[the_ad_group id=”107″]

የጳውሎስ መልእክት ወደ ቲቶ ጤናማ ትምህርት – ጤናማ ኑሮ (ክፍል 2)

በአንድ ወቅት ከአንድ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ጋር በታክሲ እየተጓዝን፣ ከቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች መካከል አንዱን አገኘን፡፡ ይህም ሰው ሞቅ ያለ ሰላምታ ከሰጠኝ በኋላ አብሮኝ የነበረውን አገልጋይ ስሙን በመናገር ለመተዋወቅ ሞከረ፡፡ በዚህ ጊዜ ግራ የተጋባው ወዳጄ ስሙን በመጥቀስ “እከሌ እኮ ነኝ” በማለት ሊያስታውሰው ሞከረ፡፡ የሚያሳዝነው ግን የቤተ ክርስቲያን መሪው ሊያስታውሰው አልቻለም፤ በድፍረትም እንደማያውቀው ተናገረ፡፡ እኔም በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አብረው እያገለገሉ ያሉ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌንና በብዛት የእሑድ አምልኮ ፕሮግራም ይመራ የነበረውን ወንድም ለማስተዋወቅ ተገደድሁ፡፡ ይህ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ የተደራረበ ሥራ ያለው ከመሆኑ የተነሣ ከቅዱሳን ጋር ኅብረት ለማድረግ ወደ እሑድ አምልኮ ፕሮግራም ከሚመጣበት የማይመጣበት ጊዜ ይበዛ ነበር፡፡

ምናልባት አንዳንዶቻችሁ እንዲህ ዐይነቱ ጊዜ የሌለው ሰው እንዴት የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ሆኖ ተመረጠ ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል፡፡ ጥያቄው ተገቢ ጥያቄም ይመስለኛል፡፡ ይህ ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን በብዛት መምጣት ባይችልም፣ ጥሩ ሥራ ስላለው ጥሩ ገንዘብ ለቤተ ክርስቲያን ይሰጣል፡፡ ምናልባት የሚሰጠው ገንዘብ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ሆኖ እንዲመረጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጎ ሊሆን ይችላል፡፡ በወቅቱ ይህ አጋጣሚ ቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ስትመርጥ የምትጠቀምባቸውን መሥፈርቶች ቆም ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል፡፡ ይህንን ባሰብኩበትና ተጨማሪ ምልከታ ባደረኩበት ወቅት የደረስኩበት ነገር ቢኖር፣ በብዙ ሥፍራ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሲመረጡ በጥቅም ላይ የሚውሉት መሥፈርቶች ተመሳሳይነት ያላቸው መሆናቸውንና በተወሰነ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አለመሆናቸውን ነው፡፡ ከእነዚህ መሥፈርቶች መካከል ጥሩ ሥራ ያለውና ዐሥራት የሚከፍል (ዐሥራት ከሚከፍሉትም ውስጥ ሞቅ ያለ ገንዘብ የሚያመጡ ቅድምያ ሊሰጣቸው ይችላል)፣ ነጋዴ፣ የተማረ (ለምሳሌ፡- ዶክተር፣ ኢንጂነር፣ ፓይለት፣ …)፣ ጓደኝነት፣ ወዘተ… ለአብነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

በርግጥ ይህንን ስል አንደኛ፣ ሁሉም ቦታ መሥፈርቶቹ እነዚህ ብቻ ናቸው ማለቴ አይደለም፤ ሁለተኛ፣ ገንዘብ ያላቸውና የተማሩ ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን እንዲመሩ መመረጥ የለባቸውም ማለቴም አይደለም፡፡ በአንጻሩ መሥፈርቶቹ ምን ያህል መጽሐፍ ቅዱሳዊ ናቸው የሚለውን ለመቃኘት ነው፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ስንመርጥ ልብ ልንላቸው የሚገቡንን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሥፈርቶች እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡ ባለፈው የሕንጸት ዕትም የቲቶን መልእክት መግቢያ (1፥1-4) የተመለከትን ሲሆን፣ በዚህኛው ደግሞ ቲቶ 1፥5-9 አብረን እናጠናለን፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በቀርጤስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለነበረው ለቲቶ ይህንን መልእክት ሲጽፍ ከመግቢያ ክፍል ቀጥሎ በቀጥታ የተሻገረው ወደ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች መመዘኛ ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን መሪዎች መጀመሩ ምናልባት በቀርጤስ የነበረውን የተበላሸ ሁኔታ በማስተካከል አማኞች ከአማኞች ጋር እንዲሁም አማኞች ከማያምኑ ሰዎች ጋር ጤናማ ግንኙነት እንዲኖራቸው መሪዎች ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ለማሳየት ሊሆን ይችላል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ውጤታማና ፍሬያማ መሆን የምትችው ትክክለኛ መሪዎች (ጸጋው ያላቸው)፣ በትክክለኛ መሥፈርት የተመረጡ ሲሆኑ ነው፡፡ ለቅዱስ ጳውሎስ ክርስትና መሪዎቹን ይመስላል፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ራሱን እንደ ዐርአያ በማስቀመጥ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” በማለት የተናገረው፡፡ ዛሬም ቢሆን ክርስትና፣ የአስተማሪዎቹንና የሰባኪዎቹን ኑሮ እና አገልግሎት ይመስላል ቢባል ሐሰት አይሆንም፡፡

