[the_ad_group id=”107″]

የክርስቶስ ወንጌል እና ሳምራውያን

“እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሓደ፣ በዐዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፣ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስ ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ፣ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፣ ጥልንም በመስቀል ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።” (ኤፌ. 2፥14-18)።

ብዙዎች ብሔረ ሰባዊ ማንነታቸውን አጉልተው መመልከት በጀመሩበት በዚህ ወቅት የታሪክ ቁርሾን በማራገብ እና የትናንት ቂምን በመንከባከብ የዛሬን የአብሮነት ኩሬ በጠብ የሚያደፈርሱ ሰዎችን አይተን አልቅሰናል። ይህ ዐይነቱ ክፉ ልብና በቀለኝነት ዛሬን ብቻ አጨልሞ አይመለስም፤ የነገም ጀንበር የሥጋት ጉም እንዲያንዣብብበት ያደርጋል። ማንም ቢሆን ከዚህም ሆነ ከዚያ ወገን መርጦ አይወለድም! ሆኖም አንዳንዶች አንዴ የተዘፈቁበት ማለቂያ የለሽ መሳዩ አዘቅት የአንድ ብሔረ ሰብ አባላት በሆኑ ወገኖች መካከል እንኳ ንቀት እና ውጥረት ሲያበቅልም ታዝበናል። አንዳንዱ ወንዘኝነትን ተመርኩዞ ከወንዝ ማዶ ያሉትን የዚያው ብሔረ ሰብ አባላት ያገልላል። ሌላው ደግሞ የብሔራቸውን የጠራ ማንነት የያዘው የራሱ ወገን እንጂ እነ እንቶኔ የተበረዘ ወይም የተከለሰ ደም እና ባህል ስላላቸው ይናደዳል። የዚያኑ ያህል በአንድ ብሔረ ሰብ መካከል ያለው የሃይማኖት ልዩነትም የውጥረት መንሥኤ ሲሆንም ዐይተናል።

ጌታ ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት በአይሁዳውያን እና በሳምራውያን መካከል የነበረው ሁናቴም ይህንኑ ነበር የሚመስለው። ሳምራውያን በይሁዳ እና በገሊላ መካከል የሚኖሩ ሕዝብ ናቸው። እነዚህ ነዋሪዎች አንድ ወቅት የአካባቢው ቅኝ ገዢ ከነበሩት አሦራውያን ጋር በጋብቻ ስለ ተቀላቀሉ (2ነገ. 17፥3-24)፣ “ደማቸው ተበርዟል” በሚል አይሁድ ይንቋቸው ነበር።[1] ለአይሁድ ሕዝብ ሳምራውያኑ በሙሉ “ርኲሳን” ናቸው፤ ስለዚህም ሳምራውያኑ የሚበሉበትን ሳህንም ሆነ የሚጠጡበትን መጠጫ መጠቀም የሚያረክስ እንደ ሆነ ያስባሉ፤ ዮሐንስ 4፥9 እንደሚያስተምረን።[2] አይሁዳውያን “ሳምራዊ” የሚለውን ቃል ለስድብነትም ይጠቀሙበታል (ዮሐ. 8፥48)።

ሳምራውያኑም ደግሞ ራሳቸውን ከያዕቆብ ዘር የሆኑ እስራኤላውያን አድርገው ቢቈጥሩም (ዮሐ. 4፥12)፣ ከሌሎቹ የያዕቆብ ልጆች ከአይሁድ ሕዝብ ጋር እምብዛም ላለመቀላቀል የአምልኮ ቦታቸውን ለይተዋል (ዮሐ. 4፥20)። ሳምራውያኑ ቅዱስ ተራራ አድርገው የሚወስዱት የገሪዛን ተራራን ነው፤ ለዚህም አብርሃምና ያዕቆብ በአካባቢው መሠዊያዎችን መሥራታቸውን ለማሳመኛ ያቀርባሉ (ዘፍ. 12፥6-7፤ 33፥18-20)፤ ሙሴም ሕዝቡን የባረከው ከዚህ ተራራ ነው (ዘዳ. 11፥29፤ 27፥12)። በዚህ ተራራ ላይም ቤተ መቅደስ ሠርተዋል።[3] ሳምራውያኑ በዚህ ሳይወሰኑ ሃይማኖታዊ ሥርዐት ለመፈጸም ከገሊላ ተነሥተው በሰማርያ በኩል ወደ ኢየሩሳሌም የሚሄዱ አይሁዳውያን በእነርሱ ከተማ እንዳያድሩ ይከለክላሉ። ስለዚህም አይሁዳውያን ይህንን የሦስት ቀን መንገድ ትተው የዮርዳኖስ ወንዝን ምሥራቃዊ ዳርቻ ተከትለው ለመሄድ ይገደዳሉ። [4] የሳምራውያን መጽሐፍ ቅዱስም አምስቱን የሙሴ መጻሕፍት ብቻ የያዘ ነበር። በአጠቃላይ በሁለቱ የእስራኤል ሕዝብ መካከል የደም እና የባህልን “ጥራት እና ንጽሕና” በሚመለከት የተጀመረው መናናቅ፣ የሃይማኖታዊ ሥርዐት ልዩነት ተጨምሮበት ጠባቸው ከርሮ ነበር። የሚገርመው ግን ሁለቱም በዚያ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የመሢሑን መምጣት ይናፍቁ ነበር (ዮሐ. 4፥25)።

