[the_ad_group id=”107″]

“ጌታን ተቀበሉ” ምን ማለት ነው?

Photo by: Abinet Teshome

ጌታን ተቀበሉ ማለት ከአንድ ሃይማኖታዊ ሥርዐት ወጥታችሁ ወደ ሌላ ሃይማኖታዊ ሥርዐት ግቡ ማለት አይደለም። ከሆነ ዐይነት የአምልኮ ሥፍራ ወደ ሌላ ዐይነት የአምልኮ ሥፍራ ተዘዋወሩ፣ በሆነ ዐይነት የዝማሬ ስልት ከማምለክ በሌላ ዐይነት የዝማሬ ስልት ወደ ማምለክ ቀይሩ ማለትም አይደለም። 

እነዚህ ነገሮች ወንጌላውያን የእግዚአብሔር መንግሥት መልእክተኞች ከሚያውጁት የምሥራች እውነት ዘላለማዊ ዋጋ አንጻር እጅግ አናሳ ናቸው። የሰው ዘላለማዊ ዕጣ ፈንታ በሰው ሠራሽ ሃይማኖታዊ ልምምድ አይወሰንም። ተቀበሉ የምንለው ጌታ በእውነትና በመንፈስ እንጂ፣ በዚህ ወይም በዚያ የሚመለክ አይደለም፤ እርሱ በስሙ አምነው የዳኑና በቅዱስ ቃሉ ሥልጣን ሥር የሚተዳደሩ አማኝ ቅዱሳኑ በሚሰበሰቡት በማንኛውም ሥፍራ የሚገኝና በመካከላቸው በልዩ ልዩ ሁኔታ የሚሠራ ሕያው አምላክ ነው። 

ጌታን መቀበል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስተምር የየትኛውም ሃይማኖት ቤት ተመላላሽ መሆን ሳይሆን፣ የራሳችንን ነፍስ ሳይቀር ክደን፣ እርሱን በነገር ሁሉ ወደ መከተል ሕይወት መግባት ማለት ነው (ሉቃስ 14፥26)። ‘ጌታን ተቀበሉ’ ስንል የምንጠራችሁ ወደዚህ በፍጹም ልብና በፍጹም ማንነት የእርሱ ወደ መሆን ሕይወት ነው። የትኛውም ሃይማኖታዊ ተቧድኖ የድነት ርግጠኝነትን አይሰጠንም። በአንድነት እናመልካለን፣ በአንድነት እንተናነጻለን፣ በአንድነት በእርሱ ዐብረን እንኖራለን፤ በአንድነት ግን አንድንም። 

ጌታን መቀበል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስተምር የየትኛውም ሃይማኖት ቤት ተመላላሽ መሆን ሳይሆን፣ የራሳችንን ነፍስ ሳይቀር ክደን፣ እርሱን በነገር ሁሉ ወደ መከተል ሕይወት መግባት ማለት ነው።

ለእኔ ማንም አምኖልኝ አልዳንኩም፤ በእኔም እምነት ልድን የምችለው እኔ ብቻ ነኝ። በጣም የምወድዳቸውንና የምሳሳላቸውን ሰዎች እንኳን በእኔ እምነት ማዳን አልችልም። የምችለው አምነው ይድኑ ዘንድ መጸለይና ድነት የሚገኝበትን እውነት በፍቅር ማካፈል ነው። ጌታን መቀበል በግላችን ዐውቀንና አስተውለን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ሕይወታችን መፍቀድ፣ ወደ ልባችንም ማስገባት ነው። 

ጌታን ተቀበሉ ስንል፣ ይህች ዓለም ዘላለማዊ አድራሻችንን መርጠን የምናልፍባት ጠፊ ዓለም ናትና፣ ለማያልፈው ዘላለማዊ ማንነታችሁ ዋስትና ግቡ፤ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የዘላለም ሕይወትን ምረጡ፤ ከዘላለም ሞት አምልጡ ማለታችን ነው። ከዓለም ሥርዐትና ከገዥዋ እንዲሁም ከሥጋችሁ ፈቃድ ባርነት ወጥታችሁ እርሱን ጌታ ብታደርጉት ለነፍሳችሁ ድነትን፣ በመንፈሳችሁም ሕያውነትን ታገኛላችሁ ማለታችን ነው። 