አንተን በቀርጤስ የተውሁህ ገና ያልተስተካከለውን ነገር እንድታስተካክልና ባዘዝሁህ መሠረት በየከተማው ሽማግሌዎችን እንድትሾም ነው (1፥5)

ቲቶ 1፥5 የደብዳቤው ዋና ዓላማ የሰፈረበት ቁጥር ነው፡፡ በዚህ ቁጥር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ቲቶን በቀርጤስ የተወበት ሁለት ምክንያቶች ተጠቅሰዋል፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት ያልተስተካከለውን ነገር እንዲያስተካክል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በታዘዘው መሠረት በየከተማው ሽማግሌዎችን እንዲሾም ነው፡፡ ባለፈው ዕትም ቅዱስ ጳውሎስ ከሮም እሥር ቤት ከተፈታ በኋላ ጢሞቴዎስንና ቲቶን ይዞ ወደ ቀርጤስ በመምጣት ወንጌልን መስበካቸውንና ከፍተኛ ተቃውሞ ስለ ገጠማቸው ቲቶን በዚህ ትተው መሄዳቸውን ማንሣታችን የሚታወስ ነው፡፡ ብዙ ያልተስተካከሉና ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ነገሮች ስለ ነበሩ ቲቶ እነዚህን በጅምር ያሉና መስተካከል ያለባቸውን ጉዳዮች እንዲያስተካክል ታዟል፡፡ በተጨማሪም፣ በየከተማው ሽማግሌዎችን እንዲሾም መመሪያ ተሰጥቶታል፡፡ ቲቶ 3፥12 እንደሚያመለክተው ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ቲቶ በዚህ ያለውን ሥራ በማጠናቀቅ ወደ ኒቆጵልዮን ተጉዞ ከጳውሎስ ጋር ይገናኛል፡፡ ከመሄዱ በፊት ግን ጅምር ሥራዎችን ማጠናቀቅና የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን (ሽማግሌዎችን) መምረጥ ይኖርበታል፡፡ ይህ ቁጥር እንደሚያመለክተው ቤተ ክርስቲያን የምትመራው በሽማግሌዎች (ከአንድ በላይ ሰዎች በሚሳተፉበት አመራር) ነው፡፡ ቀጣዮቹ ቁጥሮች ቲቶ ሽማግሌዎችን ሲመርጥ ምን ዐይነት መሥፈርቶችን መጠቀም እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡

6ሽማግሌ ነቀፋ የሌለበት፣ የአንዲት ሚስት ባል፣ ልጆቹም አማኞችና በመዳራት ወይም ባለመታዘዝ ስማቸው የማይነሣ ይሁን፡፡ 7ኤጲስ ቆጶስ የእግዚአብሔር ሥራ ባለ ዐደራ እንደ መሆኑ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋል፤ ይኸውም፣ ትምክሕተኛ፣ ግልፍተኛ፣ ሰካራም ጨቅጫቃና ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለጥቅም የሚሮጥ ሊሆን አይገባም፡፡ 8ከዚህ ይልቅ እንግዳ ተቀባይ፣ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፣ ራሱን የሚገዛ፣ ቅን፣ ቅዱስና ጠንቃቃ ሊሆን ይገባል፡፡ 9ሌሎችን ትክክል በሆነ ትምህርት እንዲያበረታታና ይህንኑ ትምህርት የሚቃወሙትን ይወቅስ ዘንድ እንደ ተማረው በታመነ ቃል የሚጸና መሆን አለበት (1፥6-9)፡፡