በዚህ ውጥረት መካከል ነበር ጌታችን አገልግሎቱን የጀመረው። ችግሩ ግን በቀላሉ የሚታይ ባለመሆኑ በኢየሱስ አገልግሎት ውስጥም ውጥረቱ በተለያየ መንገድ ራሱን ሲገልጥ ይስተዋል ነበር። ጌታ ኢየሱስ ይህንን የዘር ልዩነት ከተከታዮቹ መካከል በጥንቃቄ ለማፍረስ ሲተጋ ነው ያየነው። በመጀመሪያ ደቀ መዛሙርቱን ለአገልግሎት ሲያሰማራ ወደ ሳምራውያን መንደር እንዳያቀኑ አስጠንቅቋቸው ነበር (ማቴ. 10፥5)። ከትንሣኤው በኋላ ግን መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ ወርዶ ኀይልን ተቀብለው፣ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቹ እንደሚሆኑ ነግሯቸዋል (የሐዋ. 1፥8)። ይህም የትንሣኤው ኀይል በዘር ልዩነት ላይ የተመሠረተ ተቃርኖን በማስተካከል ላይ ምን ያህል ጕልበት እንዳለው ያሳየናል።

አንድ ወቅት ደግሞ እንዲህ ሆነ። ጌታ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲያመራ በሰማርያ በኩል ለማለፍ ወሰነ። ወደ ኢየሩሳሌም ለሚያቀኑ አይሁዳውያን ሳምራውያኑ ቀና አመለካከት እንደሌላቸው ግልጽ ነበር። በመሆኑም ጌታ  ወዴት እንደሚሄድ ካወቁ በኋላ ሳምራውያኑ ሊቀበሉት አልወደዱም። በዚህ ከተናደዱት ደቀ መዛሙርት መካከል ሐዋርያው ዮሐንስና ወንድሙ እሳት ከሰማይ አውርደው ሳምራውያኑን ለማጥፋት እንዲፈቅድላቸው ኢየሱስን ጠየቁት። ለዚህም ከቅዱሳት መጻሕፍት ጥቅስ እስከ መጥቀስ ርቀው ሄደዋል – “ኤልያስ እንዳደረገው” በማለት (ሉቃ. 9፥51-56)። የዘር ጥላቻ ይህን ያህል ያሳውራል። ዛሬም ቢሆን ለዚህ ዐይነቱ ርኲስ ተግባር ከቅዱሱ መጽሐፍ የሚጠቅሱ አይጠፉም። ጌታ ግን አብረውት ቢያሳልፉም አገልግሎቱ የማዳን እንጂ የማጥፋት እንዳልሆነ ገና ያልተረዱትን ደቀ መዛሙርት በዝምታ አላለፋቸውም፤ በብርቱ ገሥጿቸዋል።

ከትንሣኤው በኋላ ግን ፊልጶስ ወደ ሳምራውያን በመሄድ ወንጌል ሰብኮ፣ አጋንንትን በማውጣትና ፈውስ በማካሄድ ሲያገለግላቸው ቈየ። በኋላም ሳምራውያን መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ ከሐዋርያት መካከል ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደዚያው አመሩ። ትናትን እሳት ከሰማይ አውርዶ ሳምራውያኑን ለመጨረስ ሲመኝ የነበረው ዮሐንስ፣ በዚህን ጊዜ መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ እጁን እየጫነ የሚጸልይላቸው አገልጋይ ሆኖ ዐፈረው (የሐዋ. 8፥4-17)።

