[1] ጸሐፍት[2] ዜና መዋዕሉን መጻፍ የጀመሩት የሚከተለውን ጸሎት በማቅረብ ነበር። “ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ አስተብቍዖ ወሰአሎ ለእግዚአብሔር አቡከ ከመ ይፈኑ ላዕሌነ ጰራቅሊጦስሃ መንፈሰ ጽድቅ ዘኢይክል ዓለም ነሢኦቶ። ወመጺኦ ውእቱ ይመርሐነ ኀበ ኵሉ ጽድቀ ነገር። እስመ አይነግር እም ኀቤሁ ፈጠራ ወሐሰት አምሳለ ካልኣን መናፍስት እለ አልቦ ጽድቀ[ቅ] ውስተ አፉሆሙ። – ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ዓለም ሊቀበለው የማይችለውን የእውነት መንፈስ የኾነውን ጰራቅሊጦስን ይልክን ዘንድ የባሕርይ አባትኽን እግዚአብሔርን ማልደው፤ ለምነውም። መጥቶም ወደ እውነት ነገር ኹሉ ይመራናልና፤ በአፋቸው ውስጥ እውነት እንደሌላቸው እንደ ሌሎች መናፍስት የሐሰትን ነገር ከራሱ አንቅቶ አይናገርምና” (የዐፄ ሠርጸ ድንግል ዜና መዋዕል 1999፣ 3)።

ይህ ጸሎት፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ከነገራቸውና፥ “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለኹ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ኾነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውስጣችኹም ስለሚኾን እናንተ ታውቃላችኹ።” እንዲሁም፥ “የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም። ግን እርሱ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ኹሉ ይመራችኋል፤ የሚሰማውን ኹሉ ይናገራል እንጂ ከራሱ አይነግርምና፤” ባለው ቃል ላይ የተመሠረተ ነው (ዮሐ. 14፥15-17፤ 16፥12፡13)። የጸሐፍቱ ጸሎት በኢየሱስ ክርስቶስ መካከለኛነት ወደ እግዚአብሔር አብ የቀረበ ጸሎት በመኾኑ፥ ትክክለኛ ጸሎትና በትክክለኛው የጸሎት መንገድ (በኢየሱስ ክርስቶስ ስም) የቀረበ ጸሎት ነው። ጸሐፍቱ በጸሎታቸው መንፈስ ቅዱስ እንዲላክላቸው የለመኑት፥ ዜና መዋዕሉን ሲጽፉ መንፈስ ቅዱስ እውነት ወደ ኾነው ነገር ኹሉ እንዲመራቸው ሲኾን፥ ይህን ለማድረግ እርሱ የታመነ መኾኑን ገልጠዋል። ሌሎች ጥንታውያን ጸሐፍትም በጽሑፍ ሥራቸው ረድኤተ እግዚአብሔርን እንደሚለምኑ በየድርሳኖቻቸው ተጽፎ ይነበባል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአድኅኖት ሥራውን ፈጽሞ ወደሰማይ ካረገ በኋላ፥ መንፈስ ቅዱስ እንደሚመጣ ተናግሮ ነበር (ዮሐ. 15፥26፤ 16፥7፡13)። በዚሁ መሠረት ከሙታን ተለይቶ በተነሣ በኀምሳኛው ቀን፥ ወደ ሰማይ ባረገ በዐሥረኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ መቶ ኻያ በሚያኽሉ ሰዎች (ሐ.ሥ. 1፥15) መካከል ወረደ። “በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።” (ሐ.ሥ. 2፥4)። በዓለ ጰራቅሊጦስ ይህ ክሥተት የሚዘከርበት በዓል ነው።