እነዚህ መመዘኛዎች በ1ኛ ጢሞቴዎስ ምእራፍ ሦስት ላይ ከተሰጡት መመዘኛዎች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ ሽማግሌዎች፣ ኤጲስ ቆጶስ፣ ወዘተ… በተለዋዋጭነት አንዱን የአገልግሎት ክፍል ለመጥራት በጥቅም ላይ የዋሉ ስያሜዎች ናቸው፡፡ ቁጥር 6፣ የቤተ ክርስቲያን መሪ (ሽማግሌ፣ ኤጲስ ቆጶስ) ነቀፋ የሌለበት ሊሆን እንደሚገባ ይናገራል፡፡ ቁጥር 7ሀ እንደሚያመለክተው ኤጲስ ቆጶስ የእግዚአብሔር ሥራ ባለ ዐደራ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የእግዚአብሔር ሥራ ባለ ዐደራዎች መሆናቸውን ይህ ቁጥር ያስገነዝባል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሕያው እግዚአብሔር ቤት ስትሆን፣ መሪዎች ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር በሥራው ላይ የሾማቸው ባለ ዐደራዎች ናቸው፡፡ የእግዚአብሔር ሥራ ባለ ዐደራዎች እንደ መሆናቸው መጠን ደግሞ ነቀፋ የሌለባቸው እንዲሆኑ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሽማግሌ ቤተ ሰቡን በሚገባ በመምራት አኳያ ነቀፋ ሊታይበት አይገባም፡፡ “የአንዲት ሚስት ባል” የሚለውን ሐሳብ የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ መንገዶች ይፈቱታል፡፡ ለመጥቀስ ያህል፡- (1) የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ መሆን የሚችለው ያገባ ሰው ብቻ ነው፤ (2) በተለያዩ ምክንያቶች አግብቶ የፈታ ሰው የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ መሆን አይችልም፤ (3) ድርብ ጋብቻ ውስጥ ያለ ሰው የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ መሆን አይችልም እና (4) የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ የሆነው ሰው ያገባ ሰው ከሆነ ለሚስቱ በመታመን ዐርአያ መሆን አለበት የሚሉት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ የእያንዳንዱን አመለካከት ጥንካሬና ውስንነት ማብራራት ሰፊ ቦታን ይወስዳል፡፡ በተለምዶ ይህን ጥቅስ በመጥቀስ ሽማግሌ መሆን የሚችለው ያገባ ሰው ብቻ ነው ቢባልም፣ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ላገባት ሚስቱ ታማኝ የሆነና በኑሮው ነቀፋ የሚለው በዐውዱ ውስጥ የተሻለ ትርጉም ይሰጣል፡፡ በተጨማሪም፣ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ለሚስቱ ታማኝ መሆን ብቻ ሳይሆን ልጆቹንም በአግባቡ እንዲያሳድግ ይጠበቅበታል፡፡ በተለይም ልጆቹ በእርሱ አመራር ሥር ባሉበት ጊዜያት ሁሉ እንደ እግዚአብሔር ቃል በሚሄዱበት መንገድ በመምራት ለሌሎች ዐርአያ እንዲሆኑ የአባትነት ድርሻውን መወጣት አለበት፡፡

ቁ. 7ለ እና ቁ. 8 የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ምን መሆን እንደሌለባቸው (በምን በምን ነቀፋ የሌለባቸው መሆን እንደሚገባቸው) አምስት ነጥቦችን እንዲሁም ምን መሆን እንደሚገባቸው ስድስት ነጥቦችን ያመለክታሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሪ (ሽማግሌ) ሊሆን የማይገባቸው አምስቱ እኩይ ባሕርያት የሚከተሉት ናቸው፡- (1) ትምክሕተኛ፣ (2) ግልፍተኛ፤ (3) ሰካራም፣ (4) ጨቅጫቃ እና (5) ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለጥቅም የሚሮጥ ሊሆን አይገባም፡፡ በአንጻሩ የቤተ ክርስቲያን መሪ (ሽማግሌ) ሊሆን የሚገባቸው ስድስት ሰናይ ባሕርያት፡- (1) እንግዳ ተቀባይ፤ (2) በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፤ (3) ራሱን የሚገዛ፤ (4) ቅን፤ (5) ቅዱስ፤ እና (6) ጠንቃቃ ሊሆን ይገባል፡፡ እነዚህን እኩይ እና ሰናይ ባሕርያት አንድ በአንድ ማብራራት ከቦታ አኳያ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ፣ እያንዳንዱ ነጥብ ግልጽና ለመረዳት የማያስቸግር መሆኑን መናገር ይቻላል፡፡