ይህ ግን በቀላሉ አልመጣም። ጌታ ኢየሱስ ከሞት በመነሣቱ ከሚፈጠረው ለውጥ አስቀድሞ ይህን ብርቱ የጥል ግድግዳ ለማፍረስ ማስተዋል የሞላባቸው ተግባራትን ፈጽሟል። አንድ ወቅት ፈሪሳውያኑ አጋንንትን ከሰዎች እያስወጣ ሰዎችን ሲፈውስ አይተው አገልግሎቱን ለመቃወም ኢየሱስን ጋኔን እንዳለበት እና ከሳምራውያን ወገን እንደ ሆነ አስወርተውበት ነበር (ዮሐ. 8፥48)። አባባላቸው “በሃይማኖተኝነትህ ከሳምራውያኑ አትሻልም” የሚል አንድምታ ያዘለ ነው፤ የሳምራውያን ደም እንዳለበት መናገር ፈልገውም ይሆናል ይህን ያሉት። በወቅቱ በአይሁዳውያን ዘንድ ይህ ከባድ ስድብ ነበረ። ጌታ ኢየሱስም ወዲያውኑ ስድቡን ተቃወመ። ጋኔን እንዳለበት ለሰነዘሩት ስድብ ጋኔን እንደሌለበት አስረዳቸው፤ የዘር ንቀትን ያዘለውን ስድብ ግን ምላሽ ሳይሰጠው ቀረ።[5] ይህም መልእክት ነበረው።

በዚህ ብቻ ግን አልተወሰነም። አንድ የሕግ ዐዋቂ ሊፈትነው ሲመጣ በሰጠው መልስ ውስጥም ዘረኝነትን የሚፈውስ ሌላ ተግባር ፈጽሟል። ጠያቂው ከጌታ የተቀበለውን “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚል ትእዛዝ ከመፈጸም ይልቅ ራሱን ማጽደቅ ፈልጎ “ባልንጀራዬ ማነው?” ሲል ጠየቀ። ጌታም መንገድ ሲሄድ ወንበዴዎች ደብድበው ስለ ጣሉት አንድ ሰው ተረከላቸው። ያ የወንበዴዎች ሰለባ መንገድ ወድቆ ሳለ በዚያ ያለፉት አይሁዳውያኑ ሃይማኖተኞችና አገልጋዮች እንዳላዩ ሲያልፉት፣ አንድ ተራ መንገደኛ ግን የወደቀውን አንሥቶ አክሞና አስታሞ አዳነው። ያም ደግ ሰው በታሪኩ ውስጥ ሳምራዊ ተደርጎ ነው የቀረበው፤ ደጉ ሳምራዊ (ሉቃ. 10፥29-35)። አይሁድ ደግ ሳምራዊን መቀበል እንደሚተናነቃቸው ቢታወቅም ጌታ ኢየሱስ ፍቅር የዘር ድንበር እንደማያግደው ይህን አይረሴ ታሪክ ተጠቅሞ ሕግ ዐዋቂውን አሳወቀው።

ጌታ ኢየሱስ ሳምራውያኑን ለማገልገል ከመሥመሩ ወጥቶ መሄዱን ሐዋርያው ዮሐንስ በሌላ ታሪክ ዘግቦልናል። ይህ ክፍል ጌታ ኢየሱስ ደክሞት ውሃ ጉድጓድ አጠገብ ስለ መቀመጡ ይነግረናል (በዚህ ዘመን “ኧረ ‘ደከመው’ አይባልም፤ ‘በረታ’ እንጂ” በማለት ዮሐንስን ለማረም የሚዳዳቸው “የእምነት ሰዎች” እንደማይጠፉ እገምታለሁ!)። በታሪኩ ውስጥ ጌታ ኢየሱስ አንዲትን ሳምራዊት “ውሃ አጠጪኝ” ይላታል። ተጠያቂዋ እንኳ አንድ አይሁዳዊ አንዲት ሳምራዊት ውሃ እንድታጠጣው በመጠየቅ ራሱን እንደማያዋርድ ስለምታውቅ በጠያቂው ተደንቃለች (ዮሐ. 4፥9)። ደቀ መዛሙርቱ ደግሞ ከሴት ጋር ሲያወራ በማየታቸው ተደንቀዋል (ቍ. 27)። ጌታ ኢየሱስ በዚህ ድርጊቱ የባህልን፣ የዘርን፣ የጾታን ዕንቅፋቶች አፈራርሷል። ከነቢይ ጋር እየተነጋገረች እንደ ሆነ የገባት ሳምራዊቷ ሴትም የዘመኗ ልጅ ናትና “ከእኛ እና ከአይሁዳውያን ማነው ትክክል?” የሚል መንፈስ ያዘሉ ጥያቄዎችን አቅርባለታለች፤ “አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፣ እናንት አይሁዳውያን ደግሞ ‘ሰው መስገድ ያለበት በኢየሩሳሌም ነው’ ትላላችሁ” አለችው (ቍ. 19)። ጌታ ኢየሱስ እርሷ እንደ ጠበቀችው ማንኛቸው ትክክል እንደ ሆኑ በቀጥታ አልነገራትም፤ “በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል” ነው ያላት (ቍ. 21)። ክርስትና ውስጥ አምልኮን በሚመለከት ‘የትኛው ዘር ነው ትክክል?’ የሚለው ጥያቄ ፋይዳ የለውም፤ እግዚአብሔር የሚመለከው በመንፈስ እና በእውነት መሆኑን ማወቅ እና ይህንንም መፈጸሙ ላይ ነው ቁም ነገሩ (ቍ. 24)! ይህ ደግሞ ከዘረኝነት ይፈውሳል። ጌታ ኢየሱስ በሰማርያ ሁለት ቀን ቈይቶ ብዙዎችን በወንጌል ከማረከ በኋላ (ቍ. 40-41) አይሁድን ሊያገለግል ወደ ገሊላ ሄደ (ቍ. 43)።