በዓለ ጰራቅሊጦስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና[3] መሠረት ከሚከበሩ ዘጠኙ የጌታ ዐበይት በዓላት አንዱ ሲኾን፥ የትንሣኤ በዓል በዋለ በኀምሳኛው ዕለት የሚከበር በዓል ነው። ትንሣኤና በዓለ ጰራቅሊጦስ በብሉይ ኪዳን ይከበሩ ከነበሩት ከአይሁድ የፋሲካ በዓልና እርሱን ተከትሎ በኀምሳኛው ቀን ከሚከበረው በዓለ ሠዊት (የእሸት በዓል) ጋር ተነጻጽሮ አላቸው። በትውፊቱ መሠረት ከትንሣኤ በዓል ጀምሮ እስከ ኀምሳኛው ቀን ድረስ በክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ መነሣት የተገኘውን ጽድቅና ነጻነት በማሰብ ኀምሳው ዕለታት ፍሥሓና ሐሤት የሚደረግባቸው ዕለታት ናቸው። በእነዚህ ዕለታት አይጾምም፤ ለእግዚአብሔር አምልኮትን ለመግለጥ ሦስት ጊዜ ይሰገዳል እንጂ ከዚያ በላይ ብዙ አይሰገድም። ጾም ስለሌለም በኹሉም አድባራትና ገዳማት (አብያተ ክርስቲያናት) ቅዳሴ የሚቀደሰው በጥዋት ነው።

በዓለ ጰራቅሊጦስ እንደ ትንሣኤና ሆሳዕና በዓላት ዕለተ እሑድን አይለቅም። በቤተ ክርስቲያኒቱ የአምልኮ ሥርዐት መሠረት የትንሣኤ ቀለም (ለዘመነ ትንሣኤ የተመደቡት ዝማሬዎች) ፍጻሜን የሚያገኙት በጰራቅሊጦስ ዕለት ነው (የኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዐተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት 1988፤ 89፣90)።

መንፈስ ቅዱስ

መንፈስ ቅዱስ ከሥላሴ አንዱ አካል ነው። የኒቅያ ሥርዐተ ሃይማኖትና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን (ኢኦተቤክ) የእምነት መግለጫ በኾነው ጸሎተ ሃይማኖት ውስጥ ስለ መንፈስ ቅዱስ የሚከተለው አንቀጽ ሰፍሯል፤ “ጌታ፥ ሕይወት ሰጪ በሚኾን፥ ከአብ በሠረጸ፥ ከአብና ከወልድ ጋር በሚሰገድለትና በሚመሰገን፥ በነቢያት በተናገረ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን።” በዚህ የእምነት አንቀጽ መሠረት፥ መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ጋር በአንድነት የሚሰገድለትና የሚመሰገን የሥላሴ አንዱ አካል ሲኾን፥ የሠረጸውም ከአብ ነው። ይህም መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ይሠርጻል ከሚለው የምዕራባውያን አስተምህሮ ይለያል።

ስለ መንፈስ ቅዱስ ሥርጸት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሊቃውንት፥ ‘መንፈስ ቅዱስ ከአብ ይሠርጻል፤ ከወልድ ይነሣል’ የሚል ሐተታ አላቸው። ሐተታቸው ቀጥሎ በተጠቀሱትና በወንጌለ ዮሐንስ ውስጥ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሥርጸት በተነገሩት ክፍሎች ላይ የተመሠረተ ነው። “እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችኹ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥ እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል፤” (ዮሐ. 15፥26) እንዲሁም፥ “እርሱ ያከብረኛል፥ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋልና። ለአብ ያለው ኹሉ የእኔ ነው፤ ስለዚህ፦ ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራችኋል አልኹ።” (ዮሐ. 16፥14-15)።

በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ፥ “ከአብ የሚወጣ” እና “ለእኔ ካለኝ ወስዶ” በሚሉት ሐረጎች መካከል ልዩነት እንዳለ ግልጥ ነው። ከአብ መውጣት “ሥርጸትን” ለእኔ ካለኝ ወስዶ “ነሢእን (መውሰድን)” እንደሚያሳይ አጠራጣሪ አይደለም። ይልቁንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ለእኔ ካለኝ ወስዶ” አለ እንጂ “ከእኔ ወስዶ” አላለም ሲሉ በአገባብም በአተረጓጐምም ኹለቱ አነጋገሮች ልዩነት እንዳላቸው ለማሳየት ይሞክራሉ። ከምንም በላይ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ከአብም ከወልድም ሠርጿል ቢባል፥ የሦስቱን አካላት ስምና ግብር ማፋለስ ይኾናል ሲሉ ይከራከራሉ።

