[the_ad_group id=”107″]

ጤናማ ትምህርት፣ ጤናማ ኑሮ (ክፍል ሦስት)

የጳውሎስ መልእክት ወደ ቲቶ

ጤናማ ትምህርት፣ ጤናማ ኑሮ (ክፍል ሦስት)

በቀርጤስ የነበሩ የሐሰት መምህራን ባሕርያት (1፥10-16)

አንድን ሰው በትክክል ለማወቅ ምን ያህል ጊዜ ያስፈልጋል? ፈረንጆች “አንድን ሰው ማወቅ አንድ ኩንታል ጨው የምንጨርስበትን ያህል ጊዜ ይወስዳል” ይላሉ፡፡ በርግጥ የእኛ ጨው አጠቃቀም ከእነርሱ የሚለይ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እኛ ጨውን ለወጥ ማጣፈጫ ብቻ ሳይሆን ለቡና መጠጫ፣ መለስተኛ ጉዳት ለገጠመው አካል ማከሚያ (‘በጨው ዘፍዝፈው’ ይባልም የለ!)፣ ጉንዳን ለማባረር፣ ወዘተ… እንጠቀማለን፡፡ ታዲያ አንድ ኩንታል ጨው በምንጨርስበት ያህል ጊዜ አንድን ሰው ጠንቅቀን ማወቅ እንችል ይሆን? እንደው ለመሆኑ ሰው ሙሉ በሙሉ ታውቆስ ያልቅ ይሆን? በአንድ ወቅት አበጥሬ አውቀዋለሁ የምትሉትን ሰው በጊዜ ሂደት በፍጹም እንደማታውቁት ተረድታችሁ ይሆን? ሰውን ሙሉ በሙሉ ማወቅ አይቻልም ብዬ ወደ መደምደም ባልደርስም በዚህ ዘመን ሰውን ማወቅ ከየትኛውም ጊዜ ይልቅ አስቸጋሪ እንደ ሆነ አስባላሁ፡፡ በተለይም ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንመጣ ብዙዎች በማስመሰል (pretension) ተክነው ከመገኘታቸው የተነሣ፣ ማን በትክክል እንደሚናገረው እንደ ሆነ መለየት የእግዚአብሔር መንፈስ ካላገዘ በስተቀር የሚያደናግር ሆኗል፡፡ በዚህ ወቅት የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን (አገልጋዮችን) ስንመርጥ (እውቅና ስንሰጥ) ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ በክፍል ሁለት (1፥5-9) ትምህርታችን ቲቶ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ሲሾም ልብ ሊላቸው የሚገባውን መመዘኛዎች ተመልክተን ነበር፡፡ በዛሬው ትምህርት ደግሞ መመዘኛዎቹ እንዲሰጡ ምክንያት ስለ ሆኑትና በቀርጤስ ስለ ነበሩ የሐሰት መምህራን ባሕርያት እንደሚከተለው ለመመልከት እንሞክራለን (1፥10-16)፡፡

ዐመጸኞች፣ ለፍላፊዎችና አታላዮች የሆኑ ብዙ ሰዎች አሉና፤ በተለይም እነዚህ ከተገረዙት ወገን ናቸው፡፡ እነዚህን ዝም ማሰኘት ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ትክክል ባልሆነ መንገድ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ማስተማር የማይገባቸውን ነገር በማስተማር ቤተ ሰብን ሁሉ በመበከል ላይ ናቸውና፡፡ ከራሳቸው ነቢያት አንዱ ስለ እነርሱ ሲናገር “የቀርጤስ ሰዎች ዘወትር ውሸታሞች፣ ክፉ፣ አውሬዎችና ሰነፍ ሆዳሞች ናቸው” ብሎአል፡፡ ይህ ምስክርነት እውነት ነው፤ ስለዚህ አጥብቀህ ገሥጻቸው፤ ይኸውም ትክክለኛ እምነት እንዲኖራቸውና የአይሁድን ተረት ወይም ከእውነት የራቁትን ሰዎች ትእዛዝ እንዳያዳምጡ ነው፡፡ ለንጹሓን ሁሉም ነገር ንጹሕ ነው፤ ለርኩሳንና ለማያምኑ ግን ንጹሕ የሆነ ምንም ነገር የለም፤ እንዲያውም አእምሮአቸውና ኅሊናቸው የረከሰ ነው፡፡ እግዚአብሔርን እናውቃለን ይላሉ፤ ዳሩ ግን በተግባራቸው ይክዱታል፤ አስጸያፊዎች፣ የማይታዘዙና ለበጎ ሥራ የማይበቁ ናቸው፡፡ (ቲቶ 1፥10-16)

