[the_ad_group id=”107″]

ቃል፤ ምጡቅ፣ ፈጣሪ ኵሉ፣ ሥግው

በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ። ዘፍ. 1፥1

በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ። እርሱም በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ። ዮሐ 1፥1-2

በመጀመሪያ ነበርና ከሁሉ በፊት ቃል ኖሯል፤ መጽሐፉ ብሏል፡፡ 

ፍጥረት ሳይጀመር በፊት፣ መጀመሪያ ሳይጀመር በፊት፣ ከፍጥረት ጅማሮ ማዶ ቃል ኖሯል፤ “ገና ገና”፣ “አምና ዘንድሮ”፣ “ባለፈው ወር፣ በዚህ ወር” ሳይባል፣ “ትላንት ዛሬ፣ ነገ” ማለት ሳይጀመር፣ ቅድም አሁን በኋላ ትርጉም ሳያገኙ በፊት፣ የሰከንድ ደቂቀ ደቂቅ ሳይታወቅ፣ ማለትም ጊዜ “ሀ” ሳይባል፣ መጠን ኖሮት ሳይለካ፣ ገና መስፈሪያው “ዜሮ” ሆኖ ሳለ ከጊዜ “ማዶ” ከጊዜ “አስቀድሞ” ቃል ኖሯል፤ መጽሐፉ ብሏል፡፡

ይህ ቃል ከፍጥረት ሁሉ በፊት ከፍጥረት ማዶ በኩሮ ነበር፡፡ ሥፍራ (space) ብቅ ሳይል፣ ሳይዘረጋ፣ ሳይዘረጋጋ ከፍጥረት አካላት ጋር ሳይተዛዘል፣ መጠን ባልተሠፈረበት፣ አድራሻ ባልተጠቆመበት፣ በማይጠቆምበት በስቲያ ቃል ኖሯል፤ መጽሐፉ ብሏል፡፡

“የት?” ባልተባለበት፣ “መቼ?”  በማይባልበት፣ ሥፍራን እና ጊዜን መጥቆ፣ አምላክ-ቃል በየት-የለሄነት፣ በመቼ-የለሄነት ኖሯል፡፡ ደግሞም ሁሉ በእርሱ ተፈጥሮአል፤ መጽሐፉ ብሏል፡፡

ቁስ አካል ገንቢ አተሞች፣ አተም ገንቢ ኳርኮች፣ ሊፕቶኖችና ቦሦኖች ብናብኖች ሳይኖሩ፣ ግዑዝ ኀይላት፣ ስበት ድኩምና ክቡድ ኒክለየር ኀይላት፣ ጨረራ ጨረሮች ሳይከሰቱ፣ ወደ ሕላዌ ሳይመጡ ቃል ነብሯል፡፡ ኋላም እኒሁን ሁሉ ወደ መኖር አምጥቶአል፤ ሁሉ በእርሱ ተፈጥሯል፤ መጽሐፉ ብሏል፡፡

መቼም ጊዜና ሥፍራ ንክር በሆነ ቋንቋ፣ ጊዜና ሥፍራ ዝፍቅ በሆነ ቋንቋ፣ ጊዝ-መጠቅ፣ ስፍራ-መጠቅ እውነታ እውነትን፣ ዘላለም ቀመስ እውነትን ቀጥ እና ግልጽ አድርጎ ማስተላለፍ አዳጋች ነው፤ ዘይቤአዊ አነጋገርን መጠቀም የግድ ነው፡፡ ቃል እምቅድመ ፍጥረት ነበረ፤ ከአምላክ ጋር ነበር፤ ቃልም አምላክ ነበረ፡፡ ቃል የፍጥረት አካላትን የሥፍራና የጊዜ ቁርኝ ሸማ ዘንድ አኖራቸው፡፡ በሸማ ላይ ጥልፍ እንደሚጠለፍ ጥበብ እንደሚነደፍ፣ የፍጥረት ቁስ አካላትን በሥፍራ-ጊዜ ቁርኝ ሸማ ላይ ነድፎአቸዋል፤ ጠልፎአቸዋል፡፡ ጊዜንና ሥፍራን እንደ ድርና ማግ ሸምኖ ከፍጥረት አካላትና ኀይላት ጋር አዋስቦ እንደ ዣንጥላ ዘርግቷቸዋል፤ እንደ ድንኳን ወጥሮአቸዋል፡፡