ጌታን ተቀበሉ ስንል፣ ለዘላለም እንድትኖሩና ከእግዚአብሔር ልጆች ጋር እንድትቈጠሩ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ጌትነት (እግዚአብሔር ወልድነት) በእምነት ተቀበሉ ማለታችን ነው (ዮሐንስ 1፥1-18፣ ቈላስይስ 2፥9፤ 1ኛ ዮሐንስ 5፥20)።

ጌታን ተቀበሉ ስንል፣ የሰው ልጆች ሁሉ ከኀጢአት የተነሣ በሞት ፍርድ ሥር እንዳሉ ዐውቃችሁ ካልተመለሳችሁ፣ የሚጠብቃችሁ የዘላላም ሞት ቅጣት እንደ ሆነ በመገንዘብ ብቸኛ በሆነው የማምለጫ ዕድል ተጠቀሙ ማለታችን ነው። በእርሱ የሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።(ዮሐንስ 3፥18)፤ የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው። (ሮሜ 6፥23)

የትኛውም ሃይማኖታዊ ተቧድኖ የድነት ርግጠኝነትን አይሰጠንም።

ጌታን ተቀበሉ ስንል፣ ማንም በክርስቶስ ባይሆን ገና በበደል አለና ንስሓ ግቡ፤ ከያላችሁበት ጎዳና ብቸኛ በሆነው የድነት መንገድ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ ማለታችን ነው (ዮሐንስ 14፥6)።

ጌታን ተቀበሉ ስንል፣ በኀጢአት ምክንያት ቀድሞ ዝግ የነበረው ወደ አብ መግባት፣ በክርስቶስ በኵል ሊገቡ ለሚወድዱ ሁሉ ክፍት ነውና፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ይህን መብት ተካፈሉ ማለታችን ነው (ዕብራውያን 10፥19-20)።

ጌታን ተቀበሉ ስንል፣ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ እስካልታረቀ ድረስ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ጥለኛ እንደ ሆነ ተግንዝባችሁ፣ በእግዚአብሔርና በሰዎች መካካል ባለው፣ በእርሱ በጌታችን በማመን ሰላምን ፍጠሩ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ማለታችን ነው (2ኛ ቆሮንቶስ 5፥18-20፤ 1 ጢሞቴዎስ 2፥5፤ ዕብራውያን 7፥25)። 

ጌታን ተቀበሉ ስንል ቀድሞ ሕግን በመፈጸም ይገኝ ዘንድ ታስቦ የነበረው ጽድቅ፣ በዚህ በመጨረሻ ዘመን፣ በሕግ ሥራ ፍጹማን ሆነው ለተገኙት ሳይሆን (አንድም የለምና ሮሜ 3፥11-12፡ 23)፣ የሚቀበሉትን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅዱስና እንከን አልባ አድርጎ ያቀርባቸው ዘንድ አስፈላጊውን ዋጋ ሁሉ በመስቀል ላይ ሞት በከፈለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በማመን  ጽደቁ ማለታችን ነው። የሚያምኑ ሁሉ ይጸድቁ ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና። (ሮሜ 10፥4)፤ ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መሥክሮ ይድናልና።(ሮሜ 10፥9-10)።

ጌታን ተቀበሉ ስንል፣ የሰው ልጆች ሁሉ ከኀጢአት የተነሣ በሞት ፍርድ ሥር እንዳሉ ዐውቃችሁ ካልተመለሳችሁ፣ የሚጠብቃችሁ የዘላላም ሞት ቅጣት እንደ ሆነ በመገንዘብ ብቸኛ በሆነው የማምለጫ ዕድል ተጠቀሙ ማለታችን ነው። 

“ጌታን ቀበሉ” ስንል፣ ‘ዕዳችሁ ተከፍሏል፤ ቅጣታችሁንም የወሰደ አንድ ኢየሱስ አለ’ በማለት፣ ብታምኑት ያቈየላችሁን የነጻነት ሕይወት ውረሱ ማለታችን ነው (ገላትያ 3፥13፤ ቈላስይስ 2፥13-14፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 5፥21)።

ጌታን ተቀበሉ የሕይወት ጥሪ እንደሆነው ሁሉ፣ የሞት ጥሪም ነው። ለራስ ሞቶ በእርሱ ሕይወት ለዘላለም የመኖር ጥሪ ነው። ይህን ስለቈረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ፤ በሕይወት ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና  ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ። (2ኛ ቆሮንቶስ 5፥14-15)