ይህ መልእክት በዋነኛነት የተጻፈው ቲቶ የተጀመረውን ጅምር ሥራ ሲያጠናቅቅና በየከተማው የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎችን ሲሾም እንዲረዳው ነው (1፥5)፡፡ ይሁን እንጂ ከ 1፥10-16 እና ከ 3፥9-11 በመነሣት ይህ መልእክት እንዲጻፍ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል አንዱ በወቅቱ የነበሩ የሐሰት መምህራን ጉዳይ እንደ ሆነ መናገር ይቻላል፡፡ እንደ ተጨማሪ ማስረጃ የሐሰት መምህራን “ለበጎ ሥራ የማይበቁ” (1፥16) መሆናቸው እና አማኞች ለበጎ ሥራ የሚተጉ እንዲሆኑ መጠራታቸው (2፥5፣ 7፣ 8፣ 10፣ 14፤ 3፥1፣ 8፣ 14) በንጽጽር መቅረቡን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በርግጥ በቀርጤስ የነበረው የሐሰት መምህራን እንቅስቃሴ በ1 ጢሞቴዎስ የተገለጠውን ያህል አለመሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ እንግዲህ ቲቶ የተጀመረውን ጅምር ሥራ ሲያጠናቅቅና በየከተማው ሽማግሎዎችን ሲሾም ሊከተላቸው የሚገባው መመዘኛዎች በ 1፥6-9 ላይ በግልጽ ቀርበዋል፡፡ የመመዘኛዎቹ ማጠቃለያ የቀረበው በትእዛዝ መልክ ነው፤ “ሌሎችን ትክክል በሆነው ትምህርት እንዲያበረታታና ይህንኑ ትምህርት የሚቃወሙትን ይወቅስ ዘንድ እንደ ተማረው በታመነ ቃል የሚጸና መሆን አለበት” ይላል (1፥9)፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሪ እንደ ተማረው በታመነ ቃል የሚጸና መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱስ? አንደኛ፤ ሌሎችን በዚህ ትክክል በሆነው ትምህርት እንዲያበረታታ ሲሆን ሁለተኛ፤ ይህንን ትምህርት የሚቃወሙትን ይወቅስ ዘንድ ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያን መሪዎች 1፡6-9 ላይ የተዘረዘሩትን መሥፈርቶች የሚያሟሉ መሆን አለባቸው፡፡ ምክንያቱስ? ምክንያቱን ቀጣዩ ክፍል በግልጽ ያቀርባል፡፡ ቁጥር 10 ን እንመልከት ‹‹ዐመጸኞች፣ ለፍላፊዎችና አታላዮች የሆኑ ብዙ ሰዎች አሉና፤ …›› ይላል፡፡ ‹ና› (አሉና) የሚለው አያያዥ ፊደል ይህ ክፍል በምን መልኩ ከላይኛው ክፍል ጋር መያያዝ እንዳለበት ያመለክታል፡፡ ‹ና› ተብሎ የተተረጎመው ‹ምክንያቱም› (‘For’) የሚለው አያያዥቃል ነው፡፡ ቲቶ ከላይ የተጠቀሱትን መመዘኛዎች በጥንቃቄ በመጠቀም መሪዎችን መሾም ያለበት ለምንድን ነው? ምክንያቱም በቀርጤስ ዐመጸኞች፣ ለፍላፊዎችና አታላዮች የሆኑ ብዙ ሰዎች ስለ ነበሩ ነው፡፡ እነዚህ በዘመኑ የነበሩ የሀሰት መምህራን ናቸው፡፡ ይህ ቁጥር እንዲሁም ቀጣዮቹ ቁጥሮች የእነዚህን መምህራን ባሕሪያት ይዘረዝራሉ፡፡ ስለ እነዚህ ሰዎች ቀጥሎ ሲናገር ‹‹በተለይም እነዚህ ከተገረዙት ወገን ናቸው›› ይላል፡፡ እነዚህ ሰዎች ከተገረዙት ወገን የሆኑ፣ ከይሁዲነት ወደ ክርስትና የመጡ ናቸው (የሐዋ 10፡45፤ 11፡2፤ ገላ 2፡7-9፣ 12)፡፡ ሕግን እንደሚያውቁ፣ እንደሚጠብቁ ብቻ ሳይሆን ‹ከእኛ በላይ አዋቂ የለም› የሚሉም ጭምር ናቸው፡፡ ጳውሎስ እንዲህ ዓይነት ሰዎችን ምን ማድረግ እንደሚገባ ሲናገር፣ ‹‹እነዚህን ዝም ማሰኘት ተገቢ ነው›› ይላል (ቁ. 11)፡፡ እነዚህን ዐመጸኞች፣ ለፍላፊዎችና አታላዮች የሆኑ ሰዎች (ብዙ ሰዎች) አፋቸውን መዝጋት ያስፈልጋል፡፡ እንዴት? በኑሮ – ከላይ እንደ ተገለጸው በመኖር (በተለይ ቁጥር 9 – ‹እንደ ተማረው በታመነ ቃል የሚጸና› ይላል)፡፡