“… ሰማያትን እንደ ድንኳን መጋረጃ ዘረጋህ” (መዝ. 104፥2)  መዝሙረኛው ብሏል፡፡

በሥፍራ ሰበዝ በጊዜ አክርማ እንደ ተሰፋ ሰፌድ፣ በሰፌድም ላይ እንዳለ እህል ጥራጥሬ፣ የሰማይ አካላትን እያበጠረ፣ እያንገዋለለ፣ እያነፈሰ፣ እያንቀረቀበ በኀይሉ ቃል ደግፎ ያኖራቸዋል፡፡ ከዋክብትን ያንከወክዋቸዋል፤ በሥርዐቱ ያዟዙራቸዋል፡፡ ቁጥራቸው እንደ ምድር አሸዋ የሆኑትን ከዋክብት፣ የሰማይ ምድጃዎችን፣ የቶን እሳት ኳሶችን፣ አፅናፈ ዓለም-ዘለቅ የጨለማ ንጣፍ ውስጥ እንደ ፈንድሻ ቆሎ በትኖ ያኖራል፡፡ የኒኩሊየር ፊውዥን መናኸርያ ሆነው፣ በኑክሊየር ፍንዳታ ተሞልተው ነጠላም ፈትልም ጨረሮችን እየረጩ ይተማሉ፡፡ ቀበሌኛ እግረ አጫጭር (high frequency/short wave length) እነ ላዕላይ ወይናማ (አልተራ ቫዮሌት) ጨረሮችን፣ ረዥም ተጓዥ እግረ ረዣዥም (low frequency) እነ ታህታይ ቀያማ (ኢንፈራ ሬድ) ጨረሮችን፣ በሕዋ ውስጥ አስርጾ የሚያኖር፣ ሰባቱን ቀለማተ-ጨረር ፈትሎ ቀይጦ ብርሃንን ለሰው፣ ለእንሰሳት፣ ለዕጽዋት የሰጠ እርሱ፣ በጨለማ ብርሃን ይሁን ያለ ነው፡፡ እርሱ የከዋክብትን ቁጥር ያውቃል፡፡ እያንዳንዱንም በስሙ ይጠራዋል (መዝ. 147፥4)፤ መጽሐፉ በሏል፡፡

ጽልም ግዑዝ ኀይላት እና ጽልም ከዋክብት፣ ብርሃን ሰልቅጥ ጉድጓድ አካላት (Black hole) ጭምር የእርሱ ሥራ ናቸው፡፡ የከዋክብትን ሰራዊት አንድ በአንድ የሚያወጣቸው በየስማቸው የሚጠራቸው እርሱ ነው፡፡ ከኀይሉ ታላቅነት፣ ከችሎታው ብርታት የተነሣ አንዳቸውም አይጠፉም (ኢሳ. 40፥26)፤ ይላል መጽሐፉ፡፡

እያንዳንዶቹን ከዋክብት እንደ ፀሓይ ያሉትን በእዝል ጀሌ ሥልጡን ፕላኔቶች አጎናጽፎአቸዋል፡፡ የእኛ ፀሓይ ባለ ዘጠኝ ፕላኔት ናት፡፡ እኒህም ፕላኔቶች በፀሓይ የስበት ጉልበት ተሸንፈው ከፀሓይ ጋር እንዳይላተሙና እዚያው ተቀብረው እንዳይቀሩ፣ አሊያም ባላቸው የግልቢያ ፍጥነት ብልጫ ከምህዋራቸው ተወንጭፈው ወጥተው እንዳይመረትቱ፣ ʻእንደ ወጣች ቀረችʼ እንዳይሆኑ፣ ፈጣሪ በጥበቡ አንጻራዊ ክብደታቸውን፣ ርቀታቸውን፣ ፍጥነታቸውን አጣጥሞ የፀሓይ ቤተኛም፣ ተጠቃሚም አድርጎ ያኖራቸዋል፡፡ ፀሓይ ለምድራውያኑ ኀይልን በመለገስ የዘወትር ባለውለታ ነች፡፡ ምድርም መኖሪያዋን ዐውቃ ጨረቃን አንግባ በዙሪየዋ ትሾራለች፤ በሰዓት በ 103,000 ኪ.ሜ ፍጥነት ትነጉዳለች፡፡