ወንጌላዊው ሉቃስ ደግሞ ሌላ ታሪክ አቈይቶልናል። ይህም ጌታ ኢየሱስ የአይሁድ ከተማ በሆነችው በገሊላ እና የሳምራውያን ከተማ በሆነችው ሰማርያ መካከል እየተጓዘ ሲያገለግል የተከሰተ ነው። በዚህ አገልግሎቱም ሁለቱን ባላንጣ ወገኖች በአንድ ማጣመሩን ማስተዋል ይቻላል። በሁለቱ ከተሞች መካከል ሲያልፍም ዐሥር ለምጻሞችን አገኘ፤ ለምጻሞቹ ከአይሁድም ከሳምራውያኑም ወገን ነበሩበት። ሁለቱ ወገኖች የሚጠላሉና የሚገፋፉ ቢሆኑም ማኅበረ ሰቡ ያደረሰባቸው መገለል ሕሙማኑን በአንድ አሰባስቧቸዋል።[6] ጌታ ኢየሱስም ዐሥሩንም ለምጻሞች ከበሽታቸው መዳናቸውን ማረጋገጫ የምስከር ወረቀት የመስጠት ኀላፊነት ወዳላቸው አካላት ላካቸው፤ ወደ ካህናት (ዘሌ. 13፥2-3፤ 14፥2-32)። ሕሙማኑ በእምነት የጌታን ቃል ተቀብለው ሲጓዙ ፈውስ አገኛቸው። ከዐሥሩ መካከል ዘጠኙ ተደስተው ወደ ዘመዶቻቸው ሲሄዱ፣ አንዱ ብቻ ግን ፈዋሹን ለማመስገን ተመለሰ፤ ያም ሰው ሳምራዊ ነበረ። ጌታም፣ “ዐሥሩ አልነጹምን? ዘጠኙስ ወዴት አሉ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም” በማለት ይህን በማድነቅ ተናገረው (ሉቃ. 17፥11-19)። ይህ ንግግሩ ዘረኝነትን በመቃወም ላይ የሚያስተላልፈው ጠንካራ መልእክት ነበረው።