ዝም ማሰኘት (አፋቸውን መዝጋት) የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ‹‹ምክንያቱም ትክክል ባልሆነ መንገድ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ማስተማር የማይገባቸውን ነገር በማስተማር ቤተ ሰብን ሁሉ በመበከል ላይ ናቸውና›› ይላል (ቁ. 11)፡፡ ልክ በ1 ጢሞቴዎስ ላይ እንደ ተጠቀሰው መንፈሳዊነትን ምድራዊ ጥቅም ማግኛ በማድረግ፣ ማስተማር የማይገባቸውን በማስተማር ቤተ ሰቦችን ሁሉ ይበክላሉ፣ ከእምነት ያስታሉ (1ጢሞ 5፡13፤ 6፡5-10)፡፡ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ማስተማር የማይገባቸውን በማስተማር ብዙዎችን ስለሚያጠፉ አፋቸውን መዝጋት ያስፈልጋል፡፡ በመቀጠል ከራሳቸው ነቢያት መካከል አንዱ ስለ ቀርጤስ ሰዎች የተናገረውን በመጥቀስ ምስክርነት እውነት እንደ ሆነ ይናገራል፡፡ ብዙዎች እንደሚናገሩት ከሆነ ይህ ነብይ በ600 ዓ.ዓ. አከባቢ በቀርጤስ ደሴት ይኖር የነበረ የኖሲስ ተወላጅ ኤፒሜኒደስ የሚባል ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው ባለ ቅኔና ብዙ ነገሮችን ተናግሮ የተናገራቸው ነገሮች በመፈጸማቸው እንደ አዋቂ የሚታይ፣ የሚከበርና ተሰሚነት ያለው ነብይ ነው፡፡ ጳውሎስ ይህን ሰው የጠቀሰው እውነተኛ ነብይ መሆኑን ለማሳየት ሳይሆን ስለ ቀርጤስ የተናገረውን ምስክርነት እንደ ማስረጃ ለመጠቀም ነው፡፡ ይህ ሰው ‹‹የቀርጤስ ሰዎች ዘወትር ውሸታሞች፣ ክፉ አውሬዎችና ሰነፍ ሆዳሞች ናቸው›› ብሎአል (ቁ. 12)፡፡ ጳውሎስ አስቀድሞ በጠቀሳቸው ባሕሪያት ላይ ተጨማሪ ነገር ከዚህ ሰው ያቀርባል፡፡ በግሪክ ሥነ ጹሑፍ ‹ቀርጤሳዊ› የሚል ቃል ከተጻፈ ‹ውሸታም› ወይም ‹ቀጣፊ› እንደ ማለት ነው፡፡ በቀርጤስ የነበሩ የሀሰት መምህራን ውሸታሞች፣ ክፉ አውሬዎች (በምሳሌያዊ አነጋገር ክፋታቸውንና ጭካኔያቸውን ያመለክታል) እና ሰነፍ ሆዳሞች ናቸው፡፡ ሰነፎች ግን ሆዳሞች! እነዚህ ሁለቱ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ባሕሪያት ናቸው፤ ግሩም ነው! መሥራት የማይወዱ ሰነፎች፤ መብላት ‹ጸጋቸው› ይመስል በልተው የማይጠግቡ ሆዳሞች ናቸው፡፡ እነዚህን ምን ማድረግ እንደሚገባ ሲናገር ‹አጥብቀህ ገሥጻቸው› ይላል (ቁ. 13)፡፡ 1፡9 የሀሰት አስተማሪዎችን የመገሰጽ ኀላፊነት ለሽማግሌዎች እንደ ተሰጠ ሲናገር በዚህ ክፍል ግን በቀጥታ ቲቶ አጥብቆ እንዲገስጻቸው ታዟል፡፡