የሰማያትን ሥርዐት ታውቃለህ? ይህንስ በምድር ላይ እዲሰለጥን ማድረግ ትችላለህ?” (ኢዮ. 38፥33) ለኢዮብ የቀረበ ጥያቄ ነበር፡፡ ሁሉ በእርሱ ተፈጥሮአል፤ መጽሐፉ ብሏል፡፡

“ምድር በክብሩ ተሞልታለች” ብለው እነሱራፌል እንዳዜሙት፣ በአየር፣ በውሃ ታድላለች፣ ዕጽዋትን፣ እንሰሳትን ታኖራለች፤ እስትንፋሰ አምላክ ለሰረፀበት ለሰው መኖሪያነትም በቅታለች፡፡ አዎ ምድር በክብሩ ተሞልታለች፤ የእጁ አሻራ፣ የዐሳቡ ጥልቀት፣ የጥበቡ ርቀት፣ የማስተዋሉ ጥልቀት፣ በሥፍነ ተክል፣ በዕጽዋት ዓለም፣ በሥፍነ እንሰሳ፣ በእንሰሳት ዓለም፣ በሰውም ምንነት ዘንድ ይታያል፡፡ እፁብና ድንቅ ሥራው ተገልጧል፡፡ ተመርምሮ፣ ተነግሮ፣ ተተርኮ መች ያልቃል?! ሁሉ በእርሱ ተፈጥሮአል፤ መጽሐፉ ብሏል፡፡

የሰውን አካል ቢልየን ጊዜ ቢልየን ጊዜ ቢልየን በላይ በሆኑ አተሞች፣ በአማካይ ከ60 እስከ 70 ትሪልየን (ሚሊዮን ጊዜ ሚሊዮን) በሚሆኑ ሕዋሳት አዋስቦ መስቀለኛ ቅርጽ ባለው ላምኒን ፕሮቲን ሞለኪውል አያይዞ የሠራበት ጥበብ ድንቅ ነው፡፡ በቅንጣት ሕዋስ ዓለም ዘንድ ያለ ውስብ ውስብስብ የመፈብረክ ሥርዐት፣ የፈራረሱትን አባዝቶ ነድፎ እንደገና የመፍተል፣ በትኖ እንደገና የማሰናሰል ሥርዐት፣ የግንኙነት፣ የምልልስ፣ የማጋፈር፣ የተራክቦ ሥርዐት፣ የማጥራት የጽዳት ሥርዐት፣ የአስተዳደር የጥበቃ ሥርዐት ትንግርት ነው፡፡ በእነዚህ ከፀጉር ውፍረት 1/4ኛ በማይበልጡ ሕዋሳት በእያንዳንዳቸው ውስጥ በብዙ ብዙ ሺህ የሚቆጠር ዓለመ አካላትን አኑሮአል፡፡ እኒህ ጥቃቅን አካላት በረቀቀ መንገድ ከ30 በማይበለጡ ልዩ ልዩ ንጥረ ነገሮች፣ አያሌ አተሞች ተሰናስለው የተበጁ ናቸው፤ ኀላፊነታቸውንም ያውቃሉ፡፡ (ዋንኞቹ ንጥረ ነገሮች በቅደም ተከተል ኦክስጅን፣ ካርቦን፣ ሃይድሮጅን፣ ናይትሮጅን፣ ካልሽየም፣ ፎስፎረስ፣ ፖተሽየም፣ ሳልፈር፣ ሶድየም፣ ማግንዠየም ሲሆኑ አንድ ላይ 99 % ይሆናሉ፤ የሌሎቹ የኮፐር ዚንከ፣ ሴሌኒየም፣ ሞሊቢደነም፣ ፍሎሪን፣ ክሎሪን፣ አዮዲን፣ ማንጋኔዝ፣ ኮባልት፣ ዐይረን፣ ሊትየም፣ ሰትሮንትየም፣ አሉሚንየም፣ ሲሊከን፣ ሊድ ቫናድየም፣ አርሴኒክ እና በሮማይን ጥንቅር ደግሞ 1 % ይሆናል፡፡)