በትምህርተ ሥላሴ መሠረት፥ የአብ ግብር ወልድን መውለድ፥ መንፈስ ቅዱስን ማሥረጽ ነው። ወልድና መንፈስ ቅዱስ ከአብ እንደ ወጡ መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል። ከአብ የወልድ መወለድ (ልደተ ወልድ) እና የመንፈስ ቅዱስ መውጣት (ፀአተ መንፈስ ቅዱስ)፥ መወለድ እና መውጣት ተብለው ቢገለጡም፥ ምስጢራቸው ግን መውጣት ነው። ለዚህም ስለ መንፈስ ቅዱስ፥ “ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ” የተባለውንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ “ከአብ ወጥቼ ወደ ዓለም መጥቻለኹ” ያለውን መጽሐፍ ቅዱሳውያን ምስክሮች ያቀርባሉ (ዮሐ. 15፥26፤ 16፥27፡28፤ 17፥8)። በምሳሌ ሲያብራሩትም፥ “አወጣጣቸው ግን እንደ ስማቸው ልዩ ነው። ቃልና እስትንፋስ ከመዝገባቸው ከልብ ሲወጡ ፀአተ ቃል (የቃል መውጣት) አፍ ያስከፍታል። እስትንፋስ ግን አያስከፍትም። ቃል ከልብ ወደ አፍ ሲወጣ፥ ተወለደ እንደ መባል ኹሉ ተነገረ ይባላል እንጂ ተተነፈሰ አይባልም። እስትንፋስም ከአፍ ሲወጣ ሠረጸ እንደ መባል ኹሉ ተተነፈሰ ይባላል እንጂ ተወለደ አይባልም።” ይላሉ። በተጨማሪም፥ “ወንድና ሴት ልጅ ከአንድ አባት ባሕርይ ስለ ወጡ ምንም ልጅ መባል ቢያገናኛቸው ያይነትና የገላ ስማቸው ወንድና ሴት መባል እንዲለያቸው፥ የወልድና የመንፈስ ቅዱስም እንደዚሁ ነው። ምንም ከአብ መውጣት ቢያገናኛቸው በአካል ግብርና (የወልድ ግብር መወለድ፥ የመንፈስ ቅዱስ ግብር መሥረጽ ነው) በአካል ስም (ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ በመባል) እንዲህ ይለያሉ።” ይላሉ (ሃይማኖተ አበው ቀደምት ገጽ 83፣84)። ይህ እንግዲህ ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት የሞከሩበት የሊቃውንቱ ሐተታ ነው።

ጥንታውያን አበውም መንፈስ ቅዱስ ከአብ እንደሚሠርጽ ከወልድም እንደሚነሣ መስክረዋል። በሃይማኖተ አበው ላይ ኤጲፋንዮስ፥ “ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ … ዘሠረጸ እም አብ ወነሥአ እም ወልድ። – ከአብ በሠረጸ ከወልድ በነሣ … በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን።” ብሏል (ሃይማኖተ አበው 1986፣ 175)። በተመሳሳይም የሠለስቱምእት ቅዳሴ፥ “አንድ የሚኾን ኢየሱስ ክርስቶስ ልጁ እንደኾነ አብ የልጁን ነገር ይናገራል። ወልድም የወለደው እግዚአብሔር አብ እንደኾነ ይናገራል። መንፈስ ቅዱስም ከአብ እንደወጣ (እንደ ሠረጸ) ከወልድም እንደነሣ ይናገራል።” (መጽሐፈ ቅዳሴ 1986፣ 99)። ይህ ሐተታ በወንጌላት የተለያዩ ክፍሎች በቀረበው ትምህርት ላይ የተመሠረተ እንደ ኾነ ግልጥ ነው።

የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአድኅኖት ሥራውን ፈጽሞ አስቀድሞ ወደ ነበረበት እንደሚኼድ ለደቀ መዛሙርቱ በነገራቸው ጊዜ፥ እጅግ ታውከው ነበር። ጌታም አጽናናቸው። እንዲህም አላቸው፥ “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለኹ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ኾነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውስጣችኹም ስለሚኾን እናንተ ታውቃላችኹ።” አላቸው (ዮሐ. 14፥15-17)። የእርሱ ከእነርሱ ተለይቶ መኼድ፥ ለሌላው አጽናኝ ለመንፈስ ቅዱስ መምጣት አስፈላጊ መኾኑን የተናገረበት ክፍልም አለ (ዮሐ. 16፥7)። በዚሁ መሠረት ወደ ሰማይ ከማረጉ አስቀድሞ እርሱ የነገራቸውንና አብ የሰጠውን የተስፋ ቃል በመጠበቅ እንዲቈዩ አዘዛቸው (ሐ.ሥ. 1፥4፤ ሉቃ. 24፥49)። በዚህ የተስፋ ቃል መሠረት መንፈስ ቅዱስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሐዋርያት ላይ ወረደ (ሐ.ሥ. 2፥33)።

የመንፈስ ቅዱስ መውረድ በደቀ መዛሙርቱ ሕይወት ላይ ትልቅ ለውጥ እንዳመጣ በበዓለ ኀምሳ ዕለት በቤተ ክርስቲያን በስፋት ይሰበካል። የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በሐዋርያት ላይ ሲወርድ ፈሪዎች የነበሩትን ሐዋርያትን ጥቡዓን እንዳደረጋቸው፥ ያልተማሩ የነበሩት ሐዋርያት በዕውቀት እንደ ጐለመሱ በአእምሮም እንደ ታደሱ ወዘተ… ይገለጣል። የኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዐተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት የተሰኘው የቤተ ክርስቲያኒቱ መጽሐፍ እንደሚለውም፥ በዚህ ዕለት (በበዓለ ጰራቅሊጦስ)፥ “ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የሞቱና የትንሣኤው ምስክሮች ኾኑ፤ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በእነርሱ ላይ ሲያድር ለቤተ ክርስቲያን ጕዞ ዐዲስ ምዕራፍ ተከፈተ። ሊቁ ዮሐንስ አፈ ወርቅ እንዳለው ‘ይህች ዕለት የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን’ ትባላለች።” (1988፣ 90)።

የቤተ ክርስቲያን የጸሎት መጻሕፍት የመንፈስ ቅዱስን መውረድ ጠቅሰው፥ ያው መንፈስ ዛሬም እንዲወርድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይማጸናሉ፤ ለምሳሌ አንዱን እንመልከት፤ “በሐዋርያት ላይ ጸጋኽን የገለጽኽ አንተ ነኽ። በአንድ ቤት ውስጥ ተሰብስበው ሳሉ መንፈስ ቅዱስ እንደ እሳት ኾኖ በላያቸው ወረደ፡፡ በአገሩ ኹሉ ቋንቋ ተናገሩ። ሰማይና ምድርን የፈጠርኽ አንተ ይህንን መንፈስኽን ላክልን” (ሊጦን ዘእሑድ)። የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት እንዲህ የሚሉ ቢኾንም፥ መንፈስ ቅዱስ ቸል ተብሏል የሚሉም አሉ።

ችላ የተባለው መንፈስ ቅዱስ

ከላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ የትምህርትና የጸሎት መጻሕፍት ስለመንፈስ ቅዱስ የገለጧቸው እውነቶች አስደናቂዎች ናቸው። ይኹን እንጂ በመጻሕፍቱ ውስጥ የሰፈረውና አኹን የሚታየው ተጨባጭ ኹኔታ በሕዝቡ ሕይወት የሚስተዋለውም ለየቅል በመኾኑ፥ መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያኒቱ ችላ ተብሏል የሚሉ አሉ። ቸል እንዲባል ካደረጉት ነገሮች መካከል ከሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ የኾነው ሜሮን መንፈስ ቅዱስን የመተካቱ ነገር እንደ ኾነ የሚናገሩ አሉ (ጮራ መንፈሳዊ መጽሔት ቍጥር 12፣ ገጽ 5-6)። በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ መሠረት፥ ሜሮን ከጥምቀት በኋላ ተጠማቂው የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ለመቀበል የሚቀባው ቅብዐት ነው። “ሕፃናት ከተጠመቁ በኋላ መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉ ወዲያውኑ በሜሮን ይቀባሉ።” ይላል የኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዐተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነትየተባለው መጽሐፍ (1988፣ 36)።