በቁጥር 13 እና 14 ላይ የግሳጼው ዓላማ ምን እንደ ሆነ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ዓላማው፤ አንደኛ፣ ‹ትክክለኛ እምነት እንዲኖራቸው› ሲሆን ሁለተኛ፣ ‹የአይሁድን ተረት ወይም ከእውነት የራቁትን ሰዎች ትእዛዝ እንዳያዳምጡ ነው›፡፡ የአይሁድ ተረት የሚለው በግልጽ ምን እንደ ሆነ መናገር ቢያስቸግርም ለእግዚአብሔር መንግሥት ምንም ፋይዳ የሌለው ከንቱ ልፍለፋ – ከእውነት የራቁት ሰዎች የሚቀባጥሩት እንደ ተረት ተረት ያለ ንግግርን ሊያካትት ይችላል፡፡ ይህ ክፍል እንደሚያስረዳው የግሳጼ ዓላማው መመለስ፣ ማስተካከል፣ ማቅናት እንጂ ማባረር ወይም ማጥፋት አይደለም፡፡ በቁጥር 15 እና 16 ጳውሎስ በእነዚህ ሰዎች ላይ ያቀረበውን ክስ/ማስረጃ እንመለከታለን፡፡ ‹‹ለንጹሓን ሁሉም ነገር ንጹሕ ነው፤ ለርኩሳንና ለማያምኑ ግን ንጹሕ የሆነ ምንም ነገር የለም፤ እንዲያውም አእምሮአቸውና ኅሊናቸው የረከሰ ነው›› (ቁ. 15)፡፡ ይህ ቁጥር እንደሚያሳየው ‹አንዱ ችግራቸው ይህን አድርጉ ይህን አታድርጉ› ከማለት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ‹ይህ ምግብ ንጹሕ ነው፣ ይህ ምግብ ግን ንጹሕ አይደለም› በማለት ይከፋፍሉ ነበር፡፡ የሀሰት መምህራን አእምሮና ኅሊና የረከሰ (የተበላሸ) ስለ ሆነ ለእነርሱ ሌላውም ነገር የረከሰ ነው (1 ጢሞ 1፡5፤ 6፡5)፡፡ ውስጣቸው፣ አመለካከታቸው የተበላሸ ስለ ሆነ የሚያንጸባርቁት አቋም የረከሰውን የውስጥ ማንነታቸውን የሚያንጸባርቅ ነው፡፡ ለንጹሓን ግን ሁሉም ነገር ንጹሕ ነው (1 ጢሞ 4፡4)፡፡ ስለ ምግብ ጳውሎስ ያለው አቋም ቅዱስ ማርቆስ ያሰፈረውን (ሉቃስ 7) የኢየሱስን ትምህርት ያንጸባርቃል፡፡ የመጨረሻው ቁጥር እንደሚያሳየው እነዚህ ሰዎች ‹‹እግዚአብሔርን እናውቃለን ይላሉ፤ ዳሩ ግን በተግባራቸው ይክዱታል፤ አስጸያፊዎች፣ የማይታዘዙና ለበጎ ሥራ የማይበቁ ናቸው›› (ቁ. 16)፡፡ አንድ ሰው እግዚአብሔርን እንደሚያውቅ በግልጽ እየተናገረ፣ አስጸያፊ፣ የማይታዘዝና ለበጎ ሥራ የማይበቃ ሊሆን ይችላል? እግዚአብሔርን የሚያውቁቱ መታወቂያቸው ታዛዦች መሆናቸውና ለበጎ ሥራ ብቁ መሆናቸው እንጂ ‹‹በሚገባ እናውቀዋለን›› በማለት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው መናገራቸው እንዳልሆነ መናገር ይቻላል፡፡