ጌታን ተቀበሉ የምድራዊ ኑሮን ማሻሻያ አቋራጭ መንገድ ጥቆማ ሳይሆን፣ የምድር ብርና ወርቅ ሊገዙት የማይችሉትን ውዱን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት፣ በእምነት ወርሶ ለዘላለም የመበልጸግ ጥሪ ነው (ሉቃስ 12፥15)። 

ጌታን ተቀበሉ የሕይወት ጥሪ እንደሆነው ሁሉ፣ የሞት ጥሪም ነው። ለራስ ሞቶ በእርሱ ሕይወት ለዘላለም የመኖር ጥሪ ነው። 

ጌታን ተቀበሉ፦ ከቁጣ ልጅነት ወደ እግዚአብሔር ልጅነት የሚያሻግር የማንነት ለውጥ ጥሪ ነው! 

ጌታን ቀበሉ ተቀበሉ፦ በዘላለም ሞት ፍርድ ፈንታ፣ የዘላለም ሕይወት ስጦታን ተቀበሉ የሚል ቸር ጥሪ ነው! 

ጌታን ተቀበሉ፦ በዚህ በክፉ በተያዘና ለጨለማ መንግሥት በተገዛ ዓለም መካከል ብርሃን የሆነውን ኢየሱስን በመከተልና በእርሱ በመመላለስ የሚገኝ ዘላለማዊ የብርሃን ሕይወት ጥሪ ነው።

ጌታን ተቀበሉ፦ የምሕረት ጥሪ ነው!

ጌታን ተቀበሉ፦ የነጻነት ጥሪ ነው!

ጌታን ተቀበሉ፦ የዕረፍት ጥሪ ነው!

ጌታን ተቀበሉ፦ የሰላም ጥሪ ነው!

ጌታን ተቀበሉ፦ የፍቅር ጥሪ ነው!


ለዚህ ጥሪ ልባችንን በከፈትንና ፈቅደን በተቀበልነው ጊዜ፣ በወደቀው ማንነት ውስጥ ተሰውሮ ከቈየው እውነተኛ ማንነታችን ጋር ያስተዋውቀናል፤ በእርሱ የሆነውን አዲስ ቅዱስ ሕይወትን ይሰጠናል። ነፍሳችን የተጠማችው ማረፊያዋ፣ ልታመልከው የሚገባው ጌታዋ ማን እንደ ሆነ ዐውቃ ትድናለች፤ የትልቁ የእግዚአብሔር ልጆችም ሆነን እንቈጠራለን። ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው (ዮሐንስ 1፥12)፤ እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል ሰምታችሁ፥ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ(ኤፌሶን 1፥13)። ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፏል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል። (2ኛ ቆሮንቶስ 5፥17)

ስለዚህም ወደዚህ ዕረፍት ያልገባችሁ፣ አንዱን መድኃኒት ያላገኛችሁ፣ ከእግዚአብሔር አብ ጋር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ያልታረቃችሁ፣ ሌላ የመዳን መንገድ የለምና ወደ ኢየሱስ ኑ! መንገድና እውነት፣ ሕይወትም የሆነውን ጌታ ተቀበሉ!

Zeritu Kebede

የተመለሱና ያልተመለሱ ጥያቄዎች፡- ስለ እግዚአብሔር፣ ስለሰው፣ ስለክርስቶስ

ትምህርተ ክርስቶስ እጅግ መሠረታዊ ከሆኑ የክርስትና አስተምህሮዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክም ሆነ በዓለም ታሪክ ውስጥ አነጋጋሪ ከሆኑ ሰዎች መካከል ኢየሱስ ዋነኛው ነው፡፡ ገና ከጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ጊዜ ጀምሮ የኢየሱስ ማንነት አከራካሪ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ክርስቶስን በተመለከተ በያዙት የተለየ አቋሞች የተለያዩ ቤተ እምነቶች ሊፈጠሩ ችለዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

የቤተ ክርስቲያን የመድረክ አገልግሎት ከባድ ፈተና ላይ መውደቁ ተነገረ

የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የመድረክ አገልግሎቶች ከፍተኛ የሆነ ችግር እንደ ገጠማቸው ተገለጸ። ይህ የተገለጸው፣ በአዲሰ አበባ ያሉ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት መሪዎች በተገኙበት ሴሚናር ላይ ነው። ሴሚናሩ የተካሄደው ማክሰኞ ጥቅምት 27 ቀን፥ 2016 ዓ.ም.፣ በኢንተርናሽናል ኢቫንጀሊካል ቸርች (IEC) ነው። በውይይት መድረኩ ላይ ከሦስት መቶ በላይ የሚሆኑ የአጥቢያ መሪዎች ተገኝተዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ጌታን ተቀበሉ!