እያንዳንዱ ሕዋስ በውስጠኛ ሥፍራው በአስኳሉ ውስጥ የዕዝ ማዕከል፣ የመረጃ ቋት፣ የመረጃ ማኅደር የሆነ መሰላላማ የDNAን ድውር ክር ተቀምጧል፤ ቢዘረጋ እስከ ሁለት ሜትር ይደርሳል፡፡ በአንድ ሰው አካል ሕዋሳቱ ያሉቱ ቢቀጣጠሉ፣ ቅጥልጥሉ ከመቶ ቢልየን ኪሎ ሜትር በላይ ይረዝማል፡፡ በአንድ የDNA መሰላላማ ክር ዘንድ ተመዘግቦ የሚገኝ መረጃ በብሪታኒካ ኢንሳይክሎፒዲያ መድበለ መጽሐፍት ውስጥ ከሚገኙ የመረጃዎች ብዛት ጋር እንደሚስተካከል ይገመታል፡፡ ሌላው ሕዋሳት ኑረው ኑረው “ሙቱ” የሚል ትዕዛዝ ሲደርሳቸው ትዕዛዙን ተቀብለው የሚሞቱ ናቸው፤ በሌላ ይተካሉና፡፡ ሙሴ ʻከተራራው ውጣና በዚያው ሙትʼ እንደተባለና ታዞ ተራራውን ወጥቶ በዚያው እንደ ሞተ ማለት ነው፡፡ እኒህ ሕዋሳት እስከ ሞት ድረስ የሚታዘዙ ናቸው፡፡ የሙት ትዕዛዝ ወጥቶ አንሞትም ብለው መኖር፣ መባዛት ከቀጠሉ አካል በካንሠር በሽታ ተወረረ ማለት ነው፡፡

ፈጣሪ ሰውን ግዙፍ አካል ብቻ ሳይሆን ረቂቅ መንፈስም አድርጎ አበጀው፤ ባዮ-ኬሚካዊ፣ ሥነ ልቡናዊ ወማኅበራዊ፣ ደግሞም መንፈሳዊ አድርጎ ሸረበው፡፡ የራስ ልውና ግንዛቤ ያለው፣ ዕሳቤ፣ ፈቃድ፣ ኅሊና፣ ስሜት፣ ትዝታ፣ ናፍቆትን የተላበሰ አደረገው፤ ባለ እንቅልፍ ዓለም፣ ሕልም ተመልካች፣ ድምፅ አውጥቶ የመናገር፣ ቋንቋም የመቀመር ብቃት አላበስው፤ ልዩ ልዩ ፍላጎቶችንም አሳደረበት፡፡ መዝሙረኛው “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፡፡ ሥራህ ድንቅ ነው ነፍሴም በውል ተረድተዋለች”  (መዝ. 139፥4) ያለው ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡

ሌላው ነገር፤ ይህች ምድረ-ዓለም በዲያብሎስ ተደሽቃለች፣ በሳጥናኤል ተደቅታለች፣ መርዙንም ተጎነጭታለች፡፡ ሆኖም ፈጣሪዋን ቃል-ሥጋን አስተናግዳለች፡፡ ዳሩ ግን ውላ አድራ ቃል-ሥጋን አሰቃይታ ገድላለች፣ ቀብራለች፡፡ ተፀፅታ አቅምም አጥታ፣ ስበቷን አሟሻ፣ መቃብሩን ከፍታ ለቃዋለች፡፡ ዛሬ ዛሬ በእርሱ ተመልሳ መታደስን ትናፍቃለች፤ ከፍጥረት ሁሉ ጋር ሆና ትቃትታለች፡፡ ይሁንና ይህ መርገም ለሰው ልጆች በረከት፣ ሞቶ መነሣቱም ትንሣዔና ሕይወት ሆኗል፤ ይመስገነው!

ቃል ሥጋ ሆኗል፤ ከዘላለም ከመች-የለሄነት ወጥቶ ጊዜ ውስጥ ገብቷል፤ ከየት-የለሄነት ወጥቶ ጸጋና እውነት ተሞልቶ በሰዎች መካከል አድሯል፡፡ በምድር እያለ፣ ሳለ በአባቱ እቅፍም ያለ ነበረ፡፡ “በአብ እቅፍ ያለው አንድያ ልጁ የሆነው እርሱ ገለጠው” (ዮሐ. 1፥18)፤ ብሏልና ቃሉ፡፡