ከዚህ ክፍል (ቲቶ 1፡10-16) የምንማራቸው በርካታ ነጥቦች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ልብ ማለት ያለብን ነጥብ ዛሬም ዐመጸኞች፣ ለፍላፊዎችና አታላዮች (የሀሰት መምህራን) መኖራቸውን ነው፡፡ ሰዎችን ወደ ተለያዩ የአገልግሎት ክፍል ስናመጣ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ በትክክል ጸጋው ያላቸው መሆኑንና ሕይወታቸውን ሳንፈትሽ ባማሩና ባሸበረቁ ቃሎቻቸው ተታለን ቤተ ክርስቲያንን ለዐመጸኞች፣ ለለፍላፊዎችና ለአታላዮች አሳልፈን ልንሰጥ አይገባም፡፡ ሁለተኛው ከዚህ ክፍል የምንማረው ነጥብ እነዚህን ዐመጸኞች፣ ለፍላፊዎችና አታላዮች፣ ማስተማር የማይገባቸውን በማስተማር ቤተ ሰብን በመበከል ላይ የተሰማሩትን የሀሰት መምህራን በምንኖረው ኑሮና በምናስተምረው ትምህርት አፋቸውን መዝጋት፣ ዝም ማሰኘት ተገቢ እንደሚገባ ነው፡፡ በዚህ ዘመን የምናገለግል ተረኞች ሁላችን እነዚህን ትክክል ባልሆነ መንገድ ማስተማር የማይገባቸውን በማስተማር ቤተ ሰብን በመበከል ላይ የተሰማሩትን ሀሰተኞች ልንቃወም ይገባል፡፡ ዛሬ አንዳንዶች ለምድራዊ ጥቅም ማስተማር የማይገባቸውን በማስተማር ቤተ ሰብን በመበከል ላይ ናቸው፡፡ ቤተ ሰብ የቤተ ክርስቲያንና የሀገር መሠረት እንደ መሆኑ መጠን የእነዚህ ሰዎች ትምህርት ቤተ ክርስቲያንንና ማኅበረ ሰቡን የሚበክል ነው፡፡ ቤተ ሰብ ሲበከል ቤተ ክርስቲያንና ማኅበረ ሰቡ ይበከላል፡፡ ዛሬም ያለ ቤተ ክርስቲያን እውቅና በየቤቱ እየዞሩ ብዙዎችን እያሳቱ አማኞች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲሁም በማኅበረ ሰቡ ውስጥ ውጤታማ እንዳይሆኑ እያደረጉ ያሉትን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ አንዳንዶች ለምድራዊ ጥቅም ብቻ ማስተማር የማይገባቸውን በማስተማር፣ አስተምሮ አደሮች፤ መስበክ የማይገባቸውን በመስበክ፣ ሰብኮ አደሮች፤ መተንበይ የማይገባቸውን በመተንበይ፣ ተንብዮ አደሮች፤ እና መጸለይ የማይገባቸውን በመጸለይ፣ ጸልዮ አደሮች እየሆኑ ባሉበት በዚህ ዘመን በትክክል ስለ ወንጌል ጥሪ አለኝ የሚል ሁሉ በሚኖረው ኑሮና በሚያስተምረው ትምህርት እነዚህን ሰዎች ዝም ማሰኘት፣ መቃወም ይኖርበታል፡፡ ሦስተኛው ከዚህ ክፍል የምንገነዘበው አውነት ሰዎችን ስንገስጽ ዓላማችን ማስተካከል፣ መመለስ፣ ማዳን መሆን እንዳለበት ነው፡፡ ሐዋሪያው ቅዱስ ጳውሎስ የእነዚህ ሰዎች ባሕሪያት ምን ያህል የተበላሸ እንደ ሆነ በማንሳት ዝም ማሰኘት፣ መቃወም እንደሚያስፈልግ ተናግሯል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን እነዚህን ሰዎች ስንቃወም ዓላማው ማዳን መሆን እንዳለበት ከማሳሰብ አልተቆጠበም፡፡ መቼም ስለ ቤተ ክርስቲያን የሥነ ሥርዐት ርምጃ ከተነሳ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ የሥነ ሥርዐት ርምጃ የሚወስደው ማን ነው? ርምጃው የሚወሰድባቸው ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው? የሥነ ሥርዐት ርምጃው ዓይነት ምንድን ነው? የሥነ ሥርዐት ርምጃ የምንወስድበት ሞቲቭ ምንድን ነው? የመሳሰሉት ጥያቄዎች ሰፊ ውይይት የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ከዚህ ክፍል የምንረዳው አንድ እውነት የሥነ ሥርዐት ርምጃ ዓላማ ማጥፋት ሳይሆን ለመመለስ ፈቃደኞች የሆኑትን ማዳን መሆን እንዳለበት ነው፡፡ ከዚህ ክፍል የምንገነዘበው አራተኛውና ለዚህ ጹሑፍ የመጨረሻው ነጥብ በቁ. 16 ላይ የተጠቀሰው ሓሳብ ነው፤         ‹‹እግዚአብሔርን እናውቃለን ይላሉ፤ ዳሩ ግን በተግባራቸው ይክዱታል፤ አስጸያፊዎች፣ የማይታዘዙና ለበጎ ሥራ የማይበቁ ናቸው›› ይላል፡፡ እግዚአብሔርን ማወቅ ለበጎ ሥራ ሁሉ ብቁ መሆን ነው፡፡ ‹ነን› ብለን የምንናገረውና የምናደረገው አንድ ዓይነት ሊሆን ይገባል፡፡ እግዚአብሔርን ማወቃችን በአንደበታችን የምንናገረው ብቻ ሳይሆን በተግባራችን የሚገለጥ ነው፡፡ የምንኖረውና የምናስተምረው አንድ ሆኖ ለምድራዊ ጥቅም ሲሉ ማስተማር የማይገባቸውን በማስተማር ብዙዎችን እያሳቱ ያሉትን ዝም እናሰኝ፣ እንቃወምም ዘንድ እግዚአብሔር ይርዳን! አሜን!!!

ዴክሳሜታሶን እና ኮቪድ-19

“ዴክሳሜታሶን” ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ስሙ የሚነሣ መድኃኒት ከሆነ ሰንብቷል። ይህንኑ በሚመለከት ፋርማሲስት ባንቱ ገብረ ማርያም ስለ መድኃኒቱ ምንነትና ታማሚዎችን በማከም ረገድ ያለውን ድርሻ እንዲሁም ሊወሰድ ስለሚገባው ጥንቃቄ የሚከተለውን ጽሑፍ ያስነብባሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ

የመተማመን ድልድዩን እንጠግን

ይቅርታ መጠየቅ ምን ማለት ነው? ሰዎች ይቅርታ ለመጠየቅ ለምን ይቸገራሉ? የተሠራው በደል በተበዳዩ ላይ ካሳድረው ጉዳት አንጻር፣ የበዳዩ ይቅርታ ጥየቃ የሚያጎናጸፈው ሥነ ልቦናዊ ፋይዳ ምንድን ነው?

ተጨማሪ ያንብቡ

Add comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SIGN UP FOR OUR NEWSLETTER.

Hintset’s latest news and articles of the week to encourage, challenge, and inform you.