ዘሪቱ ከበደ በዚህ “ጌታን ተቀበሉ!” በተሰኘው ጽሑፍ ስለ የምስራቹ ቃልና ይህን የምስራች እንዲያደርሱ በእግዚአብሔር ስለ ተጠሩ አማኞች ታብራራለች፤ “እኔም እኅታችሁ በእግዚአብሔር ጸጋና መልካም ፈቃድ፣ የዚህ ሕይወት የሆነው ጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል አብስሪነት ዕጣ ወደቀብኝ።” ስትል የሕይወት የጥሪ አቅጣጫዋን ታመለክታለች። ተጨማሪ ያንብቡ።

ተጨማሪ ያንብቡ

8 comments

Your email address will not be published. Required fields are marked *

 • Zeritu may God bless you abundantly in His grace. Continue sharing what God taught you privately to us so that we can be rebuilt each other in his house. በአንድነት እናመልካለን፣ በአንድነት እንተናነጻለን፣ በአንድነት በእርሱ ዐብረን እንኖራለን፤ በአንድነት ግን አንድንም። Great understanding!!!! Stay blessed.

 • አንዳንዴ ማቸማቸም የማያስፈልግበት ጉዳይ እንዳለ ይሰማኛል። ጌታን ተቀበል ወይም ተቀበይ ማለት ከነበርሽበት ወይንም ከነበርክበት ስርአት፣ወግ፣አምልኮ እንዲሁም ልማድ ውጣ ማለትም ነው። ምንም እሹሩሩ የማያስፈልገው ጉዳይም እንዳለ ተያይዞ መነገር አለበት። ሌላው የኢየሱስን ስምና የምስራቹን መስማት የማይፈልጉትን መተው ነው። ሁልጊዜ የሚገርመኝ ክፍል አለ ይኸውም በ ሉቃስ 8÷37 (ሙሉው ቢታይ መልካም ነው)
  “በዙሪያውም በጌርጌሴኖን አገር ያሉት ሕዝብ ሁሉ ታላቅ ፍርሃት ይዞአቸዋልና ከእነርሱ እንዲሄድ ለመኑት በታንኳም ገብቶ ተመለሰ።” — ሉቃስ 8፥37 ድህነት የማይፈልግ ይቀርበታል። ድህነትን ማርክስ አያስፈልግም ባይ ነኝ።
  ተባረኪ!

 • Ameseginalew gin ene tenegna sewe negn ke minim neger medan ayasfeligngm, anchi le erasish erasu “evidence” makireb yematchiyibetin idea le la sew yikebel, kalhone ye zelalem sikay yitebikachewal bilo be confidence mawrat tinish yikebdal.

 • Amen! መዳን ይሁንለት ለሰው ልጅ ሁሉ፣ እረፍት ይሁንለት! ኢየሱስ ያድናል! ብቸኛ መንገድ፣ እውነት፣ ሂወት፣ ሰላም፣ ሙላት፣ እረፍት

 • አቶ ኤፍሬም

  እየሱስን በአንድ አስተሳሰብ እመኑ ተከተሉ፣ የተለያየ ሐይማኖት ቤት በመምርጥ ድነት አይገኝም ማለቷ ጥፋት ማድረግህ ተነጣይነትህን ያመላክታል እንጂ ምንም የተለየ የፅድቅ የሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ የሆነ ማሳመኛ ልታቀርብ አትችልም ።
  ማሽሞንሞን አያስፈልግም ላልከው ያቀረበችው እኮ ለክርስቲያኖች እንጂ ለሌላ አይደለም፣ መንፈሳዊ ትምህርትም በእንዳንተ አይነት ከረር ባለ አገላለፅ አይሰበክም። እስኪያምኑ እስኪቀበሉ በመትጋት ታስተምራለህ እንጂ አባሯቸው አይልም
  ወንድሜ በር ለመዝጋት አትቸኩል።

 • ሕይወትህን ካበጃት በላይ ማን ይበጃታል? ከሠራንስ በላይ ማን ያውቀናል? ስለ እኛ ለማወቅ፣ በዚያም ዕውቀት ልንሆን የሚገባንን ለማስተዋል ወደ እግዚአብሔር እንዙር። ተባረኪ በብዙ ጸጋ ይብዛልሽ 🙌

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.