የመጨረሻው ቁጥር (ቁጥር 9) የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ እንደ ተማረው በታመነ ቃል የሚጸና መሆን እንዳለበት ያሳስባል፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ለዚህ አስረጅ አድርጎ ሁለት ነጥቦችን አስቀምጧል፡- የቤተ ክርስቲያን መሪ በተማረው ቃል በመጽናት ዐርአያ መሆን አለበት፤ ምክንያቱ ቢባል አንደኛ፣ ሌሎችን ትክክል በሆነው ትምህርት ማበረታታት እንዲችል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ እውነተኛውን ትምህርት የሚቃወሙትን ይወቅስ ዘንድ ነው፡፡ መሪ (ሽማግሌ) ነቀፋ የሌለበት ከሆነ ሌሎችን በትክክለኛ ትምህርት ማስተማርና ማበረታታት ይችላል፤ በሌላ አገላለጽ ሌሎች በጽድቅ ሕይወት እንዲመላለሱ በድፍረት ማዘዝ አቅም ያገኛል፡፡ ሌላው የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ በተማረው ቃል በመጽናት ነቀፋ የሌለበት ከሆነ ተቃዋሚዎችን (የሐሰት አስተማሪዎችን) በድፍረት መገሰጽም ሆነ መቃወም ይቻለዋል፡፡

በዚህም ዘመን የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ስንመርጥ ከላይ ባየነው ክፍል እንዲሁም በ1ኛ ጢሞቴዎስ ሦስት ላይ የተዘረዘሩትን መሥፈርቶች በመከተል መሆን አለበት፡፡ የሥልጣን ምንጫችን የሆነውን የእግዚአብሔርን ቃል ቸል በማለት የራሳችን የሆኑትንና የሚመቹንን መመዘኛዎች መከተል ቤተ ክርስቲያን ፍሬያማ እንዳትሆን ከማድረጉም በላይ ለተለያዩ ችግሮች ይዳርጋታል፡፡ ገንዘብን፣ ሥልጣንን፣ ዕውቅናን፣ ጓደኝነትን፣ ወዘተ… ተመልክተን ሳይሆን በትክክል ጸጋው ያላቸውንና እነዚህ ባሕርያት የተገለጡባቸውን ሰዎች ወደ ሽምግልና አገልግሎት ልናመጣ ይገባል፡፡

በመሆኑም፣ ስለ መመዘኛዎቹ ስናስብ ልብ ልንላቸው ከሚገቡን ነጥቦች መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡- አንደኛ፣ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ምርጫ ማለት በተለያዩ መሥፈርቶች ሰዎችን መርጠን በእነዚህ ክፍሎች የተዘረዘሩትን ባሕርያት እንዲያሳዩ/እንዲኖሩ የምንጠብቅባቸው ሳይሆን፣ እነዚህ ባሕርያት ለተገለጡባቸው (እንዲህ እየኖሩ ላሉት) ሰዎች ዕውቅና የምንሰጥበት ሥርዐት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎችን አስጨንቀን፣ በትርፍ ጊዜያቸው የሚሠሩት ሥራ እንደ ሆነ አስረድተን በማስገደድ ወደዚህ አገልግሎት ካመጣናቸው በኋላ እነዚህ ባሕርያት እንዲገለጡባቸው እንጠብቃለን፤ ካልተገለጠባቸው ደግሞ እንወቅሳቸዋለን፡፡ ይህ አሠራር የተመረጡትንም ሰዎች ሆነ ቤተ ክርስቲያንን በችግር ውስጥ የሚጥል ነው፡፡

ሁለተኛው ከዚህ ክፍል የምንማረው ነጥብ፣ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ነቀፋ የሌለባቸው የመሆናቸውን መለኮታዊ ትእዛዝ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች በቅድሚያ ቤታቸውን በአግባቡ በመምራት ዐርአያ ሊሆኑ፣ ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸውም ጋር መልካም ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በትዳር ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎች ቤተ ክርስቲያንን ለማስተዳደር ደፋ ቀና ከማለታቸው በፊት ቤታቸውን በሚገባ ማስተዳደር አለባቸው፡፡ ጤናማ ቤተ ሰብ የጤናማ ኅብረት መሠረት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ʻየቤተ ክርስቲያን መሪ ልጆች አስቸጋሪዎች ናቸውʼ ሲባል እሰማለሁ፤ እኔም በዚያ መልኩ የማውቃቸው ልጆች አሉ፡፡ ምናልባት ይህ የሆነው እነዚህ መሪዎች የራሳቸውን ቤት ትተው በሌሎች ቤቶች ላይ በማተኮራቸው ይሆን?