ጌታ ኢየሱስ በምድር አገልግሎቱ በዘር ላይ የተመሠረተ ትምክህትም ሆነ ጥላቻ ቦታ እንዳይኖራቸው ሠርቷል፤ ዘረኝነትን ለማፍረስ ብዙ አድርጓል። ሞቱ ደግሞ በዘር ላይ የተመሠረተውን የጥል ግድግዳ አንኮታኩቶታል። የእግዚአብሔር መንግሥት ለዘረኝነት ቦታ የለውም። የትናቷም ሆነች የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ግን በዚህ ርእሰ ጒዳይ ስትፈተሽ በርካታ ችግሮች አሉባት። በዘር እና በጎሠኝነት ላይ የተመሠረተ አለመተማመን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ እዚህም እዚያም ይስተዋላል። ይህ ፍርሀት እና ጥርጣሬ ደግሞ እጅግ አደገኛ ነው። በዘር ላይ የተመሠረተ ጥርጣሬና አለመተማመን ደግሞ በሩዋንዳ፣ በኤርትራ፣ በአንጎላ፣ በናይጄሪያ፣ በሱዳን እና በዴሞክራቲክ ኮንጎ ተከስተው ያየናቸውን ግጭቶች ፈጥሯል፤ አገራችንም ከዚህ ነጻ አይደለችም። ይህ ውጥረት ቤተ ክርስቲያንን ማሳሰብ አለበት። በተለይ በሩዋንዳ የተካሄደው ዘግናኝ ዕልቂት ቤተ ክርስቲያን ይህን ቊስል ለማከም ምንም የሚረባ ሥራ አለመሥራቷን ያጋለጠ ጭምር ነው። በአገሪቱ የክርስቲያኖች ቍጥር ማየሉ ችግሩን ከመከሰት አላዳነውም። እንዲያውም በአንዳንድ ስፍራዎች አብያተ ክርስቲያናትም የጭፍጨፋው ተካፋዮች እንደ ነበሩ መረጃዎች ወጥተዋል።

የእግዚአብሔር መንግሥት ለዘረኝነት ቦታ የለውም።

ጌታችን ከስቅለቱ በፊት እንኳ ለማፍረስ የተጋበትን የዘር ግምብ ዛሬ እኛ በሌላው ወገናችን ላይ በጥርጣሬና በአግላይነት ልንገነባ እንሻለን። ሞቱና ትንሣኤው መወጋገድን ሳይሆን መቀባበልን ነው የሚያመጣው። ኬቪን ኮነር “ቤተ ክርስቲያን በዓለም ውስጥ እግዚአብሔር በአዲስ ብሔርነት ያበጃት ፍጥረት ናት፤ በብሔር ላይ የተመሠረቱ ክፍፍሎች ሕልውናቸው በኢየሱስ ክርስቶስ አክትሟል” ይላሉ።[7] ይህ ገብቶን ቢሆንማ ኖሮ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ብሔር ተኮር ክፍፍሎች ሲራገቡ እና ልዩነቶች ሲወጠሩ እናይ ነበርን? በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን በዚህ ርእሰ ጒዳይ ላይ አትኲሮቷን አድርጋ ካልሠራች፣ ሰዎች አማኝ ስለሆኑ ብቻ ሁልጊዜም ተኣምር እየተከሰ እያንዳንዳችን የየራሳችንን “ሳምራውያን” በፍቅር እንቀበላለን ማለት አይደለም። ለውጥ የግድ በተኣምር ብቻ አይመጣም፤ የሚያሳዝነው ግን ለረጅም ጊዜ ዐቅዶ በመትጋት የሚመጣውን ለውጥ የምድራችን ቤተ ክርስቲያን የምታውቀው አትመስልም። አሁን ግን አማራጭ የቀረልን አይመስልም፤ በውስጥም በውጭም ያለውን በዘር ላይ የተመሠረተ ፍርሀት፣ ጥርጣሬና የሥልጣን ትግል ለማክሰም ዛሬ መትጋት ከነገ ውድቀት ይታደገናል። ግና ነገን ባሻገር ተመልክተው፣ ዛሬ በማስተዋል የሚያቅዱ መሪዎች አሉንን? በመካከላችንስ ኖረው ያውቃሉ?

[1] George W. Knight and Rayburn W. Ray, The Layman’s Bible Dictionary (Uhrichsville: Barbour Publishing, 1998).

[2] NIV Study Bible (Grand Rapids: Zondervan, 2002) 1633.

[3] ዝኒ ከማሁ።

[4] ዝኒ ከማሁ፤ 1590.

[5] Philip Yancey, Vanishing Grace (Grand Rapids: Zondervan, 2014) 26-27።

[6] NIV Study Bible (Grand Rapids: Zondervan, 2002) 1605

[7] J. Kevin Conner, The Church in the New Testament (Portland: Bible Temple, 1989) 11.

Share this article:

“ብቻህን ለመቆም ተዘጋጅ”

“እግዚአብሔር የሁላችን አምላክ መሆኑ ርግጥ ነው። ግና የሁላችን አምላክ የእኔ፣ የልቤ፣ የግሌ አምላክ እንዳይሆን ምን ይከለክለዋል? “እኛ” “እኔ”ን ያስቀራልን? “እኛ” የተሠራው ከ“እኔ” አይደለምን?” ጳውሎስ ፈቃዱ

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.