ይኸው መጽሐፍ በሜሮን የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያ እንዳለው የሚናገር ሲኾን፥ የሚጠቅሰውም ሐዋርያት የእግዚአብሔርን ቃል በተቀበሉት አማኞች ላይ እጃቸውን በመጫን ሲጸልዩ አማኞቹ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ይቀበሉ የነበረ መኾኑን ነው (ሐ.ሥ. 8፥14-17፤ 19፥5-6)። ሜሮንና እጅ መጫን ተመሳሳይ ነገሮች ባይኾኑም፥ ትምህርቱ እጅ በመጫን መንፈስ ቅዱስ የሚሰጥ ከኾነ፥ ሜሮን በመቀባትም ሊሰጥ ይችላል የሚል መንገድን የተከተለ ይመስላል። ʻበዚህ ኹኔታ ውስጥ የሚኖር አማኝ ሜሮንን ተሻግሮ መንፈስ ቅዱስን መመልከት የሚችልበት አቅም ያገኛል ወይ?ʼ የሚለው ጥያቄ ግን በቀላሉ የሚመለስ አይኾንም። ደግሞም በዐዲስ ኪዳን መንፈስ ቅዱስ ራሱ ቅዱሱ ቅባት ተባለ እንጂ መንፈስ ቅዱስን የሚወክል ወይም የሚተካ ሌላ ቅባት ስለ መኖሩ የዐዲስ ኪዳን መጻሕፍት አያስተምሩም (1ዮሐ. 2፥20፡27)።

ዓለማየሁ ሞገስ “ኹሉም ኹሉን ይወቅ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ “በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደ መንፈስ ቅዱስ ችላ የተባለ ወይንም ያልታወቀ ከሦስቱ አካላት የለም።” ይላሉ። ችላ የተባለባቸውን ማሳያዎችም በወቅቱ ከሚታየው ተጨባጭ ኹኔታ በመነሣት እንደሚከተለው ያቀርባሉ፤

ለምሳሌ በአኹኑ ጊዜ (መጽሐፉ የታተመው በ1987 ዓ.ም. ነው) በዐዲስ አበባ 56 አብያተ ክርስቲያናት አሉ። በመንፈስ ቅዱስ ስም የታነጸ ግን አንድም የለም። የሥላሴ 2፣ የእግዚአብሔር አብ 3፣ የመድኀኔ ዓለም 7፣ ይህም ከማርያም ስለ ተወለደ እንጂ ማን ዙሮ አይቶት አያ፥ በጠቅላላ በአስማተ ሠለስቱ ሥላሴ አሐዱ አምላክ 10 አብያተ ክርስቲያናት አሉ። የተቀረው ግን በማርያም፥ በመላእክት፥ በጻድቃን፥ በሰማዕታት ስም ነው። ምስኪን የቤተ ክርስቲያን ጠባቂ መንፈስ ቅዱስ ግን አንድም እንኳ የለውም። ያመት እንጂ (በዓለ ጰራቅሊጦስን ነው) የወር በዓልም የለውም። ሰዎች ሲደነግጡ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ሲሉ በቀር ስሙን ማን አንሥቶት አያ፣ ከእነዚሁም በጣም ካልደነገጡ በስመ አብ ብቻ ብለው ዝም የሚሉ አሉ።” (1987፣ 140)።

ከላይ እንደ ተጠቀሰው፥ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በሐዋርያት ላይ ማደር ለቤተ ክርስቲያን ዐዲስ የጕዞ ምዕራፍ የከፈተ ትልቅ ክሥተት ነው። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ መውረድ የጀመረችውን የጕዞዋን ዐዲስ ምዕራፍ ያለ መንፈስ ቅዱስ መቀጠልና መፈጸም ትችላለች ወይ? በፍጹም አትችልም!! ያለ መንፈስ ቅዱስ ምሪት የምትጓዝ ቤተ ክርስቲያን ያለ መሪ ለመጓዝ እንደሚያስብ ዐይነ ስውር ሰው መኾኗ ነው። በዚህ ድርጊቷም መንፈስ ቅዱስን ማሳዘኗ አይቀርም። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ችላ ወዳለችው መሪዋ ወደ መንፈስ ቅዱስ በቶሎ መመለስና በእርሱ ለመመራት ራሷን ማዘጋጀት አለባት።