የእግዚአብሔር ልጅ በጲላጦስ ፊት በቀረበበት ወቅት፣ ጲላጦስ እንዳይደናገጥ ያበቃውን ቃል አሰማው፤ ምድራዊ መንግሥት ሊያቋቁም እንዳልመጣ አሳወቀው፡፡ “እኔ የተወለድሁት፣ ወደ እዚህ ዓለም የመጣሁት ለእውነት ልመሰክር ነው፡፡ ከእውነት የሆነ ሁሉ ይሰማኛል፡፡” አለው፡፡

እርሱ ለእውነት መሰከረ፤ እግዚአብሔር አብ እርሱ ብቻ እውነተኛ አምላክ እንደ ሆነ፣ መንፈስ ቅዱስም የእውነት መንፈስ፣ ወደ እውነትም ሁሉ የሚመራ እንደ ሆነ፣ እርሱ ራሱም መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት እንደ ሆነ መሰከረ፤ መንገድ ሊሆንልን እውነት ሊሆንልን፣ ሕይወት ሊሆንልን፣ ጠራን፣ ጋበዘን፣ ራሱን ሰጠን:: “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝም የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ ከቶ በጨለማ አይመላለስም” አለን፡፡

መንገድ የለሽ፣ መድረሻ የለሽ ተጓዦች፣ ተቅበዝባዦች እንዳንሆን፣ የትም ላለመድረስ ዘመናችን ሁሉ መሄድ! መሄድ! መሄድ! መባዘን ብቻ እንዳይሆንብን፤

እውነት የለሽ ዐዋቂዎች – በሐሰት ተኮፋሾች እንዳንሆን፣

ሕይወት የለሽ ነዋሪዎች – ሆነን መና እንዳንቀር፣

እኔ መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወትም ልሁንላችሁ አለን፡፡

ቤተ ክርስቲያን በእርሱ የእውነት ዐምድና መሠረት ሆነች (የዛሬዋ እንደዚያ ናት? ሌላ ጥያቄ ነው)፡፡

የእርሱ ደቀ መዛሙርት፡- የብርሃን ልጆች፣ የእውነት ማኅበርተኞች/የእውነት ምስክሮች፣ በፍጻሜ “ኑ እናንተ የአባቴ ብሩካን” ተባዮች ናቸው፡፡

ክብር ለእግዚአብሔር አብ

ክብር ለእግዚአብሔር ወልድ

ክብር ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ! አሜን!!!

Endasahaw Negash

ጽዋ ሲሞላ

በአንዳንድ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም ሚኒስትሪ መሪዎችና አገልጋዮች ዙሪያ ያሉትን ድክመቶች አስመልከቶ ለየት ባለ ግልጽነትና ʻአሁንስ በዛʼ ብለው የተነሡ ይሆኑ? በሚያሰኙ ብዕሮች የተጻፉ የሚመስሉ ጠንከር ያሉ መልእክቶች በመጽሔቶች አማካይነት ብቅ ብቅ እያሉ ነው። ደስ ይላል።

ተጨማሪ ያንብቡ

መስቀሉ፦ ሲሞን ቬይ

የክርስቶስ ስቃይ ያለ ጥርጥር ልዕለ ተፍጥሯዊ ፍትሕ ነው። ያሉትን የርኅራኄ ርዳታ ሁሉ ፍጹም የከለከል ፍትሕ ነው፤ የእግዚአብሔር አብ ፍቅር እንኳ እንዳይራራለት ያደረገ ፍትሕ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ

ለማነጽ እንሠራለን!

ሕንጸት ክርስቲያናዊ ማኅበር፣ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና ስለ ወንጌሉ እውነት እንዲሁም እርሱ ስለ መሠረታት ቤተ ክርስቲያን ግድ የሚላቸው ሰዎች ተሰባስበው ያቋቋሙት መንፈሳዊ ማኅበር ነው፡፡ ማኅበሩ በምድራችን ላይ ያለችው ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን፣ ክርስቶስን መስላ እንድታድግ በሚደረገው የማነጽ ሂደት ውስጥ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ያለመ ነው፡፡ ስያሜውም ይህንኑ የሚገልጽ ነው፤ “ሕንጸት” የግዕዝ ቃል ሲሆን፣ “ማነጽ” ወይም “መገንባት” የሚለውን ፍቺ ይይዛል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.