ሦስተኛው ከዚህ ክፍል የምንማረው ነጥብ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የእግዚአብሔር ሥራ ባለ ዐደራዎች መሆናቸውን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የመጋቢ እገሌ ወይም የሽማግሌዎች ንብረት አይደለችም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሕያው እግዚአብሔር ቤት ስትሆን፣ መሪዎች ደግሞ ባለ ዐደራዎች ናቸው፡፡ ዛሬ ብዙ ኅብረት በተለያዩ ሰዎች ስም ተሰይሞ ʻየፓስተር እገሌ ቤተ ክርስቲያንʼ የሚባልበት ጊዜ መጥቷል፡፡ ባለ ዐደራነታችንን ዘንግተን ቤቱን ከባለ ቤቱ በመቀማት ባለ ቤቶች እንደ ሆንን ራሳችንን ወደ መቁጠር መጥተናል፡፡ ቤቱን ለባለቤቱ መልሰን እንደ ባለ ዐደራዎች እናገልግል፡፡

አራተኛው ከዚህ ክፍል የምንማረው ነጥብ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በዚህ ክፍል የተዘረዘሩትን እኩይ ባሕርያት በማስወገድ ሰናይ ባሕርያትን ሊከታተሉ ይጠበቅባቸዋል፤ ይህም ክትትል የማያቋርጥ ሂደት ሊሆን ይገባል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ጢሞቴዎስ እግዚአብሔርን መምሰልን ራሱን እንዲያሠለጥን ይመክረዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን የሚመሩ አገልጋዮች እነዚህን ሰናይ ባሕርያት በመከታተል ለሌሎች ምሳሌ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን መምራት መንፈሳዊነትን ከምንከታተልበት ሂደት ማለፍ (መውጣት) ሳይሆን፣ ይበልጥ ራሳችንን የምንሰጥበትና መንፈሳዊነታችንን የምናሳድግበት የኀላፊነት ስፍራ ነው፡፡

በመጨረሻም፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በተማሩት ቃል በመጽናት ምሳሌ መሆን አለባቸው፡፡ ሌሎችን በእግዚአብሔር ቃል ለማበረታታት እና የሳቱትን ለመገሰጽ ይችሉ ዘንድ እንደ እግዚአብሔር ቃል በመኖር ዐርአያ መሆን አለባቸው፡፡ አንድ ወዳጄ እንዳለው፣ በዚህ ዘመን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሌሎችን መውቀስ የማይችሉበት አንዱ ምክንያት የእነርሱም ሕይወት ከሌሎቹ የተሻለ አለመሆኑ ነው፡፡ ሌሎችን ለመገሰጽ መጀመሪያ እኛ የምንሰብከውን መኖር አለብን፡፡ ጸጋው ኖሯቸው ወይም በመልእክቱ ውስጥ የተጠቀሱት ሰናይ ባሕርያት ተገልጠውባቸው ሳይሆን ገንዘብ ስላላቸው፣ የተማሩ የተመራመሩ ስለ ሆኑ፣ ዝና ስላላቸው ወይም በትውውቅ ከተመረጡ/ከሚመረጡ ሰዎች እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያኑን ይታደግ!

Endasahaw Negash

እውን ክርስቲያኖች ሳይሞቱ ለዘላለም ሊኖሩ ይችላሉ?

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቴሌቪዥን መስኮት ብቻ እናውቃቸው የነበሩ አንዳንድ አፍሪካውያን “አገልጋዮች” በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መድረክ ላይ መታየት ጀምረዋል። በቅርቡ የተከሰቱ ሁለት ኩነቶችን እንኳ ብንመለከት “ሜጀር ሼፐርድ ፕሮፌት” ቡሽር ከማላዊ፣ “ነቢይ” ኮቦስ ቫን ሬንስበርግ ከደቡብ አፍርካ ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ልብ ይሏል።

ተጨማሪ ያንብቡ

ቴክኖሎጂ እና ክርስትና ፪

በባለፈው ዕትም ጽሑፋችን ቴክኖሎጂ ከክርስትና ጋር ያለውን ቁርኝት እና አውንታዊ ተጽእኖዎችን ለማየት ሞክረን ነበር። በዛሬ ጽሐፋችን ደግሞ የቴክኖሎጂን አሉታዊ ገጽታዎችን በመመልከት እንዴት አድረገን ከአደጋ በፀዳ መልኩ ከክርስትና አስተምህሮ ጋር አጣጥመን መጠቀም እንደምንችል እንመለከታለን።

ተጨማሪ ያንብቡ

እንዴት እንሙት? እንዴት እንኑር?

ጌታችን ስለ ሰው ልጆች የከፈለውን ዋጋ በምናስብበት በሰሙነ ሕማማት፣ ንጉሤ ቡልቻ “እንዴት እንሙት?” የሚል ጥያቄ ይጠይቃሉ። ምላሹ በክርስቶስ ሞት ውስጥ የቀረልን ትልቅ ትምህርት ሆኖ አለ።

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.