[1]ይህ ዜና መዋዕል ኮንቲ ሮዚኒ ተርጕሞ በ1907 እ.ኤ.አ. በፓሪስ ካሳተመው መጽሐፍ የግእዙን ንባብ ዓለሙ ኀይሌ ወደ ዐማርኛ መልሰው ግእዝና ዐማርኛውን በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የቅርስ ምርምርና ማእከላዊ ዶክመንቴሽን መምሪያ በ1999 ዓ.ም. ያሳተመው ነው።

[2]የዜና መዋዕሉ ጸሓፊ ወልደ ሕይወት ሊኾን እንደሚችል ሲገመት፥ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኀይሌም የአባ ባሕርይ አስተዋፅኦ ሳይኖርበት እንደማይቀር በአባ ባሕርይ ድርሰቶች ገጽ 35 ላይ ጠቅሰዋል።

[3]በዚህ ዐውድ “ቀኖና” ማለት ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ማለት ነው።

Yimrhane Kirstos

አንብቡና አስተላልፋት

የምወድህ (የጽሑፍ ልማድ ኾኖ እንጂ አንቺም አለሽበት) አንባቢዬ ሆይ፣ “ምን ላንብብ? ለማንስ ላስተላልፋት?” እንደምትለኝ እገምታለሁ። ይህችን መጣጥፍ ለመጫር ምክንያት የኾነኝን ነገር መጨረሻ ላይ ነው የምነግርህ። በቅድሚያ ስለ ንባብ/ ማንበብ ጥቂት እንድጫጭር እያነበብህ ፍቀድልኝ።

ተጨማሪ ያንብቡ

መልካም ጅምሩ እንዳይደናቀፍ

የሥነ መለኮት ጥናት በኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን አጭር ዕድሜ ያለው ነው፡፡ የዕድሜው ዕጥረት ከወንጌላውያን ክርስትና አጀማመር ጋር የራሱ ቁርኝት አለው፡፡ የአብያተ ክርስቲያናቱ የቆይታ ዘመን በአንጻራዊነት ከታየ አጭር የሚባል ነውና፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በርካታ ቤተ ክርስቲያናት፣ አጋር ቤተ ክርስቲያናትና ግለ ሰቦች የመጽሐፍ ቅዱስ ት/ቤቶችን መክፈት ጀምረዋል፡፡ በመሠረቱ ይህን መሰሉ ጥረት ሊበረታታ ይገባል እንላለን፡፡ ይሁን እንጂ ጥረቱን ማበረታታት እንዳለ ሆኖ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በዋናነት ከትምህርት ጥራት ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

የዘመነ ዜማ ለዘመናት ንጉሥ – ዜማ ለክርስቶስ

ከ1960ዎቹ የሙሉ ወንጌል ሀ መዘምራን እስከ ዜማ ለክርስቶስ ህብረት፣ በአንድ እጅ ጣት ከሚቆጠሩ ዝማሬዎች እስከ አለንበት ዘመን የዝማሬ ጎርፍ፣ ከለሆሳስ የጓዳ ዝማሬ እስከ አደባባይ ሆታ፣ ከአንጋፋ እስከ ወጣት ዘማሪያን እስከ ወጣት ዘማሪያን . . . ይህ የኢትዮጵያ ቤ/ክ የዝማሬ ታሪክ ነው፡፡ መዝሙር ተቀዛቅዟል የለም አድጓል የሚለውን ሙግት የሻረ አዲስ የዝማሬ መንፈስ፣ ሁሉንም የሚያስማማ አቀራረብ፣ የተዋጣለትና የተሟላ ዝማሬ እነሆ ከወጣት ዘማሪያን ለኢትዮጵያ ቤ/ክ ተብርክቷል፤ ከዜማ ለክርስቶስ፡፡ ወጣትነታቸውን፣ ጉብዝናቸውንና ችሎታቸውን ሁሉ ለጌታ የሰው ወጣቶች የሰጠኸንን አንሆ ብለው ለዘመናት ንጉስ ከልብ የሆነ ሕያው ዝማሬ ተቀኝተዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.